spot_img
Wednesday, October 4, 2023
Homeነፃ አስተያየትሕገመንግሥቱን ለምን እንሞግተዋለን? (ደረጀ ይመር)

ሕገመንግሥቱን ለምን እንሞግተዋለን? (ደረጀ ይመር)

advertisement

ደረጀ ይመር

እንደ መግቢያ

የሕገመንግሥት አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ የሚጀምረው ከ1789 የፈረንሳይ አብዮት ነው፡፡ የፈረንሳይ አብዮት፣ በሰው ልጆች ታሪክ ዘንድ፣ እንደ ጉልላት የሚቆጠሩ በርካታ እሴቶችን አብርክቶ ማለፉ ይታወቃል፡፡በአብዮቱ ላይ ለመስዋአትነት የተሰለፈው ሰፊው ሕዝብ፣ የወንድማማችነት፣የእኩልነት እና የነጻነት አርማን አንግቦ የጭቆና ድባብን በመግፈፍ፤ የአምባገነናዊ ሥርዓትን ማክተሚያ አብስሯል፡፡ይህ አብዮት በፋና ወጊነቱ ከሚወደስባቸው ገድሎች መካከል መንግሥታት ያሻቸውን የግብር ውጣ አገዛዝ በሕዝቦች ጫንቃ ላይ እንዳይጭኑ የሚያግድ የተጻፈ ሕገመንግሥትን በማስተዋወቁ ነበር፡፡ይህ ሕገመንግሥት ገና በጥንስሱ ጥንድ ዓላማን ነበር የሰነቀው፡፡ሰነዱ በገዢዎች ቅጥያጣ አስተዳደር ላይ ልጓም በማበጀት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ እና ሰብኣዊ መብት እንዲከበር ዋስትናን ይሰጣል፡፡ 

ከፈረንሳይ አብዮት ለጥቆ ባሉት ዘመናት፣ የሕገመንግሥት ቅርጽ እና ይዘት እንደየሥርዓቶች ባሕሪያት ዝግመተ ለውጡ በተላያየ አጽናፍ የሚቀመጥ ነው፡፡የሊብራል ዴሞክራሲን መርህዎችን በውስጡ ያቀፈው ሰነድ፣ በአብዛኛው በምእራብዊያን ሀገራት በስፋት ሲሠራበት ይስተዋላል፡፡ በሌላ ጫፍ ደግሞ፤ የአንድ ፓለቲካ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ለማንበር፤ እንደ ዋና መሣሪያ የሚያገለግለው የቀድሞዋ የሶቪየት ኅብረት ሕገመንግሥትን መርህ የሚከተለው ሰነድ ነው፡፡ከዚሁ ጋር የሚያያዘው፣ የ1987ቱ የሕወሓት/ኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት፣ የሶቪየት ኅብረት ሕገመንግሥት ግልባጭ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡፡

በሕወሓት የሚዘወረው ኢሕአዴግ ያነጸው ሰነድ ከተነሳበት ዓላማ፣በውስጡ ካቀፋቸው አንቀጾች እና ከትግበራ አንጻር ብዙ የሚታማባቸው ድክመቶች አሉት፡፡

የሉኣላዊ ሥልጣን ጉዳይ

የ1987 ሕገመንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሰነድ አይደለም ተብሎ ከየአቅጣጫው የሚወነጨፍበት ኂስ፣ ተራ ውንጀላ እንዳልሆነ አንዱ ማሳያ የሉአላዊ ሥልጣን ጉዳይ ነው፡፡ይህ ሕገመንግሥት፣ ባእድ ጽንሰሐሳቦች ሳይፈትሹ  የታጨቁበት እንደሆነ ለማወቅ፣ ገና ከመንደርደሪያው ማወቅ ይቻላል፡፡

ገና ከጅምሩ፤ ብሔር፣በሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለው አደናጋሪ ማንነትን እንደ ቀልድ ደንጉሮ ጭራሽ የሉኣላዊ ሥልጣን ባለቤት ያደርገዋል፡፡ለመሆኑ ብሔር፣በሔረሰብ እና ሕዝቦች ተብለው የሚፈረጁት እነማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ሰነዱ መልስ የለውም፡፡እስካሁን በዚህ የጠራ ግንዛቤ ባልተያዘበት ፀጉረ ልውጥ ማንነት የተነሳ እርስ በርሳችን ስንናከስ ለመኖር በቅተናል፡፡ 

ብሔር የሚለውን ጽንሰሐሳብ ከቀደምት ሰነዶች መካከል የማርክስ ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት በእንዲህ መልኩ ነው የሚያብራራው፣ “በሔር በታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰተ የሰዎች ማኅበረሰብ ነው፡፡አንድ ብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የሚለየው ባሉት የወል ቁሳዊ የኑሮ ሁኔታዎች ነው፡፡በአንድ መልካምድራዊ ክልል ውስጥ መኖር፣ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፣በአንድ ቋንቋ መጠቀም፣በጋራ ታሪካዊ ሒደት ውስጥ የወል ሥነልቦናዊ ገጽታዎችና ባህላዊ አመለካከቶች መከሰት የብሔር መሠረቶች ናቸው፡፡”

ለመሆኑ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ክልል ብሎ ያጠራቸውን ሕዝቦች ከግምት ውስጥ ብናስገባ፤ ከቃሉ ፍቺ ጋር ማዶ ለማዶ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡የአርሲ ኦሮሞ፣ ከሸዋ ኦሮሞ ጋር በእንድ የክልል ማእቀፍ ውስጥ የተካተተው፤ የወል ስነልቦና፣የመልካምድራዊ ኩታገጠምነት እና የጋራ ታሪካዊ ሒደት ከግምት ውስጥ ገብቶ አይደለም፡፡ ከአምክንዮ በተራቆተ፣ የምንዝላታዊ መሳሳብ/ethnic identity/መለኪያ ቋንቋን ብቻ ታሳቢ ያደረ ነው፡፡ቋንቋን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ማንነትን ከግምት የምናስገባ ከሆነ ደግሞ፤ ጎሳ ወይም ነገድ የሚሉ ለዘረመል ፓለቲካ የተመቹ ሀገር በቀል ፍረጃዎችን መጠቀም የተሻለ በሆነ ነበር፡፡

 በብሔር ደረጃ የዳበረ ሕዝብ ያለው በሰለጠኑት ምእራብዊያን ሀገሮች  ነው፡፡ሕወሓት በበረሃ ቃልኪዳን ለገባለት የአልባኒያ ሶሻሊዝም፣ ታማኝነቱን ያሳየው የእንግሊዘኛውን nation, nationalities and peoples የሚለውን ጽንሰሐሳብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በሚል እንደወረደ ግንዛቤ፣ የሕገመንግሥቱ የማእዘን ድንጋይ አድርጎ ማስቀመጡን ስንታዘብ ነው፡፡በግዕዝ ብሔር ማለት ሀገር ሲሆን ሰብ ደግሞ ሰው የሚለውን ይወክላል፡፡ብሔረሰብ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሰው ሀገር የሚል ትርጓሜን ይይዛል፡፡ስለዚህ የግዕዙን ትንታኔ ከወሰድን፣ጭራሽ ደም እና አጠንት ቆጠራን አልፈን የአዳም ዘርን በሙሉ የሚያቅፍ ዓለማአቀፋዊነትን የሚሰብክ አካታች ማንነትን ታሳቢ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ሕገመንግሥቱን የክህደት ሰነድ አድርገን የምንቆጥረው፤ ካላይ ለተነሱት ወሃ የሚቋጥሩ ወቀሳዎችን አብሎ ከሩቁ ምሥራቅ ሶቪየት ሰነድ ቃል በቃል የወሰደውን አንቀጽ ስንመለከት ነው፡፡ልክ የሶቪየት ኅብረት ሕገመንግሥት የወዛደሩን የበላይነትን ለማስጠበቅ በሚል እሳቤ፤ ሁሉንም ሉአላዊ ሥልጣን ለወዛደሩ እንደሰጠ ሁሉ፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግም ሕገመንግሥት ሥልጣን ጠቅሎ ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለሚለው ባእድ ማንነት ይሰጣል፡፡ አንቀጽ 8 ላይ ይሁንን ሁኔታ በገሀድ እናገኛለን “የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ሉአላዊነታቸው የሚገለጸው በዚሁ ሕገመንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮዎቻቸውና በሚያደርጉት ተሳትፎ አማካኝነት ነው፡፡” ይላል

ሰነዱ ለዘር ማንነት የሚሰጠውን ትኩረት ያህል፣ በዜግነት ወይም ሁለት እና ከዛ በላይ የዘር ማንነት ያላቸው/meta-ethnic identities/ እውቅና አይሰጥም፡፡ ሰነዱ ኢትዮጵያዊ አሰባሳቢ ማንነትን ወዳ ዳር ገፍቶታል፡፡  በሕመንግሥቱ ፊት ግርማን ለመላበስ፤ በአንድ የዘር ከረጢት ውስጥ ራስን መክተት የግድ ይላል፡፡ 

የሥልጣን ክፍፍል ወይስ የሥራ ክፍፍል?

የሥልጣን ክፍፍል የሚለው መርህ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ እንደ ዋልታ እና ማገር የሚቆጠር የአሠራር መንገድ ነው፡፡የመንግሥት ሥልጣን ልጓም የሚበጅለት በሦስቱ  አካላት ማለትም በሕግ አውጪው፣በአስፈጻሚው እና በሕግ ተርጓሚው መካከል ተግባራዊ በሚሆነው የአግድም የቁጥጥር እና ሚዛን (Checks and Balance)  ሥርዓት ነው፡፡ 

መርሁ የትኛውም የመንግሥት አካል፣ ጡንቻውን አፈርጠሞ፤ በሌሎች አካላት ላይ የአፈና ሥርዓትን እንዳይዘረጋ ያግደዋል፡፡ለምሳሌ፣ አስፈጻሚው አካል፣ የመንግሥት ሕግን የማስፈጸም አቅሙ ከጥያቄው ውስጥ የሚውድቅ ከሆነ፣ ፓርላማው ተሰብስቦ የእምነት ማጣት ድምጽን(Vote of no confidence) ገቢራዊ በማድረግ፣ የአስፈጻሚው ቁንጮ የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥልጣን ቀነገደቡን ሳይጨርስ ማሰናበት ይቻላል፡፡ እንዲሁም፤ የአስፈጻሚው አውራ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ፤ በአንጻሩ ፓርላማው በሥራ ሒደቱ ላይ እንቅፋት እንደሆነ ካመነ፣ ሸንጎው የሥልጣን ዘመኑን ከመጨረሱ በፊት እንዲበተን፣ ድምጽ የማሰባሰብ ሥልጣን አለው፡፡ሕገመንግሥቱን በመተርጎም ረገድ ደግሞ ፤ድርሻውን የሚወጣው ሌላ ነጻ የሕግ አካል ይኖራል፡፡ 

ይህ የቁጥጥር እና ሚዛን ሥርዓት በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ውስጥ እንደ ካስማ የሚቆጠር መርህ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የአሜሪካው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ኮንግረስ) ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት (ሴኔት) እና አስፈጻሚው የበላይ አለቃ ፕሬዚዳንቱ መካከል ቁልጭ ያለ የሥልጣን ክፍፍል አለ፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ለየትኛውም የመንግሥት ክፍል ሕገመንግሥቱ ሥልጣንን ጠቅልሎ አይሰጥም ፡፡ ሥልጣን ለአንድ የመንግሥት ከፍል ጠቅልሎ በመስጠት የሚታወቀው ሰነድ፣ እንደ ሶቪየት ኅብረት ዓይነት ፀረ ዴሞክራሲዊ ሕገመንግሥት ነው፡፡ 

የእኛ ሕገመንግሥታዊ ሰንድ በአንጻሩ በፓርላሜንታራዊ ሥርዓት ውስጥ የአስፈጻሚውን ሥልጣን ለመለጎም የሚረዳው እምነት መንፈጊያ ድምጽ (vote of no confidence) አንቀጽን በውስጡ አላካተተም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፀረ ዴሞክራሲዊው የሶቪየት ኅብረት ካርቦን ኮፒ እንደሆነ ዋቢ የሚሆነን፣ በነገደ ጎበዜ ሕገመንግሥት ምርጫና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ በሚለው ድርሳን ገጽ 103 ላይ በጉልህ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡

“በደርጉ ሕገመንግሥት አንቀጽ 62 ላይ ይህ ሰፍሯል፡ በኢሕድሪ ከፍተኛው የመንግሥት የሥልጣን አካል ብሔራዊ ሸንጎ ነው ይላል፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ መጀመሪያ ከፍ ብለን እንደጠቀስነው የቡልጋሪያ ሕገመንግሥትን አንቀጽ 50/2 ላይ ፌዴራል መንግሥቱ የሕግ አውጪነትን የሕግ አስፈጻሚነትንና የዳኝነትን ሥልጣንን ጠቅልሎ እንደሚይዝ ይደነግጋል ፡፡ የሶቪየትን፣የደርግንና የሰሜን ኮርያን አባባል ቃል በቃል ወስዶ በአንቀጽ 50/3 በኢፌዴሪ የመንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡” ብሎ ይደነግጋል፡፡

ከዚህ የምንረዳው፣ የሀገሪቱ የበላይ አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ ነው፡፡የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደግሞ ራሳቸውን እንደ ሕዝብ ተወካይ ሳይሆን የሚቆጥረት፣ እንደመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኛ(ሲቪል ሰርቫንት) ነው፡፡  

የበይ ተመልካቹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዋቀረበት መርህ፣ ፀረ ፌዴራላዊ መንገድን ተከትሎ ነው፡፡በፌደራል ሥርዓት ውስጥ እንደ ፌዴረሽን ያሉ የግዛት ተወካዮች የሚካተቱበት ምክር ቤት፣ ዋንኛ ዓላማ ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር መሳ ለመሳ ሆኖ ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዲኖረው ነው፡፡ ለአብነት፤ የአሜሪካውን የፌዴሬሽን ም/ቤትን /ሴኔትን/ብንወስድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት/congress/ጋር እኩል ሕግ የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች ሴኔት እና ኮንግረስ ከ 2/3 ድምጽ በላይ አጽድቀው ያሳለፉትን ረቂቅ፣ የአስፈጻሚው ቁንጮ የሆነው ፕሬዝዳንቱ የመሻር ሥልጣኑን/ቬቶ ፓወርን/ ተጠቅሞ ውሳኔውን ማጠፍ አይችልም፡፡

 እዚህ ጋር፤ የእኛን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን መለስ ብለን ስንመለከት፣ ከሕግ አውጪ ሚና የተገለለ የበይ ተመልካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡በዚህ ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው እውቅና የተሰጣቸው 76 የዘውግ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ፣ ሕገመንግሥቱ የሰጠው ሥልጣን፣ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ጉዳዮችን እና አሻሚ የሕገመንግሥት ትርጓሜ ላይ ብይን መስጠት እንዲችል ነው፡፡ክልሎች ከድንበሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮዎችን በራሳቸው እልባት መስጠት ከተሳናቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ብይን እንደሚሰጥ አንቀጽ 48 ላይ ተደንግጓል፡፡ 

ይህ ከፓለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ያልሆነ የካድሬዎች ስብስብ፣ ሕገመንግሥቱን በተመለከተ ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጣል ብሎ ማሰብ የወሃንነት ነው የሚሆነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች ይህ ሥልጣን ከፓለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ለሆነ የዳኝነት አካል ነው የሚሰጠው፡፡ 

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገመንግሥትን ወለፈንዲነት የምንታዘበው፤ ሀገር ለመበተን ቀላል የሆነ አንቀጽን መታቀፉ ሲሆን፣ በአንጻሩ ደግሞ፤ ይኽንኑ አንቀጽ ለማሻሻል  በሚፈልግበት ጊዜ፣ ውስብስብ ሂደቶችን አስቀምጧል፡፡አንድ ክልል ከፌዴራል መንግሥቱ ተገንጥሎ በራሱ የቆመ ሀገር ለመሆን ከፈለገ፣ የክልል ምክር ቤት 2/3 ድምጽ ማግኘት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡

ከዚህ በመለጠቅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሦስት ዓመታት ሪፈረንድም ያዘጋጃል፡፡ በሌላ ጎኑ፤ እንደ አንቀጽ 39  ለማሻሻል የሁሉም ክልል ምክር ቤቶችን ይሁንታ መገኘት ይኖርበታል፡፡የዚህ ዓይነቱ አሠራር በኮንፌዴርሽን  እንጂ በፌደሬሽን አወቃቀር ላይ ፈጽሞ የሚታወቅ አይደለም፡፡ 

ለምሳሌ አንቀጽ 39ን ከሕገመንግሥቱ ላይ መፋቅ ቢፈለግ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ይሁንታቸውን ሰጥተው አንደ መቶ ሺህ የማይሞላ ሕዝብ ያለው ሐረሬ ክልል ውሳኔውን በመጻረር ውድቅ ማድረግ ይችላል፡፡ ሕገመንግሥቱ የአናሳ/የሕዳጣን/ ፍላጎት በብዙኃኑ ላይ መጫን የሚያስችል ሰነድ ነው፡፡

ማሰሪያ ነጥብ

ከሕወሓት ጋር ኩታገጠም መርህን የሚያቀነቅኑት የዘውግ ድረጅቶች፣ የሕገመንግሥቱ መርህን ከመሄስ ይልቅ፤ ትግበራው ላይ ጉንጭ አልፊ ክርክርን ያበዛሉ፡፡ለዚኽም፤ እንደዋቢ የሚያነሱት፣ ሰነዱ በውስጥ ያቀፋቸውን የሰብኣዊ መብት አንቀጾችን ነው፡፡የቬና አለም አቀፍ ድንጋጌ ውጤት የሆኑት፣ የሰብዓዊ መብትን የሚከላከሉት አንቀጾች ግን፤በደርግ ሕገመንግሥት ውስጥ እንደነበሩ፣ እነዚህ ወገኖች ለማንሳት አይደፍሩም፡፡ 

በአጠቃላይ፤ ሕገመንግሥቱ ለአፈና አገዛዝ የተመቸ ሰነድ ነው ቢባል፤ ከእውነታው ጋር መጋጨት አይሆንም፡፡ በውስጡ ያዘላቸውም አንቀጾች፣ ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት ከተጻፉበት ቀለም የበለጠ ዋጋ ሲኖራቸው መታዘብ አልቻልንም፡፡ስለዚህ፤ወደፊት ከቅብ ባለፈ የሚቀረጸው ሕገመንግሥት፣በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ፍላጎት የተንጸባረቀበት፤ ዘላቂ የሀገር ጥቅምን ከግምት የጣፈ መሆን ይኖርበታል፡፡

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,733FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. ለዘመናት አውጅ ይታወጃል።የማጠናከሪያ አዋጅ ይጨመራል።ለአዋጁ አውጅ ይደሰኮራል።ተጨማሪም ፖሊሲ ይረቃል።እንደ መስቀል ችቦ የፓርላማ አባል መማክርት እጅ ይቀሰራል።የተስማምቻለው እጅ ይቆጠራል።ሕግ ተብሎ በየመገናኛው ይደሰኮራል። የሕጎች ሁሉ ቁንጮ የተባለው ሕገ መንግሥት በኮሚቴ ጋጋታ ፣በጥናት ከበርቻቻ ይቀረጻል።ለይስሙላ ህዝብ ተቀበለው በየመገናኛው የእውሸት አምላክ እስኪማረር ይደሰኮራል።ይህ ልማድ በተለይ ለ 32 ዓመታት የነበረ የዳበረ ሕግና ፖሊስ ፊዝ ሆኖ ቀጥሏል።

    ለይስሙላ ሕገ መንግሥት ይጻፍ እንጂ ውሎ አድሮ ዋናው ጉዳይ ከበላይ የተጫኑብን አባገነኖች ፈቃድ ነው።በብዙ ሺ የአገር ቤት መንደሮችን ደምረው፣በኪሎ ሜትር የትራራቁ የሳር ጎጆውችን በሃሳብ አጠጋግተው እነዚህ ብሔሮች ናቸው ብለው በሕገ መንግስት ቢጽፉት የእንሱ ፈቃድ ብቻ ነው።በፓርላማ ጠቅላይ ሚንስቴሩ እራሳቸው ስብሰባ እየመሩ እራሳቸውን ቢያስመርጡ አስፈላጊው ሕግና ደንብ አይደለም የአምባገነኑ ፍቃድ ብቻ ነው።ፍርድ ቤት የፈታውን እስረኛ ፖሊስ ቢያስር የሹሙ በጎ ፈቃድ ነው።

    ሕግና ደንቡን ለሥልጣናቸው ማራዘሚያ ይጽፉታል።ብዙ ሕግ ፣አዋጅ፣ ፖሊስ ግን በተግባር ተፈጻሚነት የለውም።ይህ የመንግስትና የብሮክራሲው ወረርሺኝ በሺታ ነው።ታድያ መላልሰን ስለ ሕገ መንግስት የምናወሳው ለምንድ ነው? በአደንቋሪ ባሕል ተተብትበን፣በልማድ ታስረን ሕግ ተፈጻሚነት ከሌለው ፋይዳው ምንነው?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here