
የሺወርቅ ወንድሜነህ
አሌፖ ላይ ሌት ተቀን ቦምብ በዘነበበት ወቅት፣ ያኔ የሶሪያዊቷ እናት ልጆቿን ፍለጋ የግምብ ፍርስራሽ መሀል ስትባዝን፤ ሀዘኗ በምድር የሚኖር የያንዳንዱ ወላጅ ሀዘን እንዲሆን እመኝ ነበር። አሌፖ ብቻ ሳትሆን የወደቀችው በጠቅላላው የሶሪያ ነባር ታሪክ ነበር የወደመው፣ ሕዝቧ ነበር የረገፈውና የተረፈውም ለስደት የተዳረገው። በበኩሌ የሶሪያ ሕዝብ ስቃይና ሀዘን ከሀዘኖቼ ሁሉ ጋር ተቀላቅሎ ዛሬም ድረስ ያመኛል። የአገሪቷ መውደም፣ የታሪኳ መጥፋትና የሕዝቧ ለእልቂትና ለስደት መዳረግ አንድ ቀን ብቻ ተሰምቶኝና አስቤው ያለፈ ዜና ሳይሆን እንደ ማስጠንቀቂያ ደወል ሌሊት ሌሊት እየጮኸ ከእንቅልፌ ሲያባንነኝ የኖረ ነው።
ከእልቂቱ፣ ከስደቱና ከጥፋቱ በፊት ሆይ ብሎ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ትዝ ይለኛል – ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለለውጥ የተነሳ እንቅስቃሴ! ዜናው በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ የሠርግና ምላሽ ፍንድቅያ ፈጥሮ ነበር። በድህረ-ገጾች አጠቃቀም የላቁ የትግል ቀስቃሾችና እንዲሁም የተቃዋሚ ኃይል መሪዎች የሆኑ ሁሉ በኩራት ወጥተው ስለድል መቃረብ የሚናገሩበት መቅጽበት ነበር። ብሎም በአለም ዙሪያ በጨቋኝ ሥርዐት ስር የሚማቅቁ ሕዝቦችን ሁሉ የሚቀሰቅስ ስሜት ነበር ያ ወቅት የፈጠረው። ታዲያ ያ ሁሉ የት ገባ? የት ደረሰ? ሶሪያ እንዴት በአይናችን ያየነው አስከፊ ጥፋት ውስጥ ልትወድቅ ቻለች? እንዴት ’ከድጡ ወደ ማጡ’ ልትገባ ቻለች? የመአከላዊ መንግሥቱን የጭቆና ስርዐት ሊታገልና ሊለውጥ የተነሳ ሕዝብ እንዴት በአክራሪዎች ሊጠለፍና ወደ እርስ-በርስ እልቂት ሊሸጋገር ቻለ? ለዲሞክራሲና ለፍትህ የተነሳ ንቅናቄ እንዴት ከታሪክ በወረሳቸው ቅራኔዎች ላይ በመመሥረት አንደኛው ሌላኛውን የመበቀልና የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ሊሰማራ ቻለ? የሶሪያ ሕዝብ ለምን ከአፍጋኒስታን፣ ከሶማሊያ፣ ከኢራቅ ሕዝቦች ላይማር ቻለ? የሶሪያ ጠላቶች እነማን ናቸው? ጠላቶች ካሏትስ በመውደሟ የሚያገኙት ጥቅም ምንድን ነው?
ከታሪክ ተምሮ ራሱን ሕዝቡንና አገሩን ከጥፋት ለማዳንና ብሎም አዲስ ታሪክ ለመሥራት የሚፈልግ ሁሉ ሊመለከታቸው የሚገባ ሌሎችም ተጨማሪ ተመክሮዎች አሉ። እኛ አፍሪካዊያን ልንዘነጋው የማይገባን ታሪክ አለ የጥቁር ሕዝብ ልጆች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶችና ወንድሞች ከአህጉራችን ከአፍሪካ እየታደኑና እየታፈኑ፤ በግር-ብረትና በሰንሰለት ታስረው እየተጫኑ ውቅያኖስ ተሻግረው በባርነት እንዲሸጡ ዋና እገዛ ያደረገው በመካከላቸው የነበረው በጎሳ ልዩነት ላይ የተመሠረተ ግጭት እንደነበረ የታሪክ መዝገቦች የሚያሳዩት ነው። በዚያ ክፍለ-ዘመን (14ኛው መቶ አካባቢ) በአፍሪካ ውስጥ ተንሰራርቶ የነበረው በጎሰኛ መሪዎች ይካሄድ የነበረው ፖለቲካ፤ የጥሬ ሃብትና የሰው ጉልበት ፍለጋ አለምን ያስሱ ለነበሩት የነጭ ተስፋፊዎች አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸው ነበር። አንደኛውን የጎሳ ንጉሥ በወዳጅነትና በአማካሪነት በመቅረብ፤ ጠመንጃና ጥይት በመለገስም ሆነ በመሸጥና እንዲሁም በተኩስ በማሰልጠን፤ በሌላው ጎሳ ላይ ጊዜያዊ ድል እንዲጎናጸፍ ያደርጉት ነበር። ከዚህ ሴራቸው በስተጀርባ ደግሞ የተሸናፊውን ጎሳ ልጆች እያፈኑ ሲወስዱ ’የተወዳጁት’ ንጉሥ እንዳላየ ይሆን ነበር፣ አንዳንዴም ያግዛቸው ነበር። የወዳጅ ተብየው አይቀሬ ተራ ሲደርስና የራሱ ጎሳ ልጆች እየተጠለፉ ለሽያጭ ሲላኩ ደግሞ፤ ’ብድር በምድር’ በማለት መጀመሪያ የተጠቃው ጎሳ በተራው የተመልካችነቱን ቦታ ይወስድ ነበር። በዚህ መልክ የተከሰተው ሁኔታ ነባር ቅራኔዎችን በማካረርና ግጭቶችን በማባባስ ሕዝቡን በሁሉም አቅጣጫ በማዳካም ለሽያጭና ለልዋጭ እንዲቀርብ አድርጎታል። ከዚያ ቀጥሎ ለተስፋፋው የአውሮፓዊያን ወረራና የቅኝ-አገዛዝ መንሰራራትም መሠረት ሊሆን ችሏል።
ዋናው ተጠያቂ መንግሥት ወይም ገዥ ቡድን ነው
ሲጠቃለል፤ በጎሳ ላይ የተመሠረቱና የተካረሩ ውስጣዊ የሕዝብ ቅራኔዎች እንደምሳሌ ላነሳሁት የሶሪያ ውድቀትም ሆነ ለአፍሪካ የ400 አመት የባርነትና የቅኝ-አገዛዝ ሥርአት በግብር ላይ መዋል ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ነገር ግን ለቅራኔዎች ባስከፊ መልክ መካረርና ሕዝብንና አገርን፣ ብሎም ክፍለ-አህጉርን ለጥቃትና ለጥፋት የመዳረግ ዋና ተጠያቂዎች የፖለቲካ አገዛዙን ወይም የጎሳ አመራሩን የጨበጡት ቡድኖች መሆናቸው አያጠራጥርም። ተጠያቂነታቸውን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፤
1. በሕዝብ መካከል መከፋፈልን የሚፈጥረው ራሱ የገዥዎች ጨቋኝ አገዛዛዝ/አስተዳደር ነው። ይሄም ደግሞ ሊወገድ የማይችል ከራሱ ከሥልጣን-አመጣጡ ጋር የተዋሃደ ባህሪ ነው። ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት ስርዐትና የሕግ የበላይነት ያልተረጋገጠባቸው ኅብረተሰቦች ሁሉ ውስጥ፤ ገዥዎች ሥልጣን የሚጨብጡት፤ በጥቅም-አጋሮች እየታገዙ በጉልበት
ራሳቸውን በመሾም፣ በውርስ ወይም በሰማያዊ ኃይል የተመረጥን ነን በማለት እንደሆነ የመንግሥታት ታሪክ በአለም ዙሪያ ይመሰክራል። በሶስቱም አይነት መንገድ የሚመጡ ገዥዎች ሰፊውን ሕዝብ የሚፈልጉት ለአገልጋይነት እንጅ ሊያገለግሉት፤ ሊጠቀሙበት እንጅ ሊጠቅሙት አይደለም። በእርግጥ አንዱ አምባገነን መሪ ከሌላው በባህሪ ሊለይ ይችላል፤ በአስተዳደር ስልቱና በመዋቅሩም እንደዚሁ። የአስተዳደር ፍልስፍናው ወይም ርዮተ-አለሙ ግን ሰብዓዊ ክብርንና ነጻነትን መአከላዊ እስካላደረገ ድረስ ከጭቆና ሊቆጠብ አይችልም። አምባገነን ስርዐቶች አላማቸውን ከግብ ለማድረስ በማስፈራራት፣ በማስገደድ፣ አወናባጅ ፕሮፓጋንዳን በመጠቀም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ከማጋጨት ወደኋላ አይሉም። ለአጥፊ ክፍፍል ሊዳርጉት እንደሚችሉ ቢያወቁም ኃላፊነት ግን አይወስዱም። አመራራቸው በግልና በቡድን ጥቅም ላይ የተመሠረተ፣ ብልህነትና አርቆ-አሳቢነት የሌለው፣ ጦረኛና ትምክህተኛ ነው። የዚህ አይነቶቹ ገዥዎች ሥልጣናቸው ጊዜያዊ እንደሆነ የብዙ መንግሥታት ታሪክ በአለም ዙሪያ ይመሰክራል፤ ጊዜያዊነቱ ግን በእርግጥ አንጻራዊ ነው። ብዙዎቹ ሕዝብንና አገርን ለዘመናት ለማዳከም የሚበቃ ረጅም የሥልጣን እድሜ ነው የሚኖሩት። የመላው አፍሪካ ታሪክ ይናገር።
2. ጨቋኞች ሲውድቁም በስርዐታቸው ሕዝብ ከአዲስ ጭቆና ራሱን መከላከል እንዳይችል አኮላሽተው ነው የሚወድቁት። ለብዙ ዘመናት በአምባገነናዊ ስርዐቶች ጭቆና ታፍኖ የኖረ ሕዝብ በቃኝ ብሎ ለአመጽ ሲነሳ አባርነት ከሚያሳዩት ጋር ሆኖ ጨቋኞችን መፈንቀል እንጅ ትኩረቱ፤ የተተኪዎችን ማንነት የመመዘኛ አቅምና ፋታ የለውም። በዚህ የተነሳም ትግሉ ተጠልፎበት ወደ አዲስ ጭቆና ሊሸጋገር እንደሚችል ብዙ ተመክሮዎች ያሳያሉ ። የሃሳብ ነጻነት የሌለበት ስርዐት ውስጥ ታፍኖ የሚኖር ሕዝብ የተለያዩ ፖለቲካ አስተሳሰቦችን በግልጽ ሰምቶ የመተቸት፣ የማወዳደር፣ የመሞከር ወይም የመፈተን ልምድን የሚያገኝበት ሁኔታ አይኖረውምና ለድጋሚ አምባገነናዊ ስርዐት የተጋለጠ ይሆናል። ሀብቱን፣ ንብረቱን፣ ጉልበቱን ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችም ቀላል መስዋዕት ይሆናል።
የተቃዋሚ ድርጅቶች ኃላፊነት
ሁልጊዜ ዋና ተጠያቂ መአከለኛ ስልጣን የጨበጠው ኃይል ይሁን እንጅ፤ የሕዝብን የለውጥ እንቅስቃሴ እንመራለን ብለው የሚነሱ ድርጅቶችም ከኃላፊነት ነጻ አይደሉም። የሕዝብን እንቅስቃሴ ወደ ፍሬያማ ግብ ለመምራት፤ ጨቋኝ ስርዐትን በመለወጥና መሪዎችን በማስወገድ መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ጠንቅቆ መገንዘብን ይጠይቃል፤ ይህ ደግሞ መሪ ድርጅቶች ፍልስፍናቸውን፣ ራዕያቸውንና መዋቅራቸውን እንዲመረምሩ ግዴታ ይጥልባቸዋል። ለውጥ ማምጣት ማለት መጭውን ጊዜ መቅረጽ፣ ለልጆቻችንና ለትውልዳቸው ካለፈውም ሆነ ከዛሬው የተሻለ መሠረት መጣል ማለት ነው፣ ይህ ደግም ያለፈውን ከመተቸትም ሆነ ያለውን ከመዋጋት የከበደ ኃላፊነት ነውና ከትምክህተኝነትና ከጀብደኝነት ስሜት ነጻ የሆነ ብልህ፣ ትሁትና አርቆ አሳቢ አመራርን ይጠይቃል።
ድርጅቶች ውስጣቸውን ለመመርመርና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በትክክል ለመወጣት ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመገመት እንዲችሉ መመለስ ከሚገባቸው ጥያቄዎች መሀል ጥቂቶቹን እንደምሳሌነት ከታች እሰነዝራለሁ፤
• ድርጅቱ የግለሰብን ሰብዓዊ ክቡርነት ለማረጋገጥና ለማስከበር ምን ያህል የጠና እምነትና ዝግጅት አለው?
• ድርጅቱና መሪዎቹ ለሕግ የበላይነት ተገዥ እንዲሆኑ የሚያረጋግጥ (ተግባራዊ የሚያደርግ) ቆራጥ ዝግጅት አላቸው ወይ?
• ማንኛውም ግለሰብ በጎሳ፣ በዘር፣ በሚከተለው ሃይማኖት ወይም እምነት፣ በቆዳው ቀለምና በመሳሰሉት ባህሪያት እንዲሁም ሰብዓዊ ነጻነቱን በመመርኮዝ ባደረጋቸው የግል የአኗኗር ምርጫዎች የተነሳ እንዳይጨቆን፤ ድርጅቱ ምን አይነት የጠና እምነትና ዝግጅት አለው?
• ድርጅቱ የራሱን ራዕይ ከሌሎች ድርጅቶች ራዕይ ምን ያህል አስበልጦ ያያል?
• ድርጅቱ የአባሎቹንም ሆነ የሌሎች ድርጅቶችን ትችት፣ ሂስና ሃሳብ በነጻና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመስማትና ራሱን ለመለወጥ ወይም አቅጣጫውን ለማስተካከል ምን ያህል ቆራጥና ዝግጁ ነው?
• ድርጅቱ የሚዘጋጀው ራሱን ከሌሎች ድርጅቶች መሀል ለሕዝብ ምርጫ ለማቅረብ ነው ወይስ ጨቋኞች ሲወገዱ የመሪነት ቦታውን በቀጥታ ለመውሰድ ነው?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽግግር፣ የጥቁር ሕዝብ አደራ
’ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣እኩልነት፣ሰብዓዊ ክብርናና ነጻነት፣ የሕግ የበላይነት’ በሚሉት መፈክሮች ሥር በኢትዮጵያ የተካሄደው የፖለቲካ ትግልና እንቅስቃሴ ግማሽ ምእተ- አመት ሊሞላው ነው። የመጀመሪያው፤ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 1974 የፈነዳው ’የየካቲት አብዮት’ በይዘቱም ሆነ በቅንብሩ እንዲሁም በተከፈለበት ዋጋ ሊዘነጋ የማይችል ታሪካዊ ቦታ አለው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻቸን ሕይወታቸውን ለሕዝባቸው፣ ለወገኖቻቸውና ለአገራቸው ፍቅር ሲሉ ሰውተዋል። በዚህ ታሪካችንም ላይ ብዙ የተለያዩ ስሜቶች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ቢኖሩም ማስገረም የለበትም። ይህን የምልበት ምክንያት ታሪክ (የቅርቡም የሩቁም) ከአወዛጋቢነት የማያመልጥ ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፤ አካላቸው ላይ ጠባሳ መንፈሳቸው ውስጥ የማይደርቅ ቁስል ይዘው የሚጓዙ በሕይወት የሚኖሩ ብዙ ወገኖች ስላሉ ነው። እነሱንና ትናንትናም ዛሬም በአዲስ ጥይት የሚወድቁትን ወገኖቻችንን የሚያስተሳስራቸው አንድ ፍላጎት ነው – የተሻለ ለውጥ ማምጣት!
ያለፉት ሁለት የለውጥ ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ሕዝብ ከትውልድ ትውልድ እየደማ፣ ለድል ቀን ሳይደርስ በድል ዋዜማ እየወደቀ እንዳይቀር፣ የቅርቡ ጊዜ ዋዜማ አገርና ሕዝብን የሚያሻግር እንዲሆን የማድረግ አደራ ነበረብን፤ የጠቅላላው የጥቁር ሕዝብ አደራ። ችሎታውም በእጃችን ነበር። የጥቁር ሕዝብ አደራ ስል ምን ማለቴ እንደሆነ እንድትረዱኝ ሃሳቤን ባጭሩ እንደሚከተለው ለመግለጽ እሞክራለሁ፤
ኤኮኖሚን በተመለከተ ምዕርባዊያንም ሆኑ ቻይናና መሰሎቿ የምግብ ማምረቻ መሬት፣ የጥሬ ሃብትም ሆነ የገበያ ቦታ በሰፊውና በግልጽ በመሻማት ላይ ከተሰማሩ ቆይተዋል። ለዚህ ሽሚያ ዋና ትኩረት የሚደረገው በመላው አፍሪካ ላይ ነው። ይሄም የሚካሄደው አንደኛውን ወገን ብቻ በሚጠቅሙና ፈጽሞ እኩልነትን ባልተመረኮዙ ስምምነቶች ላይ በተመሠረቱ ውሎች አማካኝነት ነው። ለምሳሌ ያህል ይሄ ሂደት ባገራችን በሰፊው የተከሰተና መፈናቀልንና የርስበርስ ግጭቶችን ያስከተለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከእኛ አገር አንስቶ በመላው አፍሪካ ውስጥ ያንሰራሩት የገዥ ስርዐቶች፤ የሚካሄደው መቀራመት በአገሮችና በሕዝቦችም ላይ ሆነ በመላው አህጉር ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት የሚገነዘቡ አይደሉም። (የብዝበዛ እንጅ የንግድ ተቃዋሚ አለመሆኔን አሳስባለሁ።)
በአለም ውስጥ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ በሄደበት፣ የተዛባ የሀብትና የእውቀት ስርጭት ጎልቶ በሚታይበት፣ የወታደራዊ ኃይል በጥቂት አገሮች እጅ በገነነበትና አዳዲስ አክራሪና የነጭ የበላይነትን የሚያንጸባርቁ መሪዎች ብቅ ብቅ በሚሉበት ወቅት በአፍሪካና በጥቁር ሕዝብ ላይ ከምንጊዜው የበለጠ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን ተገንዝቦ አለመንቃት፤ የአለምን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ የኃይል አሰላለፍ በተሻለ የመረዳት እድል አግኝቷል ተብሎ የሚገመተውን ትውልዳችንን የሚያሳፍር ውድቀት ነው።
ሰብዓዊ ክብርንና ደህንነትን በሚመለከት፤ ጥቁር ሰው ዛሬም በያለበት መጨቆኑ አልቀረም። በይዘቱ በስፋትና በጥልቀቱ ትንሽ ይለያይ እንጅ ዛሬም በቆዳው ቀለም ላይ በተመሠረተ ጭቆና ይጠቃል። እንደስደተኛም ሆነ እንደዜጋ በእኩልነት የማይታይበት ጊዜ ብዙ ነው፣ በሕግ ፊት ሁልጊዜ እኩል አይሆንም፣ በፍርደ ገምድሎች የመጠቃት አደጋው የበዛ ነው። በዚህም የተነሳ ሁልጊዜ ፈተና ላይ ይወድቃል። ሆኖም የጥቁር ልጆች በመላው አለም፣ በያሉበት ኅብረተሰብ የሚያስከብራቸውን ሥራ እየሰሩና አኩሪ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚኖሩ አብሮ መነገር አለበት። ከሌሎቹ ሕዝቦችም ጋር ተደባልቀውና ተዋልደው ይኖራሉ። ጥቁሩ እንደግለሰብነቱ እጣ ፈንታው የተለያየ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ሆኖም ግን እንደጥቁር ሕዝብ አዲስ ታሪክ መጻፍ ይገባናል። ከቀሩት ያለም ሕዝቦች ጋር በመተባበር እኩልነት፣ ሰብዓዊነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ለሁሉም የተረጋገጠበትና ሰላም የሰፈነበት አለም ለመፍጠር አስተዋጾ ለማድረግ መብቃት አለብን። ለዚህ የምንበቃው መጀመሪያ ራሳችንን ስናውቅና ስናከብር ነው። መጀመሪያ ከጨቋኝ ስርአቶች ስንላቀቅና ተመልስነም ምንጊዜም በጨቋኞች እጅ የማንወድቅበትን መሠረት ስንተክል ነው።
ታላቁን አደራ ምን በላው?
በ2009 (2016 በአውሮፓዊያን አቆጣጠር) በኢትዮጵያ ውስጥ የተነቃነቀው ትግል አዲስ ምእራፍ ሊከፍት የሚችል የድል ዋዜማ ነው የሚል ተስፋ በስፋት በሕዝቡ ዘንድ አሳድሮ ነበር። በጥርጣሬ ፈንጠር ብለው መመልከትን
የመረጡት እንኳን ሳይቀር ይሳካ ይሆን? የሚል ጉጉት አልተለያቸውም ነበር። ሳይውል ሳያድር፣ ‘ከዋዜማው ማግስት’ የተከሰቱትን ስህተቶች ሁሉ በትግሥትና በተስፋ ማሳለፍ ሳይሰለቻቸው የተጓዙም አይጠፉም።
ኡ ኡ የሚያሰኘውና የሀዘን ማቅ የሚያስለብሰው ግን፤ መሪዎቼ በትምህርት፣ በንባብ፣ በአለም ዙሪያ በመገኘት ከተለያዩ ሕዝቦችና ከአኗኗራቸው በመማር እውቀትና ልምድ ያካበቱ፣ በእድሜም የጎለበቱ ናቸውና ያሸጋግሩኛል ብሎ ተስፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የሶሪያን ሕዝብ ጽዋ እንዲቀምስ እየተገፋ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ በማሽጋገርና የጥቁርን ሕዝብ አደራ በመጠበቅ ልንሠራው የምንችለው ታላቅ ታሪክም ለሁለተኛ ጊዜ በከረረ የብሄረተኝነት ርዮተ-አለም ተጠልፏል። የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ዝና ስሙ ከጠፋ ቢቆይም፤ ባሁን ሰአት ግን በአለም የርስ-በርስ የመገዳደል ታሪክ ውስጥ የአንደኝነት ቦታ እንዲይዝ ውርርድ የተገባለት ይመስላል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋዊና ሰብአዊ መብቱ ተጥሶ በማንነቱ፣ ለምሳሌ በጎሳው ወይም በእምነቱ፣ ምክንያት ህልውናው የተደፈረ እለትና መንግሥት ደግሞ ይህንን ማስከበር ዋና ተግባሩ መሆኑን ቸላ ያለ እለት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስበውና ጥያቄ ሊያነሳ ይገባዋል። ለዚህም ተጠያቂነታቸውን የሚያድበሰብሱ ብሎም የሚክዱ፤ የተለያየ ሚና ያላቸው የፖለቲካ መሪዎችንም ሕዝብ ያለወቀሳ/ያለተቃውሞ ዝም ብሎ ባሳለፈ ቁጥር ለመሠረታዊ መብቱና ለነጻነቱ ዋስትና እንደማይኖረው መረዳት ይኖርበታል። ካለፉት ሰላሳ አመታት ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማንነታቸው የተነሳ የሰባዊና የዜጋዊ መብታቸው ተገፍፎ ሲገደሉና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ኖረዋል። የዚህ ሰለባዎች ከተለያዩ ጎሳዎች ወይም ብሔሮች የተወለዱ ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ ቢታወቅም፤ ዛሬ በተለየ እቅድ፣ በርዮተ-አለምና በማኒፌስቶ በተደገፈ ጥቆማ የትውልድ ሥፍራውን ለቅቆ እንዲወጣ በብዛት እየተሳደደና እየተገደለ የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ነው። ዛሬ በተለይ በወለጋ ውስጥ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ እየበዛና እየሰፋ መሄዱ ብቻ ሳይሆን መፈጸሙን ለመካድ ወይም ለማሳነስ፣ ይባስ ብሎም ምክንያት ለመስጠት በያቅጣጫው የሚደረገው ርብርቦሽ እጅግ አስደንጋጭና ለማመን የሚያስቸግር ሆኗል።
ይህ የኔ ትውልድ የጋራ ጥቃቶችን መገንዘብና ያጭርና የረጅም ጊዜ ጥቅሞችን ለይቶ ማየት ነበረበት። ለአያት ለቅድመ አያቶቹ ታሪክም ሆነ መሠረት ለሌው ትርክት የራሱን ትውልድ መስዋእት ማድረግ አይገባውም ነበር፣ ለውርሱ ተገቢውን ቦታ ሰጥቶ አዲስ የራሱን ታሪክ ለመጻፍ መድፈር ነበረበት። ሰፊ ሃገርና ድንበርም ሆነ በርካታ ሕዝብ ኃይል ነው፤ ህብራዊነትና ብዙኃንነት የእውቀትና የሃብት ምንጭ ነው።
ከተለያየ እይታ በመነሳት ማንም ይጻፈው ማንም ሳይበላለጥና ሳይተናነስ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ በሙሉ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ ለሰብዓዊ መብት የታገሉት ወገኖቻችንን አደራ የመወጣት እድሉ ገና ጨርሶ አላመለጠን ይሆን? ተከራክረንና ተደራድረን፤ ግን ተባብረን ነጻነቱ የተከበረለት፣ እኩልነቱና ሰብዓዊ መብቱ የተረጋገጠለት፣ ተደጋግፎና ተረዳድቶ ጭቆና፣ ድህነትና ረሀብ የጣሉበትን ውርደት የሚላቀቅ፣ በኅብረትና በታደሰ አንድነት የሰላምና የጸጥታ ዋስትና ፈጥሮ መኖር የሚችል ሕዝብ እንዲኖረን ካሰብን ከራሳችን በቀር የሚያግደን ማንም አልነበረም።
የኔ ትውልድ ወገኖቹን ከድል ዋዜማ ወደ ድል ተሸጋግረው ለመላው የጥቁር ሕዝብ ትንሳኤ ምሳሌነት ሊበቁ እንዲችሉ ለማድረግ የሚያበቃ አቅም አለው ብዬ አምን ነበር፤ ዛሬችሎታውና ፍላጎቱ ቢያጠራጥረኝም። ችሎታ ጀግንነትንና ብልህነትን ይሻል። የጀግንነት መጀመሪያው ሃሳብን መቀየር መቻል፣ ራስን መርምሮ ልክ እንዳልሆኑ የተገነዘቡ እለት ለመለወጥ መድፈር ነው። በቀልን ዋና መመሪያ አድርጎ የፖለቲካ እቅድ ማውጣት ደግሞ አይንን ጨፍኖ የገደል አፋፍ ላይ እንደመቆም ነውና ከበቀል የመለያየት ፍላጎት ከሌለ መልካም ታሪክ መሥራትም አይቻልም።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ