spot_img
Saturday, September 30, 2023
Homeነፃ አስተያየትየትህነግ ነገር፡ ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ እየሆነ ነው!

የትህነግ ነገር፡ ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ እየሆነ ነው!

advertisement
TPLF _ የትህነግ ነገር

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) 
ህዳር 13/2015 ዓ.ም

ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱም ወገኖች የጦር አዘዦች በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ተገናኝተው የትግራይ ታጣቂዎች እንዴትና በምን ሁኔታ ትጥቃቸውን ይፍቱ በሚለው ሀሳብ ላይ ተወያይተው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ይህም መግለጫ አዲስ የሰላም ውይይት ወይም ድርድር ውጤት ሳይሆን የሰላም ስምምነቱን ለመተገብር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ልብ በሉ ይኸ መግለጫ ፕሪቶሪያ ላይ የተደረገውን ስምምነት ለመፈጸም ያላቸውን ዝግጁነት በድጋሜ ያረጋገጡበት እንጂ አዲስ የስምምነት ሰነድ ሆኖ የሚቀርብ አስገዳጅ ስምምነት አይደለም፡፡

ነገር ግን ይህ መግለጫ ቀደም ሲል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ሰነድ የሚያዳብር፣ ይበልጥ ዘርዘር አድርጎ የሚያሳይና የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ሀሳቦችን ይዞ ሊመጣ ይችል እንደሆነ እንጂ በዋናው የስምምነት ሰነድ ላይ ከተቀመጠው ውጭ አዲስ ሀሳብና ግዴታ ሊጥል በሚችል መልኩ መዘጋጀት የለበትም፡፡ መርሁ ይኸ ሆኖ ሳለ በዚህ መግለጫ ላይ አንድ አዲስ ነገር ተካቶ ተመልክተናል፣ ይህም የትግራይ ታጣቂ ሀይሎች ከባድ መሳሪያቸውን ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚያስረክቡበት እና የውጭ ሀይሎችን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊት አካል ያልሆኑት አካላት ከትግራይ የሚወጡበት ጊዜ ተመሳሳይ (Concurrent) ይሆናል የሚለው ሀሳብ ነው፡፡ 

በዚህም የመንግስት ተደራዳሪዎች ትልቅ ስሀተት ሲፈጽሙ የትህነግ መሪዎች ደግሞ ጥሩ የሆነ የማጓተቻ ሰበብ አግኝተዋል፡፡ ከዛም አልፎ ያን ያህል ቦታ አልሰጠነውም ነበር እንጂ ቀደም ሲል በዋናው የስምምነት ሰነድ ላይ የፌዴራል መንግስት ተደራዳሪዎች አንድ መሰረታዊ ስህተት ፈጽመው እንደነበር ተመልክተናል፡፡ ይህም የሰላም ንግግሩ የተካሄደውም ሆነ የስምምነት ሰነዱ የተፈረመው ከትግራይ ክልል መንግስት በተላኩ ሰዎች መሆኑን የዶ/ር ደብረጺዮን ደብዳቤ በግልጽ አመላክቶ እያለ በትህነግ ተወካዮች እንደተፈረመና የትህነግ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ይፈታሉ የሚል ዐረፍተ ነገር መጠቀማቸው በራሱ ለአፈጻጸሙ መጓተት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ 

ለምን ቢባል ትህነግ በተፈጥሮው የሀሳብ ልዩነቶችንም ሆነ የሚያጋጥሙ ፖለቲካዊ ችግሮችን በሀይል እንጂ በድርድርና በሰለጠነ አኳኋን ፈትቶ አያውቅም ነበርና አሁንም ምክንያት እየፈለገ አፈጻጸሙን ማጓተቱን ስራየ ብሎ ተያይዞታል፡፡ በዚህ ረገድ ትህነግ በታሪኩ የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ፈትቶ እንደማያውቅ እንደ ጥሩ ማሳያ ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ትህነግ ግንባር ገድሊ ሀርነት ትግራይ (ግገሀት) ከተባለው ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚፈልግ ፊት ካሳየ በኋላ በቀጠሮው ዕለት ሠራዊቱን በማሰማራት የግገሀትን አመራሮችና ታጣቂዎች ማስጨፍጨፉ ነው፡፡ 

ሁለተኛው ትግራይ ውስጥ የነበረውን የኢሕአፓ ሠራዊት በአጠቃላይና አሲምባ የነበረውን ሀይል ደግሞ በተለይ ጦርነት ከፍቶ ከጫወታ ውጭ እንዳደረገው ይታወቃል፡፡ ሦስተኛው በዋነኛነት በምዕራብ ትግራይ አርሶ አደሮች ይደገፍ የነበረውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) እንዲሁ በሀይል ለማስወገድ የምዕራብ ትግራይ (በዋነኛነት የሽሬ አውራጃ) አርሶ አደሮችን መጨፍጨፉም አይዘነጋም፡፡ ጠራናፊት ይባል የነበረውን የፖለቲካ ቡድንም በተመሳሳይ አኳኋን በጦርነት ወግቶ ከትግራይ እንዲወጣ ማድረጉም ይታወቀሳል፣ ለአስራ ሰባት አመታት ከደርግ መንግስት ጋር ያካሄደው ጦርነትም ሌላኛው ማሳያ ነው፡፡ ከዛም አልፎ ለምስረታው መፋጠንም ሆነ ለወታደራዊ ጥንካሬው ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገለትን ሸአብያ እንዲሁም በ1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት የከባድ መሳሪያ ምድቡን ያጠናከረለትን የሸአብያ ሰራዊት ለማጥፋት በሀገር ልኣላዊነት መደፈር ስም ስንት ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን እንዳስጨረሰ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ 

እንዲህም ሆኖ የወታደራዊ የበላይነት በያዘበት ሁኔታ ልክ እንደተሸናፊ ቡድን መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አልጀሪያ ድረስ በመሄድ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እጅ ለእጅ ሲጨባበጥ ይሽኮረመምና አንገቱን ይደፋ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም አሁንም ቢሆን የሰላም ስምምነት ሰነዱን የፈረመው ከመሞት መሰንበት ይሻላል ብሎ በተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ስለነበረ የሰላም ስምምነት ሀሳቡን በተቀመጠበት ሁኔታ ለመተግበር መቸገሩ አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል ትህነግ በአሁኑ ወቅት በሁለት ችግሮች ተወጥሮ የተያዘ ድርጅት ነው፡፡ 

አንደኛው በወታደራዊ ሀይል ተሸንፎ እንጂ አምኖበትና በሙሉ ፈቃደኝነት ውስጥ ሆኖ የሰላም ስምምነቱን ስላልፈረመው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አባላቱና ደጋፊዎቹ እንዴት ይኸ ሊሆን ይችላል ብለው ወጥረው ስለያዙት ምክንያት እየፈለገ ማጓተትን ይመርጣል፡፡ ለዚህም ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርሁት የመንግስት ተደራዳሪዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለትህነግ ጥሩ ዱላ አቀብለውታል፡፡ ይህም ማለት በአንድ በኩል ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በስምምነት ሰነዱ ላይ ትህነግና የትህነግ ታጣቂዎች የሚለውን ዐረፍተ ነገር መዞ አይ ይኸ ስህተት ነው እኔ መቼ ወኪል ላክሁ የሚል መግለጫ በማውጣት ለማደናገር ጥረት አደረገ፡፡ 

በሌላ በኩል በመርህ ደረጃ የሰላም ስምምነቱን ተቀብየ ለተግባራዊነቱም እሰራለሁ እያለ ነገር ግን ናይሮቢ ላይ የተጨመረውን ቅድመ ሁኔታ በማንሳት ታጣቂዎቼ ትጥቃቸውን ሊፈቱ የሚችሉት የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ተስፋፊዎች ከትግራይ መሬት ሲወጡ ነው የሚለውን አቋሙን ከፍ አድርጎ በማንሳት ላይ ይገኛል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ከፌዴራል መንግስት ተደራዳሪዎች መካከል የሕግ ባለሞያዎች እያሉ የእነዚህን ሀሳቦች አንድምታ ሳይገምቱ መቅረታቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው በወቅቱ ሁኔታቸው አሳሳች ሊሆን ይችላል፣ ለምን ቢባል አንደኛ ነገር ራሳቸው የትግራይ ተደራዳሪዎች የስምምነት ሰነዱ ትህነግና የትህነግ ታጣቂዎች ተብሎ ሲጻፍ አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ በመሆን አልፈውታል፡፡ 

ሁለተኛው ነገር የትግራይ ታጣቂዎችም ሆኑ ትህነግ እንዲሁም የትግራይ ክልል መንግስት ሊለያዩ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች አይደሉም እንዴ የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላልና፡፡ ይህም ሆኖ አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አለ፣ ይኸውም ትህነግም ሆነ የትግራይ ክልል መንግስት ሁለቱም ህገ ወጦች ናቸው፡፡ ትህነግ ከፓርቲነት የተሰረዘ ባቻ ሳይሆን በአሸባሪነት የተፈረጀ ድርጅት በመሆኑ ህልውና እንዳለው ድርጅት ተደርጎ አይቆጠርም፣ የትግራይ መንግስትም ባካሄደው ህገ ወጥ ምርጫ ምክንያት በፌዴሬሽን ምከር ቤት ዕውቅና ተነፍጎታል፡፡

ስለሆነም በዚህ የሰላም ስምምነት ላይ ትህነግም ተደራደረ የትግራይ ክልል መንግስት ያው አቅማዳ ቀልቀሎ ለቆታ ይሆን ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣው ለውጥ አለ ብየ አላምንም፡፡ ሆኖም ትህነግ ሰበብ እንዲያገኝ ዕድል የተሰጠው በመሆኑ አንድ ጊዜ የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት የእኔ ተወካዮች ሳይሆኑ የትግራይ ክልል ተወካዮች ናቸው በማለት ሌላ ጊዜ ደግሞ ታጣቂዎቼ ትጥቃቸውን የሚፈቱት የኤርትራና የአማራ ተስፋፊ ሀይሎች ከትግራይ መሬት ሲወጡ ነው እያለ እንዲያደናግር ምክንያት እንደሆነው አያጠራጥርም፡፡ ያም ሆነ ይህ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” እንደሚባለው የሚሻለው አሁንም በቃል ተገኝቶ የሰላም ስምነት ሰነዱን አክብሮ ለመፈጸም መዘጋጀት ነው፡፡ ለነገሩ ምንስ ምርጫ ይኖረዋል፣ መልካሙ ነገር በህገ ወጥ መንገድ የተመረጠው የትግራይ ክልል ም/ቤት ከትላንት ወዲያ ህዳር 11/2015 ዓ.ም የመጨረሻ ስብሰባውን አድርጎ የሰላም ስምምነቱን ተቀብሎታል፡፡ 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,705FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here