spot_img
Saturday, April 20, 2024
Homeነፃ አስተያየትየዘፈን ዳርዳርታው እስክስታ ነው! (ሲሳይ መንግሥቴ ዶ/ር) 

የዘፈን ዳርዳርታው እስክስታ ነው! (ሲሳይ መንግሥቴ ዶ/ር) 

ዳርዳርታው እስክስታ

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) 

መቼም የትህነግ ሰዎች ነገር ሁልጊዜም ግራ እያጋባ መቀጠሉ የተለመደ ሆኗል፣ ቀደም ሲል የነበራቸውን በማምታታትና በሸፍጥ የታጀበ ነውረኛ ድርጊታቸውን እንተወውና ከጥቅምት 23/2015 ዓ.ም ወዲህ እያደረጉት ያለውን ሸፍጥና የበዛ ማምታታት በጥቂቱም ቢሆን በመፈተሽ ለአንባቢያን ማድረስ ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ቆማጣን በጊዜ ቆማጣ መሆኑን ካልነገሩት በየቦታው እየገባ ለመፈትፈት ይሞክራልና፡፡ በዚህም መሰረት የሦስት አጋጣሚዎችን ክስተቶች ላንሳና እነዚህ ሰዎች አሁንም ከስህተታቸው ለመማር ዝግጁ አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ለሰላም ስምምነት ሰነዱ ታማኝ እንዳልሆኑም ጭምር ለማሳየት ልሞክር፡፡

የመጀመሪያው ጉዳይ ሰሞኑን የትግራይ ታጣቂዎች አዛዥ የሆነው ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የተዋጊዎቹን ትጥቅ መፍታት ሒደት አስመልክቶ በድምጽ ወያነ ቴሌቪዥን ማብራሪያ ባቀረበበት ወቅት ከተሰጠው ተግባርና ሀላፊነት አለፍ ብሎ የታችኛው የትግራይ አስተዳደር መዋቅር መፈረስ አይኖርበትም፣ ባለበት ነው መቀጠል ያለበት የሚል ሀሳብ አቅርቧል፡፡ ይኸ እንግዲህ እንዲሁ የተባለ ሳይሆን ከነ ደብረጺዮን ጋር ሲነጋገር የተሰጠው ፍንጭ መሆኑ ይመስላል፣ ሆኖም እሱ የታጣቂዎች አዛዥ እንጂ የሲቪል አስተዳደሩ አካል አይደለምና በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አልነበረበት፡፡ በሌላ አነጋገር ስለሲቪል አስተዳደሩ ህልውናም ሆነ መፍረስ የሱ ጉዳይ አይደለም፡፡ 

ይሁን እንጂ እሱም ቀደም ሲል ጀምሮ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትህነግ) ዋና ግርፍ ስሆነ በማያገባው ገብቶ ሲዘባርቅ ተመልክተነዋል፡፡ ደጉ ነገር ታጣቂዎቹን ትጥቅ እንደሚያስፈታ ማረጋገጡ ነው፡፡ ሁለተኛው ሸፍጥ የተካሄደው ደግሞ ባለፈው እሁድ ህዳር 11/2015 ዓ.ም የተካሄደው የትግራይ ክልል ምከር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ሲሆን ለግማሽ ቀን ያህል በተካሄደው ጉባኤ የቀረበው ብቸኛ አጀንዳ የሰላም ንግግሩና የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚለው ሀሳብ እንደነበር የባይቶና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ኪዳነ አመነ ከአንድ የትግርኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ገልጧል፡፡ በነገራችን ላይ ኪዳነ አመነና ፓርቲው ከትህነግ የባሱ ጽንፈኞች፣ ትግራይ ነጻ አገር መሆን አለበት የሚሉ፣ ሌላው ቀርቶ በዚህ ህገ ወጥ ምክር ቤት አማካኝነት የትግራይ ሰራዊት በአዋጅ ይቋቋም ብሎ ሀሳብ ያቀረቡ መሆናቸውን በኩራት እየነገሩን ያሉ ናቸው፡፡

በዚህም ከዋና ተደራዳሪዎቹ በተጨማሪ የቴክኒክ ኮሚቴና የአማካሪ ምክር ቤት የሚባሉ ሁለት ተጨማሪ አካላትን አቋቁመው ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ ከዛም አልፈው በህዝብ የተመረጠ ምክር ቤት እንዴት ይፍረስ ይባላል የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውንም ሰምተናል፡፡ የአገራችን ሰው እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥመው ወደሽን ቆማጢት ንጉስ ትመርቂ በማለት የፈጠረበትን ግርምት ይገልጻል፡፡ አሳዛኙ ነገር ይኸ የምክር ስብሰባም የመጨረሻቸው እንደሆነ የተነገራቸውም አይመስልም፣ ይልቁንም እንደሚቀጥልና ተግባርና ሀላፊነቱንም እየተወጣ እንደሚቆይ ተደርጎ እንደተቃኘ ከውሳኔያቸው መረዳት ይቻላል፡፡ 

እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፣ አንዳኛው የባይቶናው የአባይ ትግራይ አቀንቃኝ ኪዳነ አመነም በቃለምልልሱ ላይ እንዳረጋገጠው አስፈጻሚው አካ ይኸን ምክር ቤት ጭምር በደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት ላይ ህገ ወጥ እንደሆነ አምኖ በመቀበል ከፈረመ በኋላ እንደ ህጋዊ አካል በመቁጠር ሰብስቦ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ምክር ቤቱ ስልጣን የሌለው መሆኑ እየጣወቀ ያቋቋማቸው የቴክኒክ ኮሚቴና የአማካሪ ምክር ቤት ተግባርና ሀላፊነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ለምን ቢባል ከጥቂት ቀናት በኋላ የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን መፍታት ይጀምራሉ፣ ምክር ቤቱን ጨምሮ ህገ ወጡ የትግራይ አስተዳደርም ይፈርስና በፌዴራል መንግስቱ በሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ይተካል፡፡ ይህ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ተግባርና ሀላፊነት የሚወሰነውም በፌዴራል መንግስቱ ይሆናል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከላይ እንደገለጽሁት ምክር ቤቱም ሆነ አሁን ላይ በህገ ወጡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የተቋቋሙት አካላትም ይፈርሳሉ፡፡ ይህንን እውነት ታሳቢ ስናደርግ አይደለም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የተቋቋሙት ህገ ወጥ አካላት ይቅርና ባለፉት ሁለት አመታት ተቋቁመው የነበሩት የክልሉ መንግስት ልዩ ልዩ አካላት ፈርሰው በአዲስ መልኩ እንዲደራጁ ወይም እንደአስፈላጊነታቸው እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡ 

ታዲያ እውነታው ይኸ ከሆነ ለምን ይሆን ህገ ወጡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የዚህ አይነት የጅል ስራ የሰራው? ሌላኛው አስቂኝ ነገር የዚህ ምክር ቤት አባላት ይኸ ምክር ቤት ሳያውቅ ተደራዳሪዎችን ማን ነው የወከላቸው ብለው ሲጠይቁ ምላሹ የትህነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ (ፖሊት ቢሮ) ነዋ የሚል ሆኖ እያለና ምክር ቤቱም የትህነግ ስብስብ መሆኑን ረስቶ የክልሉ ከፍተኛ ስልጣን የዚህ ምክር ቤት ሆኖ ሳለ ለምን በሌላ አካል ተወከሉ የሚል አስተያየት የመስጠቱ ሁኔታ ነው፡፡ አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣ ትልቅ ችሎታ ነው፣ እንደሚባለው የምክር ቤቱ አባላት አንድም አቅማቸውን አላወቅም አሊያም ለማስመሰል እየሞከሩ ነው፡፡ 

የሚገርመው ነገር ግን ትህነግ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተወክለው የሄዱት ተደራዳሪዎች በትግራይ ክልል መንግስት ነው የጠወከሉት የሚል መግለጫ ባወጣ ማግስት ለምክር ቤቱ በህወሀት ፖሊት ቢሮ (ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) ነው የተወከሉት ሲል ማረጋገጡ ነው፡፡ ሦስተኛው ሸፍጥ ጌታቸው ረዳ ትላንት ከቢቢሲ ቴሌቪዥን የሀርድቶክ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ስቴፋን ሳከር ጋር ባደረገው ቃለ መልልስ ደቡብ አፍሪካ በፈረማችሁት የሰላም ስምምነት ሰነድ መርሆ መሰረት አሁን ላይ የትህነግ ሀይል ትጥቁን መፍታት ይጠበቅበታል፣ ለመሆኑ ይኸ ስራ ተጀምሯልን ሲል ላቀረበለት ጥያቄ አይ ገና ነው፣ ቅድመ ሁኔታዎችን ግን እየሰራን ነው የሚል መልስ ከመስጠቱ በፊት በትህነግ ተወካዮች የሚለው ትንሽ ተለጥጧል፣ ቅጥያው ያን ያህል የሚያሳስብ ባይሆንም ስምምነቱ የተፈረመው በትግራይ መንግስት ተወካዮች አማካኝነት ነው በማለት ለማምታታት ሞክሯል፡፡ 

ልብ በሉ ይኸ ሰውየ የሰላም ንግግሩና የስምምነት ሰነዱ ዋነኛ ተደራዳሪና ፈራሚ መሆኑ ይታወቃል፣ ተወክሎ የሄደውም በትህነግ ፖሊት ቢሮ (ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) ውሳኔ አማካኝነት መሆኑን ከላይ እንደገለጽሁት የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት ጠይቀው ሰብሳቢው በሰጡት መልስ አማካኝነት አረጋግጠውላቸዋል፡፡ በዛ ላይ በትህነግና በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ተብሎ ሲጻፍ የለም እኛን የወከለን የትግራይ ክልል መንግስት እንጂ ትህነግ አይደለም ማለት የነበረበት እዛው ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ሆኖ ሳለ ወደ ትግራይ ከተመለሰ በኋላ እንዴት እንዲህ አይነት የጅል ስራ ትሰራላችሁ ተብለው ሲዋከቡ በየአጋጣሚው ለማስተባበል መሞከር አንድም አላዋቂነት ሁለትም ሸፍጠኝነት የተጠናወተው ሀሳብ እየቀረበ እንደሆነ ይታመናል፡፡ 

ይህንንም በዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ፊርማ ተጽፎ በተሰጠውና በእጁ ይዞት በሄደው እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረትም በተላከው ደብዳቤ አማካኝነት ማረጋገጥ ይችል ነበር፣ ወይስ በጊዜው ጌችም ሆነች አባሎቿ በድንጋጤ ውስጥ ስለነበሩ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን በማጣታው ምክንያት ይህ እውነት አልተገለጠላቸውም ነበር? ሌላው ቀርቶ የትህነግ ተዋጊ ሀይል ትጥቅ ይፈታል ሲባል ምንም እንኳ ትህነግም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ህገ ወጥና አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ቢሆንም በሀገራችን ህግ የፖለቲካ ፓርቲ ታጣቂ ሀይል ሊኖረው አይችልም፣ የትግራይን ክልል መንግስት ህገ ወጥ ነው ብትሉትም መጻፍ ያለበት እውነታ ግን ይኸው ነው፣ ይህ የማይሆን ከሆነ በአፈጻጸሙ ላይ ችግር ሊገጥመን ይችላል በማለት መከራከር ነበረበት፡፡ ሌላው እዚህ ላይ ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጉዳይ ጌታቸው ረዳ በመገናኛ ብዙሀን ፊት ቀርቦ ስትጥቅ መፍታት ሲጠየቅ የትግራይ ህዝብ ደህንነት ዋስትና ሳያገኝና የኤርትራም ሆነ ሌሎች ሀይሎች ከትግራይ ሳይወጡ ትጥቅ ለመፍታት እንቸገራለን፣ በዚህም ምክንያት ትጥቅ የማስፈታቱ ሒደት ወራት አሊያም አመታት ሊወስድ ይችላል የሚለው ነገር ነው፡፡ 

ይኸ ሁኔታ የፌዴራል መንግስቱ ሀላፊነት መሆኑ በህገ መንግስቱ ላይ መቀመጡ ብቻ ሳይሆን ተዋዋይ ወገኖች በሰላም ስምምነት ሰነዱ አንቀጽ 8(1) ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዓለም አቀፍ ደንበሮች አካባቢዎች ሀይሉን ማሰማራት እንዳለበት አስቀምጠዋል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይም ይህንኑ ሀሳብ አጠናክሮ ያስቀመጠበት ሁኔታ እንዳለም ተመልክተናል፡፡ እናም ድሮም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ደንህነት ሊጠበቅ የሚችለው በትህነግ ታጣቂዎች ሳይሆን በፌዴራል መንግስት የመከላከያ ሠራዊት እንደሆነ አንድም ተስማምቶ ፈርሟል፣ ሁለትም አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የትግራይ አካባቢዎችና ህዝብ በፌዴራል መከላከያ ሀይሎች ቁጥጥር ስር በዋለበት ሁኔታ ስለየትኛው የትግራይ ህዝብ ደህንነት ነው ጌች የሚቀባጥረው?  

ለማንኛውም እንደመውጫ ይሆነን ዘንድ እግረ መንግዴን አንድ ነገር አንስቼ ትንሽ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፣ ይኸውም ቀደም ባለው ጽሁፌ ላይ አጽንዖት ሰጥቼ ለመግለጽ እንደሞከርሁትና መሆንም ያልነበረበት ተግባር መሆኑን እንደገለጽሁት የፌዴራል መንግስት ተደራዳሪዎችም ሆኑ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪዎች የፈጠሩት ስሁት አካሄድ የመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም እንዴት ትህነግ ራሱ ህገ ወጥና አሸባሪ ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈረጀና ከህጋዊ ፓርቲነትም የተሰረዘ ህገ ወጥ ቡድን ሆኖ እያለ ጌታቸው ረዳ ቀደም ሲል ከቢቢሲ ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደነገረን ከሆነ የትግራይ መንግስት የሚለውን አንቀበልም፣ ስለሆነም ስምምነቱ ከትህነግ ጋር ተብሎ መጻፍ አለበት የሚለውን አመክንዮ ያቀርባሉ? 

በጥቅሉ የእኛ አገር ፖለቲከኞች አመለካከትና ተግባር አስተውሎትና ብስለት የጎደለው፣ የሁኔታዎችን አንድምታ የማይረዳ፣ አርቆ ማሰብ የማይችልና እንደ …. አጫጅ የፊት የፊቱን ብቻ የሚመለከት መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ከላይ በአጭሩ ለመግለጽ እንደሞከርሁት የትህነግ ሰዎችም ሆኑ የፌዴራል መንግስት ተደራዳሪዎች ተግባር የሚያሳየውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ እንደዛ ባይሆንም ኖሮ በክልሉ መንግስት ተወክለው መሄዳቸውን የሚያሳይ ደብዳቤ ይዘው በተገኙበት ሁኔታ ተወካዮቹን የለም የትግራይ ክልል መንግስትን ሳይሆን የምትደራደሩትና የምትፈርሙት ትህነግን በመወከል ይሆናል የሚል አቋም ይዘው የዚህ አይነት ስህተት አይፈጽሙም ነበር፡፡ 

በአጠቃላይም ሲታይ የትህነግ ሰዎች የሰላም ስምምነቱ በመፈረሙ ለጊዜው እፎይታ ቢሰማቸውምና ህልውናቸውን ቢያስቀጥሉም፣ የአክራሪ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ጠንካራ ግፊትና በውስጣቸው የሚገኘው የአልሸነፍ ባይነት ትዕቢት ወጥሮ ስለሚይዛቸው የመገናኛ ብዙሀን አማራጭ ባገኙ ቁጥር አለመሸነፋቸውን ለማሳየት በዋናው የስምምነት ሰነድ ላይ የሌለ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጡ ጭምር ራሳቸውን ለማታለል ይሞክራሉ፡፡ 

የፌዴራል መንግስት ዝምታም ይህንን እንዲሉ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ብዙ ከማውራት ይልቅ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” የሚለውን አባባል በድጋሜ እንዲያስታውሱ አበክረን እንመክራለን፡፡     

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here