spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትቋንቋን ማወቅ ይጠቅማል፣ በግድ ሲሆን ግን ያቅራል!

ቋንቋን ማወቅ ይጠቅማል፣ በግድ ሲሆን ግን ያቅራል!

ቋንቋን

ሲሳይ መንግሥቴ አዲሱ (ዶ/ር)

መግቢያ

አሁን በምንገኝበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ቀርቶ በቀደመው ጊዜም ቢሆን ቋንቋ በመናገር፣ በመጻፍ ወይም በምልክት አማካኝነት ሕዝብን ለማግባባት የሚያገለግል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ከሌላው እንስሳ እንዲለይ የሚያደርገው ማሰብ መቻሉ ሲሆን የሚያስበውን ነገር ወይም ጉዳይ ወደ ሌላኛው ሰው ማሻገር ወይም ማጋባት የሚችለውም በቋንቋ አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቋንቋ ወሰብሰብ ያለ ሁኔታ እንዲኖረው ሆኗል፣ ከዛም አልፎ ለሰው ልጅ ወካይ የሆነ ባህሪም ተላብሷል ማለት ይቻላል፡፡ እናም ቋንቋ በተፈጥሮ ስጦታ ወይም መወለድ ሳይሆን በልምምድና በትምህርት የሚገኝ ክህሎት እንደሆነ የስነ ልሳን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ 

ይህም በመሆኑ የተለዋዋጭነት ባህሪንም ተላብሷል፣ ማንም ሰው በአንድ ወቅት የለመደውንና ሲጠቀምበት የነበረውን ቋንቋ ትቶ ሌላ አዲስ ቋንቋ ሊማር ይችላል፣ ወይም ከሚያውቀው ቋንቋ በተጨማሪነት ሌላ ቋንቋ ተምሮ ሊጠቀም ይችላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንድም የሚያስገድድ የኑሮ ሁኔታ ሲያጋጥም ለመመሳሰል ስትል አሊያም ህሊናህ ወዶና ፈቅዶ ከሁሉም በላይ ደግሞ በህይወት ምዕራፌ ውስጥ ይጠቅመኛልም ብለህ ልትማረው ትችላለህ፡፡ ስለሆነም ቋንቋ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የሰው ልጅ መሳሪያ ነው፣ ለምን ቢባል ቋንቋ እንዲሁ ለመግባቢያነት ብቻ ሳይሆን ወዳጅነትን ለማጠናከር፣ ባህላዊ ትስስርን ለመፍጠር፣ የምጣኔ ሀብት መስተጋብርን ለማሳደግ እና ማህበራዊ ግንኙነትን ለማሳለጥ፣ ወዘተ እንደሚጠቅም በተግባር የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ 

ከዛም አልፎ የሰው ልጅን አስተሳሰብና ስሜትን በሚገባ ይቀርጻል፣ የአንድ ሰው አመለካከት ምን እንደሚመስል ለማወቅም በእጅጉ ይረዳል፣ በአጠቃላይም ቋንቋ የአዕምሮ ብርሀን ነው ይባላል፡፡ ይህም ማለት አዕምሮ ውስጥ የሚፈጠር፣ የሚብላላና የሚብሰለሰል ፍልስፍናዊ እሳቤ እና እውቀት ሁሉ በቋንቋ አማካኝነት ካልተገለጸና ሌላው ሰውም እንዲጋራው ካልተደረገ አበው “የጋን ውስጥ መብራት” እንደሚሉት አይነት ይሆንብናል፡፡ በነገራችን ላይ ቋንቋ እውቀትም ነው፣ በአሁኑ ዓለማዊ ሁኔታ ከአንድ በላይ በሆነ ቋንቋ መግባባት የሚችል ሰው የተሻለ ተወዳዳሪ ይሆናል፡፡ 

ምክንያቱም አንድን ሁኔታ ይበልጥ ለመረዳትና ለማወቅ ብሎም ለመተግበር የቋንቋ መሰረታዊያን የሆኑትን መስማት፣ መናገር፣ ማንበብ፣ መጻፍ፣ መመልከትና አይቶ መለየትን መቻል የተሻለ ዕድል ይሰጣልና ነው፡፡ እንዲሁም የሰንደቅ ዓላማን ትርጉምና አገልግሎት ስንመለከትም ሠንደቅ ዓላማ የአንድን ሀገር ማንነትና ፍላጎት የሚገልጽ የአርበኝነት ምልክት ነው፡፡ ብሔራዊ ወይም ሕዝባዊ መዝሙርም የአርበኝት ስሜትን ለመግለጽ የሚያገለግል በግጥምና ዜማ የሚደገፍ የአንድ ሀገር መገለጫ ነው፡፡ ለመግቢያ ያህል ስለቋንቋ፣ ሙዝሙርና ሠንደቅ ዓላማ ይህን ካልሁ አሁን ላይ እየታዘብነው ወዳለነው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ልመለስና ትንሽ ነገር ለማለት ልሞክር፡፡

የአገራችን የቆየ ልምድና አሁን ላይ እየተከሰተ ያለው ቀውስ

በሀገራችን ቀደም ባሉት ዘመናት እንደ አሁኑ ወጥ የሆነ ሠንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር የነበረ መሆኑን የሚያመለክቱ ጽሁፎችን ማግኘት ባልችልም በየጁ ስረዎ መንግስት (በዘመነ መሳፍንት) የእያንዳንዱ አካባቢ ገዥ እኔንና አካባቢየኝ ሊገልጸኝ ይችላል የሚለውን ቀለም የያዘ ጃኖ ወይም በቆዳ ላይ የተለበጠ ምልክት ይጠቀም ነበር፡፡ በዚህ ረገድ በብዛት ጥቅም ላይ የዋሉት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት ሲሆኑ የኋላ ኋላ ሦስቱም ቀለማት በአንድ ላይ ተሰድረው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ 

ይህም በዋነኛነት አድዋ ላይ በእምየ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ብጡል መሪነት በወራሪው የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ላይ የተመዘገውን ደማቅ ድል ተከትሎ የሠንደቅ ዓላማ አስፈላጊነት ይበልጥ ትኩረት እያገኘ እንደመጣ ይታመናል፡፡ በተለይም እ.አ.አ በ1919 ዓ.ም አካባቢ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል እንድትሆን ጠይቀው የሚወክላችሁን ብሔራዊ ምልክት ላኩ ሲባሉ የአረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ዓላማ መልዕክት እንዲኖረው በማድረግ መላካቸው ይታወቃል፡፡ ከዛም መጀመሪያ ላይ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማቱ መሀል ላይ መስቀል የተሸከመ አንበሳ የሚታይበት ዓርማ ተጨምሮበት የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ስሜት ግምት ውስጥ ገብቶ መስቀሉ ተነስቶ አንበሳው ግን ከስልጣናቸው እስከተነሱበት መስከረም 2/1967 ዓ.ም ድረስ ሲያገለግል ቆየ፡፡ 

የደርግ መንግስትም አንበሳውን አስወግዶ የራሱን ሕብረተሰባዊ እሳቤ ወይም የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም የሚያመለክት ዓርማ እንዲደረግበት ወስኖ ስራ ላይ አዋለ፡፡ ይህም ሆኖ ሕዝብ ዓርማ የሌለበትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማ እንዳይጠቀም አይከለከልም ነበር፡፡ እንዳውም ዓርማ ያለበት ሠንደቅ ዓላማ በአብዛኛው በቤተመንግስትና በተወሰኑ መስሪያ ቤቶች ብቻ ያገለግል እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ኢሕአዴግ ስልጣን ሲይዝ የሠንደቅ ዓላማ አገልግሎትን አስመልክቶ የመጣው የአስተሳሰብ ለውጥና ተግባራዊ የተደረገው ሁኔታ ከቀደሙት ልምዶች የተለየ ነው፡፡ 

በመጀመሪያ ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ክብር የላቸውም፣ ከዛ ይልቅ የድርጅታቸውን ዓርማ አስበልጠው ሲመለከቱ እናያለን፡፡ በዚህም ምክንያት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለሞችን ሳይቀር በጥላቻ መልኩ በመመልከት አይደለም በሠንደቅ ዓላማነት በአልባሳት ላይ ሳይቀር ጥቅም ላይ ውሎ ሲመለከቱ አይናቸው ከመቅላት አልፎ ለባሹን ወይም ተገልጋዩን ለማስወለቅ ጥረት ያደርጋሉ አሊያም አውልቆ እንዲጥል ጫና እስከ ማድረግ ይደርሳሉ፡፡ ይህም የተሳሳተው የብሔር ፖለቲካ የፈጠረውና ሀገራዊ አንድነትን የማይፈልገው እሳቤ ውጤት ነው፡፡ የብሔራዊ መዝሙርን እሳቤ በተመለከተም ከአጼ ኃይለስላሴ ጀምሮ በተደራጀና በተሰናሰለ መልኩ ስራ ላይ የዋለ እንደሆነ ሲገመት በንጉሱ ጊዜ የነበረው ብሔራዊ መዝሙር በዋነኛነት ጃንሆይን የሚያሞግስ እና ንጉሱ የኢትዮጵያ ስጦታ መሆናቸውን የሚገልጽ ነበር፡፡ 

በደርግ ጊዜ የነበረው ደግሞ ይከተለው የነበረው ርዕዮተ ዓለምን በሚገልጽ መልኩ ሕብረተሰባዊነትን የሚያቀነቅንና ይህንን አስተሳሰብ ለማስረጽ ታስቦ ስራ ላይ የዋለ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኢሕአዴግ የመንግስት ስልጣንን መቆጣጠሩን ተከትሎ ባለፉት 30 አመታት የታየው ለውጥ የርዕዮተ ዓለም ብቻ ሳይሆን የብሔር ተኮር ፖለቲካን ለማስረጽና ሀገራዊ አንድነትን ሊያላላ በሚችል መልኩ የተቃኘ መሆኑን ከድርጊቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ችግሩን ይበልጥ የከፋ እንዲሆን የሚያደርገው ደግሞ ክልሎች ቋንቋንና ብሔርን መሰረት አድርገው ሲደራጁና የራሳቸው ሠንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር እንዲኖራቸው ሲደረግ ነው፡፡

ይህም ማለት የቀደመውን ሠንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ችግር የነበረበት እንደሆነ አድርጎ በመፈረጅ ላይ የተመሰረተ ስለነበረ የዛ ተቃራኒ ነገር የመፈለግና የቀደመውን የመጥላት ዝንባሌ እያደገ እንዲሄድ የሚያደርግ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ ማለትም የትግራይና የአማራ ገዥ ፓርቲዎች በትጥቅ ትግል ወቅት ለፖለቲካ ድርጅት ዓርማነት የተገለገሉበትን ምልክት የክልላቸው ሠንደቅ ዓላማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ይገልጸናል ያሉትን ሠንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር አዘጋጅተው ለመገልገል ወስነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን ከሚሰብኩ ይልቅ ያለፈውን ሁኔታ ማውገዝንና ማጥላላትን ሲያስፋፉ ይታያሉ፡፡

የአዲስ አበባ አሁናዊ ሁኔታና የተፈጠረው ቀውስ 

አዲስ አበባ በንጉሱ የአገዛዝ ዘመንም ይሁን በደርግ ጊዜ ራሷን የቻለችና ለማዕከላዊ መንግስቱ ተጠሪ የሆነ አስተዳደር የነበራት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በኢሕአዴግ የመጀመሪያዎቹ አራት የስልጣን አመታት (የሽግግር ወቅት አስተዳደር) አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል በመሆን ተደራጅታ እንደነበረም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ክልል 14 በመባል ትጠራ እንደነበረም እናስታውሳለን፡፡ ሆኖም ህዳር 29/1987 ዓ.ም አሁን ስራ ላይ የሚገኘው ህገ መንግስት ሲጸድቅ አዲስ አበባ ከክልልነት ወርዳ የከተማ አስተዳደር እንድትሆን ተደረገ፡፡ 

ይህም ሆኖ በዚህ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49 ላይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንዳለው ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የራሱ የሆነ ሠንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር እንደሚኖረው አልተገለጸም፡፡ በዚህም መሰረት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የአዲስ አበባ መስሪያ ቤቶችም ሆኑ ትምህርት ቤቶች የፌዴራሉን ሠንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ሲገለገሉ ቆይተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ የእኛ ናት የሚለውን ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ የኦሮምኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ በማድርግ ጀምረው ቀስ በቀስ የኦሮሚያ ሠንደቅ ዓላማንና የኦሮሚያን ክልል የሕዝብ መዝሙር በማዘመር ዓላማቸውን ለማስፈጸም የያዙትን ስልጣን በማንአለብኝነት መጠቀም ጀመሩ፡፡ 

ይህም ሁኔታ በሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ ላይ ቅሬታን ፈጥሮ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ ይህንን ተቃውሞ ለማለዘብ ከመስራትና የሕዝብን ይሁንታ ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ እልህ ውስጥ በመግባት ፍላጎታቸውን በሀይል ለመጫን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም በላይ አሳዛኙ ነገር ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ መዝሙርን ለምን እንዘምራለን? ሠንደቅ ዓላመውንስ በምን ሂሳብ እንድናውለበልብ እንገደዳለን? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ይኸማ ኦሮሞ ጠልነት ነው የሚል ፍረጃ በመስጠት ለማሸማቀቅ ከመሞከር አልፈው የኦነግ-ሸኔ፣ የጽንፈኛ ፋኖ እና የምዕራባዊያን ሴራ ነው በማለት የችግሩን ምንጭ ውጫዊ ለማድረግ ጥረት መደረጉ ነው፡፡ 

ከዛም አልፎ ይኸ መዝሙርና ሠንደቅ ዓላማኮ እኛን አይገልጽም፣ ይልቁንም የእኛን መሰረታዊ መብትና የሞራል እሴት የሚነካ ነውና ይታሰብበት የሚሉትን ዜጎች ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪ ብሎ የጸጥታ ሀይል በማሰማራት ሕጻናትንና እመጫት ወላጆችን ጨምሮ መምህራንን የማሰር እርምጃ መውሰዳቸው በእርግጥም እነዚህ ሰዎች ከስህተታቸው ለመማር ከመፈለግ ይልቅ ያሰብነውን ካላደረግን እንደመሸነፍ ይቆጠራል የሚል አይነት አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ 

ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ የኦሮሚያ ስርአተ ትምህርት የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ሲጀመር የክልሉ ሕዝብ መዝሙር ይዘመራል፣ ሠንደቅ ዓላማውም ይሰቀላል ስለሚል ነው ይህን የፈጸምነው የሚለው ደካማና መሰረት የለሽ የመከራከሪያ ሀሳብ ነው፡፡ ይህም አንድም የከተማ አስተዳደሩን ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ከማሳየት ባሻገር በማን አለብኝነት ስሜት ስርአተ ትምህርቱን ባለበት ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ከመፈለግ የተነሳ ውሳኔ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ትልቁ ችግር ደግሞ ጥቂት ግሰቦች ይህን ውሳኔ ሲወስኑ የሚመለከተው አካል ሀሳብ እንዲሰጥበትና የአዲስ አበባ ሕዝብም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው አለማድረጋቸው ነው፡፡ 

ተደጋግሞ እንደተገለጸመውም ቋንቋን ማስተማር ከሠንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር የሚያገናኘው ነገር የሌለ ሲሆን ማንኛውንም ቋንቋ ተማሪዎች እንዲማሩት ሲደረግ በዛ ቋንቋ የተዘጋጀ መዝሙርን የግድ እንዲዘምሩና የዛ ቋንቋ ባለቤት የሆነን አስተዳደር ሠንደቅ ዓላማ ማውለብለብ ግዴታ አለመሆኑን ከሌሎች አገራትም ሆነ ከራሳችን ተሞክሮ ተመልክተናል፡፡ በነገራችን ላይ የቋንቋ ትምህርት የሚሰጠው በክፍል ውስጥ ሲሆን መዝሙር ደግሞ በአደባባይ ነው የሚዘመረው፡፡ እውነታው እንደዛ ከሆነ የኦሮሚያ ካሩከለምስ ቢሆን እንዴት ብሎ ነው የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት መሰጠት ሲጀመር መዝሙሩ ይዘመራል፣ ሠንደቁም ይሰቀላል የሚለው?

የቀደመውን ትተን ባለፉት 30 አመታት ተግባራዊ በሆነው ሥርዓተ ትምህርት የአማርኛ ቋንቋ አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል የሕዝብ መዝሙር እየተዘመረ ሠንደቅ ዓላማው እንዲውለበለብ አልተደረገም፡፡ በዚህ አይነት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የሚጠቀመው መዝሙርና ሠንደቅ ዓላማም ይህንኑ ነው ማለት ነው፡፡ ይኸ ነገር በሚገባ ተጠንቶ የእርምት እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባም በዚህ አጋጣሚ ለአማራ ክልል አመራች ምክሬን እለግሳለሁ፡፡ 

ይህም ሆኖ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአማራ ክልል የሕዝብ መዝሙር እንደማይዘመር አውቃለሁ፡፡ ለምን ሲባል በመዝሙሩ ውስጥ አንድ ሀረግ ለአማራነት ክብር ስለሚልና እኛ ደግሞ ኦሮሞ ስለሆን አንዘምርም ብለዋል በሚል ነው፡፡ ሌላው ግምት ውስጥ መግባት ያለበት የመዝሙሩ መልዕክት እና የሠንደቅ ዓላማው ትርጉም ኢትዮጵያን የማይገልጽ፣ ልዩነትን ሰባኪ ብቻ ሳይሆን ያለፉትን ስርአታት መልካም ተግባራትና እሴቶች ሁሉ በጅምላ የሚኮንን የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ለመገንዘብ ይረዳ ዘንድ ከኦሮሚያ ክልል መዝሙር ውስጥ የተወሰኑ ስንኞችን ቀጥሎ ማስቀመጥ ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

… የመቶ አመት ዕድፍ በደማችን አጠብንልሽ፣

በብዙ ዕልፍ ዕልቂት ባንዲራችንን ከፍ አደረግንልሽ፣

ደስ ብሎናል ደስ ይበልሽ፡፡

ይኸ አሳፋሪ ሁኔታ በእጅጉ ያበሳጨው ተወዳጁና ታዋቂው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሰሞኑን በአሜሪካን አገር እያቀረበ ባለው የሙዚቃ ኮንሰርት ዝግጅት ላይ ስለአዲስ አበባ የሚከተለውን ልብ የሚነካ ስንኝ አቀንቅኖ የብዙዎቻችን ልብ በሀሴት እንዲሞላ አድርጓል፡፡

አፍሪካን አክሎ የተሰፋው ልብሱ፣

ኢትዮጵያን አክሎ የተሰፋው ልብሱ፣

ከምኔው ከምኔው ጠበበሽ ቀሚሱ፡፡

አዲስ አበባ ነበር የጥንቱ ስምሽ፣

ሁሉ አገርሽ ነበር የጥንቱ ስምሽ፣

አሁን ከምንጊዜው የእኔ ነሽ አሉሽ?

ማጠቃለያ

ቋንቋን ማስተማር በራሱ እንደ ችግር ሊታይ የሚችል ተግባር አይደለም፣ ሠንደቅ ዓላማ ማውለብለብም ሆነ መዝሙር መዘመርም እንዲሁ፡፡ ሆኖም እነዚህን ነገሮች በግድና በጫና እንዲፈጸሙ የሚደረግ ሲሆን ግን በአፍንጫየ ይውጣ የሚል ምላሽ እንዲሰጥ ይገፋፋል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየው ሁኔታም የዚህን መርህ ትክክለኛነት ያረጋግጣል፡፡ የቋንቋ ትምህርትን ከአንድ አካባቢ መዝሙርና ሠንደቅ ዓላማ ጋር ለማያያዝ መሞከር ደግሞ ከስህተትም በላይ የድንቁርና ጥግ ይመስለኛል፡፡ 

ስለሆነም እነዚህ በማን አለብኝነት ስሜት ውስጥ ሆነው ፍላጎታቸውን ሕዝብ ላይ ለመጫን የሚያደርጉትን ጥረት አቁመው ሕዝብን ይቅርታ እንዲጠይቁ የሚያደርግ ስራ መስራት ከሁሉም አዲስ አበቤ የሚጠበቅ ሲሆን ይህን በማድረግም ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነሱው እንደሚሆኑ ለማስገንዘብ ጥረት ማድረግም መልካም ነው እላለሁ፡፡ በሌላ አባባል ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል እንደሚባለው አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመጠቅለል የሚደረገው ጥረት አስቀድሞ የከሸፈና የማይሳካ መሆኑን በተግባር ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

    

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. በማግባባት እንጂ በግድ ማንም ማንንም አያዝም። በዚሁ ጒዳይ ላይ ጥሩ ጽሑፍ እዚህ ላይ አንብቤአለሁ፤
    ethiopianchurch.org/en/essay1/308-%E1%89%8B%E1%8A%95%E1%89%8B%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%89%8B%E1%8A%95%E1%89%8B.html

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here