
ቦርከና
በደቡብ አፍሪካ የተደረገው የሰላም ስምምነት “ለወደፊት የኢትዮጵያን ደህንነት የሚያጎለብት፣ የሚመሰገን አጠናካሪ ርምጃ ነው ብለን አናምናለን”
በሚል ስለስምምነቱ ያላቸውን መልካም እይታ ያካፈሉ ስምንት ያህል በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመብት ተሟጋች ድርጂቶች ቢያካፍሉም እሱን ተከትሎ በናይሮቢ የተደረገው ስምምነት ችግር አንዳለበት ጠቁመዋል::
በተለይም ጉዳዮ ከወልቃይት ጋር በተያያዘ ለወያኔ ምኞት መንገድ ይጠርጋል የሚል ስጋት በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወልቃይት ጉዳይ ላይ በግልጽ አቋማቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል::
የተካከልንን ድርጂቶቹ የጻፉት ደብዳቤ የአማርኛ ቅጂ ከታች አቅርበነዋል :
“ታህሳስ 12 /2015
ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ
ጉዳዩ፦ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግን ይመለከታል
ክቡርነትዎ
እኛ በዚሀ ደብዳቤ ላይ ፊርማችንን ያስቀመጥን፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የምንጥር፣ ለፍትህና ለሰብአዊ መብት የምንታገል የውጭ አገር ኗሪ (ዳያስፖራ) ተሟጋች ድርጅቶች፣ ህወሓት በወልቃይት ህዝብ ላይ ላደረሰው ከፍተኛና አስቃቂ በደል ምላሽ እንዲሠጥ ይህንን አስቸኳይ አቤቱታ አቅርበናል፡፡
በህዳር 2014 በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መሀከል በደቡብ አፍሪቃ በፕሪቶርያ የተደረገው ስምምነት ብሩህ የሆነ፣ ለወደፊት የኢትዮጵያን ደህንነት የሚያጎለብት፣ የሚመሰገን አጠናካሪ ርምጃ ነው ብለን አናምናለን፡፡
ህወሓት፣ ለንፁሐን አረጋዊያን፣ ህፃናትና እናቶች በጀምላ መጨፍጨፍ፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል፣ በአፋርና በአማራ በሺዎች ለሚቆጠሩ የትምህርትና የጤና ተቋማት መውደም ተጠያቂ ሲሆን፣ በብሔራዊ መከላከያ ሀይላችን፣ በአማራና በአፋር ልዩ ሀይልና በፋኖ በማያዳግም ሁኔታ ድል ተመቷል፡፡ በህወሓትና በደጋፊዎቹ አማካኝነት የተደረገውን አውዳሚ ጦርነት ማስቆም የተቻለበትንና ህወሓትን ትጥቅ የሚያስፈታና ታጣቂ ሚሊሻዎቹን እንዲበተኑ የሚያደርገውን ይህን ስምምነት በአሸናፊነት ያስገኙትን የኢትዮጵያ ተወካዮች የተቃና ውጤት በደስታ የምንቀበለው ጉዳይ ነው፡፡
ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመከላከያ አዛዦች በኬንያ ናይሮቢ ከህወሓት ተወካዮች ጋር በህዳር 2014 የተፈራረሙት ስምምነትና የሰጡት መግለጫ በደቡብ አፍሪካ በተደረገው ስምምነት የተገኘውን የዕፎይታ ስሜት የሚቀለብስ፣ ያልተጠበቀ፣ አሳዛኝ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሰምምነት የህወሓት ሀይሎችን ትጥቅ ማስፈታት ከኤርትራ መከላከያ ሀይል መውጣት እና የአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ከትግራይ መውጣት ከሚል ሁኔታ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፡፡
በዚህ አቤቱታ ላይ ፊርማችን ያስቀመጥን ተቆርቋሪዎች፣ ሁኔታውን ተግባራዊ ለማድረግ በወጡት በነዚህ አዲስ አንቀፆች ላይ ጥልቅ ሰጋት አለን፡፡ ይህም፣ ህወሓትና አንዳንድ የአለም አቀፍ ህብረተሰብ አባላት “ምዕራብ ትግራይ” ብለው የሚጠቅሷቸው የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት የአማራው ህዝብ ጥንታዊ እርስቶች፣ በህወሓት በጉልበትና አስከፊ በደል በመፈፀም ከሀያ ሰባት አመታት በፊት የተነጠቁ አካባቢዎቸ ላይ አንቀፆቹ ሊያስከትሉ በሚችሉት ተፅዕኖ ላይ ነው፡፡ ታሪክ በመረጃነት የሚመሰክረው፣ እነዚህ ቦታዎች፣
ህወሓት በ1983 ዓ.ም ሥልጣን ላይ ከወጣና በጉልበትና በህገወጥ መንገድ በመንጠቅ ወደ ትግራይ ከማካለሉ በፊት የበጌምድር (ጎንደር) አካሎች ነበሩ፡፡
ህወሓት እነዚህን ቦታዎች በጉልበት ነጥቆ የወሰደው ከሱዳን ጋር የውጭ ወይም የአለም አቀፍ ድንበር በመፍጠር የታላቋ ትግራይ ምስረታን ህልም ለማሳካት እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በነዚህ ቦታዎች ባለቤትና ቀዳሚ ኗሪ የሆነው የዐማራው ህዝብ ከሚኖርበት ቦታ ለማፅዳት በ1990ዎች ሆን ተብሎ እየታፈሰና እየተጋዘ ያለምንም ምክንያት በጀምላ የተጨፈጨፈና አሰቃቂ ኢሰብአዊ ዘግናኝ በደል የደረሰበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ አዛውንቶች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ የህብረተሰቡ ታላላቅ ሰዎች፣ የተማሩ ሰዎች፣ ወንዶችና ሴቶች የለማ መሬትና የውጭ ድንበር ብቻ በሚፈልገው የፋሺስቱ ህወሓት ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ በአስር ሺዎቸ የሚቆጠሩ ዜጎች
መተዳደሪያቸውን አጥተዋል፣ በዙዎች ደግሞ በአስከፊ ሁኔታ ተሰደው በሱዳን አና በሊቢያ በረሃዎች አልቀዋል ፡፡ ደግነቱ፣ የወልቃይት ህዝብ፣ ማንነቱን ለማሰረገጥ፣ ነፃነቱን ለመመለስና ደሀንነቱን ለማስጠበቅ ትውልድ ካስቆጠረ የብዙ አመታት መራራ ትግል በኋላ የአባቶቹን እርስት ማስመለስና የማንነት መብቱን ማስከበር ችሏል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ጭብጦች መሠረት በማድረግ፣ በቅርብ ጊዜ ለኢትዮጵያ ፓርላማ እነዚህ በመራር ትግል የተገኙና የማንነት ማስከበርና የተመለሱ ስተራቴጂክ የወልቃይት ህዝብ ጥንታዊ ርስቶች በሚመለከት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት ንግግር፣ ባለፉት አራት
አስርተ አመታት ህወሓት በህዝቡ ላይ ባደረሰው አሰቃቂ በደልና የዘር ማፅዳት ወንጀል ላይ ሰለሚወሰደው ርምጃና መፍትሔ አወዛጋቢና አጠራጣሪ ጥያቄዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
በዚህ ምክንያት በከፍተኛ አንክሮ የሚከተሉትን አንዲያደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን።
1. ወልቃይትና አካባቢውን በተመለከት ይደረጋል የሚባለውን ህዝበ ውሳኔ ጭምጭምታ ማስቆም፡፡ በህወሓት የተጠየቀውን የህዝበ ውሳኔ ሂደት መቀበል ወይም ተግባራዊ ማድረግ የአማራ ማንነቱን ለማረጋገጥ ለዘመናት በመታገል የትውልድ መስዋዕትነት በከፈለው የወልቃይት ህዝብ የፍትህ ጥያቄ ላይ አሰኮናኝ የሆነ የፍርደ ገምድል ውሳኔ ነው፡ ፡ ህወሓት ወልቃይትና አካባቢውን በሀይል ነጥቆ ከመውሰዱ በፊት በተደረገ ግልፅ የህዝብ ቆጠራ ከኗሪው ህዝብ 80 በመቶው (%) በላይ አማራ ሲሆን 6 ከመቶው ደግሞ ትግሬ የነበረ መሆኑ የማያወዛግብ መረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ወልቃይትን መልሶ የሚያናጋ የፖለቲካም ሆነ የፖሊስ ውሳኔ እንዳያደርጉ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ወልቃይትን ከአማራ ርስትነት ማስወጣት በኢትዮጵያ ህልውና ፣ የድንበር ባለቤትነት፣ የሀገር ደህንነትና ሉአላዊነት ላይ መመለሻ የሌለው ጥፋት የሚያሰከትል አደጋ ነው፡፡ ሰለዚህ፣ የወልቃይት ጉዳይ መልሰው የማይሻገሩት ቀይ መስመር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገራቸው በሚታገሉ፣ ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩና የሚሟገቱ ኢትዮጵያውያን በተለይም በአማራው ህዝብ ልብ ውስጥ በፅኑ የተያዘ አቋም ነው፡፡
2. ለረዥም ጊዜ ለዘገየው ለወልቃይት ህዝብ የፍትህ ጥያቄ መልስ ይሰጥ፣ መልሶ ማቋቋም መጀመር፤ በውጭ የተሰደዱት ወደ ሀገራቸውና ወደ ትውልድ ቦታ ርስታቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ ለደረሰባቸው በደል ካሳ በመክፈል፣ ለረዥም ጊዜ የዘገየባቸውን መቋቋሚያና ርዳታ ከማድረስ ጋር የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት እንዲረጋገጥ የሚደረገውን ውሳኔ በፍጥነት መወሰን፡፡
በአንድ ወቅት አርስዎ በሚገባ እንዳስቀመጡት፣ በክልሎች መሀከል ያሉ ደንበሮች የተፈጠሩት ለአስተዳደር ብቻ ነው። በርግጥ፣ በኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መሠረታዊ ከሆነ፣ የትግራይ ሰዎችም ሆኑ ወይም ማንኛው ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጣ ዜጋ በወልቃይትም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል መኖርና ራሱን ማበልፀግ መብቱ ነው፡፡ ከህወሓት የፀዳችው ኢትዮጵያም ይህንን መሆንና ለመሆን መታገልም አለባት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ
ዋናው መሠረታዊ ነገር፣ በህገወጥ በጉልበት ተነጥቀው የተወሰዱ የአስተዳደር አካባቢዎችን ወደ ነበሩበት ቀዳሚ ይዞታቸው በመመለስና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ወይም ቋሚ መፍትሔ ለማምጣት ለረዥም ጊዜ የተጠበቀውን የህገ መንግሥት ማሻሻያ ማዘጋጀት ነው፡፡ የህገ መንግሥት ማሻሻያው ተግባራዊ መሆን፣ በብሔረሰቦች መሀከል በደንበር ምክንያት ለሚነሳው ባላንጣነትና በሌሎች አካባቢዎች በሚኖሩ በቁጥራቸው አነስ ላሉ የህብረተሰቡ አባላት፣ በተለይም የአማራ ተወላጆች፣ እየተመነጠሩ ባሉበት ቦታዎች ላይ የተፈጠረው ዜጎች በሀገራቸው መኖር ላልቻሉበት ሁኔታ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል፡፡
የርስዎ አስተዳደር፣ ብቸኛ የሆነውን ፍትሐዊና ቀናውን አቋም በመያዝ ከዚህ ቀደም የነበረውንና አሁን በወቅቱ ያለውን የወልቃይት በአማራ አስተዳደር ስር መሆኑን በይፋ እንደሚያስታውቁ ፅኑ እምነታችን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ ግን ውጥረቱን የሚያባብስና ኢትዮጵያን እንደ አንድ የተረጋጋች አገር የመቀጠል ህልውናዋን የሚያናጋ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎች
ልሳነ ግፉአን – Voice of the Victim’s Org. Ethiopian American Development Council • Ethiopian Advocacy Network • Ethiopian American Civic Council • Ethiopian Public Diplomacy Network • Ethio-Canadian Network for Advocacy and Support • Gondar Hibret for Ethiopian Unity • Global Ethiopian Scholars Initiative “
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ