spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትይድረስ ያሻግራሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎቦት መሸጋገሪያ ድልድዩን ላፈረሱት መሪ ለኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር...

ይድረስ ያሻግራሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎቦት መሸጋገሪያ ድልድዩን ላፈረሱት መሪ ለኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ



ከአልማዝ አሰፋ

ወደ ገላትያ ሰዎች 05:21-22
“መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።”

ምንም እንኳ ኢትዮጵያን የጎሰኝነትና የዘረኝነት ተላላፊ በሽታ ከለከፋት ያለፉትን ዓመታት ስንቆጥር ከስባት አስርታት በልጠዋል:: የሻቢያ አገር መገንጠል ኤርትራን ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን እህቶቻቸውና ወንድሞቻቸው ለመለያየት ከተጀመረ ያለፉትን ሁለትና ስስት ትውልድ አበሻዎች በድህነት ማቅ ውስጥ ከቷቸዋል:: ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት የ”ነፃነት” ተዋጊ ነን : ለሕዝብ ቆመናል : ከኢትዮጵያውያን ጋር መኖር ወደሗላ አስቀርቶናልና ነፃ ወጥተን ኤርትራን የአፊሪካ “Monaco” ወይም “Hong Kong” እናደርጋታለን ሲሉ የጋን ድምፅ በማሰማት ያሰለቹን የጊዜው የኤርትራ የመገንጠል ፖለቲካ አቀንቃኞችና ደጋፊዎቻቸው የተማሩ ደንቆሮዎች መሆናቸውን በሂደት አሳይተውናል:: ወያኔ ሲመጣ የተመኙትን አገኙ:: ወያኔ ለኢትዮጵያ ባህር መውጫ እንኳን ሳይል ያለአንዳች ማመንታት ከአሰብ ጋር ሂዱ ራሳችሁን ቻሉ በማለት ያለድርድር ለቀቃቸው:: ኤርትራም ነፃ አገር ሆነች:: ባለፉት ሃያ ምናምን የነፃነት ዓመታት ኤርትራውያን ያሉበትን ቅዠትና ስቃይ ጭንቅላት ያለውና በነፃ ያለአንዳች የውጭ ተፅእኖ የራሴን አስተሳሰብና አመለካከት እደነግጋለሁ ያለ ሰው የኤርትራን ውድቀት በቀላሉ ማየት ይችላል:: ወያኔ ጠባብ የኤርትራ ጎሰኞች ተገንጣዮችንና መሪያቸውን ኢሳያስን አሞኝቷል:: ኢሳያስ ኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅት ከማለት ይልቅ : የኢትዮጵያ ነፃ አውጪ ድርጅት ቢል መለስ የያዘውን ስልጣን በተጎናፀፈ ነበር:: ወያኔም ባልተፈጠረ ነበር::


የኤርትራ የነፃነት ጥያቄ ወያኔን ወለደ:: ወያኔ ሻቢያ ያቀጣጠለውን የጎሳ ፖለቲካ በሰፊው ኢትዮጵያ ውስጥ አነደደው:: ይህምን ነው ዛሬ የኦሮሞ ጎሰኞችና ዘረኞች እያውለበለቡ ያሉት:: ዛሬ የኦሮሚያን ክልል የሚመራውና ከዚያ የጠባብ ጎሰኝነት ፖለቲካ አውድ ውስጥ ወጥቶ የኢትዮጵያ መሪ የተባለው : ያሳደገው እንጀራ አባቱ ኢሐደግ ሲያራምድ የነበረውን በኢትዮጵያ ስምና ባንዲራ የተሸፈነውን ኦሮሞሚያ ለማሳካት ጥንታዊና ታሪካዊ የኢትዮጵያ መሰረትና ምሰሶ የሆነችውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ቤተክርስቲያንን ውድቀት የቆሰቆሰው:: ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ማድከም ኢትዮጵያዊነትን አድክሞ ኦሮሞዊነትን ከፍ የማድረጊያ ዘይቤ ነውብለው ያሰቡ የሰው ጅላጅሎች ያልተገነዘቡት በ2000 ዓመታት በላይ ከዚህ የባሰ ውጣ ውረድን በማየት ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን በውጭና በውስጥ ጠላቶች ተደጋግማ ተፈትና ያልተበገረችውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አዙሪት እንደያዘው ውሻ የሚሄድበትን አቅጣጫ የማያውቅ ጎሰኛ ዘረኛ ጎጠኛ አያሸንፋትም:: ይህንን መረዳት ያልቻለ መሪ እንዳለፉት እብርተኛ መሪዎች የውድቀትን ጥዋ ለመቅመስ ይቅበጠበጣል:: ኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶንና ኢትዮጵያን አገር የነካ : የለውም በረካ::

ይህ ኢትዮጵያን ያሻግራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሪ እንዴት የተሰጠውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍቅርና ክብር ትእቢትና ንቀት በተሞላበት የሰላሳ ሰባት ደቂቃ ንግግር እንዳልነበረ ማድረጉ ካለፉት እብርት ካሳዩት የኢትዮጵያ መሪዎች አይለይም::


በመጀመሪያ ከራሴ ስጀምር ስልጣን ላይ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ጎሰኛ ዘረኛ አይደለም:: ኦሮሞዊነቱን ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድም ነው:: ክእሱ እድሜ በላይ ለዘመናት የቆዩትን የኢትዮጵያ ችግሮችን በአጭር ጊዜ መፍታት አይችልም:: ጊዜ ይሰጠው እያልኩ ስከራከርለት ነበር:: ከዝያም አልፎ ኦርቶዶክስ ባይሆንም ፈርሃ እግዚአብሔር ያለው ሃይማኖተኛ በመሆኑ እንዲህ አይነት ሰውነትን አውርዶ ጎሰኛ ይሆናል ብዬ አላሰብኩትም:: በተለይ በፖለቲካ ምክንያት ተከፋፍላ የነበረችውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያኔን ሁለቱን ክፍሎች የእምነቴ ክፍሎች አደሉም ሳይል በአገራችን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያላትን ታሪካዊ ከፍተኛ ቦታ በመገንዘብ በራሱ አነሳሺነት ሲያቀራርብ : ይህ ሰው ምርጥና አስተዋይ የፍቅርና የሰላም መሪ ነው በሚል ገመገምኩት:: ለዚያም ሰባት አስረ ዓመታት በዚች ሕይወት ዓለም ያሳለፈው ወገቤ የታሰረበትን መቀነቴን ጠበቅ አድርጌ በየድረገፆችም ሆነ በተመቹኝ የውይይት መድረኮች ላይ ከእኔ እኩያዎች እስክ ልጅ ልጆቼ እኩያዎች ጋር ስሟገትለት ከረምኩ:: አንዳንዶቹም እድሜ ፀጋ መሆኑን በመዘንጋትና እነሱም የእኔ እድሜ የማይደርሱ እየመሰላቸው ባልሆነ አጠራር ሲተቹኝ ዋጥ አድርጌ ስኬታማ እንዲሆን ስመኝለት ከርሜ ነበር:: ድጋፍ የባዶ ቼክ ክፍት ስጦታ እንዳልሆነ የተረዳ አይመስለኝም:: ስህተቶች ይሰራሉ:: የተወሰኑ ስህተቶች ታይተው እንዳልታዩ ሆነው ይታለፋሉ:: እንኳን የአገር መሪ ማንም ሰው ማለፍ የሌለባቸው ቀይ መስመር መታለፍ የሌለባቸው ጥቂት የሰው ልጆች መመሪያዎች አሉ:: ከእነዚህም መነካት ከሌለባቸው አብይ ነገሮች አገርና ሃይማኖትን የማፍረስ ሁኔታዎች ናቸው::

አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ክብር ቢኖረው የተገነጠለውን በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ : የክርስትና ሃይማኖት ጉዳይ የማያገባው ጀዋር አህመድ : በአዲስ አበባዋ ከንቲባ አዳነች አበቤና በተለያዩ የኦሮሞሚያ ጎሰኝነትና ዘረኝነት ፖለቲካ በተመረዙ አገር አፍራሾች ደጋፊነት በሳሬዎስ የተመራውን ተገንጣዩን የመናፍቆች ቡድንን ከእጀማመራቸው ተው ማለት ሲገባው : እንደልምዱ አልሰማሁም አላየሁም በማለት አፉን ሎጉሞ ከከረመ በሗላ በእብሪትና በትእቢት ተወጥሮ ሚኒስትሮችን በንቀት እያያቸው ስለቤተክርስትያኔ የሰጠው ዲስኩር ለእኔም ሆነ ለማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝና ተከታይ ቀይ መስመር ማለፍ ነው:: አቢይ አህመድ የደረሰበት ደረጃ “እውቅሽ አውቅሽ ሲሏት የቄስ ሚስት መፅሐፍ ቅዱስ አጠበች” የሚለውን ተረት ያስታውሰኛል:: ማንም ሰው ሁሉን ነገር አያውቅም:: ለዚህም ነው ሰዎች አንዳንድ ሙያ የሚይዙትን በዚያ የሚራቀቁት::

ምንም በእድሜ የልጆቼ እኩያ ቢሆንም እሱ ብዬ የጀመርኩትን መሪ ስለሆኑ ለአገሬ ክብር በአክብሮት ሃሳቤን ላጋራቸው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁሉም ቦታ ሲሄዱ ላስተምር የሚል ዝንባሌ ይታይባቸው ነበር:: የኢኮኖሚስቶች ስብሰባ ላይ ኢኮኖሚስት : የሐኪሞች ስብሰባ ላይ ሐኪም : እርሻው ላይ አራሽ : ውሃ ግድብ ላይ የውሃ ጥናት አዋቂ : ቤተክርስቲያን ላይ ካህን ወይም ፓስተር የመሆን ዝንባሌ ይታይባቸዋል:: ግን በአድናቆትና በፍቅር ስላየናቸው ይህ የእብሪተኘትና ሁሉን አውቃለሁ የሚል የሜጋሎማኒያክ ባህሪይ መሆኑን ለጊዜው አልተገነዘብንም ነበር:: “ልጅን ሲወዱ ከእነቅዘኑ” እንደሚለው ተረት ስለወደድናቸውምና ካለፉት የተሻሉ ይሆናሉ ብለን ተስፋ በማድረግ ቅዘናቸውን ለማየትም አልፈልግንም ነበር:: “ጉድና ጭራ ከሗላ ነው እንደሚለው” ተረት ማንነታቸውን በ37 ደቁቃዎች አሳዩን:: እኛም አንቅረን ተፋናቸው::

ወደ ንግግራቸው ስመለስ ሁሉን አውቃለሁነታቸውን የታዘብኩት ቤተክርስቲያኔ በተገንጣዩ የምናፍቆች ቡድን ስትጎዳ : ሁለቱ ክፍሎች ቢነጋገሩ ችግሩ በቀላል ይፈታል ከማለታቸው አልፈው ቤተክርስቲያኗ በሌቦችና በዘረኞች ፖለቲከኞች እንድምትመራ በማድረግ ፖለቲካ ሌብነትና ዘረኝነትን ቤተክርስቲያን ብታስወግድ ይህ ችግር አይፈጠርም በማለት ሃይማኖትን ማቅለላቸው ነው:: ፖለቲካ የሳቸው የቀን ቀን ኑሮአቸው ስለሆን ልተርክበት አልፈልግም:: ስለሌብነትና ስለዘረኝነት እናውራ:: የእሳቸው የፖለቲካ እድገት በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ አይደለም? አሁን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያኔን የሚያምሰው ቡድን በኦሮሞ ቋንቋ አልተሰበከም ብሎ አይደለም የተነሳው? ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቋንቋችሁ አትጠቀሙ ብላም አታውቅም:: ከ30 አመታት በላይ ኦሮምኛ በሚናገሩበት አካባቢዎች በኦሮምኛ ይሰበካል:: በኦሮምኛ የተተረጎሙ የቤተክርስቲያኗ ማስተማሪዎች ከ30 ይበልጣሉ:: በእርግጥ ቋንቋዎች እንዲስፋፉ ከተፈለገ በትምህርት መልክ መንግስት ማስፋፋት ስራው መሆን አለበት:: ከ80 በላይ ያሉትን ቋንቋዎች ማበልፀግና ማሳደግ የአገሪቱ አመራር ስራ መሆን ይገባዋል:: ገንዘቡ ካለና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፈቀደ መደረግ የሚቻል ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ለምንድን በወላይታ በአዲያ በሱማሊኛ ወዘተ ቋንቋዎች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አላስተማረችም አላሉም? ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገርባትን አገር ስለአንድ ቋንቋ መብት የሚያነሳ መሪ እልም ያለ ዘረኛ ነው:: በየጊዜው ኦሮሞዎች እንደተበደሉ የሚለቀስብን የትኛው ጎሳ ነው በኢኮኖሚ ሆነ በሌላ መንገድ ከኦሮሞ የተሻለ የሆነው? የትኛው ጎሳ ነው የትኛውን የጨቆነውና ኦሮሞ ልዩ በደል የደረሰበት? በኦሮሞ ሕዝብ ጫንቃና ደጉንና የዋሁን ኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን ከሌሎች ወንድሞች በማቃረር ግጭት ፈጥሮ የራሳቸውን ጥቅም ለመሙላት የሚሯሯጡትን ጎሰኞች ፖለቲከኞችን ደም እንዲያፈሱ የሚያነቃቁት? እንደ ማርያም ጠላት በግራ በቀኝ የሚወቀጠው አማራ ኢትዮጵያውያን ምን አጥፍቶ ነው? አንድ ቀን ኧረ ግፍ ነው ሰውን በአማራነቱ ለትውልዶች ኦሮምያ ክልል ውስጥ የተወለደውንና የኖረውን አታሸማቁ : አታባርሩ አትግደሉ በማለት ሰባዊነት አሳይተዋል? ባለቤቶ አማራ ኢትዮጵያዊት ስለሆኑ እንደሰው ይህ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የጥላቻ ፖለቲካ ያስከፋት ይሆን ብለው ራሶን ጠይቀዋል? ይህ የዘረኝነት ፖለቲካ ለኦሮሞም ሆነ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም ብለው አፍ አውጥተው ተናግረዋል? በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቤተክርስቲያኖች ሲደፈሩ ሲዘረፉ ሲቃጠሉ ካህናቶች ምእመናንትና ምእመናን ሲታሰሩ ሲንገላቱ ሲደበደቡና በየቀኑ ሲገደሉ በእርግጥም አልሰሙም? በሶሻል ሚዲያዎች አላነበቡም? ሻሸመኔ ውስጥ በኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ሃይል ተደብድበውና በጥይት ስለተገደሉት ካህን ቀሲስ ሃረገወይን በላይና 34 ምእመናትና ምእመናን አልሰሙም? ሽመልስ አብዲሳንና የአዲስ እበባዋን ከንቲባ አዳነች አበቤን ለሃይማኖቱ የቆመውን ሕዝብ ነፍስ አታጥፉ ብለው በይፋ ገስፀዋል? በኦሮሞ ክልል መንግስት ፖሊስና ልዩ ሃይል ብዙ የኦርቶዶክስ አማኞች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተሰቃዩ እንደሆነ አልሰሙም? አይሰሙም ብዬ አላምንም:: ሁሉንም ያውቁታል:: ግን እርሶ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በእነጀዋር መሃመድ ቄሮዎችን በማደራጀት አማራ ኢትዮጵያውያንና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታዮች ሲጨፈጨፉ : ሲያሰሙን የነበረው ይህ የሕዝብ ግድያ ተገቢ አይደለም በማለት ከማስቆም ይቅር የሞቱትን በጎሳ ስታቲስቲክስ አውጥተው ግድያውን ተገቢ ሲያስመሉ አልፈኖት ከረሙ:: እስቲ ሰባዊነት ቢሰሞት ለሞቱትና በግፍ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚያልቁት ኦርቶዶክሶች ልቦ ባይደነግጥም ድንገት እንደ ወንድ የሚቀጥለው ታሪክ ልቦን ያለሰልስ ይሆን? በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በያቤሎ በአንድ ካህን መላከ ፀሃይ ቆሞስ አባ ገብረሚካኤል ፋንቱ በሚባሉ አንድ የኦሮሞ ክልል ፖሊስ አባል የሆነ የወለጋ ተወላጅ ሱሪያቸውን አስወልቆ ሊደፍራቸው የሞከረበትን ግፍ ሲሰሙ ምን ይሰማዎታል? ወይስ እንደልምዶ አልነበርኩም አላየሁምንና አልሰማሁን ይመርጡ ይሆን? ይህን ዓይነት ድርጊት ለኦሮሞ ስም ጥሩ ነው ብለው ያስባሉ? እንደውስ ለጎሳዎት መልካም ስም አያስቡም? እርሶም ወንድ ልጅ እያሳደጉ ነው:: እኝ ካህን ልጆ ወይም ወንድሞ ወይም አባቶ ቢሆኑ ምን ይሰሞት ነበር? አጅግ አያኑም? ይህነው እንግዲህ የአቢይ መንግስትና አስተዳደር የሚመስለው:: ይህ ዘረኝነት የተሞላበት ጥላቻን በአስተዳደሮ ውስጥ ጎልቶ ከመታየቱም ሌላ በገሃድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እያስፋፋሎት ነው:: ሕዝብን ከመፈናቀልና ክማሰቃየት በተጨማሪ በይፋ እየገደለ ነው:: አዎን! ቃል የገቡት ፌደራል ወታደርና ፖሊስ እንዳይገድል ነው:: ግን የኦሮሚያ ክልል ለሚያካሂደው ግድያ እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ ብለው እጆትን እንደታጠቡ እንድንቆጥር ሳይፈልጉ አይቀርም:: ጲላጦስ ዳኛ እንጂ እንደእርሶ የአገር መሪ አልነበረም:: ዳኛ መሪዎች ሕግ በሚያከብሩበት አገሮች ትክክል ፍርድ ይሰጣሉ:: ሕጉን ማስከበር ያለበት መንግስት ከሳሽ ሆኖ ሲቀርብ ዳኛው የሚሰጠውን ፍርድ ይቀበላል:: ያኔ ፍትሕ ተሟላ ይባላል:: ግን ጲላጦስ የሰጠውን ፍርድ መሪው ጥሶ ራሱ ከሳሽና ፍርድ ሰጪ ሲሆን ዳኛው ከደሙ ንፁህ ነኝ ብሎ እጁን ይታጠባል:: እርሶና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከሳሾችም ዳኞችም ናችሁ:: እጃችሁ በንፁሃን ደም ተጨማልቋል:: ይህም የዘረኝነታችሁ ውጤት ነው:: ባንድ በኩል ዘረኝነት ይጥፋ በማለት ልታሞኙ ትሞክራላችሁ : በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ታስፋፋላችሁ::

ሌብነትም የሃይማኖት ጠንቅ ነው ብለው ሲናገሩ ሰማሆት ይሆን? በጣም የሚገርሙ የእባብ ዘይት ሻጭ ኖት:: ይህንን በጊዜው ባለመረዳቴ ተሞኘሁ:: መጀመሪያ በአጠገቦ ያሉትን ሌቦች እጃቸውን ከጣፋጩ ማሰሮ እንዲያወጡ ቆንጥጠዋል? እስቲ ሽመልስ አብዲሳን ይጠይቁት:: ሚስቱና ወንድሙ ምን እንደሚሰሩ ያውቃሉ? ሌሎች ሚኒስትሮች ምን ያህል ሀብታም ወይም ደሃ እንደሆኑ ያውቃሉ? ከዚህ በፊት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያላቸውን ሀብት በ3 ወር እንዲያሳውቁ ብለው ያወጡት ማዘዣ ስራ ላይ ውሏል? ማስረጃ ካሎት ለሕዝብ ግልፅ ማድረግ ይችላሉ? ጣቶን ሃይማኖቶች ላይ ያለአግባብ ከመጦቆም መጀመሪያ የቤት ስራዎትን ቢሰሩ ይሻላል:: አስተዋይ ሰው የሰውን ዓይነ ጉድፍ ከመጦቆም በፊት የራሱን ዓይነ ጉድፍ ያስወግዳል::

ሌላው ትዝብቴ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እብሪት ነው:: በጣም የሚያሳዝነው ስለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ችግሮች መንሴ መስሎ የታያቸውን ለማስተማር ከሞከሩ በሗላ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያደረጉትን ሁሉ ዘረዘሩ:: ይህንንም ሲዘረዝሩ የነበራቸው አቲቱድ ከማስታረቁ ሌላ የተቀሩት ያለፉት መንግስታት ወርሰው የነበረውን የቤተክርስቲያኗን ንብረት መንግስት መመለሱን የግል ስጦታ አድርገው መውሰዳቸው እኝ መሪ ለካ ግብዝና አመስግኑኝ ባይ ናቸው አልኩኝ:: ከውጭ አገር ለአገሪቱ በእርዳታ ስም ያገኙትን እንደራሳቸው ገንዘብ በመቁጠር እኔ አንድም ገንዘብ አልተበደርኩም ሲሉ የተሰጣቸው ገንዘብ አገሪቱን ለማልማትና የሕዝብን ችግር ለመወጣት የተሰጠ የሕዝብ ገንዘብ መሆኑን ይረሱታል መሰለኝ:: እንዲህ አይነት ትእቢት ተገቢ አይደለም:: ወደቀልባቸው ቢመለሱ ጥሩ ይሆናል::

ሌላው ከንግግራቸው የወሰድኩት በምንም ዓይነት የአፊሪካ መሪ ከጉልበተኝነት ስሜት እንደማይወጣ ነው:: ስለስልጣን ጉዳይ ሲናገሩ በሃሳብና በአመለካከት ተሟገቱን:: ግን በጉልበት ትጥቅ በማንሳት ለመገልበጥ አታስቡ:: ምክንያቱም በዘረኝነትና በጎሰኝነት የሚያምነው የብልፅግና ፓርቲ እጅግ በጦር ተደራጅቷል የሚል መንፈስ ውስጥ ነበሩ:: ይህ የአምባገንነት ዝንባሌያቸው በፊት አልሸተተንም ነበር:: የሚረሱት ደርግም አፍሪካን የሚያንቀጠቅጥ የጦር ኃይል ነበረው:: ግን ሕዝብ ያልደገፈው መንግስት : ሕዝብ ያልፈለገው መንግስት ሕዝብ ከተነሳና ካመፀ እንደማዕበል ነው:: በጉልበት ሳይሆን በሕዝብ ፍቅርና ቀበሌታ ብቻ ነው መቆየት የሚችለው:: ድንገት የፌደራል ጦር አልታዘዝ ካለ ለዚህ ፍራቻ ይሆን የሮሚያን ክልል ጦር በወታደር ብዛትና በመሳሪያ ክፌደራልና ከሌሎች ክልሎች የበለጠ እንዲጠናከር የሚደረገው? ይህ ሁሉ በዘረኝነት ገመድ መጎተት ይባላል::

ስለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ቱሉቱላ የሚነፋ የግለሰቦችን በነፃ እምነታቸውን ማራመድና ለእምነት ቤታቸው ልኡላዊነትና ደህንነት የመቆም መብታቸውን መጠበቅ ግዴታው ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በዛ በጉደኛው የ37 ደቂቃዎች ንግግር ውስጥ ንቀት በተሞላ መንፈስ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ሚኒስትሮቻቸው ስለእምነት ቤታቸው ጉዳይ የሚሰማቸውን ስሜትና አስተያየት እንዳይገልፁ ሲከለክሉ ዲሞክራሲን በካልቾ ከአገሪቱ አባረሩ ማለት ነው:: ይህ በዚህ ሳያበቃ ትዝ ያለኝ በደህንነትና በጦር እንደማይሸነፉ ጉራቸውን ሲነዙ እንደ ምሳሌ ያቀረቡት የግንቦትን ሰባትንና መሳሪያውን ሳይቀሙት የገባውን የኦነግን ሽምቅ ውጊያ ሁኔታ ነበር:: ይህንንም ሲሉ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋንና አቶ ቀጀላ መርዴሳን ሽምቅ እንዋጋለን ሲሉ ሽምቅ ሆነው ቀሩ:: የራሱን ሚኒስትሮች ዝቅ የሚያደርግ እንዲህ ዓይነት አነጋገር ከበሰለና ከአስተዋይ መሪ አይጠበቅም::

ስብእና ተረስቶ ሰውነት ተንቆ ጎሰኝነት ዋነኛ የአገር መመሪያ ተደርጎ ቅድሚያ የተሰጠበት : የአገር ማንነትና የሕዝብ አንድነት በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠበት የጎሳ ፖለቲካ አውድ አገርንና ሕዝብን ወደሚፈለግብበት የእድገትና የልማት ግብ አያደርስም:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አቢይ አህመድ የሰላም ግንባታ የአትቱድ ጉዳይ ነው እስካሉ ድረስ ጥያቄአችን የትኛውን የማንን አትቱድ እንቀይር ነው:: የዘረኝነትን ወይስ የአንድነትን አቲቱድ? የሕዝብን ወይስ የመሪዎችን? የዛሬ አራት አመት ከአስር ወር ወደ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመጡ የኢትዮጵያ መሪ ተብለው እንጂ አንድን ጎሳ የሰማንያዎች ጎሳዎች በላይ ለማድረግ አልነበረም:: ግን ዛሬ የተዋህዶ አማኞች ባልሆኑ የኦሮሞ ክልልና የአዲስ አበባ ፖሊሶችና ልዩ ሃይሎች የእትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን አማኞች ጳጳሳት ካህናት ዲያቆናትና ምእመናንን በመላው ዓለም ሲያስለቅሱና ሲገድሉ እርሶ እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህን ቢሉ የእነዚህ ንፁሃን እምባና ደም ለእርሶም አይበጅም:: ይህንን የዘረኝነት ግፍ ቢያስቆሙ ይሻላል::

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. Almaze,

    Confession comes first! You should confess and ask God for forgiveness for misleading the Ethiopians, especially the prime victim, the Amara people. We told you, but you were insulting us siding with a spy traitor who is worse than Yihuda. Shame on you! Your support goes to history that cannot be erased.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here