
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
በኦሮሞያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የተሰማራዉ የጸጥታ ግብረ ሀይል ለኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ሎጂስቲክ የሚያቀርቡ ከ1ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታዉቋል፡፡
ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራዉ እና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀዉ ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል በንፁሀን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ አሰቃቂ ግድያዎችን እና ማፈናቀሎችን እያደረሰ ይገኛል፡፡ይህ ቡድን ለዘመናት አብረዉ በኖሩ ህዝቦች መካከል የጥላቻ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሀገሪቱን የትርምስ ቀጠና እያደረገም ይገኛል፡፡
ቡድኑ በመንግስት መዋቅር ዉስጥም የራሱን አስተሳሰብና ተግባር የሚደግፉና የሚተገብሩ ተባባሪዎች እንዳሉትም በተጎጂዎች አንደበት ይነሳል፡፡ኦነግ ሸኔ ከሌላዉ በሽብር ከተፈረጀዉ ህወሃት ጋርም በይፋ ጥምረት መፍጠሩ አይዘነጋም፡፡
የኦነግ ታጣቂዎች ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እንዲሁም በቅርቡ በጋንቤላ ከተማ ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያዎችን ፈፅመዋል፡፡
ዛሬ በመከላከያ ሚኒስትር የደቡብ ዕዝ፤ ለሚዲያዎች በላከዉ መረጃ እንዳስታወቀዉ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የተሰማራዉ የፀጥታ ግብረ ሀይል ባከናወነዉ የዘመቻ ስራ ከ1ሺህ በላይ የቡድኑን የሎጂስቲክስ ስራ የሚያከናዉኑ አባላት በቁጥጥር ስር አዉሏል፡፡በቁጥጥር ስር የዋሉት አካላትም የኦነግ ታጣቂ ሀይልን በመደገፍ ሎጂስቲክስ የሚያቀርቡ ልጆቻቸዉን ለታጣቂ ሀይሉ አሳልፈዉ የሰጡ እና የሽብር ቡድኑን አላማ የሚደግፍ ተግባር ፈጽመዋል፡፡
በዞኑ ውስጥ ካሉ 11 ወረዳዎች መካካል በተመረጡ 7 ወረዳዎች የጸጥታ ግብረ ሃይሉ ባከናወነው ስራ ከ1ሺ በላይ የሽብር ቡድኑን ተግባር የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ አካላትን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ