
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ (ግንቦት 24 2015)
በሃገራችን፤ ሕዝብ የመረጠው መንግስት እንዲያስተዳድረን ብቻ ሳይሆን፤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፤ ማንም ይሁን ማን ከህግ በታች እንዲሆን ላለፉት 50 ዓመታት ከፍተኛ ትግል ተደርጓል ብዙ መስዋዕትነትም ተከፍሏል። የ1966 አብዮት፤ በወታደራዊ መንግስት ተጠልፎ ሲከሽፍ፤ በ1983 የመጣው ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ለውጥ ደግሞ በሕወሃት እና አጋሮቹ ተጠልፎ ከወታደራዊው መንግሥት በከፋ አገዛዝ ሥር ለ27 ዓመታት ማቀን፤ በሌላ ከፍተኛ መሥዋእትነትና እልህ አስጨራሽ ትግል፤ የሕወሃት መራሹ መንግሥት በየካቲት 2010 ከስልጣን ተወግዶ፤ በኦሕዴድ መራሹ መንግስት ሲተካ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ ሰንቆ ለውጡን ከግብ ለማድረስ ተዘጋጅቶ ነበር። የኦሕዴድ መራሹ መንግሥት፤ ፓርቲውን በተለያየ ሥም ከቀየር በኋላ፤ በመጨረሻ የብልጽግና ፓርቲ በሚል ፀንቶ፤ በሕዝብ ተመርጦ በሥልጣን ላይ ይገኛል።
የሕወሃት መራሹ መንግሥት ከጅምሩ በሕዝብ ከፍተኛ ተቃውም የገጠመው፤ ሃገሪቱን በብሔር ፖለቲካና አስተዳደራዊ መዋቅር ለመመስረት ማቀዱ፤ ባልነበረው ሕጋዊ ሥልጣን የኤርትራን ክ/ሃገር ለማስገንጠልና ለመገንጠል፤ ተግቶ በመስራቱ፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑ እሴቶችን በማጣጣሉ፤ የሰብዓዊ መብት ረገጣው፤ ገና በትረ ሥልጣኑን ሳይጨብጥ የተካነበት መሆኑና ለሕዝብ የነበረው ከፍተኛ ንቀት ነበር ከሕዝብ ጋር ያጋጨው። “ደርግን የጣልነው እኛ ነን” በሚል የቅዠት ደዌ ታሞ፤ ለ17 ዓመታት፤ በሁሉም አካባቢ ፀረ ወታደራዊ መንግሥት ትግል መደረጉንና፤ ለወታደራዊው መንግሥት መውደቅ አብዛኛው ሕዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት በመዝንጋትና በመካድ፤ “ደርግን ታግለን የጣልነው እኛ ነነ፤ ሥልጣን መያዝ ያለብን እኛ ብቻ ነን” በሚል እኩይ ስሜት፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያው ሥልተ ሥርዓት ለመገንባት ሲምል ሲገዘት እንዳልነበር፤ ሕዝብን ያላሳተፈ፤ የራሱን የፖለቲካ ሕልም ያሳካልኛል ብሎ ያመነብተን “ሕገ መንግሥት” አርቅቆ አፀደቀ። የሚገርመው፤ የሕወሃት መራሹ መንግሥት ነጋ ጠባ ስለሕገ መንግስት ቢደሰኩርም፤ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን ያመሰውና ህዝብን ያሰቃየው ሕገ መንግሥቱ ከሚደነግገው መመሪያና ሕግ ውጭ እየሰራ እንደነበር ነጋሪ አያሻውም።
የካቲት 2010 የመጣው ለውጥ፤ ለ27 ዓመታት በተደረገ መሪር ትግል እንጂ፤ ኅዳር 2008 ላይ በተጀመረው የኦሮሞ እና የአማራ ክልል ወጣቶች አመጽ ብቻ እንዳልሆነ፤ በተለይ በኦሮምያ ክልል መስተዳድር ውስጥ ያሉ ሰዎች የዘነጉት ይመስላል። ዛሬም ትርከታቸው “ኦሮሞ ያመጣው ለውጥ ነው” “ዐብይን ለስልጣን ያበቃው የኦሮሞ ወጣት ነው” የሚል የሃሰት ትርከታቸውን ተመርኩዘው “ኦሮሞ ፈርስት” በሚል ፈሊጥ የሌላውን ዜጋ መብት በሚጋፋ መልኩ በንቀትና በትዕቢት የለወጡ የጉሮሮ አጥንት ከሆኑ ውለው አድረዋል። በሚገርም መልኩ፤ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ የጠቅላይ ምኒስትሩ ጽ/ቤት እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ፤ የዚህን ክልል መስተዳድር ሕገ ወጥነትና፤ ለሕዝብ ያለውን ንቀት ሊያበርዱለት አለመቻላቸው፤ ታሪክ እራሱን እየደገመ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ነው።
ኦሮምያ ክልል ውስጥ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ በአጠቅላይ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ በተለይ ሲፈፀም የቆየውንና እየተፈፀመ ያለውን ግፍ መናገር፤ ለቀባሪው ማርዳት ይሆናልና ግፉን አልዘረዝርም። ክልሉ ከለውጡ ጅማሮ አንስቶ፤ ለእንደ ጃዋር መሐመድ ዓይነት “ትናንሽ የጎጥ ንጉሶች” ጥበቃ በማድረግ፤ ለበርካታ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት መጥፋትና በሚሊዮን ብር ለሚቆጠር የንብረት ጥፋት ምክንያት ሆኗል። በክልሉ በተደጋጋሚ አንገፍጋፊ ግፍ ሲፈፀም፤ አንድም የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣን ለዚህ ግፍ ተጠያቂ አልሆነም። ዛሬም ቢሆን በመኖርያ ቤቶች እና በቤተ እምነቶች ላይ የሚያደርገውን ሕሊና ቢስ ቤት ፈረሳ፤ ክልሉ በትዕቢትና በማን አለብኝነት መቀጠሉ፤ ለምንም ነገር ወደ ሃላ የማይመለስ መሆኑን ያሳብቃል።
የኦሮምያ ጨፌ መሪው ላይ ያንቀላፋ አጨብጫቢ እጆች እንጂ የሚያስቡ ጭንቅላቶች እንደሌሉበት ላለፉት አምስት ዓመታት በትዝብት አይተናል። አቶ ሽመልስ አብዲሳም ሥልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምረው፤ እንደ አንድ ክልል መሪ ሳይሆን፤ ድርጊታቸው፤ ለብሽሽቅ እንደሚተጋ የሰፈር ጎረምሳ በመሆኑ፤ የሚሰሩት ሥራ ሁሉ ባላንጣ የሚሏቸውን ለማብሸቅ የሚመስል እንጅ ትልቁን የኦሮሞ ሕዝብ የሚወክል አይደለም። ምንም እንኳን በ1994 የተሻሻለው የኦሮምያ ክልላዊ መስተዳደር ሕገ መንግሥት አንቀጽ 103 ቁጥር 2 “መንግስት የብሔሮችን፤ የብሔረሰቦችንና የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው አንድነትና ወንድምማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት”። ቢልም፤ አቶ ሽመልስ ግን ይህንን የሕዝብን የወንድማማችነት እሴት ሲሸረሽሩና የክልሉን ሕገ መንግሥት ሲጥሱ “ተው ባይ” አላገኙም።
ዛሬ በርካታው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ “የኦሮሞ የበላይነት በሃገር እየሰፈነ ነው” በሚል ቅሬታ ወዴት እየሂድን ነው እያለ ሲጠይቅ፤ እነ አቶ ሽመልስ ለሕዝብ ያላቸውን ከፍተኛ ንቀት ለማሳየት “የኦሮምያን ክልል ቤተ መንግሥት ለመገንባት” መሰረት ጥለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያገባው የአዲስ አበባ ሕዝብና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝምታም አስገራሚ ነው። ጋዜጠኞችም ይህ “ቤተመንግሥት ግንባታ” ሕገ የጣሰ መሆኑን ለሕዝብ የማይገልጹበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሲቪክ ድርጅቶች፤ እንዲሁም ነዋሪው በመተባበር በፌደራል ፍርድ ቤት ክስ የማይመሰረትበት እና በቤተ መንግሥት ግንባታው ላይ እግድ እንዲጣል የማያደርገውስ ለምንድን ነው?
የኦሮምያ ክለላዊ መስተዳድር ቤተመንግስት በአዲስ አበባ መገንባት፤ ለከተማው ገቢ የሚያስገኝና የሥራ እድል የሚፈጥር ቢሆንም፤ ከሕግ፤ ከፖለቲካ እይታ፤ እንዲሁም ከአስተዳደራዊ ኩነቶች አንፃር እጅግ የተሳሳተና አደገኛ የክልሎች ፉክክር ጅማሮ ሊሆን ይችላል። የዚህ ቤተመንግስት ግንባታ የኢትዮጵያን ፌደራላዊ መንግስት ሕገ መንግሥት የጣሰ ብቻ ሳይሆን፤ የኦሮምያ ክልል መስተዳድርን ሕገ መንግሥት የጣሰም ጭምር ነው። በጣም የሚገርመው በቅርቡ አሻም የተባለ ሬድዮ ፕሮግራም ላይ ለውይይት የቀረቡት የኦሮምያ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ሃላፊ፤ የኦሮምያ ክልላዊ መስተዳድር ሕገ መንግሥት “የኦሮምያ ክልል አዲስ አበባ (እሳቸው ፊንፊኔ ይሉታል) ውስጥ የኦሮምያን ክልል መስተዳድር ቤተ መንግሥት እንዲገነባ ይፈቅዳል ማለታቸው፤ ልክ እንደ ሕወሃት መራሹ መንግሥት ባለሥልጣናት፤ የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናትም የተፃፈውን ሕገ መንግሥት በቅጡ የማያውቁ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ያሳበቀ አስቂኝ ክስተት ያደርገዋል።
የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 እንዲህ ይላል፡
1. የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡ 2. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡ 3. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት ይሆናል፡፡
4. የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከላሉ፡፡
5. የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፣ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”
ቁጥር 5ን በአጽንኦት ላስተዋለው፤ “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” ይላል። አዲስ አበባ በኦሮምያ ክልል መሃል የሚገኝ እንጂ የኦሮምያ ክልል አካል አይደለችም። የ1987 ዓም ኦሮምያ ክልል መሥተዳድር ሕገ መንግስት አንቀጽ 7 “የኦሮምያ ክልል ርእሰ ከተማ ፊንፊኔ ነው” ቢልም፤ ይህ ሕጋዊ አልነበረም ምክንያቱም ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ይፃረራል። ይህ አንቀጽ ግን፤ በ1994ቱ በተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግስት ተቀይሯል።
ከዚህ በተጨማሪ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ቁጥር 3 የኦሮሞ ሕዝብ “እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው፤ በራሱ መልክአ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማትን የማቋቋምና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት አለው” ይላል። ይህ ማለት፤ ዮእሮምያ ክልል መስተዳድር፤ ተቋማቱን ሊገነባ የሚችለው በክልሉ መልክአ ምድር ውስጥ ብቻ ነው። አዲስ አበባ የክልሉ አካል ባለመሆኗ አዲስ አበባ ውስጥ የክልሉን ቤተ መንግስት መገንባት ሕገ ወጥነት ነው። የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናት የቤተ መንግሥቱን ግንባታ መሰረት የጣሉት “አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የኦሮምያ ክልል አካል ነው ከሚል የትዕቢት እሳቤ የመነጨ ለመሆኑ ጥያቄ የለኝም። የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለስልጣኑ ከአሻም ሚድያ ጋር በነበራችተው ቆይታ፤ ፊንፊኔ የኦሮምያ ክልላው መንግሥት መቀመጫ ከሆነች 30 ዓመታት ሆኗል ሲሉ የራሳቸውን የተሻሻለ ሕገ መንግሥት እንኳን እንደማያውቁ ብቻ ሳይሆን፤ የክልሉ ሕገ መንግሥት ከፌደራሉ ሕገ መንግስት ጋር የሚጻረር ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንደሌለው ያለመርዳታቸውን የሚያሳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በ1994 ዓ.ም. የተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 6 ውስጥ በግልጽ እንደተካተተው፤ “የኦሮምያ ክልል ርእሰ ከተማ አዳማ ነው” ይህ፤ በ1987 የነበረውን “የኦሮምያ ክልል ርእሰ ከተማ ፊንፊኔ ነው” የሚለውን የቀየረ ነው። ሲጀመርም “የኦሮምያ ክልል ርእሰ ከተማ ፊንፊኔ ነው” የሚለው የተሳሳተና ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ቢሆንም፤ የሕወሃት መራሹ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ሥጋት ለመፍጠር ሆን ብሎ የቀመረው ተንኮል ነበር።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት በግልጽ እንድሚያሳየው የሃገሪቱ የበላይ ሕግ የፌደራሉ ሕገ መንግሥት መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ ሕገ መንግሥት በግልጽ እንደሚያስቀምጡት፤ የየትኛውም ክልል ሕገ መንግሥት ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ሊፃረረ አይችልም። ስለዚህም ከሕግ አኳያ፤ የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ቤተ መንግስት የመገንባት ምንም ሕጋዊ መሰረት የለውም። ሌላው ቀሮት፤ የክልሉ የፖሊስ መምርያም ሆነ ሌሎች የኦሮምያ ክልላዊ መስተዳደር ተቋማት ከአዲስ አበባ መነሳት አለባቸው። ይህም እንዲሆን መብቱን ማስከበር ያለበት የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ነው። በግልጽ እንደምናየው፤ የአዲስ አበባ መስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቢቤ በተደጋጋሚ ያሳዩን የአዲስ አበባን ጥቅም ለማስከበር ከመጣር ይልቅ፤ የኦሮምያ ክልልን አጀንዳ የሚያራምዱ መሆናቸውን ነው። የአዲስ አበባ ምክር ቤት፤ የፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ የጠቅላይ ምኒስትሩ ቢሮ ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳላይ በማለፍ፤ በፖለቲካም የሚያስከፍለውን ዋጋና የሚፈጥረውን ውዝግብም ሆነ የሕዝብ ቅሬታ ከቁብ ባለመቁጠር እዎንታዊ የሰጡት የቤተ መንግሥት ግንባታ በከተማው ሕዝብ በዝምታ ሊታለፍ አይገባውም።
እስካሁን ባለው የለውጥ ሂደት፤ የለውጡ የጉሮሮ አጥንት በመሆን በሃገራችን ከፍተኛ እንቅፋት እየፈጠረና በሕዝብ ላይ ግፍ እየፈፀመ የሚገኘው የኦሮምያ ክልላዊ መስተዳደርና ሃገሪቱ የሕግ የበላይነት ያልሰፈነባትና፤ ባለሥልጣኖች ዛሬም እንድትላንቱ ከሕግ በላይ መሆናቸው ነው። ዜጎች በግልጽ ማወቅ ያለብን፤ መብታችንን ማስከበር ያለብን እኛና እኛ ብቻ መህናችንን ነው። እንደሚባለው “መንግሥት በተፈጥሮው ስድ ነው” ይህን ስድነት ሊገድቡ የሚችሉት ግን በሃገራቸው ጉዳይ ነቅተው የሚሳተፉ ዜጎች ናቸው። የተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ በዚህ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች ተቀምጠው አቤቱታ ከማቅረብ ባለፈ፤ የፍርድ ቤት ተቋማትን በመጠቀም መብታቸውን ማስከበርና የፍርድ ቢቶችን ገለልተኝነትንም ሊፈትሹ ይገባል። ስለዚህ፤ በአዲስ አባበ መሰረት የተጣለለትን የኦሮምያ ክልል ቤተ መንግስት ግንባታ ለማስቆምና ሌሎች የክልሉ ተቋማት ወደ ኦሮምያ ክልል እንዲዛወሩ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች፤ እንዲሁም ጉዳዩ ያገባኛል ለሚሉ ባለድርሻ አካላት የበኩሌን ጥሪ አቀርባለሁ። አዲስ አበባ የኦሮምያ ክልል “ቅኝ ግዛት” መሆን የለባትም።
ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ።
አሁንም ስለለውጥ ታወራለህ? አንዳንዱ ቢታጠብ ቢታጥብ አይጸዳም