spot_img
Saturday, April 20, 2024
Homeነፃ አስተያየትአንድም ሶስትም ፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የ 2012 ዓ.ም የኖቤል የሰላም...

አንድም ሶስትም ፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የ 2012 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚው የዐብይ አህመድ ሰለስቱ ማንነቶች 

(ዐብይ ሰባኪው ፤ ዐብይ ተዋኒው እና ዐብይ አጼ በጉልበቱ

በቅድሚያ የዚህ ጽሁፍ ባለቤት ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ተርጉሜ እንዳቀርበው ስለፈቀዱልኝ አመሰግናለሁ። ጸሃፊው ፕ/ር ግርማ ነዋሪነታቸው በስዊድን ጎተንበርግ ከተማ ሲሆን ጽሁፉ የታተመው ዩሮኤዥያ ሪቪው በሚባል የበይነመረብ ጋዜጣ ላይ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር [እ.አ.አ.] ግንቦት 23/2021 ዓ.ም) ነው። በእንግሊዘኛ የተጻፈውን ለማንበብ ይህንን ተስፈንጣሪ ይጫኑ። ይህንን ጽሁፍ ለመተርጎም ያነሳሳኝ አገራችንን ወደ አዘቅት ለመክተትና ከአለም ካርታ ላይ ለማጥፋት እንቅልፉን አጥቶ ቆላ ደጋ የሚሮጠው የኦነጋዊው መንግስት ቁንጮውን መሰሪ፤ አምባገነን፤ አስመሳይና ጮሌ ማንነቶች በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች፤ ጋዜጠኞች በግለሰቡ ፖለቲካዊ ማንነት እና ፍላጎት ዙሪያ በከተቧቸው ጽሁፎች ላይ በመመርኮዝ እና የሩዋንዳውን ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ በአገራችን በየእለቱ እየደረሰ ካለው እልቂት ጋር ያለውን ተመሳሳይነት በማያያዝ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይና የኢትዮጵያም ህዝብ ይሄንን መራር ሃቅ ተገንዝቦ ጊዜው እጅግ ሳይረፍድ አስፈላጊውን አገርንና ወገንን የማዳን እርምጃ ለመውሰድ ያግዘዋል በሚል እሳቤ ነው። በቅድሚያ አንባቢያን እንዲረዱልኝ የምፈልገው በስነጽሁፍ ደንብ መሰረት ዋናው ጽሁፍ ለአማርኛ እንዲመች ቃል በቃል እንዳልተተረጎመና ኢምንት የሆኑ የተርጓሚው አተያዮችና እንዲሁም ጽሁፉ ከታተመ በኋላ የተከሰቱ ሁነቶች በትርጉም ስራው ውስጥ የተካተቱ ሲሆን የዋናው ጸሃፊ ባልሆኑት ሃሳቦችና ወቅታዊ ሁነቶች ራስጌ ላይ ባለ አንድና ሁለት ኮከቦች ተቀምጠዋል። አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን ነን ባዮች እና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ስለ ኦሮሞ ብሄር አመጣጥ እና ታሪክ የፈበርኳቸውን የውሸት ትርክቶችና ታሪኮች በተመለከተ ጸሃፊው የሰጡት ተጨማሪ የማፍረሻ ሃቆች ደግሞ በባለአራት ኮከቦች ምልክት ተለይተው የግርጌ ማስታወሻው ላይ ተቀምጠዋል። ተርጓሚው ተጨማሪ ማጣቀሻዎችን በማስገባቱ የማጣቀሻዎቹ ቅደም ተከተል ላይ መጠነኛ ለውጥ መደረጉን አንባቢዎች እንዲገነዘቡ እጠይቃለሁ። በተለየ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር የዘመን አቆጣጠሮቹ በሙሉ የኢትዮጵያን የዘመን ቀመር ላይ የተመርኮዙ ናቸው። ነገር ሳላንዛዛ በቀጥታ ወደ ጽሁፉ እንግባ። 

መግቢያ 

ህዝብ ብሶቱን በትክክል የሚያዳምጡ መሪዎችን ከመጠን በላይ ያከብራል። – ሰር ዊንስተን ቸርችል 

ሁሉንም ታላላቅ መሪዎች አንድ የሚያመሳስላቸው ባህሪ ቢኖር፡ በአገዛዝ ዘመናቸው የህዝባቸውን ዋነኛ 

ስጋት በማያሻማ ሁኔታ ለመጋፈጥ ያላቸው ፍቃደኝነት እንጂ [አጽኖት የራሴ] ሌላ ምንም አይደለም። ይህ 

የተዋጣላቸው መሪዎች መሰረታዊ መለያ ከሆኑት ዋነኛው ነው። – ጆን ኬኔት ጋልብራይት

በ2010 ዓ.ም፣ ዐብይ አህመድ ቃለ መሃላ ከፈጸመና የአፍሪካ የወደፊት ብሩህ ተስፋ ነው ተብሎ በሰፊው ከተወራለት ከጥቂት ወራት በኋላ፣ አንድ ነገር ትክክል እንዳልሆነ ይሰማኝ ጀመር። እንደምታስታውሱት ከ27 ዓመታት የ ትግራይ ህዝብ ነጻነት ግምባር (ትህነግ) አምባገነናዊ አገዛዝ ሀገሪቱ ከተንገፈገፈች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየእለቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዐትን ለማምጣት “ደፋ ቀና” ይል የነበረበት ዓመት ስለነበር መቼም ያኔ ዐብይ አህመድን መጠራጠር ማለት እብደት ነበር። በወቅቱ ከ30 ዓመታት በላይ 

ስልጣን ወይም ሞት ያሉ ፖለቲካኛ ማቱሳላዎች ከነበሩት እንደ ዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ፣ የካሜሩን ፖል ቢያ ወይም የኢኳቶሪያል ጊኒው ቴዎዶሮ ኦቢያንግ አንጻር ሲታይ አፍሪካ ውስጥ ውስጥ የኢትዮጵያው ጠ/ምኒስትር የአህጉሪቱ በእድሜ በጣም ወጣት መሪ ነበር። እናማ እንኳን ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጨምሮ በዐብይ አህመድ ፍቅር እፍ ብለን ከነፍን። እንዲህ አይነቱ በጎና መጥፎ የሆኑ ጎኖችን ሳያመዛዝኑ የሚሰማ መጠኑን የለቀቀ ስሜታዊ ሁለንተናዊ መነቃቃትን ፈረንጆቹ ማኒያ ብለው ይጠሩታል። በወቅቱ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የሌላ አገራት ዜጎች ለማምለክ በሚጠጋ መልክ ለዐብይ አህመድ ያሳዩትን ቅጥ ያጣ ፍቅር ፈረንጆቹ ዐብይማኒያ ይሉታል። ለዚህ ቃል የአማርኛ አቻ ስለሌለ እንደወረደ ለመጠቅም በመገደዴ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህ ስያሜ በውዳሴ ከንቱ ለተለከፉት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎች የሚመጥን መገለጫ ነው። በትህነግ ገደብ የለሽ የ27 ዓመታት አምባገነናዊ ስርአት የተማረረውንና በአገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ የሚኖረውን በሚልዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ እንዲሁም የውጭ አገር መንግስታትን ለማማለል ዐብይ ስልጣን እንደጨበጠ እነዚህን ስርነቀል የሚባሉ ርምጃዎች ወሰደ። ለአብነት፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የማሰቃያ ማጎሪያዎች ውስጥ ታስረው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የተገዳዳሪ ፖለቲካ መሪዎችንና (አንዳርጋቸው ጽጌ፤ አንዷለም አራጌ፤ በቀለ ገርባ ወዘተ)* ተከታዮቻቸውን፤ ጋዜጠኞቹንና (እስክንድር ነጋ፤ ውብሸት ታዬ፤ ወዘተ)* ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እንዲፈቱ አደረገ፤ 

በውጭ የሚኖሩ (እንደነ ታማኝ በየነ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ)* ወዘተ ያሉ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የተቃዋሚ ፖለቲካ ማህበር መሪዎችንና አባላትን እና (በስደት ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሲኖዶስ ጳጳሳት)* ወደ አገርቤት እንዲገቡ አደረገ፤ በእኔ ዘመን አንድም ሰው ያለወንጀል አይታሰርም፤ሙስናን ታሪክ አደርገዋለሁ፤ መገናኛ ብዙሃን ያሻችውን መጻፍና መዘገብ ይችላሉ የሚሉ መግለጫዎችን ሰጠ፤ 

ከሁሉም በላይ ግን ለ 2 አሰርት ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮ ኤርትራ ፍጥጫ በ “ሰላም*” እንዲፈታ ባደረገው ጥረት ምክኛት የ2012 ዓመተምህረቱን የዓለም የኖቤል የሰላም ሽልማትን ለመሸለም በቃ። 

በመለጠቅ መደመር የሚባለውን (በማን እንደጻፈ የማይታወቅ የአማካሪው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ድርሰት እንደሆን ይታማል)**፤ ቢከፍቱት ተልባ የሆነውን ሃሳዊ የፍልስፍና ተረትተረት ተብዬውን አሳትሞ አሽቃባጭ የመገናኛ ብዙኋኖችና ተከፋይ ካድሬዎች ዝናውን በማራገብ ሰማይሰማያት ሰቀሉት። 

በዚህ ውዳሴ ከንቱ የልብልብ የተሰማው ዐብይ አህመድ አይኑን በጨው አጥቦ ያለምንም 

ሃፍረት ይሄንን ተረትተረቱን በመጠቀም ብቻ የኢትዮጵያን ዘመናት ያስቆጠሩ ችግሮች ለአንዴና 

ለመጨረሻ ጊዜ ይፈታል ብሎ በድፍረት ተበጠረቀ።

ጥድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ፤ እንኳንስ እነዚህ ዘመን ጠገብ ችግሮች ሊፈቱና ከአምስት ዓመታት የስልጣን ዘመኑ በኋላ በአሁኗ ሰዓትና ደቂቃ ኢትዮጵያና ኢትዮጵውያን ያሉበትን አሳሳቢና ፈታኝ ሁኔታዎች መግለጽ ለቀባሪው ማርዳት ነው።** በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የደሃ ልጆችን ያስጨረስ እና አገሪቷ በብድርና በልመና ያገኘችውን የውጭ ምንዛሪ ያሟጠጠ ጦርነት፤ ማቆሚያ ያልተገኘለት ማንነት እና/ወይም እምነት ተኮር ጭፍጨፋ፤ዝርፊያ፤ ማፈናቀል፤ ሰማይ ጥግ የደረሰ የኑሮ ውድነት፤ ጎጠኝነት፤ ተረኝነት፤ ስራአጥነት፤ አይን ያወጣ ሙሰኝነት፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፤ ስርዓት አልበኝነት፤ በጠራራ ጸሃይ ዝርፊያ ወዘተርፈ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ መድረሻ ካሳጡ ችግሮች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።** 

ዐብይ በስልጣኑ መጀመሪያ አመታት ላይ ያካሄዳቸው ዲሞክራሲያዊ፤ ምጣኔሃብታዊና ማህበራዊ ለውጦችና ማሻሻያዎች ሊመሰገን ቢገባም ከመጋረጃ ጀርባ ስልጣኑን ለማጽናት አብሯቸው ላለፉት ዓመታት ስርዓቱን ሲያገለግሉ በነበሩ ባልደረቦቹ ላይ የፈጸማቸው ደባዎች፤ እንዲሁም የኢትዮጵያን ህዝብ በላም አለኝ በሰማይ ተስፋዎች በማታለል ብዙ ተከታዮችን ለማግኘት የፈጸማቸው ድርጊቶች ከእነዚህ ወንጀሎች ነጻ አያደርጉትም። ለሶስት አሰርት ዓመታት ጥርሳቸውን በነቀሉበት የጎጥ ስርዓት በመመስረት ስልጣናቸውን ሲያደላድሉ የነበሩትን የጡት አባቶቹን ገሽሽ ሲያደርጋቸው በጸጋ ይቀበሉታል ብሎ ማሰብ አንድም ጥግ የደረሰ ራስ ወዳድነት አልያም ፖለቲካዊ መሃይምነት አልያም ሁለቱም ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን በተቀበለና (የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከቡራዩ እስከ ሻሸመኔ፤ አምቦና በሌሎች የኦሮሞ ክልል ከተሞች ወስጥ በሚኖሩ ኦሮሞ ባልሆኑ በተለይም በአማራዎች ላይ በተቀነባበረ ሁኔታ የተፈጸሙት እጅግ ሰቅጣጭ፤ አሳፋሪና ታሪክ ይቅር የማይላቸው በንጹሃን ላይ የተደረጉ ጭፍጨፋዎች፤ ማፈናቀሎች፤ የንብረት ማውደምና ዝርፊያዎችን*) ለማስቆም አንዳችም ጥረት አላደረገም ብቻ ሳይሆን ወንጀለኞቹን ለፍርድ እንዲቀርቡ አላደረገም። ልብ ልንል የሚገባው እነዚህ ማንነት ተኮር ግድያዎች፤ ዝርፊያዎችና ማፈናቀሎች ድንገቴ ሳይሆኑ ወያኔ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ከስልጣን ላይ ካባረራቸው በኋላ ኤርትራ በርሃ መሽገው የነበሩትና ዐብይ አህመድ 

ስልጣን ሲጨብጥ ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በተቀበላቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ነፍሰ ገዳዮችና ዐብይን ለስልጣን ያበቁት ቄሮዎች በቅንጅት በደንብ የተቀነባበሩና የተጠኑ ሲሆን እነዚህ ወንጀሎች ያለገዥው ፓርቲ እውቅናና ይሁንታ ተካሄዱ ማለት አንድም በአማራ እና በኢትዮጵያ ጠልነት ላይ የተመሰረተውን የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ማንነት እና የዐብይን መሰሪ ባህሪያት አለመገንዘብ ነው አልያም ራስን ማሞኘት ነው።* 

ዐብይ አህመድ የገባቸውን ከሰማይ መና አወርዳለሁ ቃልኪዳኖች ባለፈጸሙና ሊፈጽም 

ባለመቻሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ቢሞቱም ዐብይ አህመድን 

ያለማቋረጥ ዛሬም በእየለቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙኋን ፈታ ዘና ብሎ ለማየት ችለናል።

ይህ በጉልህ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ለምን ቢባል ለኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት ከነበሩት መሪዎች በተለይም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ሲነጻጸር የዐብይ በተደጋጋሚ ከተራው ህዝብ ጋር መታየት ትልቅ ለውጥን ያመለክታል። የኢትዮጵያ ህዝብ መለስ ዜናዊን በ25 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ በቴሌቪዥን መስኮት ለማየት የታደለው በጣት በሚቆጠሩ ጊዚያት ነው፤ ለዛውም ተኮሳትሮ እና እኔ አውቅላችኋለሁ ብትፈልጉ ተቀበሉ፤ ካልፈለጋችሁ ገድል ግቡ አይነት ባህሪ። መለስ ዜናዊ ይደነቅ የነበረው በስል አእምሮው እንጂ በሩህሩነቱ አልነበረም። የእሱን ሃሳብ እንቀበልም ያሉትን ሁሉ ድራሻቸውን አጥፍቶታል። 

ኢትዮጵያ ወደመቀመቅ እየተንደረደረች ባለችበት በዚህ ፈታኝ ወቅት የዐብይ ፖለቲካዊ ትወና ማንነት ተኮር የሆነውን የጅምላ ጭፍጨፋውን ለመካድ የሚደረግ የተራቀቀ ስልት ነው ወይንስ የፖለቲካዊ አመራር ብቃት ማነስ ውጤት ነው ብለን ራሳችንን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ሆኖም ግን መልሱ እንዲህ ቀላል አይደለም። ከዐብይ አህመድ ፈገግታ ጀርባ የሆነ የተደበቀ ጭራቅ የለም ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ዐብይ አህመድን የመሰለ ብቃት የሌለው ፖለቲከኛ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ትንቅንቅ ባህል በነገሰባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሪነት ስልጣን መብቃቱ ሌላው የሚያስደምም ጉዳይ ነው። ምናልባትም ዐብይ አህመድ ሁለገብ ብቻ ሳይሆን እነዚህ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ የማንነቶቹ (ተዋኒሰባኪአጼ በጉልበቱ) ባህሪያት አንዳቸው ካንዳቸው ጋር ሳይተዋወቁ ተዳብለው በጸጋ ይኖራሉ ለማለት ያስደፍራል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የየራሳቸው ስሜት፣ ባህሪ እና ልምድ ያላቸው ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ማንነቶችን እንደሚላበስ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ዐቢይ ሰባኪው ከዐብይ ተዋናዩ የበለጠ ደግ መስሎ ቢታይም ከአጼ በጉልበቱ ዐብይ ጭካኔ ጋር በፍጹም አይገናኝም። 

ዐብይ ተዋኒ – ገና በለጋ እድሜዩ እናቴ ሀገሪቱን ለመምራት ‘እንደተመረጥሁ’ እና 7ኛው የኢትዮጵያ ንጉስ እንደምሆን ተንብያለች፤ ሰባኪው ዐብይ – ኢትዮጵያዉያን ሃላፊነት የተሞላዉ የዲሞክራሲያዊ አገዛዝ እና መልካም አስተዳደር ያስፈልጋቸዋል፤ 

ዐብይ አጼ በጉልበቱ – ማረሚያ ቤቶቹ እንደገና በህሊና እስረኞች ከአፍ እስከገደፋቸው እንዲሞሉ አድርጓል፣ እሱ ከሚከተለው ሃሳብ ያፈነገጠ አስተሳሰብ ያሰሙ ተራ ተማሪዎችን በመንግስት ታጣቂዎች የጥይት ራት እንዲሆኑ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ ያለማቋረጥ በማንነታቸው ምክንያት ለሚገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን ዜጎች እና ወላጅ አልባ ህጻናት እጁ በደም ጨቅይቷል።* 

እስኪ አሁን የዐብይ ማንነቶችን በዝርዝር እንመልከት 

ዐብይ ተዋኒ 

በዚህ ረገድ ከመለስ ዜናዊ ጋር ሲነጻጸር ዐብይ አህመድ እጅግ በጣሙን ይለያል። የደስደስ ያለውና ፈገግታ ሁሌም ከፊቱ የማይጠፋ ሲሆን የማህበራዊ ትስስር ሚዲያውን ከማንም በላይ አቀላጥፎ እየተጠቀመበት ነው። ምንም እንኳን በሚሊዮን 

የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን አግኝተው ሊጠግቡት ባይችሉም። ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ወደ ፍፁምነት የተቃረቡ ሁለቱን የዐብይ ማንነቶች ለማየት ችለዋል፤ ማለትም ዐብይ ተዋኒውን እና ዐብይ ሰባኪውን። ነገር ግን ታዋቂነቱ እያበቃና እየተሸረሸረ የመጣው፣ አገሪቱን በእንብርክክ እያስኬድ ያለውን ዕለታዊ የጅምላ ግድያ ለማስቆም ፍላጎትም 

ፍቃደኝነትም ሊያሳይ ባለመቻሉ ነው። ይህ የታዋቂነት የጫጉላ ሽርሽር ሲያበቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣኔ የመጣ እኔን አያድርግኝ አለ እናም አጼ ዐብይ ሶስተኛውንና ሸር፤ ሸፍጥና ጭካኔ የተሞላበት እውነትኛ ማንነቱን ለኢትዮጵያውያን እነሆ ያለበት ጊዜ ነው። መቼም የሸር፤ ሸፍጥና የጨካኝ ፖለቲካ መሃንዲሱ ማኪያቬሊ** በህይወት ቢኖር በጣም ይኮራበት ነበር። 

አብዛኛውን ጊዜ እንደሚታወቀው መሪዎች መልካም ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ውጥኖች ለማሳካት የግድ በስልጣን ላይ መቆየት አለባቸው። ዙፋንን ለማጽናት በሚደረገው ሙከራ የተለያዩ በሞራልና በስነምግባር የተውተበተቡ ደንቦችን ለመጣስ ወይም ላለመጣስ ህሊናን በእጅጉ ይፈታተናል። ይሄን ጊዜ ነው እንግዲህ የስልጣን መጥፎ ገጽታ ፍንትው ብሎ የሚወጣው። አጼ በጉልበቱ ዐብይ ሁለተኛውን አማራጭ በመጠቀም በትረስልጣኑን ላለማጣት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ወደ መቀመቅ እየከተታቸው እንደሆነ ባለፉት አምስት አመታት በየእለቱ ያለማቋረጥ እየተባባሱ የመጡትና መፍትሄ ሊገኝላቸው ካልቻሉ ማህበራዊ፤ ምጣኔሃብታዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች ለመረዳት የግድ የፖለቲካ ተመራማሪ መሆን አያስፈልግም። ስልጣናቸውን ተነጥቀው መቀሌ ከመሽጉት የቀድሞ ባልደረቦቹ እየደረሰበት ካለው ተቃውሞና ዳቦ ከሰማይ አወርዳለሁ ብሎ ለስልጣን ካበቁት ተስፋ ከቆረጡበት የቄሮ ወጣቶች አንጻር ሲታይ በየጊዜው የሚጨፈጨፉትን የንጹሃን ህይወት ጉዳይ ችላ በማለት በእርሱ በሳል አመራር ኢትዮጵያ እየበለጸገች ነው በሚለው ቅዥት ውስጥ መደበቅ ይቀላል። በየቀኑ ያለማቋረጥ በጅምላ ጭፍጨፋ የሚጠፋው በሺሆች የሚቆጠሩ የአማራ ንጽኋን ህይወትና የቤተሰቦቻቸው ሃዘንና ሰቆቃ አጼ ዐብይ ካሉበት ብዙ ጉዳዮች አንጻር ሲታዩ ኢምንት ብቻ ሳይሆኑ በጭራሽ ያቺን የበለጸገች “ኢትዮጵያ” ከመገንባት ሊያደናቅፉት አይገባም። 

ዐብይ ስልጣን ከያዘበት ቀናት ጀምሮ አብዛኛዎቹ የፖለቲካና የደህንነት ጉዳዮች በእሱ ቁጥጥር ስር እንዳልነበሩ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ እንደአብነት ስልጣኑን በጨበጠ በጥቂት ወራት ውስጥ ህይወቱን ለማጥፋት የግድያ ሙከራዎች ተካሂደውበታል፤ አመጸኛ ወታደሮች ቤተመንግስቱን ሰብረው ለመግባት ጥረዋል፤ ከልላዊ የደህንነት ባለስልጣናት መንበረስልጣኑን ሊገለብጡ ሞክረዋል። 

እነዚህን በህይወቱና በስልጣኑ ላይ ከተነጣጠሩ ጥቃቶች ማምለጡን በመጠቀም አይነኬ 

መሆኑን በዐብይ ተዋኒ ማንነቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡን ለማጃጃል በቅቷል ብቻ ሳይሆን 

በርግጥም ተሳክቶለታል

የትኛው ደፋር ነው የዓለም ሰላም ሽልማት ተሸላሚውን በመንግስት ግልበጣ ከስልጣን የሚያባርረው። ተራ ኢትዮጵያዊያን ይሄንን አካሄድ ቢረዱትም ወንጀላቸው ከሌላ ብሄር በመፈጠራቸው ምክኛት ያለማቋረጥ በጅምላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በተለይም ዐብይ እወክለዋለሁ በሚለው የኦሮሚያ ክልል የሚጨፈጨፉትን ንጹሃንና ያልታጠቁ የአማራ ገበሬዎችን ጉዳይ ለምን ሆን ብሎ ችላ እንዳለው በፍጹም ሊረዱት አልቻሉም። ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የዘር ማጥፋት ዝግጅት ባህል በአገሪቱ አብዛኛው አካባቢዎች እየተስፋፋ መሆኑን እያስጠነቀቁ ከመሆኑም ባሻገር የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚከታተለው ጄኖሳይድ ዎች የተባለው ዓለም ዓቀፍ ድርጅት የጅምላ ዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተፈጸመ መሆኑን በማያሻማ መልኩ ቢገልጽምየጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ ማለፍ ብቻ ሳይሆን የችግሩን ክብደት ለማድበስበስ ወይም ለማቃለል እነዚህ ማንነት ተኮር ግድያዎች በተፈጸሙ ማግስት ወይ የስንዴ ማሳና የዛፍ ችግኝ ተከላ ጣቢያ በመገኘት ከመስሎቹ ጋር በመሆን እየተፍለቀለቀ የተነሳችውን ምስሎች በየመገናኛ ብዙኃኑ ላይ በመልቀቅ በሟቾቹና በቀሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው ሃዘን ላይ ያላግጣል አልያም “መንደር ለመንደር እየዞረ ሰላም የማስጠበቅ” ተግባር የእሱ እንዳልሆነ በድፍረት ይናገራል። 

የዚህ ክህደት አካል የሆነው ዐብይ አህመድ እንደ ቀኝ እጁ የሚቆጥራቸው እንደ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያሉ እና ሌሎች የቅርብ ረዳቶቹ የብሄር ጥላቻ ንግግሮችን በአደባባይ በግልጽ ሲናገሩ ከነበሩ የጥላቻ ጠማቂዎች ጋር ያለው ጥብቅ ወዳጅነት ነው። በአማራ ጠልነት ላይ የተመሰረተው ጎሳ መር ህገመንግስትና ፌዴራሊዝም መሰረት “የተሳሳተ የጎሳ መለያ” ማለት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ያላችሁት ነገርግን ኦሮሞ አይደላችሁም ወይም ትግራይ ውስጥ ብትኖሩም ትግራይ ለትግራዋያን ብቻ እንጂ ከሌላ ጎሳ ለመጡ ኢትዮጵያውያን አይደላችም ማለት ነው። በኦሮሚያ ክልል እየሆነ ያለው ኦነጋውያን እና የእነሱ ተከታይ እስከ አፍንጫቸው መሳሪያ በታጠቁ ሚሊሻዎች ኦሮሞ ያልሆነውን ሁሉ ‘ነፍጠኛ’ ወይም መጤ በሚል ሽፋን በማሸበር ላይ ይገኛሉ። በደንብ የተለዩት እና ጨቋኝ ብሄር ተብለው የተፈረጁት ማለትም አማራዎች ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተጨፈጨፉ ሲሆን ከእልቂቱ የተረፉትም እጩ ተጨፍጫፊዎች ናቸው። በኦሮሚያ ክልል በየእለቱ የሚገደሉት ያልታጠቁና ምንም ወንጀል ያልፈጸሙ የአማራ ተወላጆች አኃዝ ስንመለከት በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ ላይ ደርሷል። በመቶዎች በሚቆጠሩ መንደሮች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ወረራ ተጨፍጭፈዋል፣ በስለት ተወግተውና ተገፈው፣ መገደላቸው ሳያንስ ገዳዮቻቸው ተሳልቀውባቸዋል፤ አዋርደዋቸዋል። እድሜ ለተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ እነዚህ ዘግናኝ፤ ሰቅጣጭ እና ሰብአዊነት የጎደላቸው በንጹኃን አማራዎች ላይ የተፈጸሙ አረመኒያዊ ድርጊቶች ወንጀለኞቹ በፊልም ቀርጸው በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጋርተዋል/እያጋሩ ነው፤ የድፍረትና የማናአለብኝነት ጥግ ይሏል ይሄ ነው። እንዲህ አይነቱ ማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት ዘመቻ በሩዋንዳ ከሶስት አሰርት ዓመታት በፊት የሁቱ ጎሳ አባላት በቱትሲዎችና በለዘብተኛ ሁቱዎች ከፈጸሙት እጅግ ዘግናኝ እና ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ህይወትን ካጠፋው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ጋር ያለውን ተመሳሳይነት በቸልታ ሊታለፍ አይችልም። በተለይም ኦነጋውያን ጨፍጫፊዎች እየተጠቀሙበት ያለውን ቋንቋ፣ የግድያ ስልቶች እና ተጠቂዎቹን ለመጨፍጨፍ የሚገለገሉባቸውን የጦር መሳሪያዎችን በአትኩሮት ለተመለከተ። ዐብይ አህመድ እነዚህ ማንነት ተኮር የጅምላ ጭፍጨፋዎች በንጹኃን የአማራ ደሃ ገበሬዎች፤ ህጻናት፤ ርጉዝ እና እመጫት ሴቶች እንዲሁም አረጋውያን በኦነጋውያን በተከታታይ ሲፈጸሙ የሚሰጠውን ምላሽ ለተመለከተ ለሰዎቹ ህይወት መጥፋት ደንታ እንደሌለው ብቻ ሳይሆን እነዚህን ኢሰብአዊ ድርጊቶች እንደሚደግፍ በብዙ በማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል። 

2013 .ም ጥር ወር አጋማሽ ላይ ወለጋ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች እና 

ህጻናት በትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ ተቆልፎባቸው በጥይት ተደብድበው በተገደሉበት ሌላ 

የጅምላ ግድያ ማግስት፣ ዐብይ አህመድ የፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስ በአዲስ አበባ 

ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ፍልቅልቅ እያለ የገና በዓል የመልካም ምኞቱን በመግለጽ 

አሽከርካሪዎችን አስደንቋቸዋል። 

ስለ ጭፍጨፋው ግን አንዲት ቃል እንኳን አለመተንፈሱ ብቻ ሳይሆን እሱም ሆነ የእሱን ትዕዛዝ ጠብቀው ታዋቂ ሰዎችና በሌሎች አገራት በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ሰዎች የሃዘን መግለጫ የሚያዥጎደጉዱት ሎሌዎቹ እንኳን፤ የሃዘን ቀን ማወጅ፤ ከጭፍጨፋው የተረፉትን ቤተሰቦች በቦታው በመገኘት ማጽናናት ይቅርና ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን እንዳይነገር እና ማንነት ተኮር ጭፍጨፋውን በስሙ ላለመጥራት የሄዱበትን ርቀት ለተመለከተ ህዝቡ ይወክሉኛል ብሎ የመረጣቸው ሰዎች የወረዱበትን የሞራል ዝቅጠት እና ለተጠቂዎቹ ያላቸውን ንቀትና ጥላቻ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ሃጫሉ ሁንዴሳ የተባለው የኦሮሚኛ ዘፋኝ ሲገደል የአምስት ቀናት በኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ሲታወጅ (1) በሺሆች ለሚቆጠሩ በግፍ ለተገደሉ የአማራ ተወላጆች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት የተወካዮች ምክርቤቱ እንዲደረግ አንድ የአማራ ብሄር ንቅናቄ ተወካይ ሲጠይቁ ተረኛውና ኦነጋዊው አፈጉባኤ እንዴት አድርጎ ለህዝብ በቀጥታ በቴሊቪዥን በሚሰራጭ ስርጭት ላይ እንዳበሸቀጣቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። (2) 

የኢትዮጵያ አጣብቂኝ ሁኔታዎች 

በአሁኑ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ ከመንግስት ጋር ግልጽ ያልሆነ ግንኙነት ባላቸው በጎሳ ተኮር ፋሽስታዊ መንጋዎች መዳፍ ውስጥ ወድቋል በግልጽ ቋንቋ በኦነጋውያን ፋሽስቶች። እዚህ ላይ ሊተኮር የሚገባው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ የሩዋንዳው ኢንተርሃምዌ ሚሊሻዎች በ1986 ዓ.ም ሚያዚያ ወር መጨረሻ አካባቢ ጎሳ ተኮር የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማካሄድ ሲንደረደሩበት ከነበረው ጉዞ ጋር እጅግ ተመሳሳይነት አለው። የኢንተርሃምዌ ሚሊሻዎች ከሩዋንዳ መንግስት ባለስልጣናቱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ቢኖራቸውም ነገር ግን በሀገሪቱ በህዝብ ቁጥር አነስተኛ ባላቸው የቱትሲ ብሄረሰብን በተመለከት የነበሩ ‘ለዘብተኛ’ ፖሊሲዎችን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር። 

ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ስናገናዝበው የኦሮሞ ምድረገነት ማንም ሰፋሪ መጥቶ አይበልጽገበትም 

የሚል ቃል ስለገባላቸው የቄሮ ታጣቂዎች በአንድ ወቅት ከዐብይ አህመድ ጎን በመቆም የስልጣን 

ጥማቱን እንዲወጣ አስችለውታል

ጥማቱን እንዲወጣ አስችለውታል። 

እንዲህ አይነቱ ቃልኪዳን ገና ከጅምሩ የዘር ማጥፋት ፕሮፓጋንዳ የመማሪያ መጽሃፍ እንደሆን የታወቀ ቢሆንም ዐብይ አህመድ የስልጣን ጥሙን ለማሳካት በደስታ ተቀብሎታል፡ ለምን ቢባል እነዚህ ብሄር ተኮር ፋሽስቶች ከምንም በላይ የእሱ ቀንደኛ ደጋፊዎች ስለሆኑ። ይባስ ብሎ በዐብይማኒያ የመጀመሪያ ወራት አካባቢ የቄሮን የአመራር ብቃት አንቆለጳጵሷል። ይሄ አፍላ ፍቅር ግን ብዙም አልዘለቀም። ቄሮዎች ጠቅላይ ሚኒስትራቸው የገባላቸውን ቃል ለመፈጸም ፍላጎት እንደሌለው ሲገነዘቡ ኦሮሞን የከዳ በማለት በሃይል ከስልጣኑ ለማውረድ መሃላ ፈጸሙ። ቢገድሉት ደስታቸው ነበር፤ ሆኖም ግን ያላቸው አቅም አነስተኛ በመሆኑ ውስጣቸውን ያለውን ቁጣና ንዴት ወደ አልታጠቁ ንጹኃን ዜጎች ላይ አነጣጠሩ። እናማ ለዚህ ንዴታቸውና ቁጣቸው ማብረጃ በጎሰኛ አማራ ጠል ፋሽስቶች ነፍጠኛየሚል የዳቦ ስም የተሰጣቸው በሺዎች የሚቆጠሩ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ንጽኃን የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በግፍ ጨፈጨፉ። አሁን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በጣም አሳሳቢው ነገር በሙስና በተዘፈቁ የመንግስት ባለስልጣናት የሚካሄደው ብልሹ አሰራርና እና የሀገሪቱን ሀብቶች የአላግባብ ለግል መጠቀሚያቸው ማድረግ ሳይሆን በንጹኃን ዜጎች ላይ ያለምንም ተጠያቂነት በየእለቱ የሚፈጸመው ኢሰብአዊና ሰቅጣጭ ወንጀሎች ናቸው። ይሄ ጽሁፍ ከመጻፉ አንድ ወር ቀደም ብሎ ማለትም በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም ላይ ኦነግ ሸኔ ከኦሮሚያ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አጣዬ፤ ካራ ቆሬ፤ ከሚሴ እና ሸዋ ሮቢት በሚባሉት የአማራ ክልል ከተሞች ላይ ባደረሱት ጥቃት እጅግ ብዙ ሰዎች ተጎድተው ከተሞቹን ወደ ዶግ አመድነት ቀይረዋቸዋል። መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማሰከበር ከህዝቡ የተቀበለውን አደራ ባለፈጸሙ ሊጠየቅ ይገባል። 

በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ መጤእና 

ሰፋሪየሚል ስም በመለጠፍ የበቀል እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚገባ ተፈርጀዋል። 

አማራ ጠልነት እጅግ በመለመዱና እንደ ተራ ነገር በመቆጠሩ ዛሬ አማራዎች በገዛ 

ክልልላቸው በኦሮሞ ተስፋፊዎችና አሸባሪዎች በየእለቱ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል።

ነፍጠኛ ይውደም የሚለው መፈክር ለእነዚህ አክራሪዎች ከመፈክርነቱ ባሻገር በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልሎች በሚኖሩ ነፍጠኛየሚል ስያሜ በተሰጣቸው የአማራ ተወላጆች ላይ በማያሻማ ሁኔታ ያነጣጠረ ነው። የሚገርመውና እጅግ አስደንጋጭና አስፈሪ የሆነው ደግሞ በርካታ እነዚህ ልባቸው በአማራ ጥላቻ የተሞላ ኦነጋውያን እና ተከታዮቻቸው በአማራው ህብረተስብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያደርጓቸውን ዛቻዎች በቪዲዮ ቀርጸው በይነመረብ ላይ ለማጋራት የሄዱበት የድፍረት ርቀት ነው። ይሄን ያህል የልብ ልብ ያገኙት እስካሁን ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራና የሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፉ ኦነጋውያንና ተከታዮቻቸ ባልተጻፈ ህግ ያለመከሰስ መብት በገዥው መንግስት ስለተሰጣቸው ነው – እናማ ማን ሊወቅሳቸው ይችላል? ባጭሩ ሲጠቃለል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው የአማራ ዜጎች ህይወት በዐብይ መንግስት ከመጤፍ እንደማይቆጠር በጉልህ ያሳያል። (3) 

ዐብይ ሰባኪው 

እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብልጽግና ወንጌል ቤተክርስቲያን ወይም ሙሉ ወንጌል አማኞች ንቅናቄ በመባል የሚታወቁት የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ተከታይ ነውዐብይ አህመድ እነደመስበክ የሚወደው ነገር የለም እናም አዲሱ የሀገሪቷ ሰባኪነቱ ሚና እጅግ ደስተኛ ነው። ዐብይ አንደበተ ርተኡ ብቻ ሳይሆን በአፉ ጤፍ ይቆላል ቢባል ይቀላል። ኢትዮጵያውያን ግን ሰባኪው ጠቅላይ ሚኒስትራቸው መሰረታዊ የሆኑ የወንጌላውያን ስነምግባር መርሆች ላይ በመመስረት በጎሰኛ ፋሺስቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን ኢትዮጵያውያን ንጹኃን ዜጎችን አንድም ቀን ሲያጽጽና አይተውት አያውቁም። ዐብይ አህመድ እነዚህን ማንነት ተኮር የጅምላ ጭፍጨፋዎችን በስማቸው ከመጥቀስ ይልቅ ይግረማችሁ ብሎ የተለያዩ የቋንቋ ድሪቶዎችን በመጠቀም ድርጊቱን ለማቃለል ሲሞክር ብዙ ጊዜ ተስተውሏል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን የአማራ ዜጎች ‹ነፍጠኛ› እየተባሉ በገጀራና በስለት ተወግተው ሲገደሉ፣ ሲጨፈጨፉ እነዚህ ኢሰብአዊ ማንነት ተኮር ግድያዎች የሚጠቀሱት 

በሁለት የተለያዩ ጎሳዎች መከካል እንደተደረጉ ግጭቶች ነው። በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በማንነታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታቸውም ጭምር ነው። ዐብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ጠብ ያለሽ በዳቦውን ጥቃት በተለያየ ጊዜ አስመስክሯል። ይሄንን የወረሰው ደግሞ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ዐብይ ሰልጣን እስከወጣበት ጊዜ ኢትዮጵያን ሲገዛ ከነበረው የትህነግ አገዛዝ መሪዎች ከነበሩት የቀድሞ ጌቶቹ ነው። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ፖለቲከኞች የሚጠሉትና የሚንቁትን ጉዳዮች 

ማለትም በጋራ መኖርን እና መግባባትን የሚያበረታታ እንዲሁም የኢትዮጵያውያን የአብሮነት 

ስሜት የሚያበረታታ የተደራጀ እምነት ተቋም ትወክላለች። አላማውን ህዝብን በጎሳና በሃይማኖት 

በመከፋፈል፣ የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም የሌላውን መብት በመግፈፍ በማስከበር ላይ ተመስርቶ 

ስልጣን ላይ ለመፈናጠጥ ከሆነ እንዲህ ያለው የእምነት ተቋም ትልቅ ስጋት ነው። 

ሬኔ ለፎር (2013 ዓ.ም) የተባለው ጸሃፊ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እምነቱን የፖለቲካ ራዕዩን እና ተግባሩን ለማስፈጸም እንደሚጠቀምበት ጽፏል። በጽሁፉ ላይ ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን ህጋዊነቱን ለማጠናከር ዐብይ እምነቱን በድፍረት እየተጠቀመ እንደሆነ እምነታችውን ገልጸዏል። “ዐብይ ሆን ብሎ የማታለል ዘዴዎችን ቀርጾ እንደ ማሳመኛ እየተጠቀመባቸው ይገኛል” (4) ከሚለው የውጭ አገር ተንታኝ ድምዳሜ ጋር እንደሚስማሙ ገልጸዋል። እንደአብነት ብንወስድ ዐብይ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ብዛት ቁጥር ከፍተኛ ናቸው በሚባሉት ከአራቱ ክልሎች ማለትም በአማራ ትግራይ ኦሮምያና ደቡብ ክልሎች በተውጣጡ ፓርቲዎች የተመሰረተውን አገሪቱን ለ27 አመታት ሲገዛ የነበረውን ኢህአዴግን በማፍረስ ላቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ ብልጽግና ፓርቲ የሚለውን ስያሜ የመረጠው በአጋጣሚ አይደለም ብሎ ማሰቡ ተገቢ ነው። እንደብልጽግና ወንጌል መመዘኛ ከሆነ የሰው እምነቱ በጠነከረ መጠን እግዚአብሔር አማኙን በብዙ የገንዘብ በረከቶች እንደሚባርከው ነው። ሀብት ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ለሚገባቸው ብቻ የሚሰጥ ስጦታ ነው ። (5) ስለሆነም እንደለፎር (2013) አገላለጽ በጥብቅ የእምነቱ ተከታዮች ስነምግባርና ዐብይ ስጦታና ስልጣን በማንበሽበሽ ደጋፊዎችን ለመሳብ የሚያደርገው ተግባር መካከል ምንም ተቃርኖ የለም። 

ጴንጤቆስጤሊዝም በኢትዮጵያ (ዘ ኢኮኖሚስት) (6) የተሰኘው መጣጥፍ ዐብይ አህመድ ከእሱ በፊት እደነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሁሉ በጣም “አማኝ” ጴንጤ መሆኑን ይጠቅሳል። የዐብይ አህመድ ቀኝ እጅ እና የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ሊቀመንበር የነበረው አቶ ለማ መገርሳ የእግዚአብሔር ምክር ቤት የቦርድ አባል ሲሆን በዐብይ አህመድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ከፍተኛ የአመራር አባላት የፓስተር ገመችስ ደስታ የጴንጤቆስጤ ቤ/ክ ተከታዮች ናቸው። የዚህም ተፅእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዘ ኢኮኖሚስት ላይ ያለው መጣጥፍ በግልፅ እንዳስቀመጠው፡ የዐብይ ፖለቲካ በጠንካራ መዋቅሮች፣ በታሪካዊ ቅድመ ሁኔታዎች ወይም በተቋማት ላይ እንዳልተመሰረተ ነው፡ይሄንን በተመለከተ ዐብይ እንዲህ በማለት ተመጻድቋል እውነት ከእኛ ጋር ስላለች ማንም አያስቆመንምእውነትን ጨብጠን ስለምንሰራ የኢትዮጵያ አምላክ ይረዳናል። (7) ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያን ለማዳን በእግዚአብሄር መመረጡን እንደሚያምን በግልፅ ከመናገሩም ባሻገር የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችም አምላካዊ መመሪያ እስከሆኑ ድረስ በመጨረሻ አሸናፊ ሆኖ እንደሚወጣ በድፍረት ተናግሯል። “አብዛኛዎቹ መፈቃቀር እና ይቅር ባይነትን መሰረት በማድረግ የሚሰጣቸው ስብከት መሳይ ንግግሮቹ እግዚአብሔርን የሚማጸኑ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ብዙዎቹ የጴንጤቆስጤ እምነት ተከታዮች ዐብይ መለኮታዊ ተልዕኮ ለማስፈጸም እንደመጣ ያምናሉ። 

በሕፃንነቱ እናቱ 7ኛው የኢትዮጵያ ንጉስ ሆኖ እንደሚነሳ የተነበየችውን ትንቢትተቀብሎታል። 

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ጭቆናና እንግልት ለሚገኙት የአማራ ብሄር ተወላጆች ግን የጠቅላይ 

ሚንስትር ዐብይ አህመድ ራዕይ የአማራን ብሄርን ከኢትዮጵያ ምድር ላይ በማጥፋት በኦሮሞ 

የበላይነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ።

አስተዳደራዊ መዋቅሩን በመጠቀም የአማራን የዘር ማጥፋት አንዱና ቁልፉ ስልት ነው ለዚህ ደግሞ የኦሮሚያ የሲዳማ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልሎች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። በተለይ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተለያዩ ጊዜያት በአደባባይ እና በስብሰባዎች ላይ በግልፅ እንደተናገረው የኦሮሞ ተወላጆች ዋነኛ አላማ የአማራዎችን አከርካሪ በመስበር የመኖር፤ የመስራት፤ የመማር እና የፖለቲካ ተሳታፊነት መብታቸውን በመንፈግ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው። (8) 

ዐብይ አጼ በጉልበቱ 

የዐብይ አህመድ ፖለቲካዊ ገጽታዎች 

የዐብይ አህመድን የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው፣ ይህ ማለት ግን ቃል የገባቸውን ጉዳዮች በተግባር ሰለማይፈጽም ብቻ አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች በቀጣይ ለሚመጣው የጅምላ ግድያ ማነህ/ማነሽ ባለሳምንት እያሉ በስጋት እና በጭንቀት በሚኖሩባት አገር ውስጥ አዳዲስ የመዝናኛ ፓርኮችን መክፈት እና የዛፍ ችግኞችን መትከልን ይመርጣል። ከእነዚህ የሚፈጽማቸው ተራ እለታዊ ሁነቶች ውስጥ አንዳቸውም ከፖሊሲ ጋር ግኑኝነት የላቸውም፣ ይልቁንም የሆሊውድ ታዋቂ ሰዎች ራሳቸውን ለማስተዋወቅና ዝናቸውን ለማግነን የሚሳተፉባቸው ተራ እለታዊ ሁነቶች ናቸው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ጠቅላይ ምኒስትሩ በአገሪቱ ካለው ከእውነታው በራቀ እና በራሱ የተለየ የምናብ ዓለም እንደሚኖር ማሳያ ነው። በዐብይ አስተዳደር ውስጥ ተጠያቂነት አለ ለማለት አያስደፍርም። ተጠያቂነት ለመረዳት የሚያስቸግር ጽንሰ-ሐሳብ እንደሆን ቢታወቅም ቅሉ የሃሳቡን ምንነት ዜጎች ከተረዱ መንግስታቸውን እንዴት ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚችሉ መንገድ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ተጠያቂነትን ጠበብ አድርገን ብንመለከተው አንድ ሰው ለግለሰቦች፣ ለቡድኖች ወይም ለድርጅቶች ለፈጸማቸው ወይም ላልፈፈጽማቸው ተግባራት እና ወይም ቃልኪዳኖች ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ጉዳዮች ተጠያቂ ለመሆን የገባውን ግዴታ ያመለክታል።(9) የመንግስት ሃይሎች በጅምላ ግድያ ተባባሪ በሆኑበት እና ስለ ጉዳዩ ምንም በማይባልበት በዐብይ አህመድ አገዛዝ ግን ተጠያቂነት በጭራሽ አይታሰብም። 

ስለነዚህ አረመኔያዊ ድርጊቶች ዐብይ አህመድ ሲጠየቅ እኔ በየወረዳው እና በየመንደሩ እየዞርሁ 

ሰላም የማስጠብቅ ሚሊሻ ወይም ፖሊስ አይደለሁምየሚል ልበ ደንዳና ምላሽ በመስጠት 

ጥያቄውን በግዴለሽነት በማድበስበስ አልፎታል።

ዐብይ አህመድ በስልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ ዓመታት የነበረው ተቀባይነት የመነጨው በወቅቱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ታፍኖ” ስለነበርና ምንም አማራጭ በማጣቱ የምን ገዶኝ ነበር ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የስቃያቸው መንስኤ ከሆነው ግለሰብ ጋር ያላቸው ምክንያታዊነት የጎደለው ቁርኝት ግራ የሚያጋባ ሲሆን፤ ብዙዎች በእሱ ሸፍጠኛ የፖለቲካ ስብእና እየተታለሉ መሆናቸውን እንኳን ለማመን አይፈልጉም። ጀምስ ጄፍሪ በህዳር አጋማሽ 2012 ዓ.ም ላይ ኢትዮፒያ ዊፕስ አጌይን በሚል ባወጣው መጣጥፍ ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “አንዳንድ ተቺዎች……የፖለቲካውን አካሄድ በውዳሴ ከንቱ ላይ የተመሰረተ፣የታይታ እና በወግ አጥባቂነት ከተመሰረተው የኢትዮጵያ ማህበራዊ ህይወት እውነታ የተራራቀ ነው ሲሉ ይከሱታል። የአገዛዙ ዘይቤም ግልፅነት የጎደለው ነው ተብሎ ከመወንጀሉም ባሻገር የመገናኛ ብዙኃንን እንደሚያፍን እና ከእርሱ ቀደሞ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታትን አምባገነናዊ አገዛዝ እየደገመው እንደሆን ክስ ያቀርቡበታል”። ለምሳሌ ያህል አወዛጋቢ የሆነውን የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ እየመጣበት ያለውን ተቃውሞ ለማፈንና ጋዜጠኞችን ለማሰር እየተጠቀመበት ይገኛል።(10) 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ በወጣ ማግስትና አሜሪካ ለጉብኝት በመጣበት ጊዜ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ጄኒ ማርሽ (ነሐሴ 18 /2010 ዓ.ም) እንደሚከተለው ዘግባ ነበር — ኢትዮጵያውያን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑት፡ ወጣት፣ ዲሞክራሲን እና ሰላምን ለማስፈን የሚሰብክ ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱ ለዘመናት ስትጠብቀው የነበረ መሪ በመሆኑ ምክንያት ነው ።(11) ቁልፉ ጥያቄ ዐብይ አህመድ የተወራለትን ያህል መዝለቅ ይችላል ወይ ነው። ምናልባት ትልቁ ስጋት በ“አቢይማኒያ” ምክንያት ኢትዮጵያውያን የመሪያቸውን ውስጣዊ ጉድለቶች እንዳይመለከቱ አመለካከታቸውን ከመጋረዱም ባሻገር የዴሞክራሲ ሂደቱ እንዳያብብ እያዳከመው መሆኑ ነው። እንግሊዝ አገር በሚገኘው የኤሴክስ ዩኒቨርሲቲ የመንግስት አስተዳደር ትምህርት ክፍል በፕሮፌሰርነት የሚያገለግሉት ናታሻ ኢዝሮው የተባሉ መምህርት “ለሁሉም ሰው እንደመሲህ ተመስለው ከሚከስቱ መሪዎች ልንጠነቀቅ ይገባል” ሲሉ መክረዋል። በመቀጠልም በኢትዮጵያ “የዲሞክራሲ ተቋማት ካለመኖራቸው” ባሻገር “ለጡንቸኛ መሪዎች” የተመቸች አገር ሆና እንደቆየች ይገልጻሉ። ዐብይ ግላዊ ስልጣኑን መግራት እስካካልቻለ ድረስ 

አምባገነናዊ አገዛዙ አይቀሬ ነው በማለት ያስጠነቅቃሉ።(12) ይህ የሆነው ከዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በፊት ነበር። ያ ማስጠንቀቂያ እንደሚያመላክተው ወይ የዐብይ ተዋኒ ማንነቱ አልያም የአቢይማኒያን ተከትሎ የመጣው ውዳሴ ከንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። 

የሩዋንዳው የእልቂት መንገድ 

ችላ በተባሉ ማስጠንቀቂያዎች ምክንያት በንጹኃን ሰዎች ላይ የደረሱ ጥፋቶችን ከተመለከትን፣ በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሩዋንዳ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ቱትሲዎችና ለዘብተኛሁቱዎች ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጽዳት እና እልቂት ማንሳት ይቻላል። በ1986 ዓ.ም መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በሁቱ ጎሳ አባላት አቀናባሪነት የተጀመረው የዘር ማጥፋት ወንጀል በቱትሲ የጎሳ አባላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ከለላ በሰጡ ማናቸውም የሁቱ ጎሳ አባላት ላይ ጭምር ነበር። በወቅቱ በሩዋንዳ የቤልጂየም አምባሳደር ሁቱዎች ለዘር ማፅዳት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ማስጠንቀቂያ ከሰጡበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የዘር ማጥፋት ዘመቻው በመካሄድ ላይ ነበር። ሌላው ቤልጄማዊ ፕሮፌሰር ፊሊፕ ሬይንትጀንስን በቤልጂየም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ፊት በመቅረብ ሁቱዎች የአፍኖ ገዳዮች ቡድን እየመሰረቱ መሆናቸውን ከማስጠንቀቃቸውም በተጨማሪ በወቅቱ በሩዋንዳ የመከላከያ ሰራዊት ሲያገለግል የነበረውንና ኋላ ላይ የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ቀንደኛ መሪ የሆነውን ኮሎኔል ቴዎኔስተ ባጋሶራን በስም ጠቅሰውት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በጥር 1986 ዓ.ም በሩዋንዳ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦር አዛዥ ጄኔራል በመሆን ያገለገሉት ቤልጅየማዊው ሮሚዮ ዳላይር በአሁኑ ጊዜ “የዘር ማጥፋት ፋክስ” በመባል የሚታወቀውንና ለተባበሩት መንግስታት በላኩት የፋክስ መልእክታቸው ላይ የሁቱ ጎሳ አባላት ቱትሲዎችን ለማጥፋት እቅድ እንዳላቸው አስጠንቅቀው ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ጄኔራሉ የሁቱ ጎሳ የጦር መሳሪያ መጋዘንን ለማጥፋት እንዲፈቀድላቸው እና ተጨማሪ ወታደሮች እንዲላኩላቸው ቢጠይቁም የተባበሩት መንግስታት ግን ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ በምትኩ በዘር ማጽዳት ዘመቻው አስተባባሪዎች ለተሞላው የሩዋንዳ መንግስት ጉዳዩን እንዲያሳውቁ ትእዛዝ ሰጣቸው። በዚያው ወር ላይ ዳላይር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የዘር ማጽዳት ዘመቻውን የፈጸሙትን ታጣቂዎች ሲያሰለጥኑ በነበሩት የሩዋንዳ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውስጥ የነበሩትን የጦር መሳሪያዎች በእጁ አስገባ። (13) 

ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ከ1983 .ም ወዲህ በተለይም ላለፉት 5 ዓመታት ኢትዮጵያ 

ውስጥ ያለምንም ተጠያቂነት በየእለቱ በአማራ ተወላጆች ላይ በኦሮሞ ፋሽስቶች እየተካሄደ 

ያለውን ብሄር ተኮር የዘር ማጽዳት ዘመቻን ለተመለከተ ችላ ከተባለው የሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ 

ማስጠንቀቂያ ጋር እጅግ ተመሳሳይነት አለው።

ያለምንም ተጠያቂነት የኦሮሞ ፋሽስቶች ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ በአማራ ንጽኃንን ተወላጆች ላይ በማካሄድ መሆናቸውን የአማራ ተወላጆች የድረሱልኝ ጥሪ ቢያሰሙም ሰሚ አላገኙም። ከምንም በላይ የሚፈልጉት በህይወት ለመኖር ብቻ ነው። ስለፍትህ የሚጮሁት ለማስመሰል እና ለታይታ አይደለም። ሰላማቸውንና ደህነታቸውን ያስጠብቅልናል ብለው የመረጡት መንግስት ግን የዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዋናው ደጋፊ ነው። (14) 

/ሚ ዓብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ የኦሮሞ አክራሪዎች በአማራዎች እና ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ እንደ ጉራጌ፣ ጋሞ እና ሌሎች ህዝቦች ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እጅግ ተበራክተዋል። ቦርከና (ሚያዝያ 9፣ 2012 ዓ.ም) (15) እንደዘገበው በአማራ ክልል በሚገኙት በሰሜን ሸዋ እና ከሚሴ አካባቢዎች ላይ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ለተከታታይ አራት ቀናት የተደራጀ ጥቃት ፈጽመዋል። የፌደራል መንግስቱ ግን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ስለተከሰተው አስደንጋጭ ሁኔታ ምንም የሰጠው አስተያየትም ሆነ መግለጫ የለም። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማለትም ለተዋኒው ዐብይ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ እንደተለመደው ህይወት ጉዞዋን ትቀጥላለች። ዐብይ ተዋኒው ግን አዲስ በተገነባው የደህንነት ዋና መሥሪያ የሕንፃ የምረቃ ሥነሥርዓት በመገኘት የወቅቱ ዜና ዘገባዎች መነጋገሪያ መሆንን ነበር የመረጠው። (16) በማህበራዊ ትስስር መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደረጉ ውይይቶች በበኩላቸው በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ-ሸኔ) ስም ላይ እየተላከከ ያለውን የተደራጀ ጥቃት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች የተቀነባበረ እንደሆነ ያያይዙታል። በአዲስ መልክ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ያሉት አካባቢዎች በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በርካቶች እነዚህን ጥቃቶች የአማራ ብሄርን የማጥፋት ዘመቻ አካል አድርገው ይመለከቱታል። በኦሮሞ ክልል በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ እየተበራከተ ከመምጣቱም ባሻገር የአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከመቼውም ጊዜ በላይ በግልጽ እየተካሄደ ቢሆንም ጥቃቱን ለማስቆም ከመንግስት የተሰጠ ምላሽ አለ ለማለት አያስደፍርም።(17) 

ስለ ጸሃፊው፡ ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ ስዊድን አገር በሚገኘው የጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ልዩ ትምህርት ክፍል በመምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ 

የግርጌ ማስታወሻዎችና ማጣቀሻዎች 

የግርጌ ማስታወሻ፡– 

* የተርጓሚው አተያይ 

** ወቅታዊና በዋናው ጽሁፍ ውስጥ ያልተካተቱ ዝርዝር ጉዳዮች 

*** ኒኮሎ ዲ በርናርዶ ዲ ማኪያቬሊ በአውሮፓውያን የተሃድሶ ዘመን የኖረ ጣሊያናዊ ዲፕሎማት፣ደራሲ ፣ፈላስፋ እና የታሪክ ምሁር ሲሆን እ.አ.አ. በ1513 ዓ.ም አካባቢ ጽፎት ነገር ግን እስከ 1532 ዓ.ም ድረስ አልታተመም በተባለው መስፍኑ (The Prince) በተሰኘው የፖለቲካ ድርሳኑ በጣም ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ በብዛት የሚታወቀው ግን የዘመናዊ ፖለቲካ ፍልስፍና እና የፖለቲካ ሳይንስ አባት ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው። 

**** የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች ታሪክን በማጭበርበር፤ በማጣመም እና በመፈብረክ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል በገሃዱ አለም ያልነበሩ አዳዲስ ታሪኮችንና ትርክቶችን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳን የመጀመሪያዎቹ የአፍሪካ ቀንድ ቀደምት ነዋሪዎች እንዳልነበሩ ቢታወቅም በመላው ዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ የሰው ልጅ መጀመሪያዎች ነን በማለት ሃሰትኛ ትርክት በማሰራጭት ላይ ይገኛሉ። በትክክል የተጻፉ የታሪክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት የኦሮሞ ተስፋፊዎች በ16ኛው ክፍለ ዘመን የአህመድ ግራኝን ወረራ ተከትሎ በኢትዮጵያ ቀደምት ነዋሪ የነበሩ ህዝቦችን በጅምላ በማጥፋት የአገሪቱን ግዛቶችን መጥተው በጉልበት 

ተቆጣጠሩ። በኦነጋውያን ትርክት መሰረት አማራዎች “የባህል አውዳሚ ዘሮች” ስለሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረገጽ ላይ መጥፋት አለባቸው። እንደ ህዝቄኤል ጋቢሳ፣ ጃዋር መሃመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሽመልስ አብዲሳ እና መለስ ዜናዊ ያሉ አክራሪ የኦሮሞ እና የትግሬ መሪዎች ባደረጓቸ ንግግሮች ላይ እንዳስቀመጡት የእነሱ ወገን የሆነው ሁሉ በድል አድራጊነት እንዲወጣና እንዲበለጽግ የአማራን ብሄር ሙሉለሙ በጦርነት መደምሰስ የግድ ያስፈልጋል። 

ማጣቀሻዎች 

1) ቢቢሲ አማርኛ።(ሃምሌ 2012 ዓ.ም)። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የጀግና አሸኛኘት እንደሚደረግለት ተገለፀ። 

https://www.bbc.com/amharic/53237141 (መጋቢት 9/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

2) አልአይን አማርኛ።(ሰኔ 14 2014 ዓ.ም)። ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ በአብን አባላት የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ። https://am.al-ain.com/article/hopr-reject-the-request-by-nama-members-to-put-the-issue-of-wolega killing-on-the-agenda (መጋቢት 9/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

3) ቦርከና።(የበይነ መረብ መጽሄት መጋቢት 1/2013 ዓ.ም)። ሆሮ ጉዱሩ፡ የአማራ እልቂት ተረጋገጠ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መንግስትን ከሰሰ። https://borkena.com/2021/03/10/horo-guduru-amhara-massacre-confirmed-nama-accuses-govt/ (መጋቢት 9/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

4) ሬኔ ለፎር። (ታህሳስ 20/2013 ዓ.ም)። የዐብይ አህመድ አላማ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጴንጤ ማድረግ ነው። 

https://www.theafricareport.com/56718/abiy-ahmeds-aim-to-pentecostalize-ethiopian-politics/? fbclid=IwAR2lzZZf0-KDh02g1e-5yFtQ_eYnINoZ54p2-wbfJgekxcqcIO9wcijvauc (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

5) ዝኒ ከማሁ 

6) ዘ ኢኮኖሚስት።(ህዳር 15/ 2010 ዓ.ም)። ጴንጤቆስጣሊዝም በኢትዮጵያ። https://www.economist.com/middle-east-and africa/2018/11/24/god-wants-ethiopians-to-prosper (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

7) ሬኔ ለፎር።(ታህሳስ 20/2013 ዓ.ም)። የዐብይ አህመድ አላማ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጴንጤ ማድረግ ነው። 

https://www.theafricareport.com/56718/abiy-ahmeds-aim-to-pentecostalize-ethiopian-politics/? fbclid=IwAR2lzZZf0-KDh02g1e-5yFtQ_eYnINoZ54p2-wbfJgekxcqcIO9wcijvauc (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

8) ግስካአፍሪካ።(የታተመበት ቀንና ዓመተምህረት ያልተገለጸ)። ኢትዮጵያ: የአማራ የዘርን የማጥፋት እና የማጽዳት ዘመቻ። https:/ www.geeskaafrika.com/ethiopia-amhara-genocide-and-ethnic-cleansing/amp/ (መጋቢት 2/ 2015 ላይ የተገኘ) 

9) ኬሪና ዋንግ።(የዓለም ባንክ ጦማር ጥር 13 2007 ዓ.ም)። የመንግስት ተጠያቂነት እና አረዳዱ። 

https://blogs.worldbank.org/governance/how-make-sense-government-accountability (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

10) ጄምስ ጄፍሪ።(ህዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም)። የኢትዮጵያ ዳግም እንባ። https://thecritic.co.uk/ethiopia-weeps-again/ (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ)

11) ጄኒ ማርሽ።(ሲ.ኤን.ኤን ረቡዕ ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ.ም)። ስለምን ኢትዮጵያውያን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ነብይ ነው ብለው ያምናሉ? https://edition.cnn.com/2018/08/26/world/abiymania-ethiopia-prime-minister-abiy-ahmed/index.html (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

12) ዝኒ ከማሁ 

13) ኤልዛቤት ኤስ አንደርሰን።(ግንቦት 4 2008 ዓ.ም)። በዓለም ሰለደረሱ አሳዛኝ ክስተቶች ችላ የተባሉ 10 ማስጠንቀቂያዎች። https://listverse.com/2016/05/12/10-ignored-warnings-that-turned-deadly/ (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

14) ስቶፕ አምህራ ጄኖሳይድ ድረገጽ።(የታተመበት ቀንና ዓመተምህረት ያልተገለጸ)። በአማራ ተወላጆች ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል . . .። https://www.stopamharagenocide.com/ (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

15) ቦርከና።(የበይነ መረብ መጽሄት ሚያዚያ 9/2013 ዓ.ም)። የአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀል፡ የኦሮሞ አክራሪ ሃይሎች አሰቃቂ ጥቃት በአጣዬ ከተማ ላይ። https://borkena.com/2021/04/17/amhara-genocide-ataye-oromo-radical-forces-launch-attack/ (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

16) አሌክስ በቀለ።(ቦርከና፡ የበይነ መረብ መጽሄት፤ ሚያዚያ 21፣ 2013)። በምርጫን መጫወቻ ያደረገው ቁጡ ጠቅላይ ሚኒስትር። https://borkena.com/2021/04/29/prime-minister-who-makes-a-fetish-of-an-election/ (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ) 

17) ቦርከና።(የበይነ መረብ መጽሄት ሚያዚያ 9/2013 ዓ.ም)። የአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀል፡ የኦሮሞ አክራሪ ሃይሎች አሰቃቂ ጥቃት በአጣዬ ከተማ ላይ። https://borkena.com/2021/04/17/amhara-genocide-ataye-oromo-radical-forces-launch-attack/ (መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም የተወሰደ)

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here