spot_img
Monday, October 2, 2023
Homeነፃ አስተያየትያለሥርዓት ለውጥ አገር አይድንም፣ ያለሃሳብ ንቅናቄ ሥርዓት አይለወጥም  (ክፍል ሁለት)     

ያለሥርዓት ለውጥ አገር አይድንም፣ ያለሃሳብ ንቅናቄ ሥርዓት አይለወጥም  (ክፍል ሁለት)     

advertisement
ተስፋዬ ደምመላሽ    _ Ethiopian politics

 (ክፍል ሁለት)                              ተስፋዬ ደምመላሽ   

ተስፋዬ ደምመላሽ                                                      

በአለፈው ሰሞን በአዲሱ ሚዲያ ባደረገው ውይይት፣ ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ የፖለቲካ “ምርጫ” ሁኔታን፣ እንዲሁም “ብሔርተኝነት”ን በስሜት ተቸ። በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ለአገር ታማኝነቱ ያልተረጋገጠ የፖለቲካ መዋቅር በመገምገም “በሰላሳ ዓመት የምርጫ ታሪካችን ቧልት ስናደርግ እንደነበረ” ነገረን። 

አክሎም፣ አንድ ክልል [ትግራይ] አፈንግጦ የራሱን ምርጫ ተብዬ በማኪያሄዱ መንግሥት በሕግ ማስከበር ስም ያደረገው “ደም አፋሳሽ ጦርነት” ሕዝቡን የምሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም እንዳልነበረ አስታወሰን። የሕዝቡ መሰቃየት አሳዛኝ እንደሆነ፣ ግን ይበልጥ የሚያስከፋው ደግሞ ስቃዩ በከንቱ እንደነበረ፣ ምንም ጠቃሚ ውጤት እናዳላመጣ አመላከተ።  

ሆኖም፣ ደረጀ ራሱ በትክክል “አፓርታይዳዊ ሥርዓት” ብሎ በሚኮንነው አምባገነናዊ የጎሣ አገዛዝ መዋቅር ውስጥ አማራው በእውን የመረጠው ወካይ ፓርቲ የሌለው መሆኑን የውይይቱ ሌላዋ ተሳታፊ መስከረም አበራ ስታመለክት ደረጀ በቅጽበት በሰነዘረው ምላሽ አስተያየት ስለ “ምርጫ ቧልትነት” ያለውን በግልጽ ተቃረነው። “ም/ጠ/ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ተመርጦ አይደለ እንዴ [ወደ ሥልጣን] የመጣው…” ብሎ በመገረም፣ የአማራውን በእውን አለመወከል አጥብቆ ካደ።

ይህን ሲል፣ ቀደም ብሎ የገለጸውን ዕውነት፣ ማለትም ኢትዮጵያ ውስጥ በፈላጭ ቆራጭ የፖለቲካ መዋቅር ስር የሚኪያሄድ ማንኛውም “ምርጫ” በምር የማይወሰድ፣ አካቶ ትርጉም የለሽ መሆኑን በጎላ ተቃራኒ አስተያየት ሐሰት አደረገው፤ አፈረሰው። የም/ጠ/ ሚንስትሩን “ተመርጦ” ሥልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን “ሕዝቡ ፌደራል መንግሥቱ አይወክለኝም…[ካለ] በምርጫ ማስወገድ” እንደሚችል አረጋገጠልን። 

ይህ የተጣረሰ ክርክር ከትክክለኛ አስተሳሰብ የወጣ ብቻ ሳይሆን የጎሣ አገዛዙን መዋቅራዊ ጠባይ ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ለመጨበጥ የሚሞክር ነው። “አማሮች… ከማናቸውም ብሔሮች በላቀ ደረጃ…በመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ ነበሩ” ይላል ዶ/ር ደረጀ፤ ግን “መሪዎቹ [ብአዴኖች] ሕዝባቸውን የካዱ መሆናቸው አማራ በአገዛዙ የለም [አልተወከለም] ማለት አያስችልም። ተገቢውን አመራር መምረጥና በተገቢ ድርጀት መወ፟ከል የራሱ የአማራው ሕዝብ ችግር ነው”። 

እምነት የሚጣልበት፣ ኃቀኛና ትክክለኛ የምርጫ ሥርዓት በሌለበት (ኖሮም በማያውቅበት) የመንግሥት መዋቅር አማራው ተገቢውን አመራር መምረጥ ይችላል እያለን ነው ዶ/ር ደረጀ። ማለትም፣ የአማራውን ማኅበረሰብ፣ በሰፊው ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያምሰው የዋለ ያደረ የፖለቲካ ውዝግብ ሥርዓታዊ ፍልቀት፣ ቅርጽና ይዘት የለውም ማለት ነው። እንደ ደረጀ አመለካከት፣ ሕዝቡ በነፃነት ራሱን አደራጅቶና የፈለጋቸውን እንደራሴዎች መርጦ በመንግሥት ውስጥ  መወ፟ከል ይችላል። አስተዋይነቱን ከጠቆመን ምሁር በዚህ መልክ የቀረበው አስተያየት አሳዛኝ ባይሆን የሚያስቅ ነው።  

ይህ ስክ፟ነት የጎደለው ክርክር ምጸታዊ ጎንም አለው። አማራው በመንግሥት ውስጥ ወካይ ፓርቲ አልባ ነው የሚለውን እሳቤ ደረጀ “በምክንያታዊነት እንደሚያምን ሰው” አይቶ “ግራ የገባው ሃሳብ” ነው ብሎ ያጣጥለዋል። ይህን ሲያደርግ ግን ስለራሱ ግራ የተጋባና ሥነ አመክንዮን ያልተከተለ አስተሳሰብ ምንም ፍንጭ የሚታየው አይመስልም!     

እንግዲህ፣ በዘር ፖለቲካ መዋቅሩ ውስጥ የሚዘዋወሩ ይዘት የለሽ ጽንሳዊ ቃላትንና ሃረጎች (“ምርጫ”፣ “ውከላ”፣ “ፌደራል መንግሥት” ወዘተ) ደረጀ የሚጠቀምባቸው በግልጽ እንደነገረን ከአገዛዙ አድር ባይ፣ ገለባ ዲስኩር አካቶ በተለየ አስተዋይነት ወይም ሐያሲነት እንዳልሆነ እንረዳለን። ይልቅስ፣ ቃላቱን የሚወስደው በአገዛዙና ወኪሎቹ እንደተሰጡ (ማለትም፣ በትርጉም የለሽ ገለባነታቸው) ነው። ከአወሳሰዱ ጀርባ ደግሞ ጥራት የራቀው፣ የሚጣረስ አስተሳሰብ አለ። ይህ ችግር ጉልህ ስለሆነ እዚህ ምንም ያህል ተጨማሪ ትችት አያስፈልገውም።  

ቢሆንም፣ ደረጀ “ገለባውን ከግርዱ” ለዪ ነው የሚለው ንግግሩ ያለው ችግር በሥነ አመክንዮ ተቃርኖ ብቻ እንደማይወሰን ልብ ማለት ይገባል። በመሠረቱ ዲስኩሩ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያራምድ የተሻለ አገር አዳኝና አልሚ ጽንሳዊ እሳቤ አፍላቂ ሊሆን አይችልም። እንዲያውም፣ ሆን ተብሎም ባይሆን በውጤት የፀረ አማራ ዘረኛ ወገኞችንና የአገዛዝ ሥርዓቱን ፖለቲካ ቋንቋና አስተሳሰብ ያስተጋባል፣ ያደልባል፣ ብሎም ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጽንፍ ያስረግጣል። 

በዚህ ይዞታው፣ ንግግሩ በኢምክንያታዊ አማራ ጥላቻና ፍራቻ የተዋጡ ትግሬና ኦሮሞ ጎጠኞችን ለባሰ አደገኛ ጠብ ጫሪ ወረራና ጭፍጨፋ የሚጋብዝና የሚገፋፋ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። አያይዞም፣ አማራው ላይ የውስጥና የውጭ ደመኞቹ ለአስርተ ዓመታት የተበተቡትን የሐሰት ትርክት ድር በመደረት የአፓርታይዳዊ አገዛዙን እድሜ ያራዝማል፤ አስፈላጊ ሥርዓታዊ ለውጥን ከወዲሁ ይገታል፣ ያስተጓጉላል።           

ለዚህ እንደ ማስረጃ፣ ደረጀ ስለ “ብሔርተኝነት” ያለውን ዝባዝንኬ መውሰድ ይቻላል። ጠለቅ ባለ አስተውሎ ይቅርና በመለስተኛ የአእምሮ ጥረት እንኳን ሊያሳካ ሳይሞክር በስሜትና ጥድፊያ የዘከዘከው ጥርቅምቅም አስተያየት በሃሳብ የተቀናበረ ስላልሆነ ምንም ያህል ፈታሽ ትችት የሚገባ፟ው አይደለም። በዝብርቅርቅ ዲስኩሩ የወሰዳቸውን አንድ ሁለት እርምጃዎች ለናሙና ጠቁሜ ብቻ ወደ ይበልጥ ብርቱ ጉዳዮች ልለፍ። 

(1)ማስተባበል  – በአንድ በኩል ደረጀ “የአማራ ብሔርተኝነት የሚባል ነገር የለም” ይላል። (2) አድልዎ ማሳየት  – በሌላ በኩል ደግሞ የተሳሳተ አስተሳሰብና ተራ ወገንተኝነት በሚያንጸባርቅ ንጽጽር “የትግሬ ብሔርተኝነት አደገኛ ሳይሆን በጣም ተስማሚ ነው” ይልና ስለአማራው ሲናገር ግን በአገሪቱ አብዮተኞችና ዘረኞች ፀረ አማራ ትርክት የተለመደውን የ“ትምክህተኛነት” ፍረጃ ያስተጋባል። እዚህ ላይ ደረጀ የለም ያለውን የአማራ ብሔርተኝነት ሎጅክን በተጻረረ መንገድ ኮነነ፤ “የሌለን” ነገር አጠለሸ። (3) አላፊነት በጣም በራቀው አደገኛ ንግግር አማራውን አላግባብ መወንጀል – ማለትም፣ ፈጽሞ መሠረተቢስ በሆነ ጽንፈኛ ትንበያ ወይም ግምት “አማራው ሥልጣን ቢይዝ እንደናዚዎች አናሳዎችን አቃጥሎ ሊፈጃቸው የሚችል ነው” ብሎ ዘላበደ።

እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ የዶ/ር ደረጀ የግል ዲስኩር ሳይሆን ንግግሩ የሚያንጸባርቃቸው፣ በኢትዮጵያ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ ብዙ ጊዜ የሚከሰቱ፣ በከፊል ከምሁራዊ ስንፍና የሚፈልቁ የአስተሳሰብ ድክመቶች ናቸው። ከነዚህ የተለመዱ ችግሮች አንድ መሠረታዊ ስህተት መጥቀስ ይበቃል። ይኸውም ቃላትን፣ ማለትም ስሞችንና ምልክቶችን (እንበል “ፈደራላዊ መንግሥት”፣ “ዲሞክራሲ” ወይም “ምርጫ”) ከሚወክሏቸው ወይም ከሚሰይሟቸው ጽንሰሃሳቦች እና ተጨባጭ ነገሮች ጋር አጉል በማጣመር ግንኙነት ያላቸው የማስመሰል ዝንባሌ ነው። “ገለባውን ከግርዱ” ጋር የማምታታት አዝማሚያ ነው። 

በዚህ አኪያሄድ የኢትዮጵያን ነገደ ብዙ ዜጎች በእኩልነት በመወከል በኃቅ የሚሠራ ምክር ቤት ወይም ፌደራላዊ መንግሥት ቦታ በአስመሳይ (ግን ተቃራኒ፣ የማይሠራ) ዘረኛ ግልባጩ ተይዟል። በ“ሕገ መንግሥት” ስም እውነተኛ ሕገ መንግሥታዊነት ከጽንሱና መንፈሱ ተጨናግፎ አምባገነናዊ ሥርዓተ አልበኝነት ሰፍኗል። ባጭሩ፣ የጽንሰሃሳቦች፣ መርሆችና ተቋማት መጠሪያዎች ውጤታዊ ሚና በስም የሚጠሯቸውን ነገሮች ጽንሳዊና መርሃዊ ይዘት ከጅምሩ አኮላሽተው ትርጉም የለሽ ማድረግ ወይም በእውን አለመኖራቸውን በአስመስሎ መደበቅ ሆኗል።              

መዋቅር ቀያሪ ትግል ለምንና እንዴት?

ለምን? ዛሬ የኦርቶዶክስ ሥርዓተ እምነትና ተቋማት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አፍራሽ የዐመጽ ተግባሮች አካተው አዲስ አይደሉም። በዘመነ ወያኔ የተጀመሩና እየተባባሱ የመጡ የዘረኛ አገዛዞች መዋቅራዊ ድርጊቶች ናቸው። እንደ አገርም የገጠመን ይበልጥ አስጊ እየሆነ የመጣው የህልውና ውጥረትም እንዲሁ ነው። ሕመሙ በቀጥታ የቤተ ክህነት ወይም የኢትዮጵያ የራሷ ሳይሆን ባመዛኙ ከአምባገነናዊ የፖለቲካ ልምዳችን የመነጨና ዛሬም በርዝራዡ ያልተለየን ሥርዓታዊ በሽታ እንደሆነ ስውር አይደለም። 

ውጥረቱ መዋቅራዊ ወይም ሥርዓታዊ ነው ስንል አገራዊ ህልውናችንም ሆነ መንፈሳዊ ኑሯችን ለአስርተ ዓመታት የተመሳቀለው በዚህ ፈላጭ ቆራጭ ቡድን ወይም በዚያ ዘረኛ አገዛዝ ብቻ አለመሆኑን ልብ በማለት ነው። በጠብና ግጭትም ሆነ በተጨባጭ ተጓዳኝነት የተለያዩ ወገኖችና አገዛዞች በቅብብሎሽ ያነፁትንና ያራመዱትን ስታሊናዊ የትርክት፣ የአስተሳሰብ፣ የድርጅትና የገቢር መረብ በማስተዋል ነው።

ከዚህ አንጻር ስናየው የወያኔዎችና ኦነጎች አረመኔያዊ፣ ፀረ አማራ ሕዝብ ጭፍጨፋ ሳይቀር በቀኖና እና ፖለቲካ መዋቅር የታጀለ እንደሆነ እንረዳለን። የጣጠኛው ኢትዮጵያ አብዮት ተረፈ ውጤት የሆኑት ሕወሓትና ኦነግ በፉክክርም ይሁን በትብብር የሚጋሩት ጎጠኝነት የሃሳብ ይዘት አለው፣ ምንም እንኳን ሃሳቡ እዚህ ግባ የማይባል፣ ቀለም ቀመስ ድንቁርናን እና ስግብግብ ዘረኝነትን የሚያንጸባርቅ ቢሆንም። 

በዚህ ርዕዮታዊና መዋቅራዊ ጎኑ የወያኔዎችና ኦነጋውያን የዘር ፖለቲካ ልምድ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ሥልጣኔም ሆነ ዘመናዊ አገራዊ ዜግነት ጋር ተጣጥሞ አያውቅም። ሊጣጣም የሚችልም አይደለም። እንዲያውም ልምዱ በመሠረቱ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ደመኛ እንደሆነ እናውቃለን።

በተጨማሪ ልብ ማለት ያለብን ግን ገዢው ጎሠኛ ሥርዓት ለአገራዊ ህልውናችን ጠንቅ የሆነው የተገላቢጦ ራሱን የአገር ኋላ ቀርነት አስወጋጅ፣ “ተራማጅ” ወገን አድርጎ በማቅረብ ነው። የኢትዮጵያ “ችግሮች” የሚላቸውን ለመግለጽና “ለመፍታት” ምንጊዜም በሚያደርገው ከጽንሱ ብልሹ የሆነ ሙከራ ነው። 

የጎጥ ፖለቲካን መሠረቱና የሁሉ ነገር መመዛኛ ያደረገው ሙከራ የሚያጎላው የአገሪቱ ነገዳዊ ማኅበረሰቦችን ማንነቶች/ልዩነቶች በማጦዝ ደሴታዊ ቅርጽ ሰጥቶና ከአገራዊ አንድነታቸው መንፈስ ጋር አጣልቶ ነው። የእርስ በርስ “ግንኙነታቸውን” የሚያየው በአጥቂና ተጠቂነት፣ ጨቋኝና ተጨቋኝነት ወይም ጎጂና ተጎጂነት እንጂ በምጣኔ ሃብትና በማኅበራዊ ኑሮ ባሏቸውን መዋቅራዊ ትስስሮች ወይም ባህላዊ ውርርሶች አይደለም። ፖለቲካው በተንዛዛ ዘርኝነት ስለታወረ የኢትዮጵያ ብዝሃን ማኅበረሰቦች በተጨባጭ የሚጋሯቸውን መሠረታዊ ፈተናዎችና ዕድሎችም ሆነ እምቅ የልማት ኃይል የሚያይበት አይን የለውም። 

የዘውግ አገዛዙን ለአገር ጣጣዎች መፍተሔ አፈላለግ ስንመለከትም አኪያሄዱ ለመላ የኢትዮጵያ ዜጎች የሚበጅ የተመዛዘነ አገራዊ ልማት የማምጣት ዝንባሌ የሌለው መሆኑን እናያለን። “መፍትሔው” ራሱ ለአገር ትልቅ ችግር እንደሆነ ስናይ ውለን አድረናል። የአንድነትና ሰላም ውቃቢ በራቀው፣ ሕዝብ አተራማሽና አሸባሪ የዘር ማንነት ፖለቲካ፣ የዘር ማንነት ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የዘር ማንነት መንፈሳዊ ኑሮ ተከፋፍሎ የተከለለ “መፍትሔ”!  

በነዚህና ሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት የህልውና ውጥረት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥርዓት ለውጥ ፈተና እንድሆነ መገንዘብ ግድ ይለናል። ለኢትዮጵያውያን በጠቅላላና ለአማራው በተለይ የመዋቅር ቅየራው ዕቅድ እንግዲህ የቅንጦት ንቅናቄ ሳይሆን እንደ አገርና ማኅበረሰብ የምኖር አለመኖር ትግል ነው፣ ወይም ሆኖ መኪያሄድ አለበት።

መዋቅር ቀያሪ ትግል እንዴት? ኢትዮጵያን ለዘለቄታው ከጥፋት ለማዳን የሥርዓት ለውጥ አስፈላጊነትን  ማወቁ ለአገር ድኅነት ንቅናቄው አነስተኛ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ግዙፉና ፈታኙ ጥያቄ በምን መንገድ ነው ንቅናቄው ሊኪያሄድ የሚችለው ነው። ይህ ከማያቋርጥ የሃሳስቦች፣ አላማዎች፣ ድርጅቶችና እንቅስቃሴዎች ቅንብር ጋር የተያያዘ ውስብስብ ጉዳይ መሆኑ አይካድም።

እዚህ ባጭሩ ሁለት የተለያዩ ግን ግንኙነት ያላቸው (ወይም ሊኖራቸው የሚችል) የትግል መንገዶች መጠቆም እንችላለን – አንደኛው በቀጥታ ወደ ተጨባጭ ድርጊት፣ እርምጃና እንቅስቃሴ ያዘነበለ ሲሆን፣ ሌላው መንገድ ይበልጥ አላ፟ሚ፣ አሳ፟ቢና ሥር ነቀል ነው። 

የፊተኛው ዘዴ የአገዛዙ ፖለቲካ አስተሳሰብ፣ እምነቶችና ዲስኩሮች ላይ እምብዛም ሳያተኩር በቀጥታ ተጨባጭ ኃይሎቹን፣ አመራሩን፣ ፖሊሲዎቹንና ድርጊቶቹን ይገጥማል፣ ይፋለማል። በዚህ መንገድ ከተቃዋሚና አማጺ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ጋር በኅቡዕም በይፋም በመቀናጀት ገዢው ቡድን ላይ ውጤታማ የ‘ሥልጣን ልቀቅ’ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል። 

ሁለተኛው መንገድ የለውጥ ኢላማውን ይበልጥ ሰፋና ገባ አድርጎ የገዢ መዋቅሩን ርዕዮት፣ የፖለቲካ ቅርጽና ሥነ አመክንዮ ወይም ፓራዳይም እና ተያያዥ (መዋቅራዊ) ገቢሮች ያካትታል። የሥርዓት ለውጥ ትግሉን የአጭር/የመካከለኛ ጊዜ ተልዕኮዎችና እንቅስቃሴዎች ረዘም ያለ ጊዜ በሚወስዱ ስልታዊ ንቅናቄዎች ለዘለቄታው አቅጣጫና ቅደም ተከተል ያስይዛል፣ ይመራል።

ሁለቱ የለውጥ መንገዶች ያላቸው መዋቅር ቀያሪ እምቅ ኃይል እኩል አይደለም። የመጀመሪያውን ዘዴ፣ ካለ፟ አገዛዝ ውስጥ ወይም አካባቢ የሚነሱ አፈንጋጭ ቡድኖች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እነዚህ ወገኖች የውጭ ሕዝባዊ አመጽ ጉልበትን ለመሠረታዊ ለውጥ ዕቅድ ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ለተወሰነ ሥርዓት ጥገና ብቻ የመዋል አዝማሚያ ያላቸው ናቸው፣ ምንም እንኳን ለመዋቅራዊ ቅየራ አስተዋጽዎ ማድረግ ፈጽሞ አይችሉም ብለን መደምደም ባንችልም። 

እንቅስቃሴያቸው ባለ፟ ጨቋኝ የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ የተወሰኑ ለውጦችና ማሻሻያዎች ከማድረግ አልፎ ያለውን ብልሹ የፖለቲካ መዋቅር ከሥር መሠረቱ ይለውጣል ተብሎ አይጠበቅም። እንዲያውም፣ በአብይ አህመድ ወደ ሥልጣን አመጣጥና አገዛዝ እንዳየነው፣ ሥርዓት “ጥገናው” ባመዛኙ ነገሮችን የሚያባብስ ይሆንም ይሆናል። አገርን፣ መንግሥትን፣ ምጣኔ ሃብትን፣ ኅብረተሰብንና መንፈሳዊ ኑሮን ይበልጥ ሊያመሳቅል እንደሚችል ዛሬ በገሃድ እያየን ነው።

በኢትዮጵያ የሰፈነው አፓርታይዳዊ አገዛዝ ከሥር መሠረቱ ስለመፈ፟ንቀሉ መናገር ፍንቀላው ምን ቅርጽ እንደሚይዝ መግለጽ ማለት አይደለም። መሠረታዊ ለውጦች የሚለዩት በሃሳብና ስልት ጥልቀታቸው እንዲሁም በድርጅታዊ ሥነ ሥርዓታቸውና ንቅናቄያቸው ነው። በፈጣን ድርጊቶቻቸው፣ በቀውስ ፈጣሪነታቸው ወይም በደም አፋሳሽነታቸው አይደለም። በሚቀጥለው የመጨረሻ (ክፍል ሦስት) ጽሑፍ ለማሳየት እንደምሞክረው፣ ውጤታማ መዋቅር ለዋጭ ንቅናቄዎች በሃስብ መስክም ወሳኝ ቦታ አላቸው።

                                                                                                      ይቀጥላል…               

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,723FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here