spot_img
Sunday, April 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትየትግራይን እናቶች ከወላድ መካንነት ማዳን የጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት ታሪካዊ ሃላፊነት ነው! 

የትግራይን እናቶች ከወላድ መካንነት ማዳን የጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት ታሪካዊ ሃላፊነት ነው! 

ኤፍሬም ማዴቦ _ tigray mothers
ኤፍሬም ማዴቦ

ኤፍሬም ማዴቦ (emdadebo@gmail.com

ኢትዮጵያ ዘመን የጠገበ ረጂም ታሪክ፣ለብዙ ሺ አመታት የዘለቀ ተከታታይ ስርዓተ መንግስት፣ሃይማኖትና ባህል አለን ብለው ከሚኮሩ ጥቂት የአለማችን አገሮች ውስጥ ቀዳሚዋ ናት። ኢትዮጵያ ሁለቱን ትልልቅ የአለማችን ሃይማኖቶች ከብዙ አገሮች አስቀድማ የተቀበለቸ አገር ብቻ ሳትሆን፣ ዛሬ የአፍሪካን ህዝብ ሃይማኖት አስተማርነው ብለው የሚፏልሉ አገሮች በአለም ካርታ ላይ እንደ አገር ከመመዝገባቸው በፊት ኢትዮጵያ ክርስትናንም እስልምናንም የተቀበለች አገር መሆኗን ታሪክ በግልጽ ይናገራል። ለምንድነው እቺ የታሪክና የዕድሜ ባለጸጋ  የሆነችው የጀግኖች አገር ዛሬ በአገር በቀል አሸባሪዎች የምትሸበረው? ለምድነው እቺ በዘመናት ውስጥ ነጻንቷን ጠብቃና ዳር ድንበሯን አስከብራ የኖረች ብቸኛ የጥቁር አገር ዛሬ የህልውና አደጋ ውስጥ የገባችው? ለምንድነው የኢትዮጵያ ታሪክና ሥልጣኔ መሰረት ከሆነችው ከትግራይ ምድር የፈለቁ ልጆች የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑት?    

ትግራይ ኢትዮጵያ “አቢሲኒያም” ይሁን “ኢትዮጵያ” የሚል ስም ይዛ በተጓዘችባቸው የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ሁሉ የኢትዮጵያ አካል የነበረች ብቻ ሳትሆን፣ አያሌ የኢትዮጵያ ነገስታት የፈለቁባትና ትልልቅ የኢትዮጵያ የታሪክና የሃይማኖት ቅርሶች የሚገኙባት ክልል ናት። የጥንታዊቷም ሆነ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ታሪክ ከትግራይ ታሪክ ጋር አብሮ የተሸመነ ነው። የአለም ታሪክ ማዕከላዊ መንግስት መስርተው በመንግስት የሚመሩ አገሮችን ታሪክ መመዝገብ ከጀመረበት ግዜ ጀምሮ፣ትግራይ ካለ ኢትዮጵያ፣ኢትዮጵያም ካለትግራይ የኖሩበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። ዛሬ አለቦታቸው ገብተው የሚበጠብጡን አንዳንድ ምዕራባዊያን አገሮች አገር ከመሆናቸው ከሺ አመታት በፊት ትግራይን ያቀፈች ጥንታዊት ኢትዮጵያ ነበረች።  

በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረውና ክርስትና የኢትዮጵያ መንግስት ሃይማኖት ነው ብሎ ያወጀው ንጉስ ኢዛና የነበረው አክሱም ውስጥ ነው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት መሰረት ከሆኑ ጥንታዊ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ አንዷ የሆነችው አክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን የምትገኘው ትግራይ ውስጥ ነው፣በእስልምና ሃይማኖትም በ7ኛው ምዕተ አመት የተገነባውና ከመጀመሪያዎቹ የአለማችን መስጊዶች አንዱ መሆኑ የሚነገርለት የአልነጃሺ መስጊድ የሚገኘው ትግራይ ውስጥ ነው። 

ታዲያ ለምንድነው እንደ ኢትዮጵያ ረጂምና ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሩሲያ፣ ቻይናና ኢራንን የመሳሰሉ አገሮች ባህላቸውን ለማስቀጠልና ማንነታቸውን ለማስከበር አብረው ሲቆሙ፣ እኛ ይህንን ትልቅ ታሪክና ማንነት ካልተናደ ብለን የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የገባነው? ለምድነው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ አገረ-መንግስትና ሃይማኖት መሰረት በሆነችው ትግራይ ምድር ላይ የተፈጠሩ ጥቂት የፖለቲካ ልህቃን እንመራሃለን ከሚሉት ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር ፊት ለፊት የሚጋጭ አላማ እንግበው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጠው የተነሱት?  

የኋላ ኋላ ህወሓትን የፈጠሩ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና አለ፣ ይህ ጭቆና ተወግዶ ብሔሮች እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው የሚል እንቅስቃሴ የተጀመሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው፣ 17 አመት ደርግን በመሳሪያ ታግለውና አሸንፈው ኢትዮጵያን መምራት የጀመሩትም ትግል ከጀመሩበት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ዩኒቨርሲቲ በትንሽ ርቀት ላይ በሚገኘው ሚኒሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ነው። እነዚሁ የህወሓት መሪዎች የኢትዮጵያን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ከ31 አመታት በኋላ፣ የትግራይን ህዝብ ከማጥፋቱ በፊት ቀድመን እናጠፋዋልን ብለው ጫካ ገብተው የሚዋጉት ከነሱ በኋላ የመጣው አቢይ አህመድ የሚባል ሰው የሚገኘውም እዚሁ ምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ነው። ይህ ምኒልክ ቤተመንግስት የሚሉት የትልቅ ሰው መኖሪያ የነበረ ግቢ ዉስጡ ምን ጉድ ቢኖርበት ነው ለመኖር የሚገባበት ሁሉ መሳሪያ የሚያነሳው፣ገብቶ የሚኖርበት ሁሉ መሳሪያ የሚነሳበት? ጉዳዩ ከግቢው ነው፣ ከቤተመግስቱ ነው ወይስ ከነዋሪው?  

ህወሓቶች 27 አመት ብቻቸውን ሥልጣን ተቆጣጥረው ከኖሩበት ቤተመንግስት በህዝባዊ ቁጣ ተባረው የወጡት ምን ስለሰሩ ወይም ምን ስላልሰሩ ነው? የህወሓት መሪዎችና የዳያስፖራ ደጋፊዎቻቸው በተደጋጋሚ ሊነግሩን እንደሚፈልጉት በእርግጥ ህወሓቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብን ከድህነት ነጻ ያወጣ ትልቅ ኤኮኖሚ ገንብተዋል? የኢትዮጵያ ህዝብ በማዕከል ሥልጣን እየተጋራ በአካባቢው እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አድርገዋል? ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥርዓት ገንብተዋል? የዜጎችን ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መብት አክብረዋል? ህወሓቶች እነዚህን ሁሉ አይደለም፣ የእነዚህን አንድ ሦስተኛ እንኳን አድርገው ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ፍለጋ ነው ጥፉልን ብሎ የሚያባርራቸው? 

በቀኃ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ እኩልነት፣ነጻነትና ዲሞክራሲ አልነበረም፣ በደርግ ዘመንም አልነበረም። ሆኖም ግን ዛሬ ህወሓት በፈጠራት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የላላ አገራዊ አንድነት፣ የብሔር ግጭት፣የእርስ በርስ ጦርነት፣ ሙስና፣ስስት፣ ስግብግብነትና ያየነውን ሁሉ የኔ ብቻ ማለት በቀኃስና በደርግ ዘመን አለነበረም። ይህ ማለት ግን ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት ችግሮች ሁሉ ህወሓት የፈጠራቸው ችግሮች ናቸው ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ችግሮች ብዙ ናቸው፣ የተፈጠሩትም የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ሦስት መንግስታትና በእነዚህ ሦስት መንግስታት ውስጥ በነበሩ ምሁራን፣ የፖለቲካ ልህቃን፣ወታደራዊ ልህቃን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣የሰራተኛ ማህበራት፣ወጣቶች፣የወል ስብስቦች ወዘተ ነው።   

ዛሬ ኢትዮጵያን እጅና እግሯን አስረው ወደፊት አላራምድ ያሏት ችግሮች በአብዛኛው ህወሓት ከጻፈው ህገመንግስት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። የህገመንግስቱ አንቀጽ 8 አርዕስቱ ላይ የህዝብ ሉዓላዊነት ይልና ወረድ ብሎ አንቀጽ 8.1 ላይ ግን ይህንን የህዝብ ሉዓላዊነት ማህበራዊ ስሪት ለሆኑና ልዩነታቸውና አንድነታቸው በውል ተለይቶ ለማይታወቅ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለሚባሉ ሦስት አካላት በጅምላ ይሰጥና ህገመንግስቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ዜጎችን ይረሳል። ስለዚህም በዚህ ህገመንግስት መሰረት ህወሓት ኢትዮጵያን በመራባቸው 27 አመታት ውስጥ (ህገመንግስቱ በስራ ላይ ስላለ) ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ የዜጎች እስር ቤት ናት። የሚገርመው ኢትዮጵያን የዜጎች እስር ቤት ያደረጋትን ህገመንግስት የጻፉ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት ብለው ትግል የጀመሩ ሰዎች ናቸው። 

በአንድ አገር ውስጥ፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በብሔር፣በባህልና በሃይማኖት በተከፋፈሉ አገሮች ውስጥ ማህበራዊ ኮንትራት የሚፈራረሙት አካላት የትኞቹ ናቸው? የአገር ሉዓላዊነት ማደሪያው የት ነው? የፖለቲካ ሥልጣን ምንጩ የት ነው? ለሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ በአገሮቹ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ይኖራል ወይስ አይኖርም? ጠንካራ አገራዊ አንድነት ይኖራል ወይስ አይኖርም? አገራዊ ልማትና ዕድገት ዋስትና ይኖረዋል ወይስ አይኖረውም የሚለውን ጥያቄ መልስ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ እንዲሆን ያደርገዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያዎቹ ሦስት ጥያቄዎች ህገመንግስቱ የሰጠው መልስ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚል ነው። ለዚህ ነው ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በተለይ ባለፉት አራት አመታት እንደ አገር መቀጠላችን አደጋ ላይ የወደቀው፣ አንድነታችን የተፈተነውና ሰላምና መረጋጋት አጥተን ዕድገትና ልማት የራቀን። 

ህወሓት እራሱን “ወያኔ” ብሎ የሰየመው ከሱ በፊት የነበረውንና “ቀዳማይ  ወያኔ” እያለ የሚጠራውን እንቅስቃሴ ስም ተውሶ ነው። ቀዳማይ ወያኔም፣ ካልአይ ወያኔም የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ሥልጣን ባለቤትነት በሸዋዎች ተቀማን የሚልና እንደ ዳዊት የሚደግሙት የሞኝ ትርክት አላቸው። ይህ ወያኔዎች ደጋግመው የሚያነሱት የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ሥልጣን ባለቤትነት ጥያቄ ዛሬም አልቀረም። እየደበደቡ፣ እያኮላሹ፣ የሴት ጡት በጉጠት እየቆነጠጡ፣ እያሰሩ፣ ዜጎች ከአገር እንዲሰደዱ እያደረጉና እየገደሉ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት የገዙት ህወሓቶች፣ ከሥልጣን ከተባረሩ ከአራት አመት በኋላ እንደገና ወደ ሥልጣን ለመምጣት ብዙ ሙከራዎች አድርገዋል፣ አሁንም እያደረጉ ነው። 

ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ኢትዮጵያን በአመጽ የገዛው ህወሓት፣በህዛባዊ ቁጣ ከሥልጣን ከተባረረና መቀሌ ከገባም በኋላ፣ተፈጥሯዊ መለያው የሆነው አመጽ  አብሮት መቀሌ ገባ እንጂ በፍጹም አልለቀቀውም። ከ1983- 2010 ድረስ ለ27 አመታት አገርን የዘረፈውና በዜጎች ላይ በቃላት ሊነገር የማይችል ትልቅ ወንጀል የፈጸመው ህወሓት፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያ አብረን እስከገነባን ድረስ ከወንጀሉ ነጻ ነህ ቢባልም፣ ጦርነትና ሽብር በሌለበት ቦታ መኖር የማይችለው ህወሓት መቀሌ እንደገባ ጠመንጃ መወልወል፣ መድፍና ታንክ ይዞ አደባባይ መውጣትና በመቀሌ መንገዶች ላይ አርፒጂ የተሸከሙ ሚሊሻዎችን ማሳየት ነበር የተያያዘው።   

ህወሓት መቀሌ ከገባ በኋላ የኋላ የኋላ ኋላ በሰሜን ዕዝ ላይ ለመፈጸም ላቀደው እኩይ ወንጀል የጠ/ሚ አቢይ አህመድን መንግስት ይከስ የነበረው፣ አቢይ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ነው፣ አቢይ አሃዳዊ ነው፣ አቢይ የትግራይን ህዝብ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊቀማ ነው እያለ ነበር። ሃቁ ግን “እራሴን በራሴ የማስተዳደር መብቴ ይከበርልኝ” የሚል ጥያቄ ያቀረበውን የሲዳማ ህዝብ በጥይት የቆላው ህወሓት መራሹ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መንግስት ያልመለሰውን የክልልነት ጥያቄ የመለሰው የጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት ነው። በሃያ ሰባቱ የህወሓት ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘጠኝ ክልሎች ነበሩ፣ ዛሬ አስራ አንድ ክልሎች አሉ። የአሃዳዊነት መለኪያው ክልል የመሆን ጥያቄን መጨፍለቅ ከሆነ ማነው አሃዳዊው?

በ2013 ዓም ጥቅምት ወር ላይ ህወሓቶች የሰሜን ጦርን ወግተው ሰሜን ኢትዮጵያን የጦርነት ቀጣና አድርገውታል፣ በዚሁ አመት ሰኔ ወር ላይ ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን ብለው አፋርና አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ድረስ ገብተው በህዝብና በንብረት ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። የለመደች ጦጣ ሁልግዜ ሽምጠጣ እንዲሉ፣ ህወሓቶች በ2014 ዓም ማለቂያ ላይ ለ3ኛ ግዜ ጦርነት በመክፈት የኢትዮጵያን ህዝብ የአዲስ አመት ተስፋ ለማጨለም ሞክረዋል። ሆኖም ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህ ጦርነት ኢትዮጵያ ህወሓቶችን ብቻ ሳይሆን ጦርነትን እራሱን የምትገላገልበት ጦርነት መሆን አለበት ብሎ አሸባሪውን ኃይል መግቢያ መውጪያ እያሳጣው ነው። 

ብትር ሲበዛብት ጩኸቱ የሚቀድመው ህወሓት በቅርቡ ያለምንም ቅድመሁኔታ እደራደራለሁ የሚል መግለጫ አውጥቷል፣ ህወሓት እንኳን በመግለጫ ጋጋታ ታቦት ተሸክሞ አየማለ ውሎ ቢያድርም ታቦቱን ያረክሰው እንደሆን እንጂ ህወሓት በፍጹም የሚታመን ድርጅት አይደለም። ህወሓትና እውነት፣ ህወሓትና ቃል ማክበር፣ ህወሓትና በሰላም ልዩነቶችን መፍታት አብረው አይሄዱም፣አንድ ላይ ኖረውም አያውቁም። ካሁን በኋላ ህወሓትን አስገድዶ ወደ ድርድር መድረክ የሚያመጣው ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው። ህወሓት የመከላከያ ሠራዊታችን ብርቱ ክንድ ሲበዛበትና መደበቂያው ቆላ ተምቤን መቀበሪያው መሆኑን ሲያውቅ፣እንኳን ትጥቁን ሱሪውን ፈትቶ ለድርድር እንደሚቀርብ እኔ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም! 

የህወሓት ጀምበር እየጠለቀች ነው፣ ካሁን በኋላ የትግራይ ህዝብ ዕድል በትግራይ ህዝብ፣ በትግራይ ልህቃንና በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት እጅ ላይ ነው። የትግራይ ህዝብ እይኑን በአይኑ የሚያይበትን ልጆቹን ለትርጉም የለሽ ጦርነት መገበር ማቆም አለበት። የትግራይ ህዝብ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጅ እንጂ ጠላት ሆኖ አያውቅም፣ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብም ለትግራይ ህዝብ ወንድምና ወዳጅ እንጂ ጠላት ሆኖ አያውቅም። የትግራይ ህዝብ መሳሪያ አንስቶ የራሱን ወንድሞችና እህቶች እንዲገድል የሚያደርገው የሰላም ጠላት የሆነውና ካለጦርነት ውሎ ማደር የማይችለው ህወሓት ነው። የትግራይ ህዝብ ከተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ወንድምቹና እህቶቹ ጋር ሰላማዊ፣ የተረጋጋና የተሟላ ህይወት ከመኖርና፣ ህወሓትን ተሸክሞ ዝንተ አለም እየተዋጋ ከመኖር አንዱን መምረጥ አለበት!

የበኩር ልጅ ከቤተሰቡ ጋር ችግር ውስጥ ሲገባ ከእናት አባቱ ጋር ቁጭ ብሎ ይመክራል እንጂ እራሱን፣ቤተሰቡን፣መንደሩንና አገሩን የሚያጠፋ ጦርነት አይጀምርም። እሱ ዕብደት ጀምሮት ካልተዋጋሁ ቢልም እናቱ፣ አባቱ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ እጁን ይዘው ልጄ ተው ብለው ይመክሩታል እንጂ ከዕብድ ጋር አብረው አያብዱም። የአገራችን የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች መሰረት በሆነ ምድር ላይ የተፈጠረ ህዝብ የተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹንና እህቶቹን እየተሳሰብንና እየተረዳዳን አብረን እንኑር ይላል እንጂ፣ “ትግራይ ትስዕር” ከሚል የሃምሳ አመት ዕብድ ጋር ሆኖ ሁላችንም አንድ ላይ እንጥፋ አይልም። ለመሆኑ ትግራይ ትስዕር ሲባል . . . . ትግራይ ንመንያ ትስዕር፣ ወይም ትግራይ ማንን ነው የምታሸንፈው? 

ለምንድነው የትግራይ ልህቃን፣የትግራይ ወጣቶች፣የትግራይ የሃይማኖት መሪዎችና ባጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያን ያሸነፈች ትግራይ ከራሷ ጋር የተጣላች ክልል፣ ትግራይን ያሸነፈች ኢትዮጵያም ከራሷ ጋር የተጣላች አገር መሆናቸውን የዘነጉት? ሰው እንዴት እናቱን በመሳሪያ አሸንፎም ከራሱ ጋር ተጣልቶም በሰላም ይኖራል? የዋሺንግተን ዲሲንና የብራስልስን ጎዳናዎች ምላሽ በሌለው ሰላማዊ ሰልፍ ከማስጨነቅ፣ የትግራይ ልህቃን የዚህን ጥያቄ መልስ ፈልገው ቢያገኙ ትግራይ ታሸንፋለች! በተሸነፈች ኢትዮጵያ ውስጥ ትግራይ አታሸንፍም፣ የተሸነፈች ትግራይን ያቀፈች ኢትዮጵያም አታሸንፍም። የትግራይ ድል የሚገኘው በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ውስጥ ብቻ ነው።

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

2 COMMENTS

  1. አቶ ኤፍሬም ሌላ ሌላውን ነገር ትተህ ዝም ብለህ ብትጽፍ ብዙዎችን ታስተምራለህ፣ አገርንም በጣም ትጠቅማለህ ብዬ አስባለሁ

  2. There are Ethiopians who worked and lived in Tigray as government employees and private businessmen. Their view of the Tigray society is contrary to those of the elites. A considerable part of the Tigray society do not identify themselves with Ethiopia and back the anti-Ethiopia forces such as the TPLF. So let us base our analyses on the reality and seek solutions accordingly.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here