spot_img
Sunday, April 2, 2023
Homeነፃ አስተያየትመንግሥት ዐመፅን እያየ ባይተዋር ሊሆን አይገባም ...

መንግሥት ዐመፅን እያየ ባይተዋር ሊሆን አይገባም …

- Advertisement -

ግርማ በቀለ (ዶ/ር)

የመንግሥታት ሥልጣን በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተያዘ ነው። መንግሥታት ዕውቅና ሰጡም አልሰጡም፣ ለመልካም አስተዳዳር የእግዚአብሔር አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የህልውናችውና የሥልጣናቸውም ምንጭ ራሱ ሉዑል እግዚአብሔር ነው። በልዕልናው ፈቃድ ያነሣል፤ ይጥላልም። መንግሥት የእግዚአብሔር ናትና፤ ሕዝቦችንም የሚገዛ እርሱ ነው (መዝሙር 22፥28)። ስለዚህ የአገር መሪዎች የሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነውን፣ እግዚአብሔርን በመፍራት የፍትሕ፣ የደኅንነትና የሰላም ዋስትና ጠባቂዎች ሊሆኑ ይገባል።

የትኛውም መንግሥት የአድሏዊነት፣ የፍትሕ መጓደል፣ የፍርድ ሚዛን መዛነፍ፣ የአስተዳደር በደል፣ የዜጐች መጨነቅና ሰላም መናጋት ምክንያት ሲሆን፣ እርሱ [መንግሥት] ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና (ሮሜ 13፥4፤ 1ጴጥሮስ 2፥14) ከሚለው አምላካዊ ዐደራ ጋር ቀጥታ ይጋጫል፤ በእግዚአብሔርም ፍርድ ሥር ይወድቃል። እግዚአብሔር ከድኾችና ከተበደሉት ጐን የሚቆም የፍሕ አምላክ ነውና።

ሕዝብ በሚያስተዳድረው በመንግሥት ሲመረር፣ ተስፋው ሲጨልምና የአክብሮት ልቡን ሲነፍግ፣ መሪዎች ልብ ብለው ሊያዳምጡ ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደምንመለከተው፣ አስከፊውን የሰሎሞንን የመጨረሻ አገዛዝ የተረከበው ልጁ ሮብዓም፣ የሕዝብን እሮሮ አለመስማት ዕቡይነት መንገሥቱን ከፍሎታል። የአገራችን መንግሥታት የመውደቅና የመነሣት ታሪክም ተመሳሳይ ተዛማጅነት አለው። በቅርብ ጊዜ ከተነሡት መንግሥታት እጅግ በላቀ የሕዝብ ድጋፍ የጀመረው የዶ/ ዐቢይ መንግሥት፣ መድማት የጀመረው ቅቡልነት አፋጣኝ ሕክምና እንደሚያስፈልገው በቅን ልብ ሊያሰተውለው ይገባል። ዘውግ ተኰሩ የፓለቲካ ክፍፍልና ዐመፅ ቤተ ሃይማኖቶችንም እያወከ መምጣቱ፣ ውሉ እንደ ጠፋ ማግ የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር ለመፍታት ትልም ይዞ የተነሣውን አገራዊ የምክክር፣ የመግባባት፣ የዕርቅና የፈውስ ጐዳና እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

የቤተ እምነቶች የውስጥ ግጭት መፈታት ያለበት በቀዳሚነት በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ሊሆን እንደሚገባው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተከሠተውን የውስጥ ውጥረት በተመለከተ፣ መንግሥት በንግግርና በተግባር ያሳያው እርስ በርሱ የሚጋጭ አቋም ሥጋት ላይ የሚጥል ነው። የቤተ እምነቶች የውስጥ ግጭት መፈታት ያለበት በቀዳሚነት በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ሊሆን እንደሚገባው፣ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ግጭቶችን በተቻለ ዐቅም በውይይትና በዕርቅ እንዲፈቱ መንግሥት ይመክራል። የማይፈቱ ከሆን፣ በዐመፅ ሳይሆን በፍርድ ቤት የፍትሕ ሂደት ብያኔ ያገኛሉ። ይህ እጅግ ጤናማ መንገድ ነው።

መንግሥት ዐመፅን እያየ ባይተዋር ሊሆን አይገባም። ቅዱስ ሲኖዶስ በውግዘት ከኅብረቱ የለየው ቡድን፣ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በኀይል በመታጀብ፣ የቤተ ክርሲያኒቱን ሕጋዊ ይዞታዎችን በኀይል ለመንጠቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ መንግሥት ያሳየው ዝምታ እጅግ ዐሳሳቢ ነው። መንግሥት ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውን ማኅበራዊ ተቋማት መብት የማስጠበቅ ድርሻ አለበት። ሙግቶች በሙሉ በሕግ የበላይነት ሊዳኙ ይገባል። መንግሥት በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ሰላማዊ በሆነ መንገድና በውስጣዊ አሠራር መፈታት እንዲሚኖርበት እየተናገረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዐመፅ ሲሠለጥን እያየ ዝም ማለቱ ከወገንተኝነት ክስ ሊያስመልጠው አይችልም።

ሃይማኖት ዐመፅን ከለበስ፣ የአገርን አንድነት ይናጋል

እየከፋ የመጣው የሕግና የሰብአዊ መብቶች ጥስት እንዲሁም የዜጐች የሰላምና የደኅንነት ዋስትና ዕጦት ሳይረፍድ እልባት ሊደርግለት ይገባል። ሰዎች የትኛውንም እምነት የመከተል፣ የመቀየር፣ የመካድ መሠረታዊ መብት አላቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን፣ በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ የተነሣው ነውጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እልባት እንዲያገኝ መጸለይ፣ መጾምና ጥቍር ልብስ መልበስ መብታቸው ነው። ይህን በማድረጋቸው የሚደርስባቸው ውክብያ፣ መገለልና እንግልት እጅግ አሳዛኝ ነው። ከሁሉም በላይ፣ ከሕግ አግባብነት ውጭ ኀይል ያለው ተከፋይ ቡድን የሃይማኖት ተቋማትን በዐመፅ የመውረሱ አካሄድ ከአሁኑ ካልተገታ፣ ለሌሎች ቤተ እምነቶችም ትልቅ አንድምታ አለው። ሃይማኖት ዐመፅን ከለበስ፣ የአገርን አንድነት ይናጋል።

የወቅቱ ግጭት በፈሪሓ-እግዚአብሔር እንዲሁም በሰከነ ስሜት ሊገራ ይገባዋል። ቅዱስ ቃሉ እንደሚል፣ “እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?” (የሐሥ. 7፥26)፣ ወንድማማችነት ሊሠለጥን ይገባዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም ሰላምንና ይቅርታን የበለጠ በመስበክ እንዲሁም ዐመፅን በዐመፅ ከማሸነፍ ፈተና ምእመናን ራሳቸውን እንዲገቱ መምከርና ማበረታት ያስፈልጋታል። ምንጊዜም ቢሆን የመስቀሉን መንገድ ምርጫ ማድረግ ትልቅ ማስተዋል ነው። የሃይማኖት ካባ የደረበ ፓለቲካዊ ውጥረት፣ ከጦርነት ማግሥት ባልጠገገ ቍስል ለምታቃስትና በሕዝቦች መካከል የተፈጠሩ ፈርጀ ብዙ ስብራቶችን ለመጠገን ለምትታገል አገር፣ ልትሸከመው የማትችለው ተጨማሪ ጫና ነው። ቤተ እምነቶች የመንግሥትም ሆነ የተፎካካሪ ፓለቲካዊ ፓርቲዎችና ኀይላት መድረክ ሊሆኑ አይገባም። ይህ ተደጋጋፊነት የትርክትና የቂም እስረኝነትን ዑደት በማክረር፣ ለከፍተኛ ዕልቂት አሳልፎ ይሰጠናል። ሕዝቦችን ብቻ ሳይሆን መንግሥትና የጸጥታ ኀይሎችንም ጐራ በማስያዝ ይከፋፍላል፤ ዐመፅን ይቀሰቅሳል።

ልብ እንበል፤ ከእርስ በእርስ ጦርነት ያጨድነው መከራና ሰቈቃ ብቻ መሆኑን ለሁላችንም ያልተሰወረ ሐቅ ነው። የላቀው መንገድ፣ በመግባባትና በይቅርታ የታደሰ የሰላም መንገድ ነው። ከምንጊዜውም በላይ፣ መንግሥት ሕዝብን መስማት ያለበት ፈታኝ ወቅት ላይ ደርሷል። መንግሥት የወረሰውንና በጅማሬው ላይ፣ “ፍጹም ዐምባገነን፣ አፋኝ፣ በዳይና መንግሥታዊ ሽብረተኛ” በማለት ያወገዘውን ያንኑ የቀድሞ ፓለቲካዊ ሥርዐት የጥፋት መንገድ ከመሄድ ፈተና ራሱን ሊጠብቅ ይገባዋል። አብዛኛው ሕዝብ የተሻለው መንገድ ነው ብሎ ተስፋውን የጣለበት ዐዲስ የዲሞክራሲ መንገድ፣ በአሮጌው ምናልባትም በከፋ አቍማዳ ውስጥ እንዳይገባ ትልቅ ጥንቃቄ ያሻዋል።

ከዕውቀቴ ድንበር ውጭ በመሆኑ፣ በፓለቲካዊ ስብራቶች ዙርያ ብዙ ማለት አልችልም። ሆኖም እንደ ሕዝብ የመስተጋብር ፈውስ ያስፈልገናል። ቅንነት፣ የዐሳብ ንጽሕና፣ እውነትና ፍትሕ በጅምላ ፍረጃ፣ በጥርጥርና በመወጋገድ አረም ወርሷቸዋል። ለፈውሶቻችን፣ ቤተ እምነቶች ከጽንፈኝነት፣ ከፓለቲካዊና ጐሣዊ ወገንተኝነት ነጻ መሆናቸውና የይቅርታና የሰላም ድልድይ መሆናቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። እነርሱ ራሳቸው ታሪክና ትርክት የወለዷቸው ምሬትና ቂም ምንጭ ከሆኑ እንዲሁም ዕያወቁም ሆነ ሳያውቁ የመንግሥታትና ኀይላት ሃይማኖታዊ ክንፍ ከሆኑ ምን ተስፋ አለ? በይቅርታ፣ በመቻቻልና በጋራ የእሴት ድንበሮች ላይ ዐብሮ በመቈም፣ የአገራችንን የግኝኙነት ስብራቶች የመጠገን ትልቅ ታሪካዊ ዐደራ አለባቸው።

ከሁሉ የላቀው ሰማያዊ ማንነታችን

ለሥላሴ እምነት ተከታይ የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ፣ ልባችንንና የውስጥ ግፊቶቻችንን እንመርምር፤ ወደ እግዚአብሔር በእውነት እንመለስ። ምስባኮቻችን ሰማያዊ ይሁኑ። ፓለቲካና መንግሥታት ጊዜያዊ ናቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ዘላለማዊ ነው። በክርስቶስ ያገኘነውና ከሁሉ የላቀው ሰማያዊ ማንነታችን ምድራዊ ማንነቶቻችንንና መስተጋብሮቻችንን በሙሉ ሊገዛቸው ይገባል። ለእግዚአብሔር እንደ ተለየ ማኅብረ ሰብ በጽድቅ መኖራችን፣ ለአገራችን አንድነትና ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በአንድ ጊዜ የክርስቶስም የዓለምም ልንሆን አንችልም። ጌታችን ክርስቶስ እንዳለው፣ ጾምና ጸሎታችን በእውነተኛ የንስሓ ፍሬ የታጀበ ይሁን።

የክርስቶስ ቤዛዊ የመስቀል ሞት፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም እርስ በርስ እውነተኛ ዕርቅና ሰላም ያምጣልን። አሜን! 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,472FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here