spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትአዲስ አበባ ወይስ አዲስ አባባ? (ክፍል ሦስት )

አዲስ አበባ ወይስ አዲስ አባባ? (ክፍል ሦስት )

Addis Ababa _ Ephrem 3

                              

ክፍል ሦስት 
ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)   

አዲስ አበባ ውስጥ ገዳም ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ አርበኞች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመባል የሚጠራ አንድ የቆየ ትምህርት ቤት አለ። እዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ በአፋን ኦሮሞ ከሚማሩ ተማሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ከአካቢቢው የኦሮሚያ ክልል ከተማዎች እየተሰበሰቡ ጧት በአውቶቡስ ተጭነው መጥተው ማታ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ መጡበት ተመልሰው የሚሄዱ ህፃናት ናቸው። ይህ ለምን አስፈለገ? የኛ ፍጹም የተሳሳተና ማህበረሰብን የሚያጋጭ አላማ እንዲሳካ ለምንድነው ህፃናቱን የምናንገላታው? አናስብላቸውም እንዴ? እነዚህ በአውቶቡስ ተጭነው ወደ አርበኞች ትምህርት ቤት የሚመጡት ተማሪዎች የመጡበት አካባቢ ትምህርት ቤቶች አሉኮ፣ለምንድነው እዚያው ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማይማሩት? ተማሪዎቹን፣አስተማሪዎቹን፣መዝሙሩንና ባንዲራውን ሁሉንም ከኦሮሚያ ክልል አምጥተን አዲስ አበባ ውስጥ ልጆቻችንን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያስተማርን ነው ብሎ ነገር አለ እንዴ? ትንኮሳና ጠብ ያለሽ በዳቦ ካልሆነ በቀር የዚህ ፕሮጀክት አላማ ምንድነው? እንዲህ አይነቱን ፈር የለቀቀ አካሄድ መጠየቅ የአዲስ አበባ ህዝብ መብቱ መሆኑ እየታወቀ ለምንድነውሱ በነጋ በጠባ የአዲስ አበባ ወላጆች ልጆቻችሁን ካልመከራችሁ ተብለው የሚወቀሱት? ማነው መመከር ያለበት? ለልጆቹና ለራሱ መብት የተከራከረው የአዲስ አበባ ወላጅ ነው ወይስ ከምንም ግዜም በላይ ሰላምና መረጋጋት በሚያስፈልገን ግዜ ማህበረሰብን የሚያጋጭ አጀንዳ ይዘው የመጡ ኃይሎች? 

ባንዲራ ትልቅ ትርጉም፣ ታሪክና ትርክት የተሸከመ የአንድን አገር ህዝብ የሚያስተሳስር ትልቅ አርማ ነው። ባንዲራ ድንበር ላይ ሲሰቀል፣ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ሲሰቀልና ትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ ሲሰቀል የየራሱ ትርጉም አለው። የኢትዮጵያ ባንዲራ ሞስኮ ውስጥ ተሰቅሎ ስናይ ባንዲራው የተሰቀለበት ቤት ወይም ቦታ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው ወይም ቦታው በአንድ ነገር ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው ማለት ነው። በሁለት አገሮች ድንበር ላይ ባንዲራ ሲሰቀል ከባንዲራው ወዲህ የኛ መሬት ነው፣ከባንዲራው ወዲያ የናንተ መሬት ነው ማለት ነው። በ1928 ዓ.ም. ጣሊያን ባንድራችንን አውርዶ ባንዲራውን ሲሰቅል በኛ ቁጥጥር ስር ናችሁ ማለቱ ነበር፣ ለዚህ ነው አርበኞች ከየቦታዉ ተሰባስበው ባንተ ቁጥጥር ስርማ አይደለንም ብለው አምስት አመት አምርረው የተዋጉት። የባንዲራ ትርጉም፣ታሪክና ትርክት ከህዝብና ከቦታ ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው። ለምሳሌ፣አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ድንበር ላይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ቢተከል ምንም ትርጉም የለውምና የሁለቱም ህዝብ የመጀመሪያ ጥያቄ የማን ባንዲራ ነው፣ ለምን እዚህ ተተከለ የሚል ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያንም ባንዲራችንን ኢትዮጵያ ውስጥ ስናየውና በውጭ አገሮች ስናየው የሚሰማን ስሜት የተለያየ ነው። እኔ ውጭ አገር ኖርያለሁ፣ ባንዲራዬን ሳይ የኢትዮጵያ ካርታ አይኔ ላይ ይመጣል፣ደሞም ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ባንዲራዬን ሳይ ግን መጀመሪያ የሚታየኝ ነጻ አገር ዉስጥ መሆኔና ከነጻነቱ ጀርባ የተከፈለልኝ መስዋዕትነት መኖሩ ነው እንጂ ውጭ አገር የሚሰማኝ ስሜት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኜ አይሰማኝም። ይህ ሁሉ እውነት የሚነግረን ባንዲራ በየቦታው ወይም አለቦታው የሚሰቀል አርማ አለመሆኑን ነው።

በአባቱ ኬንያዊ የሆነ ሰው በአለማችን ኃብታሟና ኃያሏ አገር የአሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት በሆነበት፣ በአንድ ወቅት ግማሽ አለምን የገዛችው እንግሊዝ ውስጥ የህንድ ዝሪያ ካላቸው አባትና እናት የተወለደ ሰው እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚመራበትና ትናንት እኛ አገር ሆነን ታሪክ ስንሰራ ከተለያዩ አገሮች ተሰድደው ሄደው አገር የሆኑ አሜሪካና ካናዳን በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ሳይሆን ሰው በመሆናቸው ብቻ ሙሉ መብት፣ክብርና እውቅና በሚያገኙበት አለም ውስጥ እየኖርን፣ ለምንድነው እኛ ኢትዮጵያዊያን እዚሁ አገራችን ውስጥ ኦሮሞ፣አማራ፣ትግሬ፣ሱማሌ፣ሲዳማ ወዘተ እየተባባልን በመካከላችን የልዩነት አጥር የምንሰራው? ለምንድነው የአገራችንም የአፍሪካም መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን የኛ ናት እየተባባልን እርስ በርስ የምንባላው? ለምንድነው የአንድ አገር ህዝብ የሚያሰኙንን ብሔራዊ ምልክቶች፣ብሔራዊ ባንዲራና ብሔራዊ መዝሙር ትተን የየራሳችንን መዝሙር፣ምልክትና ባንዲራ ብቻ ይዘን አጠገባችን ካለው ኢትዮጵያዊ ወንድማችንና እህታችን የተለየን መሆናችንን ለማሳወቅ ኃይልና ጉልበት እስከመጠቀም ድረስ የምንሄደው? 

የአዲስ አበባ ህዝብ በታሪኩ የሚያውቀው አንድ ባንዲራ ብቻ ነው፣ አገሬ የሚለውም አንድ ኢትዮጵያን ብቻ ነው። ከ75% በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ማንነቱን ሲገልጽ እራሱን ኦሮሞ ነኝ አይልም። አዲስ አበባ እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ከተማ ናት። አዲስ አበባን በአስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚያስተሳስራት ቀጭንም ወፍራምም ክር የለም። ታዲያ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ውስጥ ይሰቀል የሚባለው ለምንድነው? ለሁላችንም የሚበጀው ይህንን ለምንድነው የሚለውን ጥያቄ አግባብ ባለው መልክ መመለስ ነው። በመልሱ ከተስማማን ተስማማን፣ ካልተስማማን ግን ሁላችንንም የሚያቅፈው አገራዊ የምክክር ጉባኤው በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ እስኪወስን ድረስ የሁላችንም የሆነውንና በፍጹም የማያጨቃጭቀንን የአገራችንን ብሔራዊ ባንዲራ መስቀል ነው የሚሻለው እንጂ የጉልበትና የኃይል ሩጫ የትም አያደርሰንም!

ከአንድ አመት በፊት የተጀመረውንና ባለፉት ሁለት ሳምንታት እየተባባሰ የመጣውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የ“ባንዲራ ስቀሉ አንሰቅልም” ጉዳይን በተመለከተ አንዳንድ ሃላፊነት የሚሰማቸው አካላት ጉዳዩን በውይይት መፍታት ይቻላል በሚል ከአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቢሮ ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር ያደረጉት ተከታታይ ሙከራ የትምህርት ቢሮው አስዳደር የተላከለትን ደብዳቤ አልቀበልም በማለቱ ሳይሳካ ቀርቷል። ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ደብዳቤ ጽፎ ደብዳቤው ለአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት በፓርቲው መዝገብ ቤት ሰራተኛ በኩልም በፖስታ ቤት በኩልም ሲላክ፣ ጽህፈት ቤቱ ይህ ጉዳይ እናንተን አያገባችሁም በማለት ደብዳቤውን አልቀበልም ብሏል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መሪዎችና ሰራተኞች ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሊመጡ ይችላሉ፣ አንድ መዘንጋት የሌለባቸው ጉዳይ ግን ደሞዛቸውን የሚከፍለው የአዲስ አበባ ግብር ከፋይ ነው። ስለዚህ የዚህን ግብር ከፋይ ህዝብ ጉዳይ በተመለከተ ሊያናግራቸው ከሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲን ያክል ቁልፍ ባለድርሻ ጋር ቀርቶ ማንኛውንም የከተማዋን ነዋሪ ጥያቄ የመቀበል ግዴታ አለባቸው። እነዚህ አዲስ አበባ ውስጥ እየኖሩ፣የአዲስ አበባ ህዝብ ደሞዛቸውን እየከፈለ የሚያኖራቸው ሰዎች ግን ታማኝነታቸው ለሚኖሩበት ከተማና ለሚያኖራቸው ህዝብ ስላልሆነ፣ ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታየው ቀውስ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት እንነጋገር ብሎ ሲጠይቃቸው አያገባችሁም ብለው የተላከላቸውን ደብዳቤ አንቀበልም ብለዋል።  

አንድን በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመና አዲስ አበባ ውስጥ በ23ቱም የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ ድርጅታዊ መዋቅር ያለውን ፓርቲ በአዲስ አበባ ጉዳይ አያገባችሁም ወይም የአዲስ አበባ ጉዳይ አይመለከታችሁም ማለት ለኔ የሚነግረኝ ይህንን ያሉ ሰዎች የሚያስቡት በጫማቸው ልክ መሆኑን ነው፣ እሱም እኔ ቸር ሆኜ ነው። ህግ ስለሚገዛንና፣ ስነስርዓትና ስነምግባር ስላለን ነው እንጂ፣እነዚህ አያገባችሁም ባዮች እናንተም አያገባችሁም ቢባሉ ምን ሊሉ ነው? ደሞስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያገባው በሥልጣን ላይ ያለው ወገን ብቻ ነው እንዴ? ችግሩ ጭንቅላታችን በብሔር ፖለቲካ ሲሞላ ባንዲራውን፣ገንዘብ የምናስቀምጥበትን ባንክ፣ ዕቃ የምንገዛበትን ሱቅ፣የምንኖርበትን ሰፈር፣ ጓደኝነትን ባጠቃላይ ገሃዱን አለም በብሔር መነጽር ብቻ ነው የምንመለከተው። ይህ ሁሉንም ነገር ከራሳችን ብሔር አኳያ መመልከታችን ወይም መጥበባችን ትልቋን ኢትዮጵያንም በብሔራችን ልክ አጥብበን እንድናያት ስላደረገን  ሚዛናዊነታችንና አርቆ ማሰባችን ድራሹ ጠፍቶ ነው እንጂ፣ የምንለያየውኮ በአገር ጉዳይ ላይ በተሰጠን ግዜያዊ ላይ ኃላፊነት ነው እንጂ፣ እያንዳንዱ የአገር ጉዳይማ እኩል ይመለከተናል፣ እኩል ያገባናል።

ይህ የ”አያገባችሁም” ትዕቢት በፍጥነት ተንፍሶ ችግሮቻችንን ተነጋግረን በጋራ የማንፈታ ከሆነ፣አንዳችን አገራዊ የምክክር ጉባኤውን እየጠበቅን ሌላው የሚፈልገውን በጉልበት እያስፈጸመና የማይፈልገውን በጉልበት እያስቆመ አንድ ላይ እንደ አገር መቀጠል አስቸጋሪ መሆኑን “አያገባችሁም” ባዮች ሊገነዘቡ ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ጎን ለጎን አብረን የምንኖረው እኔ አንተን ባንተ ጫማ ውስጥ ሆኜ ሳይህና አንተም እኔን በኔ ጫማ ውስጥ ሆነህ ስታየኝ ነው እንጂ፣ ጠመንጃ ስለያዝክ እኔን ብቻ ስማኝ ብትለኝ እንደ ሙሾ አውራጅ ስትጮህ ትከርማታለህ በፍጹም አልሰማህም! 

ዛሬ እጅግ በጣም በሚያሳዝን መልኩ በአዲስ አበባ ጉዳይ “እኛ” እና “እነሱ” የሚባባሉ ሁለት ቡድኖች ተፈጥረዋል፣ አንደኛው ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ መኖር እንጂ ሌላ ምንም ነገር አይመለከተውም- ይህ ቡድን በሌላው ቡድን እይታ አዲስ አበባ ውስጥ መኖር ይችላል፣ መብቱን መጠየቅ ግን አይችልም ወይም የዚህ ቡድን መብት የሚለካው በሌላኛው ቡድን በጎነት ነው። ሁለተኛው ቡድን ግን አዲስ አበባ ውስጥ መኖርም በአዲስ አበባ ጉዳይ መወሰንም ይችላል፣ ደሞም አዲስ አበባ ውስጥ የፈለገውን ነገር የማድረግ ሙሉ መብት አለው። እንዲህ አይነት ፍጹም የተዛባ ግኑኝነት እኛንም አገራችንንም ወደ ግጭት ይወስዳል እንጂ ለማናችንም አይበጅም።

ይህ ከሰሞኑ እንጦጦ አምባ ት/ቤት የተጀመረው የባንዲራችን “ይሰቀል አይሰቀልም” ግብግብ ከሽሮ ሜዳ ወጥቶ ወደ ተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እየተዛመተ ነው። ሽሮ ሜዳ፣ገዳም ሰፈር፣ ቀጨኔ፣ቂርቆስ፣ፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ልደታና መርካቶ ባንዲራን በተመለከተ ረብሻ የተነሳባቸው አካባቢዎች ናቸው። እነዚህን አካባቢዎውች በሚገባ ላስተዋለ ሰው ቦታዎቹ የሚናገሩት የራሳቸው ታሪክ አላቸው። ይህ አርብ ታህሳስ 22 ቀን በ2104 ዓም አቃቂ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጀመረው የባንዲራ ረብሻ ከሰሞኑ እንደገና አገርሽቶበት፣ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ህጻናት ተማሪዎች፣ ወላጆችና ፖሊስ በየቀኑ እየተጋጩ ነው። ይህ የሚያሳየን የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መሰቀል አለበት መዝሙሩም መዘመር አለበት የሚሉ ኃይሎችና፣ የለም አዲስ አበባ ውስጥ መሰቀል ያለበት ያለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ብቻ ነው የሚሉ ኃይሎች በፍጹም ሊግባቡ እንዳልቻሉ ነው። በጠመንጃ፣ በዱላና በማስፈራሪያ ተማሪዎቹንና ወላጆቻቸውን ማሳመን በፍጹም እንደማይቻል ወይም ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው ቁጭ ብሎ በመነጋገር ብቻ መሆኑን የፌዴራሉ መንግስትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤትም በውል ሊረዱት ይገባል። 

ባህላችን እንዲረሳ ተደርጓል፣ ማንነታችን ተንቋል፣ትምህርት ቤት ገብተን የተማርነው በግድ በተጫነብን ቋንቋ ነው ብለን ከግማሽ በላይ ዕድሜያችንን ለእኩልነት የታገልን ሰዎች ዛሬ በተራችን በጉልበት መዝሙራችንን ካልዘመራችሁ ባንዲራችንን ካልሰቀላችሁ እያልን ህዝብን የምንረግጥ ከሆነ፣ እርግጫ የትናንትናዋን አህያ ከጅብ እንዳላስጣላት የዛሬዋንም እንደማያስጥላት ማን በነገረን! ችግሩ መዶሻ የያዘ ሰው ሁሉም ነገር ሚስማር ይመስለዋል። የዛሬዎቹ ባለመዶሻዎች የሚገባችሁ ከሆነ ባለፉት ሃምሳ አመታት ሁላችንም መዶሻ የመያዝ ተራ ደርሶን ከኛ ውጭ የሆነውን ሁሉ እንደሚስማር ተመልክተናል፣ በዚህ የተነሳ ዛሬ የሁላችንም ፊት ጠባሳ በጠባሳ ነው። እንደ አገርና እንደ ህዝብ የሚበጀን አንዳችን የሌላችንን ጠባሳ አክመን ስናድን ነው እንጂ፣ አሁንም እጃችን ላይ መዶሻ አለ ብለን ሚስማር ብቻ የምንመለከት ከሆነ የሁላችንም አይን ይጠፋል። ያኔ ስለዋቃ ጉራቻም ስለሚካኤልም ብንል የሚሰማን አይኖርም!

የዜግነት መብታችንን አክብሩ፣በህይወት የመኖር መብታችን ይከበር፣ሰላምና ጸጥታ አስከብሩልን፣ እያልን ስንጮህ ጆሮ ዳባ ልበስ ለሚሉን ባለሥልጣኖች፣ምርጫ በመጣ ቁጥር ድምጻችሁን ስጡን እያሉ ሲያማልሉን እምቢ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ የቅጣት ድምጽ መስጠት እንዳለም የምናስተምርበት ግዜ እየመጣ ነው። አዲስ አበቤ ሆይ ስማ፣ዛሬ እየከፈልክ ያለኸው ዕዳ በግንቦት 2013 አንተው እራስህ ያበደርከውን ነው። የሚገባህ ከሆነ ወይም ገብቶህ ከሆነ አበዳሪውም ዕዳ ከፋዩም አንተው ነህና ንቃ፣እወቅ ደሞም ሌላ ግንቦት ይመጣልና ካሁኑ ተዘጋጅ! ዛሬ ጨቅላ ልጆችህን በየትምህርት ቤቱ እየሄዱ ባንዲራችንን ካልሰቀላችሁ እያሉ ሲያሰቃዩ ምነው ብለህ ስትጠይቃቸው አርፈህ ተቀመጥ የሚሉህ ሰዎች፣ ትናንት አንተኑ እኛን ለመምረጥ ብርድና ሙቀት ሳይበግረው ከጧት እስከማታ ቆሞ ጠበቀ እያሉ የሚመጻደቁ ሰዎች ናቸው። ባለሥልጣኖቻችን በኛ ላይ ያላቸውን ሥልጣን የምናከብረው ንብረታችንን እስከጠበቁ፣ መብታችንን እስካከበሩና እስካስከበሩ እንዲሁም ነጻነታችንን እስካልደፈሩ ድረስ ብቻ ነው። እነዚህን እሴቶች ሁሉ የቀሙን ግዜ ግን እኛ ነጻ ነን፣ እነሱ ናቸው እስረኞች የሚሆኑት። የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም አይነካንም ያሉ ባለሥልጣኖቹ በ1966፣በ1983 እና በ2012 አጃቸውን ተጠፍረው እስር ቤት ሲገቡ አይቷል። 

አዲስ አበባ ላለፉት 133 አመታት የአገራችን ዋና ከተማ ሆና ቆይታለች፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም መዲና ናት። ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ የወደፊት ዕድል ላይ የሚወሰን ምንም አይነት ውሳኔ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ውሳኔ ነው እንጂ የአንድ ብሔር፣ የአንድ ክልል መንግስት ወይም የአንድ ፓርቲ ውሳኔ ሊሆን አይችልም! የአዲስ አበባ ከተማን የማንነት፣ የባለቤትነትና የወደፊት አወቃቀር በተመለከተ የሚወሰኑ ዉሳኔዎች አሁን ከተማዋን ለሚያስተዳድረው አካልም በፍጹም መተው የለበትም! የአዲስ አበባ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነውና ውሳኔውም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ውሳኔ መሆን አለበት። ይህንን እውነት ረግጠን የአገርን አንድነትና አብሮነት የሚጎዳ ውሳኔ ብንወስን ውሳኔው እኛንም አገርንም ይጎዳል። ባለፉት አራት አመታት ከሰራናቸው ብዙ ስህተቶች መማር አለብን፣ ሁልግዜ የራሳችንን እግር በጥይት እየመታን ህክምና ፍለጋ መሯሯጥ የጤናማ ሰው ምልክት አይደለም! 

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተጀመረው የ“ባንዲራችንን እንስቀል አትሰቅሉም” ረብሻ የህዝብን ጩኸት የሚሰማ ባለሥልጣን በመጥፋቱ ሁለተኛ ሳምንቱን ጨርሶ ሦስተኛ ሳምንቱን እየያዘ ነው። ይህ የአዋቂና የህጻናት ግብግብ አዲስ አበባ ውስጥ ማን ህጻን ማን አዋቂ እንደሆነ በግልጽ እያሳየን ነው። የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ አዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መሰቀል አለበት የሚለው ፕሮጀክት ባለቤት ማነው? የዚህ ፕሮጀክት ባለቤት ለምንድነው ባንዲራው እንዲሰቀል የሚፈልገው? ተማሪዎችና ወላጆችስ ለምንድነው እንዳይሰቀል የሚፈልጉት? ለምንድነው በተማሪዎቹ ወላጆች የተመረጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዱላና ጠመንጃ የያዙ ፖሊሶችን ወደየትምህርት ቤቶቹ ከመላክ ከተማሪዎቹ፣ከተማሪዎቹ ወላጆችና ባጠቃላይ ከከተማው ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ይህንን ችግር በውይይት የማይፈታው? ወሮ አዳነች የኦሮሚያን ክልል የትምህርት ካሪኩለም እንዳለ ነው ወደ አዲስ አበባ ያመጣነው፣ ካሪኩለሙን ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እንዲመች አድርጎ መለወጥ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች አስተዳደር ስራ ነው ብለዋል። ይህ የሚያሳየን ወሮ አዳነች አዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል በባህል፣በስነልቦና፣በታሪክ አረዳድ፣ በማህበራዊ አደረጃጀትና በአስተዳደር እንደሚለያዩ መገንዘባቸውን ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች የባንዲራውን ፕሮጀክት ለማስፈጸም የተቀመጡ ስለሆነ ካሪኩለሙን እንደማያስተካክሉ ግልጽ ነው። ካሪኩለሙን ለአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ እንዲመች አድርጎ ማስተካከል የከንቲባ አዳነች አቤቤ ስራ ነው፣ ግን እሳቸውም የፕሮጀክቱ ስፖንሰር ስለሆኑ በየመድረኩ የምናያቸው ባንዲራው መሰቀል አለበት፣ መዝሙሩም መዘመር አለበት ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ነው።  ለከንቲባ አዳነች፣ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች፣ ለተማሪዎች፣ ለወላጆች፣ ለከተማዋ ነዋሪና ባጠቃላይ ለሰላም ናፋቂው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎችን ከተማዋ ውስጥ በየቀኑ በግልጽ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለማስቆምና የማህበረሰቡን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ቢጠቀምና፣ የባንዲራውን ረብሻ በውይይት ቢፈታው ነው። ደሞም ሌላ ቢቀር ካርኩለሙ እስኪስተካከል ድረስ ባንዲራውን በጉልበት መስቀል፣ የትምህርት ማስተማር ሂደቱን ማስተጓጎልና አንድ ፍሬ ልጆችን በዱላና በእርግጫ መደብደብ መቆም አለበት። የአዲስ አበባ ህዝብ መረጠን የሚሉትና እሳቸው እራሳቸው የልጆች እናት የሆኑት ወሮ አዳነች ለምድነው ህጻናት ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ካለበት የጸጥታ ኃይል ጋር በየቀኑ ድንጋይ ሲወራወሩ እጃቸውን አጣጥፈው የሚመለከቱት? ወሮ አዳነች በህግ የተሰጣቸው ኃላፊነት የመረጣቸውን ህዝብ መብትና ነጻነት ማስከበር ነው ወይስ ይህ ህዝብ አልፈልግም የሚለው የሌላ ክልል ባንዲራ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰቀል ማድረግ ነው? 

የህዝብን ጩኸት የማይሰሙና የዜጎችን መብት የሚረግጡ ባለሥልጣኖች ከታሪክ የሚማሩት “ከታሪክ አለመማራቸውን” ሆኖ ነው እንጂ፣ በሥልጣን ባልጎና ህዝብን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ መጨረሻው ያማረ ማንም የለም። በጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ተወያይተን በስምምነት ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች  “ግዜው የኛ ነው” እያልን በጉልበት ለማድረግ መሞከር ከግዜ ውጭ እንደሚያደርገን በህዝባዊ አመፅ ከሥልጣን ተባርረውና ጫካ ገብተው የትግራይን ህዝብ ለግፍ፣ለረሃብ፣ ለመከራ፣ ለስደትና ለሞት ከዳረጉት ሰዎች መማር አለብን። ቆሰልኩ ባይ ፈውስ የሚያገኘው ሌሎችን በማቁሰል አይደለምና፣ ሌሎች ቋንቋቸውን፣ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን በጉልበት ጫኑብኝ ብሎ ጫካ ገብቶ የታገለ ቡድን ለራሱም ለሌሎችም መብት መከበር ይሟገታል ወይም የፍትህና የነጻነት ጠበቃ ይሆናል እንጂ፣ እሱ በደል ነው ያለውን ድርጊት በሌሎች ላይ አይደግምም። የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የከተማውን አስተዳደር የመረጠው ህግና ሥርዓትን ተከትሎ እንዲያስተዳድረው ነው እንጂ፣ ከከተማው ነዋሪ ማንነት ጋር የሚጻረር፣የዜግነት መብቱን የሚጋፋና ከሌላ ክልል የመጣ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲያስፈጽም አይደለም! 

ከሰሞኑ የፌዴራሉ መንግስት በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ተነጋግሮ ይህ በአገራዊ አንድነታችን ላይ ከፍተኛ አደጋ ይዞ የመጣውን የአንድ ወገን የፖለቲካ አጀንዳ እንዲቆም አደረገ፣ወይም የፌዴራሉ መንግስት በአዲስ አበባ ያለ ነዋሪዎች ይሁንታ የኦሮሚያን ባንዲራ ለማውለብለብና መዝሙር ለማዘመር የሚደረገው ግፊት እንዲቆም አዘዘ ተብሎ የሚነገረው ዜና ትክክል ከሆነ፣ ይህ ውሳኔ ትንሽ የዘገየ ቢሆንም ትክክለኛና የህዝብን ምሬትና ተቃውሞ ያደመጣ ውሳኔ ነውና የፌዴራሉ መንግስት በውሳኔው እንዲገፋበት አደራ እንላለን። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤትና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለከተማዋ የሚሆን ህግ፣ደንብና መመሪያ ማውጣት ይችላሉ፣ ይህ በህግ የተሰጣቸው ሥልጣንና ሃላፊነት ነው። ነገርግን ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ባህል፣ጥቅምና ፍላጎት ጋር የሚጻረርና የአዲስ አበባን ነዋሪ ማንነት የሚጋፋ፣ ህዝብንና መንግስትን የሚያጋጭ ህግና መመሪያ ማውጣት አይችልም፣ ካወጣም ህዝብ አልቀበልም ካለ ህጉና መመሪያው በስራ ላይ መዋል የለበትም። ይህንን ሥልጣን እጃችን ላይ አለና የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን ባዮቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ጽ/ቤትና የትምህርት ቢሮ በውል ሊረዱት ይገባል። አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ናትና በአዲስ አበባ የወደፊት ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የሁላችንም ውሳኔዎች መሆን አለባቸው፣ ለዚህ ደግሞ አገራዊ የምክክር ጉባኤን ያክል ትልቅ አገራዊ መድረክ እየተዘጋጀ ነውና ሁላችንም ተረጋግተን ይህንን ጉባኤ ብንጠብቅ ይሻላል። 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here