spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትበአጣየ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በተመለከተ የተሰጠ አስቸኳይ መለግለጫ ትግስት...

በአጣየ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በተመለከተ የተሰጠ አስቸኳይ መለግለጫ ትግስት ገደብ ሲያጣ፣ ጥፋትን ያመጣ፤

በአጣዬ፣ በሸዋ ሮቢት
Google map of Ataye and area

በአጣዬ፣ በሸዋ ሮቢት እና አካባቢ በሚኖረው የዐማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ የእብሪት ወረራ እና የንብረት ውድመት ዘመቻዎች በአዲስ መልክ መቀጠሉን በከፍተኛ ኀዘን እና እንጀት በሚበጥስ ምሬት እየታዘብን እንገኛለን። መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚል የሽፋን ስም በሰጠው፣ እራሱን ግን ‘የኦረሞ ነፃ-አውጭ ሠራዊት’ ብሎ በሚጠራው እና የኦሮሞ ክልል ልዩ ኃይል እና የፖለቲካ ክፍሉ እገዛ ያልተለየው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ባለፉት አራት ዓመታት በወለጋ እና በሌሎች ቦታዎች በሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመው ማንነት/ዘር-ተኮር ሰቆቃ፣ የጅምላ ማፈናቀል እና ጭፍጨፋ ሣያባራ መቀጠሉ ይታወቃል። ይኽ አሸባሪ ቡድን መንግሥት ሊታደገው ባልፈለገው የዐማራው ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ሰቆቃ እና ጭፍጨፋ በዚኽ ደረጃ መቀጠሉ ማንኛውንም ቀና-አሳቢ፣ ሰላም ፈላጊ እና አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊያሳስብ ይገባል።

፩ኛ. ለዐማራ ክልል አመራር፡- የዐማራን ክልል የምታስተዳድሩ የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎች በሌሎች ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች በማንነታቸው ምክንያት ከቤት-ንብረታቸው በጅምላ ሲፈናቀሉ፣ አቅመ-ደካማ የሆኑት ቤት እየተዘጋባቸው በእሣት ሲጋዩ፣ እንዳውሬ እየታደኑ በጭካኔ ሲጨፈጨፉ፣ ዐማራው መታወቂያው እየታየ አዲስ አበባ እንዳይገባ ሲከለከል፣ ወዘተ.. ድርጊቱን ማስቆም ቀርቶ ይፋዊ ተቃውሞ እንኳን ማሰማት አለመቻላችሁ፣ በአሁኑ ጊዜ በአጣዬ እና በሌሎች ቦታዎች ላይ በመደረግ ላይ ላለው የወንጀል ድርጊት ይሁንታችሁን ከመስጠት ተለይቶ የማይታይ እጅግ አሣፋሪ የክኅደት ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። አመራሩ በተደጋጋሚ ያሳየው ልክ የሌለው ድክመት የዐማራን ሕዝብ የማይመጥን አሣፋሪ ተግባር ነው። በዐማራው ሕዝብ ላይ በኦሮሞ ተስፋፊዎች እየደረሰ ያለውን አውዳሚ ጦርነት ማዕከላዊ መንግሥት ያላስቆመው በአቅም ማነስ ምክንያት ሣይችል ቀርቶ ሣይሆን ስላልፈለገ እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም። ስለሆነም፣ በትሕነግ ወረራ ወቅት ማዕከላዊ መንግሥት የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማቱን ተከትሎ ከላይ-እስከ-ታች ያላችሁ የክልሉ አመራር የክልሉ ሕዝብ ያለውን ይዞ እንዲዘምት የበኩላችሁን ጥሪ እንዳቀረባችሁ እና ሕዝቡም ተገቢውን አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቶ በከፈለው መስዋዕትነት ውለታው ባይቆጠርለትም አገርን ከመፍረስ፣ መንግሥትንም ከመውደቅ መታድጉ አይዘነጋም። አሁንም ምንም ምክንያት ሳትደረድሩ አጠቃላይ የክተት አዋጅ እንድታውጁ እና በሥራችሁ ያሉት ልዩ-ኃይል እና ሕዝባዊ-ኃይል /ሚሊሽያ/ እንዲሁም ፋኖ በጋራ ተሠልፈው ማዕከላዊ መንግሥቱ ሊያቅፈው ያልፈለገውን ይኽን ሕዝብ ከተደገሰለት ዘሩን የማጥፋት ዘመቻ እንዲታደግ እና ጥቃቱን እንዲቋቋም አስቸኳይ ጥሪ እንድታቀርቡ እንጠይቃለን።

የክልሉ አመራር ይኸን ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ወረራውን ማስቆም ካልቻላችሁ፣ የዐማራን ሕዝብ የማይመጥን አሣፋሪ እና አስነዋሪ ድክመት ነውና ከያዛችሁት ኃላፊነት በፈቃዳችሁ እንድትለቁ እንጠይቃለን። በሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት የምትገኙ የክልሉ ተወካዮችም ተመሣሣይ እርምጃ እንድትወስዱ እናሳስባለን።

፪ኛ. ለማዕከላዊ መንግሥት፡- ለተደጋጋሚ ጥቃቶች ሰለባ የሆነው የዐማራ ሕዝብ በዚኽ አሸባሪ ቡድን ሊሰነዘርበት የሚችለውን ዘሩን የማጥፋት ዘመቻ በመገንዘብ ማዕከላዊ መንግሥት በሰላም የመኖር፣ ሰብዓዊ እና የዜግነት መብቱን የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ ሲያሳስብ መቆየቱ ቢታወቅም፣ ምላሹ ዕድልህ ያውጣህ ከሚል እሳቤ ያልተለዬ ታሪክ ይቅር የማይለው እሣፋሪ ቸልተኝነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ባለፉት አራት ዓመታት ተኩል በዐማራው ሕዝብ ላይ ለደረሱት እና በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ላሉ ዘር-ተኮር ጥቃቶች፣ እንግልት፣ ሰቆቃ፣ ጭፍጨፋዎች እና የንብረት መዘረፍ እና መውደም ተቀዳሚ ተጠያቂው በጠ/ሚ ዐብይ የሚመራው ማዕከላዊ መንግሥት ነው።

በቪኦኤ ኤፕሪል 24, 2021 ቃለመጠይቅ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደተናገሩት፣ ቀደም ብሎ በ2013 ዓ. ም በተደጋጋሚ ወደ አካባቢዉ በፌደራል መንግስት ተልከው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቡድን እንዳጠኑት በአካባቢው እየሰለጠነ ያለ ከፍተኛና ልዩ ትጥቅ የያዘ ተዋጊ ሃይል እንደነበረ በጥናታቸው በማወቃቸዉ ለሚመለከታቸው የፌደራልና ክልል መንግስት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ አሳዉቀዉ ነበር። የፌደራል መንግስት ግን ሰልጣኞቹን ለማጥፋት ስራ አልሰራም። በተቃራኒዉ የሰለጠነ ሃይል የለም ተራ ገበሬዎች ናቸው በማለትና ከህዝብ በመደበቅ ለአሸባሪዉ ሃይል ድጋፉን እስከአሁን ሲሰጥ ቆይቷል። የኦነጉም አሸባሪው ሃይል ተደጋጋሚ ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል።

እንዳዉም የተጎዳዉን የአማራ ህዝብ በመዉቀስ ወይም በማስፈራራት ስራ ላይ ተጠምዷል። መንግስት ሃላፊነቱን ካለመወጣትም አልፎ ይህን ነገር ሆን ብሎ ደብቆ ህዝብን ለተድጋጋሚ ለአደጋ በማጋለጡና በማስጨፍጨፉ በሃላፊነት ሊጠየቅ ይገባል። በሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሞ ክልል አስተዳደርም ይኽ ሽብርተኛ ቡድን እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ እና በክልሉ በሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች ላይ የጥፋት ዘመቻውን ሲያደርግ በዝምታ በማየቱ ወይም በተባባሪነቱ በዘር-ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ ነው።

ማዕከላዊ መንግሥት በትሕነግ ሁለት-ዙር ወረራ ከተፈጸመው የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት እና ዝርፊያ ለማገገም ዕድል ያላገኘው እና ትኩረት ያልተሰጠው የዐማራው ሕዝብ፣ ከአዲስ አበባ የቅርብ እርቀት ጭምር በኦነግ አሸባሪ ታጣቂዎች ይኽን ያኽል ግፍ ሲሠራ እና ጭፍጨፋ ሲካሄድ ቢያንስ ሕዝቡ እራሱን መከላከል እንዳይችል እንዳይደራጅ እና እንዳይታጠቅ መሰናክሎችን በመፍጠር እና ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ አመራሩን በመቀያየር ጭምር የተወሰዱ ጣልቃ-ገብ እርምጃዎች የፈጠሩት አሉታዊ ሁኔታ ለአረመኔያዊ ጥቃቶች ተጋላጭ እንዲሆን ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። አሁንም ማዕከላዊ መንግሥት ይኽ የሽብር ቡድን በዐማራው ሕዝብ ላይ ያወጀውን ዘር-የማጥፋት አረመኔያዊ ዘመቻ በአስቸኳይ ሊያስቆም እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማድረግ ኃላፊነቱን እና የዜጎችን በሰላም እና በሕይዎት የመኖር መብታቸውን የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ አበክረን እንጠይቃለን። መንግስት በውስጡ የተሰገሰጉ ኦነጋዊና ወያኔያዊ ምስጦችን በማጽዳት የሃገረ-መንግስትን ምሰሶ ማጠናከር ግዴታው መሆኑን እንዲገነዘበው እናሳስባለን።

፫ኛ. ለዐማራ ልዩ-ኃይል፣ ለሕዝባዊ-ታጣቂ /ሚሊሽያ/ እና ለፋኖ፡- የዐማራ ልዩ-ኃይል፣ ሕዝባዊ-ታጣቂ /ሚሊሽያ/ እና ፋኖ ዐማራው ወገናችሁ በገዛ አገሩ በጠላትነት ተፍርጆ ከሚደርስበት አድልዖ፣ ውርደት፣ የጅምላ መፈናቀል እና ጭፍጭፋ ለመታደግ እንዲሁም ከአገር መከላከያ ሠራዊት ፊት እና ጎን ተሠልፋችሁ ለአገራችሁ አንድነት ክቡር ሕይወታችሁን ለመስጠት ወደ-ኋላ እንደማትሉ በተግባር ማረጋገጣችሁን እኛ ብቻ ሣንሆን አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመሰክርላችሁ ጀግኖቻችን በመሆናችሁ እንኮራባችኋለን። በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት በማይፈልጉ እና በውድ አገራችን መቃብር ላይ የራሣቸውን ‘አዲስ አገር’ ለመመሥረት ያለሙ ክፍሎች ዐማራውን ለእቅዳቸው መሣካት እንቅፋት ነው ብለው ስላሰቡ የጥቃታቸው ዒላማ ማድረጋቸው ይታወቃል። ዐማራው እራሱን ከተደገሰለት ዘሩን የማጥፋት፣ ቢያንስ ተዳክሞ አቅመ-ቢስ እንዲሆን እና እንዲደኸይ ለማድረግ የተከፈተበትን ዘመቻ ሊቋቋም እና የኢትዮጵያን አንድነት ከሚሹ ወገኖች ጋር በመሆን ይኽን ሰይጣናዊ እቅድ ማክሸፍ ይኖርበታልና የዐማራ ልዩ-ኃይል፣ ሕዝባዊ-ታጣቂ /ሚሊሽያ/ እና ፋኖው ለዚኽ መራር ትግል ይበልጥ በሁሉን-አቀፍ ድርጅታዊ ቅርጽ እንድትዘጋጁ እና አንድነታችሁን ጠብቃችሁ ከሕዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን።

፬ኛ. ለአገር መክላክያ ሠራዊት፡- የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገርን አንድነት እና የሕዝብን ሰላም የማስከበር ኃላፊነት እና ግዴታ ያለበት ክፍል መሆኑ የታወቀ ነው። ማንኛውም ማኅበረሰብ በራሱ አገር ላይ በማንነቱ ተለይቶ ጥቃት ሲደርስበት እና ዘሩን የማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድበት የአገር አንድነት እና የሕዝብ ሰላም ለአደጋ እንደሚጋለጡ የሚያጠያይቅ አይሆንም። በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት የዐማራው ማኅበረሰብ በማንነቱ ተለይቶ ዘሩን የማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶበት ለተደራራቢ ጥቃቶች ሰለባ መሆኑ እና መጨፍጨፉ ይታወቃል። ይኽ ሁሉ ሲሆን ግን በሰላም የመኖር የዜግነት መብቱን የማስከበር ኃላፊነትም፣ ግዴታም ያለበት ማዕከላዊ መንግሥት ሊታደገው አልቻለም። እንደ ደን እሳት እየተቀጣጠለ ያለው ደባዊ የእርስ በርስ ጦርነት የብሄራዊ መከላከያ ሰራዊታችንን ከድንበር ማስከበር ዐብይ ተልዕኮው አስፈንግጦ ወደ ወገንተኛዊና መንደራዊ የፖሊስ ስራ (ኮማንድ ፖስት)
እያዘቀጠው መሄዱም ያሳስበናል። የተከፋፈሉ ግርግዳዎች ያሉት ቤት አይቆምምና! ስለዚህ በአገሩ አንድነት ቀናዒ የሆነው ይኽ ማኅበረሰብ ዘሩን ለማጥፋት እየተሰነዘረበት ካለው ዘመቻ እራሱን ለመታደግ በተገደደበት የአልሞት-ባይ-ተጋዳይ ፍልሚያ እና በአገሩ አንድነት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ላይ የተቃጣን ጥቃት ለመከላከል በሚያደርገው ትግል የአገር መከላከያ ሠራዊት ከጎኑ እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን።

፭ኛ. ለኢትዮጵያ ሕዝብ፡- ሆን ተብሎ በሚቀነቀን የተሳሳተ ትርክት ምክንያት በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የዐማራው ማኅበረሰብ በማንነቱ ተለይቶ ዘሩን ለማጥፋት ዘርፈ-ብዙ ዘመቻዎች እንደተከፈቱበት እና ለእልቂት እንደተዳረገ ቢያንስ አብዝሃኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው ጉዳይ ነው። በዐማራው ላይ የተከፈተው ማንነት-ተኮር ዘመቻ እሱ ላይ የሚቆም ሣይሆን ሌላውንም በየተራ የሚያዳርስ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት እና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሰላም በእጅጉ የሚፈታተን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ስለዚህ፣ ዐማራው እየተካሄደበት ካለው ዘሩን የማጥፋት ዘመቻ ለመታደግ ተገድዶ በሚያደርገው ትግል ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ፣ነግ-በኔ ብለውም ሆነ በጋራ ኢትዮጵያዊነት፣ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪውን ከአደራ ጭምር ያቀርባል።

፮ኛ. ለመላው የዐማራ ሕዝብ፡- ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት፣ ለዜጎች ሁሉ እኩልነት እና ለጋራ ሰላም ቅድሚያ መስጠትህ እና እራስህን ከዚያ ውጭ አይተህ አለማወቅህ ዘርህን ለማጥፋት አቅደው በማንነትህ ላይ ዘርፈ-ብዙ ጥቃቶች እና ግልጽ ጦርነት ታውጆብህም እንኳ መንግሥት አለ በሚል አጉል ተስፋ በመዘናጋትህ ለቀጣይ ጉዳት ተዳርገሃል። ኢትዮጵያዊ ወገኖችህም ከጎንህ ሊቆሙ እና የጋራ አገራቸውን አንድነት ማስከበር የሚቻለው ተደራጅተህ ኅልውናህን ማስከበር ስትችል ብቻ ነው። ይኽን ማድረግ ደግሞ ሳትወድ በግድ የምትገባበት ታሪክ የጣለብህ ዕዳ ሆኗል እና በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በያለህበት በተለያዩ መንገዶች ተደራጅተህ የተቃጣብህን የጥፋት ዘመቻ እንድትመክት እነሆ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በተለይ ዲያስፓራ ያለው የዐማራ ተወላጅ ሰቆቃውን ለዓለም በማሳወቅ፣ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ ለህግ ተጠያቂነትን በማመቻቸትና ቁሳዊ ድጋፎችን በማቅረብ የአለንላችሁ ስራዎቹን በመናበብ አጠናክሮ እንዲሰራ ያስፈልጋል።

በዐማራው ሕዝብ እስካሁን የታየው ከመጠን ያለፈ ትእግስት ከፍርሃት ወይም ካለማወቅ ሣይሆን ለአገር አንድነት እና ለጋራ ሰላም ሲባል የከፈለው ዋጋ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ትእግስቱ ግን ገድቡን አልፎ ሊሸከመው የማይችለውን ዕዳ ጥሎበታል። በቃ የሚልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ሁሉም ሊረዳው ያስፈልጋል።

ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም

SIGNATORY ORGANIZATIONS

 1. Adwa Great African Victory Association (AGAVA)
 2. All Shewa Ethiopian People Multipurpose International Association
 3. The Amhara Association in Queensland, Australia
 4. Amhara Dimtse Serechit
 5. Amhara Well-being and Development Association
 6. Communities of Ethiopians in Finland
 7. Concerned Amharas in the Diaspora
 8. Ethio-Canadian Human Rights Association
 9. The Ethiopian Broadcast Group
 10. Ethiopian Civic Development Council (ECDC)
 11. Freedom and Justice for Telemt Amhara
 12. Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause
 13. Global Amhara Coalition
 14. Gondar Hibret for Ethiopian Unity
 15. Major Lemma Woldetsadik Memorial Foundation
 16. Network of Ethiopian Scholars (NES)
 17. Radio Yenesew Ethiopia
 18. Selassie Stand Up, Inc.
 19. Tinsae Le’Ethiopia
 20. Vision Ethiopia
 21. Worldwide Ethiopian Civic Associations Network (WE-CAN)

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here