spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየት  ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መናዱ፣ ከሦስቱ ግንዶች አንዱ!

  ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መናዱ፣ ከሦስቱ ግንዶች አንዱ!

ወንድሙ መኰንን፣
እንግላንድ

መግቢያ

ዘረኞች ካሉ ማን በሰላም ተኝቶ ያድራል? ዘሮኞች ሥልጣን ላይ ከወጡማ፣ አያድርስ ነው። የጎጠኝነትን ጠንቅ በሩዋንዳ አይተናል። የአንድ አገር ልጆች በጎሳ ተከፋፍለው፣ ተጨፋጨፉ፣ ተገዳደሉ። ያሸነፈው አሸንፎ፣ ተሸናፊው በጄኖሳይድ ተክሶ እስከዛሬ ይወቀሳል። ከስህተቱ የተማረ የሩዋንዳ ህዝብ ዛሬ፣ ስለዘር ማውራት በሕግ የተከለከለ ነው። ዘረኝነት በዚያ አገር ዛሬ ዕርም (ታቡ) ቃል ነው። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ይላል ያገሬ ሰው። ኢትዮጵያውያን ግን ከሩዋንዳ መማር አልቻልንም። ትላንት መጥፎ ጊዜ አሳልፈን ነበር። ዛሬም ህዝባችን አሣሩን እየበላ ነው። ሕዝባችን ተገፍቶ ከድጡ ወደማጡ ገብቷል። ነገስ?

የኢትዮጵያ ዘረኞች ጥምድ አድርገው የያዙትና በየጊዜው የሚያቆረቁዙ፣ የዘረኝነት ስሜት ያልነበረውን መንዜውን፣ ጅሩዬውን፣ መርሀቤቴውን፣ ቡልጊውን፣ ተጉለቲውን፣ ወሎዬውን፣ ጎጃሜውን፣ ጎንደሬውን “አማራ” እያሉ ነው። ይኸን አማራ፣ በምናባቸው ጭራቅ አድርገው ስለው ቀን ሲያናውዛቸው ውሉ ማታ ሲያቃዣቸው ያድራል። ይኸን ምስኪን ሕዝብ ያለጥፋቱ ጥፋት ፈጥረውለት፣ (ለምሳሌ የአኖሌ የሌሌ ታርክ) ጠብ ያለሽ በዳቡ እያሉ ይጨፈጭፉታል። ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ሌላው የኢትዮጵይዊነት ትልቁ ግንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ነው። የአንድነት ተምሳሌቱን ከሦስቱ አንዱን ግንድ መገንደስ ማለት የኦርቶዶክስ ሀይማኖትን ማጥፋት ነው። ለነገሩ ደግ የማይመኙልን እንድ ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ (Baron Roman Prochazka)” እና ጄምስ ኤድዊን ባውም (James Edwin Baum) የተባሉ የነጩ ዓለም ጸሐፊዎች፣ እንዲሁም የአሜሪካ ስቴትስ ዴፓርትመንት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሄነሪ ኪሲንጀር ኢትዮጵያ ከበለጸገች ለነጩ ዓለም አደጋ ስልምትደቅን ሦስቱን አምዶቿን ማፈራረስ እንደ ረዥም ዕቅዳቸው (ስትራተጂያቸው) ንድፈው ቁጭ ቁጭ አድርገውልናል። አንዱ አንድ የሚያደርጋትን የዘውድ ሥርዓቷን መገርሰስ ነው። ያንን የደርጉ ሥርዓት አሳክቶላቸዋል። ሀለተኛው የኦርቶዶክስ ሀይማኖቷን ማጥፋት ነው። ደርግ ሞክሮ ሳይሳካለት ለዘረኞቹ ትቶት ጠፍቷል። ሶስተኛው፣ አማራ የሚባለውን ህዝቧን ከሌሎች ጎሳዎች ጋር አጋጭቶ፣ ማስጨፍጨፍ ነው። የወያኔው ኢህአዴግ ለ27 ሂዶበት አሁን ደሞ የኦህዴዱ ብልጽግና ላለፉት አራት ዓመታት እያከናወነላቸው ነው። ፕሮጄክታቸው፣ ገና አላለቀም።

በከንቱ ልፉ ብሏቸው ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያስ አትጠፋም። ኢትዮጵያ ምርጥ የእግዚአብሔር ርስት ናት።

የዘርኝነት ፖሊቲካ በኢትዮጵያ

ዘረኝነትን ሲያሰማምሯት የኢትዮጵያ ዘረኞች “ብሔር ብሔርሰቦች ህዝቦት” ብለው ጠሯት። የፖሊቲካ ቀለም ሲቀቧትም “ፌዲራሊዝም” አሏት። ድንቄም ፊዴራሊዝም! ዓላማቸውን ለማሳካት ህዝቡን በቋንቋ ከልለው፣ “በአፍ መፍቻህ ቋንቋህ ተማር” አሉት። እንዳይግባባብ እኮ ነው! ትልቁ ከፋፍሎ የመግዛቱ ፍቱን ዘዴ የህዝቡን መግባቢያ በቋንቋ አጥፍቶ መደበላለቅ ነው። ኢትይጵያ ከአፍሪካ አገራት የምትለየው አንዱ የራሷን ፊደል መጠቀም ነው። ህዝቡን የጋራ እሴት እንዳይኖረው አንድ ፊደል እንኳን እንዳይጠቀም፣ ኩቤ የሚባል የላቲን የፊደል ሾርባ ሾርበው ጋቱት።

ታላቋ የተዋጣላት ፌዴራሊስት አገር ብትኖር የተባበረችው አሜሪካ (United States of America – US) ናት። ከዚህ በኋላ እንዲቀለን፣ አሜሪካ እንበላት። እንደ አገሪቱ የሕዝብ ቆጠራ ስታቲስቲክስ ጽሕፈት ቤት፣ በአሜሪካ 350 ቋንቋዎች ይነገራሉ። ከንግሊዝኛ ሌላ፣ ከሶስቱ ሁለቱ የአሜሪካዊ የሚናገረው ስፓኒሽ ነው። የፌዴራሉ ቋንቋ ግን እንግሊዝኛ ነው። ትምህርቶቹም በቀደምትነት የሚሰጡት በእንግሊዝኛ ሲሆን፣ ተጨማሪ ቋንቋ እንደፍላጎቱ በትምሃርት ቤትም በዩኒቨርሲቲም ይሰጣል። ግዕዝም ሳይቀር። በዚህ የተነሳ ከሎስ አንጀለስ እስከ ኒው ዮርክ ከተሞች፣ ሕዝቡ በአንድ ቋንቋ ይናገራል፣ ይግባባል፣ ይነጋገዳል፣ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ይሠራል። አስተርጓሚ አያሻውም። አገሪቷ፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮናሚ በልጽጋ፣ ልዕለ ኃያል ህናለች። እነዚህ እንግዲህ በእውነቱ የተዋህዱ ሀምሳ አገራት ናቸው። እኛስ? አቦ ተወና!

ዘረኝነት የተጠናወታቸው የሕወሀት ሊሂቃን ተደራጅተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ተዋዶ፣ ተፋቅሮ፣ እና ተጋብቶ ተዛምዶ ከሚኖርበት፣ በዘር በታተኑት። በለስ ቀንቷቸው ለ27 ዓመታት በሕዝቡ ልብ ውስጥ ዘረኝነትን ዘሩት። ኢህአዴግ የሚባል ካባ ደርበው፣ የዘረኞች ካድሬ አሰልጥነው ሕብረተሰቡን በዘረኝነት  መርዝ በከሉት። የዘረኛ ሕገ-መንግስትም ቀርጸው አከናነቡት። የዘሩት የዘረኝነት ዘር፣ ዛሬ ላይ በቅሎ አብቦ፣ ፍሬው ጎመራ። ዘረኝነትን ይጸየፍ የነበረውም ”ከሌላው በምን አንሼ፣” በሚል ስሜት ዘረኛ ሁኖ ቁጭ አለ። ታዲያ በአገራችን ፍሬው የጎመራው ዘረኝነት ውሎ አድሮ መልሶ ፈጣሪውን የትግራይ ጽንፈኛን ቀረጠፈው። ጄኖሳይድ እያለ ቢጮህ ማን ይሰማዋል? ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው ይባላል። ሌላ የራበው ዘረኛ ተነሳለታ! ለሕዝቡም ተረፈለት። ለኃጢያን የመጣ ለጻድቃንም ይተርፋል ይባል የለ? መቅሰፍቱ እሱን ብቻ ይዞ በጠፋ! አማራውንና አፋሩን ረፈረፈው።

በወያኔ ሥር ተኮትኩቶ አድጎ ለቁምነገር በቅቶ፣ ጊዜ ጠብቆ፣ የሕዝቡን ብሶት ተጠቅሞ፣ አሳዳጊዎቹ ላይ በብልሀትና በዘዴ አምጾ፣ በተለይ አማራውን አግባብቶና አወናብዶ (convince and confuse) የአራት ኪሎን ወንበር የነጠቀው ተረኛው ዘረኛ የኦሮሞ ጽንፈኛ ሁኖ ተገኘ። ኮቱን ገለበጠና “ብልጽግና” ነኝ አለ እንጂ ያው እህአዴግ ነው። ያው የዘረኝነት እንጂ ሌላ ሥርዐት እኮ አያውቅማ። ለውጥ መጣልን ብለን አሸሻ ገዳሜ ያልን ሁላ ካለንበት ወርደን ከድጡ ወደ ማጡ ወድቀን እየዳከርን ነው።

ሙሉውን በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here