spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትያ ትውልድና የብሄረሰቦች ጥያቄን አስመልክቶ አጭር አስተያየት (አበጋዝ ወንድሙ)

ያ ትውልድና የብሄረሰቦች ጥያቄን አስመልክቶ አጭር አስተያየት (አበጋዝ ወንድሙ)

Ethiopia _ Ya Tiwuled

 (አበጋዝ ወንድሙ)

ያ ትውልድ ተብሎ የሚታወቀውና በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ 1960ዎቹና በ 1970ዎቹ፣ በተማሪውና በግራ ዘመም ድርጅቶች ተካፋይ የነበረው ትውልድ፣ በዘመነኞች ብዙ የሚወቀስባቸው ነገሮች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።  በጥቅሉ ሲታይ ኩነኔው የሚጠነክረው ግን ‘የ ብሄረሰቦች ጥያቄ በሚል የሌለ ነገር ፈብርኮ’ ወይንም ትንሽ ‘ቸር’ በሆኑት ወገኞች ደግሞ፣ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ ከሀገራችን ሁኔታ ሳያገናዝብ እንዳለ ኮርጆ በማምጣት አሁን ሀገራችን ለገባችበት ችግር ዳረገን የሚል ይገኝበታል።

በሌላ ወገን ደግሞ፣ ራሳቸውን የተወሰነ ብሄረሰብ ብቸኛ ጠበቆች አድርገው በሚወስዱ ጠባብ ብሄርተኛ ወገኖች ደግሞ፣ ዋለልኝ የጻፋት ባለ አምስት ገጽ ጽሁፍ ላይ ተቸክለው፣ ትውልዱ የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ የነበረውንና፣ በሂደትም፣ በጥልቀት ያዳበረውን አመለካከት ሳይሆን፣ ዋለልኝ ጽሁፍ ላይ ‘ቁንጽል ቃል ወይንም ሃሳብ ወስዳችሁ ግነትን አስወግዱ‘ ያለውን ምክር ዘንግተው የሚያካሂዱት የተዛባ እንቅስቃሴ፣ ትውልዱ ላይ ለሚደርስበት የሀሰት ውንጀላ የራሱ ድርሻ አለው።

ዋለልኝ የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ያቀረበው ባለ አምስት ገጽ ጽሁፍ፣ እሱ ራሱ እንዳለው  የጅምላ እሳቤና የደካማ ትንታኔ (suffers from generalizations and inadequate analysis) ችግር ቢኖርበትም፣ ለጀማሪ ጽሁፍ ግን ‘ተራ ወይንም እዚህ ግባ  የማይባል’ (  mediocre) እንዳልሆነ ይገልጻል ። ጽሁፉ የዋለልኝን ስም ይዞ ይውጣ እንጂ  በጽሁፉ እንደገለጸው የተወሰኑ ሰዎች በህቡዕ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ያካሂዱበት የነበረ ስለነበር ፣ ጽሁፉ የቡድኑን አመለካከት ያንጸባርቃል የሚል ግምት መውሰድ ይቻላል። 

በወቅቱ በቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ የነበሩ የተማሪው ትግል አቀጣጣይ መሪዎች ፣ በአጠቃላይ በዓለም ላይ የበላይነት ይዞ የነበረው የሶሻሊስት አመለካከት ‘ምርኮኛ’ የነበሩ በመሆኑ ፣ የህብረተሰብ ችግር ትንታኔያቸው በዚያው አውድ ውስጥ እንደነበር ይታወቃል።

 ሆኖም የህብረተሰብ ችግርን ተንትነው የሚረዱበት መንገድ፣ ሶሻሊስት አመለካከት ላይ ባላቸው ወይንም በነበራቸው በቂ ያልሆነ ወይንም የዕውቀት ውሱንነት ላይ የሚመሰረት በመሆኑ፣ የዋለልኝንም ጽሁፍ ማየትና መረዳትም ያለብን ከዛ አንጻር ሊሆን ይገባ ነበር ። 

ለዚህም ነው፣ የዋለልኝ ጽሁፍ በኢትዮጵያ የ ብሄረሰቦች ጥያቄ ላይ ያለው ፈር ቀዳጅነት እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ግርድፍና ያልተሟሸ ስለነበር ፣ የተማሪው ንቅናቄም ሆነ በወቅቱ የነበሩት የሶሻሊስት ርአዮተ ዓለም ተከታይ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሂደት ጥያቄውን በቅጡ ተወያይተው፣ አበልጽገውና አዳብረው በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችን  በማቅረብ በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ ነው ብለው የሚያስቡትን  አቋም ለመውሰድ የበቁት።

በወቅቱ ይመሩበት ከነበረው የሶሻሊስት ርአዮተ ዓለም በመነሳትም ፣ የብሄረሰቦች ጥያቄ በህብረተሰብ ውስጥ ካሉት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አንዱና ምላሽ የሚያስፈለገው ቢሆንም፣ በዋናነት ግን የህብረተሰቡ ችግር የሚፈታው የሁሉም ብሄረሰብ አባላት የተጨቆኑ መደቦች በአንድነት ፣በአንድ የሰራተኞች ፓርቲ መሪነት ተደራጅተው በሚያደርጉት የህብረት ትግልና ይዞት በሚመጣው ሶሻሊስታዊ ስርዓት እንደነበር በሙሉ ልብ  ያምኑም ነበር።

 በወቅቱ የ የካቲትን አብዮት ተከትሎ በሀገርቤት የነበሩት ሁለት ዋና ዋና የግራ ድርጅቶች፣ማለትም ኢህአፓም ሆነ መኢሶንና እንዲሁም ሌሎች ህብረብሄራዊ ድርጅቶች ፣ አደረጃጀታቸው፣ የአባላት ምልመላቸውና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ህብረብሄራዊ የነበረ ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ የብሄረሰቦችን ጥያቄ አፈታት አስመልክቶ የነበራቸው መሰረታዊ አቋም ከላይ በተጠቀሰው የሶሻሊስት ርአዮተ ዓለም የተቃኘ ነበር። (ትናንት የህብረብሄራዊ ትግል አቀንቃኝና መሪ የነበሩትን እኔ ሃይሌ ፊዳንቀይ ጎበናዎች’ እያለ ሲያወግዝ የከረመ የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኛ ዛሬ ላይሃቀኛ የኦሮሞ ታጋዮች’ በሚል ማንቆለጳጰስና ወደ ጠባብ ብሄርተኛ ታጋይ ጉያ ለመክተት ሲውተረተር ማየቱ ገራሚ ቢሆንም!)

ሁለቱም ድርጅቶች የብሄረሰቦች ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ የሚያገኘው ከመደብ ትግሉ ስኬት ጋር እንደሆነ ቢቀበሉም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የ የካቲትን አብዮት ተከትሎ የፈሉ ድርጅቶችን ፣ በየብሄረሰቡ ያሉ የገዥ መደብ አባላት ‘የኛ’ የሚሉትን፣ ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍል  ነጥሎ ለመበዝበዝ እንዲያመቻቸው ስሜት ኮርኳሪ ቅስቀሳ በማካሄድ የጭቁኖችን አንድነት ሊያላሉ ስለሚችሉ ፣ ይሄንን ለመግታትና ትግሉን ፈር ለማስያዝ ፣ በብሄር ለተደራጁትም ትግሎች ውሱን  ድጋፋቸውን አልነፈጉም። 

የብሄሮች ጥያቄን ዴሞክራሲያዊ ገጽታ ተቀብለው ድጋፋቸውን ቢሰጡም ግን በዋናነት የተንቀሳቀሱት ፣ ህብረብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበት እንደነበር በወቅቱ የሚያወጧቸው ጽሑፎችም ሆነ ውድ ህይወታቸውንም የገበሩበት የትግል ታሪካቸው ህያው ምስክር ነው።

በወቅቱ የነበሩት ድርጅቶችም ሆነ አባላቱ ሊወቀሱ የሚገባቸው ነገር ቢኖር ጠባብ ብሄረተኝነትና፣ በዛም ላይ ተመስርቶ የተደራጁ ድርጅቶች የሚያደርጉት ስሜታዊ ቅስቀሳዎች ምን ያህል  ህዝብን በቀላሉ የማማለል ሃይል እንዳላቸው ባለመገንዘብ ከድርጅቶቹ ጋር ማድረግ የነበረባቸውን አስፈላጊና ጠንካራ ርዕዮተ ዓለማዊ ትግል አለማድረግና፣ ይብሱኑ  ያሳዩት ቸልተኝነት፣ደርግ ካደረገባቸው ገደብ የለሽ ጭፍጨፋና፣ ድርጅቶቹን ለማጥፋት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ ፣ በሂደት ህብረብሄራዊ ትግሉን ሸርሽሮና አዳክሞ ጠባብነት የበላይነት እንዲጎናጸፍ ማስቻሉ ላይ ነው። 

በወቅቱ በዚህ ጥያቄ ላይ የተሰራው ስህተት ለብሄርተኛ ድርጅቶች ጎልቶ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ያገኙትን ጥንካሬ በመጠቀም ከደርጉ በትር ተርፈው ለማንሰራራት የሚሞክሩትን ህብረብሄራዊ ድርጅቶች በተቀናጀ መልክ ጦር መዘው እስከ መበተንና ራሳቸውንም እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል ።

የዚህ መዘዝም ሀገራችን ከ1983 ዓ.ም. የህወሃት ስልጣን ላይ መውጣት ጀምሮ እስካሁን የሀገሪቱን ፖለቲካ የሚንጥ፣ የሀገራችንን የዴሞክራሲና የእድገት ጎዳና በማጨናገፍ ላይ ያለ መሰረታዊ ችግር ሆኖ ዘልቋል።   

ህወሃት፣ ኢህአዴግ የሚል ጭምብል አጥልቆ አራት ኪሎን ቢቆጣጠርም፣ በጠባብ ብሄርተኝነት የተቃኘው መሰረታዊው ስትራቴጂው፣ ሃገራዊ አንድነትን በማላላትና በብሄረሰቦች መሃከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማደፍረስና ልዩነትን በማራገብ፣ የበላይነቱን ለዘለቄታው የሚያስቀጥል መስሎት ስለነበር፣ ለ 27 አመታት ሲተገብረው ከርሞ፣ በስተመጨረሻ አገዛዙ ባንገሽገሻቸው አካላት የተባበረ ህዝባዊ ትግል ለውድቀት ተዳርጓል ።

እኩልነትና ፍትሃዊ አገዛዝ በናፈቀው ህዝብ ትግል የሀወሃትን የበላይነት ተክቶ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት የጨበጠው የኦሮሞ ብልጽግና ክንፍ፣ በመጀመሪያው ዓመት በመሪው አማካኝነት ካለፈው ስህተት ተምሬ ከልዩነት ይልቅ ሃገራዊ አንድነት ላይ አበክሬ እሰራለሁ ብሎ ምሎ ቢገዘትም ፣ በሂደት ግን ከህወሃት ውድቀት ምንም ያልተማረ እንዲያውም የከፋ ጠባብ ብሄርተኛ አንጃ በውስጡ አቅፎ ሀገሪቷን ከባድ አደጋ ላይ ጥሏት ይገኛል፤ በወቅቱ ካልታረመም በታኝ የመሆን ወይንም ሀገራችንን ለማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት የመዳረግ አቅም ሊኖረው    ስለሚችል፣ ዛሬም እንደትላንቱ ጠባብ ብሄርተኝነት ለሀገር እድገትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንቅፋት ስለሆነ በጽኑ ልንታገለው ይገባል።

ያለፉት 31 ዓመታት በተግባር የታየው የጠባብ ብሄርተኞች አገዛዝ ለሀገር የማይበጅ፣ እንወክለዋለን በሚል በስሙ የሚነግዱበት ብሄረሰብንም ከርሃብ፣ከድህነትና ከቸነፈር ፈቅ ያላደረገ፣ ፍትህን የነፈገ ፣ በተቃራኒው ለአገዛዙ ቁንጮዎችና ባለሟሎቻቸው ስልጣንና ንብረት ዘረፋ የተመቻቸ እንደነበር ያየነውና በማየት ላይ ያለነው እውነታ ነው።

ጠባብ ብሄርተኛ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአንድ ህብረብሄራዊ ሀገር፣ የኛ ከሚል እሳቤ ይልቅ ሁልጊዜ የኔ ለሚለው ወገን ብቻ ተቆርቋሪ መስሎ ራሱን ለበላይነት የሚያጭን ኃይል ይመለከታል። አንዳንድ የጨነቀረ አስተሳሰብ የሚያራምዱ አካላት ከህዝብ ቁጥር ጋር በማያያዝ ፣ ጠባብነት በቁጥር ትንሽ ለሆኑ የብሄረሰብ ክፍሎች ብቻ የተሰጠ የሚመስላቸው፣ በቁጥር ትንሽ ሆኖ ሀገራችንን 27 ዓመት ያመሰውን ህወሃትና አሁን ደግሞ በተራው እያመሰን ያለውን የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን አካሄድ ማጤን ትምህርት ይሆናቸዋል። 

ከላይ የቀረበውን ዕውነታ በቅጡ ካገናዘብን ፣ የስልሳዎቹ ታጋዮች ስለ ጠባብ ብሄርተኞች መሰረታዊ ድክመት የነበራቸውን እይታ ትክክለኛነት የሚያሳይ መሆኑን፣ ጠባብ ብሄርተኞች በትግል ስም ለሰፊው ሕዝብ ሳይሆን፣ ለራሳቸው ለልሂቃኑ የዘረፋ መንገድ ለማመቻቸት የተቧደኑ ሰፍሳፋዎች መሆናቸውን ተገንዝቦ፣ ለዴሞክራሲ ለፍትህና ለሀገራዊ እድገት ህብረብሄራዊ ትግል ብችኛው አማራጭ ነዉ ብሎ መታገሉ ሊያስመሰግነው የሚገባ እንጂ የሚያስወቅሰው መሆን አልነበረበትም።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 

ትዊተር ፡ @zborkena

ፌስቡክ ፡ Borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here