
አሰፋ ታረቀኝ
ትናንት ያሞገስከውን ሰው ዛሬ እንደ መንቅፍ፣ የወደድከውን እንደምጠየፍ ውስጥን የሚጎዳ ነገር የለም፡፡ እኛ የምንፈልገውን እየነገሩን፣ እሳቸው የሚፈልጉትን እየሠሩ መሆኑን ባለመገንዘቤ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በመቆም እንደሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሌን አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ፡፡ከዶ/ር አብይ ጋር እንሰለፍ በማለት ከጓደኞቸ ጋር ተቃቅሬያለሁ፡፡ ሰውየው ግን ትናንት ከትናንት ወዲያ ከምናውቃቸው አምባ ገነኖች በከፋ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት እያደረሱ ናቸው፡፡ አሁን እያሳዩ ያሉትን ማናለብኝነት ከማሳየታቸው በፊት፣ እንደዋዛ ጣል የሚያደርጓቸውን አባባሎች የትግሉ ግፊት ውጤቶች እየመሰሉን እንደዋዛ እናልፋቸው ነበር፡፡
ለምሳሌ መንግሥታቸውን ለመገልበጥ በትህነግ አዛዦች የተላኩ ወታደሮችን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “መንግሥታችን አደጋ ደረሰበት ብለው ከቡራዩ፣ ከሆለታና ከጫንጮ የአካባቢው ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ እየመጣ ነበር” አሉን፡፡ መንግሥቴን እንዳትነኩ ከሌላ ብሔር የሆናችሁ ተጠንቀቁ፣ እያሉ የሚያስጠነቅቁ ይመስላል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አንድ እጅግ የሚገርም ሀሳብ በስብሰባ ላይ ይዘው ብቅ ብለው ነበር፡፡ በየመሥሪያቤቱ ያለ የብሔር ተዋጽዖ ሲገመገም፣ “ ኦሮሞ የሚገባውን አላገኘም” አሉና አረፉት፡፡ “ እዚህ አድስ አበባ ውስጥ ኦሮሞ ጠል አስተሳሰብ አለ” አሉን፡፡ አማራውን አስገልለው ትህነግና ኦነግ ያዘጋጁትን ሰነድ “በህገመንግሥቱ መሠርት” እየተባለ የሚቀለድበትን ውዥንብር ማለቴ ነው፣ ሲረቀቅም ሲጸድቅም እኔ አልተወከልኩም ነበር ብሎ አማራው ጥያቄ ሲያነሳ፣ ‘ለአንድ አካባቢ ህዝብ ብየ ህገመንግሥት አልቀይርም” ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡ ይኸ ሁሉ ከመስመር የወጣ አባባላቸው የጊዜያዊ የፖለቲካ ግለት ውጤት ሳይሆን፣ አቅደውና አስበውበት ያስተላለፉት መልእክት እንደነበረ እየታየ ነው፡፡ አማራው በመለስ ዜናዊ ዘመን የታረደው አልበቃው ብሎ፣ በሳቸው ዘመን በወለጋና በሻሸመኔ በግፍ እየታደነ ሲረሸንና እንደ እሾህ ምንጥር ተሰብስቦ ሲቃጠል አለማስቆማቸው፣ወይም በቦታወ ተገኝተው ለማጽናናት አልመሞከራቸው፣ የፖለቲካውን ሚዛን ለመጠበቅ ብለው ሳይሆን፣ የእቅዳቸው አንዱ አካል እንደነበረ የሰሞኑ ሥራቸው አሳይቶናል፡፡
ትህነግ የመጀመሪያዋን ጥይት ያጮኸና ጦርነቱን የለኮሰ ድርጅት ነው፡፡ ፍጅቱን የጀመረው በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ነው፡፡ ቀጥሎ መከራውን ያየው አማራና አፋር ነው፡፡ ሰላምን ማንም አይጠላም፤ ጥያቄው በማን ኪሳራ? የሚለው ነው፡፡ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከትግራይ፣ ከአማራና አፋር አልቋል፡፡ የሦሥቱም አካባቢ እናቶች ወይ ባል አልባ ወይ ልጅ አልባ ሆነዋል፡፡ ለዚያ ሁሉ ሕዝብ እልቂትና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑትን የትህነግ ወንበደዎች አድስ አበባ ላይ በሽልማት ሲያንበሸብሹ፣ በእነሱ ምክንያት በጦርነት ለረገፈው ሕዝብ የሕሊና ጸሎት እንድደረግ ጠቅላይ ሚንስትሩ አልጠየቁም ወይም አልፈለጉም፡፡ በዚያው መድረክ ላይ “ሁለት አመት ከመዋጋት ሀያ አመት መወያየት” ባሉበት አንደበታቸው፣ ልጆቹን ሰዉቶ መንግሥታቸውን ባጸናው የአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት አወጁ፡፡ ነፍሰ ገዳይን በአለም ፊት የሸለመ ጠቅላይ ሚንስትር በሰላማዊ ሕዝብ ላይ “ትጥቅ በማስፈታት” ሰበብ ጦርነት ሲያውጅ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጤነኛ ናቸው? ብሎ ቢጠየቅ ማጋነን አይመስለኝም፡ ትህነግእና ኦነግ ትግል ሲጀምሩ በጠላትነት ፈርጀው የተነሱት አማራን ነው፡፡ የሰሞኑን ዳንኪራ ለተከታተለ ሰው፣ “ታዲያ ለምን ያን ያሕል ሕዝብ እንድያልቅ ተፈለገ? ያሰኛል፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ፋሲካ ሲደልል በቅርቡ በአንድ የመጽሐፍ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር “አማራው እራሱን ከጥፋት ለመከላከል መደራጀት አለበት” በማለት የታቀደውን የአደጋ ስፋትና ጥልቀት ጠቁመውናል፡፡ ትናንት ትኩስ ምግብ ለተዋጊው ሠራዊት ያቀርብ የነበረ፣ ቁስለኛ እያነሳ ሆስፒታል ያደርስ የነበረ ሕዝብ በእንደት አይንት ፍጥነት ወደጠላትነት ቢቀየር ነው ጦር የታዘዘበት? በኦሮሞ የመስፋፋት ዘመን በአማራው፣ በሀድያውና በከንባታው ላይ ከደረሰው እልቂትና ውድመት የከፋ አማራው ምን ቢያደርግ ነው እንድህ የጥቃት ኢላማ የሆነው? አጼ ዮሐንስ በወሎና በጎጃም ሕዝብ ላይ ካደረሱት ልቂት የሚተካከል ጥፋት አማራው እንደሕዝብ ያደረሰው ጥፋት አለን? ተረትና ታሪክ ድንበራቸው ስለተደበላለቀ፣ አማራው ያለ ኅጢአቱ ሲኮነን ከመኖሩም በላይ እንደ ዘር እንድከስም የተፈረደበት መስሏል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለ ወታደሩ ቁመናና ጥንካሬ አብራሩልን፣ እንድሁም ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር ኅይልም “ሰማዩን ተቆጣጥሬያለሁ” ሲለን፣ ከወደ ካይሮ የተሰማ ነገር ይኖር ይሆን? አሰኝቶ ነበር፡፡ ጉዳዩ አማራን ከማስፈራራት ጋር የተያያዘ አስመስሎታል፡፡ እንደት ሆኖ ነው የዶ/ር አብይን መንግሥት ለማጽናት ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ያለፈው ሦሥት ዙር ጦርነት ካደቀቀው ሕይወት ሣያንሰራራ ወደ መንግሥት ግልበጣ የሚሄደው? ለምንድን ነው አማራው እንድህ የተፈራው? አማራው ከኢትዮጵያ አንድነት ውጭ ሌላ ጥያቄ የሌለው ሕዝብ መሆኑ እየታወቀ፣ ለምንድን ነው ትህነግና የኦሮሞ ጎሰኞች የአማራ ስም ሲነሳ የሚባንኑትና በሆነ ባልሆነው ሰላም የሚነሱት?
የትህነግና ኦሆድድ የጫጉላ ሽርሽር ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ፣ የአማራው እጣ ምን ሊሆን ነው? አቶ መለስ ለአማራው ያዘጋጀው እግር ብረት “ብአድን” ይባል ነበር፡፡ የዶ/ር አብይ አድሱ የአማራ እግር ብረት ደግሞ “ብልጽግና” ይባላል፡፡ የኦሆድድ ብልጽግና አማራን ያስጨፈጭፋል፤ የአማራው ብልጽግና አድስ አበባ ለስብሰባ ተጠርቶ ይሰነብትና ባሕር ዳር ሄዶ “ሐዘን ይቀመጣል”፡፡ በረቀቀ ሥልት ከራሱ ሕዝብ ጋር የተፋታ ድርጅት ተደርጓል፡፡ አማራውን ያለ መሪ ማስቀረት ማለት ይህ ነው፡፡ “መንግሥትን ለመገልበጥ” የሚል አድስ ፈሊጥ ተዘጋጅቶ የአማራው ብሶት ይመለከተናል ያሉ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎች እንድሁም ወጣቶች እየታፈሱ እስር ቤት እየታጎሩ ነው፡፡ ግፉ ድንበሩን አላለፈም?
የ1967 የመሬት አዋጅ ተከትሎ ባደግሁበት ክፍለ ሀገር የከፍተኛ ባላባቶችና የደርግ ፍጥጫ እየተካረረ መጣ፡፡በመስቀላ አምባ በኩል ደጃዝማቾቹ፣ በሌላው ግንባር የሰለጠነ የመንግሥት ጦር መሰለፉን የሰሙት የጓደኛየ አባት ሸህ ዘይኑ ዝርዝሩን ጠየቁን፡፡ ደጃዝማቾቹ ከመትረየስ ያለፈ መሳሪያ እንደማይኖራቸውና ደርጉ ግን በርቀት ሊመታ የሚችል መሣሪያ የታጠቀ አየር ወለድና ፈጥኖ ደራሽ አሰልፎ እየተጠባበቀ እንደሆነ ነገርናቸው፡፡ የዛሬ 48 አመት አካባቢ ሸህ ዘይኑ የተቀኙት እንድህ የሚል ነበር፤
“ ይኸም ወረወረ ያኛውም መከተ፣ እስኪ እናየዋለን እየሰነበተ፡
እንደ አጀማመሩ ማለቂያው ቢበጅ፣ መዘዝ ወድኋል ይኖረዋል እንጅ”፤ ነበር ያሉት
ዶ/ር አብይ የወልቃይትን በጀት ለትግራእ እየሰጠ መሆኑን ግደይ ዘረአጽዮን ነግረውናል፡፡ አማራውን ከሰሜን በትህነግ፣ በደቡብ በኦነግ/ኦሆድድ አስከብቤ እገዛለሁ ብለው ያሰቡ ይመስላል፡፡ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በፍቅር እየተገዛ ያለ ሕዝብ ለምን ለጦርነት ይጋብዙታል? አማራ ወደ አያቶቹ ከተማ አትገባም የተባለው በዶ/ር አብይ ዘመን ነው፡፡ የጤና ነው?
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ