spot_img
Tuesday, November 28, 2023
Homeአበይት ዜናየተደቀነውን የሀገር ህልውና አደጋ በቅጡ እንረዳለን፤ ጊዜውን የዋጀ አመራር ለመስጠትም ቁርጠኛ ነን!...

የተደቀነውን የሀገር ህልውና አደጋ በቅጡ እንረዳለን፤ ጊዜውን የዋጀ አመራር ለመስጠትም ቁርጠኛ ነን! (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ )

advertisement
Ethiopian News _ EZEMA

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከምስረታው ጀምሮ እንደ ሀገር የደረስንበትን የፖለቲካ ስብራት በጥልቀት በመመርመር እና በመረዳት የሀገራችንን የፖለቲካ ቋጠሮዎች ደረጃ በደረጃ የሚፈቱበትን የመፍትሄ አማራጮች ማመላከት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኢዜማ ሃገራችንን እየተፈታተኑ ያሉ የፖለቲካ ችግሮች እንዲባባሱ እና ሁላችንም እንዲሆን ወደ ማንፈልገው የከፋ ችግር እንዳንገባ ራሱን ከሃገር ህልውና በታች አድርጎ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ ያለፉትን አምስት ዓመታት ያሳለፍነው አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ የሆነ ጉዞ በፅንፈኛ ብሔርተኝነት እየተገፋ ዛሬ ለደረስንበት ጠርዝ አብቅቶናል፤ እያለፍንበት ያለውን የፖለቲካ ዑደት በጥንቃቄ ላስተዋለና ቀልቡን ሰብስቦ ሁኔታዎችን ለተመለከተ የትኛውም አካል ዛሬ የገባንበትን ቅርቃር ማስተዋል ከባድ አይሆንም፡፡

በየቀኑ በሚፈጠሩ ውጥንቅጦች እና የሚፈለፈሉ አጀንዳዎች ማህበረሰባችንን የሥነልቦና ጫና ውስጥ እንደከተተውና ሁላችንም ውጥረት ውስጥ እንዳለን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ህዝባችን የደረሰበት የመንፈስ ጭንቀት ከዛሬ ነገ ምን ይፈጠር ይሆን እያለ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመውደቁ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ኢዜማ የደረስንበት አሳፋሪ ሃገራዊ ዕውነታዎች ከሥር መሠረታቸው እንዲቀየሩ የመፍትሔ አካል መሆን እንዳለበትና ሀገራችን ወደ ቀና መንገድ እንድታመራ ከፊት ተሰልፎ አመራር መስጠት እንዳለበት እናምናለን፡፡

በተለይ በሰሜኑ የተከሰተው ጦርነት እንዲቋጭ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቷን የሚንጡ አጀንዳዎችን በመፈልፈል ዜጎችን እረፍት የሚነሱ ተግባራት ላይ የተጠመዱ በመንግሥት ውስጥና ከመንግሥት ውጪ ያሉ ፅንፈኛ ብሄርተኞች ተናበው እየሰሩ መሆኑን መረዳት አዳጋች አይደለም፡፡ በዘር ፖለቲካ የሰከሩ ሰዎችን በመጋለብ መላው ህብረተሰብ በቁጣ እንዲወጣና አጠቃላይ ሃገራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያለእረፍት እየሰሩ ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎም ሁላችንንም በስሜት ነድቶ የተዘጋጀልን ወጥመድ ውስጥ ገብተን አቅል የሳተ የእብደት መንገድ እንድንከተል ግፊት ለመፍጠር እየተሞከረ ያለውን ጫና በአትኩሮት ልንመለከተው ይገባል፤ መንግሥት በጉያው አቅፎ እዚህ ያደረሳቸው በሃሰት ትርክት የተሞሉ፣ በጥላቻ የሰከሩ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ እንወክለዋለን ለሚሉት ህዝብ እንኳን ግልጽና የጠራ መዳረሻ ያላስቀመጡ አክራሪ ኃይሎችን በግልጽ ሊፋለማቸውና፣ ከመዋቅሩ ሊመነጥራቸው ይገባል፡፡ ከመንግሥት መዋቅር ውጪ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ አክቲቪስቶችና ባለሃብቶች ጭምር እየተቀጣጠለ ያለው የአክራሪ ብሄርተኝነት ጦስ ካሁን በኋላ እያስነከሰን እንዲቀጥል ሊፈቀድ አይገባም፡፡ መንግስትም ጉዳዩን መስመር ለማስያዝ እያሳየ ያለውን እንዝህላልነት ለፅንፈኛ ብሔርተኞቹ የልብ ልብ እየሰጠ ድርጊታቸው ሁሉ መስመር እያለፈ ህዝቡ አድዋን የመሰሉ ብሔራዊ በዓላትን እንኳ በሚፈልገው መንገድ ማክበር እንዳይችል አድርጎታል፡፡ በዚህም መታለፍ የሌለበት ቀይ መስመር ታልፏል፣ በቃ ልንል ይገባል!

ኢዜማ ከአባላቱ፣ ከደጋፊዎቹ እና ያገባኛል ብለው ከሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚደርስበት ትቸት ድርጅቱ ላይ ካለ እምነት እና ሊወጣ ይገባል ተብሎ ከሚታመነው የአመራር ኃላፊነት የሚመነጨ እንደሆነ ለአፍታም አይዘነጋውም፡፡ ድርጅታችን የሚይዛቸው የፖለቲካ አቋሞች እና ትንታኔዎች መሰረት የሚያደርጉት የሰከነ አስተሳሰብን እንጂ ጊዜያዊ ድጋፍን ለማግኘት በሚል የህዝብ ብሶትን እያቀጣጠለ፣ ወቅታዊ ጩኸትን እንዲሁም ወጀቡን ተከትሎ በመንጎድ ሲመሰረት ጀምሮ ካስቀመጠው የጠራ የትግል ሥልት እና ግብ ወደጎን የሚወጣ ድርጅት አይደለም፡፡

ድርጅታችን ኢዜማ በፍጥነት ተለዋዋጭ የሆነው የሃገራችንንም ሆነ የቀጠናውን ጂኦ ፖለቲካ በሀገራችን ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ እየተነተነ፣ ሁኔታው የሚፈልገውን አቋምና ውሳኔ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔዎች እያስቀመጠ እና የትግል ስልቱንና የዓላማ መዳረሻውን እያጤነ የሚጓዝ ድርጅት ነው፡፡

በኢዜማ እምነት እንደሀገር የገባንበት ከፍተኛ አደጋ ከስሜታዊነት እና ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ፣ በወቅታዊ ክስተቶች ላይ ብቻ ተመስርተን ሳይሆን በዘላቂነት የሃገራችንን መፃዒ እድል እያሰቡ፣ ተከታታይነት ያላቸውን ማህበረሰቡን እረፍት የነሱ ክስተቶች በተናጠልና በድምርም በሃገራችን ላይ ጥለው የሚያልፉትን ጠባሳ እያሰቡ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡

የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የማንነት እና ሌሎች የልዩነት መሰረቶች ላይ ቆሞ በዘላቂነት የሃገራችንን ፖለቲካ ወደተረጋጋ ሥርዓት የሚያደርሰንን መፍትሄ ማግኘት የሚታሰብ አይደለም፡፡ መንግሥትም ሆነ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ የልዩነት ፖለቲካ አራማጅ ኃይሎች በሚያሳድሩት ቅጥ አልባ መጓተት እና ፍጭት ዛሬ ሀገራችን የሰፈነው የሥጋት ድባብና አጠቃላይ የማኅበረ-ፖለቲካ ምስቅልቅል የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በመንግሥት (በገዢው ፓርቲ) ውስጥ በገሃድ የሚታይ የብሄርተኞች የእርስ በእርስ መጓተት፣ በተቃዋሚ ጎራ ያሉ ፅንፈኛ ኃይሎች አመፅ በመቀስቀስ ሃገሪቱን ወደከፋ ትርምስ ውስጥ እንድንትገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም አለመቻል የሚያስከትለውን መዘዝ ኢዜማ በትክክል ይረዳል፡፡ ለአባላት ለደጋፊዎች እና ለመላው ህዝብ ማሳወቅ የሚፈልገው ዋነኛው ቁም ነገር ሀገራችንን እየተፈታተኑ ያሉ ነባር ውስብስብ ችግሮችንም ሆነ አንገብጋቢ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ እያየን እንጂ በዝምታ እና በቸልታ ኃላፊነት እንደሌለበት ፓርቲ ሁኔታዎቹን ዳር ላይ ቆመን እየተመለከትን እንዳልሆነ ነው፡፡ ሁኔታውን ተረድተን፣ ችግሩ እንዲቀረፍ የመሪነት ድርሻና ኃላፊነታችን መወጣት ታሪካዊ ግዴታና አደራ እንዳለብን ምንም አይነት ብዥታ የለንም፡፡

ኢትዮጵያዊነትን አስቀድማችሁ ሰለ ሀገር አንድነት በፅኑ የምትታገሉ የብሔር ፖለቲካ ምን ውስጥ አንደከተተን ተገንዝባችሁ በኢትዮጵያዊነት ከልብ የምታምኑ ሁሉ ከምንጊዜውም በላይ የሚከፋፍሉ አጀንዳዎችን እና ጥቃቅን ልዩነቶችን ከማጉላት በመቆጠብ አንድነትና ህብረት ላይ በማተኮር ከገባንበት አዘቅት ውስጥ መውጣት የሚያስችሉ የትብብር ስራዎች ላይ ማተኮር፤ ወቅታዊ የፓለቲካ ሁኔታውን ልብ ብሎ በማስተዋል በአንድነት ስም የተሰባሰበው ሀይል ቆም ብሎ ቀድሞ ሲጓዝበት ከነበረው አፍራሽ መንገድ በመውጣት እርስ በእርስ ከመጓተትና ከመጠላለፍ በመራቅ ፅንፈኛ ብሔርተኝነትን በጋራ መታገል እንደሚያስፈለግ አምኖ በሰከነ መንገድ ለመተባበር ካሁን በኋላ የምናባክነው ተጨማሪ ጊዜ መኖር እንደሌለበት በዜግነት ፖለቲካ ለሚያምኑ ሁሉ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ኢዜማ ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ መፍትሄው እኩልነት ላይ የቆመ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት መሆኑን በጽኑ እንደማመኑ፣ ይህን የምትጋሩ በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን፣ እንደዚሁም ይህንን የምትጋሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከጎናችን እንድትሰለፉ አደራ እንላለን፡፡ ከዚህ በፊት እንደሆነው በጎንዬሽ መጓተት ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ አያት ቅድም-አያቶቻችን ዋጋ ከፍለው ያቆዩዋትን ሀገር ዓይናችን እያየ ብሄርተኞች ያፈርሷታል፡፡ እኛም ይህ እንዳይሆን ቢያንስ በሚያግባቡን መሰረታዊ የሀገር ህልውና ጉዳዬች ላይ አብሮ ለመስራት እና ኢትዮጵያችንን ለማዳን በጋራ በመቆም ህዝባችንን ለመምራት ባለመተባበር ከሃገር አፍራሽ ብሄርተኞች እኩል በታሪክ የምንጠየቅ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያላችሁ የሀገርን አንድነት እና ሉዓላዊነት ከምንም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ፅኑ እምነት ያላችሁ ሁሉ በድርጅታችሁ ውስጥ ያሉ መጓተቶች ሀገራችንን ውድ ዋጋ እንደሚያስከፍላት በመገንዘብ ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳለባቸሁ ተረድታችሁ ከሀገራችሁ ጎን መቆማችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ኢዜማ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ በሥፋት ለማጥናት፣ በተጨማሪም እንደሀገር እየሄድንበት ያለውን የፖለቲካ አካሄድ እና በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታን ቆም ብሎ በመገምገም ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎቻችንን ማስመር እንዲቻል ብሔራዊ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የጥናት ግብረ ኃይል እንዲቋቋም፣ ግኝቱንም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ግብረ ኃይሉ የሃገራችንን የአምስት ዓመት ጉዞ በስፋትና በጥልቀት በመፈተሽ እንደዚሁም ኢዜማ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ያለፈበትን አራት የትግል ዓመታት እንደሀገር አሁን ከደረስንበትና ከተደቀኑብን አደጋዎች አንፃር ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶችን በሰከነ መንፈስ ተንትኖ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማሳየት የትግል መስመሩን ያመላክታል፤ ይህንንም ለሁሉም ባለድርሻዎች የምናቀርብ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ የሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ

_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. The people are very eagerly waiting for your leadership. You have led them to the very edge of the precipice. To what depths are you going to lead them next?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here