
አንዱ ዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም. (6/22/23)
(በክፍል አንድ መነሻ የሆነውን የርዕሱን መንደርደሪያ አስቀምጬ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደሩን ሂደት አስፍሬያለሁ። ይህ ከዚያ በቀጥታ የሚቀጥል ነው።)
የማንነት መሠረቱ የግለሰቡ ሕይወት ነው። የግለሰቡ ሕይወት ለግለሰብ ማንነቱ ማጠንጠኛ ነው። ከዚያ ቀጥሎ፤ ከሌሎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት፤ ለሌሎች ተከታታይ ማንነቶቹ መንገድ ይከፍታል። በርግጥ ከትውልድ ያገኘው ማንነት፤ የሰውነትን ቅርጽ፣ የቆዳን ቀለም፣ የፀጉርን ጥንካሬ ይገልጽ እንደሆነ እንጂ፤ የትኛውን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲይዝ ወይንም የትኛውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲቀላቀል፣ ምን እንደሚያስብ፣ ምን እንደሚጠላ፣ ምን የሙያ መስክ እንደሚከተል ወሳኝ አይደለም። ያ በዕድገታችን የምንገነባው የየራሳችን የግል ጉዳይ ነው። በርግጥ ዝንባሌን የሚገፉ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉበት መንገድ ይኖራል፤ ወሳኝነት ግን የላቸውም። አባትየው አጥባቂ ወገኛ ሆኖ፤ ልጅየው ነውጠኛ ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ አመለካከት ከናት ወደልጅ በእትብት አይተላለፍም። የአንዲት ግለሰብ ተመክሮ፤ ግለሰቧ ለምትከተለው የግለሰብ የፖለቲካ አመለካከት አስተዋፅዖ ያደርጋል። ይህ ግን የግለሰቧ ጉዳይ ነው። ግለሰቧ በፈለገችው ጊዜ ልትለውጠው የምትችለው ጉዳይ ነው። ማንም ሊሠጥና ሊነጥቅ የሚችለው የፖለቲካ ማንነት አይደለም። ኢትዮጵያዊት የትም ትኑር የት፤ ኢትዮጵያዊት ነች። በኢትዮጵያዊነቷ፤ በአገሯም ሆነ በውጪ አገር መብቷ የተከበረ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ፤ የላንዳች ጥያቄ ካንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ የመዘዋወር መብቷ የተጠበቀ ነው። በፈቃዷ ይሄን ትታ የሌላ ዜጋ ልትወስድ ትችላለች። ያ የርሷ ምርጫ ነው።
አዎን፤ የትውልድ ማንነት የአንድ ግለሰብ መገለጫ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ መገለጫ ለግለሰቡ የፖለቲካ ማንነት ሆኖ አያገለግልም። ፖለቲካ የተፈጥሮ ጉዳይ አይደለም። ፖለቲካ ከተወለዱ በኋላ የሚሳተፉበት የኅብረተሰብ ክንውን ነው። ሃይማኖትም፣ ሙያም ሌሎችም እንዲሁ። በሙያ መስክ፤ ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ወታደር፣ ነገዴ ሆኖ መኖር ይቻላል። በሃይማኖት በኩል የክርስትና ወይንም የእስልምና ተከታይ መሆን ይቻላል። ሃይማኖት አያስፈልገኝም ብሎ መኖርም ይቻላል። እኒህ ሁሉ ግን፤ በአገር ውስጥ ለሚደረግ የፖለቲካ ተሳትፎ፤ መመዘኛ አይሆኑም። የአገሩ ተወላጅ መሆንና ፈቃደኛ ሆኖ በፖለቲካ መድረኩ መርጦ መሳተፍ ነው የፖለቲካ ማንነትን የሚያስይዘው። የመኖሪያ ቦታም፤ የፖለቲካ ማንነት አይሆንም። የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ እንግሊዝ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ፤ ለንደን በመኖሩ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንጂ፤ በለንደን ፖለቲካ ይሳተፋል ማለት አይደለም። እናም ይሄን ሀቅ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ ይስታል። የፖለቲካ ማንነት በፈቃደኝነት የሚወሰድ እንጂ፤ በትውልድ ወይንም እንደሽልማት የሚሠጥና የሚነጠቅ ማንነት አይደለም። የአንድ ፓርቲ አባል ለመሆን፤ ያ ፓርቲ ያስቀመጠውን መስፈርት አሟልቶ መገኘት ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ያ መስፈርት፤ በአንድ አገር ላለ ማንኛውም ዜጋ ክፍት ሆኖ፤ ማንንም በትውልዱ ወይንም በሌላ ምክንያት የማያገልል መሆን አለበት። አለበለዚያ፤ ያ ፓርቲ በዚያች አገር የፖለቲካ ሂደት ተካፋይ ሊሆን አይገባውም። ምክንያቱም ዜጎችን አግላይ በመሆኑ። በርግጥ ይሄ በትክክለኛው የዴሞክራሲያዊ አሰራር የሄድን እንደሆነ ነው። እንግዲህ መነሻችን ይሄ ሆኖ፤ ሕገ-መንግሥቱ በዚያ መንገድ አገራችንን የኢትዮጵያዊያን ሳይሆን፤ በትውልድ ማንነት የተደረገ የፖለቲካ ስብስብ ናት ብሎ ካስቀመጠ፣ ይሄን እንዲተገብር መንግሥትን ኃላፊነት ከሠጠ፣ ለዚህ እንዲረዳ ክልሎችን ካዋቀረ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የመንግሥቱ ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? እንመርምር፤
የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አዲስ አበባ ሲገባ፤ የፖለቲካ መሠረት የሚሆነው ሕዝብ፣ ወይንም አገር አቀፍ ድርጅታዊ ጥንካሬ አልነበረውም። እናም አገሪቱን በመከፋፈልና ሊቀናቀኑት የሚችሉትን በማዳከም ብቻ፤ ሊገዛ እንደሚችል ተረዳ። ለዚህ ሊረዳው የሚችለው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎና ለያይቶ ማደራጀት ነበር። በርግጥ ከመሠረቱም የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ነውና፤ አንድም ትግራይን ከኢትዮጵያ መገንጠል፤ አለያም ደካማ ኢትዮጵያን ፈጥሮ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የበላይ የሆነበትን አስተዳደር በአገሪቱ መጫን ነበር። ያደረገውም ይሄንኑ የኋለኛውን ነበር። ሁላችን እንደምናውቀው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ኢትዮጵያን የገዛው፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሆኖ ነው። ትግራይን ከማን ነው ነፃ የሚያወጣ? ከኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ የትግራይ ጠላት ናት ብሎ፤ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የተመሠረተ ድርጅት ነው! ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የኢትዮጵያ ጠላት ነው! ይህ አያጠያይቅም። ማንም ነፃ አውጪ ድርጅት፤ የሕልውናው ትርጉም፤ የኢትዮጵያ ጠላትነት ነው። በኋላም እንዳየነው፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ካዲስ አበባ ሸሽቶ መቀለ ገብቶ፤ ያንኑ የመገንጠልና የራሱን መንግሥት በትግራይ መመሥረቱ ላይ ነበር የተሰማራው። በተገንጣይነቱ ቆሞ፤ የበላይ ሆኖ መግዛቱን እንዲያስተካክልለት፤ “ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያዊያን ሳትሆን፤ በትውልድ ማንነት ፖለቲካ የተደራጁ ስብስቦች ባለቤት የሆኑባት ናት!” የሚል ሕገ-መንግሥት ጻፈ። ይሄ ሕገ-መንግሥት፤ በፈለጉ ጊዜ ኢትዮጵያን ጥለ የሚሄዱበትና የራሳቸውን መንግሥት የሚመሠርቱበት ክልልን ፈጠረላቸው። ክልሎቹ የአስተዳደር ክፍፍሎች ብቻ ሳይሆኑ፤ የትውልድ ማንነት ፖለቲካ ማቅኛ፤ ለም መሬቶችም ሆኑ። እኒህ ለም መሬቶች የየራሳቸው ቋንቋ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ የትምህርትና ሕክምና ዘርፍ ያላቸው አስተዳደሮች ሆኑ። አልፎ ተርፎም የየራሳቸው ልዩ ኃይሎች እንዲኖራቸው ተደረገ። ይህ ሁሉ ሌሎችን እንዳሻቸው እንዲሠሩ ሲፈቅድ፤ አማራው በዚህ እንዲሠራ አልተፈቀደለትም። ይልቁንም አማራውን እንዲቆጣጠሩ ከገዢዎቹ ትራፊ ተወርውሮላቸው የተመደቡት የአማራው ገዢዎች፤ ለክልሉ የተመደበውን ገንዘብ፤ ክልሉን ሳያለሙ መልሰው ለጌቶቻቸው መሥጠት፣ አማራውን ማሸማቀቅና ወንጀለኛ ነው የሚለውን ትርክት ማስተማር ያዙ። ይሄ ግን ለትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርም ሆነ ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር በቂ አልሆነላቸውም። የአማራ ክልል መሪዎችን እንደፈለግን እናነሳለን እንጥላለን በማለት፤ እነ አምባቸውን፣ ምግባሩን፣ አሳምነውን ገድለው፤ ሌሎችን ተኩ። ይሄ ሁሉ በፌዴራል ብልፅግና ስም ይደረግ እንጂ፤ በአብይ አሕመድና ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ብልፅግና ነው የተከናወነው። የአማራ ብልፅግና አገልጋይ መሳሪያ ነው።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ