spot_img
Saturday, April 1, 2023
Homeነፃ አስተያየትኦርቶዶክስ ነባር እንጂ መጤ አይደለችም 

ኦርቶዶክስ ነባር እንጂ መጤ አይደለችም 

- Advertisement -

ኦርቶዶክስ ነባር እንጂ መጤ አይደለችም ፣  ከግራኝ አህመድ ወረራ እና ከኦሮሞ ጎሳዎች  መስፋፋት በፊት  ቤተክርስቲያን  በኢትዮጵያ ነበረች፣

ካህናት ያሬዳዊ ዝማሬ እያደረጉ (ፎቶ ግራፉ የተገኘው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ ማህበራዊ ድረ ገጽ ነው )

ከደረጀ ተፈራ – (በግል የቀረበ ዳሰሳ)

1. መግቢያ

እንደሚታወቀው አውሮፓውያን በተለያዩ ዘመናት በእምነት ሰባኪነት፣ በሃገር አሳሽነት (Exploration)፣ በጎብኚነት፣ በዲፕሎማት ማዕረግ እና በመሳሰሉት ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሃገራችንን በመሰለል ለቅኝ ገዥ መንግስቶቻቸው መረጃ ያስተላልፉ የእምነትና የታሪክ ቅርሶችንም በመስረቅ ወደሃገራቸው ያሻግሩ ነበር። ለምሳሌ በ 17 መ/ክ/ዘመን ጀምስ ብሩስ የተባለ እንግሊዛዊ (የስኮትላንድ ተወላጅ) የአባይን ወንዝ መነሻ ምንጭን ፉለጋ በሚል ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ታቦተ ፅዮንን ለማግኘት ብዙ ጥሮ ባይሳካለትም በመጨረሻ ግን በተሟላ ሁኔታ የሚገኙ ሁለት የመፅሀፈ ሄኖክ የግዕዝ ኮፒዎችን እና ሌሎች የብራና መፅሀፍትን ሰርቆ ሊወጣ ችሏል። ከእሱም በመቀጠል ሌሎችም ወደ ሃገራችን የመጡ ፈረንጆች በብራና የተጻፉ ቅዱሳን መጽሃፍትን፣ ታቦትን ጨምሮ በርካታ ነዋየ ቅዱሳትን እና የተለያዩ የታሪክ ቅርሶቻችን በመዝረፍ ወደ ሃገራቸው አግዘዋል። እነዚህ ወደ ሃገራችን በተለያየ ምክንያት የሚመጡ አውሮፓውያን የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነቱን በማላላት ሃገራችንን ለመቆጣጠር በህዝቡ መሃል መርዛቸውን ይረጩ ነበር። ለምሳሌ የክርስቲያኑን መንግስት ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ መተው የነበሩ ፖርቹጋሎች የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስን በሮማ ካቶሊክ ለመቀየር በመሞከራቸው በእነሱ ጦስ በርካታ ህዝብ በርስ በርስ ጦርነት እንዳለቀ በታሪክ ይታወቃል። ህዝቡን የእጅ ሞያ ጥበብ (ተግባረ ዕድ) ለማስተማር ከአውሮፓ ወደ ሸዋ የመጣ ዮሐን ክራፕፍ (Johann Ludwig Krapf) የተባለ የጀርመን ሚሲዮናዊ ነበር። ዮሐን ክራፕፍ እ.አ.አ ከ1837 እስከ 1842 ኢትዮጵያ (ሸዋ) ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት ከመጣበት ዓላማ ውጭ በሸዋና አካባቢው በየገጠሩ በመዟዟር፣ እንዲሁም ከሸዋ ርቀው በሚገኙ እንደ እናርያ፣ ከፋ፣ ጎንደር እና በመሳሰሉት የሃገራችን ክፍሎች በንግድ እና በኑሮ ወደ ሸዋ የሚመጡ ሰዎችን በማናገር መረጃ ያሰባስብ ነበር። አንዱን ህዝብ በሌላው ላይ በማነሳሳት ግጭት ለመፍጠር ሞክሯል። ለምሳሌ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን የአፍሪካ ጀርመኖች ናችሁ (“The Germans Of Africa”) ሌላ ጊዜ ደግሞ ሃገራችሁ “ኦርማኒያ (ORMANIA)” ናት፣ የአውሮፓን ባህልና ሃይማኖት ብትከተሉ መልካም በሆነላችሁ ነበር እያለ አዲስ ማንነት እንዲገነቡ መርዛማ ቅስቀሳ ያደርግ ነበር። (በስተመጨረሻ ላይ በተገለጸው ምንጭ #1፡ ገጽ 52 /Pdf ገጽ 2 ላይ ይመልከቱ)።

2. የኦነግ ምስረታ እና የሉተራን ፕሮቴስታንት፣

የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኛነት መነሻ በዋናነት የሉተራን ፕሮቴስታንት ሚሲዮናዊያን፣ የኮሚኒስቶች የጨቋኝ ተጨቋኝ የብሔር ፖለቲካ እና በማህበረሰቡ ዘንድ የቆየ የገዳ የተስፋፊነት ባህል ነጸብራቅ እንደሆነ ይታመናል። በንጉስ ሳህለስላሴ ዘመን እ.አ.አ ከ1837 ሸዋ መጥቶ የነበረው የቅኝ ገዥዋ የጀርመን ሰላይ የነበረው የዮሐን ክራፕፍ እና ከእሱም በኋላ ወደ ሃገራችን በመምጣት ወለጋ ላይ መቀመጫቸውን ያደረጉ የሉተራን ፕሮቴስታንት ሚሲዮናዊያን ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የብሄርተኝነትን ስሁት አስተምህሮ በተማሪዎቻቸው አእምሮ ውስጥ እንደዘሩና ይህ ዘረኝነት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ የኮሚኒስት የጨቋኝ ተጨቋኝ የብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብን (ርዕዮትን) እና በማህበረሰቡም ዘንድ የቆየ የገዳ የተስፋፊነት ባህል ከፖለቲካው ጋር እንደ አመቺነቱ በመቀላቀል የተጀመረ ሚስቶ ብሔርተኛነት ነው። መቀመጫቸውን ወለጋ ላይ አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የሉተራን (ስካንዴኔቪያን) ሚሲዮናውያን ህዝቡን በመያዝ እምነታቸውን በአካባቢው ለማስፋፋት ያመቻቸው ዘንድ ት/ት ቤቶችን፣ የህክምና ክሊንኮችን፣ የእርዳታ ሰጪ ተቋማትን በማቋቋም ለረጅም ጊዜ በአካባቢው በመቆየታቸው በትውልዱ ላይ ከእምነት እስከ ፖለቲካ አስተሳሰብ (ርዕዮት) ቀረጻ  ድረስ ከፍተኛ  ድርሻ አላቸው።  ወለጋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ የጀርመን (ስካንዴኔቪያን) የሉተራን ሚሲዮናውያን ህዝቡን እየሰበሰቡ በእምነት ስም የፖለቲካ መርዛቸውን ይረጩ ነበር። በአዲስ አበባ 5ኪሎ ከጀርመን ት/ት ቤት አጠገብ ወይም የቀድሞ የባህር ሃይል ክበብ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው የመካነ ኢየሱስ ቤ/ክ የኦሮሞ ነፃ አውጪ (ኦነግ) ጠንሳሾች በእምነት ሽፋን በመገናኘት ፖለቲካ የሚዶሉቱበት መነሃሪያቸው ነበር። ይህንንም በቀ/ኃ/ስላሴ ዘመን የወለጋ አስተዳዳሪ የነበሩት ፊታውራሪ ወልደ ሰማያት ከአርትቲቪ ጋር ባደረጉት ውይይት የገለጹት ሲሆን ወለጋ ውስጥ አራ ጉሊሶ እና በመሳሰሉት አካባቢዎች ጀርመኖች ህዝቡን ይቀሰቅሱ እንደነበር እና ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ተናግረዋል። በወቅቱ በሚሲዮናውያኑ እርሾ የተበከሉ የአካባቢው ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣቶች በወታደርነት ገብተው ቢያገለግሉ ስለሃገራቸው እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል፣ የፈረንጆቹን የክፋት ሃሳብ ይተዋሉ በማለት ንጉሱ የተወሰኑትን በመመልመል በወታደርነት እንዲሰለጥኑ በማድረግ እስከ መኮንንነት ማዕረግ ደረጃ ድረስ አስተማሯቸው። 

በወለጋ ይኖሩ የነበሩ የጀርመን ሚሲዮናውያን በላቲን ፊደል በመጠቀም የተረጎሙትን ወንጌል (አዲስ ኪዳን) እንደ መነሻ በማድረግ የሚሲዮናውያን ተማሪ የነበሩት እነ ኃይሌ ፊዳ አውሮፓ ለትምህርት እያሉ ከፈረንጆች ጋር በጋራ በመሆን በማሻሻል የኦሮምኛ ቋንቋን በላቲን ፊደል የአነባብ እና  የአፃፃፍ መመሪያ አወጡለት። ይህ በላቲን ፊደል የኦሮምኛን ቋንቋ አፃፃፍን የሚያሳይ ጥራዝ በአዲስ አበባ የጀርመን የባሕል ማዕከል ውስጥ በሚገኘው ቤተ መጻሕፍት በሚስጥር እንዲቀመጥ አደረጉ። ነገር ግን ይህን ያህል ርቀት ሳይሄዱ ከእዛ ቀደም ብሎ በአፄ ምኒልክ ዘመን የግዕዝ ፊደል በመጠቀም የኦሮምኛ መፅሃፍ ቅዱስ “መጫፈ ቁልቁሉ” በሚል ርዕስ በኦኒሲሞስ ነሲብ ተተርጉሞ ነበር። ይሁን እንጂ ፈረንጅ አምላኪ የሆኑ ኦሮሞ ብሔርተኞች ባህር ተሻግረው ለኦሮምኛ ቋንቋ መጻፊያነት የአውሮፓውን የላቲን ፊደል መረጡ። ባጠቃላይ የሉተራን መካነ ኢየሱስ ፕሮቴስታንት ቤ/ክ ከመነሻው ጀምሮ የኦነግ ርዕዮት መፈልፈያ እንኩቤተር ሆና አገልግላለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በንጉሱ ዘመን መጫና ቱለማ የሚባል የሸዋ ኦሮሞዎች የመሰረቱት መረዳጃ ማህበር ነበር። መጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና የልማት ስራዎችን ለማከናወን በሚል በ1956 ዓ/ም የተመሰረተ ይሁን እንጂ የማህበሩ አመራሮች እንደ ልማት ማህበር ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ድርጅት የሚንቀሳቀሱ ነበሩ። ከዚህ በላይ የተገለጸው ጀርመናዊው የዮሐን ክራፕፍ ይንቀሳቀስ የነበረው ሸዋ ውስጥ እንደነበር እዚህ ላይ ልብ ይሏል። እናም የመጫና ቱለማ ማህበር ስብሰባዎች ላይ የሚደረጉ ንግግሮች ከልማት ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው፣ ጊዜውን ባልዋጀ በተስፋፊ የገዳ ባህላዊ አስተሳሰብ እና የሚሲዮናውያኑ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ነጸብራቅ የሚታይበት ነበር። መሆኑም የሚሲዮናውያኑ ተማሪዎች የነበሩት እነ ሃይሌ ፊዳ፣ ዲማ ነግዎ፣ ሌንጮ ለታ፣ ባሮ ቱምሳ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ ኢብሳ ጉተማ እና የመሳሰሉት በ60ዎቹ በተማሪው እንቅስቃሴ ወቅት አብዛኛዎቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆኑ ኦነግ እና መኢሶን በሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶ ውስጥ በአመራር እና በአባልነት የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ጀመሩ። ኦነግ ቀጥታ ብሔርተኛ ሲሆን መኢሶን ደግሞ የኮሚኒዝም ርዕዮት የሚከተል የፖለቲካ ድርጅት የነበረና በርካታ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ መኮንኖች ይደግፉት ነበር። መኢሶን ከደርግ ወታደራዊ መንግስት ጋር ለጊዜውም ቢሆን መሞዳሞድ ቢችልም እንኳን  ደርግ ኢህአፓ የሚባል  ትልቁን ጠላቱን ካጠፋና የእውቀት  ድርቀቱን በመኢሶን ከተወጣ በኋላ በሁለት እግሩ  መቆሙን ሲያረጋግጥ መጨረሻ  ለስልጣኑ በመሰጋቱ ፊቱን ወደ መኢሶን አዞረ። በዚህ ጊዜ በርካታ የመኢሶን አባላት  ህይወታቸን ለማትረፍ ለደርግ  ወታደራዊ መንግስት በወዶ ገብነት እጃቸውን ሲሰጡ፣ ከፊሎቹ ደግሞ የጀርመንና የሌሎች የአውሮፓ የፕሮቴስታንት የእምነት ድርጅቶች ጋር በነበራቸው የቆየ ግንኙነት የሃይማኖት ሽፋን እየተሰጣቸው በመለኮታዊ ትምህርት (Theology Study) በሚል ሽፋን ወደ አውሮፓ እየሾለኩ ወጡ። የተወስውኑት ደግሞ በደርግ መንግስት ውስጥ ከነበሩ የኦሮሞ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ኔትዎርክ በወቅቱ ሶሻሊስት ሃገሮች የሚሰጡትን የነጻ ት/ት (Free Scholarship) በመተቀም ትምህርት ስም ወደ ውጭ ሃገር እየተሽለኮለኩ ከሃገር ወጡ። ለምሳሌ ከብዙ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል የመካነየሱስ (የሉተራን) ቄስ የሆኑት የቄስ ጊዳዳ ልጅ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በእምነት ስም ወደ ጀርመን ለትምህርት ከወጡት ውስጥ አንዱ ናቸው።  ዶ/ርነጋሶ ጊዳዳ ጀርመን በትምህርት ሳሉ በኦነግ ስር ወጣቱን በማደራጀት የፖለቲካ ተሳትፎ ነበራቸው፣ ሌላው ደግሞ አሰፋ ጃለታ የተባለ ሰው ነው፣ ይህ ግለሰብ ለደርግ መንግስት ያገለግል የነበረና ለአብዮቱ ላበረከተው አስተዋጽኦ ደርግ ወደ ሶሻሊስት ቡልጋሪያ “Karl Marx Higher Institute Of Economics” ለትምህርት የላከው ሲሆን “ከአርያን ዘር” የተገኘን ምርጥ የሰው ዘር ነን በማለት አውሮፓን ብሎም መላው ዓለምን በጦርነት እንዳተራመሰው የጀርመኑ ናዚ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሮሞ ህዝብ “ኦሮሙማ” ከሚባል ምርጥ  የሰው ዘር የተገኘ ነው የሚል ናዚያዊ አስተሳሰብ የሚያራምድ ግለሰብ ነው።

ይህ ሰው Journal Of Oromo Studies በሚል ስም የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጭ  የኖረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ኗሪነቱን  ያደረገ የአንድ ዩኒቨርስቲ የሶሾሎጂ መምህር (ፕሮፌሰር) ነው። ሌላው ደግሞ በንቲ  ቴሶ የተባለ ፓስተር ነው።  በንቲ ቴሶ በአንድ የጀርመን  የፕሮቴስታንት ተቋም ውስጥ መለኮታዊ ትምህርት የተማረና በጀርመን ሉተራን  ካህናት የተቀባ የኦነግ ፓስተር  (Reverend) ሲሆን  ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የኢትዮጵያ ስም በኩሽ መቀየር አለበት የሚል ዘመቻ ከፍቶ የነበረ ነው። ባጠቃላይ በትምህርት፣ በእምነት፣ በስራ እና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጭ ሃገር ወጥተው  በአሜሪካና በአውሮፓ ኑሯቸውን ያደረጉ ለሞያቸው፣  ለዕምነታቸውና ለህሊናቸው ታማኝ ያልሆኑ፣  ዋሾ ኦነጋውያን የሚገኙ ሲሆኑ ያለ በቂ መረጃና ምሁራዊ ፍተሻ በጥናት (research) ስም ለርካሽ  የፖለቲካ ዓላማቸው የሚያመቻቸውን ሃሰተኛ ትርክት እየፃፉ ህዝቡን በማስቆጣት ለአመጽ ሲቀሰቅሱ ኖረዋል መጸሃፍትና ምሁራን ለማለት ከተፈለጉት (context) ውጭ ሆን ብለው ቃላትን እና ታሪክን አጣመው በመተርጎም ብዙዎችን አሳስተዋል። በደርግ ዘመን የኦነግ አባላት የነጻ ስኮላር ሺፕ  ትምህርት ይከታተሉ በነበረበት ሶሻሊስት  ሃገራት የተማሩትን ወይም የሰሙትን የአውሮፓ ብሔረሰቦች የግጭት ታሪክ በሚያመቻቸው መልኩ የቦታና የስም ለውጥ በማድረግ በሃገራችን የተፈጸመ አስመስለው በማቅረብ በኦሮምያ ቋንቋ ለደጋፊዎቻቸው የፖለቲካ መቀስቀሻነት ተጠቅመውበታል። 

በተለይ በ1983 ዓ/ም ደርግ ወድቆ የሽግግር መንግስት ሲመሰረት የመንግስት ስልጣንን ላይ የተቀመጡት ወያኔ እና ኦነግ ነበሩ። በወቅቱም በሽግግሩ መንግስት የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር የነበረው የኦነጉ መስራች እና አመራር የነበረው ኢብሳ ጉተማ ነበር። ኢብሳ ጉተማ በ60 ዎቹ በተማሪው እንቅስቃሴ ወቅት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ “ማነው ኢትዮጵያዊ” የሚል መርዘኛ ግጥም ያቀረበ ነው። በኦነጉ ኢብሳ ጉተማ ይመራ የነበረው የትምህርት ሚኒስቴር የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ የተማሪዎችን መማሪያ መፃህፍትና የመምህራንን መመሪያ እንዲያዘጋጁ ውክልና ለክልሎች ሰጣቸው። በዚሁ መሰረት የክልል የትምህርት ቢሮዎች ካድሬ መምህራንን በመመልመልና ስልጠና በመስጠት በየክልላቸው ለሚማሩ ተማሪዎች የሚያገለግል የሙከራ (Trail edition) መማሪያ መፃህፍት በሚል ስም በየክልሉ የስራ ቋንቋ ማዘጋጀት ጀመሩ። ባዘጋጁትም የታሪክ፣ የቋንቋና የጂኦግራፊ (የህብረተሰብ) እና የሲቪክ መፃህፍት ውስጥ በካድሬዎች በተፈጠሩ አሉባልታ ወሬዎች እና በሃሰት ትርክቶች ሞሏቸው። በተማሪው መፃህፍት ውስጥ በሬ ወለደ ትርክቶችን በማካተት ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን ሳይሆን ጥላቻን እና ቂምን አስፋፉ። የትውልዱን ጭንቅላት በዕውቀት ሳይሆን በበቀል እና በጥላቻ ሞሉት። በተለይ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በመሳሰሉት ክልሎች በተዘጋጁ የመማሪያ መጻህፍት አማራውን ጠላት በማድረግ፣ ኦርቶዶክስ በማህበረሰቡ ላይ በግድ የተጫነች ናት፣ የኢትዮጵያውያን ሳትሆን የአማራ ብቻ ሃይማኖት እንደሆነች ሰበኩ። ኢትዮጵያም ከሰው ልጅ መፈጠር ጀምሮ በሂደት እዚህ የደረሰች የሰው ልጅ መገኛ ሳትሆን ከመቶ አመት የሚበልጥ እድሜና ታሪክ የሌላት፣ ህዝቦቿም በደምና በስጋ ያልተዛመዱ፣ የጋራ ታሪክ እና እሴት የሌላቸው ጥርቅም ህዝቦች እንደሆኑ አካተቱ። የአውሮፓ ሚሲዮናውያንን ታሪክን ገልብጠው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሰጡ። 

ኦነግ በወያኔ ስልጣኑን ተቀምቶ ከሽግግር መንግስቱ ከተባረረ በኋላ በኦነጉ ኢብሳ ጉተማ ተይዞ የነበረውን የት/ት ሚኒስቴርን የተካችው የህወሃት ታማኝ አገልጋይ የምትባለው የብአዴኗ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ነበረች። ገነት ዘውዴ ኦነግ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች በሙከራ ስም ጀምሮት የነበረውን ትውልድ አምካኝና ሃገር አፍራሽ የሆነውን የትምህርት ስርዓት (ካሪኩለም) እስከ ዩኒቨርስቲርስቲ ድረስ በመቀጠል አጠናቃ አፀደቀችው። 

ኦነግ ከስልጣን ከተባረረ በኋላ እሱን ተክቶ ኦሮሚያ የሚባለውን ክልል ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር እና የሚኒስትርነት ስልጣንን የተካው በወያኔ የተፈጠረው የምርኮኛ ወታደሮች ስብስብ የሆነው የትናንቱ ኦህዴድ የዛሬው የአብይ አህመድ የኦሮሞ ብልጽግና ነው። እነዚህ በኦነግ እና በህወሃት ስሁት የብሄር ፖለቲ የተቀረጹ የኦህዴድ ካድሬዎች  የሃሰት ትርክት ፈጥረው በማስጮህ የጥላቻ ሃውልት አቆሙ፣  በጀትና የሰው ሃይል መድበው በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በሚዲያ በት/ት፣ በዘፈን፣ በመዝሙር እና በመሳሰሉት  በመንግስት ተቋማት የሚመራ የተቀናጀ ዘመቻ በአማራ ህዝብና በኦርቶዶክስ ላይ ከፈቱ። ዘወትር በቅዳሴና በጸሎት መሃል ስለሃገራቸው ሰላምና ስለ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት የሚጸልዩ ካህናቱን እና መነኮሳቱን እንደ ወራሪና ባህል አጥፊ ስማቸውን አጠለሹት። በተለያዩ የጓዳ እና የአደባባይ ጎጂ አምልኮት ተተብትበው የነበሩ፣ ሰውን ከጌታው ጋር እስከ ህይወቱ እስከ መቅበር የሚደርስ ባህል የነበራቸው የሃገራችን ማህበረሰቦችን በከፍተኛ መንፈሳዊ ተጋድሎና መስዋዕትነት በብዙ ድካምና ጸሎት ነጻ ያወጡ መንፈሳዊ አባቶችን በወራሪነት ወነጀሉ። የኢትዮጵያን ህዝብን እንደ ማጣበቂያ ሰብስባ የያዘቸውን ኦርቶዶክስን ባቆመችው በሃገሯ ላይ መጤ ናት ብለው ስሟን አጠፉ። በኦርቶዶክስ እና በአማራ ህዝብ ላይ ባደረጉት ስም የማጥፋት ፕሮፓጋንዳ፣ በስውር ባደራጇቸው ቄሮና ኦነግ ሸኔ በሚባሉ ጽንፈኞች አያሌ ቤተ ክርስቲያናት በእሳት ወደሙ፣ ኦርቶዶክሳውያን በግፈኞች ደማቸው ፈሰሰ፣ ንብረታቸው ወደመ፣ ከኑሯቸው ተፈናቀሉ። 

3. ማስታወሻ፣ 

ከላይ እንደተገለፀው የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞች አንዱ መነሻ የጀርመን ሉተራን ሚሲዮናውያን የክፋት እርሾ ቢሆንም ኢትዮጵያን በማዳከም ታላቋን ሶማሊያ ለመፍጠር አልሞ የነበረው በዘይድ ባሬ የሚመራው የሶማሌ መንግስት ለኦነግ የፖለቲካና የሎጂስቲክ ድጋፍ እንዲሁም የመንቀሳቀሻ መሬት በመስጠት የኦሮሞ ብሔረተንኝነትን ለማቀጣጠል ሞክሮ ነበር። በወቅቱ በባሌ የአርብቶ አደር ጎሳዎች መሃል በግጦሽ መሬት ምክንያት የተነሳን የእርስ በርስ ግጭትን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ሞክሯል። ሌላው በአርሲና በባሌ አካባቢ ግራኝ አህመድ ጦርነቱን በሚያሸንፍበት ወቅት ከተዋጊዎቹ መሃል በመምረጥ በግራድ (በገዢነት)ማዕረግ አካባቢውን እንዲያስተዳድሩ ይሾማቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ግራኝ የክርስቲያኑን መንግስት መዋቅር እያፈረሰ የእሱን አስተዳደር ያደራጅ ነበር። ይሁንና ግራኝ ተሸንፎ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የቀድሞ መዋቅሩ ሙሉ ለሙሉ ስላልተመለሰ በተለይ ከአረብ የሚወለዱና በባሪያ ንግድ ተሰማርተው የነበሩ የአካባቢው ተወላጆች ጅማን ማዕከል አድርገው ከዘይላ እስከ ምስራቅ አፍሪካዋ ዛንዚባር (ታንዛኒያ) ወደብ ድረስ የአካባቢውን ነባር ህዝብ እያፈኑ እንደ ሸቀጥ በባርነት በሁለቱ ወደቦች በኩል እያሻገሩ ይሸጡ ነበር። ይህ የግራኝ ጦርነት ተከትሎ በአረቦች የተስፋፋው የባሪያ ንግድ እንዲቆም ለመጀመሪያ ጊዜ አዋጅ ያስነገሩት አፄ ገላውዲዎስ ሲሆኑ በኋላም አፄ ምኒልክ ይድረስ ካባ ጅፋር ብለው በጻፉት የደንብ ማስከበሪያ ደብዳቤ ላይ “የሰው ባሪያ የለውም” . . . “እንደ ከብት ልሽጠው ልለውጠው አትበል”. . . ሁላችንም የእግዚአብሔር ባሮች ነን . . . ድሃ እወደደው፣ እተመቸው ቦታ ይኑር” . . .  በማለት ማስጠንቀቂያ እንደፃፉላቸው ይታወቃል። በመጨረሻም ቀ/ኃ/ስላሴ ከመላ ኢትዮጵያ የባሪያ ንግድን በብዙ ድካምና ጥረት እንዲቆም አደረጉ። ይሁንና የባሪያ ንግድ በመቆሙ ጥቅማችን ቀረ/ ተነካ የሚሉ የጅማ፣ የአርሲና የባሌ አካባቢ የባሪያ ነጋዴዎች በአጼዎቹ ላይ ሲያምፁ እንደነበር ይታወቃል። አሁንም በዘመናችን ከዚሁ አካባቢ የተነሱ እንደ ጃዋር ምርሃመድ፣ አህመዲን ጀበል እና የመሳሰሉት የብሔር እና የሃይማኖትን ካባ እንደ ወቅቱ ሁኔታ እየቀያየሩ በሚያደርጉት ቅስቀሣ በርካታ ህዝብ እንደሞተና እንደተፈናቀለ፣ ቤተክርስቲያኖች እንደተቃጠሉ ይታወቃል።

 4. ከግራኝ አህመድ ወረራ እና ከኦሮሞ ጎሳዎች መስፋፋት በፊት ቤተክርስቲያን በመላው ኢትዮጵያ ነበረች፣

የኦርቶዶክስ ለኢትዮጵያ መጤ ሳትሆን ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የነበረች ናት። ለጊዜው የሰሜኑን የሃገራችንን ክፍል ትተን በአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያን ክልል ጨምሮ በመላው ሸዋ እና በደቡቡ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለመመልከት ብንሞክር ከግራኝ አህመድ ጦርነት እና ከኦሮሞ ጎሳዎች መስፋፋት በፊት በርካታ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች በነዚህ አካባቢዎች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ለምሳሌ የየካ ሚካኤል፣ የአዳዲ ማርያም ውቅር ቤ/ክ፣ በየረር፣ በወጨጫ እና በመናገሻ ተራራ አካባቢ ተቆፍረው የወጡ ታቦታትና ቅዱሳን መጻህፍት፣ የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ በአርባ ምንጭ (ጋሞ) የምትገኝ በኦሪት መስዋዕት ይቀርብባት የነበረች ብርብር ማርያም ቤ/ክ፣ በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት አክሱም የነበረው የፂዮንን የቃልኪዳኑን ታቦት ካህናቱ የሸሸጉት በምስራቅ ሸዋ በሚገኘው በዘዋይ ሃይቅ ደሴቶችን እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ግራኝ አህመድ ፀሃፊ የነበረው የመናዊው አረብ ፈቂህ በባሌ የሚኖሩ በርካታ ክርስቲያኖች እንደነበሩና በግራኝ ተዋጊዎች ተሸንፈው እምነታቸውን በመቀየር ሙስሊም እንደሆኑ ይገልፃል። (The conquest of Abyssinia p107 እስከ 119) 

በ1517 ዓም በግራኝ የሚመራጦር ከደዋሮ (ከሐረር) በመነሳት ፈጠጋር የተባለውን የክርስቲያኑን መንግስት አውራጃ ላይ ወረራ በፈጸመ ጊዜ መጀመሪያ በዳዋሮ (ምስራቅ ሐረርጌ) ውስጥ የምትገኝ ቤተክርስቲያንን ነበር ያቃጠለው። በመቀጠል በዘይላ (ሶማሌ) ወደብ በኩል በወቅቱ የቀይ ባህርን የባህር መስመር ይቆጣጠሩ ከነበሩት የቱርክ የጦር ጀነራሎች ባገኘው የመድፍና የሙስኬተር ጠመንጃ እርዳታ፣ ከየመን፣ ከሞሮኮ እና ከመሳሰሉት የአረብ ሃገራት የመጡ ወዶ ገብ ተዋጊዎችን ከጎኑ በማሰለፍ ጦሩን ይበልጥ አጠናከረ፣ ሃረር ይኖሩ የነበሩ የአረብ ሼኪዎችም የክርስቲያኑን መንግስት እንዲወጋ ይበልጥ አበረታቱት። የቁስና የሞራል ድጋፍ ያገኘው ግራኝ አህመድ የንጉሱን ድንበር ጠባቂዎች ዳዋሮ ላይ በማሸነፍ በምስራቅ ሸዋ ዝቋላ ተራራ አጠገብ በመምጠት መሸገ። 

በመቀጠልም በመጋቢ 1521 ዓ.ም በምስራቅ ሸዋ ደብረዘይትን አልፎ በሞጆ አካባቢ ሽምብራ ኩሬ በተባለ ቦታ በተደረገ ጦርነት ግራኝ አህመድ የንጉሱን የአፄ ልብነ ድንግልን ተዋጊዎች ድል ካደረገ በኋላ በዚሁ አካባቢ ማለትም በፈጠጋር፣ በሽምብራ ኩሬ፣ በየረር፣ በደብረዘይት፣ በዱከም፣ በአቃቂ፣ በቃሊቲ፣ በባደቂ፣ በበረራ እና በአካባቢው ይገኙ የነበሩ በርካታ አብያተ ቤተክርስቲያናት እና የክርስቲያኖች መኖሪያ መንደሮችን በእሳት አወደመ፣ እምነቴን አልቀይርም ያሉትን በርካታ ክርስቲያኖች በሰይፍ ቀላ፣ ከፊሉን በባርነት ወደ አረብ ሃገር አሻግሮ ሸጣቸው። በርካታ ክርስቲያኖች ላለመታረድ ሲሉ እስልምናን ተቀበሉ። የአረብ ነጋዴዎች ከሃገራችን የተዘረፉ የተለያዩ የታሪክ ቅርሶችን፣ የሃገር ሃብት፣ ንዋየ ቅዱሳንን እና ኢትዮጵያውያንን ወደ አረብ ሃገራት በተለይም በአረቢያ ለጅዳ ከተማ ቅርብ በሆነች Zahid (ዛሂድ) በምትባል ቦታ እንዲሁም ህንድ ውስጥ Gujarat (ጉጅራት) ወደሚባል ግዛት ድረስ እያሻገሩ በባርነት ይሸጧቸው ነበር። “The Conquest of Abyssinia” P. xvii, xix, እና P. 26። እነዚህ እና የመሳሰሉት ምሳሌዎች የሚያሳዩት ከ16ኛው ክ/ ዘመን በፊት ጀምሮ በእነዚህ አካባቢዎች የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የክርስቲያን መኖሪያ መንደሮች እንደነበሩ ነው። ከግራኝ ጦርነት በመቀጠል በባሊ፣ በዳዋሮ፣ በፈጠጋር እና በመሳሰሉ በጥንታዊ የኢትዮጵያ አውራጃዎች ይኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች በኦሮሞ አርብቶ አደሮች ወረራና መስፋፋት ወቅት አብዛኛዎቹ በመዋጣቸው እና ኦሮምኛ ቋንቋ መናገር በመጀመራቸው፣ ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከባህል፣ ከቋንቋ እና ከመሳሰለው አንጻር ህዝቡ ይበልጥ ተቀየጠ።

ኦርቶዶክስ ስትገፋ ችላ፣ ስትበደል ይቅር ብላ፣ ስሟን ሲያጠፉ፣ በፈጠራ ወሬ ሲከሷትና ሲያቃጥሏት ለአምላኳ ከመጸለይ በቀር የበቀል በትር የማታነሳ፣ ለሃገርና ለህዝቦች አንድነት፣ ለሰላም መጠበቅ ብዙ ዋጋ የከፈለች፣ ፊደል ቀርፃ፣ ብራና ፍቃ፣ ስነ ጥበብ፣ ስነ ህንፃ፣ ስነምግባር፣ ስነ መንግስትን እና የሃገር ፍቅር ያስተማረች ናት። ሃገር በጠላት ተወረረ ሲባል ቀድማ ተገኝታ  ለአርበኛው የመንፈስ  ስንቅና ብርታት (ሞራል) የሆነች፣ ለሞቱት የምትጸልይ፣ አንድነትን እና ወንድማማችነትን የገነባች፣ የሃገር ባለውለታ ናት። ካህናቱ ከሃገር ሃገር እየተንከራተቱ ጌታ እስከ ዓለም ዳርቻ ሂዱና አስተምሩ ባለው መሰረት ክርስትናን ለቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ባስፋፉ ምን ባጠፉ ነው ይህ ሁሉ ዱላ፣ ጥፊና ሞት የደረሰባቸው! ምን በድለው ነው የኦሮቶዶክስ ምዕመናን መንግስት ባለበት ሃገር ደማቸው በጽንፈኞች የሚፈሰው? ፋሽስት ጣሊያን በአውሮፕላን እና በመድፍ ያቃጠላት ሳያንሳት አሁን ደግሞ የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች ባናፈሱባት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እንዴት በሃገሯ ላይ እንደጠላት ተቆጥራ ኦርቶዶክስ ትውደም? ኦርቶዶክስ መጤ፣ ቆሞ ቀር ናት እያሉ የሚዘባበቱባት ማንን እንደሚያመልኩ፣ የሰው ልጅ በግፈኞች ተዘቅዝቆ ሲሰቀል፣ በጅምላ ንጹሃን ተጨፍጭፈው በዶዘር ሲቀበሩ እንደ መንግስት ፍትህን ከማስፈን ይልቅ ገና በግፉአን በመቃብር ላይ ዛፍ እንተክላለን በማለት የብልጽግናን የስብዕና እና የሞራል ዝቅታውን ነግረውናል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ከብዙ ሃገሮች በፊት አስቀድማ ክርስትናን የተቀበለች፣ ልጆቿን ከአውሮፓ የባህል ወረራ ጠብቃ ያቆየች ናት። ኦርቶዶክስ በመልአክት የምታምን ኋላ ቀር ናት ወዘተ እያሉ ሲንቦጣለቁ የነበሩ የአውሮፓ ሚሲዮናውያን ዛሬ እራሳቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን ማዳን አቅቷቸው ወደ ጥንቱ አረማዊ እምነታቸው እና ባህላቸው ተመልሰው ሶዶማዊና እምነት የለሽ (Atheist) ሆነዋል። ግማሹም ወንድነቱን እያስጎረደ ጾታ የለሽ ባዶ ቅል ሆኗል። ኋላ ቀር ያሏት ኦርቶዶክስ ግን ዛሬም እንደ ጥንቱ ጸንታ ታላቅ የሞራል ልዕልና ላይ ትገኛለች። ይሁንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለዘመናት የፈጸመችውን ተጋድሎዋን በመካድና በኢትዮጵያ ታሪክ ማን ሲገነባ፣ ማን ሲያፈርስ፣ ማን ከተማ ሲያቃጥል እንደኖረ እየታወቀና ዛሬም በዘመናችን በአጣዬና በሻሸመኔ የሆነውን በዓይናችን እያየን እውነትን ገልብጠው ይነግሩናል። የብልጽግና መሪ የሆነው አብይ አህመድ ለፓርቲው አባላት እና ካድሬዎቹ ባዘጋጀው የስልጠና ማንዋል ላይ ኦርቶዶክስ ለሃገር ብልጽግና የማትጠቅም ናት በማለት እያጥላላ ጽፎል። በተቃራኒው ደግሞ ፈረንጆቹ Atheist በመሆን የተውትን የፕሮቴስታንት እምነትን እያወደሰ እነ ማክስ ዌበር (Max Weber) ከዘመናት በፊት የተናገረውን ያለፈበት ቲዎሪ ሰምቶ ፕሮቴስታንት ለስልጣኔና ብልፅግና አመች ነው ይላል። ጌታን ተቀብለናል የሚሉ የኦሮሞ ብልጽግናዎች በባህል ስም አምልኮ ባዕድን፣ የቃልቻ ማምለኪያ ቤት፣ አረማዊነትን እና ስርዓት አልበኛነትን በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ማስፋፋታቸው፣ ህዝባችን ለሚሉትም ማህበረሰብ የማስቡ፣ ፕሮቴስታንትን እንደ መሰባሰቢያ ክለብ ይጠቀሙበት እንጂ እምነቱን የሚያውቁትም ሆነ የሚያከብሩት አይመስልም። የብልጽግና መንግስት አጋር የሆኑ በነብይ ስም የተነሱ ሟርተኛ ጠንቋዮች ዘወትር የሚቃዡት መልካም ነገር ሳይሆን ኦርቶዶክስ ሲሰነጠቅ፣ ሃገር ሲበጠበጥ፣ ሃይማኖተኞች ሲከፋፈሉ ነው። በብልጽግና መንግስት ያየነው እውነተኞችን ሳይሆን በካራቴ እርኩስ መንፈስ የሚያስወጡ፣ ለአማኙ በብልቃጥ ዘይት ሸጠው በሃብት የሚከብሩ የነዋይ ፍቅር ያሰከራቸውን፣ በሞባይል ከጌታ ጋር በስልክ እናገናኛለን የሚሉ ፌዘኛ ሰባኪ ፓስትሮችን ነው። የዘመናችን ፕሮቴስታንትን ነን የሚሉ አስመሳይ የብልጽግና ጴንጤዎች ሞራልን እና ስነ ምግባር የሚባል ነገር የማያውቁ፣ በመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጠው በሙስና ሃብት የተጨማለቁ፣ የከተማ መሬት ሸጠው በህግ መጠየቅ ሲገባቸው ሃይማኖትን መደበቂያ ዋሻ ያደረጉ፣ ከግል አዳኛችን ከሆነው ከጌታ ጋር በግል ተነጋግረናል እያሉ የሚያላግጡ፣ ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ ነፍሰ ገዳይ ሙሰኛ ሌቦች ናቸው።

ባጠቃላይ መጠኑ ይለያይ እንጂ ኦርቶዶክስ በተለያዩ ጊዜያት በሃገሯ ላይ ስትገፋና ስትጠቃ ኖራለች። ለምሳሌ በመለስ ዜናዊ የኢህአዴግ አገዛዝ፣ በአብይ አህመድ የብልጽግና ፕሮቴስታንት ዘመን፣ በደርግ አብዮታዊ መንግስት፣ በፋሺስት ጣሊያን ቅኝ ገዢ ወራሪ ሃይል፣ በዮዲት ጉዲት፣ በግራኝ አህመድ እና በኦሮሞ ጎሳዎች ወረራ በኦርቶዶክስ ላይ የደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመትን መጥቀስ ይቻላል። የነብዩን ስደተኞች ተቀብላ ያስተናገደች ቤተክርስቲያን ግራኝን ተከትለው በመጡ አረቦች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባታል። የሱዳኑ የደርቡሽ ወረራ በጎንደር ያቃጠለው ቤተክርስቲያናት፣ በአእሮፓ በሚሲዮናውያን የደረሰባት የልጆቿ ንጥቂያና የቅርሶቿ መሰረቅ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን መሃል የዘሩት የፖለቲካ መርዝ፣ ሚሲዮናውያኑ ተማሪዎች የሆኑት የሃገራችን ፓስተሮች ኦርቶዶክስን በስነልቦና ለማሸማቀቅ በየመድረኩ የከፈቱባት ትችት፣ ስም የማጠልሸት ዘመቻ፣ ላለፉት አምስት የብልጽግና የአገዛዝ ዓመታት በቤተክርስቲያን እና በምዕመኗ ላይ የተፈፀሙ ግፎችና በደሎችን ስናይ ከጥንት እስከዛሬ ድረስ ኦርቶዶክስ በሃገሯ ላይ የተገፋች መሆኗን ያሳያል።

አብይ አህመድ የደህንነት ሰላይ በመሆን ሲያገለግለው የነበረው የወያኔ መንግስት በፓለቲካዊ ጣልቃገብነት አቡነ ጳውሎስን በመሾምና ህጋዊውን አቡነ መርቆርዮስን ወደ ውጭ በማሰደድ ሲኖዶሱን ለሁለት ከፈለው። ከቀድሞ ጀምሮ ሲኖዶሱን አንድ ለማድረግ በብዙ አባቶች ጥረት ሲደረግ የነበረውን የወያኔ መንግስት በተደጋጋሚ እንቅፋት ሲፈጥር የቆየ ሲሆን፣ በብልፅግና የማሰልጠኛ ማንዋል ላይ ኦርቶዶክስን ያዋረዳት አብይ አህመድ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሲል በወያኔ ተዘግቶ የነበረውን የሰላም በር ከፈተው። ምስጋና ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ይሁንና በመጨረሻ እርቁ ተፈፀመ። ቅቤ ባናቱ እንደሚባለው በመጨረሻ ሰዓት አብይ አሳዳጊ ጌቶቹ የከለከሉትን ስለፈቀደ ሻምፒዮን በመሆን መድረክ ላይ በወጣ ቁጥር አመስግኑኝ ባይ ሆነ። ከዚህ በተረፈ የተወገዙት እነ አቡነ ሳቢሮስን በተመለከተ አንድ ነገር ልበል፣ በጣም የሚገርመው በቋንቋችን ሰባኪያንን እና ዳቆናትን አሰልጥኑልን ማለት አንድ ነገር ነው፣ ነገር ግን አንድ ሰው ቋንቋውን ስለቻለ ብቻ ባቋራጭ በጳጳስነት ሹሙልን አይባልም። ከቆሎ ተማሪነት ጀምሮ በአብነት ት/ት ቤት፣ በገዳማት፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጎ ከዳቆንነት ትምህርት እስከ ጵጵስና ደረጃ ተምሮ፣ ቅኔውን፣ ድጓውን፣ ወዘተ ተምሮ በዕውቀትና በመንፈሳዊነት ጎልብቶ ለቦታው ብቁ ለመሆን ብዙ መንፍውሳዊና ስጋዊ ተጋድሎ የሚጠይቅ ነው። ከዚህ ውጭ በአቋራጭ እንደ እገሌ እኔም ጵጵስና እፈልጋለሁ ማለት ሳይማሩ የፕሮፌሰርነት ወይም ወታደራዊ አካዳሚ ሳይገቡና ጦር ሜዳ ሳይውሉ የወታደራዊ ጀነራልነት ማዕረግ ይገባኛል የማለት ያህል ድፍረት ነው። ይህ ያለብቃትና መንፈሳዊ ተጋድሎ ያለ ብቃት ለእኔም ስጡኝ ማለት ልክን አለማውቅ ብቻ ሳይሆን ሴጣናዊ ቅናትና ምቀኝነት የወለደው ጭምር ነው።

 5. ማጠቃለያ

ተጨቆንኩ ብሎ ሌላን ህዝብ የሚጨቁን በቀለኛ እንጂ የፍትህና የነጻነት ታጋይ ሊሆን አይችልም። ኦነግ ከ1982 ዓ/ም አሶሳ ላይ በንጹሃን አማራዎች ላይ ከፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ጀምሮ ይኸው እስከዛሬ ድረስ ፋሽስታዊ ድርጊቱን እንደቀጠለ ይገኛል። አሁንም በህይወት ያሉት የኦነግ መስራቾች እኛ የታገልነው መብታችንን ለማስከበር እንጂ ሌላውን ህዝብ ለመጨቆን፣ ለመግደል፣ ለማፈናቀል፣ ከተማ ለማቃጠል አይደለም ሲሉ አለመሠማታቸው እስካሁን ድረስ ለሚፈሰው የንጹሃን ደም እና ለሚወድመው ንብረት ተጠያቂ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ኦነጋውያን ወደ ትግል የገቡት መብትን ለማስከበር፣ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህና ለእኩልነት አለመሆኑ የመጡበት የሃምሳ ዓመት ታሪካቸው ይመሰክራል። ሃገር በመምራት ላይ የሚገኙ የኦህዴድ/ ብልጽግና ባለስልጣናት ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጀምሮ ከላይ እስከ ታች ድረስ የፖለቲካ እውቀታቸው የተቀረጸው ከዚሁ ከኦነግ እና ከወያኔ ስሁት አስተምህሮ ሲሆን፣ ወያኔ ስልጣን ላይ እያለ ከምልመላ ጀምሮ በስልጠና/ በግምገማ ጥላቻ ፖለቲካን እየጋተ ያሳደጋቸው፣ በየመድረኩ ላይ አማራን እና ኦርቶዶክስን ሲራገሙና ሲሳደቡ የኖሩ፣ በሴራ ፖለቲካ፣ በበቀልና በጥላቻ የተሞሉ ናቸው።

የኦነግ ብሄርተኝነት መነሻው ከላይ የተገለጸው ሲሆን መድረሻው ደግሞ የማርቲን ሉተር ደጋፊዎች እምነትን ሽፋን አድርገው በአመጽና በስርዓት አልበኝነት የጀርመንን ብሔርተኝነት በመቀስቀስ በጀርመን ይኖሩ የነበሩ በርካታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያናትን ቀምተው፣ የእምነት አባቶቶችን እና ምዕመናንን ገድለውና ከሃገር አሰድደው በፕሮቴስታንት እምነት ዙሪያ ተሰባስበው ጀርመን የሚባል ሃገር እንደመሰረቱት ሁሉ የሚሲዮናውያን የመንፈስ ልጆች የሆኑት የኦነግ እና የብልጽግና ወንጌላውያን ከኦነግ ሸኔ ጋር እየተናበቡ ቋንቋን ምክንያት አድርገው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት በመሰንጠቅ በሂደት የገነጠሉትን ሲኖዶስ ወደ ፕሮቴስታንት እምነት በመቀየር ከኦርቶዶክስ ነጻ የሆነ ኦሮሚያ የሚባል ሃገር ለመመስረት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ኦነግ ህሊና እና ሰባዊነት ያልፈጠረበት፣ የንፁሃንን ደም ሲያፈስ የኖረ፣ በርካታ የኦሮሞ ወገኖቻችንን በጥላቻ የመረዘ፣ ሃገራችንን በሃሰት ትርክት በክለው የኦሮሞን ወጣት አነሳስተውና ህዝቡን አሳስተው ሃገራችንን ቀምተው ስር እንደሌለው እንጉዳይ ነቅለው ሊጥሉን የተነሱ ርህራሄ የሌላቸው አረመኔዎች ናቸው። ሰዎቹ ታሪክ እና እምነት እንደሌለው ህዝብ ሃገራችንን አፈራርሰው ሊበትኑን ተነስተዋል። ይህንንም በወሬ ሳይሆን በተግባር በአሶሳ፣ በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉል፣ በቡራዮ፣ በአጣዬ፣ በወለጋና በመሳሰሉት የንጹሃንን ደም በግፍ አፍሰውና አፈናቅለው፣ ንብረታቸውን ቀምተው፣ ቤታቸውን አፍርሰው፣ ለዘመናት የተገነቡ ከተሞችን በአንድ ቀን አቃጥለው በዓይናችን አሳይተውናል። በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እራሳችንን ከጨርሶ ጥፋት የመታደግ ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብት እንዳለን መገንዘብ ያሻል። ስለዚህ ለሃገርህ፣ ለሃይማኖትህ፣ ለሚስትህ፣ ለልጅህ፣ ለናትህ፣ ለታሪክህና ለህልውናህ ስትል በያለህበት ተደራጅ!!! –//–

ምንጭ፣

  1. J. L. KRAPF A Personal Portrait in Memory of His Entry to East Africa. In 1844
  2. “The conquest of Abyssinia” Futuh al-Habasa (Arab Faqih) 2003 
  3. The Protestant Ethic and the spirit of Capitalism (Max Weber) pdf

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,472FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here