spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትአዲሱ የሀገራችን ሁኔታ አዲስ ራእይና አዳዲስ ግንኙነት ይጠይቃል

አዲሱ የሀገራችን ሁኔታ አዲስ ራእይና አዳዲስ ግንኙነት ይጠይቃል

አክሊሉ ወንድአፈረው

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ በሚገርም ፍጥነት ከሀወሀት ጋር ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ሰፊ መቀራረብም ፈጥረዋል፡፡ ከትግራይ ህዝብ ጋር ግን እንኳንንስ ጠቅላዩ ጌታቸው ረዳም ገና አልተወዳጀም፡፡ ይህን ለማድረግ እጅግ ብዙ ፈተና ማለፍ ሰለጦርነቱ እውነታውን ፍንትው አድርጎ ማሳየት እጅግ ብዙ ኑዛዜና ንስሀን ግድ ይላል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እንደ አንድ ፖለቲከኛ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብዙ ነገር እያደረጉና ሊያደርጉም እንደሚችሉ ተረድቶ ህዝብ በሚመቸው መንገድ ጥቅሙን ለማስጠበቅ መሄድ አለበት ባይ ነኝ፡፡

ይህን እውን ለማድረግም የትግራይ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሊሂቃን የትግራይ ሌሎች ምሁራን አባቶችና እናቶች ከ ጎረቤታቸው ክልሎች እንዲሁም ከቀሪው ኢትዮጰያዊ ጋር አዲስ የሚያቀራርብ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡ እላለሁ፡፡ በዚህ አኳያ ብዙ ማለት ቢቻልም አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፡ ሃሳብ ልሰንዝር፡፡ትግራይና አጓራባቾችዋ ሌላ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ አይገባም፡ ሰለዚህም እነዙህ ጎረቤቶች መቀራረብን የሚያበረታቱ ግ ን ኙነትን ማድረግ የመጀመሪያው እርምጃቸው ሊሆን ይገባል፡፡

የትግራይ ህዝብ ከአማራም ሆነ ከአፋር ህዝብ ጋር ሌላ ዙር ጦርነት ገብቶ ህይወትና ብንረት በሁሉም በኩል መጥፋት የለበትም፣ ወልቃይትንም ሆነ ራያን በጉልበት እይዛለሁ ማለት የሚያተርፈው ሌላ ዙር እልቂት እና የማያቋርጥ ውስብስብ ግጭትን ነው፡፡ ይህ ማንንም አይጠቅምም፡፣

እነዚህ አካባቢወች እንኳንስ ለትግራይ ለአማራና ለአፋር ለሌላውም የሚበቁ ናቸው ሰለዚህ መፍትሄው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፎርሙላ ላይ መድረስ ሲሆን ይህን ወደተግባር ለመለወጥም የትግራይ ህዝብን ጥቅም በልባችሁ የያዛችሁ እንዲሁም በአማራአፋር የሚገኙ ሊሂቃን እንዲሁም አጠቃላየ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ አዲስ ግንኙነት ሊፈጥሩና ንግግርንም ሊጀምሩ ይገባል፡፡ ይህ ለብልጽና ፓርቲ የሚተው ተግባር አይደለም፡፡


ብልጽግናና መንግስቱ የኛ የሚሉት የፖለቲካ ማህበረስብ እና የራሳቸውን የፖለቲካ ጥቅም ታሳቢ አድርገው እንደሚንቀሳቀሱና ጥቅሙንም ለማስጠበቅ እንደሚስሩ ተገንዝቦ የራስን ጥቅም ሌሎች አስረክቦ በባዶ ተስፋ መኖርን አቁሞ የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ ቀጥተኛ የርስ በርስ ውይይት መጀመር እጅግ አጣዳፊ ተግባር ነው ፡፡

እነዚህ ህብረተስቦች የወደፊት እድላቸው ሁሉ በራሳቸው እጅ እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ይህን ችሎታቸውን ለሌሎች አሳልፈው ከሰጡ በቀጣይ የሌሎችን ችሮታ ጠባቂ እንጂ ሌላ ሊሆኑ እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ሀይል እስኪመጣ ድረስ ትግል ማካሄድ ለዚህ ሀይል መወልድም በጋራ መስራት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

ትግራዋይንም ሆነ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሁለተኛ ዜግ ነት ዝቅ የሚያደርገው ሀገ መንግስት በአዲስ መልክ ሁሉንም እንዲጠቅም ተደርጎ እንዲስተካከል መታገል ያስፈልጋል አሁን ያለው ህገ መንግስት አሁን በተጻፈበት ሁኔታ እንደ ሁሉም ኢትዮጰያዊ ሁሉ የትግራይንም ህዝብ በሰፊው ይጎዳዋል፤፡ ለምሳሌ፡ በ 30 ወንበር የተገደበች ትግራይ እድሜ ልክ ባለ 547 ወንበር በሆነ ፊደራል ፓርላም ውስጥ በፊደራል መንግስት ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል ምንም ስልጣን እንደማታገኝ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ቁመና ከሊሎች ጋር ትብብር ፈጥረን ወደምንፈልገው ደረጃ እንደርሳለን ተብሎ ቢታስብ እንኳ በዝቅተና ተባባሪነት ያለፈ ቦታ ማኘት እንደማይቻል ቁጥሩ ራሱ ገላጭ ነው፡፡ ይህን ጎጂና አንዱን የበላይ አንዱን የበታች የሚያደርግ ህገመንግስት ሁሉንም ሊጠቅም በሚችል መልክ እንዴት እንቅረጸው ብሎ ለውጥ ከሚፈልጉ ጋር መነጋገር አሁንም የትግራይም ሆነ የለውጥ ፈላጊ ክልልሎና አጠቃላይ ኢትዮጰያውያን ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡

አንዳንዶች “ የፊደራል ሀይሎች” በሚል የማጭበርበሪያ ስም የትግራይንም ሆነ ብዙሀኑን የኢትዮጰያን ህዝብ ከዚህ ሀገ መንግስት እንደሚጠቀም አስመስለው የራሳቸውን ስልጣን በርሱ ትከሻ ሊያጠናክሩ ሲሞክሩ ይታያል፡፡ የትግራይ ህዝብ ባህሉ ቋንቋው ማነነቱ ወዘተ እንደማንኛውም ኢትዮጰያዊ ወገኖቹ እንዲከበርለት ያስፈልጋል፡; ከዚህ ውጭ ግን ይህ ሀገ መንግስት የትግራይን ህዝብ በሁሉም መልኩ የሚጎዳው እንጂ የሚጠቅመው ሰላልሆነ እንዲለወጥ እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት በሚያካትት መልኩ እንዲስተካከል ከሌሎች ጋር ተባብሮ መታገል ያሻል፡፡

ሁሉም ኢትዮጰያዊ በመላው ኢትዮጰያ ያለ አንዳች ስጋት እንደፈለግ ሊዘዋወርና ሊሰራ የሚያስችለው መብት መደንገግ እና በትግባርም ማዋል የግድ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብም ሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመላ ሀገሪቱ እንደፈለገ ነግዶ፣ አርሶ፣ ቤትና ንብረት ይዞ የሚሰራበት ሀገ መንግስት ከለላና ተግባራዊ አፈጻጸም እንዲኖር ያስፈልጋል፡፤ ለምሳሌ የአንድ ማህበረስብ ተወላጆችን ነጥሎ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የሚያደርግ የተለያዩ ማህበረስብ ተወላጆችን “ መጤ” በሚል እሳቤ እንዲፈናቀሉ ማድረግ የሚፈውድ አሰራር በፍጹም አድልአዊ ሰለሆነ ሙሉ በሙሉ ሊወገድ ይገባል፡፡ ይህ ክልከላ ከአመት በፊት በትግራይ ተወላጆች ላይ ዛሬ ደግሞ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ አይተነዋል፡፡ ነገ ተረኛው ማን እንደሚሆን ሁላችንም የምናየው ይሆናል፡፡

ይህን ምስቅልቅል አስወግዶ በምትኩም ተጠያቂነት የሰፈነበት መንግስታዊ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ መታገል ያፈልጋል፡፤ አሁን ያለው ሀገ መንግስና የመንግስት አሰራር ሁሉንም በአጥር ከልሎ ሊያቆይና እየተነታረከ እንዲኖር የሚያበረታታ ነው፡፡ የመንግስት አካላቶች ያለ አንዳች ቁጥጥር ሰብብ እየደረደሩ የሰውን መብት ያለአንዳች ጠያቂ የሚጥሱበት እየሆነ መጥቷል፡፡ይህ በምንም መልኩ እንዲቀጥል መፍቀድ አይገባም ፡፡ እንዲቆምም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ ሊታገለው ይገባል፡፡ ይህ የትግራይን ልሂቃን አባቶችን እናቶች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር በ ጋራ ሊያስተሳስራቸው የሚገባ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

የብዙ ዜጎችን ህይወትና ንብረት ያጠፋው ጦርነት አነሳስና አካሄድ በግልጵ መመርመር እውነታውን ማወቅ ፍትህና እርቅም ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግም ያሻል ከሁለት አመት በፊት የተነሳውንንና በተለይም ትግራይን አፋርንንና አማራ ክልሎችንና ታላቅ ውድመት ውስጥ ይጣለው ጦርነት በትክክል እንዴት እንደተነሳ ለምን ቀድሞ መከለከል እንዳልተቻል ማን ሀላፊነት ሊወስድ እንደሚጋባውና ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ነጻና ገለልተኛ በሆነ አካል በግልጽ ሊመረመር ይገባዋል፡፡

እስካሁን የሚሰማው በመንግስትና በተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች እይታ እንጂ ትክክለኛውን እውነት ይህ ነው ብሎ ለመደምደም ብዙ መረጃ ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁኔታ ዳግም እንዳይከሰት ከተፈለገ የእስካሁኑን ሁኔታ በአግባቡ በነጻ አካል መመርመር እውነታውንም ለህዝብ ማሳወቅና ይህ እንዳይደገም የሚያግዝ አሰራርን ተግባራዊ ማደረግ የግድ ይላል፡፡ከ 600 ሽ ሰው በላይ ሞቶ፣ በበዙ ቢሊየኖች የሞቆጠር ጥፋት ደርሶ፣ ምንም እንዳልተካሄደ ማንም ተጠያቂ ሳይሆን ደፍፍኖ ማለፍ ይችን ሀገራችንን ለሌላ ጥፋት ማዘጋጀት ነው፡፡ ሰለዚህም ይህ ሁኔታ በነጻ አካል በአግባቡና በህዝብ ፊት በግልጥ ሊመረምር ይገባዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተከትሎም የተፈጠርው ቁርሾ ሊወገድ የሚችልበትን የብሄራዊ እርቅ ማካሄድ ያሻል፡፡ ሰለዚህም ሁሉም ዜጋ የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በነጻ አካል ይጣራ እውነቱንም እንወቀው በሚል ራእይ ስር ሊሰባሰብና ድምጹን ሊያሰማ ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

ለማጠቃለል የትግራይ ህዝብ ሊሂቃኑን ጨምሮ አዲስ በተፈጠረው የፖለቲካ እውነታ ውስጥ አዲስ እይታ አዲስ አሰላለፍን አዲስ ትብብርን ሊያማትር ያስፈልጋል፡፡ እስታተስኮው ወይም ነባሩ አሰተስብና አካሄድ ትግራይንም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያኖችን በስፋት ይጎዳል፡፡ ይህም ሰለሆነ እንዲለወጥ ያሻል፡፡ ሀገ መንግስቱ በይዘቱ የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጰያዊ በተለይም ከጎረቤቶቹ አፋርና አማራ ማህበረስቦች ጋር በጥርጣሬና በግጭት እንዲኖር የሚያደርግ እንደተፋጠጠ፣ በጠላትነት እንዲተያይ የሚጋብዝ ሰለሆነ እንዲቀጥል ፍፈቀድ ሁሉንም የማህበረስብ ክፍሎች የሚጎዳ ነው፡፡

የትግራይ አማራና አፋር የርስ በርስ ውጊያ እነዚህን አካባቢዎች ከማውደምና ህዝቡንም ለቀጣይ ስቃይ ከመጋበዝ ውጭ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ይህ የሚጠቅመው በግጭት የሚጠቀሙ ክፍሎችን ብቻ ነው፡፡ ይህን በቃ ማለት ከትግራይ፣ ከአማራና ከአፋር እንዲሆም ኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያልሙ አባቶች እናቶችና ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን ይጠበቃል፡፡
ይህን ለመጀመርም ጊዜው አሁን ነው፡፡

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here