spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትለኢትዮጵያ ጥያቄ የመጨረሻ መፍትሔ አማራጭ ሁለት? ፋሺዝም፣ ኢትዮጵያና የአፌዲሪ ሕገ-መንግሥት

ለኢትዮጵያ ጥያቄ የመጨረሻ መፍትሔ አማራጭ ሁለት? ፋሺዝም፣ ኢትዮጵያና የአፌዲሪ ሕገ-መንግሥት

Ethiopia _ ለኢትዮጵያ ጥያቄ
ከጎግል ካርታ ላይ የተገኘ

ክንዴነህ እንደግ (ፒኤች ዲ)

በሚሊዮን ሰራዊት – ያልያዘ ያልሰላ፣
በመርዝ ጋዝ እልቂት – ያልያዘ ያልሰላ፣
ጦቢያን ከምድረ ገጽ – ማጥፊያ ምርጡ መላ፣
በብሔር ቅራኔ – ፋሺስታዊ ትርክት፣
ሕጋዊ መደላድል – ወላ ሕገ-መንግሥት፣ 
በእርስ በእርስ ግጭት – ልጆችዋን ማባላት!

መግቢያ፤ ከጦሱ ፈውሱ፣ ከልክፍቱ መድኀኒቱ፣ ከጋኔሉ ጠበሉ፣ የከፋው የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ነገር! 

ይህ ክፍል በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ዙሪያ ከላይ በተመለከተው ዋና ርዕስ ሥር በተከታታይ የሚቀርቡ መጣጥፎችን ይዘት ለማስተዋቅ ያሕል ለመነሻና መግቢያ የሚሆኑ ጥቅል ምልከታዎች የቀረቡበት ነው፡፡ 

በረከት ወይስ መርገም?

የኢትዮጵያ ፓለቲካ ያለፉት ሃያ ስምነት ዓመታት አልፋና ኦሜጋ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሕገ-መንግሥቱን አራጊ ፈጣሪነት ሚና የሚጠራጠር ሰውም ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ልዩነት ያለው ይህ አራጊ ፈጣሪነት ሚና የልማት ነው ወይስ የጥፋት? ሕገ-መንግሥቱ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መጣላቸው ወይስ መጣባቸው? ተረቆ በሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ባሉት ሃያ ስምንት አመታት ሀገሪቱን ከማጥ አወጣት ወይስ መቀመቅ አወረዳት? ሕገ-መንግሥቱ ለሀገሪቱ መጻዒ እጣ ፋንታ የብሩኅ ተሥፋ ምልክት ነው፣ ወይስ የሕልውና ሥጋት ምንጭ ? የሚለው ላይ ነው፡፡

በነዚህና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ዙሪያ ያሉት የአመለካከት ልዩነቶች በአብዛኛው በኢትዮጵያ ፓለቲካ ዋነኛ ተዋንያን በሆኑት በተለምዶ የአንድነት ሃይሎች በሚባሉትና በብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች መካከል ያለው አጠቃላይ የፓለቲካ አመለካከትና አቋም ልዩነት ነጸብራቅ ነው፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን የተሟላውን ሥዕል ባይሰጠንም ለዚህ መጣጥፍ ውስን አላማ በዛው መሰረት ባጭር ባጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

በተለምዶ የአንድነት ሃይሎች በሚለው የፓለቲካ ጎራ የሚገኙት አቋም የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መርዶ ነው፤ የመጣባቸው ቁጣ፣ የወረደባቸው መዓት እንጂ የመጣላቸው በረከት፣ የወረደላቸው ምሕረት አይደለም የሚል ነው፡፡ ለአንድነት ሃይሎችና የነሱን አመለካከት ለሚጋሩት ልኂቃን ተረቆ ሥራ ላይ ከዋለበት ግዜ ጀምሮ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ፋይዳና ሚና ባብዛኛው አፍራሽና አሉታዊ ነው፡፡ ለሀገሪቱ ሕዝቦች የደኅንነት፣ የእፎይታ፣ የሃሴትና ደስታ ምንጭ ሳይሆን የስቃይ፣ የመከራ፣ የሰቆቃና ሃዘን ምንጭ ነው፡፡ 

በተጨማሪም የአንድነት ሃይሎች በተለይ ላለፉት አራት አመታት በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየጊዜው አድማሱን እያሰፋ የመጣው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ዋነኛ መንሥዔ ሕገ-መንግሥቱ ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡ ስለሆነም በነሱ አስተያየት ሕገ-መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ባይሻርና ባይቀየር እንኳን ቢያንስ ቢያንስ መሰረታዊ ማሻሻያ ካልተደረገበትና አንቀጽ 39/ሰላሳ ዘጠኝን የመሳሰሉ በጣም አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾች ካልተሰረዙ ከእስካሁኑም በከፋ ሁኔታ በሕገ-መንግሥቱ ምክንያት የሃገሪቱ ሕልውናና መጻዒ እጣ ፋንታ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች አቋም ከአንድነት ሃይሎች አቋም ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ በነሱ አመለካከት ሕገ-መንግሥቱ የሀገሪቱ ሕልውና ዋስትናና መሰረት ነው፡፡ 

ለአፍቃሪያነ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ቀድሞ ነገር ሕገ-መንግሥቱ ባይኖር ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችው በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ነው፡፡ ምክንያቱም የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ለኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት እድል ለመስጠት የወሰኑት በሕገ-መንግሥቱ ምክንያት ነው፡፡በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ሰጭነት ነው፡፡ 

እንጂማ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት፣ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት አብቆቶለት፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ ነበር፡፡

ከአንድነት ሃይሎች በተቃራኒ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ሕገ-መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሕልውና ዋስትና ነው ሲሉ ይህን ማለታቸው ነው፡፡ ይህን በመካድ ሕገ-መንግሥቱን ማብጠልጠል በሰነዱ ባለቤቶች፣ አፍቃሪያንና ጠበቆች እይታ ውለታ ቢስነት ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱን እጀ ሰባራ፣ እጀ አመድ አፋሽ ማድረግ ነው፡፡ 

በአፍቃሪያኑና በጠበቆቹ አቋምና አመለካከት መሰረት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከሌለ ለወደፊቱም ቢሆን ኢትዮጵያ ልትኖር አትችልም፡፡ ኢትዮጵያ የሕገ-መንግሥቱ ውጤት ናትና፡፡ የሕገ-መንግሥቱ ርኅራኄ፣ ችሮታ፣ ትሩፋትና፣ አበርክቶ ናትና፡፡ 

ይህ ማለት በአፍቃሪያነ ኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት እይታ ይልቁንም “ሕገ-መንግሥቱ ለኢትዮጵያ እርግማን ወይስ በረከት?” የሚለው የዚህ ጽሑፍ መነሻ በራሱ የተሳሳተና ፈሩን የሳተ ነው፡፡ ለምን ቢባል ኢትዮጵያን ከሕገ-መንግሥቱ በፊትና በላይ አድርጎ የመመልከት የተሳሳተ መነሻና አንድምታ ስለሚኖረው፡፡

በብሔር ነጻ አውጭ ተቀናቃኞቻቸው እይታ የአንድነት ሃይሎች ሕገ-መንግሥቱን ይልቁንም እንደ ታላቅ ባለውለታ፣ እንደ ኢትዮጵያ ወላጅ ማየትና አውቅና መስጠት ሲገባ ሊኮንኑት ፣ሊረግሙት፣ ሊያብጠለጥሉት፣ ሊያንኳስሱት፣ ጥላሸት ሊቀቡትና ካለስሙ ስም ሊሰጡት አይገባም፡፡

ምን አደረጋቸውና!? ባጎረስኩ ተነከስኩ!? “እንሞትልሻለን! ካንቺ በፊት ያድረገን!” ሲሉዋት ኖረው በመጨረሻ “እነሱ ካሸነፉ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት አይኖርም” እያሉ ስማቸውን ሲያከፉና ሲያጠፉ ለኖሩት የብሔር ነጻ አውጭዎች ያስረክበዋትን ሀገር ስለታደገላቸው!? 

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን ይህን ሲሉ ለወዳጆቻቸውም ለባላንጣዎቻቸው ማስታዎስ የሚፈልጉት ምን ግዜም ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር አለ፤ ይሄውም የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ተረቆና ጸድቆ በሥራ ላይ እንዲውል በተደረገበት ወቅት ማለትም የዛሬ ሃያ ስምንት ዓመት ገደማ በሀገሪቱ የሃይል አሰላለፍ መሰረት ፓለቲካዊም ወታደራዊም ፍጹም የበላይነት የነበራቸው የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ማለት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ይከተሉት በነበረው የብሔር ቅራኔ ትርክትና ከትርክቱ በተቀዳውና በፓለቲካ ፕሮግራማቸው ባሰፈሩት የትጥቅ ትግሉ የመጨረሻ ግብ መሰረት ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን የቻሉ ነጻ የትግራይ፣ የኦሮሞ ወዘተ ሀገረ-መንግሥታትን መመስረት ይችሉ ነበር (ማለትም ኢትዮጵያ በዐጤ ሚኒሊክ በጉልበት ግዛትን የማስፋፋት እርምጃ የተፈጠረች የአናሳ አማራ ገዢ መደብ የቅኝ ግዛት አስተዳረር ናት በሚለው ትርክት መሰረት)፡፡ 

ሕገ-መንግሥቱ ይህን ያስቀረ፣ ይልቁንም በወቅቱ አሸናፊንም ተሸናፊንም አሸናፊ በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ከድል ማግሥት በይቅር ባይነት፣ ታጋሽነት፣ ሆደ ሰፊነትና፣ አርቆ አሳቢነት መንፈስ የመረጡት ታላቁ አስታራቂ የመካከለኛ መንገድ አማራጭ ነው (ማለትም ባንድ በኩል የትጥቅ ትግሉን በበላይነት በማሸነፍ የማዕከላዊ መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶችን በሌላ በኩል ተሸናፊ የሆኑነት የአንድነት ሃይሎች)፡፡ 

በዚህ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን አመክንዮ መሰረት እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ዋናው ነጥብ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ እውቅና የሰጡዋት በሕገ-መንግሥቱ ምክንያት ነው የሚለው ነው፡፡ ለምን ቢሉ አንድምታው እንዲህ የዋዛ አይደለምና፤ የትየሌሌ ነውና፡፡  

እንዴት

እንዴት ማለት ጥሩ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ አንባቢ ያስተውል ዘንድ የሚገባው በብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች አቋምና አመለካከት መሰረት ቅድመ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያ ከየትም ልትመጣ፣ ምንም ልትሆን ትችላለች፡፡ ድኅረ- ሕገ-መንግሥት ግን እንደ ሀገረ-መንግሥት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ውጤት ናት፡፡ ተጸንሳ የተወለደችው ከኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አብራክ ነው፡፡ 

የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ከሕገ-መንግሥቱ አብራክ ያዋለዷት ኢትዮጵያ፤ ዳዴ ብላ፣ አድጋ ተመንድጋ፣ እንደ ሀገረ-መንግሥት ለአካለ-መጠን የመድረስ ተስፋ አላት ወይስ የላትም የሚለውን ጉዳይ በግዜ ሂደት ለማየትና እድል ለመስጠት የወሰኑት በሕገ-መንግሥቱ ምክንያትና በሕገ መንግሥቱ መሰረት ነው፡፡ ማለትም እንደ ሀገረ-መንግሥት አካለ መጠን መድረስ የምትችለውና ሕልውናዋን ማረጋገጥ የምትችለው በብሔር ነጻ አውጭዎች አስተያየት በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት እሴቶች ተኮትኩታ ካደገችና ለድንጋጌዎቹ በፍጹም ታማኝነት ከተገዛች ብቻ ነው፡፡ 

በሌላ አነጋገር ድኅረ ኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያ እንደ ሀገረ መንግሥት የመኖር ዋስትናዋ ለኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት የሚኖራት ታማኝነት እንጂ ቅድመ ሕገ-መንግስት ነበረኝ በምትለው የሶስት ሽኅ ዓመታት ገናና ታሪክ ወዘተ ሚረጋገጥ አይደለም፡፡ በቦታው በዝርዝር እንደምናየው ቅድመ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ነበረኝ የምትለው የአስደናቂ ታሪክ ድርሳን ሙሉ በሙሉ ተሽሮ ወደ ሙት መዝገብ ተላልፎ በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ተተክቶአል፡፡ ድኅረ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥትነት ተሥፋና ብቸኛ ዋስትና ሕገ-መንግሥቱ ሲሆን የቅድመ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ውርሷ ፋይዳ ለታሪክ ምርምርና ለጎብኝዎች ፍጆታነት ወደ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መዘክር በይፋ ተሸኝቶአል፡፡

እነሆ ብሔር ነጻ አውጭያኑ፣፣ በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ስላመኑ፣ ኢትዮጵያን ምን ቢመንኑ፣ የመነኗትን ኢትዮጵያ በሕገ-መንግሥታቸው አዳኑ! 

በሌላ አነጋገር የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ኢትዮጵያዊ የሆኑት ኢትዮጵያን አምነው በኢትዮጵያ ተማምነው አይደለም፡፡ በጭራሽ እንደዛ አይደለም፡፡ ሕገ-መንግስቱን አምነው፣ ሕገ-መንግሥታዊነታቸውን ተማምነው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ሕገ መንግስቱን ጥላ ከለላ፣ ዋልታ መከታ አድርገው ነው፡፡ የሆዳቸውን በሆዳቸው አድርገው፣ ይቅር ባይ፣ ሆደ ሰፊ ሆነው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ከነ ግሣንግሡ፣ ከነብዙ ጓዝ መዘዙ፣ ሥጋቱና አደጋው እግራቸውን እየጎተቱም ቢሆን እድል ለመስጠት የወሰኑት ሕገ-መንግሥቱን አምነው፣ በሕገ-መንግሥቱ ተማምነው ነው፡፡

ኢትዮጵያን ሊቀብሩ ያሉ ጥራኝ ዱሩ፣ ለኢፌዲሪ ቢያድሩ ለኢትዮጵያ ራሩ!

እንጂማ ኢትዮጵያን ማመን ቀብሮ ነው ብለው ጫካ ገብተው እንጂ ነበር!  የትጥቅ ትግሉ ዓላማ ግቡን መቶ ያሰቡት ሲሳካ፣ ያለሙት ሲደርስ ኢትዮጵያን ስለማያምኑዋት ከሚቀብሩዋት ሊራሩላት የወሰኑት በሕገ-መንግሥቱ ምክንያት ነው፡፡ ሳይቀብሩ ላያምኑዋት ምለው ጫካ የገቡትን የብሔር ነጻ አውጭዎች አንጀት ያራራላት፣አራርቶም ከብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ትሙት በቃ ፍርድ ኢትዮጵያን ያማለዳት፣ ታዳጊ መልአክ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ኀጢያት ምን በዝቶ ቢንዛዛ፣ ሕገ-መንግሥት ደርሶ ኾናት መድን ቤዛ!

እነሆ ኢትዮጵያን ያመነ ጉም የዘገነ የሚለው ሥር-የሰደደ ፍራቻቸውን በመቅረፍ ለብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ አደጋ የሕይወት መድን ዋስትና/ሽፋን የሰጠውም የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ነው!

እንዴት አድርጎ? ቢሉ አጭርና ቅልብጭ ያለው መልስ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች የታገሉለትን የመጨረሻ የፓለቲካ ግብና ዓላማ ማለትም ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ የተነጠሉና ራሳቸውን የቻሉ የትግራይ፣ የኦሮሞ ወዘተ ነጻ ሀገረ መንግሥታት ዕውን ማድረግን የማታ ማታ የትም የማያመልጣቸው፣ ይልቁንም በይደር ለክፉ ቀን ቢያስቀመጡት የሚበጅ የሚደረጅ፣ በጅ ያለ አማራጭ በማድረግ የሚል ነው፡፡

ኑ እንውረድ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ባርያችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር!

ድኅረ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂ ጉባዔ በግዜው ወታደራዊና ፓለቲካዊ የበላይነት በነበራቸው የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች (በተለይ ሕውሃት በአስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም ደረጃ በተጨማሪም ኦነግ) አርአያና ምሳሌ የፈጠራት ናት፡፡

ይህም እንዲታወቅ እንደ ባላንጣዎቻቸው የአንድነት ሃይሎች ያይደለ፤ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች የሚምሉትና የሚገዘቱት በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት እንጂ በኢትዮጵያ አይደለም፡፡ የት ያውቋትና! ኢትዮጵያን ያወቁዋትም እውቅና የሰጡዋትም እንደተባለው ሕገ-መንግሥቱ ለክቶ፣ ሰፍሮ በወሰነላት ሕገ መንግሥቱ “ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች” በሚላቸው የኢፌዲሪ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች አጭር ቁመት፣ ጠባብ ደረት ምሳሌና አርአያ፣ አምሳያና አኳያ አይደለምን!? (“ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች” ለመሆኑ ማናቸው? ድምድርንስ ናቸው? ከወድየትስ መጡ? ለሚለው በቦታው እንመጣበታለን)

ከዚህ አንጻር መሃላና ግዝታቸው፣ እገሌ ወይም ሞት መፈክራቸው፣ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት እንጂ በኢትዮጵያ ባይሆን የተገባ እንጂ ነው፡፡ እነሆ ፍጡር ለፈጣሪው እንጂ ለፍጡር መስገድ እንዳይገባው ተጽፎአልና! አፍቃሪያነ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት በኢትዮጵያ ቢምሉ ቢገዘቱ ባዕድ አምልኮ መሆኑ እንጂ ነው! የኀጢያቶች ሁሉ ኀጢያት ጣዖት አምልኮት እንጂ ነው!

መቻል ምን ባይከፋ፣ ሆድ ከኢፊዲሪ ላይሰፋ!

የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ባለቤቶች፣ አፍቃሪያንና ጠበቆች አቋም መቻል ምን ባይከፋ ትግሥትም ልክ አለው፤ ልኩ ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ ነው ባዮች ናቸው፡፡ እንደተባለው በብሔር ነጻ አውጭዎች አቋምና አመለካከት ኢትዮጵያ በስሟ እንደሚገዘቱቱ የአንድነት ሃይሎችና እንደ ኢትዮጵያ ራሷ ቅድመ ሕገ-መንግሥት ባሕሪ፣ ጠባይና፣ ምግባር ቢሆን ኖሮ እነሆ የዛሬ ሃያ ስምንት ዓመት ገደማ አብቅቶላት ነበር፡፡ ታሪክ ሆና ነበር፡፡እስካሁን ቆማ ለመሄድ የበቃችው በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ባለቤት፣ አፍቃሪያንና ጠበቆች ቻይነት፣ ሆደ-ሰፊነትና አርቆ አስተዋይነት እንዲሁም የነሱ ትሩፋት በሆነው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አማካኝነት ነው፡፡

ነገር ግን መቻል ምን ባይከፋ፣ ሆድ ካገር ቢሰፋም፤ ኢትዮጵያን ከገደል አፋፍ፣ ከመቃብር አፍ፣ የዛሬ ሃያ ስምንት አመት ያተረፈና እስካሁን ጠብቆ ያቆየው የአፍቃሪ ሕገ-መንግሥታውያን ይቅር ባይነት፣ ሆደ ሰፊነትና አርቆ አስተዋይነት ገደብ የለውም ማለት አይደለም፡፡ 

ኢትዮጵያ ሲራሩላት ሲያዝኑላት ማወቅ አለባት፡፡ ልብ መግዛት አለባት፡፡ ለኢትዮጵያ “ እሞትልሻለኹ! ያንቺን ክፉ ከማይ እኔን ያስቀድመኝ” ሲሉ የሚምሉ የሚገዘቱላት የአንድነት ሃይል ተብየ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ፡፡ ይህንንም ኢትዮጵያም ሆነች በስሟ የሚምሉ የሚገዘቱት ለኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት ያላቸውን ምስጋናና አክብሮት በማሳየት ማረጋገጥ ይገባል፡፡

ይህ ማለት ለኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን አርበኝነት ማለት “ጣል ያን ጠላትህን” በሚል ደረትን ለጦር፣ አንገትን ለሰይፍ፣ ግንባርን ለጥይት ሰጥቶ፤ ደምን አፍሶ፣ አጥንትን ከስክሶ የጣሊያን ወራሪን በዱር በገደሉ መፋለም አይደለም፡፡

ከነበረም እሱ ድሮ ቀረ! ድኅረ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያዊ አርበኝነት ማለት፣ ኢትዮጵያ ወይም ሞት! ሳይሆን ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ወይም ሞት ነው፡፡ ፌዲሪን ጎርዶ፣ ኢትዮጵያን ወዶ፣ አርበኝነት ቀልድ ዘበት! 

ብሔር ነጻውጭያኑ እንድሚሉን ከሆነ ድኅረ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የአንድነት ሃይሎችን ጨምሮ የኢትዮጵያዊያን አርበኝነት ዋነኛ መገለጫ መሆን ያለበት ከሕገ-መንግሥቱ እግሩ ስር ወድቆ ውለታውን እያስታወሱ፣ በስሙ እየማለዱና እየተማለዱ እድሜ ልክ ለሰነዱ ድንጋጌዎች መገዛት ነው፡፡ 

ሕገ-መንግሥት ቢጣስ፣ ጣጣው ቁጣው መዓቱ፣ ወይ ለኪ! አሌ ለኪ! ጦቢያ ሆይ ባንቺ ይብስ! ለብሔር ነጻ አውጭማ አያድርሱም ቢደርስ፣ ባይሆንም ሰርግ ከመልስ፣ እንጂ ነው ውርድ ከራስ፣ ግፋ ቢል እዳው ገብስ!

ከላይ የተጠቀሰው የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች የማይናወጽ አቋምና ምክር ቸል ተብሎ ሕገ-መንግሥቱ ቢጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ቢፋለሥ፣ ቢቃወስ ለብሔር ነጻ አውጭዎች እዳው ገብስ ነው፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ከራሳቸው ወረደች ማለት ነው፡፡ 

የምትቀረው፣ የምትፈርሰው፣ የምትሻረው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ጌታዋና ፈጣሪዋ ነውና ምን ግዜም ከኢትዮጵያ መቃብር በላይ በብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝቦች ዘንድ እንደተከበረ እንደተዘከረ ይኖራል፡፡ 

ካላማረባትና ጸባዩአን ካላሳመረች የኢትዮጵያ መፍረስ ይልቁንም የሕገ-መንግሥቱ ነገረ-ዕቅድ፣ ጥንተ ሥሪት፣ ቁልፍ ድንጋጌ፣ ትልም፣ ቢጋርና ተልእኮ አካል እንጂ ነው!

ይሄ ማለት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ፈጣሪ ጌታ? እንዴታ! ይሄ ማለት ኢትዮጵያ አመቱ ለኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት? እውነት እንበለ ሐሰት! ይሄ ማለት ኢትዮጵያ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አገልጋይ ሎሌ!? የሚሻል የሚበጃት እሱ እንጂ ነው ዛሬም ሁሌ! 

ይህ ማለት ሕገ-መንግሥቱ ከኢትዮጵያ በላይ  ነው! ኢትዮጵያ ከሕገ-መንግሥቱ በታች ናት፡፡ ለአፍቃሪ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥቶች በዚህ ጉዳይ ምንም አይነት ብዥታ የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ሁለት ግዜ ማሰብ ይሉት ነገር የለም፡፡  

እነሆ ፈጣሪ ከፍጡሩ እንዲቀድም፣ እንዲበልጥ፤ ፍጡርም ከፈጣሪው እንዲያንስና እንዲከተል፤ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትና የኢትዮጵያ ግንኙነትም ለሕገ-መንግሥቱ አፍቃሪያን እንደዚያው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ አቋማቸው የማይናወጽ፣ ከብረት የጠነከረና ምን ግዜም ጽኑ ነው፡፡ ማለትም ኢትዮጵያ ከአስገኝዋ፣ ከአምጦ-አምጭዋና ከፈጣሪዋ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት በታች ናት፡፡ መሆንም ግድ ይላታል፡፡

ኢትዮጵያ ብትሞት በፌዲሪ ይለቀሳል፤ ፌዲሪም ከሞተ በብሔር ይልቀሳል፤ ብሔር የሞተ እንደኹ ወዴት ይደራሳል! 

ውብ ፌዲሪ፣ ቅዱስ ፌዲሪ፣ ክቡር ፌዲሪ፤ ባንተ እኮ ነው ኩራት ክብሬ፣ መከበሬ!

ጉዳዩን የበለጠ ግልጽና ቀላል ያደርግልን ዘንድ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያን ስንጎርድ በሚቀረው ፌዲሪ መካከል ያለውን ልዩነት እናጉላ፡፡ ልዩነቱ ኢትዮጵያ እንደ ሀገረ መንግሥትና በሕገ-መንግሥቱ መሰረት የተዋቀረው ፌዲሪ (ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) እንደ መንግሥታዊ ሥርዓት/የአስተዳደር ዘይቤና መዋቀር ያላቸውን አንድነትና ልዩነት ይመለከታል፡፡  

 በዚህ መሰረት ሕገ መንግሥቱ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገረ መንግሥት ነጥሎ የሰጣት/የሚሰጣት እውቅና የለም አይኖርም፡፡ ይልቁንም ቅድሚያ የሚሰጠው ለፌዲሪ ነው፡፡ ማለትም ሕገ-መንግሥቱ እውቅና የሚሰጠው ራሱ ላስገኘውና እውን ላደረገው በኢትዮጵያ ስም ለሚጠራው ፌደራላዊ ዲሚክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥቱ በፌደራላዊ ዲሞክራሲያው ሪፐብሊክ መልክ ያዋለዳት የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ናት፡፡ እንጂ የመንግስት አስተዳደሩዋ ምንም ይሁን ምን ያለችና የምትኖር ሀገረ-መንግሥትነቷ በመንግሥት አስተዳደሩዋ ምንነትና ባሕሪ የማይገደብ ወይንም ለድርድር የማይቀርብ አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥትነት ሕልውና ወሰን፣ ድንበር፣ ገደብ፣ የለሽና ፍጹማዊ አይደለም፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት መሥፈርትና ልክ የተቀነበበና የተወሰነ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከፌዲሪ በላይ አይደለችም፡፡ ፌዲሪ ከኢትዮጵያ በላይ ነው፡፡ ከፌድሪ ውጭ ኢትዮጵያ እንደ ሀገረ-መንግሥት አለኝ የምትለው የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የለም፡፡

የኢትዮጵያ ወግ ማዕረግ፣ የፌዲሪ መስዋዕት በግ!

 በሌላ አነጋገር እንደ ሀገረ-መንግሥት የኢትዮጵያ መኖር ወይም የኢትዮጵያ ሕልውና በምትወክለው የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት አወቃቀርና ዘይቤ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እንጂ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትና የሕገ-መንግሥቱ አፍቃሪያን አቋምና አመለካከት መሰረት እውነታው የተገላቢጦሽ አይደለም፡፡ ወይም በተገላቢጦሹ አይሰራም፡፡ ማለትም የመንግሥት አስተዳደሩ ዘይቤ ትርፍ ወይም በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣና የሚታይ (ይልቁንም እንደ ግዜና ዘመኑ ተለዋዋጭ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ሆኖ) የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥትነት ግን በአንጻሩ ቋሚና መንግሥታዊ ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ ሕገ-መንግሥቱ ታሳቢ አያደርግም፤ ወይንም ዋስትና አይሰጥም፡፡

ሕገ መንግሥቱ ዋስትና የሚሰጠው በተገላቢጦሹ ነው፡፡ ማለትም በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት መሰረት መንግሥታዊ ሥርዓቱና አወቃቀሩ (ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም) ለድርድር አይቀርብም፡፡ይህ መንግሥታዊ ሥርዓትና አወቃቀር ጥያቄ ውስጥ ከገባ ካለምንም ማወላወል ሕገ-መንግሥቱ የመሥዋዕት በግ በማድረግ የሚያቀርበው ኢትዮጵያን ለፌዲሪ ነው፡፡

ማለትም በሕገ-መንግሥቱ መሰረት መታደግና ማዳን የሚገባው የፌደራል ሥርዓቱን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጦስ ቀውስ፣ ጣጣ ፈንጣጣ፣ አደጋና ሥጋት እንጂ የተገላቢጦሽ አይደለም፡፡ ማለትም ኢትዮጵያን ከሕገ-መንግሥቱና የፌደራል ሥርዓቱ ጦስ ቀውስ፣ ጣጣ ፈንጣጣ፣ አደጋና ስጋት አይደለም፡፡

እንዲያ እንጂ ነው ጉዱ! ሲሉ እንደሰማነው ቀልድ አናውቅምና በፌድሪ አትቀልዱ፣ ለኢትዮጵያ አፍቃሪያን ፌዲሪያውያን ሲያስረዱ ፣በኢትዮጵያ ስትምሉ ፣ኢትዮጵያን ስትወዱ ፣ ምን ሊረባን በሚል ፌድሪን ብትጎርዱ፣ ውርድ ከራሳችን ለናንተው ነው ጉዱ! 

ባጭር አገላለጽ ባይገባ ደግ፤ ነገር ግን ግድ ሆኖ ሀገር ወይስ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚል ንጽጽር ውስጥ ከተገባ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አቋም ግልጽና ቆራጥ ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሀገር ይቀድማል፡፡ በመንግሥታዊ ሥርዓት ቀልድ የለም፡፡ ሀገር ግን የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ 

የሶስት ሽኅ ዓመታት፣ ታሪክ ምን ቢኖራት፣ ፌድሪ ከሌላት፣ ጦቢያ ዋጋም የላት! ብቻ አንደሚንሿሿው ጽናጽል እንጂ ናት!

እርግጥ ነው ፌድሪ ተጎርዶም ኢትዮጵያ የሀገረ-መንግስትነት ምኞትና መሻት (በዝርዝር እንደምናየው በፌድሪያውያን መሰረት ድቡሽት ላይ የተመሰረተ፣ በጣም አወዛጋቢና አጠራጣሪ ቢሆንም) ሊኖራት ይችላል፡፡ ነገር ግን በአፍቃሪ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶችአቋም መሰረት የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥትነት እጣ ፋንታ ሕገ መንግሥቱ የፈጠረላትን ቅጥልጣይ ስያሜዎች በሟሟላት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከሶስቱ ቅጥልጣይ መስፈርቶች (እና መስፈርቶቹ ከሚወክሉት የፓለቲካ ጽንሰ-ሀሳብና ትርጉም) አንዱን እንኳን ካጎደለች፣ ማሟላት ካልቻለች ወይም ከጣሰች፤ ማለትም ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ካልሆነች፣ ዲሞክራሲያዊ ካልሆነች፣ ሪፐብሊክ ካልሆነች ጨዋታው ፈረሰ ዓባይ ደፈረሰ፡፡ 

የሶስት ሽኅ ዓመት ታሪክ ፋይዳ፣ በብሔር ቅራኔ ሲከዳ! በብሔር ፌደራሊዝም ሲከነዳ!

እንደተባለው ኢትዮጵያ ከሕገ-መንግሥቱ በፊት የፈለጋትን ልትሆን ትችላለች፤ የሰው ዘር መገኛ፣ የሶስት ሽኅ ዓመታት ገናና ታሪክና ስልጣኔ ባለቤት፣ የውጭ ወራሪ ሃይሎችን በተደጋጋሚ ዓለምን ባስደመመ ጀግንነት ድል በማድረግና አሳፍራ በመመለስ ነጻነቷን አስከብራ ለምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች ሳትገብርና ሳትንበረከክ የኖረች በዓለም ላይ ብቸኛ አፍሪቃዊት ሀገር ወዘተረፈ፡፡ አይሰራም!

ለሌላ ለምንም ነገር ሊሆናት ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ የገናና ታሪክና ጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትነት ብሎም ጸረ-ቅኝ ግዛት አንጸባራቂ የጀግንነት ታሪክ ዝርዝር በርግጥም አስደማሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ለኢትዮጵያም ጌጥ ወጥ፣ ውበት ደም ግባት ሊሆናት ይችላል፡፡ በክብር ላይ ክብር፣ በዝና ላይ ዝና፣ በኩራት ላይ ኩራት፣ ሊያጎናጽፋት ይችላል፡፡ 

ዳሩ ምን ዋጋ አለው! መጀመሪያ መቀመጫየን ያለችው ነገር ነው! ምንም ይኹናት ምን የቅድመ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ገናና ታሪክ፣ ሥልጣኔና ያልተቋረጠ ነጻና ራሷን የቻለች ጥንታዊ ሀገረ-መንግሥትነት አስደማሚ ድርሳንና ማስረጃ ሁሉ ተሰብስቦ ለኢትዮጵያ ድኅረ ሕገ-መንግሥት ሕልውናዋ ፋይዳ ጠብ የሚል ወላ ሓንቲ ነገር የብሉ! ከመልክ ደም ግባት፣ ከውበት ቁንጅና፣ ከኩራት ከክብር በፊት ሕልውናን ማረጋገጥ እንዲቀድም ደግሞ ግድ ነው፡፡

ትግራዋይ በኻፈሻ ከይትጎንድይ ቀልጥፍ! ናይ ፫ሽ ዘበን ታሪኽ ግበር አፈፍ!

ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንዲሉ የቅድመ ኢፌዲሪ የሶስት ሽኅ ዓመታት ገናና ታሪክና ሥልጣኔ ባለቤትነት ነገር ራሱ ውስጡን ለቄስ ሳይሆን አይቀርም! ይህም እንዲታወቅ እስከዚህ ድረስ ዝርዝር የሰነድ ማስረጃዎችን በይደር ለተከታታይ መጣጥፎች እያቆየን ብንዘልቅም እዚች ጋ ከእስካሁኑ አካሄዳችን ወጣ ባለ መልኩ ከያኔው ተሓህት፣ ከአምናና ዘንድሮው ሕውኀት የ1968 ማንፌስቶ ከዚህ በታች በጠቀስናት ማለፊያ ምንባብ ፋታ ቢጤ እንውሰድማ፤

“…ከዚህም በላይ የሚያኮራው የሕዝባችን ታሪክ፣ ባሕልና ቋንቋ እንዲዳከምና ተዳክሞ እንዲጠፋ ወይም የአማራ ብሔር የገዢ መደብ ጥቅም እንዲጠብቅ የ፫ ሽ ዓመታት ታሪክና ባሕላችን መመኪያቸውና መፎከሪያቸው ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ የታሪክ ስርቆት ባንድ በኩል የአማራው ብሔር መፎከሪያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰፊው የትግራይ ሕዝብ ታሪክ እንደሌለው ሕዝብ እንዲያስቆጥረው የተደረገ የመንግሥት መመሪያ ነው፡፡” ተሓህት ማንፌስቶ 1968 ገጽ 16

እርፍ! የምን የወል ታሪክ ሁሉንም የሚያቅፍ! ጦቢያዊን በሞላ ሰሜን ጫፍ ደቡብ ጫፍ፣ ሶማሌ ጋንቤላ ምስራቅ ጫፍ ምዕራብ ጫፍ፣የልቅ ሕዝቢ ትግራይ በኻፈሻ ቀልጥፍ! ናይ ሶስት ሽ ዘበን ታሪኽ ግበር አፈፍ! ያናሳው ገዢ መደብ አማራም አታኩርፍ፣ ያስተረፉልህን ያልተነካብህን ፉከራህን ታቀፍ!

እዚህ ላይ እርግጥ ነው አንባቢ ሊያጉረመርም ይችላል፡፡ የያኔው ተሓህት ያልበሰለ፣ ጮርቃ አቋም ከአምናና ዘንድሮ ኢፌዲሪያውያን የታሪክ ግንዛቤና አመለካከት ጋር ምን አገናኘውና ነው የቀደመው ለኋለኛው እንደ ተጨባጭ ማስረጃ የሚጠቀሰው እንደማለት/ በሚል ነቀፌታ፡፡ 

በጀ! ለዚህ ነቀፌታ ሰጥቶ ከበሬታ፣ ማቅረብ ግድ እንጂ ነው ተገቢ አጸፌታ! በዚህ መሰረት በጉዳዩ ላይ ማለትም የሶስት ሽኅ አመታት ታሪክን በተመለከተ አንድም የ1968 ተሓህት አቋም ያልበሰለና ግዜአዊ አለመሆኑን ለማጠየቅ ሁለትም የአምናና ዘንድሮ ኢፌድሪያውያን አመለካከትም ከተሓህት ጋር ተወራራሽ (የተቀዳ እንዳንል ጨዋነት ቢያግደን) መሆኑን ለማስረገጥ አንባቢ ሆይ የሕውሃትን የ1983እኤአ በእንግሊጤራ አፍ (በእንግሊዘኛ) የተከተበ የፓለቲካ ፕሮግራም ተመልከት! እነሆ ከሰነዱ 13/አስራ ሶስት ገጾች ግማሽ ያሕሉ ማለትም ከገጽ አንድ እስከ ስድስት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱ ታሪክ ላይ ሆኖ ታገኘዋለኽ፡፡ ብሎም የላይኛውን ጥቅስ አምልቶ አስፍቶ ሲተነትን ታገኘዋለኽ! 

ዳሩ እዛ ድረስ የምን ሰውን ማድከም፣ ሳለ እናቱ መዝገብ፣ አይነተኛው ድርሳን ሕገ-መንግሥት በቁም? ከተባለም ምን ከፍቶን! እነሆ ሕገ-መንግሥቱን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጉሩ አሰስነ! አስሰንም አልቀረነ! በመገረም፣ በመደነቅ መዳፋችንን ባፋችን ጫነ! ለምን ቢሉ ስለ ቅድመ ኢፌዲሪ ኢትዮጵያ ታሪክ ልናገኝ የቻልነው መግቢያው ላይ “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና…” የምትል ቀዳሚም ተከታይም አልቦ፣ አንድ ለናቱ፣ ነጠላ ሃረግ ብቻ ነው! 

እናሳ? እናማ ከድጡ ወደ ማጡን ሲያጣጥሙ፣ አልሸሹም ዘወር አሉ በምን ጣሙ! 

ይኼሳ እንደምን ነው? ቢሉ ከላይ በጥቅሱ እንዳየነው ተሓህት ቢያንስ የሶስት ሽኅ አመታቱን ገናና ታሪክና ሥልጣኔ ሙሉ ለሙሉ ሽምጥጥ፣ ምጥጥ አርጎ አላየሁም፣ አልሰማኹም ሲል አልካደም! የተሓህት ክፋቱ፣ ጮሌ ብልጣብልጥ ሞጭልፍነቱ!  ይልቁንም ዋይ አታ እንታይ እዩ እዚ ጉዱ! ወያናይ ምኻንስ ባዶ ስም ጥራኽ ድዩ”/ ወያኔነት ታዲያ ለመቼ በሚል ዳንዴ፣ ወንበዴነት የጋራ ታሪክ መሆኑን ክዶ፤ ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ሞጭልፎም ቢሆን ባትጋሩኝ ባትመራመሩኝ አይነት ለተጋሩ ብቻ መዳረጉ ነው! 

ጉደኛው ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ሆየስ? ከተሓህት የባሰ ተሓህት! የተሓህት ክሕደት ለኢፌዲሪያውያን ተራ፣ኮስማና የልጅ እቃቃ ጨዋታ ናት!

ይህም እንዲታወቅ፣ እንዳያጠያይቅ የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት የሶስት ሽኅ አመታት ታሪክ ይሉት ነገር ከነጭራሹ አያውቅም፡፡ሲያልፍም አይነካው!

ነገር ግን ይህ የሆነው ኢ/ፌድሪያውያንና ታሪክ እሳትና ጭድ፣ ሆድና ጀርባ በመሆናቸው አይደለም፡፡ እንዲያ ቢሆን በምን ጣሙ! ነገርየው ከዚያም የከፋ ነው!

ለምን ቢሉ ነገርየው የማይመስል ምጸት ወይንም የተቃርኖዎች ኹሉ ማሳረጊያ ተቃርኖ ቢመስልም ቅሉ፤ እውነታው ግን እንደ ኢፌዲሪያውያን ባጠቃላይ፣ የሕገ-መንግሥቱ ባለቤቶች በተለይ፣ ታሪክ አምላኪ፣ ታሪክ ተራኪ፣ ታሪክ ሰባኪ፣ የለምና ነው! 

ካንድ አስገዳጅ መስፈርትና ቅድመ ሁኔታ በስተቀር! ይሄውም ማንኛውም ታሪክ በኢፌዲሪያውያን ዘንድ ግርማ ሞገስ አግኝቶ፣ እውቅና ተሰጥቶት፤ ይሰግዱለት፣ ያመልኩት፣ ይሰብኩት፣ ይዘምሩለት ዘንድ የኢትዮጵያውያን የጋራና የአንድነት በጎ ታሪክ ሳይሆን የተዛባ ግንኙነታቸው ማስረጃ መሆን አለበት፡፡ ሊሆን ግድ ይላል! ወይም በተዛባ ማለትም በጠማማ፣ በከይሲ፣ በሃኬተኛ፣ ታሪክነት ተጠምዝዞ፣ ተዛብቶና ተጣሞ መተርጎም፣ መተረክ፣ መወደስ፣ መሞገስ መቻል አለበት!

ይህ ማለት ሕገ-መንግስቱን ከግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጉሩ አስሰን ስለ ቅድመ ኢፌዲሪ ኢትዮጵያ ታሪክ የምናገኘው ምንባብ ከላይ የጠቀስናት አንዲት ሀረግ የመሆንዋ አንድመታ የብሔር ነጻ አውጭ ኢፌዲሪያውያን ባጠቃላይ፣ የሕገ-መንግሥቱ ባለቤቶች በተለይ ለታሪክ ንፉግ መሆኑናቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ኢፌዲሪያውያንና ሕገ-መንግሥታቸው ለታሪክ ስግብግብና ቀናዒ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ 

እንደተባለው ይልቁንም ኢፌድሪያውያን ባጠቃላይ የሕገ-መንግሥቱ ባለቤቶች በተለይ የሙሉ ጊዜ ታሪክ አምላኪ፣ ታሪክ ተራኪ፣ ታሪክ ሰባኪያን ናቸው፡፡ እንደተባለው ቁልፍ የሆነው አስገዳጅ መስፈርት እስከተሟላ ድረስ! ይኼውም ማንኛውም ታሪክ በሕገ-መንግሥቱ በተደነገገው መሰረት ኢትዮጵያውያን ከታሪካቸው የወረሱት የተዛባ ግንኙነት ማሳያና ማስረጃ እስከሆነ ድረስ! 

ወይም በብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች አቻ ትርጓሜው፣ የብሔር ቅራኔ ትርክት ግብዓት እስከሆነ ድረስ! የብሔር ቅራኔ ትርክት ማሳለጫ፣ ማጣፈጫ በመሆን የቅድመ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ታሪክ በሙሉ የብሔር ቅራኔን የሚያወሳ ታሪክ ለመሆኑ ተጨማሪ ማሳያ እስከሆነ ድረስ! 

ከዚህ አንጻር ነገሩ ምንም የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ኢፌዲሪያውያን ታሪክን ማምለክ፣ ታሪክ መተረክ፣ ታሪክን የመስበክን ሚናና ፋይዳ እንደ ሕልውናቸው መሰረት፣ አለኝታ፣ ዋልታ ቢቆጥሩት ሲያንሳቸው ነው፡፡ ዋይ ኢትዮጵያ ትብሃል ሀገርስ ብዘይ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ብስሩ ክትነብር ዘይትክእል ከም ነበረት እዚውን ከምኡ እንበር፡፡ ስትል እንደምታብራራልን ትሓህት/ሕውሃት ወያነና! (ለሰዋሰውም ሆነ ለቃላትና ቀለም ግድፈቱ ያቀሬታ ግበሩልና)

 ኢትዮጵያ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ባይኖር ኖሮ መኖር እንደማትችለው ይኼም እንደዛው እንጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከታሪካቸው የወረሱት የተዛባ ግንኙነት ባይኖር ኖሮ፣ ናይ ብሔር ብሔረሰባት ሕዝብታት ሓርነት ውድባት ዝብሃሉ ዝነብሩሉ ኩነታት ዝአሳልጥ አጋጣም ብስሩ አይነብርን ኔሩ እንበር ብኻቂ! 

ኢትዮጵውያን ከታሪካቸው የወረሱት የተዛባ ግንኙነት ባይኖር ኖሮ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች የሚባል ነገር አይኖርም ነበር ማለት እዩ እዚ ዘረባ እዚ! የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች ባይኖሩ ደግሞ ኢፌዲሪ የሚባል ነገር ከነ ሕገ-መንግሥታዊ ግሳንግሱ የሚፈጠርበት አጋጣሚ አይኖርም ነበር፡፡

እረጅም እድሜ፣ ዘላለማዊ ክብር፣ ለኢትዮጵያውያን የተዛባ የታሪክ ግንኙነት! 

እስመ ኃያል አንተ፣ ወለከ ስብሓት፣ ዘኢትዮጵያውያን የተዛባ የታሪክ ግንኙነት ውርስ! 

እንደተባለው ይሄ ሊደንቅ አይገባም፡፡ የብሔር ነጻ አውጭዎች ተጸንሰው፣ ተወልደው፣ በእንክብካቤ አድገው የኢፌድሪን ሕገ-መንግሥት እስከ ማስገኘት አካለ መጠን የደረሱት ከኢትዮጵያውያን የተዛባ ታሪክ ግንኙነት አብራክ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፋቸው ሕገ-መንግሥቱም እንደዚሁ፡፡

የብሔር ነጻአውጭያን ወይም ሞት መፈክር፣ የኢፌዲሪያውያን ወይም ሞት መፈክር፣ ብሎም ሕዝብ መዝሙር፣ ይህንን ይመስላል በሚያምር ቅላጼአቸው ዜማ ሲንቆረቆር፦ 

ለተዛባ ታሪክ ዘላለማዊ ክብር! የተዛባ ታሪክ ለዘላለም ይኑር! የአንድነት ታሪክ ግንብ፣ ይናድ ይሰባበር! የአንድነት ታሪክ ውርስ አመድ ይሁን አፈር! የአንድነት ታሪክ ውርስ እርቆ ይቀበር!” 

ከተዛባ ታሪካዊ ግንኙነትና የብሔር ቅራኔ አቢዎታዊ አመራር ጋር ወደፊት! የተዛባ ታሪክ ይቅደም! ደገኛ/ቅን ታሪክ ይውደም!

ስለሆነም ፊተኛም ኋለኛም፣ ቀዳሚም ተከታይም የሌላት የሕገ-መንግሥቱ ነጠላ፣ ብቸኛ፣ አንድ ለናቱ “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና… ” የሚሉዋት የታሪክ ሃረግ ይልቁንም ታሪከኛ! ጉደኛ! ሃረግ እንጂ ናት፡፡ ለምን ቢሉ አንደኛ እንደሷ ቁም ነገረኛ፣ ውል አይረሴ፣ ብቀጥንም ጠጅ ነኝ በአቻዎቿ የዓለም ሃረጋት ታሪክ ፈልጎ ማግኘት መቻሉ ያጠራጥራል፡፡  ምክንያቱም ነጠላነቷ፣ ቀዳሚ ተከታይ አልቦነቷ፣ አንድ ለናትነቷ የታሪክ ስሱነት ወይ ንፉግነት ማሳያ አይደለም፡፡ ስሱነት የሚለውን አንባቢ ቀናዒነት በሚል ካልወሰደው በስተቀር፡፡ ለምን ቢባል በዚች የዋሕ፣ ምስኪን፣ ከሲታ፣ ፈ.ታ፣ ኮስማና፣ መናኛ መሳይ ሀረግ ሕገ-መንግሥቱ ያደረገው አስገራሚ ትንግርት ቢኖር ይልቁንም የቅድመ ኢፌዲሪ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ታሪክ አንድም ሳያስቀር፣ ጠራርጎ፣ አግበስብሶ ለድኅረ-ኢፌድሪ የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች አውጫጭኝ ኢትዮጵያ ማውረስ፣ ማስተላለፍ ነው፡፡ 

እንደተባለው ከአንድ ቁልፍ አስገዳጅ መስፈርት በስተቀር፡፡ ይሄውም አንድም ሳያስቀር፣ ጠራርጎ፣ አግበስብሶ ስለተባለ ከነግሳንግሱ ምንም ሳይመርጥ ማለት አይደለም፡፡ አንድም ሳያስቀር ጠራርጎ የሚወስደው የተዛባና ጠማማ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡  

ባጭሩ ሲቀመጥ በዚች የዋሕ፣ ምስኪን፣ ትሑት፣ ከሲታ፣ ፈ. ታ፣ ኮሳሳ፣ ኮስማና መሳይ ነገር ግን መሰሪ፣ ጠንቅ-ዋይ፣ ሃኬተኛ ሃረግ መመሪያና ድንጋጌ መሰረት ሕገ-መንግሥቱ የተዛባ እስከሆነ ድረስ የኢትዮጵያውያንን ታሪክ በሙሉ በታላቅ ባላደራነትና ፍጹም ታማኝነት መንፈስ ተረክቦና አግበስብሶ ከቅድመ ሕገ-መንግሥት ለድኅረ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ አውርሶአል፡፡ 

ያ ብቻም አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ እንዲሆን ግድ የሆነበት ገፊ ምክንያት እንደተባለው ይህ ከታሪክ የተወረሰ የተዛባ ግንኙነት ሕገ-መንግሥቱም ሆነ ባለቤቶቹ የብሔር ነጻ አውጭ ኢፌዲሪያውያን የተሰሩበት ጡብ ስለሆነም ነው፡፡

ይህን የበለጠ ለመረዳት ቢካተቱ የጠንቅ-ዋዩዋን ሃረግ ንባብም ሆነ መንፈስ ምሉዕና በጎ ያረጉ የነበሩ ሁለት ነገሮችን በየተራ እንመልከት ፡፡ አንደኛ ንባቡንም መንፈሱንም ሚዛናዊ ለማድረግ ቢፈለግ ኖሮ ከታሪካችን የወረስናቸውን መልካም ነገሮች የመጠበቅና የመንከባከብ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ… የሚል ነገር መጨመር ይቻል ነበር፡፡ እንዲያ ቢሆን በሚከተለው መልኩ ምንባቡ ምሉዕ መንፈሱም በጎ በሆነ ነበር፤ 

“መጭው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስናቸውን መልካም ነገሮች የመጠበቅና የመንከባከብ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ጎን ለጎን ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል ….” 

ከላይ የጨመርነውን ንባብ አለመኖር ይልቁንም የታሰበበት ግድፈት መሆኑን ከጥርጣሬ በላይ የሚያደርገው ሕገ-መንግሥቱ ታሪክን ስለመጠበቅና መንከባከብ አስፈላጊነት ባይተዋር አለመሆኑ ነው፡፡ይልቁንም ሕገ-መንግሥቱ በጣም አጽንኦት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ እሱ ነው፡፡ አንባቢ ለአብነት አንቀጽ 39/ሰላሳ ዘጠኝን ይመልከት፡፡

ችግሩ ያለው ሕገ-መንግሥቱ ለታሪክ ያለው ቀናዒነት የአብራኬ ክፋይና የእንጀራ ልጅ በሚል ልዩነት የሚፈጥርና የሚያዳላ መሆኑ ላይ ነው፡፡ የአብራኬ ክፋይ የሚለው ከፋፋይ የሆነውን የተዛባ የታሪክ ግንኙነት የኢትዮጵያውያን ታሪክ ዋነኛ መለያ መሆኑን የሚያውጀውን ነው፡፡ የእንጀራ ልጅ በሚል የሚገፋና የሚያገለው ብቻ ሳይሆን የሚያሳድድና የሚገለው ደግሞ የሶስት ሽኅ አመት የኢትዮጵያውያን የጋራ ገናና ታሪክና ስልጣኔን ነው፡፡  

ከዚህ አንጻር በጎና መልካም የሆነውን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ “የመጠበቅና መንከባከብ” አስፈላጊነትን አብሮ መጥቀሱ ቢቀር በሁለተኛ ደረጃ ማካተት ሲገባው ሆን ብሎ የዘለለው “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነትን በማረምና…” ከሚለው ቀድሞ ሊመጣ ይችል የነበረ ንባቡን የበለጠ ሚዛናዊ ሊያደርግ ይችል የነበረ ከታሪካችን የወረስነው በጎና መልካም ነገር ቢኖርም/እንዳለ  ሆኖ/እንደተጠበቀ ሆኖ በዛው መጠን ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና…” የሚል ይዘት ያለው ማሟያ ነው፡፡

ይህ ማለት ባጭሩ ሕገ-መንግሥቱ ለኢትዮጵያ የሶስት ሽኅ አመት ታሪክና ስልጣኔ እውቅና ነፍጎአል ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሕጋዊ መንገድ ሰርዞ፣ ፍቆ፣ ሙሉ በሙሉ ደምስሶ፤ በጠማማው፣ በተዛባው፣በከይሲው፣ በሃኬተኛው ታሪክ ለውጦታል፡፡ ወይም ደገኛውን ታሪክ ፍቆ፣ ሰርዞና አፍርሶ ከፍርስራሹ በደረተው የተዛባ ታሪክ ተክቶታል፡፡ 

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አስደናቂ ገድል፤ ለአኖሌ ትንሳዔ አድዋን በገደል!

ከላይ የተብራራው የሕገ መንግሥቱ የታሪክ ድንጋጌ ወደ መሬት ሲወርድ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በተጨባጭ መገለጫዎቹ ምን መልክ ሊኖራቸው ይችላል? ለሚለው ለናሙና ለመጥቀስ ያሕል፤ ከሕገ-መንግሥቱ ማስፈጸሚያ ዝርዝር መመሪያዎች አንዱ አድዋን አኮስምኑ አኮስሱ፣ አኖሌን አሞግሱ፣ አንግሱ የሚል ያልተጻፈ የሕገ-መንግሥቱ ማስፈጸሚያ ደንብ ነው፡፡ አድዋን አንኳሱ፣ክሰሱ፣ ውቀሱ (ኤርትራን ያስገነጠለ፣ ትግራይን በርሃብ አለንጋ ያስገረፈ ያቃጠለ ወዘተ) አኖሌን ሸልሙ አንቆለጳጵሱ የሚል ነው፡፡

ከዚህም በላይ ግን የሕገ-መንግሥቱ ባጠቃላይ የታሪክ ድንጋጌው በተለይ ሚና፣ ስንደርስበት በቦታው በዝርዝር እንደምናየው፣ የሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ያልተሳካ የመጨረሻ ግብና አላማ ወራሽነት ነው!! ይሄውም ሚሊዮን በሚጠጋ ሰራዊት ሲደመር የመርዝ ጋዝ ማሳካት ያልቻለውን ኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ መሳሪያነት ነው!

አዎ! ይህ ማለት የብሔር ቅራኔ ትርክት ግብዓት፣ ማቀጣጠያ ዋነኛ ባሩድ የሆነው በሕገ-መንግሥቱ ሕጋዊ እውቅና የተሰጠውና ጥበቃና እንክብካቤ የሚደረግለት ኢትዮጵያውያን ከታሪካቸው የወረሱት የተዛባ ግንኙነት ሚሊየን ከሚጠጋ ሰራዊት ሲደመር የመርዝ ጋዝ የበለጠ ውጤታማ የሆነ ለኢትዮጵያ ጥያቄ የመጨረሻ መፍትሔ አማራጭ ሁለት መሳሪያ ነው፡፡

ብቀጥንም ጠጅ ነኝ፣ ቀዳሚ ተከታይ አልቦ፣ አንድ ለናቷ ሕገ መንግሥታዊ ሃረግ ይሉኻል እንዲያ ናት! አስታውስ እንዳትረሳት! ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት… ትላለች/ትባላለች! ከናያቷ ለመጥራት የድል አድራጊው ዱቼ ፋሺስታዊ ኒውክሊየር የሚል አክልባት! 

ለኢትዮጵያውያን ተሥላ የተሰጠች፣ ኢትዮጵያውያን ማንነትን መሰረት ባደረጉ ግጭቶች ለመተላለቅ ከመጥረቢያና ምሳር፣ ቆንጨራ ከገጀራ በፊት የታጠቁዋት፣ የእርስ በእርስ እልቂት ሁነኛ መሳሪያና ሕጋዊ መደላድል ይሉኻል እሷ ናት! 

ይቆየን!

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here