spot_img
Sunday, May 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትየሰላም ስምምነቱ አንኳር ነጥቦችና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ! (ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ ዶ/ር)

የሰላም ስምምነቱ አንኳር ነጥቦችና ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ! (ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ ዶ/ር)

- Advertisement -
ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ

ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ (ዶ/ር)
ፍሪቦርግ ከተማ፣ ስዊትዘርላንድ 

  1. መግቢያ

ለአስር ቀናት ያህል በቆየውና በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር መካከል በተደረገው የሰላም ውይይት አማካኝነት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች አስራ አምስት አንቀጾችንና አስር ገጾችን በያዘው የስምምነት ሰነድ ላይ ተፈራርመዋል፡፡ የስምምነት ሰነዱ በአጠቃላይ ሲታይ የፌዴራሉ መንግስት በአሸናፊነት የወጣበትና የኢትዮጵያን ሕዝብ እፎይታ የሚያስገኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡ 

ይህም ሆኖ በሰላም ስምምነት ሰነዱ ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ድንጋጌዎች በአንቀጽ 2፣ በአንቀጽ 6፣ በአንቀጽ 7 እና በአንቀጽ 10 ስር የሚገኙት ንዑስ አንቀጾች በጣም ጠቃሚ ሀሳቦችን የያዙ ቢሆንም የተወሰኑ አወዛጋቢና አከራካሪ ሀሳቦችንም ይዘዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም አብዛኛዎቹ የሰላም ስምምነቱ ድንጋጌዎች ትህነግን ከጫወታ ውጭ እንዳደረጉ ተመልክተናል፡፡ 

ሆኖም በስምት ሰነዱ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑት ድንጋጌዎች ደግሞ ከእነ ድክመቱም ቢሆን በአፈጻጸሙ ሒደት ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ራሱ ካላበላሸው በስተቀር ትህነግ በህይወት እንዲቀጥል ዕድል የሚሰጡት በመሆኑ እና በቀጣይም በትጥቅ ማስፈታት ሒደቱ ላይ የመደራደር አቅም እንዲኖረው ስለሚያደረጉት የተወሰኑ የስምምነት ሰነዱ ድንጋጌዎችንና በስራቸው የሰፈሩ ሀሳቦችን በመጠቀም አንገቱን ቀና ለማድረግ የቸለውን ያህል መውተርተሩ አይቀርም፡፡ 

ለመሆኑ እነዚህ አራት ድንጋጌዎችን ብቻ ለይተህ ለምን ወሳኝና ትኩረትን የሚስቡ ናቸው አልህ ለሚለኝ ሰው በመጀመሪያ የእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት ምን ይመስላል የሚለውን እንዳለ እያስቀመጥሁ ለምን ወሳኝ እንደሆኑ ደግሞ በትንሹም ቢሆን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ ይህም ማለት የእነዚህን ድንጋጌዎች የእንግሊዘኛ ዐረፍተ ነገር ወደ አማርኛ እየመለስሁ ካስቀመጥሁ በኋላ የያዙት ሀሳብ ምን እንደሆነ እና በምን መልኩ ልንረዳቸው ይገባል የሚለውን ሁኔታ በአጭሩ ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡

  1. ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች መልዕክትና የእኔ ምልከታ

እንግዲህ ከላይ የሰፈሩትን አንቀጾች ይዘትና ዋነኛ መልዕክት በደንብ አስተውሎ ለተመለከተ ሰው ጠበቅ ያሉ ድንጋጌዎችና ለውዝግብ በር የሚከፍቱ ሀሳቦች ያሉት በእነዚህ አንቀጾች ስር ባሉት ንዑስ አንቀጸች ውስጥ እንደሆነ ለመገንዘብ አይቸገርም፡፡ ለምሳሌ በአንቀጽ 2 (f) እና በአንቀጽ 10 (3) ላይ የሰፈሩትን ሀሳቦች ስንመለከት በኢፌዴሪ ህገ መንግስትና በአፍሪካ ህበረት የሽግግር ወቅት ፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ተመስርቶ የተጠያቂነትና የሽግግር ወቅት ፍትህ ሊሰፍን እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ይህም ማለት ጦርነቱ ባደረሰው ጉዳት ልክና አስገፊ ገጽታ በህገ መንግስቱና በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ወቅት ፖሊሲ መርሆዎች መሰረት ተጠያቂ የሚሆን ወገን እንደሚኖር፣ እውነትን የማረጋገጥ፣ ለተጎጅዎች ዘላቂ መፍትሄ የመስጠት፣ የእርቅና ስብራትን የመጠገን ስራዎችን የመስራት ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣሉ፡፡ 

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ውዝግብ ሊነሳ የሚችለው፣ ለምን ቢባል ማን ነው ማንን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችለው? ተጠያቂ የሚሆነውን ወገንስ እንዴትና በምን መስፈርት ነው መለየት የሚቻለው? ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጡ መልሶች በራሳቸው አከራካሪ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ሌላው አንቀጽ 6 (f) ላይ በማያሻማ መልኩ እንደተመለከተው ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ የትህነግን ታጣቂዎች ቀላል መሳሪያዎችን ጨምሮ ሁሉንም አይነት ትጥቅ የማስፈታት ስራውን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል ይላል፡፡ ይህም በጣም ጠቃሚ ድንጋጌ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትህነግ ምን ያህል የታጠቀ ሀይል እንዳለውና የትኛውስ ወገን ነው የትህነግ ታጣቂ ሀይል የሚለውን ለይቶ ለማወቅ የተለየ ስልት መከተልን የሚጠይቅ ነውና ይህም ሁኔታ በራሱ ሌላ ከባድ ሀላፊነትን ይዞ ይመጣል፡፡ 

በሌላ አነጋገር ቢያንስ ባለፉት 40 አመታት በአጠቃላይና ባለፉት 30 አመታት ደግሞ በተለይ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ከሞላ ጎደል ትጥቅ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ እናም ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ታጣቂ ሀይል ወደየቤቱ ተመልሶ መሳሪያውን ቢደብቅና የሲቪል ልብሱን በመልበስ ሰላማዊ ሰው መስሎ ብቅ ቢል እንዴት ነው ለይቶ ማወቅ የሚቻለው? ይህንን “ወርቃማ ዕድል” ትህነግም በደንብ እንደሚጠቀምበት ምንም አያጠራጥርም፣ በዛ ላይ አንዳንድ ሞኝ ወይም የሰላም ስምምነት ሀሳቡ በደንብ ያልገባቸው አልያም ሆን ብለው የትግራይን ህዝባና ደጋፊዎቻቸውን ለማደናገር የሚሞክሩ የትግራይ ልሂቃንና ደጋፊዎቻቸው የጠረደቡትን መንገድ ሲገልጹ ትንሽ እንኳ ሀፍረት የላቸውም፡፡ ይህንን የማደናገሪ ሀሳባቸውን ቅጥረኛ ፈረንጆች እንደሆኑ የሚታወቁት እነ ማርቲን ፕላውት (Martin Pluat)፣ ሸትል ትሮንቮል (Kjetil Tronvoll)፣ ዊሊያም ዳቪሰን (William Davison)፣ አሌክስ ዲ ዋል (Alex de Waal)፣ ሬኔ ሌፎርት (Rene Lefort)፣ ኬኔት ሮዝ (Kennet Roth), ባሽር ሀሺይስፍ (Bashir Hashiysf) እና ሌሎችም ትህነግ ትጥቅ ይፍታ ተባለ እንጂ የትግራይ መከላከያ ሀይል (Tigray Defence Force (TDF) ትጥቅ ይፈታል አልተባለምና ይኸ ሀይል የትግራይ ህዝብ መድህን ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ 

እነዚህ ወገኖች የዘነጉት ነገር ቢኖር በስምምነቱ አንቀጽ 6 (a) ላይ The Parties Agree and recognize that the Federal Democratic Republic of Ethiopia has only one defense force; የሚል አስገዳጅ ድንጋጌ በስምምነት ሰነዱ ውስጥ ማስፈራቸውን ነው፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ አንድ ብቻ የመከላከያ ሀይል እንደሚኖራት ሁለቱም ወገኖች ተስማምተው ፈርመዋልና የትግራይ መከላከያ ሀይል የሚባል ታጣቂ ቡድን ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል አይሆንም፡፡ ለነገሩ አጉል ጉንጭ ማልፋት ስለሚሆን ነው እንጂ ይኸ ሀይል ከትህነግ ውጭ ራሱን ችሎ እንዲቀጥል የሚያደርጉት የህልውና መሰረቶች አሉት ወይ የሚል ጥያቄ በማንሳት መሞገት ይቻል ይሆናል፡፡ በዛ ላይ መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የፌዴራል ደህንነት ወደ ትግራይ ገብተው ህግ የማስከበር ስራቸውን እንደሚያከናውኑም በስምምነቱ ላይ ተቀምጧል፡፡ 

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ሁሉንም የትግራይ ሀይሎች የሚያሳትፍ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋምና ህግና ስርአት ማስከበርን ጨምሮ የእለት ከዕለት የመንግስት ተግባራትን እንደሚያከናውን ተሰምሮበታል፡፡ የፌዴራል መንግስት የቅርብ ክትትልና ድጋፍም አይለየውም፡፡ ታዲያ እነዚህ ወገኖች የትግራይ መከላከያ ሀይል (TDF) የሚሉት ገዳይ ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር ሆኖ እንዲቀጥል ፈልገው ይሆን ይህንን ትርጉም የለሽ ሀሳብ የሚያራምዱት? እረ እባካችሁ አታስቁን በሏቸው፣ አባቶቻችን እንዲህ ያለ ግራ የገባው ነገር ሲያጋጥማቸው “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” በማለት ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡ በአንቀጽ 7 (d) ላይ ደግሞ ትህነግ ወታደር እንዳይመለምል፣ እንዳያሰለጥን፣ እንዳያሰማራ፣ የማነሳሳት ስራ እንዳይሰራ ወይም ግጭትና አለመግባባትን ለመፍጠር እዳይዘጋጅ  የሚያደርግ አስገዳጅ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ 

ይኸ ስምምነት መልካም ሀሳብ ይዞ እንደመጣ ይታመናል፣ ይሁን እንጂ ትህነግ ይህንን መልካም የሆነ የስምምነት ሰነድ ያከብረዋል ወይ? ጊዜ አግኝቶ ራሱን ካደራጀ በኋላ እንደለመደው የትግራይን ህዝብ በአጠቃላይና ባለፉት 40 አመታት በአምሳያው የቀረጸውን የትግራይ ወጣት ደግሞ በተለይ በቀላሉ አነሳስቶ የራሱ የሆነ የታጠቀ ሀይል እንዲኖረው ለማድረግ እንደማይሞክር ወይም እንደማይሰራ ምን ዋስትና አለ ለሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል፡፡ በመጨረሻም በአንቀጽ 10 (4) ላይ የተቀመጠው የተቀበረ ቦንብ እንዴት ነው ጉዳት ሳያደርስ የሚተነፍሰው እና በሚፈለገው መልኩ ሊተረጎም ብሎም ሊተገበር የሚችለው የሚለው ጉዳይ ብዙዎቹን እያነጋገር እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡ ይኸ ንዑስ አንቀጽ ሁለቱም ወገኖች አጨቃጫቂ/አከራካሪ የሆኑ አካባቢዎችን በህገ መንግስቱ መሰረት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ይላል፡፡ 

ይኸ ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት በዚህ ሀሳብ ዙሪያ ጉዳዩ በቀጥታ ያገባናል፣ ያሳበናልም የሚሉ ሰዎች ወይም ወገኖች ምን ይላሉ? እንዴትስ ተረድተውታል? በሚለው ላይ ትንሽ ነገር ልበል፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ ቀላል ቁጥር የሌላቸው የአማራ ልሂቃን ደስተኞች አይደሉም፣ እንዳውም አንዳንዶቹማ በዚህም ምክንያት ትህነግ ከዚህ የሰላም ስምምነት ይበልጥ ተጠቃሚ ሆኗል እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ ይህም የሆነው የአማራን ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቁ ተደራዳሪዎች ስላልተወከሉ ለጥያቄው በህገ መንግስቱ መሰረት መልስ ይሰጠው የሚለውን የመፍትሄ ሀሳብ እንዳለ ስለተቀበሉ ነው ይላሉ፡፡ በእነዚህ ወገኖች እምነት ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር፣ አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራን ሕዝብ አይወክሉም፡፡ ለዛም ነው በስምምት ሰነዱ ላይ የእነዚህ አከራካሪ አካባቢዎች ጉዳይ ተነስቶ ለአማራ ሕዝብ በሚጠቅም መልኩ እንዲወሰን ያልተደረገው በማለት ይሟገታሉ፡፡ 

ይኸ ሙግት እስከምን ድረስ ሊወስድ ይችላል የሚለው ጥያቄ ግን በሚገባ ሊነሳና ሊመከርበት ይገባል፡፡ በተቃራኒው የትግራይ ልሂቃን ትጥቅ ማስፈታት በሚለው የስምምነት ሀሳብ ላይ በእጅጉ ቢበሳጩና ቢከፉም አጨቃጫቂ/አከራካሪ አካባቢዎች በህገ መንግስቱ መሰረት መፍትሄ ይሰጣቸዋል የሚለው ድንጋጌ ከሁሉም በላይ ለእነሱ እንደሚጠቅም አድርገው በመረዳታቸው ደስተኞች መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ አጨቃጫቂ/አከራካሪ የሚባሉት አካባቢዎች ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የእነዚህ አካባቢዎች ልሂቃን ደግሞ ከበርካታ አመታት (ለውጥ ከመምጣቱ) በፊት ጀምሮ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አንስተው መታገላቸውና ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ጥያቄያቸውን ለቀድሞው የትግራይ ክልል ምክር ቤት አቅርበው በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ምላሽ በማጣታቸው የይግባኝ አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው መታየት ጀምሯል፡፡ ይህም የሆነው ትህነግ ህገ መንግስቱን አክብሮ ለእነዚህ አካባቢ ሕዝቦች ጥያቄ መልስ ባለመስጠቱ ነው፡፡ እናም በህገ መንግስቱ መሰረት ችግሩ በዘላቂነት ይፈታ ሲባል ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሰራበት የነበረና በትህነግ እምቢተኝነት ተንጠልጥሎ የቆየ ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ትህነግ ህገ መንግስቱን አክብሮ ይሰራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስቱ እስካልተለወጠ ወይም እስካልተከለሰ ድረስ ከእነ ችግሩም ቢሆን ከህገ መንግስታዊ ስርአቱ ውጭ ሆኖ የአንድ አካባቢ ሕዝብ ችግሮች ይፈታሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡ 

ህገ መንግስቱ በፖለቲካ ሀይሎችና በሚመለከታቸው አካላት መካከል በሚደረስ ስምምነት መሰረት እንዲሁም የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ እስከሚለወጥ ወይም እስከሚከለስ ድረስ ጉዳዩ ተንጠልጥሎ ይቆይ ማለት ደግሞ ፍጹም ሀላፊነት የጎደለውና አላዋቂነትን የሚያስተናግድ ብሎም ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የሚውል አቋም ከመሆን ውጭ ውሀ የሚያነሳ ሀሳብ ሊሆን አይችልም፡፡ እናም አሁን ባለው ሁኔታ በተጀመረው መልኩ ቀጥሎ ጥያቄው እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ እና በህገ መንግስቱ መሰረት ችግሩ ይፈታ ሲባልስ ምን ማለት ነው? ጉዳዩ እንዴት ነው ሊታይ የሚችለው በሚለው ጥያቄ ላይም የተለያዩ ሀሳቦች ሲራመዱ ይስተዋላሉ፡፡ አንደኛው የሕዝቡን ስሜትና ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰን ይችላል የሚለው ነው፡፡ እውነት ነው ይኸ ሀሳብ ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 48 ጋር የሚስማማ/የሚጣጣም ነው፡፡ 

ምክንያቱም የዚህ ድንጋጌ መሰረተ ሀሳብ በክልሎች መካከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ሲነሳ ክልሎቹ ተነጋግረው እንዲፈቱት ዕድል ይሰጣል፣ ይኸ የማይቻል ከሆነ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል ስለሚል ይህንን አማራጭ መከተል ለጊዜው አዋጭ ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች ከየብሔረሰቡ የሚመጡና አማራን በአጠቃላይ እና የአማራን ፖለቲካ በተለይ በጥርጣሬ አይን እንዲመለከቱ ተደርገው የተቃኙ ሰዎች ስለሆኑ ይህን የመፍትሄ ሀሳብ በቀላሉ ሊቀበሉት እንደማይችሉ አስቀድሞ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በዛ ላይ የአንዳንዶቹ ክልል ተወካዮች እዚህ ላይ በዝርዝር መግለጽ በማልፈልገው ምክንያት የራሳቸው የሆነ ስጋት ያለባቸው መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ ሁለተኛውና ከእስካሁኑ ልምድ ተነስተን ስንመለከተው አይቀሬ የሚሆነው የመፍትሄ ሀሳብ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ወይም ማደራጀት የሚለው ነው፡፡ ይኸ አማራጭ ለሁሉም የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት ለመወሰን የሚመችና ጊዜም የሚወስድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ 

ይህም ሆኖ ይኸ የመፍትሄ አማራጭ ሀሳብ እንዴት ሊተገበር ይችላል? የሚለውን ጥያቄ በሁለት ከፍለን ብንመለከተው ይሻላል፡፡ አንደኛው ራያና ጠለምት ላይ ትህነግ የሰፈራ ፕሮግራም ስላላካሄደባቸው የነባሩ ሕዝብ ቁጥር ይበዛልና ሕዝበ ውሳኔ ቢካሄድ የሚያሰጋ ጉዳይ አይደለም የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው የወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ ሕዝብ በትህነግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች አፈና፣ ግድያና በግፍ የማፈናቀል ተግባር ሳቢያ የነባሩ ሕዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ (ከአንድ አመት በፊት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም የብልጽግና ጽ/ቤት ሀላፊ በነበሩበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ላይ በወልቃይት-ጠገዴ አካባቢ ብቻ ከ500,0000 ሕዝብ በላይ እንደተፈናቀለ ገልጸዋል) በተቃራኒው ከትግራይ አካባቢ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ህዝብ መጥቶ በእነዚህ አካባቢዎች በመስፈሩ ምክንያት ሕዝበ ውሳኔ ቢካሄድ የነባሩ ሕዝብ ጥያቄ ሊመለስ ይችላልን የሚለው ስጋት ነው፡፡ 

እዚህ ላይ አከራካሪ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም፣ ለምን ቢባል የትግራይ ልሂቃን የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ቦታቸው ከተመለሱ በኋላ እነሱ በሚሳተፉበት ሁኔታ ህዝበ ውሳኔው ይካሄድ ይላሉ፡፡ በተቃራኒው የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ እና ሕዝብ እንዲሁም ሌላኛው የአማራ ልሂቅ ደግሞ ይኸማ ሊሆን አይችልም የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ማቅረባቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም የተሻለ መፍትሄ የሚሆነው በሕዝበ ውሳኔው ወቅት ድምጽ መስጠት ያለበት ጥያቄ ያነሳው ነባር ሕዝብ እንጂ ምንም አይነት የማንነት ጥያቄ የሌለው ሰፋሪ (እኔ ትግራዋይ ነኝ የሚል የህብረተሰብ ክፍል) መሆን አይገባውም የሚለው ሀሳብ ቢተገበር ነው፡፡ እርግጥ ነው በአንድ አካባቢ ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የማያሳትፍ ሊሆን አይገባውም የሚል ወገን መኖሩ አይቀርም፡፡ 

ነገር ግን ጉዳዩ ከማንነት ጋር የሚያያዝ እስከሆነ ድረስ ይህንን የማንነት ሁኔታ መወሰን ያለባቸው የጥያቄው ባለቤቶችና ጥያቄውን በማንሳት ምላሽ በሚጠብቁት የህብረተሰብ ክፍሎች እንጂ የማንነት ጥያቄ የሌላቸው ነዋሪዎች ሊሆኑ አይገባም የሚለውን መርህ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል በዋነኛነትም በአርሲ፣ በወለጋ፣ በጅማና በኢሊባቡር አስተዳደር ዞኖች ውስጥ የሚገኙ አማሮች በኦሮሞ ጉዳይ ላይ በሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ እንዲሰጡ ይደረግ እንደማለት ነው፡፡  

ስለሆነም ቢያስ በሰፈራ መልክ የመጡትን የትግራይ ተወላጆች በህዝበ ውሳኔው ላይ ድምጽ እንዳይሰጡ ለማድረግ ሲባል ከ1984 ዓ.ም በፊት የትግራይ ተወላጆችንም ጨምሮ በወልቃይት-ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ ውስጥ የነበረው ሕዝብና ልጆቹ ለአካባቢዎቹ እንደነባር ሕዝብ ተቆጥረው በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ እንዲሰጡ ቢደረግ ይበልጥ ፍትሀዊ ይሆናል የሚል ግምት መያዝ ተገቢ ይመስላል፡፡ ከዛም አልፎ እነዚህ አከራካሪ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኙ ድረስ በማን ስር ሊቆዩ ይገባል የሚለው ሀሳብም ሌላኛው አከራካሪ ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ በ2013 ዓ.ም አካባቢዎቹ ከትግራይ ታጣቂ ሀይሎች ነጻ እንደወጡ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ በነበሩት አቶ አደም ፋራህ አስተባባሪነት የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ወደ አካባቢዎቹ በመሄድ ሕዝቡን አነጋግረው ነበር፡፡ 

በዚህም የአካባቢዎቹ (ወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ጨምሮ፣ ጠለምት እና ራያ) ነዋሪዎች ከአሁን በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ለመመለስ ማሰብ የማይሆንና በፍጹም የማይታሰብ ነገር ነው፣ ከማለት አልፈው አንዳንዶቹ የእድሜ ባለጸጋ አዛውንቶች ሳይቀሩ እንኳን ወደ ትግራይ ክልል ለመመለስ ፊታችንን ወደ እነሱ አዙረን መተኛት አንፈልግም እስከማለት ደርሰው እንደነበረም ይታወቃል (በነገራችን ላይ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እንደ አንድ የራያ ተወላጅ አላማጣ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በአካል ተገኝቶ የሕዝቡን ሀሳብና አስተያየት ማዳመጡን እንዲሁም ትክክለኛ ስሜቱንም መመልከቱን ማስታወስ ይፈልጋል)፡፡ ይህንንም እውነታ ታሳቢ በማድረግ የብልጽግና ከፍተኛ አመራር የሕዝቡ ጥያቄ ዘላቂ መልስ እስኪሰጠው ድረስ አካባቢዎቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ ይቆዩ የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ አሁንም ቢሆን ይኸ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ፖለቲካዊ ሁኔታ መኖሩ አይቀርም፡፡  

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,856FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here