spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትያለሥርዓት ለውጥ አገር አይድንም፣ ያለሃሳብ ንቅናቄ ሥርዓት አይለወጥም 

ያለሥርዓት ለውጥ አገር አይድንም፣ ያለሃሳብ ንቅናቄ ሥርዓት አይለወጥም 

 Tesfaye Demmellash _ ተስፋዬ ደምመላሽ  
ተስፋዬ ደምመላሽ  

 (ክፍል አንድ)  
ተስፋዬ ደምመላሽ      

ቅድመ አያቶቻችን ፈታኝ የውጭም የውስጥም ጠላቶችን፣ ወረራዎችንና ሁኔታዎችን ተቋቁመው ኢትዮጵያን ለዘመናት ጠብቀዋል፤ እስከዛሬ አቆይተዋል። የዛሬዎቹ አገር የማዳን ፈተናዎች ከያኔ፟ዎቹ ምንም አይመሳሰሉም ማለት ባንችልም፣ በመጠናቸውም አይነታቸውም ይበልጥ የተባዙና የተወሳሰቡ በመሆን ቢያንስ በከፊል ይለያሉ። እዚህ አራት የተዛመዱ ልዩነቶችን ማጉላት እፈልጋለሁ።

አንደኛ፣ በአገር አቅኚና ጠባቂ መሪነቱ፣ እንዲሁም በጥቃት ተከላካይ ጦረኝነቱ፣ ዘማችነቱና አርበኝነቱ ወደር የሌለው አማራው፣ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የኢትዮጵያን መንግሥት በሚቆጣጠሩ አገር በቀል ፀረ አንድነት ወገኖች በጠላትነት ተፈርጆና ተለይቶ የወረራ፣ የጭቆና፣ የብዝበዛና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ኢላማ ሆኗል። 

ለአስረተ ዓመታት አማራው በኢትዮጵያ መሠረታዊ ብሔራዊ ጉዳዮች ከአማካይ አድራጊ ኃይልነት ወይም ከብርቱ ተገዳዳሪነት ርቆ ቆይቷል። የተገላቢጦ፣ ይህ ታላቅ ማኅበረሰብ በብአዴን ወራዳ “ውከ፟ላ” አንሶ አገር አሳናሽ ለሆነ የጎጠኛ ወራሪዎች የአገዛዝ መዋቅር ተቀጥላ ከሆነ ውሎ አድሯል። እንደሚባለው፣ ጅራቱ ውሻውን ይቆላዋል።

ይህ የቆየ በጣም ወጣሪና አስከፊ ሁኔታ በአይነቱም ሆነ በመጠኑ ቅድመ አያቶቻችንን ያላጋጠመ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ታሪክና ሥልጣኔ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ፈተና እንድሆነ እንረዳለን።               

ሰሞኑን አብይ አሕመድ “አማራ ሸኔ” በሚል አስጸያፊና አወዛጋቢ ሐረግ የሰነዘረው የቃላት ጥቃት ፈተናውን ይበልጥ ሊያባብሰው የሚችል ነው። “አገር መሪው”፣ ቀና፟ ባልሆነ ወያኔያዊ ፀረ አማራና ፀረ አንድነት መንፈስ ሊያመሳስል የሞከረው ፈጽሞ ሊመሳሰሉ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም። ያነጻጸረው የፋኖ፟ን ሥልጡን፣ አገር ጠባቂ የጦረኝነትና አርበኝነት ባህል ተከላካይ አልባ አማሮችን (ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አረጋዊያንን እና ያልታጠቁ ወጣቶችን) ጨፍጫፊ ከሆኑ ኦነጋዊ ስብስቦች ቡከን “ተዋጊነት” ጋር ነው።  

ምስስሉ የአማራን የጦረኝነት ሥነ ምግባር በቃላት ከማጠልሸትና የኦነጋዊውን መንጋ አረመኔያዊ ገጽታ አዙሮ በማስፈንጠር አማራው ላይ ይለጥፋል። ከዚህም ያለፈ አደገኛ፣ ማኅብረሰብ ለማኅረሰብ አፋጂ አንድምታ አለው። የንጽጽሩ ኢላማ ጠ/ሚንስትሩና የአዲስ አበበ ከተማ ከንቲባ ተብዬዋ አዳነች አበቤ እንደሚዘላብዱት “ጽንፈኛ” ፋኖ፟ ሳይሆን ፋኖ፟ እንዳለ ነው። ፋኖ፟/አማራ ላይ ላነጣጠረ ይበልጥ የከፋ የዘር ማጥፋት ዕቅድ አገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን እግምት ውስጥ አስገብቶ ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።

ሁለተኛ፣ አገር ወዳድ ወገኖች በነፃነትና በአንድነት በአገራቸው ምድር ቆመው፣ የውጭና የውስጥ ጠላቶችንም ሆነ የራሳቸውን ጎራ በሚገባ አልለዩም። የሚገኙበት ሁኔታ ቁር፟ጥ ያለ፣ ወሳኝ ትግል ማኪያሄድ ምንም ያህል የማያስችል ዝብርቅርቅ ያለ ነው።  

በዚህ ግልጽ የጎራ ልዩነትም ሆነ የግጥሚያ ፈለግ በአድማሱ በማይታይበት ሁኔታ ሐቀኛ የአንድነት ወገኖች ከእውን መንግሥታዊ ኃይል ተገልለው፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር በጥላቻ ስሜት መቆጣጠር ለሚመኙና ለሚጥሩ፣ ግን በበጎ መንፈስ አገራዊ መሆን ለማይፈልጉ ወይም ለማይችሉ ዘረኛ ገዢዎች ድለላ፣ ጥምዘዛና ጭቆና ተዳርገዋል። ገዢዎቹ ሲያስፈልጋቸው ላፋቸውና ለታይታ ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ወደኋላ አይሉም።  

በዚህ መንገድ፣ “ፈደራላዊ” የተባለ ከጎሣ ፓርቲዎች ጥርቅምነት (የቁጥር “ድምር”) የሚዘልቅ በጎ መርሃዊም ሆነ ተቋማዊ ህላዌ የሌለው መዋቅር የታላቋ ሙሉ ኢትዮጵያን መንግሥት ቦታ ያዥ ሆኗል። ማለትም፣ ኢትዮጵያዊ መንግሥት በእውን አለመኖሩን ደብቆ ራሱን በአስመሳይነት የሚተካ ከአገሪቱ አብራክ የወጣ አገር ከፋፋይና አሰናካይ የአገዛዝ መረብ በመላ ኢትዮጵያ ተዘርግቷል። በዚህም ገጽታው የዛሬው ብሔራዊ ውጥረታችን ወደር የሌለው፣ በቅድመ አያቶቻችን ዘመን ተከስቶ የማያውቅ ነው። 

ሦስተኛ፣ ፀረ አማራና ፀረ አንድነት የጎሣ አገዛዙ ለአንድነት ኃይሎች፣ በተለይ ደግሞ ለአማራ  የሕልውና ታጋዮች ራሱን በግልጽ ተጋጣሚ ላለማድረግ፣ ከሚቃወሙት አገራዊ ኃይሎች ጋር ያለውን መሠረታዊ ቅራኔ ለማድበስበስ ሌት ተቀን ይጥራል። በዚህ ጥረቱ በርካታ ፓርቲዎች፣ ስብስቦችና ሚዲያ አርብቶ አደሮች ሆን ብለውም ይሁን በውጤት ይተባበሩታል። 

ማለትም፣ የአገዛዙን የሆኑ ያልሆኑ አጀንዳዎች ተቀብለው ሽፋን በመስጠት፣ በማሰራጨትና፣ መነጋገሪያ በማድረግ፣ እንዲሁም የተለያዩ ትኩረት ማስቀየሪያ፣ ሃሳብና አመለካከት መበተኛ ሥራዎችን በማከናወን ያግዙታል። በዚህ ሥርዓት አስቀጣይ ትብብራቸው፣ ዘላቂ አቅጣጭ የማይዙና መዋቅር ለዋጭ ሃሳብ የማይሰርጣቸው ልቅምቅም ጉዳዮች፣ አስተያየቶችና ትችቶች ማግተልተል ይቀናቸዋል። 

አገዛዙ በበኩሉ በራሱና በነገድ ዘለል የአገር ድኅነቱ ጎራ መካከል (ፋኖ፟ንም ጨምሮ) ግልጽ የኃይሎች አሰላለፍ እንዳይወጣ ከብዥታ ፈጣሪ አፈ ቀላጤነቱ፣ አስመሳይ ዲስኩሮቹና የፖለቲካ ቁማር ጨዋታው አይቦዝንም። የማይቦዝንበት ምክንያት አለው።  

የኸውም፣ ጎሠኛ ሥርዓቱ (በወያኔም በኦነጋዊም ቅርጹ) መሠረታዊ ቅራኔ ባላ፟ቸው አገር ወዳድና አገር ጠዪ ኃይሎች መካከል የለየለት ሁለገብ ግጥሚያ እንዲካሄድ ፈጽሞ አይፈልግም። በዚህ ዓይነት ወሳኝ ፍልሚያ እንደሚሸነፍ ስለሚያውቅ ተሸንፎ፣ ተንኮታኩቶ ከፖለቲካ ኃይል እንዲወገድና ለመላ የኢትዮጵያ ዜጎችና የባህል ማኅበረሰቦች የሚበጅ ዘላቂ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ አይሻም። 

ለዚህ አንድ ዋና ማስረጃ በአብይ አሕመድ የሚመራው የኦህዴድ አገዛዝ በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያኪያሄደው ግራ አጋቢ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ “ጦርነት” እና ውጤቱ ነው። ጦርነቱ የወያኔን አሸባሪ ፓርቲ ከሚገባው ፍጹም ውድመት ደጋግሞ አትርፏል። ብሎም፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም የተጠላውን የአገር ጠንቅ ዘረኛ ፓርቲ በ“ስላም ድርድር” ስም መልሶ የፖለቲካ ሕይወት እንዲዘራ አስችሎታል።  

ይህም ማለት፣ አገዛዙ በአገር ወዳድ ወገኖችና በፀረ አንድነት ጎሠኛ ስብስቦች መካከል በሰላም መንገድም ይሁን በጦር ሜዳ ወሳኝ ግጥሚያ እውን እንዳይሆን ከወዲሁ የኃይሎችን አሰላለፍ አድበስባሽ የሆኑ ያዝ ለቀቅ ጥረቶቹን በሚችለው መጠንና መንገድ ሁሉ ይቀጥላል። ሆኖም፣ በድህረ ጦርነቱ “የሰላም ስምምነት” ሳቢያ ከሕውሓት ጋር የነበረውን የሻከረ ግንኙነት አለሳልሶ ዛሬ አዲስ አደገኛ ፀረ አማራ ትብብር ፈጠራ ላይ እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። አማራው በጣም መጠንቀቅ አለበት።  

ሕወሓት ያቋቋመውና በኦህዴድ የበላይነት የቀጠለው የአገዛዝ መዋቅር የኢትዮጵያን ሉአላዊ ምድር፣ በዘር ያካለላቸውን የአገሪቱ ዘር ተሻጋሪ ግዛቶችና ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ብሔራዊ እሴቶችና መንፈስ ሳይቀር አፍኖ ከውስጥ ሲጠመዝዝና ሲቦርቡር ይኸው አስርተ ዓመታት ሆነው። ስለዚህ፣ ውሎ አድሮ የአገር ድኅነት ትግሉ የሥርዓት ለወጥ ትግል ነው የሚሆነው።    

ቅድመ አያቶቻችን በተቋቋሟቸው ብሔራዊ ፈተናዎችና በዛሬው አገርን የማስቀጠል ውጥረት አራተኛ ልዩነት መጠቆም እንችላለን። ይኸውም፣ ከዘረኛ ገዢ መዋቅሩ ጋር የዋለ ያደረ ንክኪ ያላቸው ወይም በተጨባጭ የመዋቅሩን ፖለቲካ ሰዋሰውና ቃላት በዲስኩራቸው የሚያስተጋቡ የአገሪቱ ምሁራንና ፖለቲከኞች አገር አድን ሥርዓታዊ ለውጥን ወደፊት አራማጅ ሳይሆኑ ወደኋላ ጎታች መሆናቸው ነው። 

የነዚህ የ“ተቃውሞ” ቦታ ያዢነትንና የአማካሪነትን ሥራ እያፈራረቁ የጎሣ አገዛዙን ለአስርተ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ ወገንተኞች ጎራ በዋናነት አንዳርጋቸው ጽጌን፣ ብርሃኑ ነጋን፣ ልደቱ አያሌውን፣ ያሬድ ጥበቡንና ሰሞኑን ደግሞ ለየት ባለ አወዛጋቢ አቀራረብ ብቅ ያለውን ደረጀ ዘለቀን ያካትታል።

እዚህ ላይ የምናጎላው የግለሰቦችን አሰተሳሰብ ችግሮች ወይም ልዩነቶች አይደለም። ይልቅስ፣ ከሞላ ጎደል በወል የሚያንጸባርቁት ራስን ከፍ ያለ የአዋቂነት ግምት የሚሰጥ፣ በከፊል ከዘመነ “ተራማጅነት” የፈለቀና መልሶ ያልታነጸ ርዝራዥ “ምሁራዊ” ባህል ወይም የአስተሳሰብ ልምድ ነው። በይበልጥ ትኩረት ለመናገር፣ በቅጡ ባልተብላላና ባልተሳካ ጽንሳዊ ሃሳብ አማካኝነት የኢትዮጵያን ውስብስብ ብሔራዊ ጉዳዮች ቀርጾ ለመግለጽና ለመጠምዘዝ የሚያደርጉት ሙከራ ነው። 

ሙከራው መዋቅር ለዋጭ አቅጣጫ ይዞ የማያውቅ (ወይም ሊይዝ የማይችል) ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱ የተዘፈቀበትን ውጥንቅጥ የዘር ፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አሠራር ልምድ የሚደርትና የሚያደልብ ሆኗል። ይህን ሁኔታ በምሳሌ ጎላ አድርጎ ለማሳየት ባለፈው ሰሞን በአዲሱ ሚዲያ ቃለ ምልልስ ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ በሁለት ጽንሰሃሳቦች – ማለትም፣ በ“ምርጫ”/“ውክልና” እና “ብሔርተኝነት” ዙሪያ – የሰነዘራቸውን ስክ፟ነት የጎደላቸው አስተያየቶች በመጠኑ መቃኘት የጠቅማል።

“መንግሥት… ለተራ ፕሮፓጋንዳ የሚውል ምንም ተጨባጭ ይዘት የሌለው”… [ነገር ሲናገር] ይላል ደረጀ፣ “እኛ አስተዋይ ሰዎች ግን ገለባውን ከግርዱ እየለየን ነው ማውራት ያለብን… ዕውነት ሊገለጽባቸው የሚችልባቸውን ተገቢ ቃላትና አገላለጾች መምረጥ አለብን።” በዚህ መንገድ የራሱን “ምክንያታዊ ሃሳብ” ከአገዛዙ አድር ባይ “ትርጉም የለሽ” አስተሳሰብ በግልጽ ለይቶ ያስቀምጣል።  

ደረጀ ምሁራዊ አስተውሎውን በማጋነን ትሕትናን ይሠዋል ሊባል ይችላል። ሆኖም አስተያየቱ በመሠረቱ አግባብ አለው። ዕውነት አሳዳጅ አገር ወዳድ ምሁራንና ሐያሲያን የሚጠቀሙበትን የግንዛቤ ዲስኩር፣ ማለትም ገላጭና ተቺ ቃላትን፣ ጽንሰ ሃስቦችንና የትንተና ፈርጆችን፣ ከፖለቲከኞች የወገንተኝነት ወይም የዘረኝነት ክርክሮች አራማጅ ታክቲካዊ የፕሮፓጋንዳ ንግግር መለይት አስፈላጊ እንደሆነ ያመላክታል። ይህን ልዩነት ማሳስቡ ጠቃሚ ነው። 

ምክንያቱም በአብዮቱና ድህረ አብዮቱ ዘመናት እንደሆነው፣ ሁለቱ የአነጋገር ቅርጾች ከተምታቱ፣ በአንድ በኩል ፖለቲካችን በተጨባጭ ዕውቀት ሊመ፟ራና ለዘለቄታው በሃሳብም በመርህም ጠርቶና ተደላድሎ በቅጡ ተፈጻሚ ሊሆን ወይም በሂደት ሊሻሻል አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ የአነጋገር ዘዴዎቹ መምታታት የጠራ፣ ጠቃሚ ማኅበራዊ-ሳይንሳዊ ዕውቀት ማፍለቅንም አዳጋች ያደርገዋል። በዚህ ሁኔታ፣ የዕውነት ድምፅ በአስመሳዮች ውሸት ይታፈናል፣ አብርሆት በቀለም ቀመሶች ድንቁርና ይጨልማል።

ጥያቄው ግን ንግግሩንና አስተውሎን ከመንግሥት ይዘት የለሽ የቃላት አጠቃቀምና ዲስኩር በግልጽ የለየው ዶ/ር ደረጀ፣ ልዩነቱን ምን ያህል በራሱ አነጋገርና አገላለጽ ያንጸባርቃል ነው። ጉዳዩን ትንሽ በምስፋት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውጥ ከሥርዓት ቅየራ ጋር ያለው ግንኙነት ላይ የሚያተኩር ተከታይ ውይይት በክፍል ሁለት አቀርባለሁ። አያይዤም፣ አገር ላይ መልሕቅ የጣለ የሃሳብ ንቅናቄ ምን እንደሚመስል ለማሳየት እሞክራለሁ።

ይቀጥላል…

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here