spot_img
Sunday, June 4, 2023
Homeነፃ አስተያየት“ አንጀቴ ተቆርጦ ከቦታው……….”

“ አንጀቴ ተቆርጦ ከቦታው……….”

- Advertisement -

አሰፋ ሞላ

በተለሳለሰ አነጋገራቸው የሚታወቁት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እየተቆጡ መናገር ከጀመሩ ወድህ፣ መድረክ ላይ ብቅ የሚሉት ሹመኞች ሁሉ ቁጣ ቁጣ ይላቸው ጀምሯል፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው ሥን ምግባራችን በደርግ ዘመን ቢጎሳቆልም፣ ጨርሶ አልጠፋም ነበር፡፡ በዘመነ ትህነግ ሁሉም ተሰብስቦ ተጣለና አረጋዊያንን፣ ካህናትንና በእድሜ የገፉ እናቶችን ማክበር እንደነውር የተቆጠረበት ወቅት ነበር፡፡ ዶ/ር አብይ ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ወደ ቆየው የመከባበርና ትህትና ወደ ተላበሰው አነጋገር የተመለሥን የሚመስሉ ምልክቶች ታይተው ነበር፡፡ ከተሸከሙት የውስጥም የውጭም ጫና ግፊት በሚመስል መልኩ፣ ሲጀምሩ ያሳዩን የትህትና አነጋገር በቁጣና በማስፈራራት ተተክቷል፡፡ አስገራሚው ነገር፣ ዶ/ር አብይን በቁጣና በማስፈራራት መልስ እንድሠጡ የሚያደርጋቸው ከአማራው ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ይበልጥ አስገራሚው፣ አማራን የተመለከተ ጉዳይ ከመጣ፣ በዶ/ር አብይ የተሾመ ሁሉ፣አጋጣሚው ከተፈጠረለት፣ አማራን ሳያስፈራራና ሳይዘልፍ እንዳያልፍ በመመሪያ የታዘዘ መስሏል፡፡ ባለፈው፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነትና የጸታ አማካሪ ከትህነግ ትጥቅ መፍታት ጋር ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ በስም ሳይጠቅሱ እንደት አድርገው አማራውን እንደዘለፉና ከሌሎቹ ጋር ለማቃቃር የሄዱበትን ርቀት አይተናል፡፡ የቁጣቸው ስልት የቀድሞ አለቃቸውን አቶ መልስ ዜናዊን የሚያስታውስ ነበር፡፡ ቁጣቸው ያተኮረው እብሪተኛው ትህነግ የቀሰቀሰው ጦርነት ባደረሰው ቁሳዊና መንፈሳዊ ውድመት ላይ ሳይሆን፣ አማራው አሉብኝ ባሰቸው ስጋቶች ላይ ነበር፡፡

ሰሞኑን በተነሳው የክልል ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሩጫ በሚመለክት፣ በሚያስገርም ፍጥነት ፊልድ ማርሻል እርከን ላይ የተሰቀሉት ብርሀኑ ጁላ ማብራሪ ሲሰጡ ተከታትየ ነበር፤ እንደተራራ የተከመረውን  የአማራ ፋኖ ተጋድሎ ታሪክ ፊልድ ማርሻሉ ፊት ለፊት መካድ አልሆነላቸውም፡፡

“ሦስተኛ ዙር  በተደረገው ውጊያ የአማራ ልዩ ኅይል ተዋግቷል እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም ብዙ ረድተዋል፤ መሬት ለማስመልስ የሚደረግ ሩጫ ዝምድና ማበላሸት ይሆናል፡፡ ፋኖ በአክራሪ ተጠልፏል፤ አክራሪ ፖለቲከኛው እየተጠቀመበት ነው፡፡ ልዩ ኅይሉ አስተዋጽኦ ቢያደርግም ጎጅ ጎኑ አይሏል….” መቸም የፊልድ ማርሻሉን ንግግር መስመር አስይዞ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፤ ንግግራቸው በእንግሊዝኛው incoherent መያዣና መጨበጫ የሌለው እንደሚባለው አይነት ነው፡፡ “ከአማራ ክልል በስተቀር ሁሉም ፈትቷል” ይሉናል፡፡ እዚያ ላይ ቢያቆሙ ኖሮ መልካም በሆነ ነበር፡፡ “የጎራ መደበላልቅ የገጠመው አማራ ክልልን ነው፡፡ አደናግረው የበተኑትን ልዩ ኅይል፣ ፋኖ በየቦታው ጨፈጨፈው፤ ፋኖ ገዳይ ነው፤ ፋኖ ያደረስው ጥፋት ከፍተኛ ነው፤ የፋኖ ጥንፈኛ ሽፍታ አማራ ክልልን (paralyse) ሽባ አድሮታል:: ፋኖ ስሙ ክብር አለው፣ የተሰውቷልም፤ ፋኖ ባለቤት የለውም፤ ባለቤቱ ጥንፈኛ ነው፡፡ የመከላከያ ኅይልን እየወጋ ነው፡ የተጠለፈ ኅይል ነው፡ ሴቶች ይደፍራል፡ ኬላ ይዘጋል፡ ቀረጥ ይቀበላል፤ ፉከራው አደንቋሪ ነው”፡፡

ክቡር ፊልድ ማርሻል፣

  • ምነው ይህንን ጉዳይ በዚህ ሰአት ማጮህ አስፈለገ?
  • ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ እንድህም ተደርጓል፣ እነ እገሌ እነ እገሌ ተወያይተዋል እያሉ ለማስተባበል ከመታከት፣ ለምን ሁሉም ክልሎች እንዲያውቁት በይፋ አልተነገርም? ህዝብስ ጋር መወያየት አስፈላጊ አልነበረም?
  • የማስፈታቱንስ ቅድሚያ በናንተ የቀድሞ አለቆችና የቅርብ ወዳጆች (የሽመልስ አብዲሳንና የጌታቸው ረዳን “ትዝ አለኝ የጥንቱ” አይነት ፈገግታ ልብ ይሏል)፤ ሦስት ዙር ወረራ ያስተናገደ ህዝብ ትጥቅህን ፍታ ሲባል ለምን? ብሎ ጥያቄ ቢያነሳ ይፈረድበታል??
  • ትጥቅ ማስፈታቱንስ ለምን ከአማራው መጀመር አስፈለገ?
  • መጀመሪያ ትጥቅ ማስፈታት የሚለው እቅዳችሁ ቁጣ ሲቀሰቅስ” ትጥቅ ፍታ አልተባለም የጠላት ወሬ ነው” አላችሁ፤ “ ሲቀዘቅዝ በጣት ሲፋጅ በማንኪያ” እንደተባለው መሆኑ ነው?
  • ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም እንደ ያደጉት? ፉከራና ቀረርቶ የአማራው ባህል መሆኑን ረሱት እንዴ? ወይስ ዝም እንድል ይፈለጋል?
  • የአማራው ድርጅት ሽባ መሆኑ ከፋኖ ጋር ምን ያገናኘዋል? ኦሆድድና ትህነግ የአማራውን ድርጅት ሽባ ካደረጉት ቆየኮ! “ብልጽግና” በተባለ ገመድ ተሸብቦ አማራው ሲያልቅ መግለጫ ማውጣት እንኳ አልቻልም፤ የ አብየን ወደ እምየ አያድርጉት፤ 

እንደ ልደታ ንፍሮ ድብልቅልቅ ያለውን ንግግረወን መልክ ለማስያዝ ባደረግሁት ጥረት የሚከተሉትን ነጥቦችህ ማውጣት የቻልኩ መሰለኝ፤

  • ወልቃይትን በተመለከተ የአሜሪካ ግፊት መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቷችኋል፡ ወልቃይት ለትግራይ ሲመለስ የ አማራ ልዩ ኅይል ዝም ብሎ አይመለክትም፡ ደም መፋሰስን ለመቀነስ አማራ ትጥቁን መፍታት አለበት፡፡
  • ልዩ ኅይሉ ትጥቁን ቢፈታም፣ የታጠቀ ፋኖ ስላለ፣ ይህንን ኅይል መወንጀልና የሕዝብ ጠላት አስመስሎ መፈረጅ ነጥሎ ለመምታ አመች ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
  • ፋኖን የአማራ ክልል መንግስትና የአማራ ልዩ ኅይል ጠላት አድርጎ መሳል ከረጅም ጊዜ እቅድ አኳያ ጠቀሜታ አለው፤ በተለይም “ሴቶችን ይደፍራል” የምትለዋ አገላለጽ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው ቅሬታ ተጠንቶ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡  

ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡ ልክ ኦሮሞ ረጅም ዘንጉን ይዞ እግምባሩ ላይ የሚታሰረውን አስሮ ሲወጣ በባህሉ እንደሚኮራው ሁሉ፣ ነፍጥ አንስቶ ሃገሩን መከላከል ለአማራው ባህሉ ነው፤ ፋኖነት ወንጀል አይደለም፡ ፋኖ በባህሉ ታጥቄያለሁ፣ ቦታ ተመችቶኛል ብሎ ደካማ ፍጡር አያንገላታም፤ ይጠየፈዋል! ኢሬቻ የእርሰዎ ባህል እንደሆነው ሁሉ፣ ፋኖነት ለአማራው የሚኮራበት ባህሉ ነው፡፡ የሌላውን ባህልና እሴት ለኔ አልተመቸኝም ብሎ መወንጀልና መኮነን፣ ወንጀልም፣ ኋላ ቀርነትም ነው፡፡ በትህነግ አዛዥነት፣ በእሆድድ ካድሬዎች፣ አርባ ጉጉ፣ አቦምሳና አካባቢው የተፈጀውን አማራ እርሰዎ ቢረሱት በተሰቦቹ አይረሱትም፡፡ እነሆ በለፉት አምስት አመታት፣ በወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሸዋ ሮቢት፣ የስንት አማርኛ ተናጋሪ ህብረተሰብ ደም ፈሰሰ? አብረን ኖረናል፣ ይኸም ጊዜ ያልፋል ብሎ አማራው አንገቱን ቢደፋ፣ ምነው ግፊቱ ቅጥ አጣ? ትህነግና ኦሆድድ ኢትዮጵያን ይፈልጓታል፡፡ ችግራቸው የሚመንጨው፣ ኢትዮጵያ-አማራ  

(ሲቀነሥ አማራ) እመሆኑ ላይ ነው፡፡ ይኸ ድግሞ አይቻልም፡፡ ድርቅ አሳዷቸው ከሰሜን ወሎ ሄደው የሰፈሩ ምስኪኖች ወለጋ ላይ ለ 21ኛ ከፍለ ዘመን በማይመጥን የግድያ አይነት በኦነግ ሲረሸኑ ምንም ያላሉ ሰው፤ ምነው የፋኖ ነገር እንድህ አንገበገበዎት? የፋኖ እናቶችኮ እነዚያ ትኩስ እንጀራ ከምጣድ ላይ እያወጡ ለተዋጊው ሠራዊት ያጎርሱ የነበሩት ናቸው! ተረሱ እንዴ? 

የሰሞኑ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ትንተና  የሆነ ሥስ ብልት የነካች ወይም የተደበቀ ጉዞ ያጋለጠች ትመስላለች፡፡ እርሰወ ያሉትን ቃል በቃል ላስቀምጠው፣“ ሰሞኑን የሚመታው ከበሮ፣ ሱዳን ሊወርህ ነው፣ ህዋት እየተጠጋ ነው፤ ይባላል፡፡ ራሱ ተኩሶ ህዋህት ተኮሰ ይላል”፡፡ ከትህነግ ጋር የአባትና የልጅ አይነት ፍቅር ስላላችሁ ጥብቅና ቢቆሙለት ላያስገርም ይችላል፡

የአንዳርጋቸው ጽጌን ስብዕና ከሌላ ጋር አስታከው ለመዳፈር መሞከረዎ፣ ምንም ከፍታ አይጨምርለወትም፤ አቶ አንዳርጋቸው ለባለ ጉዳዩ የአማራ ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ አድርሰዋል፡፡ መቆጣት መብተዎ ነው፤ እውነትን ውሸት ማድረግ ግን አይቻልም፡፡

ሸኔን ከፋኖ ጋር በአተያይ ማስቀመጠዎ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ እንደት ሆኖ ነው እርሻ ውለው የደከማቸው ገበሬዎችን፣ አረምና ጉልጓሎ ውለው የደከሙ እናቶችን ቤታቸው ውስጥ ዘግቶ በሳት የሚያቃጥል አረመኔ ድርጅት ከፋኖ ጋር እኩል የሚመዘነው? ምነው የሕዝብን የመመዘን ችሎታ እንድህ ናቃችሁት???

ክቡር ጀኔራል፣ የመንግሥተወንና የአማራን ሕዝብ ጉዳይ በአንድት በቆየች ስንኝ ልቋጭለዎ፤ 

አንጀቴ ተቆርጦ ከቦታው ከወጣ

ምን አይነት ወጌሻ ሊቀጥለው መጣ፡፡

 እቅዳችሁን ግልጽ አድርጉለት፡፡ የቀድሞ አለቆቻችሁ ጋር የምታደርጉት “ትዝ አለኝ የጥንቱ” ሽርጉድ፣ ጦሩን እንደመለዮ ለባሽ፣ አማራውንና አፋሩን እንድ ህዝብ የከዳችሁት አስመስሏችኋል፡፡ እስቲ ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ትበቃለች፡፡ በዚች መሬት ላይ የምንቆየውም ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም ያልፋል፡፡ 

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,876FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here