
ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ምሁራንና ባለሙያዎች የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫና ብሔራዊ ጥሪ
አሁን አገራችን ኢትዮጵያ እየተስተዳደረችበት ያለችበት ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 5፣ ቁጥር 2፣ ስለብሔራዊ ቋንቋ ሲደነግግ፣ “አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል” ይላል። እንደዚሁም መንግሥት እንደአውሮጳ አቈጣጠር (እአአ) በ1994 ያወጣዉና፣ በትምህርት ሚኒስቴሩም ድረ-ገጽ ላይ አሁን ሰፍሮ ያለው፣ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ቁጥር 3.5.4፣ አማርኛ ቋንቋ ለአገራዊ ተግባቦት በትምህርት ቤቶች እንደ አንድትምህርት መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል።1 ከዚህም በተጨማሪ፣ ይኸው የትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ በብዙ ባለሙያዎች ያስጠናው ጥናት፣ ለአገራዊ መግባቢያነት አማርኛ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደአንድ ትምህርት ተጠናክሮ መሰጠት እንዳለበት በጥኑ አሳስቧል።2
ይሁንና፣ በዚህ ወቅት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግልጽ ያልሆነ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ እየተካሄደ ስላለ፣ ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁለት ድርጅቶች ባንድነት ባዘጋጁት ጥናት ውጤትና ማሳሰቢያ ላይ ተመሥርተን፣ የድርጅቶቹ አባላት፣ ለአገራችን የዘለቄታ ህልውናና ጥቅም፣ ለሕዝባችንም አንድነትና ዕድገት ስንል፣ የአገራችንና የሕዝባችን ሁናቴና የወደፊት ዕጣፈንታ ይመለከተናል፣ ያገባናል፣ ያሳስበናልም የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲያውቀው ይኸንን መግለጫ በይፋ ልናወጣ፣ በጉዳዩም ላይ ጉልህና ጠንካራ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ብሔራዊ ጥሪ ልናደርግ ተገድደናል።
ሁላችንም እንደምናውቀው፣ እአአ በሐምሌ 2-6፣ 1991 ዓ/ም በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት)ና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ቊጥጥር ሥር የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሰላምና የዲሞክራሲ ኮንፈረንስ [ጉባኤ] በመባል በሚታወቀው ስብሰባቸው የተወሰነው የፖለቲካ ውሳኔ፣ ዜግነትን ሠርዞ ሕዝቡን ክልል በተባለ የጐሣ ሥርዐት በማደራጀት የአገሪቱን አንድነት እንዳዳከመውና ሕዝቡን እንደከፋፈለው ይታወሳል። በዚያም ጉባኤ ላይ የተወሰነውን የፖለቲካ ወሳኔ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ብለው እንዳወጡትና በትምህርቱ ጥራት ላይ ከፍተኛ ዉድቀት እንዳስከተለና አገራችንን እንደጎዳ ይታወሳል። ከሁለቱ ፓለቲካ ድርጅቶች ተከታታይ ውድቀት በኋላ፣ አሁን ሥልጣኑን እየተቈጣጠሩ ያሉት አመራሮች፣ ከነሱም ሆነ ከሌላው ታሪክ ሊማሩ የቻሉ አይመስሉም። ስለዚህም በሐሰት ትርክት፣ እንዲሁም አሻጥርና መጠላለፍ በተመላበት በከንቱ ጊዜያዊ ጥቅም በመመራት፣ እላይ ከጠቀስነው ሕገ መንግሥትም ሆነ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ባካሄደው ጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲተገበር ካማጠነው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ፍጹም ባፈነገጠና ተቃራኒ በሆነ መልኩ፣ አማርኛ እንደአንድ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት የማይጠቅስ፣ ሥርዐተ-ትምህርት ተነድፎ ከመስከረም 2015 ዓ/ም ጀምሮ በአገራችን በሥውር ተግባራዊ ተደርጓል። ይኸንን አገራዊ ቋንቋ እንዲሆን በኅቡእ ያወጣውን መምርያ፣ በሕግ ሽፋን ለማጽናት ሲል፣ መንግሥት አጠቃላይ የትምህርት አዋጅ (ረቂቅ) የሚል ሰነድ፣ በድብቅ እያዘጋጀ እንደሆነ ግልጽ ሆኗል።
ይኸ በድብቅ አወጥተው፣ ከመስከረም 2015 ዓ/ም ጀምሮ በሥራ እያዋሉት ያለው መምርያ፣ ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ ሕገመንግሥቱንና የትምህርት ሚኒስቴሩን የትምህርት ፍኖተ ካርታም ሆነ፣ በባለሙያዎች የተሰጠውን ምክር በመቃረን፣ ኢትዮጵያን እንደድርና ማግ ያስተሳሰራትንና ለዘመናት በየጊዜው ከየብሔረሰቡ ተወልደው ሥልጣን የያዙ ነገሥታት የተጠቀሙትን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ብሔራዊ መግባቢያና የሥነጽሑፍ ልሳን አድርገው ያቈዩትን፣ ለድፍኑ ጥቁር ሕዝብ ደግሞ ኩራት የሆነዉን፣ የአማርኛ ቋንቋ እንደአንድ ትምህርት እንዳይሰጥ የሚያበረታታ ነው።
ይህንን እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ አስመልክቶ፣ ሕዝብ ለሕዝብ ፅምረት [People to People (P2P) Inc.]ና ዓለምዐቀፍ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ውጣኔ [Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI)] በተሰኙት ሁለት ድርጅቶች በጋራ የተዘጋጀ፣ በውጭና በአገር ዉስጥ የሚኖሩ ምሁራንን ያሳተፈ የባለሙያዎች ውይይት ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ/ም ተካሂዷል።
ውይይቱ፣ አማርኛ እንደቋንቋ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የተቀመረና ከየማኅበረሰቡ አስተዋፅዖ የተውጣጣ ልሳን በመሆን፣ በዘመናት ዐድጎና በልፅጎ የኢትዮጵያውያን የጋራ አገራዊ መግባቢያ ከመሆኑ ባሻገር፣ በዓለምም የታወቀ፣ ለትምህርትና ለሥነ ጽሑፍ የበቃ፣ አፍሪቃውያን የሚኮሩበትና ወደፊትም በስፋት ሊገለገሉበት ብቃት ያለው ቋንቋ እንደሆነ የተለያዩ ተጨባጭና የማያፋልሙ ማስረጃዎችን በማስረገጥ አሳይቷል። አሁንም አማርኛ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ከመሆኑም በላይ፣ በአገራችን በአፍ መፍቻ ወይንም እንደ ሁለተኛ ቋንቋ በመነገር ተቀዳሚው ቋንቋ እንደሆነም አስገንዝቧል። ይህ ነባር ሐቅ መሆኑ እየታወቀ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ከመስከረም 2015 ዓ/ም ጀምሮ ተግባር ላይ ያዋለው መምርያ በሐሰት ትርክትና ጥላቻ ላይ የተመሠረተ፣ አደገኛና የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽር፣ የዘውግ ፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን በውይይቱ መድረክ ላይ ምሁራኑ በጥናት ላይ በተመረኰዘ ዘገባቸው አስረድተዋል።
ከሁሉም በላይ፣ አሁን በድብቅ በባለሥልጣናቱ እየተካሄደ ያለው፣ በአፍሪቃ ብቸኛ የሆነውን አገራዊ የጽሑፍ ቋንቋ እንደብሔራዊ ትምህርት እንዳይሰጥ የማድረግ ተግባር፣ ዓላማው ለሺህ ዓመታት በነጻነት የኖረችዋንና አኩሪ ታሪክ ያላትን አገራችንን የመናድ፣ ዜጎቿም ርስበርሰ እንዳይግባቡ፣ የገዛ አገራቸውን የጋራ ብሔራዊ ልሳን የማሳጣት፣ እንዲሁም የሕዝባችንን አንድነት የሚያናጋ፣ የአገሪቷ ህልውናና ታሪክ መሠረት የሚሸረሽር አደገኛ መምርያና አካሄድ መሆኑ በስብሰባው በአፅንኦት ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ዋና ሀብቷ ወጣት ዜጎቿ እንደመሆናቸው መጠን፣ እነሱም የሚገነቡትና አገራዊ ማንነት የሚኖራቸው ጥራት ባለው ትምህርት ታንጸውና ተቀራርበው ሲያድጉ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያም አሁን ላለችበት ቀውስና አስቸጋሪ የሰላም ዕጦት ምክንያት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ አስተዳደር ነፀብራቅ የሆነውና ጥራቱ የወደቀው የትምህርት ሥርዐት መሆኑንም ምሁራኑ አስታውሰዋል። በይበልጥም፣ የትምህርቱ ጥራትና ፋይዳ ተሻሽሎ፣ አገሪቱን ከገባችበት ችግርና ማጥ ለማውጣትና ለአገር አንድነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ አሁንም መንግሥት ትምህርትን ዜጎችን በቋንቋና በብሔር ለመከፋፈል በመጠቀም አደገኛ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑ በተሰብሳቢዎቹ አንደበት ተነግሯል።
የምሁራኑ ውይይት፣ አማርኛ ከአገሪቱ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ቋንቋ በመዛነቅ፣ ከልጆቿ አብራክ ወጥቶ፣ በኢትዮጵያ ጸንቶ የኖረ፣ በረጅም ጊዜ የዳበረ የመነጋገርያና የጽሕፈት ቋንቋ እንደሆነ አስገንዝቧል። ስለዚህም፣ ቋንቋው ከምጣኔ ሀብቷና ማኅበራዊ ጥቅሙ ዐልፎ፣ አገራችንን በአንድነትና በነጻነት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው፣ በዚህ ብሔራዊ ሚና አንጻር ሲታይ፣ በትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ የሚደረገው አዝማሚያ የሚያመጣው ጉዳት መጠነ-ሰፊና ለመጪው ትውልድ የተወሳሰበ ችግርን የሚያወርስ ነው። የዳበረውን አገራዊ ቋንቋ ከትምህርት መምሪያ መሰረዝ፣ አገርን ይጐዳል፤ ሕዝባችንን ከማቀራረብ ይልቅ ያራርቃል፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ዜጎች እፈለጉበትና እተመቻቸው አካባቢና ሙያ ተሰማርተውና ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸውን ይነፍጋል፤ እንዲሁም አገር ከመገንባት ይበልጥ ወደ አገር መናድ ያመዝናል።
ከዚህም የተነሣ፣ በምሁራኑ ዕይታ፣ የአገራችንና የመላው አፍሪካ ኩራት የሆነዉን የጽሑፍ ቋንቋችንን አዳብረን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ ማድረግ ሲገባ፣ ለቀመር [ኮምፑዩተር] ቴክኖሎጂ ተመራጭ የሆነዉንና የዳበረዉን አማርኛን በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት ይሰጥ የሚለውን መምርያ መቀየሩ፣ “አገር-በቀል ዕውቀት እናሳድጋለን፣ አገራዊ መግባባት እንፈጥራል፣” የሚለው መንግሥት ሕዝቡን የሚያስተባብር፣ አገርን የመገንባት፣ ወደፊት በአንድነቷ የሚያስቀጥልና አስተማማኝና ግልጽ ራእይ እንደሌለው ያረጋግጣል።
ይህ ክሥተት የትምህርቱን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላ የአገራችንና የዜጎቿን ህልውና ራሱን የሚመለከት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ስለዚህ የምሁራኖቹን ጥናትና ማሳሰቢያ በመከተል፣ ሳይውሉ ሳያድሩ ታይተው መታረምና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ስለሆኑ፣ የሚከተሉት ነጥቦች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረጉ በጽኑ እናሳባለን።
1. አገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ በፈጠረው ችግር ተወጥራ እያለ፣ ሕዝብ ያልመከረበት መምርያና ሕግ በድብቅ አዘጋጅቶ ማውጣት አገርንና መንግሥትን አደጋ ላይ እንደሚጥል ታውቆ፣ አሁን ድረስ ባለው የትምህርትና ሥልጠና መምርያና ራሱ መንግሥት በባለሙያዎች ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ በሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የፌደራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ለአገራዊ መግባቢያነት በመላው የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንደአንድ ራሱን የቻለ ትምህርት አላንዳች ሕገወጥነት ለሁሉም እንዲሰጥ እንዲደረግ።
2. የወቅቱ የሐሰት ትርክት በወለደው በዘውግ አመለካከትና ውሳኔ ታሪክን ማጥፋትና ወደኋላ መመለስ ለጊዜያዊ ፖለቲካ ቢያመችም፣ የሕዝብን አንድነት የሚያናጋና አገሪቱንም ለውጭ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ ታውቆ፣ በአመራር ላይ ያለው መንግሥት፣ የትምህርትና የቋንቋ መምርያን፣ ሕገመንግሥቱ በአንቀጽ ዘጠና በቊጥር ሁለት “የመማር የማስተማር ሂደት ከማንኛውም የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የባህል ተፅዒኖ በፍጹም የጠራ መሆን አለበት” ሲል በሚደነግገው
መሠረት፣ ከተራ የዘውግ ፖለቲካ እንዲለይና፣ የቋንቋ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይበልጥ ማቀራረቢያ፣ ማገናኛ፣ ማስተባበሪያ፣ ማስተሳሰርያና አገር መገንቢያ እንጂ የመከፋፈያና የጥላቻ መሣሪያ እንዳይሆን።
3. በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በሥርዐተ-ትምህርት ጉዳዮች ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ-ገብነት በአስቸኳይ እንዲቆም፤ ጉዳዩ ለዘርፉ ባለሙያዎች እንዲተው፤ ለባለሙያዎቹም ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብና፣ ዓለም-ዐቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል።
4. መንግሥት አማርኛ ቋንቋን በማበልፀግ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቀመር [ኮምፒዩተር]፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መማሪያና የምርምር ቋንቋ እንዲሆን፣ ሌሎችም የአገራችን ቋንቋዎች ተደጋግፈው የሚዳብሩበት ስልታዊ ዕቅድ በማውጣት ሥራ እንዲሠራ።
5. በቋንቋና በክልል መዝሙር ሰበብ የኢትዮጵያ ለጋ ሕፃናትን በዘውግ መለያየት ወይንም በውስጣቸው የጥላቻ ዘር መዝራት አሳፋሪና አደገኛ ተግባር መሆኑ ታውቆ፣ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲደረግ።
ይህን አገራዊ መግባቢያ ቋንቋን ጉዳይ አስመልክቶ፣ መንግሥት እየተከተለ ያለው አገር-ጐጂ መምርያ ተስተካክሎ፣ ትምህርቱ ለአገር አንድነት፣ ዕድገትና ሰላም አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ተስፋ በማድረግ መግለጫችንን እንዘጋለን። People to People (P2P) Inc.
Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI)
1https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20of%20Ethiopia.pdf
2https://planipolis.iiep.unesco.org/sites/default/files/ressources/ethiopia_education_development_roadmap_2018-2030.pdf
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena