spot_img
Wednesday, November 29, 2023
Homeነፃ አስተያየትከታሪከ ባይተዋርነት ወደ ነጣቂነት፡አድዋን እንደማሳያ (ደረጀ ይመር)

ከታሪከ ባይተዋርነት ወደ ነጣቂነት፡አድዋን እንደማሳያ (ደረጀ ይመር)

advertisement
Ethiopian _ Adwa _

ደረጀ ይመር

የዘውጌ ብሔርተኞች እንደ አደዋ ያለ በሀገራዊ ቀለም የተነከረ እንጸባራቂ ድል፣ ከቻሉ አዛብቶ የድሉን ረብየለሽነት መተረክ አልያም ድሉን በእነርሱ ዘውግ ማእቀፍ በመቀንበብ፣በጠራራ ፀሐይ ታሪክን ሲዘርፉ ልንመለከት እንችላለን፡፡

በተክለጻዲቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት ድርሳን ላይ አድዋን በሚመለከት ይህ ጉሩም የሆነ አገላለጽ ሰፍሮ ይገኛል፤ “ከ 2 ሺህ ዓመት በፊት ሐኒባል በሮማውያን ካገኘው ድል ወዲህ ያንጸባረቀው የአድዋ ድል አፍሪቃ በአውሮጳ ላይ እንዳገኘው ታላቅ ድል ይቆጠራል፡፡ 

በርግጥም ይህ ድል የአፍሪቃን የፓለቲካ-ሥነምህዳርን በመቀየሩ ረገድ የሚስተካከለው ምድራዊ ኃይል የለም ቢባል እውነታውን ማበል አይሆንም፡፡አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ለመቀራመት የቋመጡ  የፀጉረ ልውጥ ኃይሎችን ቅስም የሰበረ፣የእብሪት ሥነልቦናቸውን የእምቧይ ካብ ያደረገ፣ ዝንተዓለም ቢወሳ የማይጠገብ አኩሪ ገድል ነው፡፡ የድሉ አድማስ ዓለምአቀፋዊ ሲሆን በባሪያ ፈንጋይ ሥርዓት ካረቢያን እና ሰሜን አሜሪካ የሠፈሩትን፣የዘር ግንዳቸው ከአፍሪቃ የሚመዘዙ የነጻነት ታጋዮችን በራስ የመተማመን መንፈስ ሽቅብ እንዲመነደግ ምክንያት ሆኗል፡፡ ፕሮፌሰር ክንፈ አብርሃም የአድዋ ድል ለጥቁሮች የነበረውን አብርክቶት እንደሚከተለው  ከተበውታል፤“ታዋቂው የጥቁር ብሔርተኝነት አቀንቃኝ ማርቆስ ጋርቬይ በ 1914 በጀማይካ እና በ 1917 ደግሞ በሃረለም(ኒውዮርክ) ለፍሬ ባበቃው የነጻነት እንቅስቃሴ ላይ ያነገበው አንድ ዓለም፣አንድ አምላክ እና አንድ ፍጻሜ መሠረት ያደረገው የአድዋ አይነትን የተጋድሎን ነበር፡፡” The prominent black nationalists Marcus Garvey stated his Afro-centric Black to African movement in 1914 in Jamaica and in 1917 in Harlem (New York)his motto of “one aim, one God & one destiny” for all blacks referred to an Adowa type of African liberation and the establishment of black supremacy. 

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ገና ወገቧ ባልጠናበት በዛ ፈታኝ ወቅት፣ ከደጃፏ አሰፍስፎ የሚጠብቃትን ነጭ ጣውንት ላይ መጀገን ባትችል ኖሮ አሁን የታቀፈቻቸው መልካም እሴቶች፣ባህሎች እና ቋንቋዎች ተረት ሆነው በቀሩ ነበር፡፡ የሀገራችንም የቆዳ ሥፋት ሃያ ቦታ ተሸንሽኖ፣አንድ ብሔር ምንአልባትም ሶሰት እና አራት ጥቃቅን ሀገር ውስጥ ይበታተን ነበር፡፡ይህንንም ዋቢ ምሰክር ለማድረግ ጣሊያን ዳግም ለወረራ በመጣበት ጊዜ ያዘጋጀውን እጅ እግር የሌለው ካርታን መመልከት በቂ ይሆናል፡፡ምንአልባትም ጣሊያን አድዋ ላይ ድል ቀንቶት ቢሆን ኖሮ ለአቅመ ሀገር ያልደረሱ ኩርማን ሀገሮች ለዐይነ ሥጋ ይበቁ እንደነበር ሌሎች ቅኝ የተገዙትን ሕዝቦች ታሪካዊ ዳራ መለስ ብሎ መቃኘት በቂ ይሆናል፡፡

በወቅቱ የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ሉአላዊ ሀገርነት አውሮጳዊያን እየተፈታተናቸውም ቢሆን እንዲቀበሉ አስገድዷቸዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ሀገራችን የነበራትን የመደራደር አቅምን በእጅጉ በማጎልበት፣የወራሪዋን ኢጣሊያ የውጫሌን  ስምምነትን የሚሽር በ1889 ዓ.ም የአዲስ አበባን ውልን ለመፈራም በቅታለች፡፡ በውሉ መሠረት ኢትዮጵያ የማንም ጥገኛ ያልሆነች አገር መሆኗን የኢጣሊያ መንግሥት ለመቀበል ተገዷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ምርኮኞችን ለመቀለብ ያወጣውን ወጪ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሊሬ ኢጣሊያ እንድትከፍል ተደርጎ ከጦርነቱ በኋለ ወደ ሀገራቸው ለመግባት ችለዋል፡፡ እዚህ ጋር አጼ ምኒልክ የተገኘውን ድል ለተጨማሪ ፋይዳ ማዋል ሲገባቸው ጣሊያን ባቀረበላቸው መጠነኛ ነዋይ ተዘናግተው ነበር፡፡ የታሪክ ሊቃውንትም ቢሆኑ ይህንን የአጼ ምኒልክ ተላላ ዲፕሎማሲ እንደ ትልቅ ድክመት ይወስዱታል፡፡ በምርኮ የታያዙትን ወታደሮች እንደ መደራደሪያ በመጠቀም አጼው ከጣሊያን ጋር የፈጸሙትን የ1890 ዓ.ም የድንበር ስምምነትን የበለጠ የኢትዮጵያን ጥቅም ባሰከበረ መልኩ መዋዋል ይችሉ ነበር፡፡ 

የዘውግ ድርጅቶች ንጥቂያ

በጠባብ ዘውግ የተሰባሰቡት የፓለቲካ ኃይሎች መነሻቸው ጭቆና ነው፡፡እነዚህ ኃይሎች ወደኋላ ተጉዘው ሕዝባቸውን የሐዘን  እንጉርጉሮ ውስጥ መክተት ይቀናቸዋል፡፡ሁሉም በዘላለማዊ ጠላትነት የሚፈርጁት ጣውንት  ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለምንዝላታዊ መሳሳብ(Primordial Connection) የሚሰጡት ቦታ የላቀ ነው፡፡ ወደ ድርጅቶቹ በአባልነት የሚታቀፉ ግለሰቦች የደም ጥራት ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም፡፡

አጥንት ቆጠራን ወደ ጎን የሚገፋ የዘውግ ድርጅት በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ተከስቶ አያውቅም፡፡ የዘውግ ድርጅቶች እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ እንደ የግል ርስታቸው ነው የሚቆጥሩት፡፡ሌላ ሐሳብን መሠረት አድርጎ የተሰባሰበ የፓለቲካ ኃይል ድንገት በምህዳሩ ላይ ቢከሰት ርስታቸውን ሊቀናቀን እንደመጣ ጣውንት ስለሚቆጥሩት በምክንያት ከመሟገት ይልቅ ታፔላ መለጥፍ ይቀናቸዋል፡፡ የታሪክ እሳቤያቸውም የሚቀዳው ከእነዚህ መሠረታዊ ባሕሪያት ነው፡፡ 

እነዚህ ጠባብ ኃይሎች የሕዝቦችን የኋላ የታሪክ ትስስርን በመበጣጠስ የልዩነት ገዳምን ቀልሰው የሚወክሉትን ሕዝብ የተበስልሳይ ቅርቃር ውስጥ ይጨምሩታል፡፡ እንደ አደዋ ያለ ከዘውግ ማእቀፍ የተሻገረ አኩሪ የኋላ ገድል በዘውጌ ፓለቲካ መነጽር ሌላ መልክን እና ጠባይን እንዲላበስ ነው የሚደረገው፡፡ትናንት የሀገራችን ሕዝቦች በዘውግ ዘለል/meta-ethinc/ መሰተጋብር በአንድነት የተጓዙበትን የድል ሐዲድን በመስበር፣ ታሪክን እንደ አዲስ ለመከተብ ውሽልሽል ብዕራቸውን ያነሳሉ፡፡ 

የዘውጌ ብሔርተኞች እንደ አደዋ ያለ በሀገራዊ ቀለም የተነከረ እንጸባራቂ ድል ከቻሉ አዛብቶ የድሉን ረብየለሽነት መተረክ አልያም ድሉን በእነርሱ ዘውግ ማእቀፍ በመቀንበብ በጠራራ ፀሐይ ታሪክን ሲዘርፉ ልንመለከት እንችላለን፡፡ በዚህ ረገድ የሕወሓት እና ኦነግ ሊኂቃን ተጠቃሽ መሆን ይችላሉ፡፡ ከለውጡ በኋላ ያቆጠቆጠው የኦሮሞ ብሔርተኞች የታሪክ እይታ ሁለት እርክኖችን አልፏል፡፡ በቲም-ለማ ዙሪያ የተሰባሰበው የብሔር ልሂቃን ከሞላ ጎደል ሚዛናዊ የታሪክ እሳቤን ያቀነቅን ነበር፡፡ ይህ ኃይል ግን ብዙም ርቀት ሳይጓዝ ነበር የተሰነካከለው፡፡ በቲም ለማ ፍርስራሽ ላይ የበቀለው አዲሱ የታሪክ እሳቤ በድሮው የኦነግ ትርክት ላይ መጠነኛ የኮስሞቲክ ለውጥ አድርጓል፡፡ ለመሆኑ አዲሱ የታሪክ እሳቤ ምንድን ነው?

ከተብስልሳይነት ወደ ነጣቂነት 

የቅኝ ግዛት ሐቲትን በማስተጋባት የሚታወቁት አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ለአድዋ ያልተገባ ምስል አላብሰውት እንደኖሩ ይታወቃል፡፡ኦሪት ኦነጎች አድዋ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተጫነውን የጭቆና ቀምበርን ለተጨማሪ መቶ አመታት ከማራዘም የዘለለ ፋይዳ የለውም፤ብለው ድሉን ያራኩስታል፡፡ በዚህም የተነሳ በኦነግ ካምፕ በአድዋ ጦርነት ፊት ለፊት ተሰለፍው በጀግንነት የተዋደቁትን ጀግና የኦሮሞ ተወላጆችን እንደ ካሀዲ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ባይተዋርነትን የሚሰብከው ታሪካዊ እሳቤ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችን በብርቱ ተጠናውቱቸው እንደኖረ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡ 

የአሁኑ የኦሮሞ ብልጽግና ከኦሪቱ ኦነግ በተሰወሰነ ደረጃ ብልጣብልጥ መንገድን ለመከትል ይሞክራል፡፡ ቅርንጫፍ ድርጅቱ ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ይተገብረው እንደነበረው ስልት ታሪክን አዛብቶ እና ከልሶ እንደ አዲስ መቀመር ተቀዳሚ አላማ አድርጎ የያዘው ይመስላል ፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአክሱም ሃውልት ለወላይት ምኑ ነው፡፡ ሲሉ ሥልጣኔውን ያለታሪኩ ከበቀሉበት የዘውጌ ማንነት ጋር በማቆራኝት በቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የሥነልቦና የበላይነትን ለመቀዳጀት ነበር፡፡ የኦሮሞ ብልጽግና ተልእኮ እና አለማም ከዚህ ብዙም ፈቀቅ ያለ አይደለም፡፡ 

 አዲሶቹ የታሪክ ነጣቂዎች ከሁሉም በላይ ትኩረትን የሚስቡት የአድዋን ጉልላት እቴጌ ጣይቱን እና አጼ ምኒልክን ዘር ቆጥረው ከታሪካዊው ዝክር ገሸሽ ለማድረግ እየሄዱበት ያለው ርቀት ነው፡፡ የድሉን አድማስ በዘመኑ ከፋፋይ የብሔር አሰላለፍ አንጻር ቀንብበው የፖለቲካ ትርፍን ለማጋበስ ደፋ ቀና ሲሉ መመልከት ግርምትን ያጭራል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሀገር ፍቅር ቴአትር በተዘጋጀው የመድረክ ተውኔት የድሉ  ፊታውራሪዎች ሆን ተብሎ መዘለላቸውን ስንታዘብ ከላይ የተሰነዘረውን ሂስ ውሃ እንዲያነሳ ያደርገዋል፡፡ እነዚህን የሴራ ዳናዎች አነፍነፍን የምንደርስበት መደምደሚያ አዲሶቹ የብሔር ልሂቃን የሚሄዱበት ጎዳና ከሕወሃት ጋር ምንም የማይለይ መሆኑን ነው፡፡  በርግጥ የአድዋ ጀግኖችን ስብህና ማዶ ለማዶ በምንፈራረጅበት በዘመናችን የብሔር ኮሮጆ መለኪያ መለየት እንችላለን ? በመልሱ ላይ  ለመጠበብ መሞከር በታሪክ ፊት በየዋህነት ያስፈርጃል፡፡

በአድዋ ላይ መሪ ተዋናይ የነበሩት የጦር አበጋዞች የዘር ጥራት ለፓለቲካ ትርፍ እንዳሻን አንስተን ለማራገብ የሚመች አይደለም፡፡እጅግ ከምናስበው በላይ እርስ በርስ የተጋመዱ ውህድ ማንነቶች የናኙበት ነበር፡፡ በምኒልክ መንግሥት ውስጥ ከከፍተኛ የጦር መሪ አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና አማካሪዎች ድረስ ባሉ የተለያዩ የሥልጣን  እርከኖች የታየው  ጎጥ ወይም ዘውግ ዘለል በአጭሩ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ከሁለት የብሑር ማንነት በላይ ያላቸውን እነ  ራስ መኮንን ወልደሚካኤል፣ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ድነግዴን እና ባልቻ አባነፍሶን ዋቢ አድርገን መጥቀስ እንችላለን፡፡

አድዋ ከጎጥ እና ከዘር በላይ የሄደ የሀገራዊ ትስስራችን ዋቢ ምስክር ነው፡፡የሀገራችን ሕዝቦች  የዘመኑ የዘውጌ ድርጅቶች እንደሚያቀነቅኑት እንደ ኩሬ ውሃ በአንድ ቦታ ረግተው አይደለም የኖሩት፡፡ታሪክ የራሱን ቦይ እየቀደደ በማያቋርጥ ኡደት ሲፈስ፣ ሕዝቦችም በዚህ ሒደት ውስጥ አንዱ አንዱን ሲወጥ፤እርስ በርስ በጋብቻ ሲተሳሰሩ፤ እንደ ሰርገኛ ጤፍ መለየት የማይቻሉ መሆናቸው ገሀድ እውነት ነው፡፡ እነዚህ እንደ መዳፋ ጣቶች መለያየት የማይችሉ ሕዝቦች ናቸው በአንድነት ተሰልፈው ዓለም የተደመመበትን የአድዋን ገድል የፈጸሙት፡፡ይህም ድል የሀገራችን ሕዝቦች በበቀሉበት የጎጥ ማእቀፍ ኪሳራ ለኢትዮጵያዊ አርበኝነት ዘብ እንዲቆሙ አስችሏቸዋል፡፡ የአንዳርጋቸው ጽጌ ነጻነትን የማይውቁ ነጻ አውጪዎች መጽሐፍ ለዚህ እማኝ ላድርግ፤

“በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ግዛቶች መሳፍንት እና ባላባቶች በየአካባቢ የበላይነትን ለማግኘት ሲሉ ያድርጓቸው የነበሩ የውስጥ ግጭቶች እና ጦርነቶች በምኒልክ አሸናፊነት አብቅተው፣ሁሉም በጋራ ባህር አቋርጦ የመጣን ጠላት ለመመከት በአንድነት የተሰለፉበት፣በጋራም ድልን የተቀዳጁበት ነው፡፡ ይህ የጋራ ድል በሀገር ውስጥ የነበረውን የክልል እና የጎጥ ስሜቶች በማዳከም፣መሳፍንቱ እና መኳንንቱ በጋራ ድል አድረጊነታቸው ከጎጥ እና ከጎሳ ስሜቶች በላይ ተሻግረው በኢትዮጵያዊ አርበኝነት እና ሀገረተኝነት ቀለም እንዲነከሩ ያደረገ ነበር፡፡“ይህ ገሀድ ታሪካዊ ሐቅ ከአክራሪ የኦሮሞ ልሂቃን ጉሮሮ አይወርድም፡፡

ምሠራቃዊያን በሁለት ገሃነሞች መካከል ገነት አለ፡፡ይላሉ፡፡ የገሀነሞቹ ጫፎች የሚወክሉት ጽንፈኝነትን ነው፡፡ በአንጸባራዊ የአድዋ ድል  እኔ የለሁበትም፤የዳር ተመልካች ነበርኩም፤ ሆነ  የእኔ ብቻ ታሪክ ነው፤የሚሉት ጽንፎች ሁለቱም የገሀነም ጫፍች ናቸው፡፡ አማካኙ፤ ገነቱ፤ ታሪክን በእውነተኛ ቁመቱ እና ወርዱ መቀበል ይሆናል፡፡   

የግርጌ ማሰታወሻ 

የዘውጌ ኃይሎች በታሪክ እና በቁስ ሰቀቀን እስከአንገታቸው ድረስ የተዋጡ ስለሆኑ በየትኛውም ትርክት በቀላሉ ሊጠረቁ አይችሉም፡፡ንጥቂያ ወይም ሽሚያ ውስጥ ይገባሉ፡፡ የትግራይ ብሔርተኞች የአክሱም ሥልጣኔን፣የአድዋን የድል ታሪክን የሌሎች ሕዝቦችን ባላሳተፈ መልኩ ተምኔታዊ በሆነ አውድ ውስጥ እውን ሆኖ እንዳለፈ ጥራዝነጠቃዊ የሆነ ትንታኔን ከመሰንዘር ቦዝነው አያውቁም፡፡ የመምህር ገ/ኪዳን ከታሪክ ሥነዘዴ የራቀውን ተረት ተረት እዚህ ጋር ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በዘውጌ መነጽር ታሪክን እየበደለን የማኅብረሰብን የወል ህሊና ለማነጽ መሞከር ተምኔታዊ ነው፡፡ በመሆኑም ታሪክ የፖለቲካ ደንገጡረነት ሊያከትም ይገባል፡፡ 

አዎ የታሪክ ባለጠጋዎች ነን፡፡ የታሪክ ባለጠጋነት በራሱ የሚፈጥረው ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖርም፡፡ ፋይዳው የሚለካው የዛሬው ትውልድ በሚሰጠው ቦታ ልክ ይሆናል፡፡ትናንት አብረን የፈጸምናቸውን ታላቅ ገድሎች ለነገ መልካምነት የሚኖራቸው ድርሻ ጉልህ ነው፡፡ትናንት እርስ በርሳችን የተቆራቆስንባቸው መናኛ ልዩነቶች መልሰው ለዐይነ ሥጋ እንዳይበቁ የዛሬ አስትውሎታችን ከምንም በላይ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡በጋራ ለምናዘግምባቸው የነገ እልፍ አእላፍ እርምጃዎች የኃይል ቋት የሚገኘው ከትናንት የታሪክ ገመናዎቻችን ነው፡፡ 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here