spot_img
Tuesday, November 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትሞትና ምላሽ  (በሺፈራው አበበ )

ሞትና ምላሽ  (በሺፈራው አበበ )

advertisement
ከኦንታሪዮ ሀዘን ባለስልጣን ገጽ የተወሰደ

በሺፈራው አበበ 

በምድር ላይ ስንኖር ትልቁ አደጋ ሞት ነው። 

ድሮ ሞት ብርቅ ነበር ፣ ክብርም ነበረው። ባለፍ ባገደም የሚጠፋ ህይወት አልነበረም። በተለይ በሰው እጅ መሞት ትልቅ ጉድ ነበር፤ በመብረቅ የመመታት ያህል እንግዳ ነገር ነበር። 

ሰው እግዜሩንም መንግስትንም ፣ ማህበረሰቡንም ፈርቶና አክብሮ ይኖር ነበር። 

ዛሬ ላይ የሰው ሞት የዝንብ ሞት ያህል ተቆጥሯል። ከቅርብ ዘመድ ባለፈ ማንም ስለሌላው ሞት ግድ አይለውም። ሺህዎች በአንድ አርፋጃ በማንነታቸው ተገድለው ምንም እንዳልተፈጠረ የመንግስትም የግለሰብም ቢዝነስ እንደተለመደው ይቀጥላል። 

መንግስት ለሰው ህይወት የሚሰጠው ዋጋ ለአንድ የዛፍ ችግኝ ከሚሰጠው ዋጋ ያነሰ ሆኗል። 

ንጹሃን ዜጎች በመቶዎች ተገድለው፣ የአገሪቱ መሪዎች ነብስ ይማር እንኳ ሳይሉ የሃብታም መኪና ማቆሚያ ለማስመረቅ ተግተልትለው ይሄዳሉ። 

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ፣ የእቃ ዋጋ ሰማይ ተሰቅሏል ፤ የሰው ህይወት ግን ጥንቡን ጥሏል። 

በእርግጥ የሰው ህይወት መርከስ ከጀመረ ውሎ አድሯል፤ ሃምሳ አመት ሊሞላው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የግፍ ሞትን እንደ አርባ ቀን እድሉ ቆጥሮ መኖር ከጀመረም ያንኑ ያህል ጊዜ ሆነው። 

የደርግ መንግስት ቀይ ሽብር ብሎ ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ወጣት ጨፈጨፈ። ከቁጣ ቢዘል ከቁንጥጫ የማያልፍን ልጅ ጭምር፣ ጸረ-አብዮተኛ የሚል ታርጋ ለጥፎ በጥይት ደብድቦ ገደለ። አዛውንቱ አደባባይ ወጥቶ የወጣቶች ሬሳ ረግሞ እንዲመለስ ተደረገ። ወላጅ የጥይት ዋጋ ከፍሎ የልጆችን አስከሬን ወሰደ:: ሞቴን ከልጆቼ በፊት አድርገው ብሎ እንዳልጸለየ፣ የልጅ መቃብር ላይ ቆሞ አለቀሰ። 

ያኔ የተጀመረው ለቅሶ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፤ በስፋቱም በክፋቱም ያለፈውን እያስናቀ። መለስ የሚል የመሪ ልቦና፣ ዘንበል የሚል የፈጣሪ ጆሮ ወይም ሞት በቃኝ የሚል ህዝብ አልተገኘም!  

የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 50 አመታት ስጋትና ፍርሃት የሞላበት ህይወት ነው የሚኖረው። ጨካኝ መንግስታት ሃሞቱን አፍሰውታል። ለመብቱ መቆም ቀርቶ ፣ ርህራሄ እንዲደረግለት እንኳ በድፍረት አይጠይቅም። በእግዜር አምሳል ተፈጥሮ የሰውነት ክብሩ ምድር ላይ ሲጎተት፣ የባሰ አታምጣ ብሎ የሚኖር ነው ። 

የባሰው ከመምጣት ግን አልቀረም። ስልጣን ከአንድ “ሰው-በላ” መንግስት ወደ ሌላ “አገረ-በላ” መንግሥት 1983 ዓ.ም. ላይ ተሸጋገረ። ህወሃት-ወያኔ አገርና ህዝብን የሚክድ ስርአት በክንዱ ብርታት አቆሞ ወደግድያ ተሰማራ። አጅቦት ከመጣው ኦነግ ጋር ሆኖ በአርባጉጉ፣ በበደኖ ፣ በጋራሙለታ እና ፣ በሃረር መአት አማሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ ፈጀ። እስከዛሬ ለዘለቀው ዘር-ተኮር ግድያና እልቂት መሰረት የሆነው ይኸው ስርአት ሲሆን የሚነቀንቀው ሃይል ግን ሊገኝ አልቻለም።  

በ27 አመታት የህወሃት-ወያኔ አገዛዝ ፣ ስርአቱን በሰላማዊ መንገድ በመቃወማቸው ወይም በመተቸታቸው ብቻ በግልጽና በስውር የተገደሉት ፣ በድብደባ አካለ ስንኩል የተደረጉት እና በአስከፊ እስራት መከራቸውን የበሉት ወገኖች የትየለሌ ናቸው። ግን ማን በቁጥር ይዞት? ማንስ ግድ ብሎት? 

የኢትዮጵያ ህዝብ ስጋትና ፍርሃት በወለደው ቀቢጸ-ተስፋ የሚኖር ህዝብ ነው። ተስፋውን ወደ እምነት ፣ እምነቱን ወደ እውነት መለወጥ የሚያስችል ጠንካራ ድርጅታዊ ውክልና የለውም። አብዛኛው ፖለቲከኛ በጎጥ ተደራጅቶ የግል ጥቅምና ስልጣን የሚያባርር ነው። የተረፈው በትርኪ ምርኪ ጉዳይ ተለያይቶ ፣ የከፋፋይ ገዢዎች መጫወቻ ከመሆን አልፎ ለህዝብ ከለላ የሚሆን ድርጅታዊ አቅም ሊመሰርት አልቻለም። 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍዳ ከህወሃት-ወያኔ አገዛዝ ጋር ሳያከትም ቀርቶ፣ ዛሬ ላይ ብሶበት ይገኛል። 

የብዙ ኦሮሞ እና አማራ ወጣቶች ህይወት ተገብሮበት የመጣን ለውጥ ተጠቅመው ስልጣን ላይ ቁጢጥ ያሉት የዛሬ መሪዎች በሃያ ሰባቱ የህወሃት-ወያኔ አገዛዝ አገልጋይ የነበሩ ብቻ ሳይሆን የጥቅም ፣ የስልጣን ፣ የመብት ጥሰትና የግፍ ወንጀል ተጋሪዎችም የነበሩ ናቸው:: 

የኢትዮጵያን ህዝብ “አጥፍተናል” ፣ “እንክሳለን” ብለው የወሰዱትን ስልጣን ፣ ቃል ኪዳናቸውን ለመፈጸም ቢሰሩበት ኖሮ ባልከፋ ነበር። እነሱ ግን እጃቸው ውስጥ ያስገቡትን ስልጣን ስለመቀራመት እንጂ ፣ ስለንጹሃን ዜጎች ስቃይ እና ሞት ግድ ሊላቸው አልቻለም።  

ሰለሆነም በ”ብልጽግና” ዘመን የሰው ሞት በቁጥሩም በአሰቃቂነቱም የህወሃት-ወያኔ ዘመኑን አስከነዳ። 

በደርግና በህወሃት-ወያኔ አገዛዝ ፣ ባብዛኛው የሚገደለው የፖለቲካ ተቀናቃኝ የተባለው ነበር። ባለፉት አምስት አመታት በኦሮሚያ ፣ በቤሻንጉል ግሙዝ እና መሰል ቦታዎች ህይወታቸው የታጨደው ፖለቲካ ምን እንደሆነ የማያውቁ ለፍቶ አዳሪዎች፣ ህጻናት ፣ ሴቶች እና አረጋውያን ናቸው። ወንጀላቸው ተፈጥሮአቸው ነው። <<ዘራቸው>> ነው። ባብዛኛው አማራ ሆነው መገኘታቸው ነው። ከቤታቸውና ከቀያቸው ውጡ ተብለው የሚፈናቀሉትና መንገድ ዳር ለጅብ የሚጣሉትም እንዲሁ። 

በመንግስት ሃይላት ጭምር ፣ በገዛ አገሩ መጻተኛ የተደረገ እንደኢትዮጵያ ህዝብ ያለ ሌላ ህዝብ የለም። 

ደርግና ወያኔ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን መግደል የሚጠበቅ ነገር ተደርጎ እንዲታሰብ አድርገውት ነበር። የዛሬዎቹ መሪዎች የሰውን መገደል ባጠቃላይ ፣ እንደ ተራ ክስተት እንዲታይ ፣ ህዝብ ስለሞት እንዳይደነግጥ ፣ እንዳይጨነቅ ፣ እንዳይጠይቅም፣ እያደረጉት ነው። 

ለሰው ህይወት ግድ የሌለው መንግስት ህዝብን አያከብርም፤ ውሎ አድሮ አገርን ያጠፋል እንጂ ሊያለማ አይችልም። ሞትን ተላምዶ የሚኖር ማህበረሰብ የግፍ ተሸካሚ ይሆናል እንጂ በነጻነት መኖር አይችልም። 

የ127ኛው የአድዋ ድል በተከበረበት እለት ፣ መንግስት ታሪካዊዉን የህዝብ በአል መቀማቱ አንሶ ፣ ሁለት ወገኖች በፖሊስ እንደተገደሉ ተዘግቧል። አንድ ወጣት አስተማሪ እና አንድ አዛውንት። በደላቸው ወጣቱ “መንግስት ባልፈቀደው” የምንሊክ አደባባይ በአሉን ለማክበር መገኘቱ ፣ አዛውንቱ ባቅራቢያ ባለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ መገኘታቸው ነበር። ይህ አይነት የመንግስት እብሪት ሌላ አገር ቢሆን ኖሮ የተፈጸመው ህዝብ በታላቅ ተቃውሞ ይወጣ ነበር። የአ.አ. ህዝብ ግን አንገቱን ደፍቶ ወደቤቱ ተመለሰ። 

ከህወሃት-ወያኔ ጋር በተደረገው ጦርነት በአንዳንዶች ግምት በሚሊየን ቢያንስ ግን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። የወደመውን ንብረትና የደረሰውን መፈናቀል ማንሳት አያስፈልግም። 

ይሁንና ህዝብ ስለሞቱት አያነሳም ፤ ለምንና እንዴት ሞቱ ብሎ አይጠይቅም። መሪዎቹም ለደረሰው እልቂጥና ጥፋት ቅንጣት ያህል ሃላፊነት አልወሰዱም። 

እንዲያውም “ብልጽግና” ጄኔራሎቹን በሹመትና በማእረግ አምበሸበሸ ፤ መቀሌ ድረስ ሄዶ የጥፋት አጋፋሪዎቹን አቅፎ ሳመ። ከሞት የተረፉት የህወሃት-ወያኔ መሪዎች ትግራይ ውስጥ ዳግም ስልጣን ለመያዝ ሽር ጉድ እያሉ ነው።

እንደልማዱ ልጆቹን ገብሮ ባዶ እጁን የቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። እንደዚህ አይነት ንቀትና ውርደት የሚሸከም ህዝብ ቢኖርም እሱ ብቻ ነው!!  

ሞትን ከነምላሹ በጸጋ እየተቀበለ የሚታደም ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነው!!! 

መቼ ሞት በቃኝ ብሎ እንደሚነሳ እግዜሩስ ያውቅ ይሆን?

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here