spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትጽንፈኛ ኦሮሞዎችና የጋረጡት አደጋ። (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ጽንፈኛ ኦሮሞዎችና የጋረጡት አደጋ። (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

Tibebe _ Radical Oromos

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ኅዳር 30 2015

“ኢትዮጵያን ሲወድ ኖሮ፤ ኢትዮጵያን ሲወድ ሞተ” ሳሙኤል ፈረንጅ

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም. በቶሮንቶ ካናዳ በሚታተም ጋዜጣ፤ አባቴ በመቃብርህ ላይ ምን ተብሎ እንዲፃፍ ትፈልጋለህ ሲባል፤ የሰጠው ምላሽ ነው ከላይ በጥቅስ ያስቀመጥኩት። የጣሊያን ጦርነት አርበኛ የነበሩት የወለጋው ባላባት አያቴ፤ በግዛታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ሲያስገነቡ፤ የቤተ ከርስቲያኒቱ ግቢ በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቃ እንደነበር፤ የቅርብ ዘመዶቼ አውግተውኛል። እንደ አያቴ፤ አባቴ፤ እንዲሁም እንደ ዶክተር ለማ ጉያ፤ ፀጋዬ ገብረመድኅን፤ ለማ ጉተማ፤ ለዑልሰገድ ኩምሳ፤ ጃጋማ ኬሎ፤ ጥላሁን ገሠሠ እንዲሁም በቅርቡ ሃውልታቸው በአዲስ አበባ የተተክለውን የጀግናውን የአብዲሳ አጋ፤ ዓይነት የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን፤ ሳስብ፤ አሁን ባለው የኦሮምያ ክልልና የአዲስ አበባ ከተማ ሁኔታ፤ እንዲሁም በጽንፈኛ ኦሮሞ ፖለቲከኞች፤ ምን ያህል ያዝኑ፤ ምን ያህልስ ልባቸው ይሰበር ይሆን፤ ብዬ ከእራሴ ጋር እሟገታለሁ። እነዚህ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን፤ በአንድም ወቅት ኦሮሞነታቸው ከኢትዮጵያዊነታቸው በልጦባቸው አያውቅም። ዛሬ ግን በሚያሳዝንና በሚያሳፍር መልኩ፤ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ፤ መንደራቸው፤ ጎሳቸውና፤ ብሔራቸው ከኢትዮጵያዊነት የበለጠባቸው ዜጎች፤ በተለያየ የሥልጣን እርከን ላይ መሆናቸው፤ ለኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ ወቅት እየሆነ መጥቷል። በተለይም “ኦሮሞ ይቅደም” በሚል ጭፍን ፈሊጥ የታመሙ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች፤ ለኦሮሞ ሕዝብ የማይመጥን፤ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር የሚያጋጭ፤ ከባሕሉና ከአቃፊነት እሴቱ ያፈነገጠ የፖለቲካ ቁማር ጠጠራቸውን በመወርወር፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያም ከፍተኛ አደጋ ጋርጠዋል። ይህንን አደጋ ለመረዳት፤ ወረድ ብሎ ሕዝቡን ማየትና የሕዝቡን የልብ ትርታም ማዳመጥ ያስፈልጋል። የጽንፈኛ ኦሮሞዎችን አደገኛ አጀንዳ መታገል “ኦሮሞ ጠልነት” እንደሆነ ተደርጎ በተለያዩ ባለሥልጣናት የሚነገረው ማሸማቀቅያም አንድም የፖለቲካ ሸፍጥ ነው፤ ወይም የችግሩን ክብደት ካለመረዳት የሚመጣ የሃሳብ ድርቀት የሚመነጭ ነው።

ከ15 ዓመታት በኋላ ተመልሼ ያየኋት ኢትዮጵያ፤ ብዙ ነገርን ተምሬባታለሁ። በልመና ከሚተዳደረው እስከ ቱጃሩ ድረስ አነጋግሬባታለሁ። ከመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች፤ እስከ ጋዜጠኞች ድረስ ውይይት አድርጌባታለሁ። በነዚህ ሂደቶች፤ ብዙ ልብ የሚሰብር ያየሁበትን ያክል፤ ተስፋ ሰጪና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነገርንም አይቻለሁ። ከአሥራ አምስት አመታት በፊት ኢትዮጵያ የሄድኩ ጊዜ በርካታ አካባቢዎች ለመሄድ በመቻሌ “ኢትዮጵያን አይቻለሁ” ለማለት ብችልም፤ በአሁኑ ጉዞዬ ግን፤ ከአዲስ አበባ መውጣት ባለመቻሉ፤ አዲስ አበባን አየሁ ማለት ይቀላል። አዲስ አበባ ግን የኢትዮጵያን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና፤ የማህበራዊ ኑሮን ሙቀት መለኪያ በመሆኑ፤ ቆይታችን አዲስ አበባ ብቻ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በርካታ ችግሮች፤ የተሰሩ ሥራዎችን፤ እንዲሁም የሃገራችንን ተስፋና ሥጋት በቅጡ መለካት የቻልንበት ጉዞ ነበር። በዚህም ጉዞዋችን የኦሮሞን የተረኝነት ስሜትና ጽንፈኛ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ላይ የጋረጡትን አደጋ በተጨባጭ ለማየትም ችለናል። የዚህ ጽሁፍ አላማም፤ በተለይም ኢትዮጵያዊነታቸው ከኦሮሞነታቸው የማይበልጥባቸው ዜጎች፤ ስብዕናቸው፤ ከብሔር በላይ የሆኑ ኢትዮጵያኖች ለእውነት በመቆም፤ እየተገፋ ላለው ሕዝብ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ደወል ለመደወልና፤ የሕዝቡን እውነተኛ ስሜትና የልብ ትርታን ማዳመጥ የተሳናቸው የመንግሥት ሹመኞች፤ ጊዜው ሳይረፍድ ጆሮዋቸውንና ዓይናቸውን እንዲከፍቱና አስቸኳይ፤ ለሃገርና ለሕዝብ የሚበጅ እርምት እንዲወስዱ ለማሳሰብም ጭምር ነው።  

በአዲስ አበባ ቆይታችን፤ የከተማዋን ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ የማናገር እድል አጋጥሞናል። ከወረዳ አስተዳዳሪ፤ እስከ አዲስ አበባ የተቋማት መምሪያ ኃላፊ ጋር ያደረግናቸው ውይይቶች፤ አይን ከፋች፤ ከመሆናቸውም ባሻገር ጥሩ የሕዝብ አገልጋይ ከሆኑ ሹመኞች ጀምሮ፤ በሥልጣናቸው እስከሚኮፈሱ “ባለሥልጣናት” ለማየትም ችለናል። “የኦሮሞ የተረኝነት ስሜት” ለመኖሩም የዓይንም የገቢርም ምስክር መሆን ይቻላል። በቅርቡ፤ አቶ ነዓምን ዘለቀ የአዲስ አበባ የኢሳት “ሞጋች” የተሰኘው መርሃ ግብር ላይ ቀርበው “ተረኝነት” የሚባለው የውሸት ትርከት ነው ማለታቸው አስገርሞኛል። እሳቸው ሰራሁት ባሉት ቀመር፤ በሥልጣን ላይ ያሉት ኦሮሞዎች፤ ከሌላው አይበልጡም ብለውናል። አቶ ነዓምን የሳቱት ዋና ነጥብ ግን፤ “ተረኝነቱን” የሚያሳየው፤ የኦሮሞ ባለሥልጣኖች የቁጥር መብዛት ሳይሆን፤ በሥልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ በአንዳንድ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ኦሮሞዎች፤ ለሁሉም ዜጋ እኩል የሆነ አገልግሎት አለመስጠታቸውና፤ አንድ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ተገልጋዮች ደግሞ “የኦሮሞ ዝርያ” ስላላቸው ብቻ፤ ከሌላው የተለየ አገልግሎትና ጥቅም ለማግኘት የሚሄዱበት “ሕገ ወጥ” ወይም ደንብ አልባ ድርጊት ነው። የተረኝነት ስሜቱ፤ በመንግሥት የተነደፈ ፖሊሲ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር ባይኖርም፤ ይህንን የተረኝነት ስሜትና አድሎዋዊ አሰራር ግን በሕግ ለማገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ፤ “ኦሮሞነት” የተለየ ጥቅም የሚያሰጥ (privileged) ተደርጎ ለመወሰዱ ብዥታ የሚፈጥር ነገር የለም።

ከዚህ በተጨማሪም፤ የተለያዩ የመንግሥት የስራ ተቋራጭ (ኮንትራት) በትውውቅ፤ በሃገር ልጅነትና በዝምድና፤ የሚሰጡ ለመሆናቸው የመንግሥት ኮንትራት የወሰዱ ኩባንያዎችን በመፈተሽ፤ በቂ መረጃ ማግኘት ይቻላል። ይህ የተረኝነት ስሜት እና፤ በዜጎችቻችን ላይ የፈጠረው የሥነ ልቦና ጫና አደባባይ የወጣና ሕዝብን ያማረረ መሆኑን ለመረዳት፤ ወረድ ብሎ ሕዝቡን ማናገር ይጠይቃል። የሃገርን ልጅ ወይም የመንደርን ሰው መጥቀምና መጠቃቀም፤ ከሰው ልጅ አምሳያውን ከመጥቀም ጋር የተያያዝ “ባሕልና እሴት” ቢሆንም፤ በሃገር ሊፈጥር ከሚችለው ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦና ቀውስ አንፃር፤ መንግሥት በአስቸኳይ፤ የሕግ መአቀፍ ሊያበጅለትና፤ ዜጎች አገልግሎት ለማግኘትም ይሁን፤ በሥራ እንዲሁም በተለያዩ አገልግሎት በሚያገኙባቸው ቦታዎች ማንኛውም ዓይነት የዘር አድልዎ ማድረግ ተቀባይነት እንደሌለው ሊያስረግጥና፤ የሕግም ከለላ ሊያበጅለት ይገባል።

ይህን የተረኝነት ስሜት በቃ የሚል መንግሥት ባለመኖሩ፤ ከዚህ የተረኝነት ስሜት፤ የተነሱ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች ዛሬ በኦሮምያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎቻችን ያለምንም ርህራሄ በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛሉ። “ጊዜው የኦሮሞ ነው” በሚል የጨነገፈ ድንክዬ እሳቤም ነው፤ በተለይ፤ አማራው ሕዝባችን ከኦሮምያ ለቆ እንዲወጣ በግፍ የሚታደነው። ከዚህም የደከመ እሳቤ ነው፤ ዛሬ በአዲስ አበባ ት/ቤቶች፤ የኦሮምያ “ባንዲራ” ካልሰቀላችሁ፤ “የኦሮምያ ሕዝብ መዝሙር” ካልዘመራችሁ በሚል፤ “ኦሮሞነትን በግድ በሕዝብ ጉሮሮ ውስጥ ለመሰንቀር መንተጋተጉ የቀጠለው። ይህ ሁሉ ሲሆን፤ ከንቲባ አዳነች አቢቤ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጽንፈኞችን ከማውገዝ ይልቅ፤ በመንታ ምላስ፤ ከጽንፈኞች ጋር ለሞዳሞድ መምከራችው፤ መንግሥታቸው ጽንፈኞችን ለመጋፈጥ ቁርጠኝነት የጎደለው መሆኑን ያሳብቃል።

 የጠቅላይ ሚኒስትሩም አደንቋሪ ዝምታ፤ ምናልባትም በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ የተሰገሰጉ ጽንፈኛ ኦሮሞዎችን “ላለማስቀየም” ይሆን ብዬም ለመጠየቅ እገደዳለሁ። በተደጋጋሚ ከባለሥልጣናት እንደሚነገረው፤ ኦሮምያ ውስጥ ለሚፈፀመው ጭፍጨፋ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ጭምር አሉበት። ይህን የሚነግሩን ባለሥልጣናት ግን ከጨፍጫፊዎቹ ጋር የሚተባበሩትን ባለሥልጣናት፤ ነጥሎ ለመለየትና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ለምን ተሳናቸው? “ተስፋ አንቆርጥም፤ ሪባን ግን እንቆርጣለን” የሚለው የወርቅ ቅብ ብሂል ዋጋና ክብደት ሊኖረው የሚችለው ጠቅላይ ምኒስትሩ፤ በጽንፈኛ ኦሮሞዎች የሚፈፀመውን ጭፍጨፋ በአደባባይ ሲያወግዙና፤ ይህን ጭፍጨፋ ለማስቆም መንግሥታቸው ምን እንዳቀደ አቅጣጫ ሲያስቀምጡ አይደለምን? ጠቅላይ ምኒስትሩ፤ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምረው፤ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች የመንግሥትን ሥልጣን በመቆጣጠር፤ “ኢትዮጵያን በኦሮምያ” አምሳል ለመቅረጽ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ለዚህም ዓላማቸው፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ ተባባሪ ባለመሆናቸው ነው “አብይ ነፍጠኛ” የሚለውን ታርጋ ለጠቅላይ ምኒስትሩ የለጠፉት።

“ኦሮም ይቅደም” በሚል መርህ ከጥቂት ዓመታት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ የተጀመረው የጽንፈኛ ኦሮሞዎች የመጀመሪያ እርምጃ፤ ዛሬ አድጎና አብቦ፤ ኦሮምያን የደም መሬት አድርጓታል። እነዚህ ምናልባትም ከ5% ያነሱ ጽንፈኞች፤ የኦሮሞን ባሕልና እሴት የማይወክሉ፤ ለሌላው ኦሮሞ ሃፍረት የሆኑ፤ ኅፃናትንና ሴትችን በመግደላቸው የሚኩራሩ፤ እራሳቸውን ከባርነት አስተሳሰብ ያልፈቱ፤ የአሰተሳሰብ ድኩማኖች፤ እንኳን ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ ይቅርና፤ የእራሳቸውን ሕይወት እንኳን በቅጡ መምራት የማይችሉ፤ አረመኔዎች ለመሆናቸው ከሥራቸው የበለጠ ምንም ምስክር ሊኖር አይችልም። የኦሮሞ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በሰላም እና በፍቅር ተሳስሮ መኖር የሚፈልግ ሕዝብ ነው። አውሮፓና አሜሪካ ሆነው ገንዘብ እና የፕሮፖጋንዳ ሽፋን በመስጠት፤ በሃሰት ትርከት የተጠመቁ የድሃ ገበሬን ልጆች የሚያስፈጁትን ጽንፈኛ ኦሮሞዎች በጽኑ ልንታገል ይገባል። የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮምያ ክልል መስተዳደር፤ በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት የማይወጣ ከሆነ፤ የተቃዋሚ ድርጅቶች፤ ሕዝብን በማስተባበር የተለያዩ ሰላማዊ አመጾችን በመጠቀምና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የፌደራሉም ሆነ የክልል መስተዳደሩ ኃላፊነትና ግዴታውን እንዲወጣ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል። የኦሮሞ አባገዳዎች፤ የተለያዩ እምነቶች አባቶችና፤ የሃገር ሽማግሌዎች፤ ከምንግዜውም የበለጠ ዛሬ፤ የተሳሳተ የሃሰት ትርከት ተግተው የንፁሃን ዜጎችን በማፍሰስ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን፤ ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ይኖርባቸዋል። 

እኔ በግሌ በአቶ ሽመልስ አብዲሳም ሆነ በጨፌ ኦሮምያ ምንም ተስፋም ሆነ እምነት የለኝም። በአንድም ወቅት ጨፌው የንፁሃን ሞት ተሰምቶት የክልል መስተዳድር ፕሬዝዳንቱንም ሆነ የፀጥታ ሃላፊዎቹን፤ ስለንፁሃን ሞት፤ ግድያውን ለማስቆም የተሰራ ሥራም ሆነ የተቀመጠ አቅጣጫ ካለ፤ የጠየቀበት ወቅት የለም። ሥራቸውን ያልሰሩ ባለሥልጣናትም ከሃላፊነት እንዲነሱም ሆነ በሕግ መጠየቅ ያለባቸውንም በሕግ እንዲጠየቁ ያደረገበት ወቅት የለም። ጨፌው ከማጨብጨብ ውጭ ሌላ ሥራ የተሰጠው አይመስልም። ይህ ሁሉ እልቂት እያለ፤ የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናት ክልላቸው ውስጥ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ፤ የፌደራል መንግስቱም የንፁሃንን ዜጋ መጨፍጨፍ እንዳልሰማ በመሆን፤ ዛሬ ባለሥልጣናቱ በድግስ ውስኪ እየተራጩ ነው (ውስኪ የማይጠጡ ቢኖሩም)። ይህ የደርግን የአስረኛ የአብዮት በዓል ያስታውሰኛል። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠኔ እየተቆላ፤ ባለሥልጣናቱ ቅልጥ ያለ ድግስ ደግሰው በውስኪ ይራጩ ነበር። ይኽው ታሪክ ዛሬም እራሱን ደገመ። በአረመኔዎች ለተጨፈጨፉ ኅፃናት፤ አረጋውያንና ሴቶች፤ የኅሊና ፀሎት እንኳን ተነፍጓቸው፤ “ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች” በሚል መፈክር “የብሔር፤ ብሔረሰቦች በዓል ተከበረ”። ታዳሚው በጭብጨባ ተናጋሪውን አሰከረ እራሱም ሰከረ። ብዙዎቻችን ኢትዮጵያ እንድትበለፅግ እንፈልጋለን፤ ግን የኢትዮጵያ መበልፀግ፤ የኅፃናትን፤ የሴቶችንና የአዛውንቶችን የደም ግብር ይጠይቃል ወይ? በተለያዩ ሃገራት በሽብርተኞች፤ በጽንፈኞች፤ እንዲሁም ዓላማ የለሽ ስግብግብ አረመኔዎች፤ የንፁሃን ደም ይፈሳል። ግን ሁሉም ሃገራት በሚባል ደረጃ፤ መሪዎች ጨፍጫፊዎችን በማያሻማ ሁኔታ ያወግዛሉ፤ ሕዝባቸውን ያጽናናሉ፤ እንዲህ ዓይነት ጥቃት አድራሾች ላይ ለሚወሰደው እርምጃና ጥቃቱም እንዳይደገም ለማድረግ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለሕዝባቸው ተስፋ ይሰጣሉ። በትንሹ ይህ ከአንድ መሪ የሚጠበቅ ነው። በሃገረ ኢትዮጵያ ግን፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስከ ሃገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ተቋማት ጭፍጨፋ መኖሩን ያልሰሙ እስኪመስል ድረስ፤ የሕዝቡን እሮሮ፤ የኅፃናቱን ለቅሶ፤ የሴቱን ጩኸት፤ በአደንቋሪ ዝምታቸው አጅበው፤ ዛሬም “ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም” ይሉናል። 

ይህ ደግሞ ለጽንፈኛው ኦሮሞ የልብ ልብ በመስጠቱ፤ ሃገሪቱን አደጋ ላይ እየጣላት ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጓጓዝ ድፍረት እስኪጠፋ ድረስ፤ የዜጎች እንቅስቃሴ ተገድቧል። ኦነግ ሸኔ የተባለው የጽንፈኛ ኦሮሞዎች ጥርቅም፤ ከመንግሥት አቅም በላይ እንዴት ሊሆን ቻለ? ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንደጠቀስነው፤ ጥቃት የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ተለይተው ትኩረት የማይሰጣቸው ለምንድነው? በተደጋጋሚ እንደምንሰማው ከፍተኛ ጥቃት እየተፈፀመ ያለው በምእራብ እና በምሥራቅ ወለጋ ነው። ቢያንስ በእነዚህ አካባቢዎች መደበኛ ሰራዊት ማስቀመጥ ያልተፈለገው ለምንድ ነው? ጽንፈኛ ኦሮሞዎች በሃገራችን ላይ የጋረጡት አደጋ ከባለሥልጣናት እውቅና ውጭ አለመሆኑ እስኪሰለቸን ተነግሮናል። ይህ አደጋ በኦሮምያ ክልል ብቻ ሳይሆን፤ በአዲስ አበባም እያንዣበበ ነው። በኦሮምያ ክልልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የጽንፈኛ ኦሮሞዎች አደጋ ግን መንግሥት ፊት ለፊት መጋፈጥ ያልፈለገው ለምንድነው? በሕዝብ የተመረጡት የፓርላማ አባላትስ ምን እየሰሩ ነው? አደጋው ፈጦ መጥቶ ሃገር በንጹሃን ደም እየታጠበ፤ መንግሥት ያንቀላፋበት ምክንያትስ ምንድ ነው?  እነዚህ ጥያቄዎች መልስ በአስቸኳይ ማግኘትና ጽንፈኛ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ላይ ለጋረጡት አደጋ፤ አስቸኳይ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ። 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here