
(ክፍል ሦስት)
ተስፋዬ ደምመላሽ
አሁን ቤተ ክህነት እንደ መንፈሳዊ ተቋምና ሥርዓተ እምነት በአብይ አሕመድ አሊ ጠብ ጫሪም “አስታራቂም” መልቲነት እየታመሰች ያለችበት ሁኔታ እንደ አገር የምንገኝበት ውጥረት ዋና አካል ነው። ቀውሱ እርግጥ በተለየ መልክና መጠን ኦነጋዊ እንድሆነ ገልጽ ነው። የ“ንጉሥ” አብይ ግላዊ ሾላካነትም ዛሬ ከአንዳንድ አልነቃ ባይ ተታላይ ግለሰቦችና ስብስቦች በስተቀር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ስውር አይደለም። ሆኖም፣ እንዳገር የምንገኝበት ቋሚ፣ የተወሳሰበ ውዝግብ አገዛዝ ዘለል መዋቅራዊ ፍልቀት ያለው መሆኑ ከብዙዎቻችን የሚገ፟ባውን ቀጣይ ትኩረት አያገኝም።
ፖለቲካዊና አገራዊ ውጥረት በድፍኑ አሉታዊ ሳይሆን ከመሠረታዊ የመንግሥት ለውጥ አኳያ በጎ ተጨባጭ ጎን ሊኖረው ይችላል። ሰሞኑን ጎሠኛው ገዢ ወገን በቤተ ክህነት ውስጥና ዙሪያ የለኮሰው እሳት ራሱን ሲለበልበው አይተናል። ከዚህም አልፎ፣ ውዝግቡ አገዛዝ መዋቅሩን እንዳለ ለሥር ነቀል ለውጥ ይበልጥ ሊያጋልጥና ሊያመቻች ይችላል።
ገዢው የኦነግ መንጋ በአገርና ሕዝብ ወረራው ራሱን የሰነቀረበት አጣብቂኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለና እየከረረ መምጣቱ አይቀርም። መንጋው ወደር በሌለው ጎጠኛ ስግብግብነት ሰማዩም ምድሩም ሁሉ የኔ የብቻዬ ነው ብሎ የሚሄድበት መንገድ በጎ መዳረሻም ሆነ መውጫ የሌለው ጎዳና እንደሆነ ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ነው። ይህ ሲሆን በአገዛዙ የነበራቸው እምነት የሚጠፋባቸውና አማራጮችን ታሳቢ ማድረግ የሚጀምሩ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የምሁራንና የቴክኖክራሲ መደቦች አባላት ቁጥርም እንዲሁ ከለት ተለት እየጨመረ ይመጣል።
ቢሆንም፣ እነዚህ እያደር ቅሬታ የሚገባቸው ወገኖች በቋሚ ውጥረት የሚዋልለውን የአብይ አሕመድ ኦነጋዊ የአገዛዝ ዓይነት (የጎሣ ፖለቲካ ፓራዳይም) እንዳለ ይክዳሉ ወይም ይተዋሉ ተብለው አይጠበቁም። ተኪ ወይም አማራጭ የመንግሥት ሥርዓት በአድማሱ ሳይታይ ያለ፟ው የአገዛዝ ሞዴል ብዙውን ጊዜ ውድቅ አይደረግም፤ አካቶ አይተ፟ውም። የነባሩ ፖለቲካ መዋቅር ውጥረት እየተባባሰ ሲመጣ ግን ብዙዎች ለአገር ተቆርቋሪ ኃይሎች – ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተንቀሳቃሾች፣ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ታጣቂ ታጋዮችና መንፈሳዊ መሪዎች – ሥርዓታዊ ለውጥ ፈላጊና ደጋፊ ይሆናሉ።
የሚፈለገው መሠረታዊ ቅየራ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ግን ለለውጡ ቃል የገቡ የተወሰኑ ቆራጥ፣ አገር ወዳድ፣ ቀለም ቀመስ ታጋይ ግለሰቦች ተሰባስበው በሚፈጥሩት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቆርቋሪ ማኅበርሰብ ነው። በዚህ መልክ በተለያዩ ክፍለ ሀገራት ወይም ተቋማት አካባቢዎች የሚፈጠሩ ጥቂት አስኳል ማኅበረስቦች በሚዘረጉት ተለማጭ የግንኙነትና ትብብር መረብ ራሳቸውን ለትልቅ አገራዊ የለውጥ ንቅናቄ መነሻ የሚሆን ዋነኛ ግዙፍነት ያበቃሉ። በዚህ መንገድ ለሰፊ ሕዝባዊ ትግል የስበ፟ት መኻልም ይሆናሉ።
ያን ጊዜ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ውስጥ ሁለት ዋና ፟ተጋጣሚ ጎራዎች ወይም ወገኖች ይኖራሉ። አንዱ ጎራ ያለ፟ውን አገር አፍራሽ፣ አማራ ጨፍጫፊ ጎጠኛ ያገዛዝ መዋቅር በመከተልና በመደገፍ የሚያስቀጥል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከአማራውና ከመላው የኢትዮጵያ ዜጎች ሰላም፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ልማት ጋር የሚጣጣም አዲስ የመንግሥት ሥርዓት ለመገንባት የሚጥር ይሆናል።
መዋቅር ለዋጭ የሐሳብ ንቅናቄ እንዴት?
የሥርዓት ለውጥ ትግል ከሚደረግባቸው ሜዳዎች መካከል ቁልፍ የሆነው የሐሳብ መስክ ነው። እዚህ “ሐሳብ” ወይም “አስተሳሰብ” ስል ሰፋ አድርጌ የተዛመዱ ረቂቅ ነገሮችን፣ ማለትም መርህን፣ እምነትን፣ እሴትን፣ ትርክትን፣ ዓላማንና ጥልቅ ስልታዊ ቀመርን በማካተት ነው።
እንዴት ነው አንድን ሐሳብ በፖለቲካ ሥራ፣ በተለይ በመዋቅር ለውጥ ትግል ውስጥ የምንለየው? አስተሳሰብ ወይም ርዕዮት ለማም ከፋም ብዙውን ጊዜ ከእውን እርምጃዎች፣ ገቢሮችና ንቅናቄዎች ጋር ስለሚያያዝ ተጨባጭ የትግል ድርጊቶችንና እንቅስቃሴዎችን ሊያሳካና ሥርዓት ሊያስይዝ ይችላል። ይዘቱ (ወይም ይዘት አልበኝነቱ) ከሞላ ጎደል በጽንሳዊ አቀራረጹ፣ አተረጓጎሙና አፈጻጸሙ ሊገለጽ ይችላል።
በመዋቅር ቅየራ ትግል መሣሪያነቱ፣ የአስተሳሰብ ንቅናቄ ያለ፟ን የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም የዕውቂያ ባህል በማሻሻል ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከዚያ አልፎ፣ ቀደም ያሉ የሐሰት ትርክቶችን መናድ፣ እንዲሁም የተዛቡ ግምቶችንና ግንዛቤዎችን መልሶ ፈትሾና ውድቅ አድርጎ መለወጥ፣ እንዲሁም ጽንሰሃሳቦችን ይበልጥ ገላጭና ለሕዝብ ተደራሽ በሆነ አረዳድና አገላለጽ እንደገና መቅረጽ ያስችላል።
ለምሳሌ የሕወሓት ወይም ኦነግ አገዛዝ “ሕገ መንግሥት” እሳቤን ከተንኮለኛ ፀረ አማራና ፀረ አንድነት ዳራውም ሆነ ከዘረኛ አፓርታይዳዊ መንፈሱ እንደገና የመቅረጽ አቅማችንን ይጨምራል። ሰፋና ጠለቅ ያለ ሐሳብ ሲኖረን፣ ያለ፟ው ሕገ መንግሥት ተብዬ ጎጂ ነው ወይስ ጠቃሚ ከሚል መለስተኛ ክርክር ማለፍ እንችላለን። ይበልጥ ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሻግረን የሕገ መንግሥትን መርሃዊም ተቋማዊም ምንነት – ቃል በቃል የሚለውን ብቻ ሳይሆን ሥራ ላይ የሚውል ኃቀኛ ይዘቱንና አቀራረጹን፣ እንዲሁም እውን የአተረጓጎምና አፈጻጸም ደንቦቹን – መልሰን መረዳት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ማስረዳት እንችላለን።
ሥርዓት ቀያሪ የሐሳብ ንቅናቄ የአገርና የክፍለ ሀገራት “ችግሮች” ትረካን ወይም ገለጻንም ይመለከታል። ነባሩ የአገዛዝ መዋቅር የሚያተኩርባቸው ነገድን ከነገድ የሚያናቁሩ፣ በተለይ አማራን ኢላማ ያደረጉና የባህል ጦርነቶች ላይ የተጣዱ ትርክቶችና ገለጻዎች ናቸው። ሥርዓት ለዋጩ አስተሳሰብ የሚያማክለው ግን መላ የኢትዮጵያ ዜጎችና ባህላዊ ማህበረሰቦች የሚጋሩትን አገር አቀፍ የጉዳዮች መረብ ነው። ተያያዥ ጉዳዮቹ በዋና፟ነት የመሠረታዊ ልማት ጉድለትን፣ የኑሮ ደርጃ ዝቅተኛነትን፣ እንዲሁም የፍትሕና መልካም አስተዳደር እጦትን በዋና፟ነት ያካትታሉ።
እዚህ ላይ የለውጡ ሐሳብ ማለፍ ያለበት ፈተና የአገርና የአካባቢዎች ችግሮችን መጨበጫ አዲስ አመለካከትና አረዳድ ማዳበር እንጂ በአሮጌው ጎጠኛ የትርክትና ገለጻና አውታር ውስጥ ሆኖ ተጨማሪ መረጃዎችና ትችቶች ማራባት አይደለም። ወይም ደግሞ ‘መፍትሔዎች’ ማግኘት አይሆንም። ፈተናው በነባሩ የአገዛዝ መረብ ውስጥ የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት ሳይሆን ዚበዛ አስቸጋሪ የሆነውን አገዛዝ እንዳለ አወላልቆ በምትኩ ለአገርና ሕዝብ የሚበጅ የተሻለ የመንግሥት ሥርዓት መገንባት ነው።
እዚህ ላይ ተንቀሳቃሽ ሐሳብ ለመዋቅራዊ ለውጥ ትግሉ እንዴት መሣሪያ እንደሚሆን በቅጡ መገንዛብ ይጠቅማል። ዋናው ሥራ መሠረታዊ ሐሳቦችንና እሴቶችን ከተጨባጭ የአገርና ክፍለ ሀገራት ጉዳዮች፣ ከኅብረተሰብ አካላት ጥያቄዎች፣ ፍላጎቶችና እንቅስቃሴዎች ጋር ማቀነባበር ነው። ሆኖም፣ ትግሉን በዚህ ስልታዊ መልክ ቀርጾ ዘላቂ አነሳስ መስጠትና አቅጣጫ ማስያዝ ባለንበት ዘመን ቀላል አይደለም።
አዳጋች ለመሆኑ ሦስት ምክንያቶች ባጭሩ ልጠቁም። መጀመሪያ ነገር፣ የሐሳብን መስክ ራሱን ከሥርዓት ለውጥ አኳያ መልሶ መመንጠር፣ መጎልጎልና መኮትኮት ፈታኝ ሥራ ነው። ሜዳው የትግሉ ሐሳቦችና አላማዎች ብቻ ሳይሆኑ ተጨባጭ የዜጎችና አካአቢዎች ጉዳዮች፣ እንዲሁም ተያያዥ የለውጥ ዕቅዶችና መላዎች ነጥረው የሚወጡበት በመሆኑ ለአስርተ ዓመታት ከዋጠው አረም መላቀቁ ወሳኝ ነው።
ይሁን እንጂ ብዙዎቻችን፣ ምሁራን የተባልንም ጭምር፣ በአንድ አፍታ በሚታዩ አገዛዙ የሚፈጥራቸው፣ በሚዲያም የሚዘከዘኩ ተለዋዋጭ ችግሮችና ውጥረቶች እንሸበራለን። በዚህም ምክንያት አስተውሏችን ስለማይሰበሰብ፣ ትኩረታችንም ስለሚበተን ዝርዝር የአገር ጉዳዮችን ሰከን ባለ ስልታዊ ትንተና ለይተንም አቀናብረንም መጨበጥ ያዳግተናል።
ሁለተኛ፣ ንድፈ ሐሳብ ራሱ “በረቂቅነቱ” ከተለምዶ እውቀትና ግንዛቤ ወይም ከተጨባጭ መረጃዎችና ሁኔታዎች ጋር ምንም ያህል የማይቀራረብ ስለሚመስለን ይሆናል። በእውነቱ ግን ሰፋና ጠለቅ ያለ እሳቤ እንዳለ በቀጥታ ከሚስቡን የተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮችና ኩነቶች የራቀ አይደለም። አንድን “መሬት ላይ አለ” የተባለ እውነታ ጫር ጫር ስናደርገው ወይም ትንሽ ጠጋና ገባ ብለን ስንፈትሸው ሐሳብ፣ እምነት ወይም ትርጉም ይወጣዋል። ከአንጻራዊ አመለካከት ወይም አተረጓጎም አካቶ ነፃ ነው የሚባል አይደለም።
ሦሰተኛ፣ አገር አድን ሥርዓታዊ ለውጥን ከማራመድ አንጻር አስተሳሰብ ጠቃሚ የትግል መሣሪያ የሚሆነው ተግባራዊ እርምጃዎችንና እንቅስቃሴዎችን ሲመራ (ብርሃን ሲሰጥ) እንደሆነ እናውቃለን። ሆኖም፣ አንዳንድ ጊዜ ይህ ግንዛቤያችን ሐሳብ በቀጥታና ባንዳፍታ ድርጊታዊ ትርጉም ወይም ጥቅም ከሌለው ዋጋቢስ ነው ወደሚል፣ የዋህ ተግባራዊነትን የሚያንጸባርቅ እምነት ሊወስደን ይችላል።
ይህን የከረረ እምነት ስንከተል ሐሳብ (ርዕዮት) በአማራጭ መንገድ የመዋቅር ለውጥ ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል በቅጡ አንረዳም። ማለትም፣ ባንዳፍታና በተወሰነ ሁኔታ ተግባራዊ የትግል መሣሪያ ያልሆነ አስተሳሰብ በሰፊው ውጤታማ ሊሆን የሚችልበት ሌላ መንገድ እንዳለ “እንረሳለን”። በአብዮቱ ዘመን እንዳየነው፣ ንድፈ ሐሳብ ሙሉ የኃይሎች ሜዳ ሊከፍት ይችላል። በዚህም መንገድ የተለያዩ፣ ተባባሪም ተፎካካሪም ወገኖችን ለተግባራዊ ትግል በማደራጀትና በማነሳሳት፣ ትግላቸውንም ቅርጽና አቅጣጫ በመስጠት ሥራ ላይ ይውላል።
አገር ላይ መልሕቅ የጣለ የሐሳብ ንቅናቄ
ከአንድ ሁለት ወራት በፊት ከአገር ውጭ ያሉ በርካታ የኢትዮጵያ ስቪክ ማኅበራት በወለጋ ኗሪ አማሮች ላይ ስለሚካሄደው “መንግሥት መር የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ” ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም አረመኔያዊውን ወንጀል ሊያስቆሙት እንደሚገባ አጥብቆ ያሳስባል።
ግን መግለጫው አክሎ “ያለፍትህ ስለአገራዊ አንድነት…ማሰብ ቅዠት” እንደሆነም የነግረናል። “ፍትሕ” በሌለበት ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ሕዝብ ወይም አገር መኖራችን እውን ሊሆን ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል መሆኑንም የሚያጎላ የመስላል።
እዚህ ላይ መግለጫውን ያወጡት ለአገር ተቆርቋሪ ወገኖች “የረሱት” አንድ መሠረታዊ ነገር አለ። ይኸውም፣ ፍትሕም ሆነ ማንኛውም ሌላ ረቂቅ የእሴት ሥርዓት (ለምሳሌ “ዲሞክራሲ”፣ “ነፃነት” ወይም “ሕገ መንግሥት”) በጥልቅ ታሪካዊ ከሆነ የኢትዮጵያውያን እውን ብሔራዊ ሕይወት በፍጹም ተለይቶ ሊታይ አይችልም። ለአገር ችግር እንደ “መፍትሔ” የሚቀርበውም በድፍኑ ከአገር ማንነትና አንድነት “ውጭ” ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሥልጣኔ፣ ሞላም ጎደለም የራሱ የሥነ ምግባር፣ የብይንና የፍትህ ባህል አለው።
ይህን ውይይት ከመዝጋቴ በፊት የኃልዮ ንቅናቄን አገራዊ ሕንጸት ወይም ውቅር (ቅርጽና ይዞታ) በሚመለከት የሚከተሉትን የተያያዙ ጥቂት ነጥቦች ላስቀምጥ። አንደኛ፣ የፖለቲካ ሐሳብ ዋጋ ወይም ተገቢነት የሚተመነው ቃል በቃል በተወሰደ ረቂቅ ፍቺው ሳይሆን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህልና መንፈስ ጋር በሚኖረው ተጣጣሚነት ወይም ተዛማጅነትና ግንኙነት ነው። ከዚህ የግንኙነትና ተግባቢነት መንፈስ የራቀ ማንኛውም አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ላይ መልሕቅ መጣሉ ቀርቶ ክብደትና አቅጣጫ ሳይኖረው እንደ ጉም ተኖ ጠፊ ነው።
ሁለተኛ፣ ዘመን አመጣሽ ረቂቅ እሴቶችን አገራዊ የምናርገው ከብሔራዊ ባህላችን ጋር አቃቅረንና አጣልተን ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ልምድ ስንተችም ቢሆን አገራዊ ማንነታችንን እንደ ልብስ አውልቀን ለመጣል መሞከሩ ጅምር የለሽ “አብዮተኛ” ወይም ዘረኛ ሙከራ ነው የሚሆነው። በሐያሲነት ባህላዊ ጉድለታችንን እንዳስፈላጊነቱ ስንነቅፍም አስቀድመን የኢትዮጵያ ምድር ላይ ቆመን፣ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተነስተንና ተንቀሳቅሰን መሆኑ መረጋገጥ አለበት።
ሦስተኛ፣ ውድቀት የደረሰበት የኢትዮጵያ አንድነት በተሳካ፣ ተንቀሳቃሽ ሐሳብ መልሶ ሊጠናከርና ሊዳብር ይችላል። ይህ ግን ዘርፈ ብዙውን ብሔራዊ ኅብረታችንን አቃለን ወደ ሐሳብ አንድነት ዝቅ እናደርገዋለን ወይም እንቀንሰዋለን ማለት አይደለም። በአስተሳሰብ እንቅስቃሴዎች ስናደርግም አገራዊ አንድነታችን የሐሳቦችን ስክ፟ነት ወይም ቅንብር የሚዘልቅ ሕንጸታዊ ሙሉነት ያለው መሆኑን በመገንዝብም ነው።
ማለትም፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ህላዌና ምንነት በመልካዓ ምድር፣ በግዛታዊ አንድነት፣ በማኅበራዊ ኑሮ እና በሌሎች የሚዳሰሱና በቀጥታ የሚታዩ ገጽታዎች ሳይወሰን ብሔራዊ ባህልን፣ ስሜትንና ንቃተ ኅሊናን፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ኑሮንም አሳክቶ ያካትታል። ስለዚህ በቀላሉ እንዳልነበረ ሊሆን የማይችል፣ ለለውጥና መሻሻል በአንጻር ክፍት የሆነ ሕያው ውቅር ነው።
በዚህ አካታች ሙሉ ሕንጸቱ ኢትዮጵያዊነት የተለዋዋጭ አገዛዞችን ወይም ወገኖችን ክፉም በጎም አድራጊ ፈጣሪነት አልፎ ራሱ እምቅ ተንቀሳቃሽ ኅይል ነው። የምናስበው እውነታ ብቻ ሳይሆን በጥልቅ የሚሰማንና የምንኖረው፣ እንዲሁም ሊያንቀሳቅሰን የሚችል መሆኑን እንረዳለን።
አራተኛ፣ በወያኔና በኦነግ ቅርጹ ለአስርተ ዓመታት ሰፍኖ የቆየው የዘረኛ አገዛዙ አስመሳይ “ኢትዮጵያዊነት” በመሠረቱ የሙሉ ኢትዮጵያ ጠንቅ የሆነው ተጨባጭ የብሔራዊ ህልውናችን አካላት (በተለይ የመንግሥት፣ የምጣኔ ሐብት፣ የሃይማኖትና የትምህርት ዘርፎች) ውስጥ ሰርስሮም ወሮ፟ም ገብቶ በጭቆና መያዙ ብቻ አይደለም። በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያዊነትን እንደ እሴት፣ አስተሳሰብና እምነት ሥርዓትም እንዲሁ ወራሪና ጨቋኝ በመሆን ነው።
በዚህ ጠላታዊ መንፈስ ኦሮሟዊው አገዛዝ ኢትዮጵያን አካቶ ማፍረስ ካልሆነለትም ተጠባባቂ እቅዱ በኢትዮጵያዊነታቸው ከጸኑ ዜጎችና አገር ወዳድ ወገኖች የጸዳች “ኢትዮጵያ” በመፍጠር አገሪቱን መቆጣጠር ነው። ያም ሆነ ይህ፣ አገዛዙ የታሪካዊ ኢትዮጵያዊነትን ትርጉምና እሴቶች ዋጋቢስ አድርጎ ትናንት ወያኔዎች አሜባ አስመስለው የፈጠሩትን “ኦሮሚያ” የተባለ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ጎጥ “አገር” ለማድረግ ላይ ታች ይላል፣ አማሮችን ይጨፈጭፋል።
ይህ ቋሚ አወዛጋቢ ሁኔታ አገራዊ መሠረትና መነሻ ያለ፟ው መዋቅር ለዋጭ የሐሳብ ንቅናቄ ማኪያሄድን የበልጥ ፈታኝ እንዳደረገው አይካድም። ዛሬ ሙሉ ኢትዮጵያዊነት ለትግሉ ዝግጁ ሆኖ የተሰጠ መነሻ ሳይሆን ራሱ በትግሉ መጠጋገንና መጠናከር የሚያስፈልገው ብሔራዊ እሴትም ስልታዊ መሣሪያም ነው።
ለማጠቃለል፣ በዚህና ባለፉ ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ ከተጠናወታት አስከፊ ውጥረት ለማላቀቅ መዋቅራዊ ለውጥ ለምን እንደሚያስፈልግና እንዴትስ ሊካሄድ እንድሚችል በተጨማሪ ውይይት ሊዳብሩ የሚችሉ አስተያየቶች አቅርቤያለሁ። እንደሚታየኝ፣ ለውጡን የምናራምደው በሁለት የተለያዩ ግን ግንኙነት ያላቸው የሐሳብም የገቢርም መስኮች ወይም ደረጃዎች ነው።
መጀመሪያ፣ ዘላቂ ተጨባጭ ዕውቀት ለማፍራት ሐሳብን ከነተግባራዊ አፈጻጸሙ ሰፋና ጠለቅ ባለ ስልታዊ አቀራርብ ለመረዳትና ዜጎችን ለማስረዳት የምንጥርበት የትግል ሜዳ ነው። ቀጥሎና ተያይዞ ደግሞ ሕዝብን በሰፊው ለማግባባትና ለማነቃቃት፣ ብሎም ዘረኛ አገዛዙን በታክቲካዊ ዲስኩርና መልዕክቶች ለመግጠም የሚያስችል የፕሮፓጋንዳ ሥራና እንቅስቃሴ መስክ አለ። በዚህ መስክ ትኩረታችን የመልዕክቶች ይዘት (ዝርዝርነት ወይም ረቂቅነት) ሳይሆን በተለያዩ ሁኔታዎች የሚኖራቸው ቀልጣፋ ሰርጭት፣ አቀባበልና ፖለቲካዊ ውጤታማነት ነው።
ሁለቱ የተዛመዱ የሥርዓት ለውጥ ትግል ዓይነቶች ወይም ደረጃዎች እንዳይምታቱ ልዩነታቸውንም ግንኙነታቸውንም ጠብቆ መጠቀሙ አስፈላጊ ነው። የፊተኛውን ወደ ኋለኛው ዝቅ ካደረግነው፣ ሁኔታዎችን አይተን የምናደርጋቸውን የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች የሚገባ፟ቸውን የገለጻ፣ የዕውቀትና የንቃት ምንጭ እንነሳቸዋለን።
የኋለኛውን ታክቲካዊ የትግል ደረጃ ሆን ብለንም ይሁን ሳናውቅ ወደፊተኛው ስናጣጣው ወይም ስናሰፋው ደግሞ የሐሳብ ጥራትንና የስልት ጥልቀትን መስዋዕት ስለምናደርግ መዋቅራዊ ለውጥን በዘላቂነት መተለምና ተፈጻሚ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ለዘለቄታው ለማንም የኢትዮጵያ ነገድ የማይበጀውን ግን በአገሪቱ የተንሰራፋውን ፈላጭ ቆራጭ የዘር ፖለቲካ ሥርዓት ንዶ የተሻለ አማራጩን የመገንባቱን የአብርሆት ሥራ አዳጋች ያደርገዋል።
ሆኖም፣ ያለ፟ው አፓርታይዳዊ የዘር አገዛዝ መዋቅር ሳይወገድ አገር የማይድን መሆኑን፣ መዋቅራዊ ቅየራው ራሱ ደግሞ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚጠይቅ መረዳቱ ራሱ ወሳኝ የትግሉ መጀመሪያ እርምጃ ይመስለኛል። ቁም ነገሩ ኢትዮጵያዊነትን የለት ተለት አገራዊ ጭንቀታችን፣ በደል ተቀባይነት ስሜታችንና ብሶታችን፣ እንዲሁም በጠባቡ ተከላካይ የሆነ ተቃውሟችን መገለጫ ከማድረግ ማለፋችን ነው።
ከዚህ ውስን አሉታዊ አዝማማያ ዘልቀን ሰፋና ጠለቅ ባለ ወደፊት ተመልካች አስተውሎ ለብሔራዊ ሕይወታችን መትረፍ ብቻ ሳይሆን ማበብም ጭምር የሚበጅ የለውጥ ሽግግር መቀየስ ያስፈልገናል። ማለትም፣ ኢትዮጵያን/ኢትዮጵያዊነትን በሚቻለው መንገድ ሁሉ ተነቃናቂ የራስ አድን ዘመቻ ቅርጽና አቅጣጫ ማስያዝ ግድ ሊለን ይገ፟ባል።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
ሸጋ ነው ጋሼ።
ግን
የስርአት ለውጥ አገር ያድናል የሚለው መደምደሚያ “ስርአቱ የኛ ነው እስከ ደም ጠብታ መስዋእት ሁነን እንጠብቀዋለን” የሚሉት የሀገሪቱ ከግማሽ በላይ እየሆኑ ነው።
እንደምናየው ኦሮሙማ በአብዛኛው ኦሮሞ የገዛው እንቅስቃሴ ነው። ሌሎቹም የራስ ክልልነት ጥያቄ አቅራቢዎች ትግራይን ጨምሮ የራሳቸውን ማንነት ለማጉላት የአገርነትን አስተሳሰብ (ዜግነትን) ካካ የነካው እንጨት አድርገውታል። ማለትም አገር ማዳን ለእነዚህ ቡድኖች ምን ድምጸት አለው?
ሁሉም የሚውተረተረው በየራሱ ዘውግ ነውኮ። ይኼ ደግሞ ብሔርተኝነት በተጀመረበት በድሮው ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን በሙሉ ቅቡልነትና ፍላጎት ነው።
ታዲያ አገርስ ምንድን ነው? ሀገር ከብሔር የበለጠ ጥቅሙስ ምንድን ነው?
ማለቴ:
መቼም ዓለም የውድድር ነች። አገር ከብሔር የተሻለ ጠቃሚ መሆኑን ማሳመን ሲቻል ነው ብሔር አቀንቃኙን ወደ ዜግነት መሳብ የሚቻለው (አገር ማዳን እሱ ከሆነ)።
አሁን ባለው ሁኔታ አገር ምንም የለውም። ከብሔር በጣም ያነሰ ነው። አወ ያነሰ! አገር ምን አለው? ብሔርኮ መሬት አለው፣ ስራ ያስቀጥራል፣ ያስተምራል፣ ዳኝነትና አስተዳደር አገልግሎትም ይሰጣል ሌላም ሌላም።
አገር ምን አለው? የሌለውንስ ከየት አምጥቶ ይሰጣል?
አወዳድረውና አስመርጠን ጋሼ።
የኔ ማጠቃለያ
እውቀት የለኝም። ህይወት እና የራሴ ኑሮ ግን አለኝ። ስለ ስርአት ለውጥ እና አገር ሲነሳ ለምሁራን የሀሳብ መንሸራሸር ብቻ ቢሆንም ለብዙዎቻችን ግን እንድሞት ወይም እንድኖር የሚያደርግ ውጤት አለው።
ከዚያ ውጤት አኳያ በእውኑ የምንኖርበትን አውድ፣ መዋቅር፣ ስርአት ነው የምንፈልገው። በእውን የምንኖርበት! የምናብ አገር ልናስበው ብችልም ሊያኖረን ግን አይችልም። በእውኑ ደግሞ ኦሮሙማ እየሸመጠጠ ባለበት አካሄድ ሀገርነትን ማቀንቀን ምናልባትም ሌሎች ማንነቶችን ደምስሶ በለስ ቀንቶት የበላይነት ያገኘውን ማንነት የመቀበል አደጋ አለው። አዲሲቷ ኢቶጲያ እንደዛ ነው የታቀደችው። “እርሶ አገር ማዳን” ሲሉ ያንን ፕሮጀክት እውን ማድረግ ማለትዎት እንዳልሆነ እገምታለሁ።
እድሜና ጤና ይስጥዎ!
ካጠፋሁ መብቴ ነው 🙂