
ቦርከና
በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት አማጺዎች መካከል ለአስር ቀናት ያህል ውጥረት የተሞላበት በሚባል ሁኔታ ሲካሄድ የሰነበተው የሰላም ንግግር ዛሬ መጠናቀቁ ይፋ ሆኗል::
በንግግሩም ህወሓት ወታደራዊ ትጥቁን እዲፈታ ስምምነት ላይ የደርሰ ሲሆን ታጣቂዎቹም ወደ ሰላማዊ ህይወት የሚመለሱበት ሁኔታ አንደሚፈጠር ታውቋል::
ስምምነቱ ከነገ ጀምሮ ባሉት ቀናት ገቢራዊ የሚሆን ሲሆን አሉኝ የሚላቸውን ከባድ አና የቡድን መሳሪዎች ቆጥሮ ለፌደራል መንግስት አንደሚያስረክብ ተገልጿል ::
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በማንኛውም የትግራይ ክፍል የሃገር ህልውና የማስጠበቅ ስራውን ኢንዲሰራ ህወሓት የተስማማ ሲሆን መቀሌም በቀናት እድሜ በመከላከያ ሰራዊት ስር እንደምትሆን ታውቋል::
ሁለቱ ወገኖች ወደ ድርድር ከመሄዳቸው ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ጥምር ጦር አብዛኛውን የትግራይ ክልል ከተሞች በቁጥጥር ስር ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን መቀሌ ከተማም በጥምር ጦሩ እጂ የመግባት እድሏ የቀናት እድሜ ብቻ መሆኑ ሲተነበይ እንደነበረ ይታወቃል::
ስምምነት የተደረሰበት ሌላኛው ነጥብ ታጣቂው የህወሓት ቡድን የትግራይ ክልል መንግስት ነኝ የሚለውን የይገባኛል ጥያቄ የሰረዘ ሲሆን በክልሉ ጊዚያዊ አስተስዳደር አንደሚመሰረት እና በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ውክልና እንደሚኖራቸው ታውቋል::
የፌደራል መንግስትም የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦትን እንደሚያሳልጥ እና መሰረታዊ ማህበራዊ ግልጋሎቶችን በመላው ትግራይ እንደሚያዳርስ ታውቋል::
ኤርትራን በሚመለከት የህወሓት ቡድን የኢትዮጵያ መንግስት በድንበር ውዝግቡ ላይ የተላለፈውን አለማቀፋዊ ውሳኔ ተቀብሎ በባድመ ጉዳይ ላይ ለኤርትራ የሰጠውን እውቅና ይቀበላል:: የህወሓት ቡድን ከደረሰበት ወታደራዊ ሽንፈት እና ትጥቅ ለመፍታት ከመስማማቱ አንጻር ጉዳዮ የስምምነቱ አካል አካል ሆኖ መካተቱ ራሱ ትርጉም የሚሰጥም አይደለም::
የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አባላትን ባልታሰበ ሁኔታ በማጥቃት ከስድስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያን ሰራዊት አባላት ያስገደሉ እና ሌሎች መሰል ወንጀሎችን የፈጸሙ የህወሓት ባለስልጣናት እጣ ፋንታ ምን እንደሚሆንም የታወቀ ነገር የለም::
ምንም እንኳን ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት ህወሓት በቀሰቀሰው ትርጉም አልባ ጦርነት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማለቃቸውን እና መጠነ ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፈጠሩ ለቡዙ ኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ስሜት የፈጠረ ቢሆንም የሰላም ስምምነት ላይ በመደረሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ድረ ገጽ ደስታቸውን እየተገለጹ ነው ::
ሆኖም የስምምነቱ ተግባራዊነት በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት የሚታይ ይሆናል ::
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ