spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትዕውን ትግላችን ፀረ ኦሮሞ ነውን? የነቃና የተደራጀ ትግል ያሸንፋል!  

ዕውን ትግላችን ፀረ ኦሮሞ ነውን? የነቃና የተደራጀ ትግል ያሸንፋል!  

በብሔር ብሔረሰቦች መብት ዙሪያ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ መቀንቀን ከጀመረ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ይሆነዋል። ይህ ጥያቄ የፖለቲካ ቅርፅ ከያዘና ድርጅቶችም መፈጠር ከጀመሩ እንዲሁ ተመሳሳይ ዘመን አሳልፏል። በመጀመሪያ በእድርና መረዳጃ ማህበራት ዙሪያ የተጠነሰሰው ብሔር ጠቀስ መሰባሰብ የፖለቲካ ባህርይ የያዘውና በድርጅታዊ ይዘት መከሰት የጀመረው ከየካቲት 66 ዓም ህዝባዊ ንቅናቄ ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። 

አብዛኛው የጥያቄው አቀንቃኞች የየብሔር ብሔረሰቡ ምሁራን ቢሆኑም፣ ጥያቄውን ህዝባዊ መሠረት ለማስያዝ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበረው የመደብ ልዩነትና ስልተ ምርቱ የፈጠረው የኢኮኖሚ ይዞታ ልዩነት ወደማይታረቅ ደረጃ ስለደረሰ የአብዮትን አዋላጅነት አስከትሏል። በዚህም ረገድ የገዢ መደብ ተብሎ በዋናነት የተነጣጣረበት “የአማራው የገዢ መደብ” በመሬት ይዞታ ባለቤትነት፣ በአስተዳደር ቁንጮነትና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ጭምር የተለየ ስለነበር፣ የብሔሮችን እኩልነትና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ሲያቀነቅኑ የነበሩ የብሔር ድርጅቶች ሁሉ ይህ የመደብ የበላይነት የፈጠረውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን አለመመጣጠን ምክንያት በማድረግ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ሲቀርፁ የአማራውን የገዢ መደብ ዒላማ በማድረግ ነበር። ይሁንና ይህ እውነታ በ1967 ዓም ከታወጀው ስር ነቀል የመሬት አዋጅ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ የባላባትና ጭሰኛ ግንኙነት አክትሟል። በመሆኑም የአማራ ገዢ መደብ የሚባለውም እሳቤ አብሮ ሞቷል። ይሁን እንጅ ተከዮቻቸውን በዚህ የሀስተ ትርከት ላይ ተመስረተው ያሰባሰቡት የብሔር ድርጅቶች ይሁነን ብለው በቀረፁአቸው የፖለቲካ ፕሮግራሞች ውስጥ ይህንን ጊዜው ያለፈበት ክስ ሲደረድሩ ይሰማሉ። የብሔር ፖለቲካ የርዕዮተ ዓለም መሠረቱ የጥላቻ ትርከት ሲሆን ግቡም ልዩነትና መነጣጠል እንዲያም ሲል  በብሔሮች መብት አስጠባቂነት ነው የስልጣን ክርቻ ላይ መንጣላጠል እንደሆነ ዛሬ እያስተዋልን ነው። 

ታሪክ እንደሚመሰክረው አብዛኞቹ የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች አቅምና የበላይነት አግኝተው ፍላጎታቸውን በኅብረተሰቡ ላይ መጫን የጀመሩት ከደርግ መንግሥት መውደቅና ከወያኔ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ነበር። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ህገ መንግሥት ሲቀረፅ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥቅም በማስቀደም ሲሆን ይህም በበኩሉ በብሔረሰቦች መካከል እርቅን፣ የኢኮኖሚ ጥቅምንና ፍትሓዊ ክፍፍልን ከማረጋገጥ ይልቅ፣ በተለይ የአማራውን ብሔር በጠላትነት ያስቀመጠ ስለሆነ፣ የመቶ ዓመታት ታሪክ ወደኋላ እየተጠቀሰ ቅራኔውን ከማርገብ ይልቅ የበለጠ እንዲጦዝና ለብጥብጥም ምክንያት እንዲሆን አድርጎታል። 

በቀደመው ሥርዓት ማለትም የመሬት ላራሹ አዋጅ አርሶ አደሩን ባለመብት ከማድረጉ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም የሲሶ መንግሥት ድርሻ ተጠቃሚ ስለነበረች ለውጡ ከመጣባቸው የኅብረተሰቡ አካላት ጋር በመጣመር በተቃዋሚነት መቆሟ የግድ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ሥዩመ እግዚአብሔር የነበሩበትና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ለሥርዓቱ ቡራኬ በመስጠት ተጓዳኝ ተጠቃሚ የነበረችበት ሥርዓት ሲያከትም፣ የተከሰተው የመደብ አሰላለፍ ለውጥ የሃይማኖትን እኩልነት ያቀዳጀ ቢሆንም፣ የመንግሥት ሥልጣንንና የሃይማኖት ነፃነትን የለያየ አልነበረም። 

ስለሆነም የደርግ መንግሥት ሥልጣን እንደተቀዳጀና የፊውዶ ቡርዧ ሥርዓቱ ቁንጮ የነበሩትን ንጉሠ ነገሥትና ባለሥልጣናት ሲያስወግድ በወሰደው ተዛማጅ እርምጃ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባት የነበሩትን ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ በግፍ አፍኖና ገድሎ ሲያበቃ ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጪ የራሱን የይስሙላ ፓትርያርክ በማስመረጥና በኢአማኒነትም ጭምር የተዋህዶ ሃይማኖትን ሥፍራ ዝቅ አድርጓል። 

ሆኖም አያሌ የእምነቱ ተከታዮችን ድጋፍ ላለማጣትም ጭምር፣ በየህዝብ በዓላቱ መድረክ ላይ የኦርቶዶክሱን ፓትርያርክና የሙስሊሙን የሃይማኖት መሪዎች በአቻነት በአደባባይ እንዲታደሙና እንዲታዩ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ወያኔ ኢህአዴግ የፖለቲካ ሥልጣን ላይ እንደወጣ በደርግ አገዛዝ ዘመን በፓትርያርክነት ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲመሩ የነበሩትን የሃይማኖት አባት ከሀገር እንዲሰደዱ በማድረግ በብሔር ማንነት ላይ በተመሠረተ ምርጫ የትግራይ ብሔረ ሰብ ተወላጅ የነበሩትን አቡነ ጳውሎስን በስደት ከነበሩበት ሀገር በማስመጣት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በጣሰ መልኩ በፓትርያርክነት እንዲሰየሙ አድርጓል። 

በወያኔ አባል ድርጅቶች መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ትንንቅና በተለይም በአማራና ኦሮሚያ አካባቢ በተከሰተው ያላሰለሰ ተቃውሞ የተወለደው ፣በዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመራው “የቲም ለማ”  የለውጥ አንጃ ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ “ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደመና የኅብረተሰቡን ቅራኔዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያለመ በሚመስል” መንገድ ተለያይተው የነበሩ ሁለት ሲኖዶሶችን በማስታረቅ የለውጡን ጎዳና ጀመረ። 

ይሁን እንጂ የወያኔ ኢህአዴግን ሥልጣን በብልፅግና ስም አደላድሎ በኦሮሞ የበላይነት ውስጥ የከተተው የዐቢይ አህመድ መንግሥት፣ ሁሉንም አደረጃጀቶች በበላይነት መያዙን ካረጋገጠ በኋላ የኢትዮጵያዊነት የመጨረሻ ምሽግ ናት ብሎ የሚያምናትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዒላማ በማድረግ ተንቀሳቀሰ። 

ከዚህ አንፃር “በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ እኩልነት የለም፣ ምእመናን በቋንቋቸው እንዲማሩ አልተደረገም፣ ስለሆነም የኦርቶዶክስን ሃይማኖት እየለቀቁ በሚገባቸው ቋንቋ የሚያስተምሩትን እምነቶች እየተቀላቀሉ ነው” በሚል ተልካሻ ሰበብ ቋንቋን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት በቤተ ክርስቲያኒቱም ውስጥ እንዲፈጠር አደረገ። በመሆኑም “የኦሮሚያና የብሔረ ብሔረ ሰቦች ሲኖዶስ” የሚል አሻንጉሊት አስኳል ፈጥሮ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ዶግማ ውጭ በሲኖዶስ ላይ ሲኖዶስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ። በመሆኑም በኅብረተሰቡ ውስጥ ብዙ ተከታይ ያላትንና ታሪካዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚንድና በኅብረተሰቡም ውስጥ ክፍፍልና ግጭትን የሚቆሰቁስ አደረጃጀት እንዲፈጠር ሰበብ ሆነ።

ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት ዘመናትን የባጀ ልምድና ከዚያም በተወለደው በሳልና አርቆ አስተዋይ አመራር፣ በመንግሥት ድጋፍ የተጀመረውን ፀረ ኢትዮጵያ አንድነት ቆስቋሽ እርምጃ ለጊዜውም ቢሆን ማምከን ተችሏል። የዚህ “የዲቃላ ሃይማኖትን ሽፋን” ያደረገ እንቅስቃሴ ጠንሳሾች እንደሚነገረው የተወሰኑ አፈንጋጭ ካህናት ሳይሆኑ፣ የገዢው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ አመራር አባላትና የኦሮሚያን ነፃ መንግሥት የመመስረት ህልም ያላቸው የኦሮሞ ጠባብ ብሔረተኛ ድርጅቶችም የተቀናጀ እቅድ ነው። 

በሰሜን ተጀምሮ የነበረው የህወሓት የመስፋፋትና የመንግሥትን ሥልጣን መልሶ የመንጠቅ እንቅስቃሴ ለጊዜው የባላይነቱን በማጣቱና በኦህዴድ ብልፅግና የሚመራው አንጃም በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነቱን በማስረገጡ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የፖለቲካ ሥልጣን ጠቅልሎ ለመያዝና በተለይ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ዋና ከተማ አድርጎ የመግዛት ህልሙን ለማሳካት ለሚያደርጋቸው ዝግጅቶች፣ ሁለቱን ትልልቅ ሃይማኖቶች በቁጥጥር ስር ማዋል አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው መገመት አያዳግትም። 

በዚህም ረገድ በመጀመሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮችን መጅሊስ በክልል እንዲደራጅ በማድረግና ሙፍቲውንም በኦሮሞ ተናጋሪ መሪነት እንዲተኩ ካደረገ በኋላ፣ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ አመራር ላይ ማዞሩ ይታወቃል።  በቅርቡ እነ አባ ሳዊሮስ በመባል የተለዩት “የኦሮሚያና የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” መሥራች ነን ባዮች የዚሁ የኦሮሚያን የበላይነት ያለመ ውጥን አካል በመሆን የመጨረሻውን የኢትዮጵያዊነት ምሽግ ለመስበር የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። 

አስተዋይ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህንን ዘር መሠረት ያደረገ ትንኮሳ የተቋቋሙበት ዘዴ ሙሉ በሙሉ ከቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ዶግማ ጋር የተያያዘ በመሆኑና ህዝበ ክርስቲያኑንም ወደ በለጠ አንድነት ያመጣ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሊሎቹንም የእምነት ተከታዮች በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ትዕግሥት ተባባሪ ማድረግ በመቻሉ፣ ጭንቀት ውስጥ የገባው የዐቢይ አህመድ አስተዳደር እውነተኛ ፋሺስታዊ ባህርይው ገሃድ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል። 

ለሃይማኖቱ ቀናኢ የሆነውንና የተዋህዶን አባቶች ጥሪ ተቀብሎ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድነት ሆ ብሎ የተነሳውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከፋፈል፣ ለማስፈራራትና የእንቅስቃሴው መሪዎች የሚባሉትን ወጣት የሃይማኖቱ ተከታዮችንና አባቶችን እንዲሁም ለእውነት የቆሙትን ሀቀኛ የእስልምና፣ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን ሳይቀር በገፍ አፍሶና አፍኖ ወደ አዋሽ አርባና ሌሎች ማጎሪያዎች በማጓጓዝ ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው። ብዙዎች አሁን ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። 

ከኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ የደረሰ በማስመሰል የተነሳውን ህዝባዊ የቁጣ ማዕበል ለጊዜውም ቢሆን ለማብረድ ከቻለ በኋላ፣ ካህናቱንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ሸውዶ በማግስቴው የደህንነትና የፀጥታ ልምምድ ማድረግ በሚል ሽፋን አፈሳና አፈናውን ማጧጧፉ የአደባባይ ምስጢር ነበር። በዚህ ረገድ የደብረ ብርሃንና የጎጃምን መስመር በፀጥታ ሰበብ በመዝጋት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡትን ተጓዦች በሙሉ አግዷል። 

በሻሸመኔ ከተማና ዙሪያዋ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተ ክርስቲያኖችን በኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ሃይል ታጣቂዎች በመውረር ባካሄደው ጭፍጨፋ ከ37 የሚበልጡ ንፁሃን የሃይማኖቱ ተከታዮች ሲገደሉ ከመቶ በላይ የሚደርሱ ቁስለኞች በአዋሳ ሆስፒታል እንደሚገኙ እየተገለፀ ነው። በቅርቡ በአጣዬና ሸዋ ሮቢት አካባቢ ራሱን ኦነግ ሸኔ በሚል በሚጠራው በኦሮሚያ መንግሥት የተደገፈ የውንብድና ቡድን ዘርን መሠረት ያደረገ አስከፊ ጭፍጨፋ ተካሂዷል። ከ 250 ሺ የሚበልጡ የአማራ ተወላጆች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በየቦታው ተበትነው የስቃይ ኑሮ በመግፋት ላይ ይገኛሉ። 

ይኸ ሁሉ ዘር ተኮር ግፍ፣ መታፈን፣ ጭፍጨፋና መፈናቀል በሚካሄድበት ወቅት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ህግን ለማስከበር ካለመቻሉና ፍቃደኛም ካለመሆኑ ባሻገር፣ ለጨፍጫፊዎቹና ህገ ወጥ ለሆኑት የኦሮሞ ፅንፈኞች ጥብቅና በመቆም ዓይን ያወጣ ዘረኝነትና ማናለብኝነት ውስጥ ተዘፍቋል። የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርጎ በመጥራቱና ባሳየው “ትህትና” የኢትዮጵያዊያንን ልብና ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዐቢይ አህመድ የቀበሮ ባህታዊነት ፍንትው ብሎ በመውጣቱ፣ እምነቱና ድጋፉ ሁሉ እንደበረዶ ክምር ቀልጧል።  ስለሆነም በተለመደው ስብከት ማታለል እንደማይቻለው የተረዳው የኦሮሞ ብልፅግና መሪ ሁሉንም የአስተዳደር ዘዴ እርግፍ አድርጎ በመተው በሃይልና በሃይል ብቻ አንበርክኬ እገዛዋለሁ ወደሚል እብሪት ተሸጋግሯል። 

ዳር እስከዳር የተነሳሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማኮላሸት በማሰብ የትግራይ አማፅያንን መለማመጥና የኦሮሞ ተቃዋሚዎችንም ድጋፍ ለማግኘት የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። የኦህዴድ ብልፅግና ፕሬዜዳንት በሆነው ሽመልስ አብዲሳ አማካይነት “ኦነግ ሸኔ” ብለው እነርሱ በፓርላማ ካወገዙት ሃይል ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ጥሪ አድርጓል። 

የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ለማመስና ለማዳከም የተጀመረው አደገኛ ሙከራ ለጊዜው የተገታ ቢመስልም፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖች አካባቢ ግን የህጋዊው ኦተቤክ ንብረቶች እንዲዘረፉ፣ ካህናትና አገልጋዮች በግፍ እንዲታሰሩና እንዲፈናቀሉ፣ ቤተ ክርስቲያናት ላይ ገሃድ ወረራ በመፈፀም በአንጃው ሲኖዶስ የተሰየሙ “ኤጲስ ቆጶሳትን” የቤተ ክርስቲያናቱ አስተዳዳሪና የበላይ ተጠሪ አድርጎ በመሾም ህገ ወጥ መፈናቀሎች እየተፈፀሙ ይገኛል። 

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ህግ የማስከበር አቅምም ሆነ ፍላጎት ያለው አይመስልም። እያየ እንዳላየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ በመምሰል ለህዝብ ጩኸትና ሰቆቃ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሏል። በእያንዳንዱ ህዝባዊ፣ ባህላዊም ሆነ ታሪካዊ በዓላት ላይ አገር አቀፍ አከባበር እንዳይፈፀም የብሔር መሰናክል በመፍጠር ሁሉንም ማኅበረ ፖለቲካ ተዋስኦ የዘር ቅርፅና የተንጋደደ ትርክት በመስጠት፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ድር እንዲበጣጠስና ኢትዮጵያዊ ቅርፁን እንዲያጣ እየተደረገ ነው። 

በቅርቡ በተከበረው 127ኛው የአድዋ ክብረ በዓልም ላይ የታየው መፈራቀቅ የዚሁ የጠባብ ብሔረተኝነት የተንሸዋረረ ታሪክ ትርጓሜ ውጤት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በተመዘገቡት ፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግሎች ውስጥ በቀዳሚነትና በአብነት የሚጠቀሰውን ኢትዮጵያዊያን በኢጣሊያ ኮሎኒያሊስቶች ላይ የተቀዳጁትን ድል ሳይቀር፣ ጦርነቱን ከመሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ማንነት ጋር በማስተሳሰር፣ መታሰቢያ በዓሉም በርሳቸው ስም በተቋቋመው አደባባይ እንዳይከበር ለማድረግ በብልፅግና መንግሥት መሪዎች የተደረገው ብልግና፣ ተንኳሽነትና ትዕቢት በህዝቡ ውስጥ ትልቅ ቅሬታን፣ ትዝብትንና የእምነት መሸርሸርን አስከተሏል። 

በታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘው፣ አንድነታቸውን ያስከበሩና ከዘመነ መሳፍንት ጣጣ የተላቀቁ የአውሮፓና የእስያ ነገሥታት ሃይልን በመጠቀምና ደካማውን በማስገበር ወደ ዘመናዊ ሥልጣኔ እንደተጓዙ ይታወቃል። ይህ በታሪክ እድገት ህግ የግድ መታለፍ የነበረበት የፊውዳሊዝም ሥርዓተ ፍኖት ጥሎት የሄደውን የታሪክ ጠባሳ እየፋቁ፣ የደረቀው ቁስል እንዳዲስ እንዲያመረቅዝ ለማድረግ እንቅልፍ ያጡ፣ ጠባብ ብሔረተኛ ምሁራን ተብዬዎች የማይፈነቅሉት የታሪክ ቋጥኝ የለም። በታሪክ አጋጣሚ የፖለቲካ ሥልጣኑን የተረከበው የኦሮሞ ብልፅግና መንግሥትም ከዚህ ሀገር አፍራሽ የቁልቁለት ጉዞ መላቀቅ አልተቻለውም። “ወቅቱ አሁንና የኛም ነው” በሚሉና “በሕዝብ ብዛታቸው” ሥልጣን ላይ ባለው የኦሮሞ ብልፅግና አንጃ በሚመኩ አክራሪ ጠባብ ብሔረተኛ ምሁራን ተብዬዎች የሚመራው ይህ ፅንፍ፣ በሚያልመው ከአፍንጫ የማይርቅ መታበይ ሦስት ጉዳዮችን ለማሳካት ሲታትር እንመለከታለን። 

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት፣ ኦሮሚፋ የፌዴራል ቋንቋ መሆን አለበትና የመንግሥት ሥልጣንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም በብዛታችን መጠን ይገባናል በማለት የጀመሩት እንቅስቃሴ ከሁሉ አስቀድሞ የአማራ ተወላጆችን ከኦሮሚያ ክልል በማፈናቀልና 

በመጨፍጭፍ እየተከሰተ እንደሆነ እንመለከታለን። ከወለጋ ክፍለ ሀገርና ከሰሜን ሸዋ አካባቢ የተፈናቀሉት ቁጥራቸው ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች፣ ህይወታቸውን ለማቆየት ወደ አጎራባች የአማራ ክልል መሰደዳችው ሳያንስ፣ በነፃነት ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወሩና በተለይም ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ብሔራቸውና ማንነታቸው እየተለየ በመከልከልና እንዲያም ሲል በመታገት ላይ ናቸው። 

በአሁኑ ሰዓት ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ሳይሳቀቁ መኖርም ሆነ መሥራት አስቸጋሪ እየሆነና በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው አማርኛ ተናጋሪ፣ በገዛ ሀገሩ ባይተዋር እንዲሆንና በማንነቱ እንዲሸማቀቅ ከመደረጉም በላይ፣ በጅምላ በሚካሄድበት ጭፍጨፋና ማፈናቀል አበሳውን እየከፈለ ይኖራል። ሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና መንግሥት ህግን ማስከበርና የማህበረሰቡን ደህንነት ማረጋገጥ እያቃተው በመሆኑ፣ ህዝቡ በአመራሩ ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሮ አልቋል። ችግሩ ዛሬ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጭምር እየተከሰተ በከንቲባዋ አንደበት ሳይቀር ዘርን መሠረት ያደረገ የአደባባይ ፍረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛል። አንደበቷ ያልተገራው፣ የእውቀት ማነስ፣ የበታችነት ስሜትና ከዚያም የተወለደ የድንቁርና ግብዝነትና ማናለብኝነት የወጠራት ከንቲባ፣ ወደ ዋና ከተማው ለሥራ ፍለጋና የህግ ጥላ ለማግኘት ከየቦታው በመሸሽ በመምጣት ላይ ያሉትን ዜጎችና በተለይም የአማራ ተወላጆችን እንደ አሸባሪና የሥርዓቱን “ሥልጣነ መንበር ለመነቅነቅ” የሚመጡ ናቸው በማለት ወገንን ከወገን ጋር ሊያጋጭ የሚችል ተንኳሽ ቋንቋ ስትጠቀም እየተሰማ ነው። 

ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው?  

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ የምንታዘባቸው የፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ ለውጦች በሚያስደንቅ ፍጥነት እየተቀያየሩ ነው። የብልፅግና መንግሥት ሲያስመስል ከቆየበት “ኢትዮጵያዊነት”  ተንሸራቶ ወትሮውንም ሲጠረጠር እነበረበት ኦሮሞ ብሔረተኝነት ጓዳ ውስጥ ሲርመጠመጥ ይታያል። በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ የሚታየው ነባር ቅርሶችንና ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ፣ የአድዋ በዓልን አከባበር አስመልክቶ ዳግማዊ ምኒልክን ከአድዋ ድል የመነጠል ሴራ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን የሱሉልታ፣ ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ቃሊቲ ወዘተ… የመሳሰሉ ትናንሽ ከተሞችን ሸገር በሚል አላስፈላጊ ስያሜ አዲስ ከተማ የመፍጠርና አዲስ አበባን የመክበብ አዝማሚያ፣ የኦሮሞ ልዩ ሃይልንና የኦሮሚያ ፓሊስን በከፍተኛ ደረጃ ማሰልጠንና ከመከላከያ ሃይሉ ተገዳዳሪ በሚሆኑበት ደረጃ ማሳደግ፣ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመቀራረብ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ለድርድር ኦፊሴላዊ ጥሪ ማድረግ፣ የተቃዋሚ ድርጅት አባላትን፣ ጋዜጠኞችና፣ የማህበረሰብ አንቂዎችን በአደባባይ ማፈንና ወደ ኦሮሚያ ክልል እየወሰዱ መደብደብና አስፈራርቶ መልቀቅ እንዲሁም አለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ “ፀረ ኦሮሞ” የሚል ታፔላ የተለጠፈባቸውን ታዋቂ ግለሰቦች(ታዴዎስ ታንቱ፣ ታዬ ቦጋለ፣ ጎበዜ ሲሳይ፤ መዐዛ መሃመድ፣ መስከረም አበራ፣ ንጉሤ ብርሃኑ…ወዘተ) ማሰርና ማጉላላት ከሚጠቀሱት ጥቂቶች ክንውኖች መካከል ናቸው። 

ከህወሓት ጋር የነበረው የፖለቲካ ፍጥጫ በእርቅ የሚቋጭበት መንገድ በጓዳ ስምምነት“እየተሳለጠ” ሲሆን፣ ድርጅቱ ከአሸባሪነት እንዲነሳ በፓርላማ ከመፅደቁም በላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደገፈና የፀደቀ የሽግግር መንግሥት ጊዜያዊ ፕሬዜዳንትነት ሥልጣን ለአቶ ጌታቸው ረዳ ተሰጥቷል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ በፓርላማው በተደረገው የሁለት ጎራዎች ክርክር ባንድ በኩል ኢዜማና አብን የአሸባሪነት ፍረጃውን መነሳት ተቃውመው ሲሟገቱ፣ በሌላ በኩል ግን አብላጫው የብልፅግና ፖለቲካ ተከታይ የሆነው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” የፍረጃውን መነሳት ደግፎ አቋም ሲወስድ ታይቷል። በፕሬቶሪያው ስምምነት ሳቢያ መልሶ ነፍስ የዘራው ህወሓትም ቢሆን፣ ትግራይን ለያስተዳድር ያልቻለና የህዝብን ተቀባይነትንም ያጣ የአንድ ቤተሰብ ቡድን ስብስብ  እንደሆነ እያደር በመጋለጥ ላይ ያለ ይገኛል። 

ዛሬ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም አለ ማለት አይቻልም። በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ከተወለዱበት፣ ካደጉበትና ካለሙት አካባቢ በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ሲገደሉ፣ ሲሰደዱና ሲፈናቀሉ እንመለከታለን። የኦሮሚያን ክልል ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙት ዋና ዋና ጎዳናዎች የፀጥታ ስጋት ተደቅኖባቸዋል። “ኦነግ ሸኔ” በመባል በሚታወቀው ታጣቂ ቡድን እየታፈኑ የሚገደሉት፣ እየታገቱ ገንዘብ የሚጠየቅባቸው፣ ማንነታቸው በመታወቂያቸው እየተለየ የአማራ ተወላጅነታቸው ብቻ እንደወንጀል እየተቆጠረባቸው የሚሰቃዩት ዜጋዎች ምሬት ሲታሰብና፣ ህግንና ሥርዓትን የሚያስከብር መንግሥት በሌለበት ወይም ይሁነኝ ብሎ የሕዝብን ምሬት የሚጋብዝበት ሁኔታ ሲታይ፣ ወዴት እየሄድን ነው? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ ተገቢ ይሆናል። 

በሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና መንግሥት ለኦሮሚያ ክልል ህዝብ ጥቅም ብቻ የቆመ በሚመስል ሁኔታና በተለይም የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ይታያል። የኦሮሚያን ባንዲራ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መስቀል፣ የኦሮሚያን ህዝብ መዝሙር በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲዘመር ማስገደድ፣ የኦሮሚያ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያን፣ የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፅህፈት ቤትን፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት በአዲስ አበባ ከተማ መካከል በሰፊ ቦታ ላይ እንዲንጣለሉ ከመፍቀድ ባሻገር ባንኮችን፣ የንግድ ተቋማትን፣ ኢንሹራንስ ድርጅቶችንና ታላላቅ ሆቴሎችን ሳይቀር በክልሉ ስም ማቋቋምና አውራ መንገዶችን በኦሮሚያ ታዋቂ ሰዎች ስም መስየም፣ ከሚጠቀሱ ገሃድ የወረራ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። በቅርቡ በይፋ በመሀል ከተማ፣ ቦሌ ከፍለ ከተማ ውስጥ ሊገነባ መሠረት የተጣለለት የኦሮሚያ ቤተ መንግሥት ግንባታ የዚሁ የማናለብኝ ኦሮሙማ ትርዒት አካል ነው።

የህግ የበላይነት የሚባል እሳቤ ከጠፋ ስንብቷል። ኅብረተሰቡ በዘልማድና አብሮ በመኖር በፈጠረው ልማዳዊ መተሳሰር እርስ በርስ ተከባብሮና ተፈቃቅዶ ከሚኖር በስተቀር፣ መብቴ በህግ ይከበርልኛል፣ ጉልበተኛ እንዳያጠቃኝ፣ ቀማኛ እንዳያስቸግረኝ፣ ባለጊዜ እንዳይጫነኝ፣ በማንነቴ እንዳልሳቀቅና እንዳልመናጭቅ፣ እምነቴና አመለካከቴ ተከብሮ፣ በትውልድ ሀገሬ በፈለግሁበት ተዘዋውሬና ሰርቼ ለመኖር እንድችል፣ አላግባብና ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጭ እንዳልታሰርና እንዳልንገላታ ጥበቃ የሚያደርግልኝ ህግና የህግ አስከባሪ ሥርዓት አለ ብሎ እንዳያምን ተደርጓል።  

ህጉንና የፍትሕ ሥርዓቱን በመዳፋቸው ስር ባደረጉ ባለጊዜዎች ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ ሲታፈኑ፣ ሲደበደቡና በአደባባይ በድንጋይ ተወግረውና ተዘቅዝቀው ሲሰቀሉ፣ የእምነት ቦታዎች ሲወረሩ፣ ሲደፈሩና ሲቃጠሉ የተመለከትንባቸው ያለፉት አምስት ዓመታት በቅርብ ታሪካችን ውስጥ ማነፃፀሪያ የሚገኝላቸው አይደሉም። በቅርቡ በህገ ወጥ ወረራ፣ በግዛት ማስፋፋትና፣ በህግ ማስከበር ስም በተደረገው አስከፊ ጦርነቶችና የርስ በርስ ውጊያዎች በሚሊዩን የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ሲቀጠፍ፣ አካላቸው የጎደሉትንና ከመኖሪያ አካባቢያቸው በግፍ የተፈናቀሉትን፣ የፆታ ድፍረት የተፈፀመባቸውንና የተለያየ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን ህይወት ስናስብ ሀገራችን የምድር ላይ ሲኦል እንደሆነች ተጨማሪ ማጠየቂያ አያሻም። 

“አንድም ሰው አለፍርድ ቤት ትእዛዝ አይታሰርም”፣ “ካሁን በኋላ ሳናጣራ አናስርም”፣”ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩ የግፍና የማሰቃያ ማዕከሎችን ዘግተን የታሪክ ማሳያ ቤተ መዘክር እናደርጋቸዋለን”፣ ሲሉን የነበሩት አፈ ቅቤው የሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በዚያው አንደበታቸው “ካስፈለገ ከደርግም ጊዜ በሚያስንቅ መንገድ ማሰቃየቱን እናውቅበታለን” በማለት በይስሙላው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፊት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በማናለብኝነት ሲፎክሩ፣ አንዱን ብሔር በሌላው ብሔር ላይ የሚያነሳሳ ሀላፊነት የጎደለውን ቱሪናፋ ሲነፉ ተደምጠዋል። ሕዝብን በጅምላ “ኦሮሞ ጠል” ብለው ሲፈርጁና ጦርነትም ሲቆሰቁሱ ተደምጠዋል። ዛሬ በየክልሉ ካሉትና በይፋ ከሚታወቁት እስር ቤቶች በተለይ፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞችና የሰብኣዊ መብት ታጋዮች በምስጢርና ባደባባይም እየታፈኑ የሚታጎሩባቸው፣ የሚገረፉባቸውና እርቃናቸውን ሳይቀር በፎቶና ቪድዮ እየተቀረፁ እንዲሽማቀቁ የሚደረግባቸው የነውርና የግፍ ስውር እስር ቤቶች በየስርቻውና በተለይም በኦሮሚያ ክልል እንደ አሸን ፈልተዋል። አገራችን በሰብኣዊ መብት አያያዝ ደረጃ፣ ቀድሞ ከነበሩት የደርግና የወያኔ ማጎሪያዋች በባሰና አስከፊም በሆነ ሁኔታ ወርዳና ተዋርዳ በዓለም አቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ የመብት ጥሰት የሚከናወንባቸው ሥፍራዎች ከመጨረሻዎቹ ተርታ እንደምትገኝ ዓለም እየመሰከረ ነው። የኖቤል ሽልማት አሽናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ከሚመራው ሕዝብ ሳይቀር ተደብቆ እንደ ሸለ ምጥማጥ የሚሽሎክሎክበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።  

ከዚህ የቁልቁለት ጉዞ እንዴት እንላቀቃለን?  

ይህ ጥያቄ ከባድና ድርብርብ ሲሆን ምላሹም እንደዚሁ ልዩ ትኩረትን፣ ጥሞናንና ማስተዋልን፣ ታሪክን ወደኋላ ሄዶ መመርመርንና ከዚያም በመነሳት በሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ላይ የተመሠረተ ለውጥንና የሕግ የበላይነትን የሚያስረግጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረትን የሚሻ ነው።  

የተደራጀ የሕዝብ ትግል በሌለበት እንደዚህ ዓይነቱ ለውጥ የማይታለም ነው። ዘረኝነትና በሙስና የተዘፈቀ አስተዳደር ዋነኛ መለያው የሆነውን ይህንን የበሰበሰ ሥርዓት ለማስወገድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዳር እስከ ዳር ነቅለው እምቢኝ እስኪሉ መጠበቅ የሚያሻ አይሆንም። በሥልጣን ላይ ያለው የኦሮሞ ብልፅግና መንግሥት፣ ከኢህአዴግ በወረሰውና ዘርን ማዕከል ባደረገው የከፋፍለህ ግዛ ማኪያቪላዊ ስልቱ በመጠቀም የኦሮሞ የበላይነትን የሚያስረግጥ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመጫን የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ ከጠቅላላው ኢትዮጵያዊ ሕብረተሰብ ጋር በገባበት ቅራኔ የተነሳ ይህ ውጥኑ ይሰምርለታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። 

ያለፉት አምስት የመከራና የእልቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ በዘርና በሃይማኖት ዙሪያ የተደረገ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነነት የተደረገበት፣ የእምነት መሠረቱንና አንድ አድርጎ ያቆየውን ታሪኩን ለመናድና ቅርሱን በማጥፋት በመንግሥት የታገዘ የጥፋት ዘመቻ በኢትዮጵያዊው ላይ የታወጀበት፣ ቤተ እምነቶች የተደፈሩበትና የተቃጠሉበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬና መንደር በማንነታቸው ሳቢያ የተፈናቀሉበት፣ ልቅሶና ሞት የዕለት ልምድ የሆነበት፣ ሴቶች የተደፈሩበት፣ ህፃናት የታረዱበት፣ ስዎች በቁመናቸው ተወግረውና ተዘቅዝቀው የተሰቀሉብት የሰቆቃና የብካይ ዘመን ነበር። ይህ ዳርቻው የማይታይ አስከፊ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መውረድ አለበት፤ የኢትዮጵያና የልጆቿ እንባ ታብሶ ለውርደትና ለመከራ የዳረጓት መሪዎች በፍርድ አደባባይ የሚቀርቡበት የፍትህና የእርቅ መድረክ መመቻቸት አለበት። ይህንን ከተራራ የገዘፈ የታሪክ እዳ ለመወጣት እውነተኛ ልጆቿ ሁሉ ባንድነት የሚቆሙበትና የሚመክሩበት ወቅት ዛሬ ነው።  

ይሁንና ይህ ተግዳሮት ያለኅብረት፣ ያለምክክርና ያለድርጅት የሚሞከር አይሆንም። ብሶት ምሬትን ይፈጥራል እንጅ በራሱ ለውጥን አያመጣም። የግፈኞችን ጫና በዘዴና በስልት ተቋቁሞ የአጭርና የመካከለኛ እንዲሁም የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፎ፣ በሽብር፣ በአፈና፣ በግድያና እንዲያም ሲል በማባበል የማይበገር በጠንካራ ዲሲፕሊንና በግልፅ ርዕይ የሚመራ ጠንካራ ድርጅት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ከግፈኛው አስተዳደር የአፈና ክልል ቀጠና ውጭ የሆነው የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አስተዋጽዖ ከፍተኛ ግምት ይሰጠዋል።  ሳይማር ያስተማረውንና ጠበቃና ተገን የሚፈልገውን ደጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከዐቢይ አህመድ አረመኔያዊ ዘረኛ አገዛዝ ለማላቀቅ በሚደረገው ትግል ቀዳሚ ሚና ይኖረዋል። ሆኖም ትግሉ በቀበሮ ባህታዊያን የአገዛዙ ስላዮች እንዳይጠለፍና ጉዳቱም አገር አቀፉን የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዳያደናቅፍ ታስቦ፣ በጥንቃቄና በጠንካራ ዲሲፕሊን መመራት ይጠበቅበታል። 

 በሰላማዊ ትግል ሳቢያ፣ ሰላማዊነት ማለት በገሃድ ወጥቶ መጋፈጥ ብቻ ነው በሚል የተሳሳተ ይትበሃል፣ ለግፈኞች ጥቃት እየተጋለጠ የሚታፈነውና በግፍ የሚገደለው ዜጋ ቁጥር ድካ የለውም። ይህንን አካሄድ በጥንቃቄ መርምሮ የተቀናጀ ህጋዊና ህቡዕ ትግል የሚካሄድበት የአደረጃጀትና የአመራር ስልት መቀየስ ጊዜው የሚጠይቀው ተግዳሮት ነው። መሪዎች ሲታሰሩና ሲሰደዱ የማይቆምና አስተማማኝ ምትክ የሚያዘጋጅ፣ ሕዝቡን ምሽግና መሠረት ያደረገ ፣አገር አቀፍ ሕብረ ብሔር ድርጅት መቋቋምን ወቅቱ የግድ ይላል። 

የምንታገለው ሥርዓት በገንዘብ አቅም፣ በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በፍትሕ ተቋማት ድጋፍ የታገዘ ስለሆነ እንዲሁ በቀላሉ ይወድቃል ብሎ ማሰብ አንድም ከልምድ አለመማር፣ እንዲያም ሲል የፓለቲካ ጨቅላነት ምስቅልቅል (infantile disorder) የሚወልደው አደጋ ነው። አገራቸውን የሚወዱ፣ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ የሆኑና በግፍ መፈናቀልና መገፋት የሰለቻቸው ዜጎች በሙሉ፣ ይህንን አስከፊ ሥርዓት ከጫንቃቸው ላይ አሽቀንጥረው ለመጣል እንዲችሉ በጠንካራ ዲሲፕሊን ላይ የተመሠረተ አስተባባሪና መሪ ድርጅት ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ድርጅት ሲኖር፣ የገዢው ሥርዓት እንደፈለገው እንዳይፈነጭ ልጓም ሊደረገለት ይችላል።  

ኦሮሙማንና የኦሮሞውን ተወላጅ ለያይቶ መመልከቱ ጊዜው የሚጠይቀው ቀዳሚ ተግባር ነው። በማኅበራዊ ሜድያም ሆነ በፅሁፍ በሚካሄዱ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች ላይ ልዩ ጥንቃቄን በማድረግ፣ አገር ወዳዱንና የጥቅም ተጋሪ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል ማቀፍና የትግሉ አካል ለማድረግ ልዩ ጥረት ማድረግ ያሻል። የጅምላ ዘለፋውንና “ንቀት የተሞላበት የሚመስለውን” አላስፈላጊ ትንኮሳ መግታትና አጥብቆ መሞገትም ያሻል። ይህንን የዘነጋ ትግል የኦሮሞ አርበኞችን ትግልና ደማቅ ታሪካዊ አስተዋፅዖ የዘነጋና የካደ ከመሆኑም በላይ፣ ደጉንና፣ ጀግናውንና አገር ወዳዱን የኦሮሞ ሕዝብ አሳልፎ ለጨቋኞችና ዘረኞች በመሣሪያነት እንዲያገለግል መገፋፋት 

ነው። ጥቂት አምባገነን የብልፅግና መሪዎችና ሙሰኛ የጥቅም ተቋዳሾቻቸው የኦሮሞን ሕዝብ እንደማይወክሉ መታወቅ ይኖርበታል።  ትግላችንም ስኬታማ እንዲሆን ይህንን ቁም ነገር በልዩ ትኩረት ልንተገብረውም ይገባል። በምንም ዓይነት ትግላችን ባንድ ወይም በሌላ ብሔር ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ መሆን አይገባውም። እንዲህ መሰሉን አንድን ዘረኛ በሌላ ዘረኛ የመተካት አካሄድና የቆስቋሽ ሰላዮች ተንኮል፣ አጥብቀን ማውገዝና መቃወም ይገባናል። ይህንን ሳንፈፅም ብንቀር ውስብስቡንና መራራውን ሕዝባዊ ትግል አደጋ ላይ እንጥላለን። 

ዋናውን ጠላት ፋታ በሚሰጥ መንገድ በአገር ወዳድ ድርጅቶችና ግለሰቦች መካካል የሚደረገውን የጎን ብሽሽቅና ሽኩቻ ገትቶ፣ በሥልጣን ላይ የሚገኘውን የብልፅግና አመራርን ዒላማ ያደረገና የተቀናጀ የፖለቲካና የፕሮፓጋንዳ ሥራ መሥራት የግድ ይሆናል።  

የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ከሕዝቡ ልጆች የተውጣጣና ብዙ መስዋዕትነትን በመክፈል የወያኔን ኢትዮጵያን የማፍረስ አደጋ የታገለ ሃይል መሆኑን ግንዛቤ በማስገባት፣ በጥንቃቄና በዘዴ እየቀረቡ የሕዝባዊ ትግሉ አካል እንዲሆን መጎትጎት፣ ማሳመንና ማደራጀት ያስፈልጋል፤ ይቻላልም። በኅብረተሰቡ አባላት መካከል ያለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልዩነት በመከላከያው ሠራዊትም ውስጥ ስለሚንፀባረቅ፣ ያንን በመከላከያው ጥቂትና “ምርጥ ተጠቃሚ” መሪዎችና በተራው ወታደር መካከል የሚታዩትን የአደባባይ ልዩነቶች መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥራ መሠራትም ይኖርበታል።  

አገራችን ኢትዮጵያ ከተነከረችበት ታይቶ የማይታወቅ የታሪክ አረንቋ እንድትወጣና ፣እንደሕዝብ ባንድነት፣ እንደሃገር በፅናት እንድንቆምና ይህንን ወቀታዊ ተግዳሮት ተቋቁመንም ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ወንድማማችነት ወደሚኖርባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድንሸጋገር ሁላችንም ባንድነት መነሳት ይገባናል። በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካካል በዘር ላይ የተመሠረተ ክፍፍልና የጥላቻ ስሜት እንዲፈጠር ሳይታክት የሚሠራውንና የወያኔ ኢህአዴግ ተቀጥያ የሆነውን የባለተረኞች አገዛዝ፣ አከርካሪውን መስበር እንዲቻል የጠንካራ ኅብረ ብሔር ድርጅት መገኘትን የግድ ይላል።  

በሀገራችን ምድር እንደልብ ተዘዋውረን፣ የዘር፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበን በፈለገን ቦታ ሠርተን መኖር እንድንችል፣ ከዚህ የዘረኞች የብልፅግና ሥርዓት መላቀቅ ይኖርብናል። እስላምና ክርስቲያኑ ለዘመናት ተዛምዶ፣ ተስማምቶና ተከባብሮ የኖረባትን አገራችንን ክብርና ሞገስ ቀድሞ ወደነበረበት የታሪክ ማማ ለመመለስ ነቅተን መታገል ይኖርብናል። ሴቶቻችን ለፔትሮ ዶላር የዐረብ ህብታሞች ግርድና የማይዳረጉባትና ባገራቸው ተከብረውና ታፍረው እየሠሩ የሚኖርባት ሀገር ያሰፈልጋቸዋል። ለዘመናት የቆዩ ማኅበረሰባዊ ትስስሮችን እየበጣጠሰ፣ በጉርብትናና አብሮ በመኖር የተመሠረቱ እድሮችን እያፈረሰ፣ ቅርሶችን እያጠፋና በጉቦ በታወረ አእምሮው ኢትዮጵያችንን ሊያሳጣን በመታተር ላይ የሚገኘውን የብልፅግና የጥፋት መንጋ ልናስቆመው የምንችለው በተደራጀ ህዝባዊ ትግል ብቻ ነው። ተስፋችንንና ዓላማችንን ለስግብግብና ከሃዲ፣ ቃል  አባይ መሪዎች አሳልፈን የምንሰጥበት ዘመን አብቅቷል።  

ለጠላት ጥቃት የማይመችና የማይበገር፣ የሕዝብን አመኔታና መከታን የተቀዳጀ፣ ከተደቀነብን የሀገር መፍረስና መበታታን አደጋ ሊታደገን የሚችል፣ ሕዝቡን መሠረት አድርጎ፣ የሕዝብን ሃይልና የፈጠራ አቅም ተማምኖ፣ የሀገራቸውንና የህዝባቸውን ጥቅም ባሰቀደሙ ምሁራን ታግዞ፣ ትግላችንን የሚያስተባብር መሪ ድርጅት በማቋቋም የተበታተነውን አቅማችንን ሰብስበንና ከጎን ሽኩቻና እንካ ስላንቲያ ታቅበን፣ እንደሃገር ለመቆየት፣ እንደሕዝብ ለመኖርና የታሪክ ቅብብሎሽ በኛ ትውልድ ዘመን እንዳይቋረጥ ለማድረግ የታሪክና የዜግነት ግዴታ ወድቆብናል። 

እንቀራረብ! እንወያይ! ሃይላችንን እናስተባብር! ህጋዊውንና ኅቡዑን  ትግላችንን የሚያስተባብር መሪ ድርጅት ለመፍጠር እንታገል! የነቃና  የተደራጀ የሕዝብ ትግል ያቸንፋል!  

ይኽንን ፅሁፍ ካነበባችሁ በኋላ አስተያየታችሁን በሚከተለው አድራሻ ብትልኩልን ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው። Jijiga-Hargesa@proton.me

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here