spot_img
Wednesday, November 29, 2023
Homeአበይት ዜና"መርህና ሕግ ያልተከተለው የብልፅግና መንግስትና የትህነግ/ወያኔ ግንኙነት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል" ልሳነ ግፉዓን...

“መርህና ሕግ ያልተከተለው የብልፅግና መንግስትና የትህነግ/ወያኔ ግንኙነት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል” ልሳነ ግፉዓን ድርጅት 

advertisement

ቦርከና

ልሳነ ግፉአን ድርጂት ዛሬ ባወጣው መግለጫ መርህ እና ህግ ያልተከተለ ነው ያለውን የአብይ እህመድ ብልጽግና መንግስት እና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ግ ንኙነት ባስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ድርጂቱ በመግለጫው ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት አንድ ባንድ እየጣሰ መሆኑን ፤ ከባድ መሳሪዎችን ሙሉ በሙሉ አለማስረከቡን እና ለአራተኛ ዙር ጦርነት ዝግጂት እያደረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

“የፌደራል መንግስቱ ለትህነግ/ወያኔ ያለውንና ይዞት የቆየውን የተሳሳተ አረዳድና ግምገማ ዛሬም እንደተጠበቅ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።” ሲል አስታውቋል፡፡

የድርጂቱ ሙሉ መግለጫ ከታች እንደሚከተለው ቀርቧል ( በ ፒ ዲ ኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)

መርህና ሕግ ያልተከተለው የብልፅግና መንግስትና የትህነግ/ወያኔ ግንኙነት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል! 

“ነገርን ከስሩ፣ ውሃን ከጥሩ” እንዲሉ የብልፅግና መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ከመጋቢት 24 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ድረስ “ትህነግ/ወያኔ ወደ ጦርነት አይገባም” ፣ “በሀገርና በህዝብ ላይ ወረራ አይፈፅምም” ወዘተ የሚል ግምገማና ስሌት እነደነበረው በግልፅ ይናገር ነበር። ከዚህ የተሳሳተ ግምገማና የመረጃ ትንተና በመነሳት ይመስላል ህዝብንና ሀገርን ለከፋ ጥቃትና አደጋ ያጋለጠ ጥፋት ተፈፅሟል። 

በአንፃሩ ደግሞ የአማራ ክልላዊ መንግስትን በወቅቱ ይመሩ የነበሩት መሪዎች ትህነግ/ወያኔ አማራ ክልልን በጦር ሃይል ለመመውረርና ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገና ምሽግ ቁፋሮ ላይ እንደተጠመደ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፌደራል መንግስቱ በይፋ ይገልፁና ያስጠነቅቁ ነበር።  

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ትህነግ/ወያኔ ከ 2 ዓመታት በላይ ያደረገውን ያልተቋረጠና ይህ ቀረው የማይባልለት የወረራ ዝግጅት የሰሜን ዕዝ አባላትን በተኙበት በመጨፋጨፍ ጉዞውን የጀመረ ሲሆን፤ ጎንደር ደሴና አፋር ላይ ቁርስ፣ ባህርዳር ላይ ምሳ፣ እራት 4 ኪሎ ለመብላት የቆረጠ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ከአንድ ቀን በፊት በአውሮፕላን አዲስ የተቀየረውን የገንዝብ ኖት በገፍ ወደ መቀሌ ያጓጉዝ ነበር። 

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከ80% በላይ የጦር ክምችቷ በወያኔ እጅ በወደቀበትና የመከላከያ ሰራዊታችን በግፍ በተጨፈጨፈበትና ከፊሉ የሰሜን ዕዝ ጦር በከበባ ውስጥ በሚገኝበት ወቅት የፋሽስቱ የጥፋት ወረራና ግስጋሴ የተገታውና ከከበባ ነፃ የወጣው የአማራ ክልላዊ መንግስት መሪዎች በሰጡት ቆራጥ አመራርና የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሺያና፣ ፋኖ ባደረጉት የተቀናጀ ተጋድሎና ክቡር መስዋዕትነት ነው። የሚያሳዝነውና የሚያስቆጨው ነገር ትህነግ/ወያኔ በከፈተው የ 3 ዙር ጦርነት ሰላም ወዳዱ ህዝባችንና ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪካችን አይተነው የማናውቀውን አይነት መራር የመከራ ፅዋ፣ መስዋዕትነትና፣ ውድመት ተጎንጭተናል። 

ትህነግ/ወያኔ በእብሪት በከፈተው የመጀመሪያው ዙር ጦርነት የተገኘውን ታሪካዊና አንፀባራቂ ድል ማስጠበቅና ቀጣይ ዙር ጦርነቶችን ማስቀረት ያልተቻለው በፌደራል መንግስቱ የተሳሳተ ግምገማና ትንተና መሆኑን ለመረዳት “እንደ ዱቄት ተበትነዋል” የሚለውን አይረሴ የጠ/ሚ አብይን የፓርላማ ንግግር ብቻ ማስታወስ በቂ ነው። 

በዱቄት የተመሰለው ትህነግ/ወያኔ ከተበተነበት ተሰባስቦ የተረፈውን የመከላከያ ሰራዊት ደም ዳግም እንዲጠጣ፣ መቀሌን በጀግና አቀባበል እንዲረከብና ዛሬም ድረስ የሚመፃደቅበት ትጥቅና ስንቅ እንዲበረከትለት ያበቃው፤ አንድም በፌደራል መንግስቱ የተሳሳተ ስሌትና ቀመር የአማራን ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና፣ ፋኖ ወደ ትግራይ እንዳይገቡ በመደረጋቸውና መከላከያ ሰራዊታችን ከደጀኑ ሃይልና ህዝብ ተነጥሎ እንዲመታ ባስቻለ ታሪካዊ የአመራር ስህተት ጭምር ነበር። 

ትህነግ/ወያኔ በ 2ኛው ዙር ጦርነት በአፋር፣ በወሎ፣ በጎንደርና፣ በሸዋ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋና ውድመት ከወራሪው ሃይል ጥንካሬና ጀግንነት የመነጨ እንዳልሆነ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ፋሽስቱ ቡድን ደብረ ሲና እስኪደርስ ድረስ የመጣበት የጥፋት መንገድና 4 ኪሎ አፋፍ ላይ የተገታበት መንገድ እስከዛሬ ድረስ ለሁላችንም እንቆቅልሽ ነው። 

ከዚህ በላይ ለማሳያ ያህል ያነሳናቸው ቁም ነገሮች የጠ/ሚ አብይን መንግስትን ለማሳጣት ወይም የተደረጉትን መልካም ነገሮች ጥላሸት ለመቀባት ሳይሆን በመንግስት በኩል ለትህነግ/ወያኔ ያለውን ስስ ልብና የተያዘውን የተሳሳተ አረዳድና ግምገማ ለማሳየት ብቻ ነው። 

የፌደራል መንግስቱ ለትህነግ/ወያኔ ያለውንና ይዞት የቆየውን የተሳሳተ አረዳድና ግምገማ ዛሬም እንደተጠበቅ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆች ክቡር መስዋዕትነት የተንበረከከውና እጅ የሰጠው ፋሽስት ወያኔ ተገዶ ከፈረመው የጥቅምት 23ቱ የፕሪቶሪያው ስምምነት ውጭ በሆነ መንገድ እየተስተናገደ የሚገኘበት መንገድ እንዱና ዋነኛው ነው። በተለይም፦

1ኛ. ትህነግ/ወያኔ ፕሪቶሪያ ላይ ከፈረመው ባለ 15 አንቀፅ ሰነድ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታና ተዋጊዎቹን በሙሉ ወደ ተሃድሶ/ማሰልጠኛ ካምፕ እንደሚገቡ አንቀፅ 6 “Disarmament, Demobilization, and Reintegration (DDR)” የሚለው ክፍል በግልፅ ያትታል። ይህን ወሳኝ የሰላም ስምምነት ተከታትሎ የማስፈፀም ሙሉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የፌደራል መንግስቱና ሽማግሌዎች ያቋቋሙት ታዛቢ ቡድን ነው። ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ትህነግ/ወያኔ ለይስሙላ በሽማግሌ/ታዛቢ ቡድኑ ፊት ካስረከባቸው 3% የማይሞሉ ከባድ መሳሪያዎች በስተቀር ከ97% በላይ የሚሆኑት አሁንም በፋሽስቱ እጅ ናቸው። ይህም ትህነግ/ወያኔ በህዝባችን ላይ ተጨማሪ አደጋ እንዳይጥልና ለዳግም ወረራና እልቂት እንዳንዳረግ ስጋት አድሮብናል።  

2ኛ. የፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀፅ 10 “Transitional Measures” በሚለው ክፍል ስር በትግራይ አዲስ የሽግግር አስተዳደር ይቋቋማል ይላል። በሚቋቋመውም አስተዳደር ውስጥ የትህነግ/ወያኔ ድርሻ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሳተፍ ብቻ ነው። ነገር ግን የፌደራል መንግስቱ በሚከተለው የተሳሳተ መርህና እየወሰደ ባለው ህገወጥ አካሄድ ምክንያት ህገወጡና ወንጀለኛው ትህነግ/ወያኔ የትግራይን ጊዚያዊ የሽግግር መተዳደሪያ ሰነድ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብና አስተዳደሩንም እንዳሻው በብቸኝነት እንዲያዋቅር እየተደረገ ይገኛል። 

ይህ መርህ አልባና ህገወጥ አካሄድ ትህነግ/ወያኔ ከፍጥረቱ ጀምሮ የያዘውን የአማራ መሬቶችን በሃይል የመውረር፣ የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ የማጥፋትና፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የመበታተን አላማና እቅድ ዳግም በሽግግር ሰነዱ ውስጥ እንዲያካትት አስችሎታል። ይህንንም ህገ-ወጥ ሰነድ የጥፋት አጀንዳውን የትግራይ ህዝብ መመሪያና አቋም አድርጎ ለዳግም ጥፋትና እልቂት በማዘጋጃት ለመቀስቀሻነት እያዋለው ይገኛል። 

ለአብነትም ያህል የትግራይ መከላከያ ሃይል /TDF/ የሚባለውን ወንጀለኛ ቡድን እየመራ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት አባላት በውድቅት ሌሊት ያሳረደውና ኢትዮጵያን በ 3 ዙር ጦርነቶች የወጋው ታደሰ ወረደ የጦርነት ቅስቀሳውን እንዲያጧጡፍና ዳግም በህዝባችን ላይ ስጋት እንዲፈጥር አስችሎታል።  

3ኛ. የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትግራይን ተረክቦ ሰላም እንዲያስከብርና ከሁሉም የተወጣጣ የአካባቢ ሚሊሻና የክልል ፖሊስ እንደሚዋቀር በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀፅ 7 /Confidence-building measures/ ላይ በግልፅ ተደንግጓል። ይሁንና ከስምምነት ውጭ በሆነና ምክንያቱ ለህዝብ ባልተገለጠበት ሁኔታ በአሁኑ ሰአት ትግራይ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ለትህነግ/ወያኔ አስረክቦ በከፍተኛ ቁጥር ከትግራይ እየወጣ ይገኛል። የሚወጣውንም ሰራዊት ከባድ መሳሪያዎቹን ትግራይ ውስጥ እየተውና ተተኪ ሌላ ሃይል ወደ ትግራይ ባልገባበት ሁኔታ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። 

እነዚህ በፌደራል መንግስቱ የሚወስዱ የተሳሳቱና ከህግ አግባብ ውጭ የሆኑ ተግባራት ህዝባችንና ሀገራችን እጅግ ውድ ዋጋ አስከፈለዋል። አሁንም የትግራይ ክልልን ለትህነግ/ወያኔ መሪዎችና ጭፍራዎች አስረክቦ መውጣት ለ 4ኛ ዙር ጦርነት እንዲዘጋጁና እንዲበረታቱ የሚያመቻችና መንገድ የሚጠርግ ታሪካዊ ስህተት ነው ብለን እናምናል። 

4ኛ. አሁንም በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀፅ 7 /Confidence-building measures/ መሰረት በትህነግ/ወያኔ ወረራ ምክንያት በፌደራል መንግስቱ ጥሪ ወደ ትግራይ ክልል ገበቶ የነበረውና ኢትዮጵያ ዳግም ለጥቃት እንዳትጋለጥ ወሳኝ ሚና የነበረው የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ፣ እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች የተወጣጣው የሰላም አስከባሪ ሃይል ሙሉ በሙሉ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ ይታወቃል። 

ይሁን እንጂ ትህነግ/ወያኔ በወረራ የያዛቸውን የአማራ መሬቶች ካለመልቀቁም በተጨማሪ ዳግም የአማራና የአፋር መሬቶች ለመውረር ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገና ግልፅ ወታደራዊ ትንኮሳዎችን እየፈፀመ በሚገኝበት በአሁኑ ሰአት መንግስት ምንም አይነት የእርምት እርምጃዎች እየወሰደ አይደለም። ይህም ቀደም ሲል የጠላትን ሃይል አንኳሶ በመመልከት በተደጋጋሚ እንደ ተፈፀሙት ስህተቶች ሁሉ ህዝባችን ለዳግም ጥፋት የሚያጋልጥ ታሪካዊ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል። ስለሆነም፦

1. ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት 

በአሁኑ ሰአት የጠ/ሚ አብይ መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ባከበረ ሁኔታ የትግራይ ህዝብና ክልሉ ከፌደራል መንግስቱ ማግኘት የሚገባቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶችና ጥቅማ ጥቅሞች በተሳለጠ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝ ግልፅ ነው። 

ይሁን እንጂ የትህነግ/ወያኔን የሽብር አላማና ተግባር በሚያመክን መልኩና የኢትዮጵያንና ይህዝቧን ደህንነትና ሰላም በዘላቂነት በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲከወኑ የተደረሰባቸው ስምምነቶች ወደ ጎን እየተገፉና እየተጣሱ መሆናቸው በግልፅ ይታያል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጥቅምት 23/ 2015 ዓ.ም ፕሪቶሪያ ላይ በፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ ህዝብና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተጣለበትን ህግን የመጠበቅና የማስጠበቅ መንግስታዊ ሃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣና ከላይ በዝርዝ ያቀረብናቸውን ግልፅ ግድፈቶቹን እንዲያረም አበክረን እንጠይቃልን! 

2. ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ 

ትህነግ/ወያኔ የተንበረከከውና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የፈረመው የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት ተነስተው ለሀገራቸውና ለወገናቸው ሲሉ ባፈሰሱት ክቡር ደማቸውና በገበሩት ውድ ህይወታቸው መሆኑን ልሳነ ግፉዓን በፅኑ ያምናል።  

ነገር ግን በዝርዝር ከላይ እንደ ገለፅነው የጠ/ሚ አብይ መንግስት ከመርህና ከህግ ባፈነገጠ ሁኔታ ፋሽስቱ ትህነግ/ወያኔ ዳግም ከሞት እንዲያንሰራራና የጦርና የፖለቲካ ሃይል እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑ በግልፅ ይታያል። ይህ የመንግስት መርህ አልባና ህገወጥ አካሄድ ከጅምሩ ማስቆም ካልተቻለና ከወዲሁ መልክ እንዲይዝ ካልተደረገ በስተቀር ሀገራችንና ህዝባችን ዳግመኛ ለማይቀረው የትህነግ/ወያኔ የእብደት ወረራና የሽብር ጥቃት መጋለጣቸው አይቀሬ ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የውድ ልጆቹ ክቡር መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይቀርና በአሁኑ ሰአት በእጃችን የገባው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዳይደፈርስ መንግስትን በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊያሳስብና ሊጠይቅ ይገባል ብለን እናምናለን። 

3. ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 

በትህነግ/ወያኔ ፋሽስታዊ እርምጃ ግንባር ቀደም ተጠቂና ገፈት ቀማሽ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መሆኑን ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። ይልቁንም ለዚህ ሁሉ ሰቆቃና መከራ የተዳረጋችሁት በማን ስህተትና በምን ምክንያት መሆኑን እናንተው ታውቃላችሁ። በውድቅት ለሊት በተጠቃችሁም ግዜ ከጎናችሁ ሆኖ ውድ የህይወት መስዋዕትነት የከፈለውና ደጀን የሆናችሁ የአማራ፣ የአፋርና ቀሪው ኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ወንድም የሆነው የኤርትራ ህዝብና ሰራዊት መሆኑን ማስታወስ የግድ ይላል። 

በአንፃሩ ደግሞ ጠላት የሆኑትን የትህነግ/ወያኔ መሪዎችና ወራሪ ሃይል ከአንድም ሶስት ጊዜ ከታሪካዊ ሞታቸው እየታደገና እንደ እባብ አፈር ልሰው እንዲነሱ ያደረገው የመንግስት የተሳሳተ ስሌትና ግምገማ መሆኑ ከእናንተ በላይ የሚያውቅ ይኖራል ብለን አናስብም። ዛሬም የፕሪቶሪያው ስምምነት በጣሰ ሁኔታና ለጠላት ዳግም ማንሰራራትና መደራጀት እድል በሚፈጥር ሁኔታ የትግራይ ክልል ለማን እንዳስረከባችሁ እንኳ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ለቃችሁ እየወጣችሁ መሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል። 

በተለይ መንግስት ከመርህና ከህግ አግባብ ውጭ ሀገርንና ህዝብን በሚጎዳ ተደጋጋሚ ስህተት ውስጥ ሲዘፈቅና ሀገርና ህዝብ በተደጋጋሚ ለጠላት ጥቃት ሲጋለጡ ህዝባዊና ህገ-መንግስታዊ ሀላፊነትን መወጣትና ሀገርንና ህዝብን ማዳን ከማንም በላይ የመለዮ ለባሹ ነው ብልን እናምናለን። ስለሆነም በአንድ ወቅት ጠ/ሚ አብይ “መለዮ ለባሹ የሀገርና የህዝብ ጠባቂ እነጂ የማንኛውም መንግስት ስልጣን ጠባቂ መሆን የለባችሁም” እንዳሉት ቅድሚያ ለህዝባችሁና ለእናት ሀገራችሁ ታማኝ እንድትሆኑ እየጠየቅን፤ ከፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ውጭ ትህነግ/ወያኔን ዳግም ለማዳን የሚደረገውን ህገወጥ ተግባርና ሀገርንና ህዝብን ለቀጣይ ዙር ወረራ የሚያጋልጠውን የመንግስት ያልተገራ አካሄድ እንዲስተካከል በማድረግ ከዳግም ጥፋት ሀገራችሁንና ህዝባችሁን ትታደጉት ዘንድ ወገናዊ ጥሪያችን እናቀርባለን።

4. የአማራ ክልላዊ መንግስትና ልዩ ሃይል 

የአማራ ክልላዊ መንግስት የትህነግ/ወያኔን የጦርነት ዝግጅትና ሀገርና ህዝብ ለመውረር ያነገበውን እኩይ አላማ ቀድሞ በመረዳትና ተመጣጣኝ ዝግጅት በማድረግ ሀገርን ከመፍረስና ህዝብን ከከፋ እልቂት ለመታደግ ላደረገው ብልህነት የተሞላበት አካሄድና በቁርጠኛነትና በጀግንነት ለሰጠው አመራር ከልብ እናደንቃልን። 

ዛሬ የምንገኝበት አንፃራዊ ሰላምና ድል የተገኘው የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና መላው ህዝባችን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመንቀሳቀስ በከፈለው የላቀ መስዋዕትነትና በፈፀመው ወደር የለሽ ጀግንነት መሆኑ እሙን ነው። በዚህም እኛ ብቻ ሳንሆን መጭው ትውልድ ጭምር የሚኮሩበትና በክብር የሚዘክረው እንደሚሆን ጥርጥር የለንም። 

ይሁን እንጂ ወራሪውና ፋሽስቱ ትህነግ/ወያኔ በከፈተብን 3 ዙር ጦርነቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊና ንፁሃን ወገኖቻችን አማራ በመሆናቸው ብቻ በማይካድራ፣ በጭና፣ በኮምቦልቻና፣ በሰሜን ሸዋ በግፍ ተጨፍጭፈዋል። እናቶቻችን፣ እህቶቻችና፣ ሴት ልጆቻችን በአደባባይ ተደፍረዋል። ወጣቶችና አዛውንቶች በጀምላ ተረሽነዋል። አቅመ ደካሞች ህፃናትና እናቶች በረሃብና በችግር ረግፈዋል። ጀግኖቻችን ከወራሪ ጋር አንገት ላንገት ተናንቀው ወድቀዋል። የቤት እንስሳት ሳይቀሩ በቁማቸው ስጋቸው ተበልቷል፥ በጥይት ተደብድበዋል። ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ይህ ሁሉ ግፍና መከራ በህዝባችን ላይ የተፈፀመው የአማራ ህዝብ ወደ ትግራይ ሄዶ ሳይሆን ከትግራይ በመጣ ትህነግ/ወያኔ መራሽ ወራሪ ሃይል መሆኑ ነው። 

ትላንት በጀግኖች ልጆቻችን ክቡር መስዋዕትነትና አኩሪ ተጋድሎ ከሞት አፋፍ ላይ “በሰላም ስምምነት” ስም የዳነው ትህነግ/ወያኔ ነብስ ዘርቶ ለዳግም ወረራና ጦርነት እየተዘጋጀና ከበሮ እየደለቀ እንደሚገኝ ከአማራ ክልላዊ መንግስትና ከክልሉ የሰለምና የፀጥታ መዋቅር እይታ የተሰወረ አይደለም ብለን እናምናልን። በተለይም ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጭ ትህነግ፦ 

1. በወሎና በማይጠምሪ በኩል ዛሬም ድረስ የአማራን መሬቶች በወረራ ይዞ እንደሚገኝ እየታወቀ፣ 2. ትጥቁን ሳይፈታ፣ ከባድ መሳሪያወቹን ለፌደራል መንግስት ሳያስረክብና፣ ተዋጊዎቹን ወደ ተሃድሶ ካምፕ ሳያስገባ እንደሚገኝ በግልፅ እየታየ፣ 

3. ህገወጡን የትግራይ ክልል ምክር ቤት ሳያፈርስና ከሁሉም አካላት የተወጣጣ ጊዚያዊ የሽግግር አስተዳደር ሳይቋቋምና፣ 4. ዳግም አዳዲስ ወታደር እያሰለጠነና ነባር ተዋጊዎቹን ወደ ህዝቡ በፖሊስና በሚሊሻ ስም እየቀላቀለ ባለበት ሁኔታ፣ 5. ይለቁንም ዳግም የአማራ ክልልና ህዝብን ለመውረርና የኤርትራን ህዝብና መንግስት ለመውጋት በትግራይ ክልል ሚዲያዎች ህዝብ እየቀሰቀሰና ሽብር እየነዛ በሚገኝበት ሁኔታ፣  

በአጠቃላይ ህዝባችን ለትህነግ/ወያኔ 4ኛ ዙር ወረራና ጥቃት በተጋለጠበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለማን አስረክቦ እንደሚወጣና በምን ሁኔታ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሶ ትህነግ/ወያኔ ዳግም እንዲያንሰራራና ለህዝባችንና ለሀገራችን ስጋት እንዲሆን እድል እንደተሰጠው ግልፅ አልሆነልንም። ለዚህም የክልሉ መንግስት ግልፅነትና ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ለአማራ ህዝብ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃልን። 

በተጨማሪም የአማራ ክልላዊ መንግስትና የክልሉ የሰላምና የፀጥታ መዋቅር እንደዚህ ቀደሙ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ በመውሰድ ህዝባችንን ከማንኛውም ጥቃትና ወረራ እንዲታደግ አበክረን እየጠየቅን፤ የክልሉ መንግስት በሚወስዳቸው ማንኛውም የመከላከል እርምጃዎች ሁሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከጎኑ መሆናችንን ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በድጋሚ ያረጋግጣል። 

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በክብር ትኑር!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት 
የካቲት 17/ 2015 ዓ.ም “

_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here