
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለዉ ጦርነት እስካሁን እልባት አላገኝም፡፡ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ለማድረግ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነቱ እስካሁን ድረስ የሚቋጭበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡
በእርስ በርስ ጦርነት፤ በጎሳዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች እንዲሁም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱ አመራሮች እና በተቃዋሚዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶችና ዉዝግቦች ከዑመር አልበሽር አስተዳደር በኋላ እስካሁን መረጋጋት ያልቻለችዉ ሱዳን፤ ሁለቱን ተፋላሚ ሀይሎች ለማደራደር እንደምትፈልግ አስታዉቃለች፡፡
የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት አመራር አባል የሆኑት ሌተራል ጀነራል ሸምስ አላዲን ካባሺ፤ የአዉሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ከሆኑት አኔት ዌበር ጋር በካርቱም በተወያዩበት ወቅት ነዉ ሀሳባቸዉን የገለፁት፡፡ እንደ ጄነራሉ ገለፃ ኢትዮጵያና ሱዳን ረጂም ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸዉ ሲሆን ሰፊ የሆነ የጋራ ድንበርንም ይጋራሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለሱዳን እና ለአካባቢዉ መረጋጋት ትልቅ አስተዋፅኦ አለዉ ብለዋል፡፡ሱዳን የኢጋድ ሊቀመንበር እንደመሆኗ ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡና እንዲነጋገሩ ትፈልጋለች በማለት ለኔት ዌበር መናገራቸዉን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡እንደዘገባዉ ከሆነ ሱዳን ሁለቱን ተፋላሚ ሀይሎች የማደራደር ጥያቄ በይፋ ስለማቅረቧ የተባለ ነገር የለም፡፡
ሱዳን በሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ተአማኒነትን ማግኘቷ ያጠራጥራል ያለዉ ዘገባዉ፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በኩል በሱዳን ላይ እምነት ላይኖር ይችላል ብሏል፡፡ለዚህም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሶስትዮሽ ድርድር ጋር ተያይዞ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረዉ አለመግባባት አንዱ ነዉ ሲል ገልጧል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት በህወሃት ሀይሎች የተከፈተበትን ጦርነት ተከትሎ በሱዳን ድንበር የነበረዉን የሀገር መከመላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ ክልል ሲያንቀሳቅስ ሱዳን ደግሞ የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበትን የአልፋሽጋ ለም መሬት በወረራ መያዟ ይታወሳል፡፡ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን በወረራ ከያዘችዉ የኢትዮጵያ ግዛት እንድትወጣ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ማዉጣቱ ይታወቃል፡፡ይሁን እንጂ ቦታዉን እስካሁን ድረስ ሱዳን በወረራ እንደያዘችዉ ነዉ፡፡ይህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያሻከረ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የህወሃት ወጣቶች ክንፍ የሆነዉ ሳምሪ የተባለዉ ታጣቂ በማይካድራ በንፁሃን የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ካደረሰ በኋላ ወደ ሱዳን በመሸሽ በስደተኛ ስም ትጥቅና ስንቅ ከተለያዩ አካላት እየቀረበለት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እየፈፀመ ይገኛል፡፡ለታጣቂ ሀይሉም ነፃ የመንቀሳቀሻ ቦታ ሱዳን መስጠቷ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እምነት እንዳይጣልባት ያደርጋል፡፡
ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበዉ በጦርነቱ ምክንያት የተሰደዱ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች በሱዳን ይገኛሉ፡፡
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ