spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትበአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ  ውሳኔ መወሰን ያለበት ማነው?  

በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ  ውሳኔ መወሰን ያለበት ማነው?  

ኤፍሬም ማዴቦ _  አገራዊ ምክክር
ኤፍሬም ማዴቦ (ከአባይ ሜዲያ ቃለ ምልልስ ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ነው)

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)  

በአንድ አገር ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ የሚወሰኑ አገራዊ ዉሳኔዎችን የሚወስነው ማነው የሚለው ጥያቄ መልስ በየአገሮቹ ውስጥ እንዳለው የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀርና እንደየአገሮቹ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታ ይለያያል። ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በህዝብ በተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ነው፣እንዲህ ማለት ግን ዲሞክራሲ ባለባቸው አገሮች ውስጥ ሁሉ አገራዊ ውሳኔዎች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይወሰናሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ ጀርመንና አሜሪካ ዉስጥ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት መንገድ ይለያያል። አሜሪካ ውስጥ ህግ የማውጣት ሥልጣን ያለው ምክር ቤቱ ነው፣ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፕሬዚደንቱም ህግ የማውጣትና ምክር ቤቱ ያወጣውን ህግ ያለማጽደቅ ሥልጣን አለው። ጀርመን ውስጥ ግን ፕሬዚደንቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩም/ቻንስለር የአሜሪካ ፕሬዚደንት ያለው ሥልጣን የላቸውም። ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ ህገመንግስቱ እንደተጻፈበት መንገድ፣ የህግ አስፈጻሚው አካል፣ የህግ አውጪው አካል፣ፕሬዚደንቱ፣ ፕሬዚደንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የህግ አውጪውና የህግ አስፈጻሚው አካል በጋራ አገራዊ ውሳኔ መወሰን ይችላሉ። በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወስኑት በአምባገነን መሪዎች ናቸው። 

ይህ በመግቢያው ላይ የተመለከትነው የውሳኔ አወሳሰን በሂደት ይለያያል እንጂ በየትኛውም ሉዓላዊ አገር ዉስጥ የሚኖር መደበኛ ሂደት ነው፣ ደሞም ዲሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ መደበኛ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በህዝብ በተመረጡ አካላት ነው። እንዲህ አይነቶቹ መደበኛ ውሳኔዎችና በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሳው “ውሳኔ” የሚለው ቃል በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ቢመሳሰሉም በቅርጽና በይዘት ግን ይለያያሉ። በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በአንድ አገር ውስጥ በህግ አውጪውና በህግ አስፈጻሚው አካል ከሚወሰኑ መደበኛ ውሳኔዎች ይለያሉ፣ እንዳውም አገራዊ ምክክር ያስፈለገው በመደበኛ ውሳኔ ሰጪ አካላት ደረጃ ሊወሰኑ የማይችሉ ውሳኔዎች በመኖራቸው ነው።   

ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ትላልቅ አገራዊ ውሳኔዎች የተወስኑት በጠመንጃ ኃይል ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ነበር። በነገስታቱ ዘመን ንጉሱና በባለሟሎቻቸው፣ በደርግ ዘመን ኮሎኔል መንግስቱና ኢሠፓ፣ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ደግሞ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ያሻቸውን ውሳኔ ወስነዋል። ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ከገዢው ፓርቲ ፍላጎት ውጭ የሆነ አገራዊ ውሳኔ አይወሰንም፣ ወይም ገዢው ፓርቲ የወሰነውን ውሳኔ ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ማስቀየር የሚችል አገራዊ ተቋም የለም። አገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው ግማሽ ምዕተ አመት የተጓዘችበት ጨለማው የቁልቁለት መንገድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ መንግስታት የወሰኑት ውሳኔ ውጤት ነው። ይህ የጨለማ መንገድ ተቀይሮ የብርሃን መንገድ እንዲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት  መንገድም ውሳኔ የሚሰጡ አካላት ማንነትና ስብጥርም መቀየር አለባት።

የአለማችን የቀውስ፣ያለመረጋጋት፣ የግጭትና የርስበርስ ጦርነት ምልክት የሆነችዉ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምትገኝበት ውስብስብና አደገኛ ቦታ ላይ እንድትደርስ፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጨምሮ ሦስት ተከታታይ መንግስታትና በእነዚህ ሦስት መንግስታት ውስጥ የነበሩ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ልህቃን፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ የጾታ ማህበራት፣የእምነት ተቋማትና ማህበራዊ ስብስቦች በማድረግም ባለማድረግም የየራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ዛሬ የገባንበት አገራዊ ቀውስ ምንጩ ባለፉት ሃምሳ አመታት አንዱ ሌላውን፣ ለማጥፋት፣ለማሸነፍ፣ ለማሳነስ፣ ለማንቋሸሽ፣ ለማውገዝና ለማሳደድ የሄድንበት የግራ ኃይሎች፣ የቀኝ ኃይሎችና ግራ የገባቸው ኃይሎች አፍራሽ የፖለቲካ መንገድ ነው። 

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ እኔን ጨምሮ የኔ ትውልድ፣ ከኔ የቀደመው ትውልድና የዛሬው ትውልድ በግልም በቡድንም ያበላሸነውን የአገራችንን ፖለቲካ በጋራ መፍትሄ እንድንፈልግለት መንገድ ከፍቶልናል። ይህንን አገራዊ ምክክር ብለን የጀመርነውን አዲስ መንገድ ስንጀምር፣ ነገሮችን በተለየ መንገድ መመልከት መጀመር አለብን እንጂ፣ያለፈው ሃምሳ አመት ልምዳችንን ለመድገም መሞከር “ሁላችንም ተያይዘን ገደል እንግባ” ከማለት ያላነሰ ዕብደት መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ አለብን።

በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ ልህቃን፣ምሁራን፣የማህበረሰብ ተወካዮች፣ሲቪክ ማህበራት፣የሰራተኛ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ወጣቶችና ሴቶች በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሂደት አሸናፊና ተሸናፊ፣ የሚከስርና የሚያተርፍ፣ የሚገንና ኮሳሳ ሆኖ የሚታይ፣ የሚኮራና የሚያፍር፣ የሚደሰትና የሚከፋ የማህበረሰብ ክፍል እንደማይፈጠር ተገንዝበውና፣ ከዚህ በፊት በተለያየ መልኩ ያደረጉት አፍራሽ እንቅስቃሴ በአገር ላይ ላደረሰው አደጋ ሃላፊነት ወስደው፣ ካሁን በኋላ ምንም አይነት አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ስራ እንደማይሰሩ ለራሳቸውና ለኢትዮጵያ ለህዝብ ቃል መግባት አለባቸው።

አገራዊ የምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን ህዝብ አሸናፊ የሚያደርግ እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ የሚፈጥር እንዳይሆን፣የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሂደት መንግስትን ጨምሮ ማንም አካል የኔ ነው የማይለውና ማንም አካል እንዳሰኘው የማይዘውረው ነጻ፣ግልጽና ገለልተኛ ሂደት መሆኑ መረጋገጥ አለበት። የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሥልጣንና ሃላፊነት ወሰን መወሰን ያለበት የጋራ በሆነ መድረክ ላይ እንጂ፣ በመንግስትም ሆነ በሌላ ሦስተኛ አካል መወሰን የለበትም። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ከረጂም ግዜ ግጭትና የርስበርስ ጦርነት ተላቀው ከዲሞክራሲ ጋር በሚተዋወቁ አገሮች ውስጥ የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ሲዘጋጅ ሁለት ትልልቅ ችግሮች ይገጥሙታል – አንደኛው- በህዝብ ያልተመረጠና ህዝባዊ ቅቡልነት (Legitimacy) የሌለው መንግስት መኖር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ቢኖርም የተመረጠበት መንገድ አጠያያቂና ህዝባዊ አመኔታ የጎደለው ሲሆን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ሁለተኛው አይነት ችግር ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረገው አገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ላይ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የምክክር ኮሚሺኑ ከሚጠይቀው አስተዳደራዊ፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስና የቴክኒክ ዕርዳታ ውጭ በጉባኤው ዝግጅት ሂደት ላይም ሆነ በጉባኤው ሂደት ላይ በምንም አይነት እጁን ማስገባት የለበትም።  

ብሔራዊ ውይይቶች ባለፉት ሃምሳ አመታት አውሮፓ፣ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ በተለያዩ አገሮች ውስጥ ተካሂደዋል፣ እነዚህ ውይይቶች በየአገሮቹ የወደፊት ላይ የተለያዩ ዉሳኔዎችን ወስነዋል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ህገ መንግስት አሻሽለዋል ወይም አዲስ ህገ መንግስት አርቅቀዋል፣ አንዳንድ አገሮች ውስጥ ግዜያዊ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም አድርገዋል፣ በአንዳድን አገሮች ውስጥ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሥልጣን ገድበዋል፣ የሽግግር ግዜ ፍትህ እንዲኖር ወስነዋል፣ ብሔራዊ የሰላምና ዕርቅ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ የምክክር መድረክ ያስፈለገው በአንድ በኩል እኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ማህበራዊ ኮንትራት መፈራረም አለብን የሚል ዘመናት ያስቆጠረ ጥያቄ በመኖሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የገባችበት እጅግ በጣም ውስብስብ የሆነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግር በሥልጣን ላይ ባለው መንግስት የሚፈታ ችግር ባለመሆኑ ወይም መንግስት እራሱ የችግሩ አካል በመሆኑ ነው። እንዲህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ የምክክር መድረክ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ መክሮ የተለያዩ ውሳኔዎች ይወስናል ማለት ነው። ለመሆኑ በአገራዊ የምክክር መድረኮች ላይ ውሳኔ የሚወስነው ማነው? የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ይነግረናል? እኛስ አገር በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ የሚወስነው ማነው?  

የውሳኔ አወሳሰንን በተመለከተ በተለያዩ አገሮች ዉስጥ በተካሄዱ ብሔራዊ የውይይት መድረኮች መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትና ዘዴ ላይ ነው እንጂ፣ ጉባኤው ዉሳኔ የመወስን ሥልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለው ላይ አይደለም። አንዳንድ አገሮች ውስጥ ለምሳሌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቤኒንና የመን ውስጥ የተለያዩ ውሳኔዎችን የወሰነው ጉባኤው ሲሆን፣ ሜክሲኮ ውስጥ በተካሄደው ብሔራዊ ጉባኤ ውሳኔ የወሰኑት ጉባኤው የሰየማቸው የስራ ቡድኖች (Working Groups) ናቸው፣ ሶማሊያና ቶጎ ውስጥ ደግሞ ለዚህ ጉዳይ የተቋቋሙ የውሳኔ አሰጣጥ ኮሚቴዎች ናቸው። በአገሮች መካከል እንዲህ አይነት የዉሳኔ አሰጣጥ ልዩነት የኖረው፣ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ያለው ችግር፣ የውሳኔ አሰጣጥ ባህል፣ የልህቃኑ የርስ በርስ ግኑኝነትና የመተማመን ደረጃ ስለሚለያይ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ በእነዚህ ልዩነቶች ላይ ተመስርቶ ዲዛይን ስለሚደረግ ነው። 

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ የሚወስነው ማነው? ባለፈው ታህሳስ ወር የወጣው የአገራዊ ምክክር ኮሚሺን ማቋቋሚያ አዋጅ ውሳኔን በተመለከተ ምን ይላል? በአገራዊ ምክክሩ ላይ የውሳኔ አወሳሰንን በተመለከተ  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 በክፍል ሁለትና በክፍል አራት ላይ የተቀመጡ ሁለት አንቀጾች አሉት 

አዋጅ ክፍል 2 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 10

የአገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልፅ ሰነድ በማዘጋጀት ለአስፈጻሚ አካሉ፣ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀርባል፣ ለህዝብም ይፋ ያደርጋል፣

አዋጅ ክፍል 4 አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2

በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለአስፈጻሚ አካሉ፣ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው  የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ማፅደቅ፣

ይህ ሁለተኛው አንቀጽ (አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2) ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ አስተያየት ቀርቦ ከተሻሻለ በኋላ የወጣው ነው፣ ከመሻሻሉ በፊት ይህን ይመስል ነበር

“በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለመንግሥት እንዲቀርብ ማፅደቅ”

የምክክር ኮሚሺኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ፓርላማ ቀርቦ ህዝብ አስተያየት ሲሰጥበት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ፓርላማ ተገኝቶ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራትና ሌሎችም የተለያዩ አካላት በተለያየ መልኩ ባቀረቡት ጥያቄ እንዲሻሻል ከጠየቁትና በዕለቱ ፓርላማው ውስጥ ከቀረቡት ህዝባዊ አስተያየቶች ውስጥ ብዙዎች እንዲሻሻል ከጠየቁት አንቀጽ ውስጥ ውሳኔን የሚመለከተው ይህ ካላይ የተቀመጠው አንቀጽ አንዱ ነበር። ሆኖም ከላይ እንደምትመለከቱት በመጀመሪያውና በተሻሻለው አንቀጽ መካከል ያለው ልዩነት የቃላት እንጂ የይዘት አይደለም። ለኔ ይህ የሚያሳየኝ መንግስት በአገራዊ ጉባኤው ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከእጁ እንዳይወጣ መፈለጉን ነው። አሁንም ይህ አንቀጽ ተሻሽሎ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከመንግስት እጅ ወጥቶ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው ካልተሰጠ፣ከዚህ ለአመታት ከተጮኸለትና ብዙ ከተደከመለት አገራዊ ምክክር እንደ አገርና እንደ ህዝብ የምናገኘው ብዙ ነገር አይኖርም! ለምንድነው መንግስት ባወጣው አዋጅ ላይ “አካታች” የሚል ቃል በተደጋጋሚ እየተጠቀመ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሲደርስ ግን አካታችነቱን ረስቶ የውሳኔ መወሰኑን ስራ ለራሱ የወሰደው?

በነገራችን ላይ የአገራዊ ምክክር ኮሚሺን ማቋቋሚያ አዋጅ ለኮሚሺኑ የሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት አዋጁ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፣ ኮሚሺኑ ብዙ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራ ቢሆንም የኮሚሺኑ ዋና ስራ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የምክክር ጉባኤዎችን ማደራጀት ነው። ኮሚሺኑ የሚያደራጀው ጉባኤ በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዋቀረው ጉባኤ የሚኖረው ሥልጣንና ኃላፊነት ግን በአዋጁ ላይ አልተቀመጠም። የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የሚኖረውን ሥልጣንና ኃላፊነት የሚወስነው በኮሚሺኑ ነው እንዳይባልም ይህንን በተለመከተ አዋጁ ለምክክር ኮሚሺኑ የሰጠው ምንም ሥልጣን የለም። ለመሆኑ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቀውና ብዙ የተደከመለት አገራዊ የምክክር ጉባኤ ምን አይነት ሥልጣንና ኃላፊነት ነው ያለው? ጉባኤው የራሱ የሆነ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሌለው ለምን ተዋቀረ፣ ለምንስ አስፈለገ? 

በአዋጁ ላይ “ምክረ ሃሳብ” የሚለው ቃልና “ዉሳኔ”/Decision የሚለው ቃል ተመሳሳይ ናቸው? ተመሳሳይ ከሆኑ ለምን አዋጁ ላይ ሁላችንም በቀላሉ የምንረዳው “ውሳኔ” የሚል ቃል አልተቀመጠም? ሁለቱ ቃላት ተመሳሳይ ካልሆኑ፣ አንደኛ- ሁሉን አቀፍ ሆኖ የሚቋቋመው አገራዊ የምክክር ጉባኤ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ እንጂ ውሳኔ መወሰን አይችልም ማለት ነው፣ሁለተኛ- በአዋጁ መሰረት የጉባኤውን ምክረ ሃሳቦች ተመልክቶ ውሳኔ የሚወስነው መንግስት ነው ማለት ነው። ለምንድነው ምክረ ሃሳብ ለመንግስት ብቻ የሚቀርበው? ሌሎቹስ ባለድርሻዎች? ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ አላስማማ ብለው ባጋደሉን ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መንግስት የሚወስን ከሆነ አገራዊ ምክክር ለምን አስፈለገ? በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እምነት በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ውሳኔ መወሰን ያለበት በጉባኤው በራሱ ወይም ጉባኤው በሚሰይማቸው አካላት ነው እንጂ፣ መንግስት በምንም አይነት ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ሊሰጠው አይገባም! 

በ2013ቱ ምርጫ በዕጩዎችና በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ፣ በምርጫ ዘመቻው ወቅትና በድምፅ አሰጣጡ ሂደት ላይ የታዩ መሰረታዊ ችግሮች አንዳሉ ሆኖ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ የተመረጠ ፓርላማ አለ። ፓርላማ ደግሞ የአንድ አገር ህግ የሚወጣበትና የተለያዩ አገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ቦታ ነው። ሆኖም በኔ እምነት የኢትዮጵያን የሚቀጥሉት መቶና መቶ ሃምሳ አመታት ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ገጽታ የሚቀርጹ ትላልቅ አገራዊ ውሳኔዎች የአንድ ፓርቲ ቤት በሆነ ፓርላማ መወሰን የለባቸውም። በእርግጥ ፓርላማ የህዝብ ተመራጮች ያሉበት ቦታ ነው፣ ሆኖም ፓርላማ በተፈጥሮው በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ባለድርሻዎች በሙሉ የሚገኙበት ተቋም አይደለም፣ የኢትዮጵያ ፓርላማ ደግሞ ጭራሽ አንድ ፓርቲ ያለምንም ተቃውሞ ያሰኘውን ውሳኔ የሚወስንበት ፓርላማ ነው። 

አገራዊ ምክክር ጉባኤ እንደ ፓርላማ በቀጥታ በህዝብ የተመረጡ አባላት ባይኖሩትም በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ከፓርላማው በበለጠ መልኩ የሚያሰባስብ አካል ስለሆነ በአካታችነቱ፣በስብጥሩና በህዝባዊ ቅቡልነቱ ዛሬ በስራ ላይ ካለው ፓርላማ የበለጠና የተሻለ ነው የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ከዚህ በተጨማሪ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች መክረው የሚወሰኑት ውሳኔ፣ ሰፋ ያለ ግዜ ተወስዶባቸውና ጥልቅ ውይይት ተካሂዶባቸው የሚወሰኑ ህዝባዊ ውሳኔዎች ስለሚሆኑ፣ በውሳኔው ሂደት ውስጥ የተሸነፉ ወገኖች ውሳኔው ባይስማማቸውም  የውይይቱና የውሳኔ አሰጣጡ ሂደት አካል ስለሆኑ ውሳኔውን ያከብሩታል።

አገራዊ ምክክር በየትም አገር በተለይ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ካለው መንግስት በጎ ፈቃድ፣ትብብርና ድጋፍ ውጭ መካሄድ አይቻልም። አገራዊ ምክክር እንዲካሄድ የመንግስት በጎ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ፣የሎጂስቲክስና የጸጥታ ድጋፍም አስፈላጊ ነው። አገራዊ ምክክር ተካሂዶ፣ ዉሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ትብብር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን መንግስት ውሳኔዎቹ እንዲካሄዱ የተለያዩ ድጋፎችን ይሰጣል፣ ውሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ይተባበራል ማለት ነው እንጂ፣ መንግስት በምክክሩ ዝግጅት፣ በምክክሩ ሂደትና በምክክሩ ውሳኔዎች ትግበራ ላይ የሚፈልገውን ያደርጋል የማይፈልገውን አያደርግም ማለት አይደለም። 

አገራዊ ምክክር በብዙ አገሮች ውስጥ በተለይ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ካለው መንግስት በጎ ፈቃድ፣ትብብርና ድጋፍ ውጭ መካሄድ አይቻልም፣ አገራዊ ምክክር ተካሂዶ፣ ዉሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ትብብር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን መንግስት ውሳኔዎቹ እንዲካሄዱ የተለያዩ ድጋፎችን ይሰጣል፣ ውሳኔዎች ከተወሰኑ በኋላም ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ይተባበራል ማለት ነው እንጂ፣ መንግስት በምክክሩ ዝግጅት፣ በምክክሩ ሂደትና በምክክሩ ውሳኔዎች ትግበራ ላይ የሚፈልገውን ያደርጋል የማይፈልገውን አያደርግም ማለት አይደለም።

ከአገራዊ ምክክር ጉባኤው ስራዎች አንዱና ትልቁ የኢትዮጵያን የሚቀጥሉት ሃምሳና መቶ አመት ዕድል መወሰን ነው። ይህንን ግዙፍና በአሁኑ ትውልድ ላይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት በሚመጣው ተከታታይ  ትውልድ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችልንና ሁላችንንም የሚነካ (Consequential) ውሳኔ ለአንድ ፓርቲ፣ ለጥቂት ፓርቲዎች ወይም በሥልጣን ላይ ላለው መንግስት ብቻ በፍጹም መተው የለብንም! የአገራዊ ምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባለድርሻዎችና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያቅፍ ነጻና ገለልተኛ አካል እስከሆነ ድረስ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል። የውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ ግዜ ወስደን መወያየት ያለብን አገራዊ የምክክር ጉባኤዉ የወሰነው ውሳኔ እንዴት መጽደቅ አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ ነው እንጂ፣ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የመፍጠርን ውሳኔ በምንም አይነት ለመንግስት ብቻ መተው የለብንም። 

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል የሌለው ችኮ ልህቅ ያለባት አገር ናት። እንዲህ አይነት ልህቅና ችኮነት የተጠናወተው የፖለቲካ ባህል ባለበት አገር ውስጥ የወደፊቷን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽታ በሚወስኑ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ዉሳኔ ማሳለፍ ከባድና ብዙ ግዜ ሊወስድ የሚችል አድካሚ ስራ ነው። የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሥልጣንና ሃላፊነት ምን ያክል ነው? ማነው ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው ሥልጣን የሚሰጠው? በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ ማን ይወስናል፣ እንዴትስ ይወስናል የሚሉ ጥያቄዎች አገራዊ ምክክር ጉባኤ በሚደረግባቸው አገሮች ውስጥ በጣም ቁልፍ የሆኑና በቀላሉ ስምምነት ላይ የማይደረስባቸው ጥያቄዎች ናቸው። 

እንደ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ በጦዘበት፣የፖለቲካ ልዩነቱን በውይይት የመፍታት ባህል የሌለውና ጎራ ለይቶ የተጋደለ የፖለቲካ ልህቅ ባለበት አገር ዉስጥ ዋናው ቁምነገር ህዝብ ለዘመናት የጠየቃቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸው ብቻ አይደለም። ጥያቄዎቹ መልስ የሚያገኙበት ሂደትና እነማናቸው ጥያቄውን የሚመልሱት ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስም አጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን ማን ይመርጣቸል፣ ተሳታፊዎች በምን መስፈርት ይመርጣሉ፣ ጉባኤው እነ ማንን ያካትታል፣ የጉባኤውን አጀንዳ ማን ይቀርጻል፣ የጉባኤውን ውሳኔዎች ማን ያጽድቃዋል ለሚሉ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ የጉባኤውን ዉጤታማነት፣ ቅቡልነት፣ህጋዊነትና ተግባራዊነት በቀጥታ ይወስናልና፣ የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ዲዛይን ሲደረግ ቁልፍ ባለድርሻዎች በተገኙበት በከፍተኛ ጥንቃቄ ዲዛይን መደረግ አለበት። 

ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ የምክክር ጉባኤ ያስፈለገው ዘመን ያስቆጠሩ ችግሮቻችን አሁን በስልጣን ላይ ባለው መንግስትና መንግስታዊ መዋቅሮች የሚፈቱ ችግሮች ባለመሆናቸው ብቻ አይደለም፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ልህቅና የፖለቲካ ባለድርሻ መንግስት የችግሩ አንዱ አካል ነው ብሎ ስለሚያምን ወይም መንግስት ብቻውን የችግሮቻችን መፍትሄ ይሆናል የሚል ዕምነት ስለሌለው ነው። ሰለዚህ ውሳኔን በተመለከተ አዋጁ ላይ የተቀመጡት ሁለቱ አንቀጾች ተሻሽለው፣ የተሻሻለው አዋጅ ውሳኔ የመወሰንን ሥልጣን በግልፅ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው መስጠት አለበት። ይህ እንዲሆን፣ የምክክር ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቭክ ማህበራት፣የሰራተኛ ማህበራት፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች፣ የጥናትና ምርምር ተቋሞች፣መገናኛ ብዙሃን፣የሰብዓዊ መብት ተቋሞች፣ ሴቶችና ወጣቶች በገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከመንግስት እጅ ወጥቶ የጉባኤው ሥልጣን እንዲሆንና ባጠቃላይ አዋጅ ቁጥር 1265 ላይ ውሳኔን በተመለከተ የተቀመጡ ሁለቱ አንቀጾች እንዲሻሻሉ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደር አለባቸው።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here