spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeአበይት ዜናኢትዮያጵዊያንን አንድ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖረን የሚያደርገውን  የትምህርት ፖሊሲና ረቂቅ የትምህርት...

ኢትዮያጵዊያንን አንድ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖረን የሚያደርገውን  የትምህርት ፖሊሲና ረቂቅ የትምህርት ሕግ በምክንያት እቃወማለሁ።  

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ምሁራንና ባለሙያዎች የቀረበ የህዝብ ማመልከቻ ማመልከቻዉን ለመፈረም ይህን ተጫኑ  

Ethiopian News _ Language

መጋቢት 24፣ 2015 ዓ.ም. 

የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፤ 

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢትዮጵያዊያን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖረን ፖሊሲና ረቂቅ የትምህርት ሕግ ቀርፆ ለመተግበር ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይህ ጊዜ ሕዝባችን በአንድነት አገራዊ ቋንቋውን እና ትምህርትን ተጠቅሞ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያውና ፖለቲካዊ ችግሮቹን ለመፍታትና የአገር አንድነትን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ዕርብርብ ማድረግ የሚኖርበት ዘመን ነው። ለዚህም የአገር አንድነት፣ ሰላምና እድገት ራዕዩ የሆነ የትምህርት ፖሊሲ ያስፈልጋል። መንግሥት ግን አገርን የሚከፋፍልና ሕዝብን የሚያራርቅ፣ ህዝብ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲሄድ ባይተዋር የሚያደርግ፣ አንድ የጋራ ቋንቋ አንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዳይማር የሚያደርግ፣ የትምህርት ፖሊሲ አውጥቷል። 

የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በጥናት ከደረሰባቸው የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች ባፈነገጠ አሠራር የብልጽግና መንግሥት እመራበታለሁ የሚለዉን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎችን በመጣስና በጎሳ ፖለቲካ ውሳኔ አደገኛና ከፋፋይ የትምህርት ፖሊሲ ለመተግበር እየተሯሯጠ ይገኛል። በ 1986 ወጥቶ በነበረው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አማርኛ ለአገራዊ መግባቢያነት በአገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መሰጠት እንዳለበት በግልጽ ይደነግ ነበር። አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ግን ይህን ድንጋጌ ሰርዞታል። ይህ አገርጎጂ የትምህርት ፖሊሲና ረቂቅ የትምህርት አዋጅ እንዲቆም የስነትምህርት ምሁራን የትምህርትና ቋንቋ ፖሊሲ ውይይት ምክረ ሃሳብን ከማሳወቅ በተጨማሪ ለትምህርት ሚኒስትሩ ግልጽ ደብዳቤ በመጻፍ ብዙ ጥረት ብናደርግም፣ ምላሽ አላገኘንም። በፖለቲካ ውሳኔ ይህ ፖሊሲ እንዲጸድቅ ተደርጓል። ይህንን አደገኛ ኢትዮጵያዊያንን የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ የሚያሳጣ የፖሊሲ አካሄድ በጽኑ በመቃወም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያወግዘውና በሥነ ትምህርት ባለሙያዎች መሪነት አዲስ የትምህርትና የሥልጠና ፖሊሲ እንዲቀረፅና ተግባራዊ እንዲሆን ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስድ አስቸኳይ ጥሪ እናደርጋለን። በተጨማሪም በትምህርት ፍኖተ ካርታው ምክረ ሃሳቦችን መሰረት፣የፌደራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ፣ ለአገራዊ መግባቢያነት በአገሪቱ ትምህርት ቤቶች ሁሉ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ የሚያደርግ ፖሊሲ እንዲወጣ እንዲደረግ አጥብቀን ጥሪ እናደርጋለን። 

የተከብርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ 

የሃገራችን ኢትዮጵያ ልማትም ሆነ የሕዝቧ ኑሮ መሻሻልና በሥልጣኔ ዕርምጃ ወደፊት ለመጓዝ የትምህርትና የተማረ ዜጋ ሚና ከፍተኛ ነው። አንድ አገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ የሌለውና ትምህርት ላይ ትኩረት ያልሰጠ ሃገር ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ አይቻለውም። የዓለም ማህበረሰብ ዕውቀት-መር ወደ ሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት በፍጥነት እየገሰገሰ በአለበት በዚህ ዘመናችን በጥራትና በስፋት የሠለጠነ የሰው ሃብት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ትክክለኛና አዲስ የትምህርት ዘርፍ ፖሊሲ መቅረጽና ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።

ትምህርትና ዕውቀት የሥልጣኔ መሰረት ነው። አሁን በኢትዮጵያ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙትን ከ26 ሚልዮን በላይ ተማሪዎችንም ሆነ ቀጣዩን ትውልድ በትምህርትና በዕውቀት ታንፆ የሚያድግበት ምቹ አውድ መፍጠር ያስፈልጋል። ታዳጊ ዜጎቻችን በዕውቀት፣ በአንድነት፣ በሃገር ፍቅር፣ ለሕዝብ አገልጋይነት ዝግጁ ሆነው ትምህርት የመቅሰም መሰረታዊ ሰብዓዊ መብታቸው ነው። የሕዝባችን ኑሮውና ሕይወቱ እንዲሻሻል የትምህርትና ዕውቀት ሚና ትልቅ ነው። ሆኖም ግን በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ገደብ ያልተበጀለት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የመማር ማስተማርን ሥርዓት ከማናጋት አልፎ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዳያገኙ፤ መምህራን በሙያ ዘርፋቸው በነፃነትና በሃላፊነት ሥራቸውን እንዳይሠሩ የማድረግ ወንጀል ይኸው ብዙ አሥርት ዓመታትን አስቆጥሯል። ይህንን መሰል የሰው ሃብት ብክነትና የተበላሸ የትምህርት ፖሊሲ ልጆችህ ተገቢውን ዕውቀት ለመቅሰም ሳይችሉና ለራሳቸውም ሆነ ለሃገራቸው ሊያበረክቱ ይችሉ የነበረውን ሁሉ ሳያበረክቱ ቀርተዋል። የዚህ ብልሹ አሠራር ለሃገራችን እናም ለሕዝቧ ከፍተኛ ችግሮችን መፍጠሩን በብዙ መልኩ ለመገንዘብ ችለሃል። በመሆኑም የትምህርት ፖሊሲውን በፍጥነት ማስተካከል አስቸኳይ እርምጃ የሚፈልግ ሃገራዊ ጉዳይ መሆኑን በጽኑ ለማስገንዘብ እንወዳለን። 

የትምህርት ፖሊሲ ችግሮች ተያያዥ ተግዳሮቶችን አብረው እየወለዱ ይገኛል። አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ስለአገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ጉዳይ “አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል” በማለት በአንቀጽ 5፣ ቍጥር 2  ላይ ደንግጓል። በተጨማሪም የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን በተመለከተ በ1986 .. ያወጣው ፖሊሲ ቍጥር 3.5.4፣ አማርኛ ቋንቋ ለአገራዊ ተግባቦት በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ላይ ያተኮረና በሃገሪቱ ከፍተኛ የሥነ ትምህርት ባለሙያዎች የተሳተፉበት የጥናት ቡድን አጽንዖት ሰጥቶ ያቀረበው ምክረ ፖሊሲ ሃሳብ ለሃገራዊ መግባቢያነት አማርኛ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ ትምህርት ተጠናክሮ መሰጠት እንዳለበት በጥኑ አሳስቧል። በአሁኑ ወቅት በሕገ መንግሥቱ አማርኛ ብቸኛው የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሲሆን ይህንን ቋንቋ በትምህርት ቤቶች በተገቢው ጥልቀትና ጊዜ መማር ያልቻሉ ተማሪዎች ላይ በትምህርትም ሆነ በሥራ ገበታቸው ላይ አሉታዊ ሳንካ ይፈጥራል። አንድ ሃገራዊ መግባብያ ቋንቋ አስፈላጊነት እየታወቀ፤ ለዚህም ብቁ የሆነው የአማርኛ ቋንቋና ፊደል ያለን ማህበረሰብ ሆነን ሳለ አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳን ከመጽደቁም በፊት አደገኛና ሕገ ወጥ ፖሊሲ በሥራ ውሏል። 

የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውስጣዊና ሥርዓታዊ የፖሊሲ ችግሮችና ተግዳሮቶች ላይ ወድቋል። በመሆኑም የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻል በጥናትና በትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች የመሪነት ሚና እንዲጫወቱና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበና ትክክለኛ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ መተግበር የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የተበላሸ የትምህርት ፖሊሲ ሰለባ የሚሆኑት ተማሪዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ መላው ማህበረሰብ በተለይም መምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ በአጠቃላይ፤ ወላጆች፤ ከተማሩት ልጆቹ ማህበራዊ ችግሮቹን ለመፍታት ተስፋ ያደረገውን ዜጋ በሙሉ ሲሆን በወልም ሃገራችን ኢትዮጵያንም ከዕርስበርሰ መገዳደል፣ ከድህነትና ኋላቀርነት አረንቋ እንዳትወጣ የሚያደርግ ነው። 

የትምህርት ፖሊሲውን በአደገኛ ፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና የኢትዮጵያ ህልውናን ለመሸርሸር የሚታገሉ አካላት በሕዝባችን ላይ ለመጫን ድብቅ እንቅስቃሴ መኖሩ አሳስቦን የትምህርት፣ የታሪክና የፖሊሲ ሙያተኞችን ያሳተፈ ውይይትና የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝባችን እንዲያውቀው ተደርጓል (ውይይት ክፍል 1፣ ውይይት ክፍል 2)። የትምህርት ሚኒስቴርም እያቅማማም ቢሆን ደብቆት የነበረውን ረቂቅ ሰነድ ጥር 6፣ 2015 ዓ.ም. ይፋ ለማድረግ ተገዷል። እንዲሁም የካቲት 20፣ 2015 ዓ.ም. ይህን ረቂቅ ሰነድ ፖሊሲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጽድቆታል። ሊኖረን ይገባ የነበርውን አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ አስመልክቶ ፖሊሲውና ረቂቅ የትምህርት አዋጁ እንደሚከተለው ብሎ አልፎታል፤ 

አንድ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ከፌደራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪው/የወላጅን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ በየደረጃው ባለው የትምህርት መዋቅር ተወስኖ ከ3ኛ እስከ 10ኛ ክፍል የሚሰጥ ይሆናል።” 

ይኸ ከመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ የዋለው የትምህርና ሥልጠና ፖሊሲ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት ምክረሃሳብ በመቃረን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለዘመናት የአገራዊ መግባቢያና የሥነጽሑፍ ልሳን አድርገው ያቈዩትን ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያበለጸጉትንና ያሳደጉትን የአማርኛ ቋንቋን እንደ አንድ ትምህርት ዓይነት እንዳይሰጥ ያደርጋል። በመሆኑም በአፍሪቃ ብቸኛ የሆነውን አገራዊ የጽሑፍ ቋንቋ እንደ አገራዊ ትምህርት እንዳይሰጥ የማድረግ ሸፍጥ ስውር ዓላማው ለሺህ ዓመታት በነፃነት ጮራ ያልደበዘዘባት አገራችንን የመናድ፣ ዜጎቿም ዕርስበርሰ እንዳይግባቡና የገዛ አገራቸውን የጋራ ልሳን የማሳጣት፣ እንዲሁም የሕዝባችንን አንድነት የሚያናጋና የአገሪቷ ህልውና መሰረት የሚሸረሽር አደገኛ ፖሊሲ ነው። 

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ቀውስና አስቸጋሪ የሰላም ዕጦት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ ሥርዓት ነጸብራቅ የሆነውና አደገኛው የትምህርት ሥርዐቱ ነው። በይበልጥም፣የትምህርቱ ጥራትና ፋይዳ ተሻሽሎ፣ አገሪቱን ከገባችበት ችግርና ማጥ ለማውጣትና ለአገር መግባባት፣ ምክክርና አንድነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ አሁንም መንግሥት ትምህርትንና ዜጎችን በቋንቋና በብሔር ይበልጥ ለመከፋፈልና ለማጋጨት በመጠቀም አደገኛ ሁኔታን እየፈጠረ ነው። 

ምሁራን በውይይቱ በጥልቅ ከተወያዩበትና ታሪካዊና ሥነትምህርታዊ እንደምታዎችን በመመርመር የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲን በተመለከተ የሚከተሉት ጉዳዮች ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስቸኳይ ትኩረትና ማስተካከያ እንዲወሰድ ጫና እንዲፈጥር ጥሪያችንን እናቀርባለን። 

1. የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናትን በመመርኮዝ አዲስ የትምህርት ፖሊሲ እንዲቀረፅና በሁሉም ትምህርት ቤቶች ሥራ ላይ እንዲውል። አገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ በፈጠረው ችግር ተወጥራ እያለ፣ ሕዝብ ያልመከረበት፣ ከሕጉና ራሱ ትምህርት ሚኒስቴር ካስጠናው ጥናት ተቃራኒ የሆነ ፖሊሲና ሕግ በድብቅ አዘጋጅቶ ማውጣትና፣ በይፋ ሳይጸድቅ ተግባርዊ ማድረግ አገርን አደጋ ላይ ይጥላል። ስለዚህ አሁን ድረስ ባለውና በ1986 ዓ.ም. በወጣው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲና እንዲሁም በኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት መሠረት፣ በሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የፌደራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ለአገራዊ መግባቢያነት በመላው የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንደአንድ ራሱን የቻለ ትምህርት አላንዳች ሕገ ወጥነት ለሁሉም እንዲሰጥ እንዲደረግ። 

2. የትምህርት ሥርዓቱ ከማናቸውም የፖለቲካና ሃይማኖታዊ ተፅዕኖዎች ነፃ ሆኖ እንዲዋቀርና ትምህርትን በጥራትና በስፋት በማዳረስ ላይ ማተኮር ይኖርበታል። ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ ዘጠና በቊጥር ሁለት “ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ፣ አመለካክቶችና ባህላዊ ተጽዕኖዎች ነጻ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት።” ሲል እንዲሁም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሥልጣን አስመልክቶ በሚገልጻው አንቀጽ ስባ ሰባት ቍጥር ስድስት መሰረት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራተጂዎችን ይነድፋል ያስፈጽማል።” ይላል። አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ክልል-ተሻጋሪ ስለሆነ፣ ፖሊሲውን የማውጣት ሥልጣኑ ለክልል የሚተው ሳይሆን፣ የፌደራል መንግሥት ሥልጣን ነው። ስለዚህ የአገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ጉዳይ፣ ከተራ የዘውግ ፖለቲካ እንዲለይና፣ የቋንቋ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይበልጥ ማቀራረቢያ፣ ማገናኛ፣ ማስተባበሪያ፣ ማስተሳሰርያና አገር መገንቢያ እንጂ የመከፋፈያና የጥላቻ መዝሪያ መሣሪያ እንዳይሆን። 

3. በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በሥርዐተ-ትምህርት ጉዳዮች ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ-ገብነት በአስቸኳይ እንዲቆም፤ ጉዳዩ ለዘርፉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲተው፤ ለባለሙያዎቹም ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም-ዐቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል። 

4. የትምህርት ሥርዓቱ አማርኛ ቋንቋን በማበልጸግ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቀመር [ኮምፒዩተር]፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መማሪያና የምርምር ቋንቋ እንዲሆን፣ ሌሎችም የአገራችን ቋንቋዎች ተደጋግፈው የሚዳብሩበትና የሚያድጉበት ሥልታዊ ዕቅድ በባለሙያ በማውጣት ሥራ እንዲሠራ። 

5. በቋንቋና በክልል መዝሙር ሰበብ የኢትዮጵያ ለጋ ሕፃናትን በዘውግ መለያየት፣ ወይንም በውስጣቸው የጎሳ ጥላቻ ዘር መዝራት አሳፋሪና አገር የሚያፈርስ አደገኛ ተግባር መሆኑ ታውቆ እንዲቆም እንዲደረግ። ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጥላቻንና የጎሳ መለያያ ቦታ ሳይሆኑ፣ መተሳሰብን፣ አካታችነትን፣ አብሮነትን፣ ሕግ አክባሪነትን፣ በምክንያት ማሰብና መወያየትን፣ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን የአገር ፍቅርንና የጋራ አገራዊ ራዕይና አመለካከትን የሚያዳብሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ተገቢው ሥራ እንዲሠራ እናሳስባለን። 

People to People (P2P) Inc.  

Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI)

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የኢትዮጵያ ድርጅቶች ይህን የሕዝብ ማመልከቻ አጽድቀውታል። 

1. Adwa Great African Victory Association (AGAVA) 

2. All Shewa Ethiopian People Multipurpose International Association 3. Amhara Dimtse Serechit 

4. Amhara Well-being and Development Association 5. Communities of Ethiopians in Finland 

6. Concerned Amharas in the Diaspora 

7. Ethhub 

8. Ethio-Canadian Human Rights Association 

9. Ethiopian Advocacy Network (EAN) 

10. Ethiopian American Civic Council (EACC) 

11. Ethiopian American Development Council (EADC) 12. Ethiopian Civic Development Council (ECDC) 

13. Ethiopiawinnet: Council for the Defense of Citizen Right 14. Freedom and Justice for Telemt Amhara 

15. Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause 

16. Global Amhara Coalition 

17. Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI) 

18. Gonder Hibret for Ethiopian Unity 

19. Major Lemma Woldetsadik Memorial Foundation 20. Network of Ethiopian Scholars (NES) 

21. People to People (P2P) Inc. 

22. Radio Yenesew Ethiopia 

23. Selassie Stand Up, Inc. 

24. The Amhara Association in Queensland, Australia 25. The Ethiopian Broadcast Group 

26. Tinsae Le’Ethiopia

_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here