ህዳር 20 2015 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በትኅነግ መካከል ድርድር ተካሂዶ ስምምነት ላይ መደረሱና ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ለጊዜውም ቢሆን መቆሙ፣ ለሕዝባችን እፎይታ ስላስገኘ በመሰረቱ የሚደገፍ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ጉዳዩ በቅርብ የሚመለከተው የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የራያ ሕዝብ በስምምነቱ፣ በተለይም በትህነግ መሳሪያ ማውረድና በአንድ አገር አንድ መከላከያ ብቻ መባሉ አስደስቶታል። የቀረውን ደግሞ ከጀርባው ምን ይኖረው ይሆን ብሎ በጥያቄና በጥርጣሬ ቢያየውም ለስምምነቱ ዕድል ላለመንፈግ በዝምታው አልፎታል:: ከቀን ቀን ጥያቄው እና ጥርጣሬው እየጨመረ፣ በተደራዳሪዎች መካከልም አለመተማመን እየተነገረ፤ የትህነግን ታሪክ በማስታወስም፣ የስምምነቱ አሻሚ አንቀጾች እየተናነቀው ሲመጣ ጥርጣሬዎቹ ወደ ጥንቃቄና ‘ያልጠረጠረ ተመነጠረ’ ማደጉ ግድ እየሆነ መጥቷል።
ታዛቢውና ታጋሹ የኢትዮጵያ ሕዝብ የትህነግን ምንነትና ማንነት ከማንም የበለጠ ጠንቅቆ ያውቃል። ከጅምሩ ከትኅነግ ጋር ድርድር አልተዋጠለትም። የአማራው ሕዝብ በተለይም ከ40 ዓመታት በላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈጸመበት ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ስለትኅነግ የሚያውቀው ታሪክ፣ ዘር ማጥፋት፣ ስበአዊ መብት መግፈፍ፣ ተንኮል፣ ክህደት፣ ውሸት፣ ሴራ፣ ለሌላው ሕዝብ ንቀት፣ … ነው። ያለፉትን ሁለት ዓመታትን እንኳ ብንወስድ በአማራና በአፋር ሕዝቦች ላይ የፈጸመው ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የኢኮኖሚ ውድመት፣ በሕዝቦች መካከል በታሪካችን ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ ጥላቻ መዝራትና፣ ከባዕዳን ጋር አብሮ አገርን መውጋት፣ ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ‘እንጦሮጦስ ድረስ እንወርዳለን’ እስከማለት መድረስ፣ ቆምንለት የሚሉትን የትግራይን ወጣት በመቶ ሺዎች ማስፈጀት ነው። ይህ ሰለባ የሆነው ሕዝብ
በጦርነት የተሸነፈው ትኅነግ በሰራው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆንና ካሳ እንዲከፍል፤ የተፈናቀለውና በስደት ላይ የሚገኘው ወገኑ መንግሥታዊ እርዳታ አግኝቶ ወደ ቀዬው እንዲመለስ መደረግን ከስምምነቱ ይጠብቃል።
ይህ ድርጅት በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ክህደት ተከትሎ የአማራና የአፋር ሕዝብ ከኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች ጋር ተጣምሮ ትኅነግን በጉልበት ከተወሰዱ የአማራና የአፋር ክልሎች ማስወጣት ችሏል። በተለይ የወልቃይት የጠገዴ እና የጠለምት ሕዝብ ብዙ መስዋእትነትን ከፍሏል። ልዩ ኃይሉ፣ ፋኖና (ፋኖ ማለት ሕዝቡ ነው)፣ ሚሊሺያው ከመከላከያ ሃይላችን ጋር በመሆን ተዋድቋል። በጦርነት ያልተካፈለ፣ በጦርነቱ ያልሞተበት፣ ያልቆሰለበት፣ ንብረቱ ያልወደመበትና ያልተፈናቀለ ቤተሰብ አለ ብለን አናምንም። የመጀመሪያውን የትኅነግ ጥቃት በቅራቅር (ጠገዴ) የቀለበሰና በየግንባሮቹ ለማንነቱ የተዋደቀ ሕዝብ ነው። ከ40 ዓመታት ሰቆቃና ትግል በኋላ ያገኘህውን ነፃነት ታጣለህ ብሎ የሚፈርድ ዳኛ አለ ብለን አናምንም። በወረራ ሕዝብ ተጨፍጭፎ የተወሰደ መሬትና ንብረት ወደ ባለቤቱ መመለሱን እውቅና መስጠት እንጅ ሕዝበ-ውሳኔ እያለ ለዳግም ወረራ ማዘጋጀት ኢትዮጵያን ለሌላ የባሰ የጦርነት መከራ መዳረግ ነው። ይህ ጥያቄ በዋናነት የፍትህና የማንነት ጥያቄ ነው።
ያለ ሕገ መንግሥትም ይሁን በሕገ መንግሥቱ ትህነግ ክልሎችን ሲፈጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ እንዲሰጥ አልተጠየቀም፤ ድምጽም አልሰጠም። በህዝበ-ውሳኔ የተከለለ ክልልም የለም። ትኅነግ ለራሱ የሚወስደውን ወስዶ፣ የቀረውን እንደመሰለው ሰጥቶ፣ የተረፈውን አማራ ክልል አለው። ትኅነግ የፈጠረው ሕግና ሕገ መንግሥት አሁን ላለንበት ጦርነትና ቀውስ አብቅቶናል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት አሻሚ በሆነ መልክ ያስቀመጣቸው አንቀጾች (ለምሳሌ አንቀጽ 5 ውስጥ የፌደራል መንግሥቱ የተፈናቀሉና የተሰደዱ እንዲመለሱ አሳልጦ ይሰራል የሚለው፤ እንዲሁም አንቀጽ 10 ላይ ሁለቱ ተደራዳሪዎች አወዛጋቢ የሆኑ ቦታዎችን በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንዲፈታ ያደርጋሉ የሚለው፤ በተጨማሪ በናይሮቢው ስምምነት ላይ በቁጥር 2 ውስጥ የትጥቅ ማስፈታቱ ሂደት ከ ’ውጭ ሃይሎች’ እና ‘የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያልሆኑ ሃይሎች’ ከአካባቢው መውጣት ጋር ተያይዞ መቅረቡ ከዋናው የስምምነት መንፈስ በራቀ መንሸራተትን ያሳየ አንቀጽ በመሆኑ አሳሳቢ ሆኖ አግኝተነዋል። ከባርነት ወደ ነፃነት የተሻገረውን የወልቃይት፣ የጠገዴ.፣ የጠለምትና የራያ ሕዝብ ወደ ባርነት የሚመልስ ማንኛውም አሻሚ አንቀጽ ተስተካክሎ በማያሻማ ሁኒታ ካልተቀመጠ ወደ ባሰ ችግር እንዳይወስደን ማሳሰብ እንወዳለን።
ዛሬ በተቃውሞ የቆመውን ያህል ሕዝብ ባልነበረበት ጊዜ 30 ዓመት ሙሉ ያለምንም ድጋፍ የታገለ ሕዝብ ነው። ከዚያም በታሪክ ወደኋላ እንውሰዳችሁ፤ በ 1964 ዓ.ም (እ ኢ አ) የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ መንግሥት ለሱዳን መሬት ሊሰጥ ነው ሲባል በፓርላማ ጥያቄውን በማንሳት፣ ሕዝባዊ ንቅናቄም በማስነሳትና ትጥቅ ትግል በመጀመር የተዋጋው የጎንደር ክፍለ አገር ብቻ ነበር። ስለነዚህ አካባቢዎች መወስን የሚችሉት የነዚህ አካባቢዎች ተወላጆች ብቻ ናቸው። ‘ከእንግዴህ ወዲህ ይህን አገር መልሰን አናገኘውም’ ብለው አማራን ጨፍጭፈው ወደ ሱዳን የሸሹ ሳምሪዎችና ወንጀል ሰርተው ወደ ትግራይ ያመለጡ ወንጀሎች በነዚህ ቦታዎች ላይ ምንም ዓይነት ድምጽ አይኖራቸውም። ቢመለሱ በነፍስ አጥፊነትና በንብረት አውዳሚነት ተጠያቂ ናቸው። ፍርዳቸውንም ያገኛሉ። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ የሆነው የትህነግ አመራርም ለፍርድ መቅረብ አለበት።
የትህነግ አመራር አንድን ሕዝብ አጥፍተህ መሬት መውሰድ ይቻላል ብሎ የመነና ለመተግበርም የሞከረ ድርጅት ነው። ዛሬ ይህን ሃቅ አለባብሰን ብናልፍ ወደፊት ብዙ ትህነጎች እንዲፈጠሩ መንገድ መክፈትና እኩይነትን ማንገስ ነው። ከትህነግ ውድቀት ሁሉም ትምህርት መውሰድ አለበት። ምንም እንኳ መደራደርም መስማማትም ያለ ቢሆን፣ የቆምንባቸውን መሰረታዊ መርሆችን ማናጋት ወደፊት የበለጠ ችግሮችን ይዘው ይመጣሉ ብለን ስለምናምን ስምምነቶች ከዘላቂ መፍትሄ ጋር ይታዩ እንላለን።
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ