
እዮብ ሰለሞን
የዘር ፖለቲካ የቆሰቆሳችሁ፤ ሕዝብን በዘረኝነት እሳት የለበለባችሁ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከከፍታው ማማ አውርዳችሁ የተዘባበታችሁ፤ የትግራይ ሕዝብ የመሰረታትን ሀገሩን እንዲያፈርስ የጎተጎታችሁ፤ ትግራይ ከአፋር፤ አማራ እና ኤርትራ ወገኖቿ ጋር ደም እንድትቃባ ያደረጋችሁ፤ ሀገሩን ትቶ መንደሩን ብቻ እያሰበ እንዲኖር የኢትዮጵያዊውን ወጣት አዕምሮ በቆሻሻችሁ የበከላችሁ፤ ለመቶ ሺዎች ንፁሃን ኢትዮጵያዊያን ሞት እና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆናችሁ፤ የሀገር ሉዓላዊነትን ያራከሳችሁ፤ ሀገር ጠባቂውን ወጥቶአደር ከጀርባው የወጋችሁ፤ ሰንደቅዓላማችንን ያዋረዳችሁ፤ የአክሱምን ክብር ያንቋሸሻችሁ፤ የነጃሺን ቅድስና ያበሻቀጣችሁ፤ የዐፄ ካሌብን መንበር የተዳፈራችሁ፤ የኢዛናን እርስት ሀገር የበደላችሁ፤ ወንድምን በወንድሙ ላይ ያነሳሳችሁ፤ የአዴታት ተጋሩን ማሕፀን ያነጠፋችሁ፤ ትግራይን የወላድ መሀን ያደረጋችሁ፤ የአፋሮችን እና የአማሮችን ጎጆ ያፈረሳችሁ፤ የአድዋን ድል እሴት የሸረሸራችሁ፤ የዐፄ ዮሐንስን ቃልኪዳን ቀርጥፋችሁ የበላችሁ፤ ሀገር ምድሩን ያሸበራችሁ፤ ግብረገብ ያላነፃችሁ፤ ሃይማኖተ ሕግ ያልበገራችሁ፤ ፋሺስትነት የተጠናወታችሁ፤ የጭካኔ ጥግ ያወራችሁ፤ እናንተ የምድር ጉዶች ሆይ! የዐፄ ዮሐንስ መስዋዕትነት ይታዘባችኋል፤ የአሉላ አባነጋ አጥንት ይወጋችኋል፤ የንፁሃን ደም ይፋረዳችኋል፤ የፈጣሪ ፍርድም ይጠብቃችኋል፡፡
አኹን ጦርነቱ እያበቃ የሰላም በሮች መከፈታቸው እየተሰማ ባለበት በዚህ ወቅት የፍርድ ዙፋን ላይ ራስን አስቀምጦ የጦርነት ቆስቋሾችን በቃላት መሸንቆጥ የሰላም አደናቃፊ ለመኾን አይደለም፡፡ የአፈሙዞች ላንቃ ሊዘጋ ባለበት በዚህ ሰዓት የጦርቱን ገፅታ መዳሰሱ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” የሚለው ተረት ደርሶብኝ አይደለም፡፡ የጠብመንጃ ላንቃ ሲዘጋ የብዕሬ ጫፍ ቃላት መትፋት የጀመረው የነፍስ ሰቆቃ አስገድዶኝ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን የሚፈጅ የፖለቲካ ርዕዮትዓለም ሊያመጣ የሚችለው አደጋ ተደጋግሞ ለዓመታት ተነግሮም፤ ጆሮ ዳባ ልበስ መባሉ ሚሊዮኖችን ፈጀ፤ ሀገር አጎሳቆለ፤ ማሕበራዊ ውልን አናጋ! ዛሬም በዘር ፖለቲካ ሙዚቃ እንደንሳለን የሚሉ ድኩማን መኖራቸው ደግሞ የነገ ሰቆቃችን ምን ሊኾን እንደሚችል ማሰብ ብዕር አያስመዝዝምን?
600 ሺ የኢትዮጵያ ልጆችን ማን ገደላቸው?
ከሩዋንዳ አንማርም ያልን ጉዶች ከራሳችንስ ኹኔታ መቼ ይኾን የምንማረው? ሚሊዮኖችን የበላ የዘር ፖለቲካ እሳት ዛሬም የምናሽሞነሙነው ምን እርኩስ መንፈስ ተጠናውቶን ይኾን? የ“እኛ እና እነርሱ” ትርክት የአንድ ሀገር ልጆችን ሲያገዳድል ይኸው በአይናችን እያየነው፤ በብሔረሰቦች መብት ሥም ለቀጣይ ትውልድ የሞት ድግስ የምንጠነስሰው እኛ የዓለም መሳቂዎች አናሳፍርምን? ስንት ሚሊዮን ሕዝብ ሲያልቅ ይኾን የዘር ፖለቲካ ጦስ የሚገባን?
ለመኾኑ ለኹለት ዓመት ያህል ሀገራችንን በጥይት አረር ሲቆላ የቆየው ጦርነት ምንጩ የዘር ፖለቲካ ጦስ አይደለም ብሎ የሚከራከር ይኖር ይኾን? በዘር ፖለቲከኞች ፕሮፓጋንዳ የተጠመቀ ወጣት በበዛበት ሀገር የዘር ፖለቲካን ጣጣ ለማስረዳት ተራራ የመውጣት ያህል መከራችንን መብላታችን አያስገርምም፡፡ የጦርነቱ ሥረ መሠረት የዘር ፖለቲካ መኾኑን አንባቢ እንዲገነዘበው ትንሽ ማሳያ ማቅረቡ ጠቃሚ ነው፡፡
ያ ትውልድ የሌኒንን መፈክር አነገበ፡፡ “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል ይከበር” አለ፡፡ የያ ትውልድ አባላት የኾኑት አባይ ፀሐዬ እነ ሥዩም መሥፍን በስታሊን ርዕዮት መሠረት “የትግራይን ጭቁን ብሔር ከአማራ ጭቆና ነፃ እናወጣለን” ብለው ትግል ጀመሩ፡፡ በለስ ቀንቷቸውም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን ተቆጣጠሩ፡፡ ቀጠሉና የቆረቡበትን የስታሊን ፍልስፍና በህገመንግሥት ፃፉት፡፡ ዘረኝነት ፖለቲካውንም፤ ኢኮኖሚውንም፤ ቤተ እምነቱንም፤ እንዲቆጣጠር የሕግ፤ የመዋቅር እና የፕሮፓጋንዳ መላ አበጃጁ፡፡ ሕዝቡንም በዘረኝነት መርዝ ነደፉት፡፡ ከአድዋ እስከ ማይጨው፤ ከካራማራ እስከ ዶጋሊ ለአንዲት እናት ሀገር ኢትዮጵያ የተዋደቀውን የሀገር ልጅ በዘር ክልል ሸነሸኑት፡፡ ሀገሩ ክልሉ የሚመስለው አድማሰ ጠባብ ትውልድ ፈጠሩ፡፡ በዘር ተቧነው ዘረፋ እና በደል ፈጸሙ፡፡
የኋላ ኋላ የግፍ ፅዋ ሲሞላ የህወሓት ቁንጮዎች ከስልጣን ተወግደው መቀሌ ከተሙ፡፡ የዘረፉትን ቁጭ ብለው ለመብላት ሆዳቸው አልፈቀደም ነበር እና “እኛ ያልመራናት ኢትዮጵያ ትፍረስ” ብለው የጦርነት እሳት ለኮሱ፡፡ በዘረኝነት መርዝ በክለው ያሳደጉትን ወጣትም እንደገና ሀገሩን እንዲያፈርስ በገፍ እየጫኑ የጥይት ሲሳይ አደረጉት፡፡ ከአሞራ እና ከጅብ እራትነት የተረፈውን የትግራይ ወጣት ደግሞ በአፋር እና በአማራ ክልል የገዛ ወገኖቹን እንዲጨፈጭፍ፤ እንዲደፍር እና እንዲዘርፍ አሰማሩት፡፡
ይህ ኹሉ የህወሓት መሪዎች የጥፋት ታሪክ የሚያመለክተው በዘር ተቧኖ ፖለቲካ መሥራት ተያይዞ ከማለቅ ውጪ የሚያመጣው ጥቅም እንደሌለ ነው፡፡ ህወሓት በዘረኝነት ተቧድኖ እና ታውሮ ሀገር ባያጠፋ ኖሮ፤ ከመንደርተኝነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን ቢያስቀድም ኖሮ፤ “የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው” በሚል ፀረ-ኢትዮጵያ መርህ ባይመራ ኖሮ፤ “ከአማራ ይልቅ ሱዳን ትቀርበናለች” በሚል ትዕቢት ባይወጠር ኖሮ፤ በአጠቃላይ በዘር ፖለቲካ ቡድንተኝነት ርዕዮትዓለም ባይመራ ኖሮ፤ ዛሬ ሀገር አንገቷን አትደፋም ነበር፡፡ የንፁሃን ሚሊዮኖች እልቂትም አይኖርም ነበር፡፡ ሀገራችን የማንም ጸረ-ኢትዮጵያ ፈረንጅ መዘባበቻ አትሆንም ነበር፡፡
አዎን ላለፉት 30 ዓመታት በአጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ ላለፉት ኹለት ዓመታት፤ ሀገራችን ላይ ለደረሱ ሰቆቃዎች ዋነኛ ምንጩ የዘር ፖለቲካው ነው፡፡ የትግራይ ዳያስፖራዎች “ሞተዋል” ወይም “ጄኖሳይድ” ተፈፅሞባቸዋል ላሏቸው የኢትዮጵያ ልጆች የመጀመሪያም የመጨረሻም ተጠያቂው የዘር ፖለቲካ ቡድንተኝነት ነው፡፡ በትግራይ ሕዝብ ሥም እየማለ የትግራይን ሕዝብ ያስፈጀው በህወሓት በኩል የዘር ፖለቲካው ነው፡፡ ይህንን ሀቅ እየመረረንም ቢኾን ካልዋጥን ሌላ የመከራ ድግስ ኢትዮጵያችንን እንደሚጠብቃት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵዊያን ኹሉ የነገ ተረኛ ዕጩ መከረኞች ነን
ይህ ትንቢት አይደለም፡፡ ቅዠት እና ማስፈራሪያም አይደለም፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ለመላው ኢትዮጵያዊ የተላለፈ የጥንቃቄ ጥሪ ነው፡፡ ከእንድ ተራ የኢትዮጵያ ልጅ የተላለፈ ወገናዊ ጥሪ ነው፡፡ ኹሉም ኢትዮጵያዊ የነገ ዕጩ መከረኛ መኾኑን ሊያውቀው ይገባል፡፡ በዘር ፖለቲካ መርዝ በተነደፈች ሀገር ውስጥ እየኖርን የተድላ ሕይወት ከጠበቅን በጣም ተሳስተናል፡፡ በዘር የተደራጀ ህገመንግሥት፤ ፓርቲ፤ ክልል፤ ልዩ ኃይል፤ ሚዲያ፤ ባንክ፤ ማሕበር ወዘተ እያቋቋምን ነገ የሚያስተሳስረን ነገር ኹሉ ተበጣጥሶ የእልቂት አዙሪት ውስጥ እንደምንገባ ማሰብ ካልቻልን አደጋ ላይ ነን ማለት ነው፡፡
ዛሬ ላይ በዘረኝነት መንፈስ የተቃኘ የክልል እና የልዩ ኃይል መዋቅር መሥርቶ ሀገራችን ላይ ጦርነት መለኮሱ በዚሁ የሚያበቃ ቢኾን ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን በአንድ ብሔረሰብ ሥም ብቻ የሚቋቋም ፓርቲ፤ ክልል እና ልዩ ኃይል መኖሩ እስከቀጠለ ድረስ ነገ ከነገወዲያ ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ሀገር እና ሕዝብ የሚያደማ የእልቂት ድግስ መኖሩ አይቀርም፡፡ አንድ ነገር ግልፅ መኾን አለበት፡፡ ህወሓት ከውልደቱ ጀምሮ ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ ሕዝብ አቋም እያራመደ ሀገር ያሸበረው በተከተለው ርዕዮትዓለም ምክንያት እንጂ አመራሮቹ ከሌላ ፕላኔት ስለመጡ አይደለም፡፡ ህወሓት በትግርኛ የሚያቀነቅነውን የዘረኝነት ሙዚቃ በአማርኛ፤ በኦሮምኛ፤ በሶማሊኛ እና በሲዳምኛ ደግመን ካስተጋባነው የኢትዮጵያ መከራ በቀጠሮ ለሌላ ጊዜ ይተላለፋል እንጂ ችግሩ ከምንጩ አይደርቅም፡፡ እንደውም ሰቆቃችን ተባባብሶ በሌላ ጊዜ እና ኹኔታ ይከሰታል፡፡
በአንድ መሬት ላይ በጋራ እየኖርን መሬቱ የኔ ብቻ ይኹን እያልን፤ ብዙ ቋንቋች ባሉበት ሀገር የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ በስማቸው ምክር ቤት እየተቋቋመላቸው፤ በብዙ መስዋዕትነት አያቶቹ ያስረከቡትን ሀገሩን እንዲጠላ የተደረገ ትውልድ እየተፈጠረ፤ በአባቶች መስዋዕትነት ቀኝ ሳይገዛ ነፃ ኾኖ የኖረውን ሕዝባችንን በእከሌ ብሔር ቀኝ ተገዝተሀል ብለን እየሰበክን፤ የክልል ወሰኖች እንደ ሀገር ድንበር ተቆጥረው ደም እያፋሰሱ ባለበት ኹኔታ፤ ከኹለት ቋንቋ ተናጋሪዎች የተወለደን ኢትዮጵያዊ የግዴታ ማነትህ በአባትህ ወገን ብቻ ነው በሚል እሳቤ ትውልድ ከሀገር እንዲያንስ እየተደረገ፤ ዜጎች ከገዛ ሀገራቸው ይህ የእናንተ እርስት አይደለም በሚል በሚገደሉበት እና በሚፈናቀሉበት ሀገር፤ የክልል ፕሬዝዳንቶች በክልላቸው አንድ ብሔረሰብ ብቻ የሚኖር ይመስል የአንድ ብሔረሰብ ወኪል ኾነው በሚቀርቡበት ኹኔታ፤ የክልል የፀጥታ መዋቅሮችም የአንድ ብሔረሰብ ጠባቂ ብቻ ኾነው በሚጠመቁበት ሀገር፤ ኢትዮጵያችን ነገ ከጦርነት አዙሪት ትወጣለች ብለን ካመንን በሚሊዮኖች ሕልውና ላይ እቀለድን ነውና ቆም ብሎ ማሰቡ ከዘላለማዊ ፀፀት ያድናል፡፡
እንደሀገር እናስብ፤ እንደትውልድ እንዳን
ዛሬ ላይ ቆመን ስለነገ እናስብ፡፡ ከትናንት ጥፋታችን እንታረም፡፡ የዘረኝነት ፖለቲካ እንዳወደመን እንመን፡፡ ኹላችንም ለአንዲት ሀገር በአንድነት እንቁም፡፡ የአንድ ሀገር ሰዎች፤ የአንድ ቤተሰብ ልጆች መኾናችንን እንቀበል፡፡ መቀሌ ተወልዶ ያደገም ኾነ የሐዋሳው ልጅ የኢትዮጵያ እኩል ባለቤቶች እንደኾኑ በህግ፤ በመዋቅር እና በትርክቶቻችን እናስተጋባ፡፡ “አክሱም ለወላይታው ምኑ ናት” የሚለውን አፍራሽ አስተሳሰብ አክሽፈን፤ አክሱም የኢትዮጵያዊያን ኹሉ እርስት ናት እንበል፡፡ ትውልዱን በሀሰት ትርክት አናባላው፡፡
በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰችውን ሀገር በቆሻሻችን አንበክላት፡፡ ኢትዮጵያዊ እሴትን አናፍርስ፡፡ ሀገራችንን እየተቃረንን ከራሳችን ጋር አንጣላ፡፡ የጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት ይታወሰን፡፡ አባቶች በፍቅር ያቆሟን ሀገር በጥላቻ አናሸብራት፡፡ የፖለቲካችን መዋቅርም ዜግነታችንን እና ብቃታችንን እንጂ የበቀልንበትን አካባቢያዊ ማንነት መሠረት አያድርግ፡፡ በሀሳብ እንጂ በጎሣ አንደራጅ፡፡ የኦሮሞ ጥቅም ከአማራው፤ የአማራው ከትግሬው፤ የትግሬው ከጉራጌው፤ የጉራጌው ከሲዳማው፤ የአፋሩ ከሶማሊው ተነጥሎ ሳይሆን በሕብረት ሊከበር እንደሚችል እናስብ፡፡ እንዴት እንደምንጣላ ሳይኾን እንዴት እንደምንተባበር እናስብ፡፡ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ሀገር መኾን ኹላችንንም የሚጎዳ አፍራሽ አካሄድ እንደኾነ እንገንዘብ፡፡ የባህል፤ የቋንቋ እና የማንነት ጥያቄዎቻችንን ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር አናጣብቀው፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሕበሮቻችን ኹሉን አቃፊ እንጂ በጎሣ የምንሰባሰብበት አናድርገው፡፡ የህወሓትን ስህተት አንድገመው፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ሰቆቃ በእኛ እንዲያበቃ እናድርገው፡፡ የእኛን ኢጎ ለማርካት በሚሊዮኖች ሕይወት አንቀልድ፡፡
በኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች ኹሉ ፍላጎታቸው የተሻለ ኑሮ፤ ትምህርት፤ የስራ ዕድል እና ክብር ነው፡፡ ይህንን ፍላጎት ለሟላት በዘር እየተቧኑ መቧጨቁ፤ መሿሿሙ፤ ጦር መማዘዙ፤ መገዳደሉ፤ ንፁሀንን ማፈናቀሉ፤ ትውልድን በጥላቻ ትርክት መበከሉ በማያልቅ የግጭት አዙሪት ውስጥ እንድናልፍ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ህወሓት የተጓዘበትን የውድመት መንገድ ደግሞ መጓዙ እንደማይበጀን አኹኑኑ መገንዘብ አለብን፡፡ ነገሮችን እያሽሞነሞኑ በዘር ፖለቲካ አዙሪት መቀጠሉ ለሕዝብ ስቃይ ኹኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡
የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞቻችን ዛሬ ነቅተው የችግሮችን ምንጭ ለማድረቅ ከሰነፋችሁ ወይም ካልፈለጋችሁ፤ በዕርግጥም የዐፄ ዮሐንስ መስዋዕትነት ይታዘባችኋል፤ የአሉላ አባነጋ አጥንት ይወጋችኋል፤ የንፁሃን ደም ይፋረዳችኋል፤ የፈጣሪ ፍርድም ይጠብቃችኋል፡፡ ዐፄ ዮሐንስ መስዋዕትነት የከፈሉት ኢትዮጵያን ከወራሪዎች ሲከላከሉ ነው፡፡ አሉላ አባነጋ ዘመናቸውን የጨረሱት ለኢትዮጵያችን ሲዋደቁ ነው፡፡ የትግራይ ብሔርተኞች በትግራይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵን በመመስረት፤ በመጠበቅ እና በማልማት ላይ ያለውን አስተዋፅዖ ወደጎን ብለው ኢትዮጵያ የተወለደችበትን ስፍራ በጸረ ኢትዮጵያ ትርክት በክለው፤ ሀገር የሚያፈርስ ጦርነት ከፍተዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲሞቱ እና ሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ አድርገዋል፡፡
አኹን ላይ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ የጠብመንጃ ላንቃዎች ሊዘጉ መኾኑን እየሰማን ነው፡፡ ይህ አንድ እርምጃ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እነዚህ የትግራይ ብሔርተኞች በፀረ ኢትዮጵያ ትርክት የቃኙትን የትግራይ ወጣት በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለማደስ ካልሰሩ፤ ነገሩ ኹሉ ታጥቦ ጭቃ መኾኑ አይቀርም፡፡ አሉላ አባነጋ የተዋደቀላትን ሀገር በልኳ እንድትገኝ ካልተባበራችሁ ጥፋታችሁ መቼም ቢኾን ሊካካስ አይችልም፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያላችሁ የዘር ፖለቲካ ዘፈን ዳንሰኞችም ብትኾኑ ሀገራችን ላይ ከደረሰው ውርደት እና እልቂት ተምራችሁ፤ ስርነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ ካላደረጋችሁ፤ የጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት ይታዘባችኋል፤ የሀገር ባለውለታዎች አጥንት ይወጋችኋል፤ የንፁሃን ደም ይፋረዳችኋል፤ የፈጣሪ ፍርድም ይጠብቃችኋል፡፡ በታሪክ መዝገብ ላይም በክፋት ተምሳሌትነት ስትጠቀሱ ትኖራላችሁ፡፡
_
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ