spot_img
Sunday, April 2, 2023
Homeነፃ አስተያየትማሰብ ማስተዋል አይነሰን ፣ እናስብ እናስተውል (ተሻገር ጓንጉል )

ማሰብ ማስተዋል አይነሰን ፣ እናስብ እናስተውል (ተሻገር ጓንጉል )

- Advertisement -

ተሻገር ጓንጉል    

በእልህ፣ በቁጭት፣ በስሜት በግንፍልነት ይገድስ አይገድስ ያበጠው ይፈንዳ የሚል የስድሳው ትውልድ ፖለቲካ ጉዳት ነው ያመጣብን። ስንራመድ የምንረግጠውን እንይ። በርካታ ደም የሚያፈሉ፣ ፀያፍ ነገሮች አይተናል፣ እያየንም ነው። በዘዴ በጥበብ እንጂ በመንጨርጨር መፍትሔ አይመጣም። ሀያ ሰባት ዓመት ሙሉ ወያኔ እንዴት ስልጣን ላይ ቁጭ ብላ እልቆ መሳፍርት ጉዳት ማድረስ ቻለች ብለን ራሳችን እንጠይቅ። ያ እንዳይደገም ምን እናድርግ? እንዴት ነው የማይመጥኑን የመሩን ብለን ረጋ ብለን እናስብ። ፕሮፌሰር መስፍን “መንቀል እንጂ መትከል አልቻልንም” ያሉት በተግባር አይተነዋል። አንድ መሪ ወይም አንድ ስርዓት መንቀል ላይ ብቻ ማተኮር ብልህነት አይደለም። የተሻለ አማራጭ ይዞ መቅረብ ጠቃሚ ነው። አንድ ወዳጄን አቢይ ቢሄድ ማን ይምጣ ብለህ አስበህ ነው ስለው፣ ልክ አቢይ እንደመጣው አንዱ ይመጣል ብሎኝ እርፍ። ትኩረቱ ሰው መቀየር ላይ ሳይሆን ስርዓት መቀየር ላይ መሆን አለበት። መንግስቱ ኃማ ብቻ ይውደቅ ከርሱ የባሰ አይመጣም ብለን ሚልየን ጊዜ የባሰ ነው የመጣብን። 

በ1966 ዓም ልጅ እንዳልካቸው መኮንን እባካችሁ ፋታ ስጡኝ ሲሉ ፋታ አግኝተው ቢሆን ኖሮ  ሰውዬው ትልቅ ስራ ይሰሩ ነበር። ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በ1968 ዓም አብረን እንስራ ብሎ የግንባር ጥሪ ሲያቀርብ ኢሕአፓ እና መኢሶን ተስማምተው ግንባር ፈጥረው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ አሁን ትልቅ ደረጃ ትደርስ ነበር። በ1983 ዓም መንግስቱ ኃይለማርያም የፕሮፍ መስፍንን ፕሮፖዛል ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ወያኔ በአገር በህዝብ የመቀለድ የማላገጥ ዕድል አይኖራትም ነበር። በተማረው የህብረተሰብ ክፍላችን በኩል ችግርን ወይም በጎ ጎንን ማጉላትና ወደ አጎላው ጭልጥ ብለን ጭፍን ተቃዋሚ ወይም ጭፍን ደጋፊ መሆን ጥበብ የጎደለው መደዴ ፖለቲከኛነት ይታያል። አንድ ነገር ስንቃወም የምንተካውንም እናስብ። አፄ ኃይለስላሴን ያን ያህል አምርረን ስንኮንን ስንቃወም ምን ለማምጣት እንደፈለግን አናውቅም ነበር። ደርግን ስንቃወም ለስልጣን የቋመጡ ግልገል ፋሺስቶች ደርግን ይተኩታል ብለን አልገመትንም ነበር። ወያኔ አስመርራን፣ ቁም ስቅል አሳይታን ነበር። ከሂትለር እና ሙሶሎኒ የሚወዳደር ወንጀሎች በአማራው ሕዝብ ላይ ስትፈፅም በርካታ አማራ ነን የሚሉ አሁንም ስልጣን ላይ ያሉ ተባብረዋል።ንስሐ እንኳን አልገቡም። የአማራ ሕዝብ ዋና ተቆርቋሪ ሆነው አዲስ የፖለቲካ ቡድን ሁሉ አቋቁመዋል። ይባስ ብለው ወያኔን ያልተጠጉ፣ ወያኔን አምርረው የታገሉት የዘር ፖለቲካ አያዋጣም ብለው ሲቃወሟቸው እነዚህ ኮፍያ ለውጠው ማዕድ ላይ የተቀመጡ  የወያኔ ሎሌ የነበሩ ዓይን አውጣዎች ሐቀኞች ፀረ የዘር ፖለቲካ አቋም ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን “ፀረ አማራ” ብለው ይከሳሉ፣ ይሳደባሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመንግስት በተቃዋሚውም በስርዓት በሎጂክ በፕሪንስፕል አልተያዘም። መንግስትም ሆነ የብልፅግና ፓርቲ ፍኖተ ካርታ የለውም። የዛሬ አምስት ዓመት አቢይ የመጀመርያ ንግግሩን ካዳመጥን በኋላ ለሁሉም ወዳጆቼ ንግግሩ as a piece of rhetoric ወርቅ ነው።  ነገር ግን ፍኖተ ካርታ የለውም ነበር ያልኩት። አሁንም የወያኔን ጭቃ ዝቃጭ ሕገ መንግስት ይዘን ነው የምንተራመሰው። ችግሩን የፈጠረውን ችግር ፍታ እያልን በሀገር በሕዝብ እያላገጥን ነው። ይሄ ሕገ መንግስት ተቀዳዶ ካልተጣለ ከችግር አንወጣም። አሁንም እንደ 1966ቱ፣ እንደ 1969ኙ መተራመስ እንጂ ተቀራርበን መወያየት አልቻልንም።

የምክክር ጉባኤው ምን እየሰራ እንደሆነም አናውቅም። ፕሮግረስ ሪፖርት የለም። ብቅ ብሎ እዚህ ደርሻለሁም አይለንም። ለአስር ደቂቃ ከህዝብ ጋር አልተወያየም። የምክክር ጉባኤው ስራውን ሳይጀምር በእሽቅድድም አዳዲስ ክልል መፍጠርም ተጀምሯል፣ ክልል እንሁን ትርምስ እየተስተናገደ ነው። ሶሻል ሚድያ እንደ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ነው የሚሰሩት። የስዩም ተሾመን የኔታን እና 360ዎችን ማየት ይበቃል።  360ዎች 24/7/365 የሚባዝኑት አቢይን ለመጣል ብቻ ስለሆነ የፓለቲካ ቡድን ልሳን ነው የሚመስሉት። የኔታ ደግሞ በተቃራኒው። ስርዓት ሳይሆን ግለሰብ ላይ ነው በድጋፍም በተቃውሞም የሚረባረቡት። 360ዎች ይሄን ስርዓት የፈጠሩት፣ ያፋፉት፣ የበደኖ ወይም የአርባገጉ ወይም የጉራፈርዳ ሆሎካስት ጊዜ የወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ናቸው። በከፍተኛ ደረጃ መወቀስ ያለበት ዝም ያለው ብዙኃን The silent majority ነው። እውነት ያለው፣ ሐቀኛው ዝም ያለው ብዙኃን ነው። ይሄ የሕብረተሰብ ክፍል ተቃወም ወይም ደግፍ ብለው የሚቀሰቅሱት ሁለቱ ፅንፎች አልጣሙትም። ጭፍን ደጋፊ እና ጭፍን ተቃዋሚዎችን በአርምሞ እያያቸው ነው። ጠሚ ዶር አቢይ ፍኖተ ካርታው ቢታወቅ ይሄን የሕብረተሰብ ክፍል ከጎኑ ማሰለፍ ይችላል።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,472FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here