spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeአበይት ዜናአማራንና አፋርን ያገለለ ድርድር ውሎ አያድር  (ጋዜጣዊ መግለጫ )

አማራንና አፋርን ያገለለ ድርድር ውሎ አያድር  (ጋዜጣዊ መግለጫ )

እፋር  እማራ ህወሓት

ዋሽንግተን፣ ዲ.ሲ. 
መስከረም ፲፬፣ ፪ ሺህ ፲፭

የአገራችን ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታ፤  

ከሰሠላሳ አመታት በላይ በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየው፣ ኋላ-ቀርና ከፋፋይ የሆነው በዘር የተማከለዉ ስርዓት፣ ወደሚጠበቀዉ አሳዛኝ መጨረሻው ሲያሽቆለቁል እየታየ ነው። በሕገመንግሥት እውቅና የተሰጣቸው የክልል ግዛቶች፣ መጠናቸው ከፍ ያሉ ጎሰኛ የጦር ኃይሎች ገንብተው፣ ራሳቸዉን እንደመንግሥት በመቁጠር፣ ግዛታችዉን ለማስፋፋትና ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በመጣር ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በዋናነት ጎልተው የሚታዩትና የፌደራሉን መንግሥት የሚፈታተኑት የትግራይና የኦሮሞ ልዩ ኃይሎች ናቸው። የትግራይ ሰራዊት እንደ ኦሮሞ ፅንፈኞች ከቀበሌና ወረዳ የዘር ማጥፋትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ከመፈጸም አልፎ፣ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ያተኮረ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ካወጅ ቆይቷል። ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በመደበኛ ጦር በተደገፈ ወረራ ከፍተኛና አስከፊ የብዙሃን ግድያ፣ ዝርፊያና የንብረትና ኃብት ጥፋት አድርሷል፣ እያደረሰም ይገኛል።  

በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የተጫነው ማንነትን ዋነኛ መርኆ ያደረገ መዘዘኛ የፖለቲካ አመለካከትና የአስተዳደር ዘይቤ በአገራችን ላይ የሚታየውን ደም-አፋሣሽ እልቂት፣ የሰላም እጦት፣ የንብረት ውድመትና የአንድነት መሸርሸር አደጋዎችን አውርሶናል። ይህም ጦስ ወደፊት እንደማይቀጥል አስተማማኝ ምልክቶች አይታዩም። ይኽ የከፋፍለህ ግዛ ካልሆነ ደግሞ ተገነጣጠል ቅኝት እንዲቀጥል በፍርሃትና በቸልተኝነት እስከተፈቀደ ድረስ አስተማማኝ ሰላም፣ የዜጎች እኩልነትም ሆነ ከአድልዖ የጸዳ ፍትኅ፣ ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ እድገትና አንድነቷ የተከበረ አገርን ማግኘት እንደማይቻል ያንኑ ያኽል ግልጥ ነው። 

በትሕነግ-መሩ ኢሕአዴግም ሆነ ባለፉት አራት ዓመታት በኦሕዴድ/ኦብፓ በሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በጠላትነት ተኮንኖ በዋነኝነት የጥቃት ሰለባ የሆነው የአማራው ሕዝብ መሆኑ የማያሻማ ሀቅ ነው። ስለዚህ ነው በዚህ ጽንፈኞችና ወሮ-በሎች ስር በሰደዱበት አገር ፤ በአማራው ላይ የተደረጉ የጠላትነት ፍረጃዎች፣ ጭፍጨፋዎችና የውሸት ትርክቶች እንዳይቀጥሉ አማራው ህልውናውን ለማስከብር አንዲችል በማንኛው የድርድርና የስልጣን ክፍፍል መድረክ ላይ በማያሻማ መንገድ የመወከል እድል ሊኖረው የሚገባው። ቀድም ሲል የደርግ ስልጣን ተገርስሶ የወያኔ አረመኔአዊ አገዛዝ ሲመሠረት በኸርማን ኮኽን መሪነት በለንደን ስብሰባ እንደተከሰተው፣ ዛሬም አማራው በድርድር ጠረቤዛ መቀመጫ እንዳይኖርው የሚደረገው ሴራ በቀላሉ ታይቶ መታለፍ የማይገባው ጉዳይ ነው። 

ስጋቶቻችንና ግንዛቤዎቻችን፤  

እንደሚታወቀው ደም-አፋሣሽ ጦርነቶች በአንድ መልኩ ይሁን በሌላ በድርድር የመቋጨት ዕድል ይኖራቸዋል። ሆኖም በትሕነግና በፌደራል መንግስት ብቻ የሚኪሄድ ውስን የሁለትዮሽ ድርድር ከታሰበ የሚከተሉት ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ እንዲገቡ ግድ ይላል።

አንደኛ፣ ሕወሓት በአገር-መከላከያ ሠራዊት የሰሜን-ዕዝ ጦር ላይ በወሰደው አረመኔኣዊ እርምጃ፣ አገርን ለማፍረስ ያለውን ዓላማ በይፋ አሣውቆ መንግሥትን ለመገልበጥ ጦርነት በማወጅና ግልጽ ወረራ በማካሄድ፣ የውስጥ ፀረ-አንድነት ቡድኖችን በማደራጀት፣ በማሰልጠንና በማስታጠቅ፣ እንዲሁም ከአገሪቱ የውጭ ካሉ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመመሳጠር የሕዝብን ሰላምና የአገርን አንድነት ለአደጋ ያጋለጠ፣ በአሸባሪነት የተፈረጀ በመሆኑ፤ 

ሁለተኛ፣ ይኽ ድርጅት በመሪዎቹ በይፋ እንደሚነገረው ትግራይን “አገር” የማድረግ ሥር-የሰደደ ኅልም በማንገቡ፣ እንዲሁም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከማንኛውም ተጻራሪ ክፍል ጋር ያለውን ልዩነትም ሆነ አለመግባባት በሰላምና በድርድር የፈታበት ታሪክም ሆነ ልምድ የሌለው ከመሆኑ አኳያ በሁሉን-አቀፍ ፍጹም የኃይል የበላይነትን ካረጋገጠ ይዞታ ውጭ በሚደረግ ድርድር ትርጉም ያለው ውጤትን የማስገኘት ዕድሉ ሲበዛ አጠራጣሪ እንደሆነ፤እንዲሁም 

ሦስተኛ፣ የትሕነግ መሪዎች በድርድር የማይተዋቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩ ሊታወቅ ይገባል። ከእነዚኽ ውስጥ ዋነኛው እነሱ ምዕራብ ትግራይ የሚሉትን የአማራን ርስት በማጠቃለልና እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሕዝብን (በተለይ አማራን) በምስለኔዎቻቸው ማዋከብ፣ ከተጠቃሚነት ማግለል፣ማፈናቀልና መግደል የፓለቲካ ፕሮግራማቸው አንኳር ስልቶች መሆናቸው ትልቅ ስጋቶች ናቸው። 

በአንፃሩ የአብይ አህመድ አስተደደር ሁኔታውን በሚመለከት ያለው አቋም ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ብዙ ግራ-የሚያጋቡና የሚያሳስቡ ገፅታዎች እየተንፀባረቁበት ይታያል። ይህንንም ከሚያመላክቱት በዋናነት የሚከተሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፦ 

1. በሚስጥር የሚካሄደው ድርድር በነጻ ስለተመረጥኩ ሙሉ ቅቡልነት አለኝ እያለ የሚመጻደቀው የፌደራልም ሆነ ክልላዊ መስተዳደር አማራውን በቅንነት ሊወክል ቀርቶ አንዱ ጥቃት ፈጻሚና አግላይ ሆኖ በመቆየቱ አማራው በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተከድቶ ተገላይነቱ ለመቀጠል ያለው እድል ከፍ ያለ መሆኑ፣ 

2. መሪ-አልባው አማራ እንዳሻንጉሊት ሲፈለግ ላገር ሙት ተብሎ ይዘምታል፤ ሳይፈለግ ደግሞ ትጥቅ ፍታ፣ ሽፍታ ነህ የሚለው ብልጣብልጥነት መቀጠሉ፣ 

3. ስለ ድርድር አካሄድና ይዘት ብዙ ውዥንብሮች ይታያሉ። ድርድር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ደረጃዎች እንዳሉት ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል ተኩስ ማስቆምና ማረጋጋት፣ ብሄራዊ መግባባትና እርቀሰላም፣ የሽግግር ስርዓት፣ መዳረሻውም አዲስ ሕገመንስት ማጽደቅ መሆናቸውን መገንዘብ፣ 

4. የመጀመሪያውን የተኩስ ማቆምና መረጋጋትን ማስፈን በተመለከተ ድርድሩ በሁለት ቡድኖች መካክል (ወያኔ/ሕወሐትና ፌደራል) ብቻ መሆኑና፣ 

5. በዚህም የመጀመሪያ ድርድር ላይ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያውቁና ገለልተኛ የሆኑ አደራዳሪዎች አለመታየታቸው፣እንዲሁም የሲቪክና የፓርቲዎች ተወካዮች በታዛቢነት አለመመደባቸው ናቸው። 

አስገዳጅ ጥሪዎቻችን፤ 

በመካሄድ ላይ ያለው የሰላም ድርድርና የአደባባይ ትረካ፣ የአማራውን ሕዝብ በስነልቦና፣ በጭፍጨፋና በዝርፊያ አዳክሞ፣ የሕወሓትና ኦሮሙማን ዘላቂ ጥቅምና የበላይነት ፍላጎት ለማስጠበቅ የታቀደ መሆኑን በማያወላዳ መንገድ እንድንገነዘብ አድርጎናል። አገሪቱ ከዘር-ተኮር ወደ ዜጋ-ተኮር የፖለቲካ ስርዓት ወደፊት የሚደረገው አይቀሬ ሽግግር ስኬታማ እንዲሆን ፈር-ቀዳጅ የእርቀሰላም ሂደት ቁልፍ ሚና አለው።

ስለዚህ ሁሉም ያገባኛል ባይ ባለድርሻዎች፣ በተለይም አገር ወዳድ ዜጎችና አማራ ተኮር ድርጅቶች/ንቅናቄዎች እንዲሁም በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች እንደ ግዳጆች አይተው ከተበደለው ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ በጥሞና እንጠይቃለን፦ 

1. የአማራና የአፋር ሕዝቦች በሁሉም የድርድር ዐውዶች እንዲወከሉ መጣር፣ 

2. ከሃዲው ሕወሐት ከባድ መሳሪያንና ቋሚ ሰራዊቱን ለፌደራል አስረክቦና ህጋዊ ፓሪቱነቱ ተሰርዞ በቀጣዩ እርቀሰላም ሂደት የሽግግር ፍትህ እንዲሰጠው ማድረግ፣ኦነግንና ዝርያውቹንም እንዲሁ፣ 

3. ሕወሐት (እንዲሁም ብልጽግና) በዘረፋና በሙስና የገነባው በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሐብት ተቀምቶ ወሮ ላወደማቸው ዜጎችና ወራሾች ሙሉ ካሳ እንዲሰጥ መጠየቅ፣ 

4. በአማራነታቸው ተለይተው የታሰሩትን የህሊና እስረኞች፣ ጋዜጠኞችና፣ ፋኖዎች ካለ ቅድመሁኔታ እንዲለቀቁ በመንግስት ላይ ያልተቋረጠ ጫና ማድረግና፣ 

5. የነዚህ ሁሉ የማያባሩ ሰቆቃዎች መንስዔው ዘር ተኮር ህገመንስቱና አፋኝ አውታሮቹ ስለሆኑ አሳሪ መፈክራችን “የድርድር መነሻው ተኩስ ማቆም፣ መድረሻው ግን ለህግ በላይነት ምሰሶው ዴሞክራሳዊ ሕገመንግስት” እንደሆነ ምክረ ሃሳብን ማበርከት ናቸው ብለን እናምናለን። 

ከላይ የተጠቀሱትን መዳረሻዎች ተልዕኮ ያላደረገ ተኩስ ማቆም ብቻውን አገርን ከቀጣይ የቀውስ አዙሪት ሊያላቅቅ እንደማይችል ግልጽ ነው። መንግስት ታዛዥ እንጅ አዛዥ መሆን ስለማይገባውና ቆሞ ማየት ደግሞ ሞኝነት ስለሆነ ሁላችንም አወንታዊ አበርክቶች ላይ በቅንነት እንረባረብ። 

ፍታሃዊና ዘላቂ ሰላም ለአማራና ለኢትዮጵያዊ ሕዝባችን በሙሉ!!  

ፈራሚዎች፦  

1. Adwa Great African Victory Association (AGAVA) 

2. All Shewa Ethiopian People Multipurpose International Association 

3. The Amhara Association in Queensland, Australia 

4. Amhara Dimtse Serechit 

5. Amhara Well-being and Development Association 

6. Communities of Ethiopians in Finland 

7. Concerned Amharas in the Diaspora 

8. Ethio-Canadian Human Rights Association 

9. The Ethiopian Broadcast Group 

10. Ethiopian Civic Development Council (ECDC) 

11. Freedom and Justice for Telemt Amhara 

12. Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause 

13. Global Amhara Coalition 

14. Gonder Hibret for Ethiopian Unity 

15. Major Lemma Woldetsadik Memorial Foundation 

16. Network of Ethiopian Scholars (NES) 

17. Radio Yenesew Ethiopia 

18. Selassie Stand Up, Inc. 

19. Vision Ethiopia 

20.Worldwide Ethiopian Civic Associations Network (WE-CAN)

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here