
ከጓንጉል ተሻገር
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማግኘት የሚባዝነው የዚህ የዚያ ጎሳ አባል ሳይሆን ብሔራዊ ጅግና National hero ነው። አብይ የዛሬ አራት ዓመት አገር ምድሩ ግልብጥ ብሎ የደገፈው ብሔራዊ ጀግና አገኘን ብሎ ነው። አሁንም ድረስ በአብይ ደጋፊ እና ተቃዋሚ መካከል ያለው የጦፈ ክርክር ብሔራዊ ጀግና ነው አይደለም በሚል ነው። የምንደግፈው አሁንም ብሔራዊ ጀግና ነው። ወያኔ ሰላሳ ዓመታት የተከለውን ነቀርሳ ለመንቀል እየታገለ ነው ስንል ሌላው የሚቃወመው ( ቁጥራቸው እየበዛ መጥቷል) የለም መስሎን ተሸውደናል፣ አቢይ ወያኔ ቁጥር ሁለት ነው፣ ከትግራይ ቡድን (ትህነግ) ጭቆና ምዝበራ ወደ ኦህዴድ/ኦነግ ጭቆና ምዝበራ ነው የተሸጋገርነው ይላሉ። በእኔ እይታ አቢይ አሁንም ብሔራዊ ጀግና ነው። ሁኔታዎች በይዘትም በፍጥነትም እንደ አጀማመራቸው አልሄዱም። ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ጥቂቶቹን እንያቸው
— አጠገቡ በድርጅትም በግለሰብም ደረጃ የተኮለኮሉት የጎሳ መሳፍንት ናቸው። በግለሰብ ደረጃ በሚዘገንን መልኩ ግርማ ፣ ገመዳ፣ ተሾመ፣ ሽፈራው ወዘተ ሁሉ አሉ። እነዚህ የጎጥ መሳፍንት ብቻ ሳይሆኑ የወያኔ የቅርብ ሎሌ የነበሩ አቢይን ራሱ ለመግደል ሲያሳድዱት የነበሩ ናቸው።
— በድርጅት ደረጃ የወያኔ/ኢሕአዴግ አባል የነበሩት ስም ቀይረው ብልፅግና ነን ቢሉም ውስጣቸው ያለው የጎሳ፣ የጎጥ አስተሳሰብ ስለሆነ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆና አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ብላ ስትናገር እንሰማታለን። ድርጅቶቹ ከዘር አስተሳሰብ አልፀዱም
— ኦነግ ኦነግ ሸኔ የሚባል ከስያሜው ጀምሮ የሚወዛገቡበት ድርጅት ኦህዴድ (ኦ ይቅርታ በኦሮሞ ብልፅግና) ውስጥ በተለይ በወለጋ ብልፅግና ውስጥ ከላይ እስከ ታች ሰርጎ ስለገባ የወለጋ ብልፅግናን እና ኦነግ ሸኔን ለመለየት እስኪይስቸግር ድረስ ምንም በማያውቁ የወራት የቀናት ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት፣ ነፍሰጡር ሴት፣ አዛውንቶች ሊያርድ በመቻሉ እና የዐቢይ መንግስት ከቁጥጥሩ ውጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለማውገዝም ዳተኝነት በማሳየቱ የወያኔ ቅጥረኛ የነበሩት አማካሪዎቹ አታውግዝ ብለውት ነው የሚል ጥርጣሬ ጭሯል።
— ሕገ መንግስቱ እስካሁን እንደ ታቦት ያለመነካቱም ዋና ችግር ነው። ሌላው ቀርቶ ለህዝብ ውይይት ለማቅረብ ፍርሀት መታየቱ የአቢይን ተወዳጅነት ከቀነሱት ምክንያቶች አንዱ ነው
ምን ይደረግ? Way forward
====
መደረግ ያለበት አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው
ሕዝብ እንዲመክር ተጠርቶ
- በሕገ መንግስት አጠቃላይ ይዘት
- በውስጥ ክፍላተሀገራት ክፍፍል
- በጎሳ ፖለቲካ ፣ የጎሳ ፖለቲካ ቡድን (በእኔ እይታ በኦሮሞ፣ በትግሬ፣ በአማራ፣ በወላይታ ወዘተ ስም የተሰባሰቡትን ሚልየነር ከማድረግ ያለፈ የጎሳ ፖለቲካ ለህዝብ ምንም አልጠቀመም)
- በሐይማኖት ነፃነት (ማጭበርበርን ሳይጨምር)
— በቋንቋ አጠቃቀም ላይ ውይይት አድርጎ ሕዝብ እንዲወስን ማድረግ ያላግባብ ዘግይቷል። ጎጠኞች ውይይት እንዲኖርም አይፈልጉም።
መደምደሚያ Conclusion
===
ከሩቅ፣ ዳር ሆኖ በስሚ ስሚ Hearsay እና አሉባልታ Rumour ላይ ተመስርቶ መቀባጠር እና በቅርበት በዓይን እርቀት ለመረጃ ቅርብ ሆኖ ሁኔታዎች ላይ አቋም መያዝ ይለያያል። አብን በቅርበት ሁኔታዎችን ለመረዳት ከመቻሉ በፊት ይቀባጥር ነበር። አሁን ሰክኗል፣ አገር መምራት የሚችል ድርጅት ሆኗል። አገር ለመምራት ማቻቻል፣ ሆደ ሰፊነት፣ ትዕግስት አስፈላጊ ነው። ኦነግ ነኝ ወይም የአማራ ተቆርቋሪ ነኝ ብለህ ሀያ ሰላሳ ሚልየን ሕዝብ እየዘለፍክ እንዴት ሀገር ለመምራት ታስባለህ? አይቻልም! በቅርበት inner circle ሆኖ ኃላፊነት በተሞላው መልክ መከታተል በሳል ፖለቲከኛ ያደርጋል። ከሩቅ መንጫጫት ግልብነት ነው። ከ1967-70 በነበሩት ዓመታት ጥፋት የደረሰበው ግልብ የሆኑ በዝተው ነው። ያንን ስህተት ይሄ ትውልድ ካላወቀበት ይደግመዋል። ያን ጊዜ የፖለቲካ ቡድኖች ግጭት ነው። ሕዝብ አልነበረበትም። አስራ አንድ የኢሕአፓ ወጣት ክንፍ አመራር አባላት ሲታሰሩ ቀጥ አለ።አሁን በግልብ ፖለቲከኞች ግጭት ውስጥ ከገባን ግጭቱ ሚልየኖች ለሚልየኖች ነው። ጥንቃቄ ያሻል።
ይሄው ነው
ቸር ይግጠመን!
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ