spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየት“ኧረ ባኬ! ነው እንዴ አይነኬ!? ኧረ ባኬ! ሆነ እንዴ አይተኬ!” የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት...

“ኧረ ባኬ! ነው እንዴ አይነኬ!? ኧረ ባኬ! ሆነ እንዴ አይተኬ!” የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታረክ፣ ተሞክሮና ልምድ አንጻር

- Advertisement -
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት

(ክፍል ፪) ክንዴነህ እንደግ (ፒ.ኤች.ዲ)

በሕገ-መንግሥት ታሪክ ምሁራን አካባቢ የታወቀች ቀልድ አለች፡፡ እንዲህ የምትል፦ በአንድ ወቅት አንድ ግለሰብ ወደ ታዋቂ የፈረንሳይ ቤተ-መጽሐፍት ጎራ በማለት ከዓቃቢያነ-መጽሐፍቱ ወደአንደኛው ጠጋ ብሎ “ ጤና ይስጥልኝ ጌታው፤ ባስቸገርኩ ይማሩኝ፡፡ የፈረንሳይ ሕገ-መንግሥትን መመልከት ፈልጌ ነበር ቅጂውን ያገኙልኝ ይሆን? ለሚደረግልኝ ትብብር ሁሉ ምስጋናየ ላቅ ያለ መሆኑን አስቀድሜ ልገልጽልዎት እወዳለኹ” በማለት በፍጹም ትሕትና ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ዓቃቢ-መጽሐፍቱ በወገኑ በቅያሜና የመከፋት ስሜት “ምነው ጌታው? ምን በደልንዎ? ምን የተከፉበት ነገር ቢገኝ ነው በድፍን ፈረንሳይ ስመ-ጥር የሆነ ተቋማችንን እንዲህ ማቃለልዎ!? የተከበረው ቤተ-መጽሐፍታችን የሳምንታዊና ወርኀዊ መጽሔት መደብር ይመስልዎታልን?” በማለት መለሰለት ይባላል፡፡

የቀልዷ መልእክት ፈረንሳይ ሕገ-መንግሥት የማይበረክትላት ሀገር መሆኑዋን ማጠየቅ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቷን የወርኀዊ መጽሔት ያሕል በየጊዜው ትቀያይራለች እንደማለት፡፡

ከአንጋፋዎቹ የአሜሪካ መስራች አባቶች በግንባር ቀደምትነት ለሚጠቀሰው ቶማስ ጃፈርሰን ግን ነገሩ ትንሽ የተጋነነ ቢሆንም በመሰረቱ ነውር የለውም፡፡ ሕገ-መንግሥት በወረፋ፤ የሚያስወርፍ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ሕገ-መንግሥትን እንደግዜው እንደወቅቱ ተለዋዋጭ ማድረግ፣ ማፈራረቅ፣ ማቀያየር ብልኅነት ነው፣ ተፈላጊም ነው ባይ ነው፡፡ ከወዳጁ ጀምስ ማዲሰን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ካደረጋቸው በርካታ የመልእክት ልውውጦች በአንደኛው ጭራሽ ቀን ቆርጦ የአንድ ሕገ-መንግሥት የእድሜ ጣሪያ ቢበዛ ከ19 ዓመት መብለጥ የለበትም ሲል ይሞግታል፡፡ አመክንዮው ደግሞ ስለምን ሙታን በሕይዎት ባለው ትውልድ ላይ ይሰለጥኑ? በውኑ ሙታን መጭውን ትውልድ ይገዙ፣ ይነዱ ዘንድ ተጽፉልን? የሚል አሉታዊ ተጠየቅ ነው፡፡ 

ቀልዱንና የጃፈርሰንን ምልከታ ያስቀደምነው የዚህ ክፍልን ዋነኛ ትኩረት ቢያስተዋውቅልን በሚል ነው፡፡ ይሄውም የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የሃያ ስምንት ዓመታት የአገዛዝ ዘመንና ልማድ፣ ብሎም ከሕገ-መንግሥት ዘለቄታና የቆይታ ግዜ አኳያ የአፍቃሪያኑ አቋምና አመለካከት ከተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታሪክ፣ ልምድና ተሞክሮ አንጻር ምን ይመስላል የሚል የንጽጽር ሐተታ ነው፡፡

ክቡራን አንባቢያን እንደሚያስታውሱት በክፍል አንድ ከይዘት አንጻር የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከመደበኛው የሕገ-መንግሥት ባሕሪያት ወጣ ያሉና ያልተለመዱ ገጽታዎች እንዳሉት ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ከነዚህም አንዱ ሕገ-መንግሥቱ እንደ ሀገረ-መንግሥት ከኢትዮጵያ በላይ መሆኑ ነው፡፡

ከቋሚና ዘላቂነት አንጻርም የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ጠበቆችና አፍቃሪያን አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ ማለትም “የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን መቀየር፣ በኛ ወይ በኢትዮጵያ መቃብር!” ባዮች ናቸው፡፡ “የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን ለመንካት፣ ለመተካት፣ መጀመሪያ ኢትዮጵያን መሰናበት/ማሰናበት ይገባል” ባዮች ናቸው፡፡ 

ብለውም አልቀሩ፣ ተብሎም አልቀረ፡፡ እነሆ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ፦“እኔን እነካ ባይ፣ እኔን እተካ ባይ፣ ሕልሙ እውን ሆኖ የሚያይ፣ መሆኑን ይወቀው ጦቢያ መቃብር ላይ!” ሲል እያስፈራራ፣ ሲል እየፎከረ፣ አይነኬነቱን ይፋ እንዳስከበረ፣ አይተኬነቱን እንዳስመሰከረ፣ ሰላሳ ዓመት ሊደፈፍን ሁለት ዓመት ቀረ! 

አፍቃርያንና ጠበቆቹ ግን “አየ ሃያ ስምንት አመት ምን አላት” ባዮች ናቸው፡፡ ሃያ ስምንት አመት ለኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከሚመኙት ሙሉ ጤንነትና ከሚሟገቱለት እረጅም እድሜ አንጻር ከእንቅልፍ ለመንቂያ፣ ለሰውነት ማነቃቂያ እንኳን የማትበቃ ኢምንት ናት፡፡ እንደነሱ ሃሳብ እንደነሱ ምኞት፣ ለዝንተ ዓለም ጸንቶ መኖር ባይሆንለት፣ ደስታቸው ነው ቢነግሥ ኢፌዲሪ ሽኅ ዓመት፡፡

ችግሩ ያለው አፍቃርያነ ኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ይህን የሚሉት በራሳቸው ጥይት ራሳቸውን እያቆሰሉ መሆኑን አለመገንዘባቸው ላይ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ሕገ-መንግሥት ሌላ፤ አይነኬ አይተኬነት ሌላ፡፡ አይነኬ አይተኬም፣ ሕገ-መንግሥትም፣ መሆን አይቻልም፡፡ 

ለምን ቢሉ አጭሩ መልስ ኧረ ባኬ! ነው፡፡ “ኧረ ባኬ! ከየት የመጣ ነው፣ ሕገ-መንግሥት ብሎ አይነኬ አይተኬ!?”

አይነኬ አይተኬነት የሕገ-መንግሥት ባሕሪ አይደለምና፡፡ ይልቁንም የሕገ-መንግሥት ባሕሪን በጅጉ የሚጻረር አባዜ ነው፡፡ በመሆኑም ይልቁንም የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ነው “እድሜ ለኢትዮጵያ” ማለት ያለበት፡፡  ምክንያቱም ይህኔ ከኢትዮጵያ ውጭ የሌላ ሀገር ሕገ-መንግሥት ቢሆን ኖሮ የምን አይነኬም፣ አይተኬም ሆኖ ሃያ ስምንት አመት መዝለቅ! ቁም ስቅል እያዩ፣ ከዓመት እስከ ዓመት በሄደ በመጣው ሁሉ ሲነሱ ሲጣሉ መኖርን ችሎም ሃያ አመት መድፈን በሕገ-መንግሥታት ዓለም ጭንቅ ጥብ ነውና! ብርቅ ነውና! ያደላቸው የተመረጡ ሕገ-መንግሥቶች ብቻ ናቸው የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲል፣ ውጣ ውረዱን ተቋቁመው፣ ቁም ስቅላቸውን እያዩ እንኳን ሃያኛ ዓመት ልደታቸውን ለማክበር የሚታደሉት፡፡    

ይህ ማለት በተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታሪክ፣ ተሞክሮና ልምድ መሰረት ቢሆን ኖሮ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ይልቁንም ጸባዩን አሳምሮ፤ ለኢትዮጵያ በፍጹም ታማኝነትና ራስን ዝቅ የማድረግ የትሕትና መንፈስ  “እንዳሻሽ አድርጊኝ፣ አንቺን ደስ እንዳለሽ (ድገመው!)፣ እነሆኝ በደጅሽ፣ ታማኝ አገልጋይሽ (ድገመው)፣” የሚለውን የጥሌን ዜማ ከራሱ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በማንጎራጎር እየተጽናና አገልግሎ እንኳን፣ ከአስር ዓመት በፊት የመጠቀሚያ ግዜውን ጨርሶ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ሕገ-መንግሥት ያለመቀየር ዋስትና አይኖረውም ነበር፡፡ 

ይህ ማለት አይነኬ አይተኬ ሆኖ መዝለቁ ከሕገ-መንግሥት መሰረታዊ ባሕሪ የወጣ ያደርገዋል፡፡ ሥለሆነም ቀጣዩ ጥያቄ መሆን ያለበት ይህ የአይነኬ አይተኬነት አባዜው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን ከዓለም ሕገ-መንግሥታት ማኅበር አባልነት ካሰረዘው በምትኩ ምን አደረገው? 

ይህን ከመመለሳችን በፊት ግን አይነኬ አይተኬነት በርግጥም ከዓለም ሕገ-መንግሥታት ማኅበር አባልነት የሚያሰርዝ፤ ከሕገ-መንግሥት መሰረታዊ መርኅና ሥነ-ምግባር አንጻር የተወገዘ፣ ክፉ አመል፣ ጸያፍ ልማድ መሆኑን የተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታሪክ፣ ልምድና ተሞክሮ የሚያረጋግጥ መሆን ባጭሩ እንመልከት፡፡

ከዚህ ጋር በተየያዘ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በመስኩ የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች የኅትመት ውጤቶች ሚና መተኪያ የሌለው መሆኑን አብሮ ማስታዎስ ይገባል፡፡ ከተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታሪክ፣ ልምድና ተሞክሮ አኳያ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን በንጽጽር መተንተንና ማብራራት በጉዳዩ ላይ የሚኖረንን ግንዛቤ ከተለመደው እርስ በእርስ መወነጃጀልና ፍረጃ አውጥቶ በእውቀትና በማስረጃ ላይ የተመረኮዘ፣ ብሎም ምክንያታዊና ሚዛናዊ ያደርገዋል፡፡የኅትመት ውጤቶቹ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ዙሪያ በፓለቲካ ድርጅቶችም ሆነ በምሁራን መካከል ለሚደረጉ ክርክሮች የሚኖራቸው ሚናም እንደዚሁ በጣም ወሳኝና መተኪያ የሌለው ነው፡፡በዚህ መሰረት ሊታለፉ ከማይገባቸው መካከል ሶስቱን የኅትመት ውጤቶች እንደሚከተለው ባጭር ባጭሩ እናስተዋውቃለን፡፡

በቁጥር አንድነት መጠቀስ ያለበት ጥናት ዘካርያ ኤልኪንስ፣ ቶም ጊንስበርግና፣ ጄምስ መልተን የተባሉ ስመ-ጥር የሕገ-መንግስት ምሁራን The endurance of National Constitutions  የሀገሮች ሕገ-መንግሥታት ዘላቂነት/የቆይታ ዘመን በሚል ርዕስ እኤአ 2009 ዓም ያሳተሙት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ እንደ ምሁራኑ እምነት ይህ መጽሐፍ እኤአ ከ1789 እስከ 2000 ዓም ድረስ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሀገራት በሙሉ ተረቀው ሥራ ላይ የዋሉ ሕገ-መንግሥቶችን ዝርዝር መረጃ ያካተተ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ጥናቱ በሚሸፍነው የሁለት መቶ አስራ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሁለት መቶ ሀገራት 935 (ዘጠኝ መቶ ሰላሳ አምስት) ሕገ-መንግሥቶች በሥራ ላይ መዋላቸውን ለማወቅ ተችሎአል፡፡     

ከላይ በተጠቀሰው አሃዛዊ መረጃ መሰረት ምሁራኑ ባደረጉት ሥሌት እኤአ ከ1789 እስከ 2000ዓም ድረስ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የአንድ ሕገ-መንግሥት አማካኝ እድሜ 19/አስራ ዘጠኝ ዓመት ያሕል ነው፡፡ እርግጥ ነው ላይ ላዩን ሲታይ የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ታሪክ ከዚህ በጣም የተለየ ይመስላል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ከሚጀምርበት 1789 እስካሁን ድረስ ከ230 ዓመታት በላይ ካለማቋረጥ በሥራ ላይ መቆየቱ ዓለም ያወቀው፣ ጸሐይ የሞቀው እውነታ ነውና፡፡

በዚህ ምክንያት አንባቢ፦ “ይህ ማለት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የአንድ ሕገ-መንግሥት አማካኝ የእድሜ ጣሪያ 19/አስራ ዘጠኝ ዓመት ከመሆኑ አንጻር የአሜሪካ ሕገ-መንግሥትን በዓለም ዙሪያ ያሉ አቻዎቹ ከኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትም በላይ “ይኽ ገፊ! ጉትት ሽሜ ጉጉ!”  እያሉ የሚያሙት፣ የሚረግሙት፣ የሚያወግዙት፣ ሕገ-መንግሥት ነው ማለት ነውን?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ለምን ቢሉ የራሱን እድሜ ገና ድሮ በሕገ-መንግሥታት ቅድመ ታሪክ ቅርጥፍ አድርጎ፣ ከአስር ሕገ-መንግሥቶች በላይ ተጨማሪ የሕይዎት ዘመን ኖሮአልና፡፡

ላይ ላዩን ሲታይ ይህ ትዝብት ከፊል እውነትነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተነሳንበትን ዋና ሀሳብ የሚያፋልስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በቦታው እንደምናየው የአሜሪካ ሕገ- መንግሥት “አይተኬ መሆኑን ያረጋገጠው/እውን ያደረገው ወረድ ብለን እንደምናየው በጊዜ የሚበጀውን በማወቁ ነው፡፡ ገና በማለዳው ማለትም ተረቆና ጸድቆ በስራ ላይ በዋለ ማግሥት በአጉል ጀብደኝነት ለምን ተነክቼ፣ እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት እንደማያዋጣ አምኖ ጸባይ በማሳመሩ ነው፡፡ 

ባጭሩ አይተኬ ለመሆን የበቃው፣ የታደለው የአይነኬነትን መዘዝ አውቆ ጸባይ በማሳመሩ ነው፡፡  አይነኬነትን ለአይተኬት መሰዋዕት በማድረጉ፣ በመገበሩ ነው፡፡ እንዲያ ሲያደርጉ ደግሞ ማለትም አይነኬነትን ለአይተኬነት ሲገብሩ፣ መሰዋዕት ሲያደርጉ “አይተኬነትም” የይስሙላ፣ ውስጡን ለቄስ የመሆን እድሉ ሰፊ መሆኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በተነኩበት መጠን የነበረው ቀርቶ አዲስ ነገር ተፈጠረ/ተተካ ማለት ነውና፡፡ ማለትም ከነበረው ተቀነሰ፣ ያልነበረ ነገር ተጨመረ ወዘተ ማለት ነውና፡፡

ለማንኛውም ለአሁኑ መተኮር ያለበት ነጥብ ከላይ ያስተዋወቅነው ጥናት አይተኬነት የሕገ-መንግሥት ባሕሪ አለመሆኑን ማረጋገጡ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሕገ-መንግሥት የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ በአዲስ ለመተካት የሚወስደው ግዜ በአማካኝ አስራ ዘጠኝ ዓመት ነውና፡፡

ይሄው ጥናት በተጨማሪ እንዳረጋገጠው በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራት ሕገ-መንግሥቶች በሥራ ላይ በሚቆዩባቸው ዓመታት በየዓመቱ ካለማቋረጥ ማሻሻያ የማድረግ እድላቸው አርባ በመቶ ያህል ነው፡፡ ይህ ማለት አብዛኛው የዓለም ሀገራት ሕገ-መንግሥቶች  ሙሉ በሙሉ ሳይቀየሩ ተሳክቶላቸው አስራ ዘጠኝ አመት ድረስ ለመዝለቅ በዓመት አንድ ግዜ፣ ካለሆነም በአማካኝ በሁለት አመት ወይም ቢበዛ በሁለት አመት ተኩል አንድ ግዜ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማለትም ለመጀመሪያ ግዜ ተረቀው ጸድቀው በሥራ ላይ ሲውሉ ከነበሩዋቸው አንቀጾች በሂደት የማይሰሩ መሆናቸው የተረጋገጠ፣ አላስፈላጊ ሆነው የተገኙ፣ ወይም ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዝኖ የተገኘ አንቀጾች መሻሻል ወይም ሙሉ በሙሉ መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሕገ-መንግሥቶች ተረቀው፣ ጸድቀው ለመጀመሪያ ግዜ በሥራ ላይ ሲውሉ ያልታሰቡ ወይም አስፈላጊ ሆነው ያልተገኙ ነገር ግን በሂደት ከተፈጠሩ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ለውጦችና አዳዲስ ክስተቶች አንጻር በሕገ-መንግሥት ድንጋጌነት መካተት ያለባቸው ጉዳዩች በአዳዲስ አንቀጽነት መካተት ይኖርባቸዋል፡፡ 

ባጭሩ በፍጥነት ተለዋዋጭ ከሆኑ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፍ እውነታዎች ጋር እራሳቸውን እያጣጣሙ መሄድ ይችሉ ዘንድ፤ ሕገ-መንግሥታት ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ ሲውሉ የነበሩዋቸውን አንቀጾች ለማሻሻል፣ ከነበራቸው ለመቀነስ፣ ያልነበሩዋቸው አዳዲስ አንቀጾችን በደስታ በተጨማሪነት ለመቀበል አመች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ማለት እስቲ ማን ጀግና ነው አጠገቤ ድርሽ የሚል! ንክች የሚያደርገኝ! ዝንቤን እሽ የሚለኝ! ከሚል አጉል ድንፋታ፣ እብሪትና አይነኬነት ጀብደኝነት ይልቅ፣ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነውና፣ ለራሱ የሚያውቅ ሕገ-መንግሥት ባሕሪ ለለውጥ በጎ አመለካከት ያለው መሆኑን ማስመስከር፣ ብሎም ለውጥን ለማስተናገድ አመች መሆን ነው፡፡ ዝቅ ብሎ እንደምናየው የአሜሪካ ሕገ-መንግሥትም ከ230 ዓመታት በላይ ለመዝለቅ ያስቻለው አንዱ ባሕሪ- ሥንደርስበት በዝርዝር እንደምናየው ምንም እንኳን ሁሉንም በሚያረካ መልኩ ባይሆን- ይህ ለውጥን አሻፈረኝ ያለማለት፣ ማለትም “ማነው ዝንቤን እሽ የሚል” ከሚል አጉል ጀብደኝነት መራቁ ነው፡፡

ሕገ-መንግሥታት ዝንብ ሲያርፍባቸው በጀ ኸረ ምን ቆርጦኝ እንዳሻህ ሁን” በማለት “እሺ!” ብለው ማስተናገድ የለባቸውም፡፡ ምንጊዜም ዝንባቸው እሽ እንዲባልላቸው ፈቃደኛ መሆን አለባቸው፡፡ 

ከዚህ አንጻር የዓለም ሕገ-መንግሥታት ማኅበር በጠቅላላ ጉባዔው ባንድ ድምጽ አስዎስኖ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን ከአባልነት ያገደበት ምክንያት ማነው ዝንቤን እሽ የሚል!” በሚለው ነውረኛ ዝንብን በፈቃደኝነት እሺ ብሎ የማስተናገድ ባሕሪው ምክንያት ነው፡፡ 

ለማጠቃለል ያህል ከላይ በአንደኛ ደረጃ የጠቀስነው የሕገ-መንግሥት ጥናት የኅትመት ውጤት የሚያረጋግጠው አይተኬነት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከአይተኬነት በበለጠ አይነኬነት የሕገ-መንግሥት ባሕሪ አለመሆኑን ነው፡፡ ይልቁንም አይነኬነት ከሕገ-መንግሥት ባሕሪና ሥነ-ምግባር አንጻር ክፉ አመል፣ ጸያፍ ልማድ፣ መጥፎ አባዜ መሆኑን ነው፡፡ 

በሁለተኛ ደረጃ መጠቀስ ያለበት የኢፌዲሪን ሕገ-መንግሥት በዓለም ዙሪያ ካሉ አቻዎቹ አንጻር ለመረዳት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የኅትመት ውጤት ሄንዝ ክሉግ የተባሉ ምሁር Constituting Democracy: Law, Globalism and South Africa’s Political Reconstruction ሕገ-መንግሥታዊ (ዋስትና ያለው) ዲሞክራሲ፤ ሕግ፣ ልዑላዊነትና የደቡብ አፍሪካ የፓለቲካ መልሶ ግንባታ በሚል ርዕስ በ2000 ዓም እኤአ በመጽሐፍ መልክ ያሳተሙት ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው ከ1989 እስከ 1999 እኤአ ባሉት አስር ዓመታት ብቻ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት መካከል 56/አምሳ ስድስት/ በመቶ ያህሉ በአዲስ የመተካት ያሕል በሕገ-መንግሥቶቻቸው ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡ ይህ ከላይ በአንደኛ ደረጃ ያስተዋወቅነው ጥናት ያረጋገጠውን ማለትም አይነኬነትም ይሁን አይተኬነት የሕገ-መንግሥት ባሕሪ አለመሆናቸውን ይልቁንም ከሕገ-መንግስት መሰረታዊ መርሖና ሥነ-ምግባር ያፈነገጡ አባዜዎች መሆናቸውን የበለጠ ያረጋግጣል፡፡ የሚሸፍነው ግዜ ከኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የመጀመሪያ አምስት ዓመታት የሥራ ዘመን ጋር የሚገጣጠም መሆኑ ደግሞ የውጤቱን ፋይዳ ለኛ ፍጆታ የበለጠ ተፈላጊ ያደርገዋል፡፡  

በሶስተኛ ደረጃ መጠቀስ ያለበት ዴቪድ. ለውና ሚላ ቨርስቲግ የተባሉ ስመ ጥር የሕገ-መንግሥት  ምሁራን The Evolution and Ideology of Global Constitutionalism የልዑላዊ ሕገ-መንግሥታዊነት ርዕዮተ ዓለምና የለውጥ ሂደት በሚል ርዕስ ታዋቂ በሆነው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ/ በርክሌ የሕግ ሐተታ መጽሔት (California Law Review) በ2011 ዓም እኤአ አሳትመው ለንባብ ያበቁት በዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የጥናት ውጤት ነው፡፡ከላይ በአንደኛ ደረጃነት ካስቀመጥነው የኅትመት ውጤት ባልተናነሰ የዚህ ጥናት አድማስና ሽፋንም ከግዜም ከቆዳ ስፋትም አንጻር አመርቂ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሁሉንም የተጻፈ ሕገ-መንግሥት ያላቸው ሃገራት እኤአ ከ1950ቹ መጀመሪያ ጀምሮ ያለውን 60/የስልሳ ዓመታት ልምድና ተሞክሮ ከሞላ ጎደል ያካተተ ነው፡፡  

የዚህ ጥናት ውጤትም አይነኬ አይተኬነት የሕገ-መንግሥታት ባሕሪ አለመሆኑን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው፡፡ በተለይ ለመጥቀስ ያሕል በሃያኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አስር ዓመታት ውስጥ በሕገ-መንግሥቶቻቸው ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ ካደረጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት መካከል 70/ሰባ በመቶ የሚሆኑት የነበሩዋቸውን ሕገ-መንግሥቶች አስወግደው ሙሉ በሙሉ በአዲስ የተኩ ናቸው፡፡ 

እንደተባለው ላይ ላዩን ሲታይ ከአይነኬና አይተኬነት አንጻር ከተቀረው ዓለም ተሞክሮ የተለየ የሚመስለው የ230 አመታት የእድሜ ባለጸጋ አዛውንቱ የዩ.ኤስ አሜሪካ ሕገ-መንግሥት ነው፡፡ ነገር ግን ነገሩን የበለጠ በቅርበት ስንመረምር የምንረዳው ነገር የአሜሪካ ሕገ-መንግሥትም ቢሆን አይነኬ አይተኬነት የሕገ-መንግሥት ባሕሪ አለመሆኑን እንደማይጻረር ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከላይ ያልነውን ደግሞ ለማስታዎስ አይተኬ ሆኖ መዝለቅ የቻለው አይነኬነትን መሰዋዕት በማድረግ ነው፡፡ አይነኬነትን መስዋዕት ሲያደርጉ ደግሞ አይተኬነትም ለዘበ ተገራ ማለት ነው፣ በተወሰነ መልኩ ለድርድር ቀረበ ማለት ነው፡፡ 

ይህም እንዲታዎቅ የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ከሃያ ሰባት በላይ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል፡፡ ማለትም አዳዲስ አንቀጾች ተጨምረውበታል፡፡ ከነዚህ ተጨማሪ አንቀጾች ውስጥ የመብት ድንጋጌዎች Bill of Rights በመባል የሚታዎቁት በጣም ቁልፍና ዝነኛ አስር አንቀጾች የተጨመሩት ሕገ-መንግሥቱ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ማለትም ከ1789 ዓመ እኤአ ከሁለት ዓመት በኋላ በ1791ዓም እኤአ ነው፡፡ (ሃያ ሰባቱ የማሻሻያ አንቀጾች ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠውን የአሜሪካ ላዕላይ ፍርድ ቤት ብያኔዎችን እንደማያካትቱ እዚህ ላይ በተጨማሪ ግልጽ ማረግ የተገባ ነው፡፡ በአሜሪካ የፌደራላዊ ሥርዓት የመንግሥት አወቃቀር የሥልጣን ክፍፍልና ሃላፊነት መሰረት ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ላዕላይ ፍርድ ቤት ችሎት ብዙ ግዜ ከሕግ-አውጭው ማለትም ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በተጨማሪ የሕግ አውጭነት ሚናን የሚጫዎትበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ይሄም የሚሆነው የሕግ ትርጓሜ ያሻዋል በሚል በቀረበለት ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ችሎት አስችሎ የሰጠው ብያኔ፣ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ የሆነ አካል አንድን ድርጊት የሕገ-መንግሥቱን ንባብም ሆነ መንፈስ ይጥሳል በሚል ይታይልኝ ያለው ጉዳይ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ፍርድ ቤቱ የሚያስተላልፈው ውሳኔ እራሱ ፍርድ ቤቱ በሌላ ጊዜ በሚያስችለው ችሎት እስካልተሻረ ድረስ የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ያሕል ተፈጻሚነት የሚኖረው ድንጋጌ ስለሚሆን ነው፡፡ እኤአ በ1954 ዓም የተወሰነው በሕዝብ ትምሕርት ቤቶች የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረገ ማግለልና መድልዖ ሕገ-መንግሥቱን የሚጻረር መሆኑን የሚደነግገው Brown Vs Board of Education/ ከሳሽ ብራውን ተከላካይ የትምሕርት መማክርት ጉባዔ በመባል የሚታወቀው ብይንና በቅርቡ እንደገና ቢሻርም እኤአ 1973 ዓም ጽንስ ማስወረድ ሕገ-መንግሥቱን የሚጻረር አለመሆኑን የሚደነግገው Roe Vs Wade ከሳሽ ሮ ተከላካይ ሔንሪ ዌድ የተባለውን ብይን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዋናው ትኩረታችን ብዙም ላለመራቅ አንባቢ ለግዜው ከዚህ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲገነዘብ የተፈለገው በአሜሪካ ሁኔታ ላዕላይ ፍርድ ቤቱ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን በተመለከተ በተለይ በሁለቱ ተቀናቃኝ የፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል ቁልፍ በሆኑ የፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና፣ ባሕላዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረገው ሽኩቻ ተጨማሪ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች የፍልሚያ ሜዳ መሆኑን ነው፡፡ ዘጠኙ የፍርድ ቤቱ የእድሜ ልክ ሥዩማን ዳኞች ለይስሙላ ከሁለቱ የፓለቲካ ፓርቲዎች አባልነት ነጻ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)  

እንግባ ኀበ ጥንተ ነገር…ለዚህ መጣጥፍ ውስን ዓላማ መተኮር ወዳለበት ጉዳይ ስንመለስ ከላይ እንደተመለከትነው የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ተረቆ በሥራ ላይ በዋለ ባጭር ግዜ ውስጥ አስር አንቀጾች ጨምሮአል፡፡ ይህ አይነኬ አይተኬነት የሕገ-መንግሥት መገለጫ ሳይሆን ይልቁንም ከሕገ-መንግሥት መርሖና ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ ባሕሪ ለመሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡ 

ለምን ቢሉ ይህ እውነታ የሚያሳየው ሕገ-መንግሥታት ገና ከማለዳው ይህ ቀረሽ የማይባሉ፣ ፍጹምና ምሉዕ በኩለሄ ሆነው እንደማይፈጠሩ ነው፡፡ እንደዛ እንዲሆኑ መጠበቅም በፍጹም አይቻልም፡፡ ወይም ይቅርታ ይሄን አረፍተ ነገር እንደገና ለማረም፦ ገና ከማለዳው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ተረቆ፣ ጸድቆ ሥራ ላይ በዋለበት ቁመናና ይዘት እንከን የለሽና ምሉዕ በኩለሄ ሆኖ መገኘት በዓለም ሕገ-መንግሥታት ታሪክ ለኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ብቻ የተሰጠ የፍጹምነትና ምሉዕነት ልዩ ጸጋ ነው፡፡ 

ለማጠቃለል ያሕል የተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታሪክ፣ ተሞክሮና ልምድ በተጨባጭ የሚያሳየው አይነኬ አይተኬነት የሕገ-መንግሥት መገለጫ ሳይሆን ከሕገ-መንግሥት ባሕሪ ያፈነገጠ መሆኑን ነው፡፡ ያም ሆኖ ቁጥር አይዋሽም ቢባልም አሃዛዊ መረጃም የራሱ ውስንነት እንዳለው/ሊኖረው እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም አንዳንዴ አሃዛዊ መረጃና ትንታኔ ብቻውን ከሚነግረንና ከሚገልጥልን፣ የሚደብቀውና የሚሰውርብንም ሊበልጥም ይችላል፡፡

ከዚህ አንጻር ለምሳሌ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን “የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት 230 ዓመታት መዝለቅ ከቻለ፣ የኛስ ምን ይጎለዋልና ነው ሃያ ስምንት ዓመት እንኳ በዝቶበት ምድረ ምቀኛ አይኑ የሚቀላው፣ ሕገ-መንግሥታችንን በክፉ አይን የሚያይብንና አይንህን ላፈር የሚለው?” ሊሉ ይችላሉ፡፡

በዚህ ምክንያት ከአሃዝ ወጣ ብለን ጉዳዩን ከይዘት አንጻር ጭምር መመልከት ይኖርብናል፡፡ እንዲያ ሲሆን መልሱ፣ “እንኳን እንደ አሜሪካ 230 ዓመት መኖር ሊገባው፣ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን በጽንሱ የማጨናገፍ የሾተላይነት እርምጃ ለኢትዮጵያውያን ኀጢያት ሳይሆን የጽድቅ ስራ ሆኖ ሊቆጠር ይችላል” የሚል ሆኖ ልናገኘው እንችላለን፡፡

ለምን ቢሉ የሁለቱ ሕገ-መንግሥታት ግብና ተልዕኮ ለየቅል ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒ ስለሆነ፡፡ የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት እኛ የተባበሩት ግዛቶች ሕዝቦች… ብሎ ሲነሳ መዳረሻ ግቡን የተበታተኑ ግዛቶችን በማሰባሰብና ወደ አንድነት በማምጣት በወቅቱ ያልነበረች አንድ የጋራ ሃገረ መንግሥትን መመስረት፣ ማስገኘት አድርጎ ነው፡፡ ይህ ማለት የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ተረቆና ጸድቆ በሥራ ላይ የዋለበት ዋነኛ ግብ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ነው፡፡ ማለትም ከተበታተኑ ግዛቶች አንድ የጋራ ሀገረ-መንግሥት መፍጠር፡፡ ከዚህ አንጻር የዛሬይቱን የ54 ግዛቶች ስብስብ የጋራ ሃገረ-መንግሥት ከመነሻው ዕውን ያደረገ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሰነድ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ (ከግዛቶቹ ውስጥ ግማሹ በዘር ማጥፋት ቅሚያና ዝርፊያ፣ ግማሹ በግዢ ወዘተ የሚለው ለጊዜው እንዳለ ሆኖ፡፡ ማለትም ላሁኑ ያነሳነውን ሃሳብ ስለማይቃረን)

ከዚህ በተቃራኒ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች… ብሎ ሲነሳ ተልዕኮው የተረከባትን ሀገረ-መንግሥት አክስሞ በምትኩዋ የበርካታ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” ሀገረ-መንግሥታትን መፍጠር ነው፡፡

ለዚህ ነው የአሃዝ መረጃና ትንታኔ ብቻውን ሁሉንም ነገር አይነግረንም ያልነው፡፡ ጭራሽ ወደተሳሳተ መደምደሚያም ሊወስደን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከላይ ከይዘት ንጽጽር አኳያ እንዳየነው የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት 230 ዓመታት ጸንቶ የኖረው እድሜውን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ በማዋል ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ገና ከጽንሰቱ ሀገረ-መንግሥት የማፍረስ ተልዕኮ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም እንደተባለው እንኳን የአሜሪካ ዕድሜ ሊገባው ከጽንሰቱ ማጨናገፍ ቢቻል ኖሮ እርምጃው ሾተላይነት ሳይሆን ኢትዮጵያን ከሾተላይ የመታደግ የጽድቅ ስራ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ (ምነም እንኳን አሁንም ውንጀላውን፣ ፍረጃውን ገታ፣ ግንዛቤና መረጃውን ገፋ ማድረግ ማስቀደም ቢኖርብንም)

ያም ሆኖ ላሁኑ በተጨማሪ ግልጽ መሆን ያለበት የአሜሪካን ሕገ-መንግሥት ጻዲቅ ማድረጋችን በፍጹም አይደለም፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ሀጢያትም አንድ የጋራ ሀገረ-መንግሥት አክስሞ ለበርካታ (እራሳቸው የሕገ-መንግሥቱ ባለቤቶች እንኳን በርግጠኝነት ቁጥራቸውን መናገር ለማይችሉት) “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” ሀገረ-መንግሥታት መሸንሸን ብቻ አይደለም፡፡ ሁለቱንም የሚያመሳስላቸው ከኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የጋራ ሀገረ-መንግሥትን አክስሞ ለብዙ ክፍልፋዮች ከመሸንሸን ኀጢያት በጣም የከፋ ኀጢያት አለ፡፡ ይሄውም ሁለቱም ድምጽ አልባ፣ ጅምላ ጨራሽ፣ የዘር ማጥፊያ ኒውክሊየር ቦንብ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ድምጽ አልባ፣ ጅምላ ጨራሽ፣ ኒውክሊየር ሁለቱም ሕገ-መንግሥታት በግልጽ ከሚያውጁት ይልቅ በዝምታ ያወጁትን/ያጸኑትን የዘረኝነት ርዕዮተ-ዓለም የሁለቱንም መግቢያዎች ዝምታ በንጽጽር በማንበብ በተከታይ መጣጥፎች እናመጣዋለን፡፡

ላሁኑ የዚህን ክፍል ዋና ዋና ነጥቦች በማጠቃለልና በይደር ለሚቀጥለው መጣጥፍ ያስተላለፍነውን ባጭሩ በማስተዋወቅ እንቋጨው፡፡

አንባቢ እንደሚታዘበው ይሆነኝ ብለን ባናረገውም የእስካሁኑ ሂደት የሚያሳየው ዙሩ እየከረረ፣ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን የቤት-ሥራ እየከበደ መሄዱን ነው፡፡

ምክንያቱም ነጥብ እየጣሉ ነው፡፡ ያስጣልናቸው ነጥቦች ደግሞ ቀላል አይደሉም፡፡ የአቋም መዛነፍ የሚያመጡ ናቸው፡፡ 

ከዚህ አንጻር በዚህ መጣጥፍ ያጋለጥነው ወሳኝ ነገር፤ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን “ሕገ-መንግሥቱ አይነኬ አይተኬ ነው” ለሚለው የማይናወጥ አቋማቸው “ምክንያቱም ሕገ-መንግሥት ስለሆነ” የሚል መከራከሪያ ማቅረብ የማይችሉ/የማያዋጣቸው መሆኑን ነው፡፡

ምክንያቱም አንድን ሕገ-መንግሥት አይነካም አይተካም የሚል አቋም የሕገ-መንግሥታዊ አርበኝነት ወይም የሕገ-መንግሥታዊነት መገለጫ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተቃራኒው የሕገ-መንግሥት ኑፋቄ መገለጫ ነው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃሪያን ሕገ-መንግሥቱ አይነካም፣ አይተካም የሚል አቋም ከሕገ-መንግሥታዊነት አንጻር መናፍቃን ያደርጋቸዋል፡፡

ይህ በተጨማጭ ምን ማለት ነው? “ሕገ-መንግሥቱ አይነካም፣ አይተካም፤ ማሻሻያ የሚደረግበት ወይ በኛ፣ ወይ በኢትዮጵያ፣ መቃብር ላይ ነው” የሚል አቋም የሕገ-መንግሥቱን ጠበቆችና አፍቃሪያን የሕግ-የበላይነት አቀንቃኝና ጠበቆች፤ ማለትም ሕገ-መንግሥታውያን፤ “የለም ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል አለበት!” የሚሉ ተቀናቃኞቻቸውን ደግሞ የሥርዓት-አልበኝነት ሃይሎች ወይም ነፍጠኞች አያደርጋቸውም፡፡

ይልቁንም ሁለቱን ወገኖች ከሕገ-መንግሥታዊነትና ከነፍጠኝነት (ማለትም የሕገ-አራዊት ሃይልነት) አንጻር ቦታ እንዲቀያየሩ ያደርጋል፡፡ 

ምክንያቱም ፦ሕገ-መንግሥቱ በጭራሽ መሻሻል የለበትም ይህ የሚደረገው በኛ መቃብር ላይ ነው! የሚል ወገን ከሕገ-መንግሥታዊነት ወጥቶ የሕገ-አራዊት ሃይል ነፍጠኛ ሆነ ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ እንዲህ ያለው አቋም ሕገ-መንግሥታዊነት ሳይሆን ነፍጠኝነት ሕገ-አራዊትነት ነው፡፡ የራስን ፍላጎት በሌላው ላይ በሃይል በጉልበት መጫን ነው፡፡ ምክንያቱም “ይሻሻልልኝ ይቀየርልኝ” የሚለው ወገን “ሕገ-መንግሥቱ የኔን ፍላጎት አይወክልም አያንጸባርቅም” እያለ ነው፡፡ ከዛም አልፎ “እየጠቀመኝ ሳይሆን በሱ የተነሳ ብዙ ጉዳት እያገኘኝ መከራና ስቃይ እያመጣብኝ ነው” እያለ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ይሻሻል ይቀየር የሚለውን ወገን “እንኳን ማድረግ ይህን ማሰብ ወይ በኛ መቃብር ወይ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ” እያሉ እያስፈራሩ መቀጠል፣ ሥርዓቱን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሳይሆን የጉልበተኛ፣ የእውነተኛው የነፍጠኛ ሥርዓት ያደርገዋል፡፡

በዚህ ምክንያት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አፍቃርያን ድርቅና ስለማያዋጣ ከላይ ያብራራነውን የአቋም መዛነፍ ለማስተካከል ቢያንስ አመክንዮአቸውን እንደገና ለማጤን ይገደዳሉ፡፡ ማለትም ሕገ-መንግሥቱ የማይነካው የማይተካው ሕገ-መንግሥት ስለሆነ ሳይሆን ከሕገ-መንግሥት በላይ ስለሆነ ነው የሚል መከራከሪያ ማምጣት አለባቸው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የማይነካው የማይተካው ከመደበኛውና በተቀረው ዓለም የሕገ-መንግሥት ታሪክ፣ ልምድና ተሞክሮ ከሚታወቀው ሕገ-መንግሥት የተለየ ስለሆነ ነው፣ የሚል መከራከሪ ማምጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ማለትም የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከመደበኛ ሕገ-መንግሥት በላይና የተለየ መሆን ይኖርበታል፡፡ 

አፍቃርያኑ አይነኬ አይተኬ ነው! ሲሉን ኧረ ባኬ! እንዳንል የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ተልዕኮ ከመደበኛ ሕገ-መንግሥት ተልዕኮ የተለየ፣ የተቀደሰ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

እንዲያ ከሆነ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ቅድስና/የተቀደሰ ተልዕኮ ምን ይሆን? ይህን የተቀደሰ ተልዕኮ እንዴት ባለ ብቃት ቢወጣውስ ነው የማይነካው የማይተካው?

በጣም አጓጊ ጥያቄዎች!

የሚቀጥለው መጣጥፍ በአማርኛ/በዓረቢ ዕርም/ኻራም፤ በግዕዙ ግዝት ሲል፤ ዕርም/ኻራም ግዝት በሚል ያመጣዋል፡፡

ይቆየን

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,866FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here