spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትሕገ-መንግስቱን ለማሻሻል ለሚደረገው ሕዝባዊ ውይይት ይጠቅማሉ የምንላቸው ሐሳቦች 

ሕገ-መንግስቱን ለማሻሻል ለሚደረገው ሕዝባዊ ውይይት ይጠቅማሉ የምንላቸው ሐሳቦች 

Concerned Ethiopians Constitution

(ከተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን)

የአገርን ጉዳይ ለፖለቲከኞች ብቻ መተው ኢትዮጵያን በጣም ጎድቷታል።  ስለዚህ ሀገራችንን ከባሰ ጥፋት ለማዳን ማህበራዊ ድርጅቶችና ዜጎች የመፍትሔ አካል ለመሆን እንድንችል ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል የሚያገለግሉ ግባዓቶችን የሚያዘጋጅ መድረክ (Forum) ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን (Concerned Ethiopians) እንዲቋቋም ሐሳብ ያቀርባል። ይህ የሚቋቋመዉ መድረክ የምክክር ኮሚሽን ሥራውን ጀምሮ ሕዝባዊ ውይይቶችን በየዪኒቨርሲቲዎች እንደሚያደርግ ማሳወቁን ተከትሎ የቀረበ ጥሪ በመሆኑ፣ ዋናና አንኳር ጉዳዮችን የኢትዮጵያ ሕዝብ መወያየቱ ለኮሚሽኑ ሥራ ቀናነትና ፍጥነት የሚያግዘው ይሆናል።

በአገራችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፍትሕ መዛባት፣ የሰላም ማጣት እና የድህነት መብዛት በጥቅሉ የችግሮቻችን መንስዔው የጎሣን ፖለቲካ ያወጀው ሕገ-መንግሥት ስለሆነ ተቀዳሚው ሥራ ሊሆን የሚገባው ይህን ሰነድ በማሻሻል የአፓርታይድ ሥርዓት ተወግዶ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን የሚሆንበትን ንድፍ ማዘጋጀት ነው።

በኢትዮጵያ የዘውድ፤ የወታደራዊ አምባገነንና የጎሣ የበላይነት አገዛዝ ስርዓቶች ተቀይረው፣ ኢትዮጵያ የሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ የሚያገለግል ሕዝባዊ የሪፐብሊክ መንግሥት እንድትመሠርት ፣ ሕዝቡ ዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት ኢትዮጵያን ማየት መፈለጉን ሕዝባችን እስከዛሬ ባደረገው ተጋድሎ በግልጽ አሳይቷል።

እኛ ኢትዮጵያውያን የተሠራንበት ሥሪት የተለየ ነው። የራሳችንን ፊደል ቀርጸን ስነጽሑፋችንን ያዳበርን ፤ በጠላት አንገዛም ስንል  ለጥቁር ሕዝብ ነጻነት ፈር ቀዳጅ የሆነዉን የአድዋ ድል አድራጊዎችም ነን። ዛሬም “እኔ በሕግ እንጅ አልገዛም በሰው” በማለት ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገንን ዘዉጌ ሕገ-መንግሥት ለማሻሻል በሙሉ ልብ እና በቁርጠኝነት ተነስተናል።

የጎሠኞች ክልል የዲሞክራሲ መቃብር ነው፣ ለሀገር ሕልውናም አደጋ ነው። ለሦስት አሥርተ-ዓመታት ግጭትና ቀውስም መንስዔው ይኸው የጎሣ ፖለቲካ ቁማር ያወጀው ሕገ-መንግሥት ነው።ሕገ-መንግሥቱ፤ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ሳትሆን ፤ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መሬት ናት ይላል። ኢትዮዽያዊ የሚባል የጋራ ማንነትን አይጠቅስም። እውቅና የሚሰጠን በኢትዮዽያዊነት ሳይሆን በክልላዊነት ነው የሚል መነሻ አለው። የእኛ ልዕለ-ግብ ግን የከፋፋይ ሥርዓትን ለመለወጥ ነው። ዓላማችን ከጎሣ ፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ወደ የሁሉም ዜጎች እኩልነትና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት፣ የሥልጣን ምንጩ የሕዝብ የሚሆንባት 

ዲሞክራሲያዊት ኢትዮዽያን ለመገንባት የሚጥር የአገር-አድን ትግል ነው። በአሁኑ የአገር ማዳን ዘመቻ ወቅት ትኩረታችን ለሚቀጥለው ምርጫ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ ነው።

ዓላማችን ፀረ-ኢትዮዽያና ፀረ-ዲሞክራሲ የሆነውን የጎሠኛ ሕገ-መንግስት እና የጥላቻ ከፋፋይ ርዕዮተ-ዓለም እንዳይቀጥል የሚያደርግና በኢትዮዽያዊነት እሴቶች የሚተካ ነው። 

አሁን ያለው ሕገ-መንግስት ለጎሣ መብትና እኩልነት የቆመ ሰነድ ሳይሆን ጎሣን ከጎሣ ጋር የሚያጋጭ እና ግጭቱም እንዳይቆም የሚያደርግ ነው። በኢትዮዽያዊ ዜግነት ጠንካራ አገራዊ ስሜት እንዳይኖር ሕገ-መንግስቱን የድርጅት ሥራ ማስፈፀሚያ በማድረግ በክልላዊ ሥርዓት ትግሬ ፣ አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ሶማሌ ፣ አፋር ፣ ሐረሬ… ወዘተ የሚባሉ ጥቃቅን፣ ደካማ መንግሥታት (mini states) እርስ በእርሳቸው ሲዋጉ እንዲኖሩ ቀምሮ የተነሳ አገር-በቀል ፀረ-ኢትዮዽያ ሰነድ ነው።

በሰሜን ኢትዮጲያ ላለፈው ሁለት ዓመት የተደረገው የእርስ በእርስ ጦርነት፤ የሰው እልቂትና የንብረት መጥፋት የጎሳ ፖለቲካዉ ያስከተለዉ ውጤት ነው። በተጨማሪም ይህ የጎሳ ፖለቲካ የወለደው ጥላቻ፣ እጅግ አሰቃቂ የዘር ተኮር ጥቃትና ዘር የማፅዳት ዘመቻ ማቆምያ አልገኝለት ብሎ እንዲቀጥል አድርጓል። ለዚህም ማሳያዉ በወላጋ የሚገኙ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለዉ አሰቃቂና አሳዛኘ ጭፍጨፋ በቂ ማስረጃ ነዉ። በአሁኑ ስአት ሀገራችን ኢትዮጵያን የሚመራት የብልጽግና መንግስት ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ንፁኃን ወገኖቻችን ድረሱልን እያሉ ሲማፀኑ ከሞት አለማትረፉ ልብ የሚሰብር ነው። የሀገራችን ትምህርት ፖሊሲ ይህን አይነት ዘግናኝ ድርጊት እንኳን መፈፀም፣ መታሰብ እንደሌለበት ለወጣቶች ማስተማር ስላልቻለ ሊቀየር ይገባዋል።

አገር ወዳዱና ለውጥ ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ያለው ምርጫ፣ በጎሣ መለያየቱን ትቶ ተባብሮ በመደራጀት በጎሣ ፖለቲካ ሥርዓት አልገዛም በማለት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ በማጠናከር በአንድ አገር ዜግነት መቆምና ያለውን የጎሣ ፖለቲካ የሚያስወገድ ስር-ነቀል ለውጥ ማምጣት ነው።

ሁሉም ኢትዮጲያዊ፤ መንግሥት፣ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ለውጥ እንዲያመጡ ጫና መፍጠር አለበት። እውነተኛና ጠንካራ የሆነ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስት ለመቅረፅ የመጀመርያው ተግባራችን ሕገ-መንግሥቱን ማስተካከል ስለሆነ ይህንንም ለመተግበር ሀገር ወዳድ እና  ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን የሆን ሁሉ  በመወያየት  ለችግሩ የመፍትሔ አካል ለመሆን እንትጋ።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here