spot_img
Wednesday, October 4, 2023
Homeነፃ አስተያየትየፖለቲካ ማንነትና የብዙኀን መንግሥት በኢትዮጵያ (ክፍል ፩)  

የፖለቲካ ማንነትና የብዙኀን መንግሥት በኢትዮጵያ (ክፍል ፩)  

advertisement
ከ “ፊፍቲ ሸድስ ኦፍ ፈደራሊስም” ድረ ገጽ የተወሰደ

አንዱ ዓለም ተፈራ 

ማክሰኞ፣ ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም.  

በአገራችን በኢትዮጵያ ያሳለፍነውን የሃምሳ ዓመታት የፖለቲካ ሂደት ዞረን ብንመለከት፤ ተጨባጩ እውነታ ብዙ የተመሰቃቀሉ ለውጦች እንደተስተዋሉበት እንረዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ኑሮ አንገፈገፈኝ ብሎ ከተነሳበት ከየካቲት አስራ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት ዓመተ ምህረት ጀምሮ፤ የተለያዩ የነፃ አውጪ ግንባሮች በየቦታው ተፈጥረዋል። መሪ ልሁን ባዮች በብዛት የፖለቲካ መድረኩን አጥለቅልቀውታል። ረሃብ የአገሪቱን አንዳንድ ክፍሎች እስካሁንም ወጥሮ ይዟል። እጅግ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለስደት ተዳረገዋል። በጎረቤት አገራትና በሩቅም ተበትነዋል። ከገጠር ወደ ከተማ ብዙ ሰው ጎርፏል። የሕዝቡ ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ አድጓል። ብዙ ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ ቢሆኑም፤ የትምህርቱ ጥራት ከመውደቁ ሌላ፤ ለተመራቂዎች ሥራ አልተፈጠረላቸውም። ከመቼውም ጊዜ በላይ የቴሌቪዝን፣ የሬዲዮ እና የስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር አይሏል። እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ሰዎች በልፅገው፤ የነሱ ሀብት እጅግ እየበዛ ሲሄድ፤ በአንጻሩ የድሃው ቁጥር እየጨመረና ድህነቱ እየከፋ ሄዷል። የአብዛኛው ሰው ኑሮ፤ ከእጅ ወደ አፍ፤ አለያም ጦም ማደር ሆኗል። በተመፅዋችነት የሚተዳደረው የወገናችን ቁጥር ወደላይ ጉኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘይት ዋጋ መናር፤ በሸቀጣ ሸቀጥና ዝውውሩ ላይ የዋጋ ክምር በማስከተሉ፤ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ ሄዷል። የውጪ መንግሥታትና የውጪ ኃይሎች በአገራችን የፖለቲካ ሂደት፤ የጣልቃ ገብነት ድርሻቸው እያየለ ሄዷል። ይህ በድምሩ፤ በሕዝቡ ግንዛቤና የኑሮ ሀቅ ላይ ያስከተለው ብዙ ለውጥ አለ። ይሄ ሁሉ ሲሆን፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየተፈራረቁ ያስተዳደሩትና አሁን በፌዴራል የተዋቀረው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በምን መርኅ ነበር አገሪቱን የሚያስተዳድሯት? በዚህ ሁሉ ሂደትስ የመንግሥት ሚናው ምንድን ነበር? እንዴት ነበር አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የቆዩት? በዚህ ጊዜ ምንድን ይሠሩ ነበር? አሁን ላለንበት ተጨባጭ ሀቅ ምን ያህል ባለቤትነት አላቸው። የመንግሥቱና የሕዝቡስ ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? በዚህ ጽሑፍ ይሄን ትኩረት ሠጥተን እንመለከታለን። 

የመንግሥት ምንነትና ተግባር የሚገለጠው፤ በአገሪቱ በተቀመጠው ሕገ-መንግሥት፣ ይህ አካል በሚያራምደው የአስተዳደር መመሪያ፣ በተግባር በሚያውለው ሕግና ደንብን የማስከበር ድርጊቱ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕገ-መንግሥት፤ በመጀመሪያ፤ አረመኔው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን፤ በራሱ ፍላጎት ዙሪያ የስቀመጠውና ከአገራችን ጊዜያዊ ሀቅ ጋር ያልተዛመደ ስርዓትን ያወጀ ነበር። የደርግ መንግሥት በወደቀበት ጊዜ፤ ለወቅቱ የፖለቲካ ግኝት፤ በወቅቱ በትውልድ ማንነት (በጎሣ) ፖለቲካ ተደራጅቶ ሥልጣን የወሰደው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ለራሱ የሚፈልገውን ግብ ያስገኝልኛል ብሎ ባስበው መሠረት የጻፈው ነው። ይህ ሕገ-መንግሥት አገራዊ ሳይሆን፤ የገዢውን ጠባብ ወገን በሚጠቅም ሁኔታ የተሰናዳና፤ በዝግጅቱ ወቅት፤ የአማራውን ወገን ለውክልና እንኳን ያልጋበዘ ነበር። በወፍ በረር የዚህን የትውልድ ማንነት ፖለቲካ መሠረት ያደረገ ሕገ-መንግሥት እንመርምር። መሠረቱ፤ አገሪቱ የኢትዮጵያዊያን ሳትሆን፤ በትውልድ ማንነት ላይ ተመርኩዘው የተደራጁ ክፍሎች ባለቤትነት ያላቸው ስብስቦች፤ ንብረት ናት! ይላል። ለሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች፤ ተጠያቂው አማራ ነው ይላል። በቀጥታ ለመጥቀስ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መርኀ-ግብር መግቢያ፤ “ . . . የአማራን የበላይነት በመገርሰስ” ይልና፤ “በአማራው መቃብር ላይ . . . ” ይላል። እንግዲህ በሥልጣን ላይ የወጣው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ በኢትዮጵያ የገዢ መደብ ሳይሆን፤ “አማራዎች በአንድነት የበላይ ሆነው ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ሲገዙ የነበረበት ሀቅ ነግሦ ነበር!” ብሎ አሰራጭቷል። ይህ ደግሞ፤ ደርግን የሚመለከትና፤ ደርግና የአማራ ነው ብሎ የፈረጀ ነው። ተከታዩ በሙሉ የዚህ ትርክት ውልድ ነው። እናም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ የትውልድ ማንነትን የፖለቲካ ማንነት ይዘት ሠጥቶ ቀጠለ። 

በኢትዮጵያ፤ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ አንኳር የሆኑ የመብት ጥሰቶችን አካሂዷል። በኢትዮጵያ፤ ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን የሉም። እንግዲህ በዚህ ከሄድን፤ እያንዳንዱን ዜጋ፤ ቁጥርና ድምር ተደርጎ ስለተቀመጠ፤ የግለሰቦች መብት ተሽሯል። ግለሰቦች ቁጥር ናቸው። በአገር ደረጃ፤ የቁጥር ሂሳብ መቀመሪያ ሆነው፤ የፖለቲካ ክንውኑን በመወሰን በኩል፤ መሳሪያ ተደርገው ተቀምጠዋል። ይህ እንግዲህ ግለሰቦች፤ በግል አመለካከታቸውና በግል ፍላጎታቸው ሳይሆን፤ በትውልድ ማንነታቸው፤ የፖለቲካ አመለካከታቸውና ተሳትፏቸው ተወሰነ ማለት ነው። ይህ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ፤ ግለሰቦችን ሲወለዱ ጀምሮ እንደ እጅና እግር ሊለውጡት የማይችሉት ዕሴት ሠጥቶ፤ ሰዎችን ተገዢ እንጂ ባለቤትነት የሌላቸው አደረጋቸው። እናም የየክልሉ ልሂቃንና ሥልጣን ጥመኞች፤ ዕቃ አደረጋቸው። አንድ ግለሰብ የኦሮሞ ተወላጅ፤ ኦሮሞ ክልል ብቻና፤ በኦሮምኛ ብቻ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርግ፤ ትግሬውም እንዲሁ፤ በትግራይና በትግርኛ ብቻ ተሳትፎውን አደረገ። እዚህ ላይ የዴሞክራሲ አሰራር ቦታው ተሻረ። ግለሰብ፤ የሚያስብ፣ ምኞት ያለው፣ ሃሳቡን በፈለገው ጊዜ ሊቀይር የሚችል አካል ሳይሆን፣ ግዑዝ እንደ ዕቃ ተቆጣሪ ሆነ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሳይሆን፤ በትውልዱ ፖለቲካ ብቻ እንዲሳተፍ ተደረገ። በፌዴራል ደረጃ ለሚደረገው ክንውን፤ የትውልድ ማንነቱን ተሸክመው የሄዱት ወከሉት። ቀጥሎ ደግሞ፤ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ፤ የ“እኛና” የ“እነሱ”  ክፍፍልን ፈጠረ። ይህ የአገር አንድነቱን ከመሸርሸሩ በላይ፤ ወደ የማይመለሱበት የልዩነት መንገድ እንዲያመራቸው ገፋቸው። እናም ይሄ አገር አፍራሽ እርምጃው፤ አሁን ላለንበት እውነታ ዳረገን። አሁን ያለንበት እውነታ፤ ከኔ አካባቢ አትኖርም እየተባለ፤ በተለይ አማራው፤ የሚባረርበት፣ ንብረቱ የሚዘረፍበትና፣ ሕይወቱ በኢሰብዓዊ መንገድ የሚቀጠፍበት ነው። እንዴት ለዚህ በቃን? በሕዝቡ ፍላጎት ነው ወይንስ በፖለቲካ ባለሥልጣኖች የሰላ ጥረት?

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,733FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here