spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትወደ ሰላም ወይንስ ወደ ቀውስ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

ወደ ሰላም ወይንስ ወደ ቀውስ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

አንዳርጋቸው ጽጌ
አንዳርጋቸው ጽጌ

ወደ ወገኖቼ! ብዙዎቻችሁ ጽሁፍህ ባይረዝም ትሉኛላችሁ። እኔም ባይረዝም ፍላጎት አለኝ። ስንፍናዬ የሚመኘው ማሳጠሩን እንጂ ማርዘሙን አይደለም። ግን የማነሳቸው ጉዳዮች ሰፋ ተደርገው መቅረብ ስላለባቸው ብቻ ነው ጽሁፌን የሚያረዝሙት። በሃገሩ ጉዳይ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ የሚል የተማረ ሃይል፣፣ ሞልቶ ክተረፈው ጊዜው ጥቂት ደቂቃዎችን ሰውቶ ጽሁፍ ማንበብ ሊከብደው አይገባም ባይ ነኝ። ሰፋ አድርገን ነገሮችን ማየት ካልቻልን እንዴት መግባባት በመረጃና በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መወሰን እንችላለን። በዚህ መንፈስ ይህን ፌስ ቡክ በሁለት ክፍል እንድከፍል ያስገደደኝን ጽሁፍ በትእግስት እንድታነቡ በትህትና እጋብዛችኋለሁ።

ቀን – መጋቢት 5 2015 ዓ .ም.

ወደ ሰላም ወይም ወደ ቀውስ፤ የትግራይ ኢትዮጵያ ጉዳይ

ማሳሰቢያ፣ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የሚከተለው ምክንያት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ማለቂያ በሌለው ቀውስ እየታመሰች ነው። ከእነዚህ ቀውሶች መሃከል አንዱ በወያኔ የተቀሰቅሰው የሰሜን ጦርነት ነው። ይህ ጦርነት ለጊዜው ቆሟል። ሆኖም ግን በደንብ በታሰበበትና በጥንቃቄ ሁኔታው ካልተያዘ ይህ ያልጠና ሰላም በቀላሉ መደፍረስ የሚችል፣ እስካሁን ህዝብ ከቀመሰው መከራ በላይ የከፋ መከራ ሊያመጣበት እንደሚችል፣ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጠናው የሚያናጋ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል በጊዜ ለማመላከት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጽሁፉ እንደሚያመላክተው በትግራይ ውስጥ ድምጻችን እየተሰማ አይደልም የሚሉ ለሰላም የቆሙ አካላት ድምጽ ባስችኳይ እንዲሰማ የማድረግ ግፊት በመፈጠሩ ነው።  አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሉም ወይ? አዎ አሉ። ሞልተው ተርፈዋል። አቅሜ በፈቀደ መጠን ወደ እነሱ እመለሳለሁ።

 1. እንደ መነሻ!

ትንሽ እውቀት፣ ትንሽ ተመክሮ ያለው ራሱን የፖለቲካ ሰው አድርጎ የሚቆጥር ዜጋ፣ በዘርና በሃገር ጥላቻ፣ በነዋይ ፍቅር፣ በግል ስምና ዝና ስካር፣ በስነልቦና ቀውስ፣ በስልጣን ሱስ፣ በፍራቻ ቆፈን፣ ስንፍና በወለደው ግድየለሽነት እና  በሌሎችም የማሰላሰል እና የመተንተን አቅምን በሚገሉ እንከኖች እስካልተሰለበ ድረስ የአንድን ሃገር እውነታ በፍጹም ነጻነትና ገለልተኛነት ለማጤን የወደፊቱንም ለመተንበይ የሚቸገር አይሆንም።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ በተከታታይ ስልጣን ከያዙት የቅርብ ጊዜ ሁለት መንግስታት፣ የወያኔ እና የብልጽግና መንግስታት  ወይም የመንግስት አመራሮች ጋር በነበረኝ ግንኙነት ሊመጡ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ችግሮችና የሃገሪቱ ፖለቲካ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የሚመስለኝን  ከመጠቆም ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም። በዚህ ጽሁፍ የቀረቡ መረጃዎችና እይታዎች በስልጣን ላይ ላለው መንግስት እንግዳ ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም። አቅሜ፣ ልምዴ እውቀቴ በፈቀደ መጠን ያለምንም ይሉኝታ፣ ግብዝነትና አድርባይነት በድፍረት ሃሳቤን በቃል፣ በጽሁፍ አቅርቤያለሁ። ህዝብ በአደባባይ ከሚያውቀው ይበልጥ በግል የሰጠኋቸው አስተያየቶች ይበዛሉ።

በተለይ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ፣ ከወያኔ ሰዎች ጋር በተለይ ትግራይን በተመለከተ ያደረግኋቸው ክርክሮች “ከፓፓሱ በላይ ቄሱ እስኪሉኝ ድረስ” ከየትኛውም የኢትዮጵያ አርሶ አደር ይበልጥ ለማውቀው የትግራይ አርሶ አደር ወገንተኛነቴን አሳይቻለሁ።

የወያኔ መሪዎች የትግራይ ህዝብ ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል የከፈለውን ከፍተኛ መስዋእትነት ለግል ስልጣናቸውና ጥቅማቸው እንዴት እየመነዘሩ እያባከኑት እንደሆነ፣ እንዴት የእነሱ መጨረሻ የማያማር እንደሚሆን፣ የትግራይም ህዝብ የእነሱ እብሪት ብልግና እና ዘረፋ የመጨረሻው እዳ ከፋይ እንደሚሆን ያለማታከት አስጠንቅቄያለሁ። አክረው ሲገፉት የነበረው የዘር ፖለቲካ ህዝብን ለመከፋፈል ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ካልሆነ በስተቀር “በቁጥሩ አነስተኛ ለሆነው፣ በመላው ሃገሪቱ ተበትኖ ለሚኖረውና ለሚሰራው በኢትዮጵያዊነቱ ቀናኢ ለነበረው የትግራይ ህዝብ አይጠቅመውም” በማለት ተሟግቻለሁ። የቋንቋን እና የባህልን እኩልነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን በዘር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ክልሎች ሳያስፈልጉ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑን፤ የዘር ፖለቲካው ሁሉንም ዘሮች እርስ በርሳቸው እንዲባሉ አድርጎ ሃገር አውድሞ እንደሚጠቃለል ለማሳየት ሞክሪያለሁ።  የቪዲዮ የድምጽና የሰነድ መረጃዎቹ በወያኔና በወቅቱ ኢህዴን ተብሎ በሚጠራው በኋላ ብአዴን በተባለው ድርጅቶችና በየሚድያ ተቋማቱ እጅ እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ።  ይህን ያደረግሁት ወያኔ እየወደቀ ባላበት የመጨረሻው ሰአት ላይ አይደለም። ወያኔ ስልጣን ከያዘ ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ጀመሮ ነበር። ከወያኔና ከተላላኪዎቻቸው የኢህዴንና የኦህዴድ ሰዎች ጋር ያደረግሁት ጭቅጭቅ ከአንድ አመት በላይ ቀጥሎ በመጨረሻም ከወያኔ/ ኢህአዴግ ጋር ለመለያየትና በ1985 አ.ም ለሁለተኛ ዙር የስደት ህይወት መጀመር ምክንያት ሆኖኛል።

ዛሬ በህይወት ያሉ ከወያኔዎቹ ወገን፣ እነተወልደ ወልደማሪያም፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ከብአዴኖቹ እነበረከት ሰምኦን፣ እነተፈራ ዋልዋ፣ እነአዲሱ ለገሰና ታምራት ላይኜ፣  በምን ጉዳይ ምን እንደተነጋገርን ያውቁታል። ዝርዝሩ ብዙ ነው።

በተለይ ተወልደ የኢህአዴግ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የወያኔ የፖሊት ቢሮ አባል በመሆኑና በወቅቱ የድርጅት ጉድይ ትልቅ ተጽእኖ በሃገሪቱ ላይ የሚያደርግ ስለነበር፣ እኔም የዛ ኮሚቴ አባል በመሆን ካየኋቸው ችግሮች በመነሳት የዛሬ ሰላሳ አመት፣ በ1984 አ.ም፣ ቀኑን እና ሰአቱን ባልረሳሁት አንድ ማክሰኞ እለት ከጠዋቱ 4.30 ላይ፣ ቢሮው ቀጠሮ በመያዝ የኢህዴን እና የኦህዴድ ድርጅቶች ደካማ መሆን ወያኔን ራሱን ለከፍተኛ አደጋ የሚዳርገው መሆኑን በማንሳት ሰፊ ውይይት አድርጌያለሁ። የክርከሬ ጭብጥ “የእነዚህ ድርጅቶች ደካማነት በጊዜያዊንት ለእናንተ የሚያመች ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ስታጠፉ ማረም አለመቻላቸው፣ ድርጅታችሁ በስህተት ላይ ስህተት እየሰራ ገደል እንዲገባ ያደርጋል” የሚል ነበር። የተወልደ መልስ “ድርጅቶች በሰው ሃይል ደካማ እንደሆኑ እናውቃለን፤ ግን ነጻ ድርጅቶች ስለሆኑ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ወደ ድርጅታቸው እንዲያመጡ ህወሃት ማዘዝ አንችልም” የሚል ነበር። በወቅቱ ይህ መልስ እንደማያሳምነኝ ነግሬው ተለያይተናል።

ከወያኔዎች ጋር ወልቃይትና ራያንም በተመለከተ ብዙ ተባብለናል። በተለይ ገብሩ አስራት በ1995 አ.ም እንግሊዝ ሃገር በመጣበት ወቅት ወልቃይትና ራያን በተመለከተ ያደረግነውን ውይይት ይረሳዋል ብዬ አላስብም። የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ እልቂት እንደሚያስከትል፣ በመጨረሻም ወያኔዎች ተሸናፊ እንደሚሆኑ ነበር ለማስረዳት የሞከርኩት።

ያ ወቅት ገብሩና ጥቂት ጓደኞቹ በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ ከህወሃት አመራርነት የተባረሩበት ነበር። እቤቴ እራት ጋብዠው በጫወታችን መሃከል ለገብሩ አንድ ጥያቄ አነሳሁለት።

“ያን ሁሉ ዘመን በረሃ ለበረሃ ተንከራታችሁ ይሄው አሁን መለስ ከድርጅቱ አባረራቸሁ ድካማችሁ መና ቀረ። ምን አተረፋችሁ?” አልኩት።

ለዚህ አባባሌ ገብሩ እንዲህ ብሎ መለሰለኝ። “መና አልቀረንም አንቀጽ 39ን በህገ መንግስቱ እንዲካተት አድርገናል።” 

ይህ መልሱ በጣም ስላስገረመኝ። በተናገረው ላይ ሌላ ጥያቄ ጠየቅሁት። “ለመሆኑ ትግራይ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 አማካይነት የመገንጠል መብት ብታገኝ የትኛውን ድንበር ይዛ ነው ነጻ ሃገር የምትሆነው?” በማለት፤

ገብሩም መለሰ፣ “የድንበር ጉዳይ ችግር አይደለም። ትግራይ በህገ መንግስቱ የጸደቀ ድንበር አላት” አለኝ

እኔም “ይህ ህገ መንግስታዊ የምትለው ድንበር በጉልበት ከወሎና ከጎንደር የጠቀለላችሁትን ወልቃይትና እና ራያን የሚያካትት ከሆነ ችግር ይፈጠራል” አልኩት።

“ምን ችግር” አለኝ።

ለማስረዳትም እንዲህ አልኩት፣

“በአንድ ሃገር ውስጥ የአስተዳደር ወሰን አድርጎ ክልል መመስረትና የአንድ ነጻ ሃገር ድንበር መመስረት ሁለቱ ይለያያሉ። ትግራይ ኢትዮጵያ አካል ስለሆነች የወልቃይትና የራያ ነገር እስከ አሁን የሚገባውን ትኩረት አላገኘ ይሆናል። ግን ወልቃይትን እና ራያን የነጻ ትግራይ ሪፓብሊክ አካል አድርጌ ድንበር አሰምራለሁ ብለህ ስትነሳ ችግር ይፈጠራል” አልኩት።

ምን ችግር ? አለኝ በድጋሚ

“ጦርነት” አልኩት

የበለጠ ለማስረዳትም የኤትራን ጉዳይ አነሳሁ። “ኤርትራ ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት ግልጽ የሆነ ድንበር ኖሯት በባድመ ሰበብ የደረሰውን እልቂትና ውድመት አስበው። እንዲህ አይነት ግልጽ የሆነ ነባር ድንበር የሌላቸውን ትናንትና ወያኔ ክልሎች አድርጎ የፈጠራቸውን አካላት አስተዳደራዊ ወሰኖች ወደ ቋሚና ነጻ ድንበርነት እቀይራለሁ ብለህ ስተነሳ፣ አጎራባችህ ያለውና ከዛም ውጭ ያለው ህዝብ ዝም ብሎ የሚያይህ ይመስልሃል? ሁሉም ለእያንዳንዷ ሳንቲሜትር መሬት መዋጋቱ አይቀርም። ይህ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ራሱን ነጻ ሃገር አደርጋለሁ ብሎ ለሚያስብ የትኛውም ትልቅ ሆነ ትንሽ ክልል የሚሰራ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከቅኝ ገዥዎችና ከሌሎች ወረራዎች ራሷን ተከላክላ የተረፈችውና የቆየቸውም ከሁሉም አካባቢ ዜጎቿ በሁሉም የሃገሪቱ ምድር ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነው። እንደ ብሄር ወይም ህዝብ ብቻውን ራሱን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክሎ ያተረፈ ህዝብና ግዛት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት የትም ቦታ ሰርቼ መኖር እችላለሁ በሚል እምነት የህዝቡን ቁጥር በማይመጥን መሬት ላይ የተቀመጠው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ አጎራባች የሆነውን ሰፊ መሬት የኔ ነው ብሎ ለሚነሳ ተገንጣይ በህገ መንግስቱ መሰረት ያሻህን አድርግ ብሎ የሚተወው ይመስልሃል። ትግራይም የሚገጥማት ችግር ይህ ነው” አልኩት።

ዝምታ ሰፈነ

ቀጥዬም ወያኔዎች በጦርነት እንዴት ራሳቸውን እንደሚያዩ ስለማውቅ፣

“ግጭት የሚነሳ ከሆነ የምትዋጉት በሁሉም መንገድ የውጊያ ታሪክ አቅምና ስነልቦና ካለው የአማራ ህዝብ ጋር ነው።” አልኩት።

የራት ግብዣው በዚህ ቆምጣጣ ውይይት  ተዘግቶ ገብሩን ወደሚሄድበት ሸኘሁት።

በግንቦት 7 ንቅናቄ የጸሃፊነት ሃላፊነቴ “የወያኔ ቅጣ ያጣ እብሪትና ዘረፋ ሌላው ህዝብ የትግራይን ህዝብ በበጎ እንዳይመለከተው ማድረጉ አይቀርም” የሚል ስጋት ስለነበረኝ፣ በግሌ የትግራይ ህዝብና  የትግራይ ገዥ ጉጅሌ የሚል ስያሜ የሰጠሁትን የጥቂቶች ስብስብ ያላቸውን ልዩነት በየመድረኩ ለማሰረዳት ሞክሪያለሁ። በተለይ ከወያኔ ጋር ትስስር ያልነበራቸው የትግራይ ምሁራን  የወያኔን የግፍና የዘረፋ ስርአት በመቃወም ከፊተኛው እረድፍ ላይ ለምን መገኘት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ማብራሪያ በመስጠት ጥሪ አቅርቤያለሁ። “ህዝብ ሁሉም ትግሬዎች ወያኔዎች አይደሉም” የሚል ጠንካራ አቋም እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው  “እናንተ የትግራይ ልጆች ወያኔን በመቃወም ትግሉን ስትመሩት ብቻ ነው። እኔ የትግራይ ሰው ያልሆንኩት ከምናገረው እናንተ ብትናገሩት የበለጠ ተደማጭነት ታገኛላችሁ” ብያለሁ። በጣት የሚቆጠሩ ትግራዋይ ይህን ያደረጉ ቢኖሩም የእነዚህ ጥቂቶች ተሳትፎ ብቻውን እየገጠመን ከነበረው ፈተና ጋር ሲነጻጸር እርባና አልነበረውም።

በኢትዮጵያ ወያኔን ከስልጣን ያስወገደው ለውጥ ከመጣና እኔም ከእስር ከተፈታሁ በኋላም ከተለያዩ የሚድያ ተቋማት ጋር ባደረግኋቸው ቃለ መጠይቆች ህዝብ በወያኔ መሪዎችና በትግራይ ህዝብ መሃከል ያለውን ልዩነት እንዲያውቅ ስራዬ ብዬ ስለትግራይ ህዝብ የማውቀውን የህዝቡን ስብእና እና ደግነት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘብ ለማድረግ የቻልኩትን ጥረት አድርጌያለሁ። ለብቻዬ ከሰው ሁሉ ተገልዬ በታሰርኩበት ቦታ ጠባቂዎቼ ተመርጠው ሁሉም የትግራይ ተወላጆች የነበሩ ቢሆኑም ከነሱ መሃከል ከፍተኛ ስብእና የነበራቸው፣ ወያኔ ከሰጣቸው መመሪያ ወጭ ወጥተው ደግነትና ርህራሄ  ያሳዩኝን እንደ ለተማርያም ያሉትን ሰዎች በአደባባይ ህዝብ እንዲያውቃቸው ያደረግሁት “የዘር መጥፎ የለውም የግለሰብ እንጂ” የሚል መልእክት ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተላለፍ በመፈለጌ ነበር።

በአንድ ቃለ መጠይቅ በኢትዮጵያ ደም መፋሰስን፣ የበቀል አዙሪትን ለማስቆም፣ ጌታቸው አሰፋን ጋር ተቃቅፌ ሰላም ለመባባል እንደማይቸግረኝ የተናገርኩት ጌታቸው በወያኔ ዘመን ለተፈጸሙ አሰቃቂ የስብአዊ መብት ጥሰቶች  ዋናው ተጠያቂ እንደሆነ አጥቼው አልነበረም። ሌሎችም የወያኔ አመራሮች ከኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ የዘረፉት አስደንጋጭ መጠን ያለው ሃብት ለሚሊዮን ህፃናት በአጭር መቀጨት፣ በመቶ ሽዎች ለሚቆጠሩ እናቶች በወሊድ እንክብካቤ እጥረት መሞት፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ አጥነትና ተስፋ መቁረጥ፣ በሃገር ውስጥ በዜጎች መሃል እንደሰደድ እሳት ለተስፋፋው ሌብነትን ነወር አድርጎ የማያይ ባህል ተጠያቂ እንደሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም። በሃገሪቱ ሰላም ከወረደ መጪው ዘመን ብሩህ ይሆናል ከሚል ተስፋ ብቻ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝም የወያኔዎች አስተሳሰብና አካሄድ በደንብ ስለሚገባኝ በወቅቱ መጥቶ የነበረውን ለውጥ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት በሚታደግበት መንገድ መስመር ለማስያዝ፣ በተለይ ወያኔዎች ለውጡን በስጋት እንዳያዩትና ወደሌላ አላስፈላጊ መንገድ እንዳይጓዙ ለጻድቃን (ጄ/ል) ሆነ ለአበበ ተክላይሃማኖት ግንቦት 7 ንቅናቄ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ነበር በአካል ተገናኝተን እንምከር የሚል ጥያቄ እራሴ ስልካቸውን አፈላልጌ የደወልኩላቸው። የስልክ ጥሪዬን በጨዋነት ቢመልሱልኝም ከዛ በኋላ ለመገናኘት ያደረግሁት ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።

በማአከላዊ መንግስትና በወያኔ መሃከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ፣ ቱባ የወያኔ መሪዎችና ሌሎችም የወያኔ ሁነኛ ሰዎች ትግራይ ላይ ሲሰባሰቡ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ወያኔዎችን በደንብ ለሚያውቃቸው ለኔ አይነቱ ሰው ከባድ አልነበረም።

ቀደም ብሎ በትግሉ ወቅትና በኋላም ከወያኔዎች ጋር በሰራሁባቸው የተወሰኑ ወራቶች የተረዳሁት፣ ወያኔዎች በተከታታይ የገጠሟቸውን ባላንጣዎች በውጊያ ስላሸነፉ “ከኛ በላይ ጀግና ተዋጊ፣ የሚሊተሪ ሳይንስና ስትራተጂ አዋቂ የለም” የሚል ሰለራሳቸው እጅግ የተጋነነ ግምት እንዳለቸው አውቅ ነበር። ከዛም አልፎ ወታደራዊ ድሎቻቸው የመጡት በበሳልና ሳይናሳዊ በሆነ የፖለቲካ አመራር ነው ብለው ከልባቸው ያምኑ ነበር።

ከወያኔ ጋር በሰራሁበት አጭር ጊዜ ወስጥ  በተደጋጋሚ በሚደረጉ ግምገማዎች፣ “አሸናፊነትና ተሸናፊነትን የሚወስኑ በርካታ ጉዳዮች ስለሆኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ብቃታችሁን ከሚገባው በላይ አጋናችሁ አትዩ። ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል የሻብያ እርዳታ፣ ከደርግ ጋር ሆድና ጀርባ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ደርግ ራሱን ሶሺያሊስት ነኝ በማለቱ እንዲፈርስ የሚፈልጉ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የአረብና የጎረቤት አገራት ድጋፍ ለድላችሁ የነበራቸውን ሚና አትርሱ። ከዛም በተጨማሪ በአንድ ወቅት የሰራ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስትራተጂ በሌላ ወቅት ላይሰራ ይችላል። እንዲያውም ስልጣን ከያዛችሁ በኋላ በሀገር ውስጥና በድርጅታችሁ ውስጥ  የሚታየው ቀውስ ጨብጠናዋል የምትሉት ሳይንሳዊ የፖለቲካ አመራር እንደምትሉት ያልተጨበጠ መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ ልተፈትሹት ይገባል” በሚል ተሟግቻቸዋለሁ። በአንድ ግምገማ ላይ  ይህን አባባሌን ከምር እንመልከተው የሚሉ ደጋፊዎችም አግኝቼ ነበር። ጌዜው ሁሉም በድል አድራጊነት የስከረበት ወቅት ስለነበር የትም ሳይደርስ ቀርቷል።

ባለፉት ሁለት ንኡስ ምእራፎች ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች በመነሳት ነበር የወያኔዎች  ሰዎች አዲስ አበባን እየተው መቀሌ ላይ መሰባሰባቸው ያሳሰበኝ። በተለይ ስዩም መስፍን እና ስዬ አብረሃን የመሳሰሉ ጉምቱ የወያኔ መሪዎች ከመቀሌው ድምጸ ወያኔ የትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች የሰጧቸው አስተያየቶች የወያኔ ሰዎች አሁንም ከድሮ የአዋቂነትና የጀግንነት የበላይነት ቅዥታቸው እንዳልተላቀቁ በሚያሳዩ ቃላቶች የተሞሉ መሆናቸውና በትግራይ የጦርነት ድግስ እየተደገሰ መሆኑን ግልጽ ያደረጉ ነበሩ። እነዚህ ቃለ ምልልሶች ጦርነት ቢከፍቱ የውጭ መንግስታት የሚያግዟቸው እንደሆነ ቃል የተገባላቸው እንደሆነ የሚያሳዩ አነጋገሮች ነበሩባቸው። “ጦርነት ከተነሳ ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ሃይሎች የሚሳተፉበት ይሆናል የሚለው” የስዬ እና የስዩም አባባል ከጎናቸው ከሚቆሙ የውጭ ሃይሎች ጋር ስምምነት መድረሳቸውን ያሳይ ነበር። በዚህ ላይ የወታደራዊ ሰልፉ፣ የትጥቅ ማስጣቱ (ኤግዚብሽኑ)፣ የፉከራውና የቀረርቶው ጉዳይ ሲታከልበት ሁኔታው ወደ ጦርነት እንደሚያመራ ገሃድ ሆኖ ነበር።

በዚህም ወቅትም ቢሆን፣ ስዬ አብረሃ ከ28 አመት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ የተጠቀመባቸውን ቃላቶች ሳይቀይር “ጦርነት መስራት እንችልበታለን፣ ክፍለጦር አፍርሰን ክፍለጦር መገንባት ሜካናይዝድ አፍርሰን ሜካናይዝድ መገንባት እናውቅበታለን።” የሚል በእብሪት የተሞላ ንግግር በትግራይ ቴሌቪዥን ሲናገር በሰማሁብት ጊዜ ዝም ብዬ አላለፍኩም። የስዬና የጓደኞቹ የዛን ወቅት አነጋገርና አስተሳሰብ፣ የተቀየረውን የአለም፣ የቀጠናውን፣ የሃገርና የትግራይም ሁኔታ በደንብ ያላገናዘበ፣ የትግራይን ህዝብ ለከፋ ችግር ሊዳርግ የሚችል መሆኑን የሚገልጽ መልእክት እንዲደራሳቸው በአደባባይ የስዬን ስምና ንግግሩን ጠቅሼ መልእክቴን አስተላፌያለሁ። “ተው ይህ የጦርነት መንገድ አያዋጣም” ብያለሁ።

ለራሳቸው በሰጡት የተጋነነ የአይበገሬነትና የአዋቂነት ቅዥትና በውጭ ደጋፊዎቻቸው ቃል በተገባላቸው ድጋፍ ታውረው ወያኔዎች ጦርነት ከፈቱ። ለትግራይ ህዝብ ይህን ጦርነት ለምን እንደከፈቱ “የሰጡት ማብራሪያ የትግራይን ህዝብ ከጥፋት ለማዳን” የሚል ማጭበርበሪያ ብቻ ነው። በተሳሳተ የራስ ጥንካሬና የሌላው ደካማነት ትንተና እና በአሜሪካ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ባሉ ከረጅም ዘመን ጀመረው በገንዘብ በገዟቸው ባልስልጣናት ሸሪኮቻቸው አበረታችነትና የአሜሪካ ጥቅም ለማስከበር የተከፈተ ጦርነት እንደሆነ ለትግራይ ህዝብ አልነገሩትም። የወያኔ መሪዎች አብይን ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት በቀላሉ አሽቀንጥረው ከጃቸው ያመለጠውን ስልጣን በዚህ ስልጣን አማካይነት የተቀዳጁትን የመዝረፍ መብት መልሶ መያዝ ይቻላል በሚል የጀብደኝነት ስሌት የተጀመረ ጦርነት እንደሆነ ለትግራይ ህዝብ የነገረው የለም። ስልጣን ተይዞ ምን ሲሰራበት እንደነበር የሚያውቀው የትግራይ ህዝብ ይህን ሃቅ አውቆ ቢሆን ኖሮ ለሶስተኛ ዙር ልጆቹን የመስዋትነት ጭዳ በማድረግ የወያኔ መሪዎችን ህልውና  እና የኢትዮጵያን ጠላቶች ጥቅም ለማስከበር ሆ ብሎ አይነሳም ነበር። የትግራይ ህዝብ እንደርሱ በድህነት ተቆራምደው በሚኖሩ ደሃ የአማራ እና የአፋር ወንድሞቹንና እህቶቹ ላይ በአረመኔያዊ ጭካኔ አይዘምትም ነበር።  

አሁንም በዚህ ሰአት ይህ የወያኔዎች የጦርነት አጀማመር ትርክት ከአንድ ጉዳይ በስተቀር ብዙም  የተቀየረ ነገር የለውም።  በአደባባይ ጦርነቱን በመብረቃዊ ጥቃት ጀመርነው ብለው እንዳልተናገሩ፣ ዛሬ ወያኔዎች ጀማሪዎቹ እነሱ እንዳልሆኑ አድርገው እያቀረቡት ነው። “የትግራይን ህዝብ ከጥፋት ለማዳን” የሚለው የሃሰት ትርክት ግን ዛሬም በወያኔ አባላት መሃከል ብቻ ሳይሆን በመላው ትግራይ እንደታመነ እንዲቀጥል አድርገዋል።  ይህን ትርክት ለማስቀጠል እንዲቻል ወያኔዎች ከጦርነቱ በፊት ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡ የዲፕሎማሲ ስራቸው ግብአት እንዲሆን የተዘጋጁበትን የጄኖሳይድ ትርክትና ሰበብ በማጠናከር፣ የጄኖሳይድ ኮሚሽን አቋቁመው በትግራይ ውስጥ ብቸኛው ስራ የሚሰራ፣ በቂ በጀት የተመደበለት የመንግስት ተቋም አድርገው ገንብተውታል።

ኮሚሽኑ ወያኔዎች ከመደቡለት በጀት በተጨማሪ፣ አለም አቀፍ የትግራይ ምሁራን ድርጅት በሚያሰባስበው ገንዘብና ራሱ የኢትዮጵያ መንግስት በሚያቀረበው ገንዘብና እርዳታ ተደግፎ የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግስት በአለም ፊት የሚያሳጣ፣ ምእራባውያኑ መውሰድ ለሚፈልጉት ጸረ ኢትዮጵያና ኤርትራ እርምጃ ሽፋን የሚሆን በሚገባ የታቀደና የተደራጀ፣ ወደፊት ወያኔ ለሚያደርገው የዲፕሎማሲ ዘመቻ የሚያገለግል የተቀነባበረ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።  

ኮሚሽኑ በየቤቱ ሰራተኞቹን እየላከ ለጄኖሳይድ ክስና ለካሳ ማሰባሰቢያ የሚሆን መረጃ እየሰብሰብኩ ነው በማለት የትግራይ ህዝብ ጄኖሳይድ ሊፈጸምብኝ ተሞክሮ ነበር በሚል እምነት ውስጥ እንዲኖር እያደረገው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን “አሁንም የትግራይን ህዝብ ከወያኔ ውጭ ከጄኖሳይድ የሚያተርፈው የለም የሚል” ሰበካውን ቀጥሎበታል። አሁንም የወያኔ መሪዎች የሰላም ስምምነቱ በጦርነት አስገድደው ያገኙት ድል አድርገው ለትግራይ ህዝብ እያቀረቡለት ነው። ህዝቡ “የዚህ ድል ባለቤት ወያኔ ስለሆነ፤ ከህልውና ጥፋት የታደገህ ወያኔ ስለሆነ፤ እጣህን ከወያኔ ጋር አቆራኝተህ መቀጠል አለብህ” እየተባለ ነው።

ወያኔዎች ያሻቸውን ቢሉ ይህ አላስፈላጊ የነበረ ጦርነት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱን የደሃ ልጆች ህይወት ቀጥፎ የዚችን ደሃ ሃገር ሃብትና ጥሪት አራቁቶ በነሱ ወታደራዊ ሽንፈት ለጊዜው ቆሟል። ከጦርነት ጋር በተያያዘ የሆነው ሁሉ ጸሃይ የሞቀው ጉዳይ ስለሆነ ብዙ ማተት አያስፈልግም። ከዚህ በላይ ያቀረብኩት መንደርደሪያ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን ዘመን በጥንቃቄ እንድንመለከት የእይታ ማእቀፍ ለመስጠት ብቻ ነው። የወያኔ መሪዎችን እና ከእነዚህ መሪዎች ጋር የተጣበቀውን የትግራይ ልሂቅ የአእምሮ ውቅር በሚገባ  ማወቅ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እውነተኛ ሰላም ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትግራይን ህዝብ ጨመሮ ከዛም አልፎ ለቀጠናው እንዲያመጣ ከተፈለገ በስርአት መሰራት ያለባቸውን ነገሮች ለመዘርዘር ያግዛል በሚል እምነት ነው።

ከዚህ ቀጥሎ አሁናዊ የትግራይ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ይህ ሁኔታ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል፣ የሰላም ስምምነቱ አንኳር በሆኑት የስምምነት ነጥቦች ዙሪያ በምን ደረጃ ይገኛል? እውነተኛ ሰላም በትግራይ ሆነ በተቀረው ኢትዮጵያ ለማስፈን ምን መደረግ ይኖርበታል? የሚሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት መንግስት ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳዩ በዋንኛነት ለሚመለከተው ህዝብ መስጠት የሚገባቸውን ነገር ግን እያደረጉት ያልሆነው ምልከታ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

 • የወቅቱ የትግራይ የፖለቲካ ሁኔታ ከሰላም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ፤

በትግራይ ውስጥ የሰላም ስምምነቱ ከመፈረሙ ከወራት በፊት ወያኔ የጀመረው ጦርነት በትግራይ ህዝብ ላይ ያሳደረውን እልቂትና ጥፋት የሚቃወሙ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች በከተማው ጎዳናዎችና በየቤተክርስቲያኑ ይበተኑ ነበር። (የሰንድ ማስረጃዎች አሉ)  ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በጥቂት ሰዎች የሚደረግ ቢሆንም በራሱ በወያኔ ውስጥ ያሉ ጦርነቱ እንዲቆም በሚፈልጉ የአመራር አካላት ጭምር የሚደገፍ ነበር።

ይህ እንቅስቃሴ ያሳሰባቸው የወያኔ አመራሮች “ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት አላቸው፣ የወያኔ መሪዎችን ለመግደል አሲረዋል፤ እንዲሁም መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አስበዋል  ” በሚል በወዲ ሃጎስ የምትመራዋን በመቀሌ ዙሪያ ለጥበቃ የተመደበች ወደ አምስት መቶ የሰራዊት ብዛት የነበራትን አሉላ የተባለች ብርጌድ ላይ እርምጃ ወስደዋል። ወዲ ሃጎስ ለእስር ተዳረገ። በመፈንቅለ መንግስት ክስ ተከሶ ዛሬም እስር ቤት ነው ። የሰራዊቱ አባላት ትጥቅ አውርደው መቀሌ ቢዝነስ ኮሌጅ ውስጥ በተሃድሶ ስም በጥበቃ ላይ ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን እንዴት አታውቅም በሚል የመቀሌው የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተስፋዬ ከስራው ተነስቶ ለቁም እስር ተዳርጎ ነበር። ኮሚሽነር ኪሮስ የተባለው የጸጥታ ሃላፊም ተመሳሳይ እጣ ገጥሞት ነበር። የመቀሌው ከንቲባ ዶ/ር ገብረመድህን ከሃላፊነቱ በማንሳት ለእስር ተዳርጓል።  በወያኔ ውስጥ ጦርነቱን የሚቃወሙ የአመራር አካላት ቁጥራቸው እየተበራከተ በማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ አቅም እየፈጠሩ በመሄድ ላይ ነበሩ።

በዚህ ወቅት በጦር ሜዳ በኩል የሎጂስቲክ ችግር እያደገ፣ በሰራዊቱ ውስጥ የመንደርተኛነት ክፍፍል እየሰፋ፣ ወያኔ በገፍ በቅርቡ ያሰባሰባቸው ወጣቶችና ከእስር ፈትቶ ወታደር ያደረጋቸው ወንጀለኞችና የድርጅቱ የቆዩ አባላቶች ተጣጥመው መስራት እየተሳናቸው በሰራዊቱ ውስጥ ለጋራ አላማ መሰለፍ አዳጋች የሆነበት ሁኔታ በስፋት መስተዋል ጀመሮ ነበር። በርካታ የሰራዊት አባላት ሰራዊቱን እየከዱ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። እነዚህን ተመላሾች ስራዬ ብሎ እያሳደደ የሚለቅም በኮማንድ ፖስት በኩል ሰፊ የተደራጀ ስራም ተጀምሮ ነበር። የሰራዊቱ መሪዎች የሙስና ድርጊት እየባሰበት፣ ሙስናው የሰራዊቱን ቀለብ ከመሸጥ አንስቶ እንዲሁም አብዛኞቹ ወታደራዊ መኮንኖች (እንደወዲ እምበይትይ የመሳሰሉ ጀነራሎች) ወደ ትግራይ የሚያስገቡ ኬላዎች እየዘጉ ከአፋር ፌዴራል ሃይሎች ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ በሆነ የጨው ንግድ በመስማራታቸው በሰራዊቱ ውስጥ ትልቅ መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከአማራና ከአፋር ክልል የተዘረፈውን ሃብት የግል እስከማድረግ ድረስ የሚያካትት ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ራሱ ወያኔ፣ ኮነኔል ጉና (ገብሩ) የአዋሽ አርባ አዲስ ራእይ ማሰልጠኛ ሰራ አስኪያጅና በነበረው በሌሎችም ወታደራዊ አመራሮች ላይ የእስራት እርምጃ እስከመውሰድ ደርሶ ነበር።

በራሱ በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ትግራይ ለገባችበት አሰቃቂ ሁኔታ ተጠያቂዎች መሆን የሚገባቸውን ሰዎች ለይተው ሊጠየቁ ይገባል የሚል ድምጻቸውን ማሰማት የጀመሩ አባላት ብቅ ያሉበት ሁኔታ ተፈጠሮ ነበር። ወያኔ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠጋግኖ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ለማለት ነበር የሶስተኛ ዙር የወረራ ጥቃቱን በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ የከፈተው። የሶስተኛው ዙር ወረራ አላማ ቀደም ብሎ እንደታሰበው አዲስ አበባ ለመግባትና የመንግስት ስልጣን ለመቆጣጠር ሳይሆን ከወያኔ መሪዎች አቅምና ቁጥጥር ውጭ እየወጣ የነበረን መጨረሻው የማያምረውን የወያኔን የውስጥ ድርጅታዊ እና የትግራይን  ፈተናዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደራደር ለመፍታት የሚያስችል የተወሰነ የመደራደሪያ አቅም ለመፍጠር የተደረገ ነበር። የትግራይ ህዝብና ወጣት የወያኔ አመራሮች ለጦርነቱና ለእልቂቱ የወያኔን ነባር መሪዎች ተጠያቂ እንዳያደርጋቸው ከመስጋት የተደረገ የማደናገሪያ ወረራ ነበር።  ወረራው ወያኔዎች እንዳሰቡት ሳይሆን የኢትዮጵያ ጦር ሰፊ የትግራይን ክልል ተቆጣጥሮ ጭራሽኑ ትግራይ ወስጥ ገበቶ መቀሌን በቅርብ ርቀት የሚያይበት ሁኔታ ተከሰተ።

ይህ ወታደራዊ ሽንፈት በአንድ በኩል ወያኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲቀበል ያደረገው ቢሆንም ከዚሁ ያልተናነሰ ጫና ያሳደረው በራሱ በወያኔ ውስጥ የተነሳው ነባር መሪዎቹን ሊበላ ወደሚችልበት ደረጃ እያደገ በመሄድ ላይ የነበረው የውስጥ ትግል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።

ወያኔዎች ከአሜሪካን መንግስት ባላስልጣናት ጋር በቅርበት እየተመካከሩ የሚሰሩ በመሆናቸው ወታደራዊ ሁኔታውን የተረዳው የአሜሪካ መንግስት የወያኔ መሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደራደር ራሳቸውን ከጥፋት እንዲያድኑ ተጸእኖ ሳያደርግባቸው እንዳልቀረ መገመት ከባድ አይሆንም። የአሜሪካ ተጽእኖ በወያኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግስትም ላይ የተደረገ ለመሆኑ ፕሬዚደንት ኢሳያስ በጥር 2015 በሰጠው ቃለ ምልልስ ጥቆማ ሰጥቶናል። በሌላ መንገድም ይህ ተጽእኖ ቀላል እንዳልነበር መረዳት ተችሏል። ይህም ሃቅ እንዳለ ሆኖ የወያኔ የውስጥ ሽኩቻን ያሳደረውን ከፍተኛ ተጽእኖ አሳንሰን ማየት አይገባንም። 

የውስጥ ሽኩቻው ከሰላም ስምምነቱ በፊት በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ በነባር አመራሮችና በወጣት አመራሮች መሃከል ይካሄድ ነበር። ሽኩቻው ወጣቶች በጎደሉ የስራ አስፈጻሚ አባላት ምትክ አዳዲስ አባላት እንሙላ ሲሉ፣ ነባሮቹ ወቅቱ አዲስ አባላት ለመሙላት አይፈቅድልንም የሚል ነበር። ወጣቶቹ አዲሶቹ አባላት ከወጣት መሪዎቹ ጎን ይቆማሉ ብለው ስለሚያስቡ ሃሳቡን ሲገፉ ነበር። ነባሮች ይህን ስላወቁ ሃሳቡን ሲቃወሙ ነበር። ሌላው የሽኩቻ ነጥብ በስልጣን የሚታየው ያልተቀየረው የአሻአ (የአክሱም ሽሬ እና አድዋ)  ሰዎች በፖለቲካውም፣ በአስተዳደርም በወታደራዊ መስኮች የነበራቸው የበላይነት አሁንም በከፋ መልኩ እየቀጠለ ከመሆኑ ጋር ተያያዞ የሚነሳ ነበር። በተደጋጋሚ በማእከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ይህ ጉዳይ እየተነሳ ያወዛግብ እንደነበር ይታወቃል። ማወዛገቡ ብቻ ሳይሆን ሰዎች የመጡበትን አውራጃ እየጠቀሱ በታማኝነት በከሃዲነት የመፈረጅ ንትርክ ጭምር የተለመደ ሆኖ ነበር። 

ከሰላም ስምምነቱ በፊት በነበሩ ጥቂት ወራት በአጠቃላይ በወያኔ አመራር ካምፕ ውስጥ የነበረው ክፍፍል ለተፈጸመው ሁሉ በተጠያቂነት እንያዛለን የሚሉ ጥቂት አመራሮችና ሊጠየቁ ይገባል በሚሉ በርካታ አባላት መካከል እያደገ የመጣ ክፍፍል ነበር። እጣቸውን ከተጠያቂነት ጋር የሚያስተሳስሩ መሪዎች ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ራሳቸውን ለማዳን ሴራ በመሽረብ፣ እቅድ በማውጣት ነበር።

በዛን ወቅት የማእከላዊ ኮሚቴው ለሁለት እንደተከፈለ ሁሉ የሰራ አስፈጻሚውም ለሁለት ተከፈሎ ነበር። ጌታቸው ረዳ እና ደብረጽዮን በአንድ ወገን፣ ጌታቸው አሰፋና ፈትለወርቅ አለም ገብረዋህድ በሌላው ጎራ ቆመው ነበር። የጌታቸው ረዳ ነገር መቼም አስገራሚ ነው መባሉ አይቀርም።  በዚህ የውስጥ ሽኩቻ በትግራይ ውስጥ ከሚገኙ ከ35ቱ (ከ37ቱ ሁለቱ ውጭ ሃገር ናቸው) የወያኔ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መሃል በየቀኑ አቋማቸው የሚለዋውጡ አስራ አራት አባላት ያሉት ሲሆን የተቀሩት በሁለት ጎራ ተከፍለው የእነዚህ የ14 ኮሚቴ አባላት ድጋፍ በማሰባሰብ የሚተናነቁባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ነበሩ።

የውስጥ ሽኩቻው የደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ  የሚያሳየው ሃቅ በጥር 2015 ውስጥ ተከስተ። የወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ እና ከእያንዳንዱ አርሚ ሶሶት ሶሶት ሰው የተወከለበት በደጀን የርእሰ መስተዳደሩ ቢሮ፣ ከጥር 7 እስከ ጥር 10 በተደረገው ስብሰባ ኮሚቴው በወሰነው ውሳኔ መሰረት ደብረጽዮን ገብረሚካኢኤል፣ ፈትለወርቅ  ገብረእግዚአብሄር፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አለም ገብረዋህድና ጌታቸው ረዳ፣ ሁሉም የህወሃት የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት፣ በትግራይ ለሆነው ሁሉ  ተጠያቂዎች ናቸው በሚል ከስልጣናቸው ታግደው እንዲቆዩ እስከመወሰን እና  ይህ ውሳኔ በምክር ቤት እንዲጸድቅ ጥያቄ እሰከማቅረብ ደርሶ ነበር።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የጥቂት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የአቋም መገለባበጥ ከሚታይበት ሁኔታ በስተቀር በወያኔ ውስጥ በትግራይ ለውጥ እንዲመጣ በሚፈልጉ እና በማይፈልጉ፣ የሰላም ስምምነቱን በሚደግፉና በሚቃወሙ ሁለት ዋና ቡድኖች የማእከላዊ ኮሚቴው እንደተሰነጠቀ ነው።

አንዱ ቡድን የሞንጀሪኖ ቡድን በመባል የሚታወቀው ሲሆን የውናትና የባይቶና (በስም የተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸው ነገር ሁኔታዎች ሲከፉ ከዚህ ቡድን ጋር የሚለጠፉ እንደሆነ ይታወቃል) ድጋፍ ሲኖረው፣ ከወታደራዊ ተቋሙም ጋር ከተወሰኑ አካላት ጋር ቁርኝት ያለው ቡድን ነው። የዚህ ቡድን አባላት ጌታቸው አሰፋ ራሷ ሞንጀሪኖ (ፈትለ ወርቅ ገ/እግዚአብሄር )አለም ገብረዋህድ፣  አልማዝ ገ/ጻድቅ የክልሉ የትራንስፖርት ሃላፊ፣ ገነት አረፈ የማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ፣ ሃጎስ ጎድፋይ ጤና ቢሮ ሃላፊ ( አሁን የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት ሃላፊ)፣ ፍስሃ ሃፍተፅዮን ፣ ሃዱሽ ዘነብ ፣ አማኑኤል አሰፋ ፣ ይትባረክ አምሃ የመቀሌው አዲሱ ከንቲባ፣ አርአያ ግርማይ፣ ዶ/ር አማኑኤል ሃይሌ፣ ሊያ ካሳ የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ፣  እነዚህ የሰላም ስምምነቱ በመቃወም በጋራ የቆሙ ሲሆን፤ በሌላ ወገን ከጌታቸው ረዳና ሌሎች ሰላሙን የሚደግፉ አባላት፣ ብርሃነ ገብረየሱስን፣ የአሁኑ የምእራብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ነጋ አሰፋ፣ የህብረት ስራ ማህበር የክልሉ ሃላፊ፣ ሰብለ ካህሳይ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊ፣ በየነ ሙክሩ የፋይናንስ ሃላፊ፣ ሃብቱ ኪሮስ ቆይቶ የተቀላቀለ የደቡብ ዞን አስተዳዳሪ፣ ዶ/ር አትንኩት መዝገበ፣ ረዳኢ ሃለፎም የትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ለምለም ሃድጉ ባህልና ቱሪዝም ሃላፊ የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ተከራክረው ያሸነፉ ናቸው። አንዲሁም ከተለያዩ አርሚዎች የተወከሉ የጦር መሪዎች አብዛኞቹ  የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ ከእነዚህ የለውጥ ሃይሎች ጋር በመሆን የቆሙ ነበሩ፡፡ በዚህ ስብሰባ ጌታቸው አስፋ አሞኛል በሚል ሰበብ ስብሰባውን አቋርጦ አስከመሄድ ደርሷል። በተጨማሪም ጄነራል ወዲ እምበይተይ በስብሰባው ሊገኝ አልቻለም ፡፡

ይህም ሆኖ የሰላም ስምምነቱን ያልተቀበለው ቡድን በጁ ባለው የገንዘብና አሰተዳደራዊ አቅም እና በሰራዊቱ አመራር ውስጥ ባለው ድጋፍ የተለያዩ እንቃስቃሴዎችን ማድረጉን አላቆመም። ይህን አቅም በመጠቀም ጥር 24 እና 25 /2015 ከመላው ትግራይ የቡድኑ ደጋፊዎች ናቸው የሚላቸውን እስከ 600 የሚደርሱ ወጣት ካድሬዎች መቀሌ በሃውልት ሰማእትታ አዳራሽ በማሰባሰብ፣ “ህወሃት ታሪካዊ ድርጅት ነው መፍረስ የለበትም፣ ይህን ታሪካዊ ድርጅት ለማፍረስ ከሚሰሩ ተንበርካኪዎች ጋር  መታገል አለብን” የሚል አጀንዳ መወያያ እንዲሆን አድርጓል። በዚሁ አጋጣሚ ተንበርካኪዎች በሚባሉ ግለሰቦች ላይ የግድያ፣ የግድያ ሙከራ መፈጸም መጀመሩን፣ ወደፊት ይህ የወንጀል ድርጊት እየጨመረ እንደሚመጣ መታወቅ አለበት። በዚህ ስብሰባ ላይ ሁሉም የማእከላዊ ክሚቴ አባላት ተገኝተው ነበር። አላማው ለውጥ ፈላጊ አመራሮችን ለማሸማቀቅ ከተቻለም ከዚህ በፊት በ1993 መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቹን በካድሬዎች አማካይነት አዋክቦ ከድርጅቱ እንዲባረሩ ያደረገውን አሰራር ለመድገም ነበር። እንዲህም ሆኖ ስብሰባው ለወጥ በሚፈልገው ወገን አሸናፊነት ተጠናቋል።

ይህ መንገድ አላዋጣ ያለው ጸረ ሰላም ቡድን ከለውጡ በኋላም ስምምነቱን የማጨናገፍ በኢትዮጵያ ደረጃም ሃገር የማናጋት እቅዱን በስራ ለመተርጎም የራሱን እንቅስቃሴዎች ማድረጉን ቀጥሏል። ለስራ ገንዘብ ያስፈልገናል በሚል 350 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅድ አውጥቶ ይህን ገንዝብ የመቀሌን ከተማ መሬት በመቸብቸብ ገንዘቡን ማሰባሰብ ችሏል። የመቀሌን መሬት የገዙት ግለሰቦች ከአማራና ከአፋር ክልል እንዲሁም ከራሱ ከትግራይ ህዝብ ገንዘብና ንብረት የዘረፉ የሰራዊቱ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ናቸው።

ይህን ገንዘብ በመጠቀም ለውጥ የማይፈልገው ቡድን ሰራዊቱ ውስጥ ካሉት አጋሮቹ ጋር በመሆን በልዩ ሁኔታ ለተመለመሉና ለሚያስለጥናቸው እስከ 7000 የሚደርሱ የሽብር ስራ በመላው ኢትዮጵያ ለማካሄድ ለሚሰለጥኑ  ሴትና ወንድ አሸባሪዎች ማሰልጠኛ በተግባር ላይ እያዋለው ነው(የመሰልጠኛ ቦታው ይታወቃል)። የአሰልጣኝነት ሚና የወሰዱት ግለሰቦች የልዩ ኮማንዶ አሰልጣኞች ብቻ ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ የደህንነት አባላት ጭምር ናቸው። እነዚህ ወጣቶችን እስራኤል ጠላቶቿን በተለያዩ ሃገሮች ውስጥ ለማጥፋት እንደምታሰማራቸው የጥቃት ቡድኖች እንጠቀምባቸዋለን በሚል ሂሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የተለያዩ የሽብር ስራዎችን የሚያከናውኑ ተደርገው እየተቀረጹ ነው።

ከዚህ ውጭም ወያኔዎች በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖር ለመጠቀሚያነት ሲያዘጋጇቸው የነበሩ በተለይ አዲስ አበባ ገብተን ስልጣን እንይዛለን ባሉበት ወቅት እንደ መናጆ ሊገለገሉባቸው አሰባስበዋቸው የነበሩ የተለያዩ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ሰራዊቶች ስልጠና እንዲቀጥል ተደርጓል። በመቀሌ አካባቢ ብቻ እስከ 8000 ቁጥር ያለው የኦነግ ሰራዊት አሁንም ያለ ሲሆን፣ በሮማይ ኪሮስ የሚመራ የአገው ነጻ አውጭ  ታጣቂዎችን ሳምረ በሚባል ቦታ ማሰልጠኑን  አሁንም አላቆመም። የአፋርና የሌሎችም ነጻ አውጭዎች ነን የሚሉ ድርጅቶች አሁንም ሰላም ከማይፈገው ቡድን ጋር ተቀራርበው እየሰሩ ነው።

የእነ ጌታቸው አሰፋና የነሞንጀሪኖ ቡድን፣ በአስተዳደርና በወታደሩ ውስጥ ካለው ጉልበቱ በላይ፣ በጁ የገባው ሃብት የሰላም ስምምነቱን የራሱን ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት እየተጠቀመበት ይገኛል። መንግስት ከጦርነቱ በፊት ወደ ትግራይ  ልኮት የነበረው ገንዘብና የወያኔ የዶላር ክምችት አሁንም ያለው በዚህ ቡድን እጅ ነው። የተወሰነ ዶላርና ብር በተቀበረበት ብል በልቶት ቢገኝም፣ አሁንም ከፍተኛ ክምችት ያለው ገንዘብ በእዚህ ቡድን እጅ በተለያዩ ግለሰቦች ቤት በአደራ ተቀምጧል። ከኤፈርት ካምፓኒዎች አንዱ የሆነው በኢዛና የማእድን ኩባንያ ቀድሞ ሲወጣ የነበረና በጦርነቱም ወቅት እየወጣ የነበረው ወደ አምስት ኩንታል የሚሆን ወርቅ በተመሳሳይ መንገድ የሰላም ስምምነቱን በማይደገፍው ቡድና ቁጥጥር ስር ሆኖ በግለሰቦች እጅ ተቀምጧል። 

በጦርነት ወቅት ይደረግ እንደነበረው ዛሬም ወርቅና ሳፋየር በእርድታ ማስተባበሪያ መኪናዎች፣ በተለይ በአፋር፣ በአፍዴራና ሶርዶ ኬላዎች በአባዲ አፍሮ መኪናዎች  ከትግራይ እየወጣ ኢትዮጵያ ውስጥና ጅቡቲ እየተሸጠ ነው። በጦርነቱ ወቅት ሲሸጥ የነበረው ወርቅና ሳፋየር ብቻ ሳይሆን፣ ለትግራይ ህዝብ በእርዳታ የገባ መድሃኒት ወደ አፋርና አማራ ክልል እየወጣ ይሸጥ እንደነበር የራሱ የወያኔ የግምገማ ሰነድ አመላክቷል። ይህ የእርዳታ መድሃኒት ዛሬም በዘመድ በተሳሰሩ የትግራይ መድሃኒት ቤቶች ውስጥ መሸጡን እንደቀጠለ ነው ። ለምሳሌ መድሃኒቱ ሲሸጥባቸው ከነበሩ ቦታዎች መካከል ፋሚሊ ፋርማሲ ፣ ሂወት ፋርማሲ ሲሆኑ እነዚህ መድሃኒትቶችም ከEPSA ፣ ከዓይደር ሆስፒታል እና ከመቀሌ ሆስፒታል በአቶ አለማየሁ የ EPSA ስራ አስኪያጅ፣ ዶ/ር ሃጎስ ጎዲፋይ፣ ዶ/ር ፊሊሞን የመቀሌ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አማካኝነት እየወጡ ይሰራጩ እንደነበረ በሚስጥር የተያዘው፣ ጉጅለ ሰለስተ በተባለው / የወያኔ ኢንተለጀንሲ ሰርቪስ በ3/12/2014 ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበ ሪፖርት ያመለክታል ፡፡ 

በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ዳያስፖራዎች ለቤተሰቦቻቸው ይልኩት የነበረው ዶላር ጅቡቲ ውስጥ የወያኔ ተባባሪዎች በከፈቱት አካዎንት እየገባ ብሩ ትግራይ ውስጥ እየተከፈለ ነበር።  በዚህ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች የትግራይ ዳያስፖራ ለቤተሰቦቹ ከሚልከው ገንዘብ እስከ 50 ከመቶ የሚደርስ ኮሚሽን ያስከፍሉ እንደነበር ይታወቃል። 30 በመቶ ኮሚሽን የተከፈለባቸው የሰነድ መረጃዎች በእጃችን አሉ። ይህን ስራ ትግራይ ውስጥ የሚቆጣጠረው ሰላም የማይፈልገው ቡድን ሲሆን፣ ከትግራይ ውጭ ደግሞ ስራ የሚያስተባብሩ ከወያኔ ጋር የሚሰሩ በስም የምናውቃቸው ትግራዋይ ያልሆኑ የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ጭምር አሉ። ሌሎችንም ከወያኔ ጋር የተያያዘ ከፍተኛ ሃብት የነበራቸውን ግለሰቦችን ሃብት የሚያንቀሳቅሱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ንብረት እየሸጡ ገንዘቡን በዶላር የሚያስተላልፉ፣ ዛሬ የወጭ ምንዛሪ ዶላር ከመቶ ብር በላይ በጥቁር ገበያ እንዲዘረዘር ያደረጉ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔዎች ተክተው እየተንቀሳቅሱ ነበር፤ አሁንም አልቆመም። በትግራይ የባንኮች መከፈት በጅቡቲ ወስጥ ከፍተኛ ኮሚሽን በመውሰድ ይደረግ የነበረውን የዶላር ምንዛሪ ያስቀረው ቢሆንም በሌላ በኩል ከየትኛዎቹም ክልሎች ይበልጥ ከባንክ ውጭ ትግራይ ውስጥ በጸረ ሰላም ሃይሉና በግለሰቦች እጅ የሚገኘውን ጥሬ ገንዘብ በትግራይና በሌላውም የኢትዮጵያ ግዛት የዶላር ምንዛሬውን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ዘርዛሪዎቹ ከሞንጆሪኖ ቡድን ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ ግለሰቦች ሆነዋል። ህገወጡን ምንዛሬ እስከ 120 ብር አድረሰውታል።

በትግራይ ውስጥ ያለውን በለውጥ ፈላጊና ለውጥ በማይፈልጉ ሃይሎች መሃከል ያለውን ሽኩቻ ከዚህ በላይ የተቀመጠውን ሃተታ ከጀርባ በማድረግ ስንቃኘው ነው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ፖለቲካው የሚሄድበትን መንገድ መረዳት የምንችለው።

የሰላም ስምምነቱ በፖለቲካ መስኩ ያስቀመጠው መፍትሄ በትግራይ የሽግግር መንግስት እንዲሚቋቋም፣ ይህን የማቋቋም ሃላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚወስድ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በስምምነቱ መሰረት የተሰጠውን ስልጣን ምን እያደረገበት እንደሆነ ባናውቅም ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ቡድኖችና በሶስተኛ ደረጃ የተጨመረ የነጻድቃን ቡድን ታክሎበት የሽግግሩን ሂደት በበላይነት ለመቆጣጠር እየተራኮቱ ያሉበት ሁኔታ ይታያል።

የተጠያቂነት ፍራቻ ያለበት የሞንጀሪኖ ቡድን የመጀመሪያውን እርምጃ በመውሰድ የካቲት 3 /2015 ሶስት ከወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ፣ ሶስት ከወታደሩ ክንፍ፣ ሶስት ከምሁራን የተወጣጣ የጊዜያዊ መንግስት መስራች ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር።  በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ፈትለወርቅና ራሱ ጌታቸው አሰፋ ራሳቸውን ማስገባት ያልፈለጉት በህዝብ ተቀባይነት ስለሌለን ከጀርባ ሆነን በራሳችን ሰዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እንመራለን በሚል ስሌት ነው። የዚህ ኮሚቴ አባላት ከህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ኢሳያስ ታደሰ፣ አማኑኤል አሰፋ፣ ዶ/ር ሃጎስ ጎድፋይ በሞንጀሪኖ ቡድን የተመረጡ ሲሆኑ፣ ከሰራዊቱ ታደሰ ወረደ (ጀ/ል) ተክላይ አሸብር (ጀ/ል)፣ ጉእሽ ገብረ (ጀ/ል) በተመሳሳይ ያለ ሰራዊቱ እውቅና እንዲካተቱ የተደረጉ፣ እንዲሁም ከምሁራን፣ ሙሉ ኪዳነ ማሪያም፣ መረሳ ጸሃዬ፣ ሃንሳ ረዳ በቡድኑ በተመሳሳይ መንገድ የተመረጡ ናቸው። ከምሁራኑ፣ የተመረጡት ሙሉ ኪዳነ ማሪያም፣ መረሳ ጸሃዬ፣  ሁለቱ የፌደራል መንግስቱ ያልተቀበለው በትግራይ የተደረገው ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመነበር ሆነው በወያኔ ተሹመው የነበሩ ናቸው። ይህ ኮሚቴ በፍጥነትና በዚህ መልኩ የተዋቀረበት ዋናው ምክንያት የሽግግር ሂደቱን ነባሮቹና በተጠያቂነት እንያዛለን ብለው የሰጉት የህወሃት አመራሮች ለመቆጣጠር አስበው ነበር።

ይህን በነጌታቸው አሰፋ ውሳኔ ወደ ሽግግር መንግስት አሸጋጋሪ በሚል ስም የተቋቋመ ኮሚቴ ከህበረተሰቡ ቅቡልነት ለማግኘት ብዙ ጥረት አድርጓል። የተሳካለት ሊሆን አልቻለም። የካቲት 9 2015 ከሶስት በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በዘማሪያስ ሆቴል ለአሸጋጋሪ ኮሚቴው ድጋፍ ለማሰባሰብ የተጠራው ስብሰባ አብረው ፎቶ  ከመነሳት የዘለለ ሌላ ምንም ውጤት ሳያመጣ በተቃውሞ ተበትኗል። በተከታታይ ቀናትም በፕላኔት ሆቴል ከሙያ ማህበራት፣ ከጋዜጠኞች ማህበር፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከነጋዴዎች ማህበር፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ማህበራት ጋር የተደረገው ስብሰባ ሃያ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተቃውሞ ተበትኗል። ከዚህ በኋላም ከመላው ትግራይ ከእያንዳንዱ ወረደ 3 ተወካዮች በመጥራት በደጀን የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት የተደረገው ስብሰባ የኮሚቴውን አባላት ማን መረጣችሁ በሚል ጥያቄ በማፋጠጥ ተበትኗል።

ከዚህ በተጨማሪ ከሰራዊቱ ተወክለዋል የተባሉትን ግለሰቦች ሰራዊቱ ያልመረጣቸው፣ እነ ጻድቃን እንኳን የማያውቋቸው በመሆናቸው ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ከዚህ ውዝግብ በኋላ ነው ጻድቃን የኮሚቴው አመሰራረት ትክክል እንዳልነበር እና ሁሉንም አካታች ሊሆን ይገባዋል የሚል ረጅም ሰነድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “አዘጋጅቶ”  ለአለም ያሰራጨው። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈበት ምክንያት ሪፖርቱ ለአሜሪካ መንግስት እንዲቀርብ ታስቦ የተደረገ እንጂ የመጀመሪያው አድማጭ የትግራይ ህዝብ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።  

ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ ቅቡልነት ያጣው ኮሚቴ የካቲት 13 2015 ስራውን በተመለከተ ሪፖርት ለማቅረብና ግምገማ ለማድረግ በሚሉ አጀንዳዎች ሰበብ  የህዋሃት ስራ አስፈጻሚና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ እንዲቀመጡ አደረገ። ይህን ስብሰባ ከጀርባ ሆኖ የሚመራው ያው ሰላሙን ተቃውሞ የቆመው ቡድን ነው። ይህ ስብሰባ የትም መድረስ ባለመቻሉ የካቲት 15 2015 የሴንትራል ኮማንድና ወታደራዊ ኮማንድ እንዲካተቱበት ተደርጎ ስብሰባው ቀጠለ።

በእዚህ እለት በተደረገው ስብሰባ ደብረጽዮን ከስልጣን እንዲወርድ ተጠይቆ ከስልጣን ከሚወርድ ሞቱን እንደሚመርጥ በፊት ለፊት በስብሰባው ላይ በመናገሩና ደብረጽዮን ከሞንጆሪኖ ቡድን ሰዎች በላይ በህዝብ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የሞንጆሪኖ ቡድን ሴረኞች አካሄድ ችግር ገጠመው። በዚህ ስብሰባ ላይ ደብረጽዮን አፉን ሞልቶ “ዶ/ር አብይ ከፈለግህ በፕሬዚደንትነት መቀጠል ትችላለህ” ብሎኛል በማለት ተናግሯል።   

አሁንም ከገባበት ችግር ለመውጣት የሞንጆሪኖ ቡድን አስቀድሞ የተዘጋጀበትን የተሳታፊውን ቁጥር ያበዛ በተከታታይ የተደረገ ስብሰባ ላይ ተቀመጠ። ስብሰባው ጉባኤ የሚል ስም የተሰጠውና በህዝብ ተወክለናል የሚሉ ነባር አመራሮች፣ የህወሃት የስራ አስፈጻሚና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የሰራዊቱ ኮማንድ እና የሴንትራል ኮማንድ አባላት የተሳተፉበት ነበር። የጉባኤተኞች ብዛት በጥቅሉ 401 ሲሆን 351 ድምጽ በመስጠት የሚሳተፉ፣ 50 ድምጽ መስጠት የማይችሉ ታዛቢዎች ነበሩ። በዚህ ስብሰባ ላይ ጻድቃን አልተሳተፉም ነበር ። ሆኖም ግን በምግበይና ወዲ አሸብር አሸማጋይነት ከሰአት በኋላ ተሳትፏል ። በጉባኤው ላይ ፣ ሰራዊቱ የመረጣቸው ተወካዮች፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከሲቪክ ማህበራት ቢሳተፉም የተወከሉበት መንገድ ትክክል ባለመሆኑና ህወሃት የመረጣቻው በመሆናቸው በህዝቡ እና እንወክለዋለን በሚሉት አደረጃጀት ተቀባይነት ኣላገኙም ። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ሙሉ በሙሉ አልተሳተፉም።

የዚህ የጉባኤ አጀንዳና አካሄድ የሚዘውረው አሁንም የሽግግር ሂደቱን ከኋላ እየተቆጣጠረው ያለው የነጌታቸው አሰፋ ቡድን እንደሆነ በጉባኤው አጀንዳ አቅራቢና ተደራጅቶ በቀረበው ውይይት ባልተደረገበት አጀንዳ አጸዳደቅ የተረጋገጠ ሆኗል።  አጀንዳ አቅራቢው አለም ገበረዋህድ፣ የነጌታቸው አሰፋ ቡድን ቀኝ እጅ ነው። የመጀመሪያው አጀንዳ ጉባኤውን የሚመራ ፕሬዚደየም መምረጥ ሆነ። አሰቀድሞ ድርጅታዊ ስራ በተሰራበት መንገድ ዶ/ር ደብረጽዮን ሊቀመንበር፣ ታደሰ ወረደ ምክትል፣ ሊያ ካሳ፣ ዘውዱ ኪሮስ፣ ሙሉወርቅ ኪዳነ ማሪያም፣ አባላት አድርጎ መረጠ።   ምርጫውን በተመለከተ ጆን መዲድ(ጀ/ል) “አዲስ ፊት ያላየንበት አሳፋሪ ምርጫ ነው” በማለት በስብሰባው ላይ አስተያየቱን ሰጥቶበታል ።  

በዚህ ጉባኤ ላይ በአለም ገብረዋሃድ የተዘጋጀው የሽግግር መንግስት ሰንድ ላይ ውይይት ተደርጎ ስብሰባው ተበተነ። ሰኞ የካቲት 20/2015 አለም ገብረዋህድ የህወሃት ጽ/ቤት ሃላፊ የስራ አስፈጸሚ ኮሚቴ የማእከላዊ አባላት ስብሰባ ጠራ። በስብሰባው ላይም ፕሮፖዛል ይዞ መጣ። ፕሮፖዛሉ የሽግግር መንግስቱ መመራት ያለበት በወያኔ መሆኑን በማተት፣ ደብረጽዮን በፕሬዚደንት ይቀጥል፣ አቶ በየነ ምክሩ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ ሊያ ካሳ የተፈጥሮ ሃብት ክላስተር አሰተባባሪ፣  ወ/ሮ የአለም ጸጋይ የኢንፍራ ስትራክቸር ክላስተር አስተባባሪ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ፣ ዶር እያሱ እርሻ ቢሮ ሃላፊ ፣ ዶር አማኑኤል ሃይሌ የጤና ዘርፍ ሃላፊ ፣ ዶር ኪሮስ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ፣ ወ/ሮ ገነት አረፈ ታክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ሃላፊ ፣ ወ/ሮ አልማዝ ገ/ፃዲቅ ከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊ ፣ ዶር ሃጎስ ጎዲፋይ ፕሬዚዳንት አማካሪ ፣ አቶ ዘበርህ የመሬት አጠቃቀም ሃላፊ፣ ወ/ሮ ምህረት የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ በማድርግ አዲስ ካቢኔ እንዲቋቋም የሚያደርግ ሃሳብ ያቀረበ ነበር፡፡

ይህ ፕሮፕዛል ደብረጽዮንን ሊቀመንበር አድርጎ ብቻ በማቅረቡ እንደ ደብረጽዮን በማእከላዊ ኮሚቴው ውስጥ የሚዋልል አቋም ያላቸውን አባላት ድጋፍ ስላገኘ ጸደቀ። በዚህ ፕሮፕዛል ውስጥ የደብረጽዮን ጉዳይ አንዳለ ሆኖ ከበየነ ምክሩ በስተቀር የተቀሩት ስራ አስፈጻሚ አባላት ቀንደኛ የነጌታቸው አሰፋ ጸረ ስላም ቡድን አባላት ናቸው። የካቢኔው አባላትም በአለም ገብረዋህድ አቅራቢነት በመምጣታቸው ከነጌታቸው አሰፋ ቡድን ውጭ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። አስገራሚው ነገር ጉባኤ እንዲመሩ የተመረጡ ሰዎች እራሳቸው በሚመሩት ስብሰባ ላይ ተመልሰው መመረጣቸው ነው። ደብረጺዮን እና ሊያ ካሳ ጉባኤ መሪዎች ተበለው ተመርጠው ነበር።  

በእንዲህ አይነት ቅጥ አምባሩ በጠፋ የሴራ ሂደት የነጌታቸው አሰፋ ቡድን የሽግግር መንግስቱ ከወያኔ እጅ እንዳይወጣ በማድረግ የራሳቸው ሰዎች በበላይነት የሚቆጠጠሩት መንግስት አቁመው ለኢትዮጵያ መንግስት ውጤቱን አሳውቀዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ የጌታቸው አሰፋ ቡድን ደጋፊዎች የተሰጡት አስተያየት፣ ይህን ወሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት የማይቀበለው ከሆነ እስከመጨረሻው እንደሚታገሉትና ጉዳዩን ወደ አባሳንጆና ኡህሩ ኬንያታ እንደሚውስዱት ነው። ይህ ማለት ጉዳዩን ወደ አሜሪካ መንግስት በማቅረብ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተጽእኖ በማድረግ የትግራይን ሽግግር መንግስት እንዲቀበለው ለማድረግ እቅድ እንደተያዘ የሚያሳይ ነው። አሁን ባላንበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ የቀረበለትን ፕሮፖዛል አልቀበልም ብሏል። ይህን ምላሽ የሰማው ህወሃት እንደገና ስብሰባ ተቀመጧል።  

ዛሬም በወያኔ ውስጥ ያሉ ጸረ ሰላም አመራሮች  አላማቸውን ማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው። የአመጽ እርምጃዎች ለመውሰድ ከሚያስችሉ ዝግጅት አንስቶ በተለያዩ ሰላማዊ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ስልቶች ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈጸም እንደሚችሉ በሙሉ ልብ እየተናገሩ ነው። ብልጽግና ውስጥ በመግባት አብይን መስሎ አብይን ማሸነፍ፣ የአማራ ክልል መንግስትን እና የኤርትራ መንግስትን የሰላም ስምምነቱ የማይደግፉ ሃይሎች አድርጎ በማቅርብ ከማእከላዊ መንግስት መነጠል፣ አልፎም ከማእከላዊ መንግስት ጋር በመሆን መውጋት፤ ይህን ለማደርግ የሚያስችል በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ “ሌሎች ችግሮች በህገመንግስቱ መሰረት ይፈታሉ የሚለው አንቀጽ” እንደሚጠቅማቸው፣ የወልቃይት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት የሚፈታ ከሆነ ህገመንግስቱ ወልቃይት የትግራይ ግዛት አድርጎ ስለሚያስቀምጥ በቅድሚያ ሌላ መፍትሄ ከመታሰቡ በፊት ግዛቱ ወደ ህገመንግስታዊ ባላቤቱ መመለስ አለበት የሚለው ጥያቄያቸው ፍትሃዊ ተደርጎ በፌደራል መንግስቱና በአሜሪካኖች እንደሚታይ፣  ይህ የማይዋጥላቸው የአማራ ክልላዊ መንግስትና  የኤርትራ መንግስት ተቃውመው እንደሚቆሙ፣ ይህን ተቃውሞ ምክንያት በማድረግ በሰላም ስምምነቱ ማስከበር ስም ሁለቱን ታሪካዊ ጠላቶች መውጋት እንደሚቻል፣ በአማራ ህዝብና በኤርትራ ህዝብ መሃል የተፈጠረውን ግንኙነት መበጠስ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ውስጥ ተመልሰን መግባታችን እና ሹመት ማግኘታችን የማይቀር በመሆኑ እንዲያውም በቅርቡ ሹመቱ ይመጣል በማለት ይህን ሹመት ትልቅ ተጽእኖ አሳዳሪ ጉልበት በመከላከያው ውስጥ እንደሚሰጣቸው፣ የፌደራል መንግስቱን መከላከያ አመራሮችን ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረው በወያኔዎች እጅ ባላው ከፍተኛ ሃብት የወያኔ ፍላጎት ፈጻሚዎች ማድረግ እንደሚቻል፣ የሰሜን ጦር ከመጠቃቱ በፊትና በተጠቃበት እለት ከኢትዮጵያ የሰራዊት  አመራሮች መሃል በጥቅማ ጥቅም የገዟቸውን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም በሚሊዮኖች ገንዝብ ስጥተው ማስከዳት የቻሏቸውን ዛሬ መቀሌ ተቀመጦ የኦነግ ሰራዊት አደራጅ የሆኑት አንዳንድ የጦር መሪዎች መመልመል እንደቻሉ ሌሎችንም መመልመል እንደሚቻል እቅድ እያወጡ ይገኛሉ።

በዲፕሎማሲ መስኩ ለሚያደርጉት ስራ አለም አቀፍ የትግራይ ምሁራን ድርጅት እና በውጭ የሚገኙ የስርአቱ ደጋፊዎች በሚያሰባስቡት ገንዘብና መንግስት በሚያቀረበው ገንዘብና እርድታ ተመስርቶ የኢትዮጵያን መንግስት ለማሳጣት  የሚያስችል ዝርዝር የሆነ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በጦር ወንጀለኛነት መንግስትን ሊያስፈርጅ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በተመሳሣይ ግን በወያኔ በትግራይና በሌሎች ክልሎች በራሱ በወያኔ ሃይሎች የተፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር የግድያ፣ ሌሎችንም ዘግናኝ ወንጀሎችን በተመለከተ በተደራጀ መንገድ መረጃ የሚያሰባስብ አካል አለመኖሩ የሚያስገርም ነው። 

 • የሰላም ስምምነቱ ከወታደራዊ ጉዳዮች አንጻር

የሰላም ስምምነቱ ሌላው አካል፣ ወያኔ ሁሉንም ትጥቆቹን ያወርዳል ሰራዊቱንም በካምፕ ያስገባል የሚል ነው። ከትግራይ የሚሰብሰው መረጃ የሚያሳየው በአጉላ እና በአካባቢው የነብሩ ተተኳሽ ያለቀባቸው የተበላሹ ጥቂት ታንኮችና መድፎች ማስረከባቸውን ነው። ከዚህ ውጭ በመረጃ ስማቸው በሚታወቁ ከእይታና የትራንስፖርት መግቢያ የሌላቸው፣ ሚስጥር በመጠበቅ የማህበረስቡ አንድ ወጥ አሰፋፍር ባላቸው በርካታ ቦታዎች ላይ በርካታ ከባድና የቡድን መሳሪያቸውን አስቀምጠዋል።

ሰራዊቱ በካምፕ መሰብሰብን በተመለከተ፣ በመንገድ ዳር ከሚገኙ በቀላሉ በሚታዩ በመቀሌ ዙሪያ፣ ገረብ ግባ፣ምላዛት፣ ሳምረ፣ አዲ ጉደም፣ አራአ ሰገዳ፣  እና በቆላ ተንቤን ወረዳ በአግበ ከተማ ካሰባስቧቸው የሰራዊት አባላት ውጭ በሌሎች በመረጃ ተደግፈው መቅረብ በሚችሉ ከመንገድ በራቁ ለትራንስፖርት አመቺ ባላሆኑ በርካታ ቦታዎች ላይ ወታደራዊ ዝግጅቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የውጊያ ስልት፣ የእግር ጉዞ፣ የወታደራዊ ጽንጸ ሃሳብ ትምህርቶች ያለፈው ውጊያ ግምገማዎች እየተካሄዱ ነው። ለትግራይ ህዝብ  የተላከወን የእርዳታ እህል ወያኔዎች ይህን ሰራዊት ለማሰልጠኛነት እየተጠቀሙበት ነው።

ቀደም ተብሎ የተጠቀሰው ወያኔዎች ለሽብር ስራ እያዘጋጁት ካለው 7000 ከሚቆጠር ልዩ ሰልጣኝ እና በነጻ አወጭ ድርጅት ስም አሁንም ስለጠና እየሰጧቸው ያሉትን የኦሮሞ፣ የአገው፣ የአፋርና ሌሎችንም ነጻ አውጭ ሰራዊትን ስንጨምርበት ወያኔዎች እውን ለሰላም እየተዘጋጁ ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል። ሌላው በከፍተኛ ጥንቃቄ መታየት የሚገባው ጉዳይ ወያኔዎች በጃቸው ያለውን ከፈተኛ ሃብትና ከዚህ ቀደም ሰዎችን በሙስና የማጥመድ ችሎታቸውን በመጠቀም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የማእከላዊ መንግስት ወደ ትግራይ የላካቸው የመከላከያ፣ የፖሊስ የደህንነት አባላት በጥቅም በገንዝብ በሌሎችም ዘዴዎች የመያዝ ስራ መጀመራቸው ነው። ይህ የሙስና ስንሰለት የት ድረስ ሊዘረጋ እንደሚችል በተለይ በሃገሪቱ ውስጥ ከሰፈነው የሙስና ባህል አንጻር መገመት ከባድ አይደለም። በጦርነቱ ወቅት የወያኔ የመረጃ ሃላፊ የነበሩ፣ በረሃ ገብተው ሲያዋጉና ሲዋጉ የነበሩ በወያኔ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ የሰለጡኑ ሰዎች አንዳንዶቹ በቻርተር አይሮፕላን ሲንቀሳቅሱ የነበሩ ዛሬ አዲስ አበባ ከተማ መሃል በነጻነት የሚንቀሳቅሱበት ሁኔታ እያየን ነው። በመንግስት የሚያሳምን መግለጫ እስካልተሰጠበት ድረስ እንደዚህ አይነት ግለሰቦች ያለምንም ስጋት በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቅሱበት ምክንያት የወያኔዎች የሙስና የስራ ውጤት ከመሆን አይዘልም። በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው ግለሰቦች የመቀሌን ኤርፖርት ብቻ ሳይሆን በቦሌ ኤርፖርት ጭምር ወደ ውጭ ሃገር የወጡበት ሁኔታ እንዳለ መረጃዎች አሉ። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ምን ያህል ሰዎች ወያኔ ወደፊት ላቀደው የኢኮኖሚና የሽብር ስራ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል ሌላው መንግስትን እና ህዝብን ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ ነው።

 • ኢኮኖሚያዊና ሁኔታዎች በተመለከተ

በመሰረተ ልማትና በተቋማት ውድመት ደረጃ በትግራይ ውስጥ ወያኔ እራሱ ካደረሳቸው ጥፋቶች፣ ለምሳሌ በአክሱምና በሽሬ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን የኢትዮጵያ መንግስት እንዳይጠቅምባቸው ለማድረግ ከተከናወኑ ጥፋቶች ውጭ ወያኔዎች በአማራና በአፋር ክልል ሆን ብለው ያወደሙትን አይነት የመሰረተ ልማትና የተቋማት ውድመት በትግራይ ውስጥ አልደረሰም። በተቋማት ውስጥ የነበሩ ንበረቶች በተለያዩ አካላት የተዘረፉ ቢሆንም ዘረፋው የተወሰኑ ቦታዎችን የሚመለከት እንጂ በአፋርና በአማራ ክልል ወያኔዎች ሆን ብለው የህዝቡን የመንግስትን ተቋማትን ንበረት በዘረፉበት ደረጃ የተዘረፈ አንዳልሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለምሳሌ ከኮመቦልቻ ደሴ በርካታ ማሽነሪዎች ፣ ጀነሬተሮች በገብረሊባኖስ የተባላው የሞንጀሪኖ ባል እንደዘርፈ እና እንደሽጣችው በሰኔ 15/2014 በአክሱም ሆቴል በነበረው የአመራር ስብስባ ላይ ተገምግሟል፡፡  እንዳውም አንዳንዶቹ ተቋማት በራሱ በወያኔ ትእዛዝና በወያኔ ተባባሪዎች ንብረቱን ለጦርነቱ በግብአትነት እንዲያስረክብ ተደርጓል። ዶ/ር ፋና ሃጎሰ የቀድሞ የትግራይ ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበረች እና ፌዴራል መንግስት መቀሌን ሲቆጣጠር የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ሆና የተሾመች  ቀንደኛ የእነ መንጆሪኖ ደጋፊ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንትነቷ የዩኒቨርስቲዎን የምግብ ማብሰያዎች፣ ፍራሾችና ኮምፕዩተሮች እና ሌሎቸ ንብረቶች ለሰራዊቱ አሰርክባለች። ባሁኑ ወቅት መቀሌን ዩኒቨርስቲ ምንም አይነት የማስተማሪያ ግብአት የሌለው ሲሆን ሃላፊዋ መንግስት ዩኒቭርስቲውን መልሶ እንዲያደራጅ አይኗን በጨው ታጥባ ትምህርት ሚኒስቴርን እየወተወተች ነው ። ሌሎችም መንግስታዊ የሆኑና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የግል ድርጅቶች ከኤሌትሮኒክስ እቃ አንስቶ እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ለጦርነቱ መሳለጥ እንድያዋጡ በደብዳቤ ተጠይቀው በርካቶች አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በትግራይ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ችግር ጦርነቱ ምርት አንዳይመረት በማስተጓገል የእህልና የጥራጥሬና ሌሎችም የምግብ ፍጆታዎች እጥረትና ዋጋ ማሻቀብ ነው። የሰላም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላም የምግብ እርዳታ በገፍ ቢገባም ህዝብ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘው ችግሩ አሁንም አልተፈታለትም። በተለያዩ ቦታዎች የእርዳታ እህል በተለያዩ መጋዘኖች ተከማችቶ ይታያል። ህዝብ እርዳት ሲጠይቅ የሚሰጠው መልስ “እህሉ ለከፉ ቀን የተያዘ ነው” የሚል ሆኗል። በወታደራው መስኩ ትግራይ ውስጥ ካለው ሁኔታ በመነሳት ክፉ ቀን ማለት ምን ማለት እንደሆነ መገመት ከባድ አይሆንም።

ሌላው በትግራይ ውስጥ ትልቅ ችግር የሆነው ጉዳይ በአንዳንድ ግልሰቦች እና ባለስልጣኖች እጅ  የሚንቀሳቅሰው ከፍተኛ ብዛት ያለው ጥሬ ገንዘብ ነው። ይህ ጥሬ ገንዝብ ጦርነቱ አንድ ቀን ሲቀረው፣ ለትግራይ ንግድ ባንክ ተልኮ የነበረውን በወያኔዎች እጅ የወደቀውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ጨምሮ፣ ከአማራና ከአፋር ህዝብና ባንኮች ወያኔዎች በመዝረፍ የሰበስቡት ተደምሮበት እንዲሁም በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ለባንኮች የላከው 5 ቢሊዮን ብርና ከዚህ ውጭ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች በየወሩ ወደ ትግራይ የሚልኩት ከ1 ቢሊዮን እስከ 1.5ቢሊዮን የሚደርስ ጥሬ ገንዝብ ነው። በተለይ ገንዘቡን የያዙ ግለሰቦች ከ20 እስከ 50 % የሚደርስ ወለድ በማስከፈል ለህዝቡ ብድር የሚሰጡ ሲሆን የህዝቡን ስቃይና መከራ እያባባሱበት ይገኛሉ ፡፡

በባንክ የሚደረግ የክፍያ ስርአት ፈጽሞ የለም፣ ገንዘብ ያገኘ ሰው ገንዘብ በእጁ ይዞ የሚዞርበት ከፍተኛ ግብይቶች ሳይቀሩ በካሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል ። አለም አቅፍ ድርጅቶ የሚልኩት ገንዝብ ለደሞዝና ለሌች ስራዎች ወጪ ተደርጎ በካሽ መልኩ ሆኗል ህብረተሰቡ ውስጥ የሚበተነውና የሚከማቸው። በትግራይ ውስጥ ያሉ ባንኮች ከሞላ ጎደል ሁሉም ባዶ ናቸው። ይህን ችግር ለመቅረፍ በሳምንት አምስት ችህ ብር በግለሰብ ደረጃ ወጪ እንዲደረግ ቢወሰነም ውሳኔው በዘምድ አዝማድ፣ በምልጃ በጉቦ ተፈጻሚ መሆን አልቻለም። ይህ የጥሬ ገንዝብ ዝወውር ብዛት በትግራይ ውስጥ ከየትኛውም የሃገሪቱ ክልል በላይ የዋጋ ግሽበት በማስከተል የተራውን ህዝብ ኑሮ  የከፋ እንዲሆን አድርጎታል።  ይህ ብር ቀደም ተበሎ እንደተገለጸው ከትግራይ አልፎ በተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ መበተን በመጀመሩ የውጭ ምንዛሪ የጥቁር ገባያ የሚያጠናክር፣ የደሃውን ህዝብ ህይወት የከፋ የሚያደርገውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚያባባስ እየሆነ እየሄደ ነው። በተጨማሪም እነዚህ ግለሰቦች በራማ በኩል በዶላር እስከ 120 ብር ድረስ እንዲመነዘር በማድረግ ብሎም ብሩ የተለያዩ ንብረቶች እና የመሬት ግዥ ላይ በማዋል የአገሪቱ የመግዛት አቅም በማዳከም ላይ ይኛሉ ፡፡ በዚህም መሰረት እነሞንጀሪኖን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ ብር ከዝነው ያሉ ግለስቦች፣

1 አባዲ ግርማይ { አዋሽ ትራንስፖርት }

2 ሃይለ ላምባ ፣ ትራንስፖርት እና ማደያ

3 ሃይለ አስፍሃ { ማይ ሱር ትራንስፖርት {

4 ሃይላይ ደስታ ሃደራ [ ትራንስፖርት

5 ሙሴ መርሳ

6 እንዳ ሃድጉ ቤተስብ

7 ራሄል ጣፍ

8 አብረሃ ተክለሃይማኖት

9 ሌሎችም

ሌላ ከኢኮኖሚው ጋር መጠቀስ ያለበት ጉዳይ የእነጌታቸው አሰፋ ቡድን በጁ ካስገባው ወርቅና ሳፋያር እንዲሁም ከእነዚህ ማእድኖች ጋር በተያያዘ ከሚያኪሂደው ሽያጭ በተጨማሪ የመቀሌን ህዝብ አገልግሎቶች ለምሳሌ እንደ መብራት አገልግሎት አይነቶቹን ገቢ በቀጥታ የሚቆጣጠር መሆኑ ነው። በቅርቡ በመብራት ክፍያ ላይ 15 ከመቶ ጭማሪ በማድረግ የመቀሌ ህዝብ አፍንጫውን ተይዞ ክፍያ እንዲከፍል እየተደረገ፣ ክፍያው በጥሬ ገንዝብ ብቻ እየተሰበሰበ፣ በሞንጆሪኖ ቡድኖች እጅ በየሰው ቤት የሚቀመጥ ሆኗል። ይህን ክፍያ የሚያሰባስበው የመብራት ሃይል ሃላፊ የሞንጀሪኖ ቤተሰብ ነው ። በሌላው መልኩ ከአንዳንድ የወያኔ ወዳጅ ሃገራትና ከትግራይ ዳያስፖራ ለጸረ ድሮንና ለጦር መሳሪያ መግዢያ በሚል የተሰበሰበው ብዙ ሚሊዮን ዶላር በሞንጀሪኖ አካውንት መግባቱ በወያኔ ግምገማ የተደረገበት ጉዳይ ቢሆንም እስካለነበት ሰአት የተቀየረ ነገር ባላመኖሩ ዶላሩ አሁንም በሞንጀሪኖ አካዎንት ይገኛል።  

ተመሳሳይነት ያላቸው የማፍያ አይነት፣ የወያኔ አመራሮች በቀጥታ እጃቸውን የሚያስገቡባቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተበራክተዋል ። በቅርቡ የመስቦ  ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ እንዲጀምር የቀረበውን ሃሳብ ተፈጻሚ ለማደርግ ፋብሪካው የሚያስፈልገውን የከሰል ድንጋይ ከደቡብ አፍሪካ እና ከአገር ውስጥ አስመጭዎች የሰራዊቱ አመራሮች እንዲሆኑ በወያኔ ተወስኗል ። ፋብሪካው ሲጀመር መቀጠር የሚችሉ ሰራተኞች  የቅጥር መስፈርት የካቲት 25 2015 በ/ገሚካኤል ገብሩ  ፊርማና ማህተም በወጣው ማስታወቂያ ላይ፣ በቁጥር 4) መታገሉን ከትግራይ ሰራዊት ማምጣት ይሚችል፣ 5) ባላፈ ሁለት አምት ውስጥ ራሱን እና ቤተሰቡን ያታገለ 6)  ቅድሚያ የሚሰጠው ከአንድ ቤት ሁለት እና ከዛ በላይ ላታገለ የሚሉ መስፈርቶች ተካተውበታል። የወያኔ መሪዎች በኢኮኖሚ መልኩ ለ27 አመት ያካባተቱን ሃብት በመጠቀም በትግራይ ውስጥ ህዝቡ እነሱ የፈለጉትን ነገር እንዲፈጽም ማድረግ እንደሚችሉ ሙሉ እምነት ያላቸው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብም ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ ማድረግ እንደሚችሉ ተማምነው እየተንቀሳቅሱ ናቸው።

 • ማህበራዊ ሁኔታን በተመለከተ

ትግራይ ውስጥ የሰላም ስምምነት ይደረግ እንጂ ማህበረስቡ ሰላምና መረጋጋት እንደራቀው ነው።  በጦርነቱ የተነሳ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች አሁንም በችግር ላይ ናቸው። በመሳሪያ የተደገፈ ዘረፋ፣ የመሳሪያ ሽያጭ፣ ጾታዊ ጥቃት የመሳሰሉት ወንጀሎች እንደቀጠሉ ናቸው። በመቀሌ ከተማ በአንድ ሳምንት ብቻ 31 ሰዎች በጩቤ ተወግተው አይደር ሆስፒታል ለህክምና ገብተዋል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ በተለይ ህጻናት ሴቶች አረጋውያን የገቡበት የስነልቦና ቀውስ ለመገመት ከሚቻለው በላይ ነው። የልጆቻቸው መኖርና አለመኖር ሃቁ ያልተነገራቸው ወላጆች በመርዶ ይደርሰኛል ስጋት በሰቀቀን እየኖሩ ነው። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እጅና እግሩ የተቆረጠው አይኑ የጠፋው ሌላም የአካል ጉዳት የደረሰበት በርካታ ወጣት በከተሞች ማየት ራሱን የቻለ የስነልቦና ችግር ፈጣሪ ሆኗል።

ወያኔ በጀመረው ጦርነት ህይወቱን ያጣው፣ አካሉ የጎደለው የትግራይ ወጣት ብዛት በውል አይታወቅም። በልጆቻቸው ድጋፍ የሽምግልና እድሜያቸውን በሰላም እንገፋለን ያሉ በርካታ ወላጆች ያለ ጧሪና ቀባሪ ቀርተዋል። ስጋትና ፍራቻ የህዝቡ የቀን ተቀን ህይወት ድርና ማግ ሆኗል። እድል ቢያገኝ ከትግራይ ነቅሎ ለመውጣት የሚፈልገው ሰው ብዙ ነው። የተቻላቸው በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ቤታቸውን እየሸጡ ጉቦ በመስጠት በተለያዩ አቅጣቻዎች በአየርና በመኪና ከትግራይ እየውጡ ነው። በዚህ ላይ በጦርነቱ ወቅት የቆሙ የትምህርት የጤና ሌሎችም  መንግስታዊ አጋልግሎቶች ስራ አልጀመሩም። ባጭሩ የሰላም ስምምነት ይፈረም እንጅ የትግራይ ህዝብ ሰላም አላገኘም። በፖለቲካውና በወታደራዊ መስኩ የሚታየው የፀረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ የትግራይ ህዝብ ሰላም እንዲህ በቀላሉ የሚያገኝ አይመስልም።

በህዝቡ ውስጥ ወያኔ ችግሬን ይፈታልኛል የሚል እምነት እየተመናመነ መሄዱን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አሉ።  በፖለቲካ መስኩ የትግራይን ችግር የፈጠሩና ያባባሱ የፖለቲካ ሰዎችን ለማስወገድ ከተጀመረው ጥረት በተጫማሪ ህዝብ ወያኔ የተመሰረተበትን የካቲት 11ን እንዲያከበር ተጠይቆ ይህ በአል የኔ አይደለም በሚል በመላው ትግራይ በበአሉ ባለመገኘት አቋሙን ገልጿል። በወያኔ ጥሪ የተደረገላቸው ከዚህ ቀደም ወያኔ ዝለሉ ሲላቸው ስንት ሜትር በማለት ይጠይቁ የነበሩ ማህበራት ሳይቀሩ በበአሉ ላይ አልተገኙም። በአንዳንድ እንደ ሓሓይለ የመሰሉ የማእከላዊ ዞን ወረዳዎች ወያኔ በሹመት የላካቸውን አሰተዳዳሪዎች ህዝብ አንቀበልም ያለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጠቃላይ በአሁን ወቅት ስደት ፣ ህገወጥ የሰው ዝውውር ፣ ዝርፍያ ፣ የኑሮ ውድነት ፣ ፆታዊ ጥቃት እና የመሳሰሉት ችግሮች ከሰላም ስምምነት በኋላም ቢሆን ያልተፈቱ ችግሮች ሆነው ቀጥለዋል።

 • የዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ በተመለከተ፣

ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ዛሬ በትግራይ ውስጥ፣ ለውጥ በሚፈልገው የትግራይ ህዝብና የህወሃት ወጣት አመራርና በጸረ ስላም ሃይሉ የነጌታቸው አሰፋ ቡድን መሃል ያለውን ትግል በከፍተኛ ደረጃ ወደ ጸረ ሰላም ሃይሉ እንዲያዘነብል የሚያደርገው ጸረ ሰላም ሃይሉ በዲፕሎማሲ መስኩ ያለው ድጋፍ ነው። ይህ ድጋፍ የትግራይን ሰላም ብቻ ሳይሆን በጥንቃቄ ካልተያዘ የኢትዮጵያን እና የቀጠናውን ሰላም የማናጋት አቅም አለው። ይህ አቅም የተገነባው በሶስት መሰረታዊ ዋልታዎች ላይ ነው።

የመጀመሪያው፤ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ገና በትግሉ ጊዜ የጀመረ የወያኔ መሪዎች የአሜሪካን ጥቅም በምስራቅ አፍሪካ ለማስጠበቅ መሳሪያ ለመሆን ዝግጁነታቸውን ከገለጹበት ዘመን ይጀመራል።  ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ በሂደት እንደታየው የአሜሪካ መከላከያ ተቋም፣ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ የስለላ ድርጅቶች ከወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩበት፣ ወያኔ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የአሜሪካንን ቆሻሻ ስራ ፈጻሚ የሆነበት ሁኔት ተፈጥሯል። ወያኔ የአሜሪካኖችን ጥቅም ለማስከበር ከፔንታጎን ጀነራሎች ጋር ተስማምቶ አንድን ሏላዊ ሃገር ሶማሊያን እስከመውረር ደርሷል። ከስለላ ድርጅቶቹ ጋር በመተባባር የግድያ የአፈና ስራ ሲሰራ ነበር። የወያኔ ጀነራሎች የፔንታጎን፣ የወያኔ ሰላዮች የሲአይኤና የእንግሊዙ ኤም አይ 6 ቤተኞች ነበሩ።  ለ27 አመት የአሜሪካንን እና የምእራባውያን ጥቅም በማስጠበቅ ወያኔዎች ለእነዚህ መንግስታት የዋሉትን ውለታ እነዚህ መንግስታት የሚረሱት አይደለም። በተለይ በምእራቡ አለም ቁልፍ የሆነውን የሰው ለሰው ግንኙነት ኔትዎርክ ወያኔዎች በ27 የስልጣን ዘመናቸው በሚገባ ያደራጁት በመሆኑ በየትኛውም የምእራብ መንግስታት ተቋማት ውስጥ ሊተባበሯቸው የሚችሉ በርካታ ወዳጆች አፍርተዋል። ይህ የግንኙነት መረብ ከነጩ ቤተመንግስት አንስቶ፣ በመከካከያ፣ በስለላ ድርጅቶችና በሚድያ ተቋማቱ የተዘረጋ ለመሆኑ ወያኔ የአንድን ነጻ ሃገር የመከላከያ ሰራዊት አጥቅቶ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ በከፈተበት ወቅት ከአሜሪካና ከምእራብ መንግስታ እንዲሁም ከሚድያ ተቋማቱ ካገኘው ምንም ይሉኝታ በሌለው ድጋፍ ተገልጿል።

ሁለተኛው፤ ለጸረ ሰላም ሃይሉ የዲፕሎማሲ አቅም የሚሰጠው በጁ ያለው ሃብት ነው። ብዙ ጊዜ ስለሃብት ሲወራ ሰዎች የሚጠቅሱት ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ ከሀገር በተጭበረበረ ሰነድ አማካይነት ከንግድ ልውውጥ ጋር ተያያዞ ከኢትዮጵያ ስለወጣው ዶላር ፍሮብስ የተባለው መጽሄት ያቀረበውን ሃተታ ነው። ፍሮብስ ወያኔ ስልጣን በቆየባቸው 17 አመታት 17 ቢልዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ከሃገር መውጣቱን አስነብቦ ነበር። ይህ በአመት አንዲ ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ዘረፋ ከኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔዎች የዘረፉትን ሃብት ብዛት በጥቂቱ ብቻ የሚገልጽ ነው። በተጭበረበረ ደረሰኝ ዶላር የሚያወጡት ሁሉም ወያኔዎች ስላልነበሩ 17 ቢሊዮኑ በወያኔዎች ብቻ ካገር የወጣ አድርገን ማየት አንችልም።

በሌላ መንገድ ግን በቀጥታ በወያኔዎች ተዘርፎ ካገር የወጣ ገንዝብ ከ50 እና 60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሁለቱን የዚህ ገንዘብ ምንጮች እንጥቀስ። ወያኔ ኢትዮጵያውያን ከመላው አለም ከባንክ ውጭ ገንዝብ ለዘመዶቻቸው የሚልኩባቸውን መንገዶች በሙሉ ለብቻው መቆጣጠር ችሎ ነበር። በአለም ባንክ ግምት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በአመት ከ3 እስከ 4  ቢሊየን ዶላር ወደ ሃገር ቤት እንደሚልክ ይነገራል። አብዛኛውን ገንዘብ ባንክ ከሚሰጠው በላይ ህገወጥ በሆነ መንገድ ሲመነዘሩ የነበሩ የወያኔ ባላስልጣናትና ሸሪኮቻቸው ነበሩ። ዛሬም አላቆመም።  ከዚህ ገንዘብ በአማካይ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር መመንዘር ከተቻለ በ30 አመት 30 ቢሊየን ዶላር ወያኔዎች ወደ ውጭ ማሸሽ ችለዋል። በዚህ ላይ ስልጣናቸውን በመጠቀም ወያኔዎች በሱዳን እና በጅቡቲ በኩል ያለማንም ጠያቂ በቀጥታ እያወጡ የሸጡትን ሰሊጥ ወርቅና ሳፋየር ሲንደምርበት ዘረፋው ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ያሳየናል።

በህገወጥ መንገድ እየወጣ ይሸጥ የነበረው ሰሊጥ ኢትዮጵያ ከቡና ከምታገኘው ከነበረው የውጭ ምንዛሪ የሚበልጥ እንደነበር ስለእዚህ ህገ ወጥ ንግድ እውቀት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ። ይህ በህገ ወጥ መንገድ በአውሮፓና በአሜሪካ ባንኮች የተከማቸ ገንዘብ ወያኔዎችና ዘርማንዘሮቻቸውን የድሎት ህይወት እንዲኖሩ ማስቻል ብቻ ሳይሆን፣ ገንዝብ ማንንም ምንም መግዛት በሚችልባቸው የምእራብ ሃገራት፣ የመንግስት ባላስልጣናትን ፖለቲከኞችን፣ የሚድያ ተቋማትና ጋዜጠኞችን ሌሎችንም ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ግለሰቦችን መግዛት አስችሏቸዋል። የአሜሪካ መንግስት ለጥቅሙ ሲል ወያኔን በመደገፍ ከወሰደው ኢትዮጵያን የማጥቃት እርማጃዎች በተጨማሪ ወያኔዎች በጃቸው ያለውን ገንዘብ በመጠቀም የአሜሪካ መንግስት ይህን ውሳኔ እንዲወስን ተጽእኖ አሳዳሪ ግለሰቦችን በመግዛት የሚፈልጉትን ማስወሰን እንደቻሉ መታወቅ አለበት።

ሶስተኛው የትግራይ ዳያስፖራ ነው። የትግራይ ዳያስፖራ ስንል ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ከወያኔ ጋር በቅርበት በተሳሰረ መንገድ የተፈጠረውን ዳያስፖራ ማለታችን ነው። ይህ አካል በውጭ ሃገር የተፈጠረለት የመማር፣ በድሎት የመኖር እድል በከፍተኛ ደረጃ ከወያኔ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑ ይታወቃል። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ በቀጥታ ከወያኔ ከፍተኛ እና መካከለኛ ደረጃ መሪዎች ጋር በቀጥታ በቤተሰብነት በዝምድና የተሳሰረ ነው። ይህ አካል ከየትኛውም በውጭ ከሚኖር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በላይ የገንዘብና የድርጅት አቅሙ የጎለበተ ነው። ወያኔ የከፈተውን ጦርነት በዲፕሎምሲና በገንዝብ ምን ያህል ለመደገፍ እንደሚንቀሳቀስ ታይቷል። የትግራይ ዳያስፖራ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተቃውሞ ሰልፍ የወጣበት ምክንያት ውግንናው፣ ጸረ ሰላም ከሆነው ሰላም ፈላጊዎችን ተንበርካኪዎች በሚል ከፈረጀው የትግራዩ የወያኔ ቡድን ጋር ስለሆነ ነው። ዳያስፖራው የሰላም ስምምነቱን ተቃውሞ ያወጣው መግለጫ ላይ የሰላም ስምምነቱን የፈረሙትን ግለሰቦች “ተንበርካኪ” በሚል ቃል መግለጹ የተራ አጋጣሚ አይደልም።

ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ዋልታዎች ላይ የቆመው የጸረ ሰላም ሃይሉ የዲፕሎማሲ ጉልበት ሊያስፈጽማቸው የተነሱት ግልጽ አላማዎች አሉት። እነዚህ አላማዎች ከአሜሪካ መንግስት ጋር በቅርበት በመነጋገር የተቀረጹ የአሜሪካንን መንግስት ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው።

የመጀመሪያው ወያኔን እንደ ድርጅት አትርፎ፣ የትግራይ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ በተጠያቂነት እንዲቀርቡለት የሚፈልጋቸውን ነባር የፖለቲካ የደህንነትና ወታደራዊ አመራሮች ከተጠያቂነት ነጻ ማድረግ፣

ወያኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረውን ያልተገባ ድርሻ በአዲስ መልኩ ማስቀጠል በተለይ የወያኔ ባልስጣናት በዘረፋ በሃገር ውስጥ ያካበብቱ ሃብት እንዳይነካባቸው ማድረግ። ወያኔዎች ጥቃት ሰንዝረው መሳሪያውን በገፈፉትና ሰራዊቱን ባረዱበት የመከላከያ ተቋም ውስጥ መልሶ ማካተት፣

በኢትዮጵያ በኤርትራ መንግስት መሃከል ተፈጥሮ የነበረው መልካም ግንኙነት እንዲሻክር፣ እንደቀድሞው ኢትዮጵያና ኤርትራ በጎሪጥ የሚተያዩ፣ ቢቻልም ወደሌላ ጦርነት እንዲገቡ ማድርግ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካኖች ጉያ ውስጥ የተወሸቀ የአሜሪካኖችን ጥቅም አስከባሪ መንግስት እንዲሆን ነው። በመጪው ሳምንት ውስጥ የአሜሪካው መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን የሚጎበኘው እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ አላማዎች ለማሳካት ነው። ለዚህ እንደካሮት የሚያገለግሉ የገንዝብ እርዳታ፣ ወደ አግዋ መመለስ የመሳሰሉ ጉዳዮችን ይዟል። በዱላ መልኩ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ቀውስ ማባባስ የሚችል መሆኑን መጠቆም ነው።   

 • እንዴት ከዚህ ችግር መውጣት ይቻላል።

በቅድሚያ ከትግራይ ጋር የተያያዘውና ትግራይ ውስጥ የሚታየው ችግር የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የተቀረው የኢትዮጵያም ህዝብም ችግር መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ጦርነቱና ከጦርነቱ ጋር የተፈጠረው መመሰቃቅል ሁሉንም ህዝብ ሁሉንም ክልል ያዳረሰ ነው። ሞትና መፈናቀል፣ መዘረፍ መዋረድ መደፈር መጠኑ ይለያይ እንጂ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ተከስቷል። የኢኮኖሚው ምስቅልቅልም፣ ህዝብን ለከፍተኛ ስቃይ እየዳረገ የሚገኘው የኑሮ ወድነት፣ እየተስፋፋ የሄደው ሌብነት ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ጦርነቱ በፈጠረው የተመቻቸ ሁኔታ ወስጥ የተስፋፋ ነው። በዲፕሎማሲው መስክ እየመጣ ያለው ጫና ቀጠናውን ሌላ ትርምስ ውስጥ የሚከት ነው።  

ከጦርነቱ ርቆ በሃገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ይህ ጦርነት በሞት የቀጠፈው የሰው ህይወት ብዛት ትግራይ ውስጥ ደርሷል ከሚባለው በመቶ ሽዎች ከሚቆጠር እልቂት ወጭ ሌላ መረጃ የለውም። የሚሰጠው ስለሌለ። በሚገባ አልተነገረም እንጂ እልቂቱ በሌሎች ቦታዎችም አሰቃቂ ነበር። በቅርቡ በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር በጦር ሜዳ ላይ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች መርዶ ለቤተሰባቸው ተነግሮ ነበር። በምስራቅ ጎጃም ብቻ የ8020 ሰዎች ሞት መርዶ ተነጓሯል።  ቀደም ብሎ የተነገረ በምስራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ ከሸበል በረንታ ወረዳ ብቻ ከዘመቱ ሚሊሻዎች መሃል በአንድ እለት በአቀስታ ግንባር ዶባ ተራራ ላይ 19ኙ ተሰውተዋል። እነዚህ የሚሊሺያ አባላት ያለአባት ትተዋቸው የሄዱ የታዳጊ ልጆቻቸው ብዛት 96  ነው። በመላው ሃገሪቱ ከዚህ ጦርነት ጋር ብቻ በተያያዘ ያለቀውን የህዝብ ብዛትና ጥሎ ያለፈውን ሰቆቃ ከእነዚህ ሁለት መረጃዎች መገመት ይቻላል። በመሆንም የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ሂደት በተመለከተ ለህዝብ ወቅታዊ መረጃ የማቅረብ ግዴታ አለበት።   

የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሰላም እጦት ቀውሶች እርስበርስ የተቆራኙ ናቸው። ዝርዝሩ ወስጥ መግባት አያስፈልግም። የዚህ ጽሁፍ አላማ በትግራይ ውስጥ ባለው ችግር ላይ ያተኮረ በመሆኑ ወደዛው እመለሳለሁ።

የትግራይ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚገኝበት ችግር እንዲወጣ ከተፈለገ የኢትዮጵያ መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በተሰጠው ስልጣን የሚከተሉትን እርምጃ ቢወስድ በሚል ምክረ ሃሳቤን አቀርባለሁ። ምከረ ሃሳቡን ለትግራይ በጎ የሚመኙ በትግራይ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ወጣት ፖለቲከኞች እንደሚደግፉት ማሳወቅ እፈልጋለሁ።

ሀ) በፖለቲካ ዘርፉ

የፖለቲካው መፍትሄ በትግራይ ውስጥ ዛሬ የትግራይ ህዝብ ወያኔን እንዴት ያየዋል፣ በወያኔ አመራራ መሃከል ጸረ ሰላም የሆነው ሃይል ምን እየሰራ ነው፣ ሰላም እንዲስፍን የሚፈልገውስ አካል ምን እያደረገ ነው ከሚለው የወቅቱ የትግራይ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ መሆን አለበት።

በፖለቲካ መስኩ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የሽግግር መንግስት የማቋቋም ዋናው ሃላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት ስለሆነ መንግስት የማቆሙን ስራ በተደራጀ መንገድ ለግልና ለቡድን ጥቅማቸው መቆጣጠር ከሚፈልጉ የተደራጁ አካላት ነጻ ማድረግ መቻል አለበት። እስካሁን የተሄደበት መንገድ ህዝብ አምሮ የሚጠላቸውን እና የሚቃወማቸውን በዚህ አጋጣሚ ከጫንቃው ላይ ሊያነሳቸው የሚፈልጋቸው የወያኔ አመራሮች የልብ ልብ የስጠ ለለውጥ የተነሳሳውን በወያኔ ውስጥ ያሉትን ወጣት አመራሮችና ህዝቡን እራሱን ተስፋ የሚያስቆርጥ አካሄድ ባስቸኳይ መቆም መቻል አለበት።

አሁን በትግራይ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር በቅድሚያ በሽግግር መንግስቱ ፈጠራ ሂደት፣ ትልቁን ስልጣን እና መብት፣ የመከራው ዋናው ገፈት ቀማሽ የሆነው የትግራይ ህዝብ የሚቆጣጠረው እንዲሆን ማድረግ ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት ቀድሞ የሚያውቃቸውን ወይም እራሱ ያደራጃቸውን ወይም በራሳቸው የተደራጁ የጥቂት ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከማመን የትግራይ ህዝብን ማመን የተሻለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገዋል። የትግራይ ህዝብ ሰላምና ፍትህ እንዲያገኝ ከገባበት የህይወት መከራ እንዲወጣ በንጽህና ከሚታገሉ ወጣት ፖለቲከኞች ጋር ተቀራርቦ መስራት የሚኖረውን ጠቀሜታ መረዳት ያስፈልገዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የብልጽግና መንግስት ከዚህ ቀደም እንዳደረገው የራሱን የብልጽግና ሰዎች የትግራይ ጊዜያዊ አሰተዳዳሪዎች አድርጎ መሰየም አይችልም። የዚህ አይነቱ ሙከራ ተሿሚዎቹን እንደ ወራሪ ሃይል  አድርጎ ህዝብ እንዲያቸው በማድረግ ከዚህ ቀደም የተከሰተው የፖለቲካ ችግር እንዲከሰት ያደርጋል። ለጸረ ሰላም ወያኔዎችም ተቃውሞና አሻጥር የሚመች ሁኔታ ይፈጥራል።

በሌላ መልኩ የብልጽግና ሰዎች የቀድሞ ጓደኞቻቸውን መልሰው የትግራይ ጊዚያዊ መንግስት እንዲቆጣጠሩ የሚያደርግ ሂደት ከፈቀዱ በትግራይም ይሁን በተቀረው ኢትዮጵያ ሰላም የመጥፋቱ ሁኔታ እንዲቀጥል ከማድረግ እንደማይመለሱ ለማሳየት ሞክረናል። ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል በሚል ብሂል የሚመራ የሚመስለው የማእከላዊ መንግስት አካሄድ ሰይጣን ሁል ጊዜም ሰይጣን መሆኑን መረዳት ያስፈልገዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት መንግስት በሃገሪቱ የደሃ ልጆች እጃቸው በደም የተጨማለቁ ግለሰቦችን መልሶ ወደ ስልጣን ማምጣት የሚል አንቀጽ አልተካተተበትም። እነዚህ ግለሰቦች ድጋሚ እድል ቢያገኙ በሃገርና በህዝብ ላይ ከሚያስከትሉት ውድመት በተጨማሪ የጥፋት እጃቸውን በማን ላይ በቅድሚያ ለማንሳት ሲዶሉቱ እንደሚውሉ የአዲስ አበባው መንግስት አልሰማ ከሆነ ልንነግረው እንችላለን። በህጻናት ጓንቲ በሚያሽሞነሙኗቸው፣ ከዚህ ሁሉ እልቂትና ውድመት በኋላ ምንም እንዳልሆነ በሚያመስል ደረጃ በሳቅና በፈገግታ የሚያቅፏቸው የወይን ብርጭቋቸውን እያነሱ ለጤናቸው በሚጠጡላቸው የብልጽግና አመራሮች ላይ ነው። አሁንም በድጋሚ ሰላም ፈላጊው በወያኔ ውስጥ ያለው የአመራር አካል የሚያነሳው ጥያቄ “መቼ ነው የፌደራል መንግስቱ በፕሪቶሪያው ስምምነት የተሰጠውን የሽግግር መንግስት የማቆም ስልጣን ተጠቅሞ መብቱ የሌላቸውን የወያኔ አመራሮች ጊዜያዊ መንግስት የማቆም ሆነ ሂደቱን የማስጀመር መብት የላችሁም የሚላቸው? እነዚህ ሃይሎች እየተሰባሰቡ ደብረጽዮን ፕሬዚደንት ጻድቃን ምክትል አድርገናል እያሉ መግለጫ ሲያወጡ ዝም ብሎ የሚያያቸው እስከመቼ ነው? የሚሉ ናቸው?

በሌላ በኩልም የፌደራል መንግስቱ የትግራይን ጊዜያዊ መንግስት በወታደር እጅ ማስያዝ አይችልም ። በወታደራዊ ስሌት አደገኛ ነው።  ለከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ፣ ለወያኔ አመጽ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጣሪ ስለሆነ ሊታሰብ አይገባውም።

ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው። በየቀበሌው  ኗሪ የሆነው የትግራይ ህዝብ በአካል በማሰባሰብ በጊዚያዊነት የሚያስተዳድሩትን እየመረጠ በሁሉም እርከኖች እንዲሾማቸው ማድረግ።  ይህን አሰራር የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በተቆጣጠረባቸው ቦታዎች በሙሉ በስራ ላይ መዋል የሚቻል ነው። እያንዳንዱን ቀበሌ በጊዜያዊነት የሚያስተዳደሩ፣ በወረዳ ደረጃ የሚወከሉ ሰዎቹን እየመረጠ፣  ወረዳቸዎችም  በዞን የሚወከሉትን እየመረጡ ዞኖችም ትግራይ የሚያስተዳድሩትን ሰዎች መምረጥ የሚችሉበትን ብዙ ወጪ ግዜና ጉልበት የማይጠይቅ አሰራር በስራ ላይ ማዋል ይችላል። ይህ አሰራር ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ተደርጎ በጊዜያዊነት በደንብ ሰርቷል።

ከዚህ የአስተዳደር ስራ ጋር እያንዳንዱ ቀበሌ ሰላሙን የሚያስጠብቁለትን ራሱ የመረጣቸውን ማእከላዊ መንግስት የሚያስታጥቃቸውን ግለሰቦች እንዲመርጥ በማድረግ ማስታጠቅና ማሰልጠን ነው። ይህን አሰራር በመላው ትግራይ ለመፈጸም የሰላምና የደህንነት ችግር ካለ፣ ችግር በሌለባቸው ቦታዎች መጀመርና በሂደት ወደሌሎች ከባቢዎች ማስፋት ይቻላል። በዚህ መንገድ ለተመረጡ የአስተዳደር እርከኖች በጀት መልቀቅና በፍጥነት መንግስታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ማድረግ ነው። ይህ ተግባር እንዲሳካ ለእውነተኛ ሰላም የቆሙ በወያኔ አመርራና ከዛም በታች ባሉ የድርጅቱ እርከኖች ውስጥ ያሉ ተባባሪዎችን ድጋፍ መንግስት በቀላሉ ማግኘት ይችላል።  የመከላከያ ሰራዊቱ ባልገባቸው ቦታዎች መግባት የሚቻልበትን ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር ተያይዥነት ያላቸውን ወታደራዊ ውሳኔዎች ተፈጻሚ በማድረግ በመላው ትግራይ የጸጥታ ሃላፊነቱን መረከብ ነው። ይህን ለማድረግ፣

ለ) በወታደራዊ ዘርፉ መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች

 • የወያኔ መሪዎች የትጥቅ መፍታቱን ስምምነት ጥሰው በተለያዩና በሚታወቁ ቦታዎች ያከማቿቸውን መሳሪያቸው በአፋጣኝ እንዲያስረክቡ ማድረግ
 • በተለያዩ በሚታወቁ ቦታዎች አሰባስበው አሁንም ስልጠና የሚሰጧቸውን የሰራዊት አባላት ስልጠና አቁመው እነዚህ የሰራዊት አባላት መንግስት በሚያዘጋጀው በቀላሉ በሚታዩና መደረስ በሚችሉ ካምፖች እንዲሰባሰቡ ማድረግ፣
 • ለሽብር ስራ መልምለው የሚያዘጋጇቸውን ሰዎች ስልጠና እንዲያቆሙና አባላቱ እንደሌሎች የትግራይ ሰራዊት በካምፕ እንዲገቡ፣
 • የትግራይን ሰላም ማረጋጋትና ህግ የማስከበር ስራ በሁሉም አካባቢዎች በህዝብ የተመረጡ የሰላምና መረጋጋት አባላት በሃላፊነት እንዲመሩት ማድረግ፣ በእነዚህ አባላት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በወንጀል የተካፈሉ የመከላለካይ የደህንነትና የፖሊስ አባላት መሳተፍ የሚችሉ መሆናቸውን ግልጽ መመሪያ ማስቀመጥ

ሐ) በኢኮኖሚ ዘርፉ መወሰድ የሚገባው እርምጃዎች

 • ህዝብ ጊዚያዊ አስተዳደር ባቆመባቸው አካባቢዎች በሙሉ የመንግስት አስተዳደር ማስጀመር የሚቻልበትን በጀት በቀጥታ በመመደብ ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ። ጤና ጣቢያዎች ት/ቤቶች ስራ እንዲጀመሩ ጊዚያዊ መንግስቱ መቀሌ ላይ እስኪቋቋም መጠበቅ አያስፈልግም።
 • በትግራይ ውስጥ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የተሰበሰበ የውጭ ምንዛሪና የሃገር ውስጥ ገንዘብ ወርቅና ሌሎች ማእድናት ተሰብስቦ በጦርነት ለወደሙ አካባቢዎችና በጦርነቱ የተነሳ አሳዳጊ ላጡ ህጻናት እንዲሁም ጧሪ ቀባሪ ላጡ አረጋውያን ወላጆች በስራ ላይ እንዲውል ማድረግ። ይህ ሃብት ከዚህ አላማ ውጭ ለሌላ ተግባር ወደ ሌላ ቦታ የማይሄድ መሆኑን ለትግራይ ህዝብ ግልጽ ማድረግ።
 • ህገወጥ በሆነ መንገድ ጦርነቱን ሽፋን ተደርጎ፣ በተዘረፈ ገንዝብ የተገዙ የህዝብ መሬቶችን ወደ ህዝብ ማስመለስ።
 • በተቻለ ፍጥነት የገበያው ልውውጥ ለትንንሽ ግብይት ካልሆነ በስተቀር ሌላውን በባንክ በኩል እንዲሆን ማድረግ፣ ከተወሰነ ገንዘብ በላይ በካሽ ገንዘብ ይዞ መገኘት የሚያስጠይቅ ማድረግ፣

መ) በማህበራዊ ዘርፉ

በትግራይ ውስጥ የሚገኝ ሰላም ከማንም በላይ የሚመለከተው የሚጠቅመው ራሱን የትግራይን ህዝብ ስለሆነ የትግራይን ህዝብ ያገለለ የሰላምና መረጋጋት ስራ የህግ ማስከበር ስራ ሊኖር አይገባውም። በመሆኑም፤

 • በካድሬዎች የተሞላውና በጉቦ የነቀዘው ፍርድ ቤት በጊዚያዊነት አግዶ ፍትህ ከቀበሌ ጀመሮ ህዝብ በመረጣቸው የሸንጎ አባላት በሁሉም እርከኖች እንዲሰጥ ማድረግ፣
 • የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት የማስጠበቁ ሃላፊነት ህዝብ በመረጣቸው የሰላምና መረጋጋት ኮሚቴ አባላት አማካኝነት በከፈተኛ የህዝብ ድጋፍ ተፈጽሚ በማድረግ ዘረፋን፣ ወሲባዊ ጥቃትን ሁከትና ግድያን ማናቸውም ህገወጥ የመሳሪያ የገንዝብና የሰዎችን ዝውውር መቆጣጠር፣
 • የፌደራል መንግስቱ አካል ሆነው በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ አካላት በከፍተኛ ዲሲፕሊን እና ህዝብ አክባሪነት ከህዝቡ ጋር ተቀራርበው የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠርና ስራዬ ብሎ እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር። ካሁኑ የጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ የሚችል ከማእከላዊ መንግስት በተመደቡ አካላት ዘንድ የሚታይ ጉቦኝነት ህዝቡን ከማስመረሩ በፊት በአጭር እንዲቀጭ ማድረግ።
 • በተለይ በሙስና ስራ የተካኑና ሙስንን በመጠቀም የመንግስት ባለስልጣናትን የማጥመድ ልምድ ካላቸው የወያኔ አመራሮችና ወኪሎቻቸው፣ የፌደራል መንግስቱ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ አመራሮች እንዲርቁ ጥብቅ መመሪያ መስጠትና መቆጣጠር። ካሁኑ እየታዬ ያለውን አደገኛ ከሆኑ አካላት ጋር የሚደረግ መቀራረብ ባስቸኳይ ማስቆም።
 • በፕሪቶሪያው ስምምነት የተቀመጠውን የሽግግር ሂደት ፍትህ የትግራይን ህዝብ ባካተተ መልኩ በፍጥነት ተግባራዊ የሚሆነበትን መንገድ አቅዶ መንቀሳቅስ። 

ሠ) በዲፕሎማሲ ዘርፉ

ትልቅ ጥንቃቄ የሚያስፈገው ዘርፍ ነው። በአለም ላይ የተፈጠረው አዲስ የሃይል አሰላለፍ፣ በተለይ አሜሪካንን ብቸኛ ለእለ ሃያል ሃገር ያደረገው ዘመን ማብቃት፣ አሜሪካኖችን የሚይዙትና የሚጨብጡትን እያሳጣቸው ነው። የአፍሪካ ቀንድ አንዱ ከተጽኖአቸው ውጭ እንዲወጣ የማይፈልጉት ስትራተጂክ ቀጠና ነው። ከወያኔ ጋር የሙጥኝ ብለው የተጣበቁበት አንዱ ምክንያት ወዳጃቸው ወያኔ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ከወጣ በዚህ ቀጠና በሎሌነት የሚያገለግለን አካል አይኖረንም የሚል ስጋት ነው። የአሜሪካኖች አካሄድ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስኮች እየጨመቁ ወያኔን በኢትዮጵያ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪነቱ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። አሜሪካኖች  በእርዳታ ስም የሚሰጡትን ገንዘብ ለመልቀቅ፣ ከአለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ብድር እንድታገኝ ወደ አገዋ እንደትመለሰ ቅደመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው አይቀርም። ይህ ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ወያኔን እንደ ድርጅት ማዳን ነው። ወያኔ የሚፈልገውን በተለይ ወልቃይትን በወያኔ አገዛዝ ስር መልሶ እንዲገባ ህገ መንግስቱን እያጣቀሱ መሞገት ነው። በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ነው። ቢቻላቸው የኤርትራን መንግስት ቀድሞ ሲያደርጉት ወደነበረው አፈና ከበባ ውስጥ ማስገባት ነው። ኤርትራ ከሩሲያና ከቻይና ጎም በመቆም ለወሰደቻቸው አቋሞች ዋጋ እንድትከፍል ማድረግ ነው። በመጨረሻም ትልቅ ስትራተጂያዊ ጠቀሜታ ያላትን ኤርትራን መንግስቷን በመጣል የአሜሪካ አሻንጉሊት በሆነ መንግስት መተካት ነው።

የሚያሳስቡ ነገሮች እየታዩ ነው። አሜሪካኖች የሚፈልጉትን በመስጠት ኢትዮጵያ ከገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ ፋታ ታገኛለች በሚል የተሳሳተ ስሌት ሊሰራ የሚችል ነገር የከፋ አደጋ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል። በአለም ላይ የተፈጠረው በሁለት የተከፈለው ጎራ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን ሁሉ አሜሪካኖች በከፍተኛ ትኩረት እንዲከታተሉት እንዳደረገ ሁሉ የሩሲያውና የቻይናውም ጎራ ይከታተሉታል።

ቻይና እና ሩስያ በተከታታይ ምእራባውያኑ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲነሳና በኢትዮጵያ ላይ ጎጂ ውሳኔ እንዲወሰን የተደረገውን ተደጋጋሚ ጥረት ኢትዮጵያን ወግነው አክሸፈዋል። ኤርትራ በክፉ ቀን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም መስዋእተነት ከፍላ አለኝታነቷን አሳይታለች። እነዚህ አካላት የኢትዮጵያ መንግስት ውለታቸውን ዘንግቶ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ ወደ መሆን ሲሄድ ዝም ብለው የሚያዩት አይሆንም። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አንዱን መምረጥ ይኖርበታል። አሜሪካኖች የአጭርና የረጅም ጊዜ ጥቅሞቻቸውን አስልተው ኢትዮጵያ እንድትፈጽም የሚፈልጓቸውን ነገሮች መፈጸም ወይም አሜሪካኖች የሚጠይቋቸውን ፍትሃዊ ያልሆኑ ጥያቄዎች አልቀበልም በማለት መከፈል የሚገባውን መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ እየሄደበት ያለው መንገድ አሳሳቢ ነው። ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ስራዋ ሩቅ ካሉ ሃገሮች ይልቅ በአካባቢዋ ካሉት ጎረቤት ሃገሮቿ ጋር የሚኖራት መልካም ግንኙነት ዘለቄታ ጥቅሟን የሚያስከብር መሆኑን ማወቅ ይኖርባታል። ለአሜሪካኖች ተብሎ ከየትኛውም ሃገር ህዝብ በላይ የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆነ ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር መቃቃር ለኢትዮጵያ ትልቅ ጉዳት የሚያስከትል ነው። ኤርትራ አሜሪካ ብቸኛዋ ልእለ ሃያል ሃገር በነበረችበት ወቅት ተገልላ ስትኖር ከነበረበት አፈና የሚያወጣ አዲስ የአለም ስርአት ተፈጥሮላታል። እሷም ጥቅሟን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ በተፈጠረው የአለም ጎራ ውስጥ የወሰደቻቸው በብልሃት የተሞሉ አቋሞች ትልልቅ ሃያላን ወዳጆች እንድታፈራ አድርጓታል። ዛሬ አሜሪካኖች ኤርትራን ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበር ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ የለም። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ይህን ሃቅ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። ዲፕሎማሲው አሜሪካ ላይ መለጠፍ ሳይሆን ከአሜሪካ ተጽእኖ እንዴት መላቀቅ ይቻላል በሚል ስሌት መመራት አለበት። ኢትዮጵያ በጦርነቱ ወቅት ከአሜሪካን ተጽእኖ ራሷን ለማላቀቅ ተፈጠሮላት የነበረውን እድል በማባከኗ ወደፊት የምናየው ይሆናል ብዙ ዋጋ ትከፍልበታለች። ሃቁ በአሜሪካ ተጽእኖ ስር ወድቀው የበለጸጉ፣ ሰላም ያገኙ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የገነቡ፣ የህዝባቸውን መብቶች ያስከበሩ ታዳጊ ሃገሮች ቀርቶ አንድም ሃገር የለም። ይህን ሃቅ አገናዝቦ ብልሃትና ጥበብ በተሞላው መንገድ የዲፕሎማሲ አቅጣጫቻን ማስተካከል ይገባል። ይህ ጉዳይ እራሶች አሜሪካኖቹ እንደሚሉት “እንደሚናገሩት ቀላል እንዳልሆነ” ይገባኛል። ከባድ ያደረግነው እኛው ራሳችን መሆናችንን መገንዘብ ግን ይገባናል።

አንዳርጋቸው ጽጌ

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

3 COMMENTS

 1. አንተ ሰውዬ ጡረታ ውጣ፣ ተፋታን፣ ማንም የሚሰማህ የለም። ወደ ዋሻህ ተመለስ።

 2. አሁን በትግራይ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር በቅድሚያ በሽግግር መንግስቱ ፈጠራ ሂደት፣ ትልቁን ስልጣን እና መብት፣ የመከራው ዋናው ገፈት ቀማሽ የሆነው የትግራይ ህዝብ የሚቆጣጠረው እንዲሆን ማድረግ ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት ቀድሞ የሚያውቃቸውን ወይም እራሱ ያደራጃቸውን ወይም በራሳቸው የተደራጁ የጥቂት ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከማመን የትግራይ ህዝብን ማመን የተሻለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገዋል። የትግራይ ህዝብ ሰላምና ፍትህ እንዲያገኝ ከገባበት የህይወት መከራ እንዲወጣ በንጽህና ከሚታገሉ ወጣት ፖለቲከኞች ጋር ተቀራርቦ መስራት የሚኖረውን ጠቀሜታ መረዳት ያስፈልገዋል።

  አሁን ባለው ሁኔታ የብልጽግና መንግስት ከዚህ ቀደም እንዳደረገው የራሱን የብልጽግና ሰዎች የትግራይ ጊዜያዊ አሰተዳዳሪዎች አድርጎ መሰየም አይችልም። የዚህ አይነቱ ሙከራ ተሿሚዎቹን እንደ ወራሪ ሃይል አድርጎ ህዝብ እንዲያቸው በማድረግ ከዚህ ቀደም የተከሰተው የፖለቲካ ችግር እንዲከሰት ያደርጋል። ለጸረ ሰላም ወያኔዎችም ተቃውሞና አሻጥር የሚመች ሁኔታ ይፈጥራል።

  From Andy’s article is the above. As usual the author put a lot of thought into his writing. Meanwhile EZEMA seems to be on the verge of giving up all the hope it had on fed gov’t and the ‘reformers’ in it. I know the essay is of limited scope but still. Not entering Mekelle is a smart move according to many who know what we don’t and advised against it at the end of Nov 2020. Fighting a guerrellae in Tembien Mountains is just too costly both financially and in dead body counts. Already ‘8020 militias from East Gojjam Zone; 19 in one night on Doba mountain on the AQesta front from Shebel Berenta district of the same zone killed leaving 96 children fatherless..it is not only the 600 000 Obasanjo mentioned but many more and many will be angry if and when the numbers were made public’. And still the hard core TPLF is preparing for yet another round of death and destruction in an effort to take power in Addis, if possible, and to keep Tigray thinking TPLF’s way is the only way in the short term. I understand this is a plea to all kinds of Ethiopians..

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here