
(ከቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)
መግቢያ
የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ ከያዛቸው ቁምነገሮች መካከል አንደኛው ንጉሠ ነገሥቱ የመጣውን ጠላት የገለጹበት መንገድ ነው። በአጭሩ እንዲህ ይነበባል፡-
“… አሁንም አገርን የሚያጠፋ ሃይማኖትን የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷል እና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው እያለፈ ደግሞ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም … “
ይህ በብዙ የታሪክ ሊቃውንት ብዙ የተባለበት የክተት አዋጅ ለእኔ የሚከተሉትን ቁምነገሮች ይዟል። 1ኛ/ የመጣው ጠላት “አገርን የሚያጠፋ ሃይማኖትን የሚለውጥ ጠላት” መሆኑ፣ 2ኛ/ ይህንን ጠላት ለመዋጋት ደግሞ አገርንና ሃይማኖትን ከመውደድ በተጨማሪ “ለልጅህ ለሚስትህ ስትል” በምትለው ሐረግ ሰው ለቤተሰቡ ሲል መዋጋት እንዳለበት ያሳስባል። በጠቅላላው የኢትዮጵያ ታሪክም የምንገነዘው ጠላቶቻችን አገራችንን አጥፍተዋል፣ ሃይማኖታችንን ተዋግተዋል፣ ቤት-ቤተሰቦቻችንን ንደዋል፣ አፍርሰዋል። ዛሬስ? በ 2015 ዓ.ም?
መንግሥት በጣሊያን መንገድ
ወራሪው የጣሊያን ጦር የጥፋቱ ዒላማ አድርጎ የተነሣባቸው ነገሮች አገር፣ ሃይማኖትና ቤተሰብ ነገሩ። ሌሎች ጥፍቶች በሙሉ ቢዘረዘሩ ከነዚህ ከሦስቱ አይወጡም። በሚደንቅ ሁኔታ ዛሬም በሀገራችን ያሉት ኢትዮጵያዊ ቆዳ ያላቸው አድራረ ኢትዮዽያ በነዚህ በሦስት ጉዳቶች ላይ መዝመታቸውን ስንመለከት የታሪኩ ተመሳሳይነት ያስደንቀናል።
የብልጽግና መንግሥት ለማንም በማያሻማ ሁኔታ በነዚህ ሦስት ተቋማት ላይ ግልጽ ጦርነት ማወጁን በግልጽና በተግባር አሳይቶናል።
U. መፈንቅለ ሲኖዶስ
መንግሥት ቀደም ብለው ከመጡት ፀረ ሃይማኖት መንግሥታት በመማር የእምነት መሪዎችን ከመቀየር ሙሉ በሙሉ ተቋሙን ወደ መውረስ (መፈንቅለ ቅዱስ ሲኖዶስ) ተሸጋግሯል። ለረዥም ጊዜ በታቀደ ሁኔታ በተለይም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ቅርጿን፣ ዓላማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ታሪኳንና አንድነቷን ለመናድ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል። በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተወሰኑ ጳጳሳትን በመገንጠል 25 መነኮሳትን እንዲሾሙ አስደርገዋል። በመንግሥት ታጣቂ በመታገዝ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች በጉልበት ተወርሰዋል።
ይህ ሁሉ ወንጀል ሲፈጸም መላው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ኃዘን ሲመታ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ መሪነት ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም የእምነት ልዩነት ጉዳዩን በይፋ ሲቃወሙ እና አስፈላጊ ከሆነ ሕይወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን በዕንባ ጭምር መግለጽ ሲጀምሩ መንግሥት አንገቱን ለመድፋት መገደዱን፣ የችግሩ ጠንሳሸና ባለቤት በችግር ፈቺነት ራሱን ሲያቀርብ ተመልክተናል። በጣም ተወኔታዊነት የተለበስ የዕርቅ ውይይት በቴሌቪዥን ሲተላለፍም አየን። ጠ/ሚሩ ቅዱስ ፓትርያርኩን “የጠፉትን በጎች ይዤ መጣሁ” ሲሉ ሰማን። ቀኖና ጥሰው ከወጡት የቀድሞ ጳጳሳት ሁለቱ ሲመለሱ አንደኛው አለመመለሳቸውን፣ ሾምናቸው ያሏቸው መነኮሳትም የጠ/ሚሩንና የፍርድ ቤት ውሳኔን ተቃውመው በሕገ ወጥ መንገዳቸው መቀጠላቸውን አየን። ጠሚሩ ፊጸምኩት ያሉት እርቅ የስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ እንጂ ከልብ የተደረገ መመለስ አለመሆኑን በተግባር አየን። እነሆ መፈንቅለ ሲኖዶሱ አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ይህ ችግር ሳይቀረፍ ሌላ ችግር ፈንድቶ ወጣ። መፈንቅለ ቤተሰብ።
ለ. ቤተሰብ የማፍረስ ዘመቻ
የብልጽግና መንግሥት ከሚታወቅባቸው ተግባራትና በታሪክ ፊት ለዘወትርም ከሚነሳባቸው ተግባራት አንዱ በቤተሰብ ማፍረስ ላይ ያደረገው ትልቅ ዘመቻ ነው:: ለውጥ መጣ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በሚያሰልስ ሁኔታ የተለያዩ ብሔረሰቦች አባላት (በዋነኝነት የአማራው) ደም ያለ ገደብ ፈስሷል። የዘር ማጽዳት ተፈጽሟል፤ እየተፈጸመም ነው። አጼ ምኒልክ በአዋጃቸው “ለልጅህ ለሚስትህ ስትል” እንዳሉት ብልጽግናም ልጄን/ ልጆቼን፣ ሚስቴን/ ትዳሬን (ቤተሰቤን) ለሚል ሁሉ ብልጽግና ጠላት ሆኖ መጥቷል። ማንም ጠላት ለማድረግ አስቦ ሙሉ ለሙሉ ሊፈጽም ያልቻለውን ቤተሰብ የመበተን ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል። ቤት ያፈርሷል፤ ቤተሰብ ይንዳል። ሕዝብ እትዝብቱ ከተቀበረበት ቀዬው በጉልበት ተነቅሏል፡ እየተነቀለ ነው። ሀብቱ፣ ንብረቱ ወድሟል፣ ተዘርፏል። እየወደመ እየተዘረፈም ነው። “ቢይ ኩን አባ’ ቀባ” (ይህ ሀገር ባለቤት አለው) በሚል የምሥጢር ቃል ተጠቅልሎ ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆነ ሁሉ “ሀገርህ አይደለም፣ ቤትህ ንብረትህ አይደለም” ተብሎ ተዘምኖበታል:: ሕጻናት ልጆቹ በጅብ ተበልተዋል፣ ነፍሰ ጡር ሚስት በጥይት ተገድላለች፣ የተረፉት ወደማያውቁት “ሀገራቸው” ተባርረው በድንኳንና በሜዳ ተበትነው ቀርተዋል። ይህ ሁሉ ሳያንስ አድዋ ላይ መፈንቅለ በዓል ተጀምሯል።
ሐ . አድዋን መሥረቅና መቅበር
የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የዋለው የአድዋ በዓል በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነው። በዓሉን ለማክበር የወጡ ሰዎች በመንግሥታቸው የተገደሉበት፣ የተደበደቡበት፣ የተዋከቡበት፣ የተንገላቱበት አሳዛኝ ቀን ነው። ከበዓሉ ቀን አስቀድሞ የመንግሥት ጎምቱ ባለሥልጣናት የዘመቻውን መሪ አጼ ምኒልክን ከበዓሉ ለማውጣት መንቀሳቀስ ጀመሩ። የቲያትር ቤቶች ንጉሡና ንግሥቲቱ የሌሉበት ድራማ እንዲያዘጋጁ መታዘዛቸው ታወቀ:: ሚዲያዎች ይህንኑ በተግባር አውለውት ታየ። ሕዝብ አዘነ። ተቆጣ፡፡ መንግሥት የሕዝቡን የቍጣ ማዕበል ሲመለከት ታክቲኩን በመቀየር በዓሉን መከላከያ እንዲያከብረው ትዕዛዝ ሰጠ። መከላከያም ያለውን ሕዝባዊ ቅቡልነት በመጠቀም በዓሉን አዘጋጀ። በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ።
ዋናው በዓሉ በሚከበርበት በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ጠዋት የመንግሥት ባለሥልጣናት በሐውልቱ ሥር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠው ተመለሱ። ምዕመናን በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ የቅ/ጊዮርጊስንና የአድዋን በዓል ለማክበር ተሰበሰቡ፡፡ ከአደባባዩ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ በዓሉ ለመግባት የሞከሩ ወገኖች ተከለከሉ። የዳግማዊ አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ያለባቸው አልባሳትን የለበሱ እየተለዩ በፖሊስ ጥቃት ደረሰባቸው፡፡ ሌሎችም ላይ አስለቃሽ ጭስ ተተኮሰ፡፡ ሕዝብ ተተረማመሰ፣ ተረጋገጠ። ብዙ ሰው ራሱን ስቶ ወደቀ። ከፖሊስ የተተኮሰ ጥይት የሰው ሕይወት ቀጠፈ።
በቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሕዝቡ ላይ አስለቃሽ ጭስ በመተኮሱ ሕጻናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን፤ ምዕመናን፣ ካህናትና መነኮሳት ራሳቸውን እየተሳቱ ወደቁ። በአምቡላንሶች ወደ ሕክምና ተቋማት ተወሰዱ። ታቦተ ሕጉም በዓሉ ሳይፈጸም ወደ መንበሩ ተመለሰ። በዓሉም ተቋረጠ፡፡ ሕዝብም አለቀሰ።
ይህ ሁሉ ለምን?
የካቲት 23 ቀን በብልጽግና እና አክራሪ ጎሰኞችና ስትራቴጂስቶች የተያዘው ዘዴ ሕዝቡ ተረጋግቶ በዓሉን እንዳያከብር ማድረግና በዓሉን ከሕዝብ በዓልነት ወደ መንግሥት በዓልነት የመውሰድ “መፈንቅለ-በዓል” ነው። ምን ይጠቅመዋል የሚለውን በአጭሩ ላቅርብ።
አድዋ ሕዝባዊ፣ ሀገራዊ/ ዓለምአቀፋዊ እና በተወሰነ ደረጃም ሃይማኖታዊ በዓል ወደ መሆን ያደገ በዓል ነው። ሕዝባዊ ነው ማለት ያለ ምንም አስገዳጅነት፣ ያለ ማንም አስተባባሪነት እና መሪነት በሕዝብ ፈቃድና በሕዝብ ገንዘብና ጉልበት፣ ኃይልና ጥበብ የሚከበር በዓል በመሆኑ ነው። በዓሉ በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች ስለሚከበር ሀገራዊ ነው። በመላው ዓለም እንደ አድዋ ለመከበር ዕድል ያገኘ ኢትዮጵያዊ በዓል የለም። በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ባሉ ከተሞች ይፋዊ ሆኖ እንዲከበር ዕውቅና ያገኘ በዓልም ነው። ከዚህም በላይ ድሉ የተገኘው በእግዚአብሔር ቸርነት በሰማዕቱ በቅ/ጊዮርጊስ አማላጅነትና ተራዳዒነት ነው ብላ የምታምነው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመናገሻ ገነት ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ታቦተ ሕጉን አውጥታ በታላቅ ሁኔታ ታከብረዋለች:: ታዲያ መንግሥት እነዚህን ሁሉ አከባበሮች በመደምሰስ የግሉ በዓል ለማድረግ ኩ’ዴታ/coup d’etat ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ተይዟል:: ግን ለምን ኩ’ዴታ አስፈለገ?
ብልጽግና እና ሌሎች አክራሪ ብሔረተኞች የተቸገሩት ነገር ሕዝብ የኢትዮጵያ ማማ እና ካስማ መሆኑን ለማስቀረት ለማስቀየር አለመቻላቸው ነው። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን ላይ ከ30 ዓመታት በላይ መንግሥታዊ የጥላቻ ዘመቻ ተካሂዶበታል፡፡ በዘመነ ወያኔ የነበረው ሰንደቅን የመጥላት ዘመቻ በዘመነ ብልጽግና በመሣሪያ በታገዘ ሁኔታ መንግሥት መር ሀገራዊ እመቃ/ Crackdown ወደመሆን የተሻገረ ጉዳይ ነው። የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ፖሊሶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ በያዙና በለበሱ ሰዎች የፈጸሙት ግፍ ጉዳዩ መንግሥታዊ እንጂ የግለሰብ ፖሊሶች ችግር አለመሆኑን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። ጠበቃ አንዱዓለም በዕውቀቱ ስለዚሁ ጉዳይ ሲገልጽ የሚከተለውን ብሏል።
“የባሰ አታምጣ አለ ያገሬ ሰው! አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሲያይ የሚያቅለሸልሸው የጸጥታ አካል ይዘን የት ልንደርስ ነው?!🤔 እኔን ይቺን ቲሸርት ለማስወለቅ የተረባረበው የፖሊስ ብዛት ትንሽ ኃይል ቢጨምር አልፋሽጋ ላይ [በሱዳን] የተወሰደብንን መሬት ማስመለስ ይችል ነበር!!😀 ደሞኮ የአንዳንዶቹ የንቀታቸው ልክ! እንግዲህ መንግሥት በዓሉን የምታከብርበትንም ሆነ የምትለብሰውን ልብስ እኔ ነኝ የምመርጥልህ ብሏል!.. ከታሪክ ጋር ግብግብ ነው የተያዘው!!”።
መንግሥት በምኒልክ አደባባይና በቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በዓሉን ለማክበር የተሰበሰበውን ሕዝብ በኃይል በሚበትንበት በዚያው ሰዓት በመስቀል አደባባይ ግን ታላቅ መንግሥታዊ የአድዋ በዓል በመከበር ላይ ነበር። የብዙ ሀገራት የጦር አታሼዎች፣ ጸጉረ ልውጥ የውጪ ሀገር ሰዎች፣ በመንግሥት ተመርጠው የመጡ የጠሚ ዐቢይን ፎቶና መፈክሮች ያነገቡ የከተማው ነዋሪዎች እና የተለያዩ የመለዮ ለባሽ ክፍሎች (መከላከያ፣ አየር ኃይል፣ ፖሊስ ወዘተ) የተሳተፉበት በዓል በሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ይህ በመንግሥት ደምቆ የተከበረው በዓል ጊዮርጊስ አካባቢ ከተከበረው በዓይነቱም በይዘቱም የተለየ ነው:: የበዓሉ ባለቤትነት ለጊዜው ለመለዮ ለባሹ ይሰጥ እንጂ በቀላሉ ከመከላከያውም ሊወሰድ የሚችል ነው:: ያለሕግ የተሰጠ ነገር ያለ ሕግ ይወሰዳል። ጦሩም የእኔ በዓል ነው ብሎ ሊከራከርለት የሚችለው ጉዳይ አይደለም።
መንግሥታዊ በዓልን በአንድ ደብዳቤ መሠረዝ ይቻላል። በሕዝብ ፍቅር ተጀምሮ በሕዝብ ልብ የተቀበረን በዓል ግን በምንም አዋጅ ልታስቀረው አትችልም። መፈንቅለ በዓሉ ሳይጀመር የከሸፈውም ለዚህ ነው።
ማጠቃለያ
የመንግሥት ርምጃ የግብታዊነት ውጤት አይደለም። የታቀደ እና የታሰበበት ነው። በጊዜያዊ ጩኸትና ተቃውሞ ይገታል ብሎ ማሰብም የዋህነት ይሆናል። መሠረታዊ ዓላማቸውን ከመረዳትና በመሠረታዊና አመክኖአዊ ተቃውሞ ማድረግ ግዴታ ነው። በተለይም መንግሥት ይህንን ፍፁም ፀረ ኢትዮጵያዊ እና ፀረ ሃይማኖታዊ ተግባር የሚፈጽመው በኦሮሞ ስም እንደመሆኑ ጉዳዩን ለኦሮሞ ሕዝብ በግልጽ ከማስረዳት ጋራ ይህንን አክራሪ እንቅስቃሴ ፊት ለፊት መግጠም ይገባል።
ምናልባት በመንግሥት ኃላፊዎች ውስጥ የቀረ እንጥፍጣፊ የኃላፊነት ስሜት ካለ ይህንን ሀገር አፍራሽ ታሪክ-ጠልነት በመተው አድዋን የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት ሕግ በምክር ቤት ማስጸደቅና ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል።
በሀገሪቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተቋማት ላይ የተጀመረው የጉልበት ወረራ እና ሕዝብን ከቤቱ የማፈናቀል ዘመቻ አንደ መፈንቅለ ሲኖዶስና የአድዋ በዓል ግልበጣ ሁሉ መንግሥት ላይ የሚያመጣው ተቃውሞ ከባድ ይሆናል። ለጊዜው እሳተ ገሞራው ባለመታየቱ የሌለ ይመስላል። መፈንዳቱ ግን አይቀርም:: ብቻውን ሳይሆን ከመሬት መንቀጥቀጥና ከማዕበሎች ጋራ ተደባልቆ። በኢትዮጵያ እየጋመ የመጣው ሕዝባዊ ቁጣ ማዕበልና ርዕደመሬት ሆኖ ይመጣል። የሚተርፍ አይኖርም። አስተዋይ መንግሥት ለራሱም ለሀገርም ሲል መንገዱን ያስተካክላል፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ግርግር መካከል አንዲት ዕድሜዋ ከ15 ዓመት የማይበልጥ ልጅ የተናገራችውን ነገር መጥቀስ ለጽሑፉ ጥሩ ማጠቃለያ ይሆናል። “አትሩጡ እምነታችሁ ያድናችኋል! ፈረሰኛው ይመጣል! እንደዚህ እንዳስለቀሱን አይቀርም!” የብላቴናዋ ንግግር ከመንፈስ እንጂ ከሥጋና ከደም አይደለም። ልብ ያለው ልብ ይላል።
ይቆየን
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ