spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeአበይት ዜናበዐብይ አህመድና ሽመልስ አብዲሳ መሪነት እየተስፋፋ የመጣውን የፅንፈኛ ኦሮሙማ የጥፋት ዘመቻ በተመለከተ...

በዐብይ አህመድና ሽመልስ አብዲሳ መሪነት እየተስፋፋ የመጣውን የፅንፈኛ ኦሮሙማ የጥፋት ዘመቻ በተመለከተ ከቪዥን ኢትዮጵያ የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫ

Vision Ethiopia _ abiy - shimeles

ከቪዥን ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ

የዘረኛው የወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ በሕዝብ ትግል ተገርስሶ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ በዐብይ አህመድና ሽመልስ አብዲሳ መሪነት በአማራው ላይ ሲካሄድ የቆየው የኦሮሙማ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ዛሬ ወደ ሌሎች ክፍሎች ተስፋፍቶ፣ የጉራጌ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የቤኒሻንጉል፣ የሱማሌ፣ የጋምቤላና ሌሎች ወገኖቻችንም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተጠቁ፣ ንብረታቸው እየተዘረፈና ሰላማዊ ነዋሪዎች እየተጨፈጨፉ ይገኛሉ::

በዘር ማጥፋት፣ በታሪክ ክለሳ፣ በባህል ምረዛ፣ በሃይማኖት ብረዛ፣ በሃብት ዝርፊያና በእርስት ቅሚያ ላይ የተመርኮዘው፣ የኦሮሙማ ኋላ ቀርና ስግብግብ ስርአት፣ አገሪቱን እያናወጠ ይገኛል::

በቅርቡ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ላይ የተነጣጠረ የከፋፍሎ ማዳከምና የማፈራረስ ዘመቻ አካሂዶ አገሪቱን እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰሯትን እሴቶች በተቀነባበረ ስልት እየበጣጠሰ ይታያል።

በይበልጥም፣ በአረሜኔያዊ ድንቁርናው ታውሮ፡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጭቁን ሕዝብ መመኪያ በሆኑ ቅርሶችና የምርምር መሰረቶች ላይ ከመጠን ያለፈ ጉዳት አድርሷል::

የመላው ሕዝብ መግባቢያ ቋንቋ የሆነውንና የፅሁፍና የምርምር መሣሪያነቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተደናቂነት ያስመዘገቡትን የአማርኛ ልሳንና የግእዝ ፊደልን አግዶና በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በትምህርት ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጓል::

የጥቁር ሕዝብ ነፃነት መንፀባረቂያና መመኪያ የሆነውን የአድዋ ድል በአል በአግባቡ እንዳይከበር በተደጋጋሚ አስተጓጎሎአል፣ ይባስ ብሎም በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በአማኞችና የአድዋ በአል ኣክባሪዎች ላይ ፋሽሽታዊ እርምጃ በመውሰድ አስከፊ የታሪክ ጥቁር ነጥብ አስፍሮአል።

የአዲስ አበባ ከተማን አስተዳደር በኦርሙማ አክራሪ መሪዎች እጅ አስገብቶ፣ ብዙውን የከተማይቱን ክፍል ወደ ኦሮሚያ ክልል አስተላልፎአል። ከዚያም በላይ፣ ወደ መዲናይቱ መግቢያ የሆኑ የአካባቢ መንደሮችን “ሸገር” በሚል ስያሜ አደራጅቶ በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። ወደ አዲስ አበባ በነፃነት የመግባትና የመውጣት እድልን ዘር እየመረጠ ያግዳል፤ በተለይም አማሮችን እየመረጠ ይከለክላል።  ከዚህም አልፎ፣ የኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች፡በተለይም የአማሮችን የመኖሪያ ቤቶች እያፈረስ ተከላካይ የሌላቸውን ወገኖቻችንን መጠጊያና መጠለያ አጥተው እንዲሰቃዩ አድርጓል::

በወለጋ፣ ሰሜን ሸዋና ተመሳሳይ ቦታ ነዋሪ የነበሩትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ከቀያቸው አፈናቅሎ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ፈጅቶ ሲያበቃ፣ አሁን በጉራጌና በሌሎች ወገኖች ላይ ተመሳሳይ የሕግ አልባና የወንጀለኛ ድርጊቶችን እየፈፀመ ይገኛል::

ኢትዮጵያዊነቱን በጽኑ የሚያምነውን የደቡብ ክልል ለኦሮሙማ በላይነት በሚያመች መንገድ በማፈራረስና ከፋፍሎ እያዳከመ ይገኛል። የራሳቸውን ክልል የመመስረት ጥያቄ ያቀረቡትን እንደ ጉራጌና ወላይታ ላሉት ዜጎቻችን ለጥያቄቸው መልስ መስጠት ቀርቶ መብታቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን እንዳያደርጉና ድምጻቸዉን እንዳያሰሙ እየታፈኑ፤ ከሥራ እየተባረሩ የእስር፣ የድብደባና የእንግልት በደል እንዲደርስባቸው ሆነዋል።

በተለይም ሰሞኑን በወልቂጤና ሌሎች አካባቢዎች በሚኖረው የጉራጌ ሕዝብ ላይ እየደረሰ የሚታየው ከፍተኛ ዝርፊያ፣ ግድያና እስራት የዚህን አስተዳደር ኋላቀርና ጨካኝ አረመኔያዊ ገፅታ በጉልህ የሚያሳይ ማስረጃ ሆኖ ይቆጠራል። የዞኑን በጀት ለደቡብ ልዩ ኃይልና ለፌዴራሉ ኃይል አፈና ማስፈፀሚያ በማድረግ፣ ውሃ ፍለጋ ጀሪካን ይዞ የወጣው ሰላማዊ ሰው እስከመገደል ጥቃት ደርሶበታል። የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሕዝብ ምክር ቤት ተመራጮች፣ ነፍሰጡርና የቤት እመቤቶች ሳይቀሩ የህክምና እርዳታ እንዳያገኙ ተከልክለው፣ በእስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል። 

ቀደም ሲል የአማራውን ሕዝብ ለማዳከም ባለው እኩይ አላማ፣ ክልሉን ለሕወሓትና ለሰሜን ሱዳን አጋልጦ እንዳስጠቃ ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ የጋምቤላን መሬት በደቡብ ሱዳን አስወርሮ፣ የወገናችን ኃብት እንዲዘረፍ፣ እርስቱ በውጭ ወራሪ ኃይል እንዲነጠቅና ሕዝቡም በባእድ ጦር እንዲሰቃይ አድርጓል::

“ሁሉም የእኔ” በሚል የነጣቂ መንፈስ የተለከፈው የኦሮሙማ ስርአት፣ ሰሞኑን ትኩረቱን ወደ ታላቁ የአባይ ግድብ (GERD) አዙሮ፣ ለዓመታት የዘር ማፅዳት ዘመቻ በአማራው ላይ ሲያካሄድበት በነበረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የተስፋፊነት ጦሩን እያዘመተ ይታያል::

ቪዥን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንዳስገነዘበው፣ በዐብይ አህመድና ሽመልስ አብዲሳ መሪነት ኢትዮጵያን እያፈራረሰ፣ ነዋሪወቿን እየጨፈጨፈና እየዘረፈ የሚገኘውን የኦሮሙማን ፋሽሽታዊ ስልቀጣ መግታት የሚቻለው በተቀነባበረና በተናበበ ሕዝባዊ ትግል ብቻ መሆኑን አጥብቆ ያምናል:: ስለሆነም ወገኖቻንን ከከፋ ችግርና እልቂት ለመታደግና አገራችንንም ከተደቀነባት አደገኛ ቀውስ ለማዳን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የትግል ስልቶች በመጠቀም ይህን ዘረኛ ስርዓት መታገል የግድ ይሆናል። ለዚህም የህልውና ትግል ጥሪ በድጋሚ ያቀርባል::

  1. በአገር ውስጥ የሚገኙ ተጠቂ ዜጎቻችን በሙሉ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በሥራ ማቆም አድማ እና ሌሎችም የኦሮሙማን የጭቆና አገዛዝ በሚጎዱ ሰላማዊ መንገዶች ባለማቋረጥ ተቃውሟቸውንና እምቢተኝነታቸውን መግለፅ::
  2. በውጭ የሚኖሩ ፍትህ-ወዳድ ወገኖች፣ የኦሮሙማ የጭቆና አገዛዝ የገንዘብ ምንጭ የሆኑትን መንገዶች ሁሉ ማድረቅ:: በተለይም የአገዛዙን ጨካኝና አደገኛ ባህሪ ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲያገኝ በማድረግ የውጭ እርዳታ ማእቀብ ማስደረግና እንደ ኢትዮጵያ አየር መንግድ ያሉትን የዘረኛው መንግሥት የገንዘብ ምንጮችን መጠቀሚያ አለማድረግ:: 
  3. በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች የጋራ የትግል መርሀግብር በአስቸኳይ ነድፈው፣ በዲሞክራሲያዊ አሠራር ላይ የተመረኮዘ አንድነትን መፍጠር:: በተለይም የአማራው ክፍል በአንድነት ቆሞ፣ አሁን በመጠቃት ካሉት ወገኖቹ ጋር ኃይሉን በማቀናጀት፣ የራሱን ህልውናና የወገኖቹን ደህንነት ለመከላከል በቁርጠኝነት መነሳት::
  4. በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ምሁራንና  የተለያዩ የሀይማኖት ተከታዮች፣ በኦሮሙማ እየተካሄደ የሚታየውን የታሪክ፣ የእምነትና የባህል ማጥፋት ዘመቻ በሚቻለው መድረክ ሁሉ አጥብቆ መዋጋት::
  5. በመጨረሻም፣ ዐብይ አህመድ፣ ሽመልስ አብዲሳና ጭፍሮቻቸው በተከታታይ የፈፀሙትን ፋሽሽታዊ ወንጀል ለፍርድ አቅርቦ፣ ወንጀለኞቹ ለተግባራቸው ተመጣጣኝ የሆነ ዓለማቀፋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ::

ከላይ የተዘረዘሩትን የትግል ስልቶች ተግባራዊ ለማድረግ በቂ ኃይልና አስተማማኘ ነባራዊ ሁኔታ አለ ብሎ እያመነ፣ ቪዥን ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ትጋትና አለመሰልቸት ከጭቁን ወገኖቹ ጋር በመሰለፍ፣ በዘር ላይ የተመረኮዘውን አረመኔያዊ አገዛዝ ለመታገል  ጠንክሮ እንደሚሠራ እንደገና ያረጋግጣል::

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here