
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ታህሳስ 02 2015 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49 በግልጽ እንዳስቀመጠው፤ አዲስ አበባ የፌደራል መንግሥቱ ርዕሰ ከተማ ከመሆኑም በላይ “የአዲሰ አበባ ከተማ መስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል” ይላል። ከዚህም አልፎ ይኽው የሕገ መንግሥት ድንጋጌ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፤ አዲስ አበባ በኦሮምያ ክልል መሃል የምትገኝ ከተማ እንጂ፤ የኦሮምያ ክልል አካል አለመሆኗን በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል።
የአዲስ አበባ ሕዝብ የብልጽግና ፓርቲ እንዲያስተዳድረው ሲመርጥ፤ የከተማ መስተዳደሩ ከተማዋን በሕዝቡ ፍላጎት እንዲያስተዳድር እንጂ፤ የከተማው ሹማምንቶች፤ የራሳቸውን የብሄር ቋንቋ፤ ባሕልና፤ የኑሮ ዘይቤ በግድ እንዲጭኑበት አስቦና አልሞም አለመሆኑ ነጋሪ የሚያሻው አየመስለኝም። ክብርትነትዎ፤ ከኦሮሞነቶ ይልቅ ኢትዮጵያዊነቶ ይበልጥቦታል የሚል እምነት ነበረኝ። የሰሞኑ የከተማ መስተዳድርዎ ሥራ፤ በተለይም የኦሮምያን ክልል ባንዲራና የሕዝብ መዝሙር፤ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጉሮሮ ውስጥ በግድ ለመሰርነቅ የሚያዳርገው ጥረትና ይህንን ኢ-ሕገ መንግሥታዊና ሕገ ወጥ ድርጊት በማያሻማ ሁኔታ ከማውገዝ ይልቅ፤ ተበዳዩን የአዲስ አበባ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ሲወቅሱ መስማቴ ዓላማዎንና አቋሞን እንድጠይቅ አስገድዶኛል።
የኦሮምያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ የትኛውም ትምሕርት ቤቶች የሚሰቀልበትም ሆነ የኦሮምያ ክልል የሕዝብ መዝሙር የሚዘመርበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሰረት የሌለው ከመሆኑም በላይ፤ ምንም ዓይነት አሳማኝ አመክንዮ የለውም። ሕዝቡ “በኦሮሞ እየተገፋሁ ነው” የሚለውን እውነት ጭብጥ የሚሰጥ እኩይ ተግባር ነው። ይህ ድርጊት የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላው ወንደምና እህት ሕዝብ የሚነጥል አደገኛና ጽንፈኛ አካሄድ ለመሆኑ በቅርቡ በከተማችን የተደረጉ ተቃዋምዎች በግልጽ አሳይተዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ቆይታዬ በርካታ ኢፍትሃዊና የኦሮሞን ተረኝነት የሚያንፀባርቁ ድርጊቶች አይቻለሁ። ሕዝቡም በዚህ እጅግ እየተማረረ መሆኑንም ታዝብያለሁ። ይህ ካልታወቃችሁ፤ ወረድ ብላችሁ ከሕዝቡ ጋር ውይይት አድርጉ። ይህ “ኦሮሞ ጠል” ከሆኑ ዜጎች የሚንፀባረቅ እሳቤ ነው የሚለው ትርክት ብዙ አያራምዳችሁም። ለሃገርም፤ ለፓርቲያችሁም ትልቅ አደጋ የሚፈጥር ለመሆኑ በአጽንዎት ልነግርዎት እወዳለሁ።
ኦሮሞነትን በግድ በሕዝብ ላይ ለመጫን የሚደረግ መንተጋተግ፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ፍፁም አይጠቅምም፤ ይህንን በሕወሃት ዘመነ መንግሥት አይተነዋል። የሕወሃት ባለሥልጣናት በሰሩት እኩይ ሥራ፤ ምስኪኑ የትግራይ ሕዝብ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። አሁንም እንደ እርሶ ያሉ የኦሮሞ ዝርያ ያለባችሁ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያዊነታችሁ ይልቅ ኦሮሞነታችሁ እየበለጠባችሁ፤ የኦሮሞ ሕዝብ በሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲገለል አቅጣጫ እያስቀመጣችሁ ነው። ይህንን አደገኛ አካሄድ እንዲያርሙና፤ አስተዳድሮም ለመረጠው የከተማ ሕዝብ ጥቅም እንዲቆም በአክብሮትና ትሕትና እጠይቆታለሁ። መስተዳድሩ ከሕግ ውጪ ያሰራቸው ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን በአስቸኳይ እንዲፈቱም እጠይቃለሁ። በከተማው ትምህርት ቤቶች ለተፈጠረው ሁከት ተጠያቂው መስተዳድሮ እንጂ ነዋሪው ወይም ተማሪው ሊሆን አይችልም። ኦርሞነትን በግድ ማንም ላይ መጫን አይቻልም። እኔም እንድ እርሶ የኦሮሞ ዝርያ ያለብኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ። “ኦሮሞ ይቅደም” በሚል እሳቤ እየሰራችሁት ያለው ሥራ ግን የኦሮሞን ሕዝብ የአቃፊነት እሴት የሚመጥን አለመሆኑን ልነግርዎት እወዳለሁ።
ይህ ድርጊታችሁ የኦሮሞን ሕዝብ አንገት የሚያስደፋ እንጂ፤ የሚያኮራ ሊሆን አይችልም። እርሶ የተመረጡት የአዲስ አበባን ሕዝብ በቅንነት እንዲያገለግሉ እንጂ፤ የኦሮምያ ክልል ተሟጋች እንዲሆኑ አይደለም። የኦሮምያን ክልል ጥቅም ለማስጠበቅ ከፈለጉ፤ በኦሮምያ ክልል ሊወዳደሩ ይገባል። ምንም እንኳን በርካታ በጎ ሥራዎችን እየሰሩ ቢሆንም፤ በዘር ፖለቲካው ላይ እና በከተማችን “የኦሮሞ የተረኝነት ስሜት” ላይ ዓይኖን ነቅለዋልና፤ ይህን አደገኛና ጽንፈኛ አካሄድ በአስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱበት በትሕትና እና በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ