spot_img
Saturday, April 13, 2024
Homeነፃ አስተያየት“አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” የኢ-ዲሞክራሲና ጽንፈኛ ኃይሎች ቅዠት፤ (ክፍል ሁለት)

“አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” የኢ-ዲሞክራሲና ጽንፈኛ ኃይሎች ቅዠት፤ (ክፍል ሁለት)

 ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ 


 ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ   
ሰኔ 24 2015

አመጽ ሁሉ መመራት ያለበት ለበቀል ባለህ ጥማት ሳይሆን፤ ለፍትሕ ባለህ ከፍተኛ ፍላጎት መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው” 

              ደራሲ አብሂጂት ናስካር


1. ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ።


በቅርብ ዓመታት ለምዕራባውያን መንግሥታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያሻማ ሁኔታ ያስተላለፈው መልዕክት “ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚል ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ መብትና ድምጽ በረገጠ እቡይ መንፈስ፤ ዶ/ር ዮናስና አጋሮቻቸው፤ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ፤ ደጅ ጥናት ላይ ናቸው። ይህ ዓይነት እኩይ መንንፈስ፤ እንኳን ትላንት ወደ ፖለቲካው መድረክ አንገታቸውን ብቅ ላደረጉ ይቅርና፤ ከ40 ዓመታታ በላይ በምዕራባውያን ጉያ ውስጥ የነበረውና የኢትዮጵያን ጥቅም ለምዕራባውያን አሳልፎ ለሸጠው ለሕወሃትም አልበጀም። ገራሚው ነገር፤ ከዓመት ተኩል በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር ታመው የነበሩት ዮናስ ብሩ፤ “ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ መጣል የእርስ በእርስ ጦርነት ያስነሳል“ ሲሉን እንዳልነበር፤ ዛሬ ደግሞ ምሁራዊ በሆነ ሸፍጣቸው እና ከበርካታ እውቅ ኢኮኖሚስቶች እሳቤ ውጭ፤ “ኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ማእቀብ ቢጣል ደሃውን አይጎዳም” ይሉናል። ይህን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ስዓት ሕዝባችንን በርሃብ ለመቅጣት ተግተው በሚሰሩ ጽንፈኞች ላይ በረዶ ያፈሰሰ ውሳኔ ወስኗል፤ ይህም ኢትዮጵያ ላይ የጣለውን አንዳንድ ማዕቀብ ለማንሳት መወሰኑ ነው።   

ዶ/ር ዮናስ ብሩ MLI ለተባለ ኢንስቲትዩት ባቀረቡት “Why the US needs to reset its approach to the conflict in Ethiopia” በሚለው ጽሁፋቸው፤ ዶ/ር አብይና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያለውና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መሆኑን በመግለጽ የቀድሞው የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩትን ጄፍሪ ፌልትማንን በመጥቀስ፤ እሜሪካን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የምታደርገውን ማስፈራራት እንድታቆም ጠይቀዋል። ከዚህም አልፈው ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ቢጣል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊነሳ እንደሚችልና፤ ኢትዮጵያ ወደ ያልተጠበቀ ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ይነግሩናል። ከዚህ በተጨማሪም “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማግለልም ሆነ ለመለወጥ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሚያጣጥልና የአፍሪካ አንድነትን ለወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ምንም ምህረት የማያደርግ መሆንኑ የሚገልጽ ቻርተሩን የሚጥስ ይሆናል” ይሉናል። ይህ ጽሁፍ በዶር ዮናስ የተፃፈው በኅዳር 19፣ 2021 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከዛሬ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት ነው።

 ዛሬ ደግሞ፤ “በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ አለም አቀፍ ማዕቀብ ለድሆች ጥሩ ነው”፤ በሚል በቦርከና ድኅረ ገጽ ላይ በታተመው ጽሁፋቸው፤ ከእውቅ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚስቶች እሳቤ ጋር የሚፃረረ ነገር ነግረውናል። በዚህ ጽሁፋቸው፤ ምሁራዊ ሸፍጣቸውን ለመደበቅ፤ እኔ የምሟገተለት ማዕቀብ፤ ሰብዓዊ እርዳታን አይጨምርም ይሉናል። በተቃራኒው፤ ዶ/ር ዲለን ኦድሪስኮል የተባሉ የማንችስተር ዩኒቨርስቲ ፕሮፌስርና ተመራማሪ. የ ዶ/ር በርት ቮጋል፣ የዶ/ር ሮሲን ሪድ እና የዶ/ር ጆናታን ፊሸር ኤክስፕርትነትን ያካተተውን “ማዕቀብ በድህነትና በኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለው ተጽእኖ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፤ ማዕቀብ፤ የሚጎዳው በድህነት ወለል ላይ ያሉ ዜጎችን እንጂ፤ ማንኛውንም የአገዛዝ ሹም ሆነ በተሻለ የኢክኖሚ ደረጃ ላይ ያለ ዜጋን እንዳልሆነ፤ እንዲሁም ምዕራባውያን በተለያዩ መንግስታት ላይ በሚጥሉት ጫና ተጎጂው ሕዝብ እንጂ የመንግሥት አካላት እንዳልሆኑ፤ በሱዳን፤ በኢራቅ፤ በማይማር ላይ የተደረጉ ማዕቀቦችንና ውጤታቸውን በመጥቀስ፤ ማዕቀብ በሕዝብ ላይ የሚፈጥረውን ቀውስ ይነግሩናል። በተለይ ደግሞ በመንግሥታት ላይ በሚደረግ ማዕቀብ፤ ኅፃናትና ሴቶች እንዴት የማዕቀቡ ሰለባ እንደሚሆኑና ተቀዳሚ ተጎጂዎች እንደሚሆኑ ይነግሩናል። ዶ/ር ዮናስ ድሃው አይጎዳም የሚለው የሃሰት ትርከታቸውን ለመሸፈን፤ “እኔ ያልኩት ማእቀብ የሰብዓዊ እርዳታን አይጨምርም” ይሉናል። በሌላ አነጋገር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምጽዋት እንዲኖርና እራሱን እንዳይችል ለምዕራባውያን ተንበርካኪ እንድንሆን የሚስብክ እኩይ እሳቤ ነው።ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማዕቀብ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስነሳል ሲሉ ከዓመት በፊት የፃፉት ሰው፤ ዛሬ፤ “ማዕቀብ ድሃውን አይጎዳም” ብለው ሲጽፉ ሃፍረት የሚባል ነገር እንኳን አይሰማቸውም። ይህ እሳቤያቸው አሜሪካ AGOA ላይ በጣለችው ማዕቀብ፤ ዛሬ በሥራ አጥነትና በችግር የሚንገላቱትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕመም ላይ የተሳለቀ ዕቡይ መንፈስ የወለደው እሳቤ ነው። 

እኝህ ሰው፤ በኢትዮጵያ ላይ ባወጁት የጥፋት አዋጅ “አለም አቀፍ ጫና ብቸኛው አማራጭ ነው” በሚል ያሳተሙት ጽሁፋቸው፤ ጽሁፍ፤ ዶ/ር ዓብይን ለመስደብ የተጠቀሙበት ከአርዕስቱ የወጣ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖትና በብሔር እንዲገዳደሉ የሞት ድግስ የደገስ መልዕክት ነው። ዶ/ር ዮናስ በዚህ ጽሁፋቸው እንዲህ ይሉናል። “ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት በኋላ አለም አቀፉ ማህበረስብ ‘’አይደገምም ‘’ ሲል ቃል ገብቶ ነበር። የሩዋንዳ የዘር ፍጅት በፍጥነት የተፈፀመ ነው ። የኦሮሙማ የዘር ፍጅት ቀስ በቀስ እየተብላላ ነው። አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ የመግባት የሞራል ሃላፊነት አለበት ። ቀደም ብለው በተጠቀሱት ምክንያቶች አለም አቀፍ ማህበረሰቡ የአፍሪካን ቀንድ መረጋጋት የሚፈልግበት ፖለቲካዊ ና ከባቢያዊ ፍላጎቶች አሉት ። እየተባባሰ የመጣውን የኢኮኖሚ ቀውስ ና የኦሮሙማ የሃይማኖት የዘር ፍጅት የሚያስከትል ጦርነት ለማስቆም የሚያስችሉ አዋጭ እርምጃዎችን ከማየታችን በፊት ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን መረዳት ይኖርብናል ። የመጀመሪያው መሰረታዊ ነጥብ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኦሮሙማ አስተሳሰብ መሪዎች ፍላጎታቸውን ለማሳካት ያላቸውን ኃይል ሁሉ እየተጠቀሙ መሆኑ ነው። ለኢኮኖሚው መውደቅ ና እየቀረበ ለመጣው የኦሮሙማ ዘር ፍጅት ምልክቶች በፍጥነት እየታዩ ነው። ሁለተኛው ኢትዮጽያውያን በሁለት ግንባር በኢኮኖሚው ና ሃይማኖት ንቅናቄ ማድረግ ይገባቸዋል የሃይማኖቱ ያለፖለቲካ አክቲቪስቶች ጣልቃ ገብነት በሃይማኖት ተቋማት ብቻ መመራት አለበት የኢኮኖሚው ንቅናቄ ከሃይማኖቱ ተለይቶ መደረግ አለበት አለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ና ሃይማኖታዊ ንቅናቄዎች አትኩሮት እንደሚስቡ ማስታወስ ያሻል።” ይሉናል። 

ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮኻል የሚሉት፤ እንዲህ ዓይነቱን ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከሩቅ ሆነው አመጽ እያስነሱና ሕዝብን በሕዝብ ላይ እያነሳሱ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም” የሚል ፕሮፖጋንዳቸውን ያሰራጫሉ። የኢትዮጵያን ሕዝብ በሃሰት ትርከት ኮርኩረው፤ በምናባቸው የሚያዩትን “የዘር ጭፍጨፋ” ለዓለም እንዲያሳውቅ የሚሰበክ ስብከት መሆኑ ነው። የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ፤ ዴቪድ ሺን፤ ከሁለት አመታት ገደማ በፊት፤ ለአልጀዚራ እንደገለፁት፤ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ስለሚደረግው ነገር የማያውቀው ነገር የለም፤ ለዚህም ነው ሰላዮች ያሉት ብለውናል። ዶር ዮናስ ይህ ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም፤ ይህ የሃሰት ትርከታቸው የማንን ቀልብ ለመሳብ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፤ ጽንፈኛውን ኃይል በስሬ ያሰባስብልኛል ብለው እንዳመኑበት ጥርጥር የለኝም። የሳቸውን የበቀል ጥም ለማርካት፤ ኅጻናትን ወደ መሰውያው እሳት ሲጎትቱ ግን ፀፀት የሚባል ነገር እይሰማቸውም። በብሔርና ብሔር በሃይማኖትና በሃይማኖት መካከል ግጭት የሚሰብክ ሰው፤ ለኢትዮጵያ ጤናማ እሳቤ አለው ብሎ መቀበልም ያዳግታል። እነሱ ሰላም እንዲደፈርስ ጠንክረው እይሰሩ፤ ሰላም ደፍርሷል ሲሉ መስማት ገራሚ ብቻ ሳይሆን፤ የጭካኔያቸውን ጥግ ያሳያል። እርግጠኛ ነኝ፤ ዶ/ር ዮናስ ከምቹ ወንበራቸው ተነስተው “የሚሰብኩትን ትግል” በቦታው ተገኝተው አይታገሉም።  

ደግነቱ፤ የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች እኩይና እቡይ መልዕክት መሬት ላይ ካለው ጭብጥ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእነዚህን ጽንፈኛና አደገኛ ሰዎች የሃሰት ትርከት የሚቀበልበት ምንም ምክንያት የለውም። ትላንት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መከበርና መጠበቅ አለበት ብለው የሰበኩን ዮናስ ብሩ፤ ዛሬ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ ከሚንፈራገጡት የብዕር ጦረኞች አንዱ ያደረጋቸው የበቀል እሳቤያቸው ለመሆኑ መጠራጠር እንዴት ይቻላል? ቀደም ብዬ እንድገለጽኩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዶ/ር ዮናስ ብሩ ወደ ዓለም ባንክ ተመልሰው እንዲገቡ ባለማገዛቸው ነው ዶ/ር ዮናስ የጭቃ ጅራፋቸውን የሚያነሱትና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ልመበቀል ሃገርን ወደ ማጥፋት ዘመቻ የሄዱት። “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንዲሉ” ዶ/ር ዮናስ እራሳቸውን በጣም አግዘፈው የሚያዩ እቡይ በመሆናቸው፤ ሃገርን ለማጥፋት የጀመሩት ዘመቻ ምን ያክል የወረደና አስቂኝ መሆኑን እንኳን አልተገነዘቡም። በእንደ ዮናስ ዓይነት ሰዎች እሳቤ ሃገር ትፈርሳለች ብሎ ማሰብ “ቁጫጭ ዝሆንን እንድትጥል የመመኘት ያክል ነው።     

2. የኢትዮጵያ አሁናዊ ኢኮኖሚ፡

ኢኮኖሚስቶች የአንድን ሃገር የኢኮኖሚ እድገት የሚለኩት፤ በአገሪቱ በአጠቃላይ ያለውን በቁስና በአገልግሎት የሚመረተውን ምርት ቀመር በመስራት ነው (GDP)፤ የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ አይደለም። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2018 የኢትዮጵያ GDP  $84.27 ቢልዮን ነበረ፤ በ2023 የኢትዮጵያ GDP  $156.8 ቢልዮን እንደሚሆን የአለም ባንክ ግምቱን አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ በ2028 የኢትዮጵያ GDP $280.98 ቢልዮን እንደሚሆን እስታቲስታ የተባለው የዓለም የኢኮኖሚ ጥናት ምርምር ተቋም ገልጽዋል። የኢትዮጵያ የመግዛት አቅምም መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ፤ የኢትዮጵያ የመግዛት አቅም፤ በ2022 $445.82 ቢልዮን ነበር አሁን ደግሞ $473.02 ቢልዮን እንደሆነ የአለም የኢኮኖሚክ ጥናት ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ ያሳያል።  ቢዝነስ ኢንሳይደር የተባለው ድህረ ገጽ በሚያዚያ 14 2023 (እ.አ.አ) የአለም የገንዘብ ድርጅትን (IMF) ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ኢትዮጵያ በእድገት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ በኮረና ችግር፤ በአንበጣ ወረርሽኝ፤ በጦርነት፤ በድርቅ እንዲሁም የራሽያ በዩክሬን ላይ ባደረገችው ወረራ ምክንያት በዓለም ላይ በተፈጠረው ጫና፤ በዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ፤ ከሳሃራ በታች ካሉ አፍሪካ ሃገራት (ከ 46 ሃገራት ውስጥ) በሶስተኛ ደረጃ ትገኛለች፤ ከሳህራ ካሉ ሃገራት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴ የሚበልጧት ናይጄርያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 55 ሃገራትም አምስተኛ ስትሆን፤ የዓለም ባንክ በመጋቢት 2023 ባወጣው መረጃ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 10 ሃብታም ሃገራት 6ተኛ ናት ይላል። ለደቂቃ ቆም እንበልና እስቲ ይህንን እናስብና ወደ አእምሯችን ይዝለቅ። 

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ኩነት የሚለኩት አሃዞች የሚያሳዩን፤ ዮናስ እንደሚሰብኩን፤ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዳለች ሳይሆን፤ በእድገት ግስጋሴ ላይ እንዳለች ነው። ይህ ማለት፤ በሃገራችን ችግር የለም ማለት አይደለም። በግጭትና በጦርነት የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች አሉን፤ ሥር በሰደደ ድህነት ውስጥ እና ከአእምሮ በላይ በሆነ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች አሉን። ይህን ነባር ችግር በአምስት ወይም በአስር ዓመታት በአንዴ እንቀይረዋለን ማለት ከባድ ነው። ችግሮቻችንን ለመፍታት የመንግሥት ጥረት ብቻ አይበቃም። እያንዳንዳችን እንደ ዜጋ የሃገራችንን የኢኮኖም ገጽታ የመቀየር ሃላፊነት አለብን። ለዓመታት የነበሩና አሁንም የተፈጠሩ በርካታ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች በሃገራችን አሉ። እነዚህን ችግሮች ግን በነ ዶ/ር ዮናስና ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የሻገተ የጦርነት እሳቤ ልንፈታቸው አንችልም። 

የኑሮ ግሽበቱ፤ ሕዝብን ያማረረ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፤ የኑሮ ግሽበቱ በዓለም ላይ የመጣ ፈተና እንጂ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተደቀነ ችግር አይደለም። አሜሪካ ለምንኖረው እንኳን የኑሮ ግሽበቱ ፈተና ሆኖብናል። ምናልባት ዶ/ር ዮናስ ወደ ሱቅ ወጣ ብለው ዕቃ ሸምተው አያውቁ ይሆናል። ለሸማቾች ግን፤ የኑሮ ውድነቱ ግልጽ ነው። ብዙዎቻችን የማንገምተው  በበጋ መስኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንዴ ባይመረት ኖሮ የኑሮ ውድነቱ ምን ያክል የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነው። በርካታ አፍሪካ ሃገራት ስንዴ ከውጭ ሲጠብቁ፤ ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ እራሷን ቻለች፤ ይህ ዓለምን ያስደመመ ዜና፤ ለነ ዮናስ ብሩ የጉሮሮ አጥንት ሆነባቸው። ለዚህ እውቅና አለመስጠት ክህደት እንጂ ምንም ሊባል አይችልም። ኢትዮጵያ ዛሬ ስንዴ ከውጭ ወደ ሃገር የማታስገባ ሃገር ሆናለች። ይህ ትልቅ እምርታ ነው። መንግሥት፤ የሃገር ውስጥ ፍጆታን በበቂ ሁኔታ ሳያሟላ፤ ለውጭ ገበያ ማዋሉ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው የፖሊሲ ክርክር ቀና የሆነ እሳቤ ባላቸው ሰዎች ሊሞገት ይችላል። የሃገር ፍጆታ ሳይሞላ ስንዴ ለውጭ ንግድ መቅረብ የለበትም የሚሉት ሰዎች ግን ያላገናዘቡት አንድ ነገር አለ። ለውጭ ሃገራት የተሸጠው ስንዴ፤ ይዞ የሚመጣው ዶላር ነው። ይህ ዶላር ደግሞ ሃገሪቱ ለሚያስፈልጋት ወሳኝ ለሆኑ እንደ ቤንዚን ያሉ ግብአቶች፤ ለኢንዱስትሪ ስራ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችና የመለዋወጫ እቃዎች አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አይከቱም። ስንዴ ለማጉጓዝ፤ ቤንዚን ያስፈልጋል፤ ቤንዚን ለመግዛት ዶላር ያስፈልጋል። ይህንንም በቂ ውይይትና ጥናት አድርጎ ጥቅሙና ጉዳቱን እንደማስላት፤ እነ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ይኮንናሉ። ይህ የስንዴ ምርት ውጤት የመጣው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበጋ መስኖ ምርት ፖሊሲ ለመሆኑ እንኳን እውቅና የማይሰጡ ሰዎች፤ ስንዴ ለምን ለውጭ ገበያ ቀረበ ብለው የሕዝብን ስሜት ለመኮርኮር ሲጋጋጡ ማየት፤ ጥላቻቻው አስተሳሰባቸውን ምን ያክል እንደጋረድው እንረዳለን።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገቱ እንደሚቀጥል፤ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተነበዩ ቢሆንም፤ በውስጥና በውጭ ጠላቶቻችን በተቀነባበረ ሴራ ብዙ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው። ስግብግብ ነጋዴዎች፤ ምርት ይደብቃሉ፤ የሃሰት ብር እየተሰራ በሃገር ውስጥ የሚዘዋወረው ገንዘብ እንዲጨምር ይደረጋል፤ ዶላር በጥቁር ገበያ መመንዘሩ ብቻ ሳይሆን ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዶላር በጥቁር ገበያ እንዲመነዘሩ እንደ ዶ/ር ዮናስ ብሩ ዓይነት ሰዎች ግፊት ያደርጋሉ። ይህም ለኑሮ ግሽበት የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት በጥቁር ገበያ እየተሸጠ ሃገራችን ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ያደርጋሉ፤ በየባንክ ተሰግስጎ ያለ ስግብግብ ቢሮክራት፤ ዶላር ከባንክ አውጥቶ በጥቁር ገበያ ይመነዝራል። በየአካባቢው ያሉ ግጭቶችም ምርት እንደ ልብ እንዳይዘዋወር እንቅፋት በመሆናቸው፤ በምርት አቅርቦት ላይ ችግር በመፍጠር የሕዝብ ፍላጎት እንዳይሟላ ያደርጋሉ። ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ኢኮኖሚስቶች የማይነግሩን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር መጨመርና በሺህ የሚቆጠሩ ከሃገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው መመለስ ለኑሮ ግሽበት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው። አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን ሲወርዱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ወደ 31.4 ሚሊዮን ነበር፤ ዛሬ ሕዝባችን ከ120 ሚሊዮን በላይ ነው። ይህ በአማካይ በዓመት ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሕዝብ የሚጨምር ሃገር በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ተግዳሮትም ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

ዛሬ ችግኝ ለምን ይተከላል፤ ፓርክ ለምን ይሰራል፤ ቤተመንግሥት መሥራት ጊዜው ነው ወይ ወዘተ የሚሉን ሰዎች፤ ያልተረዱት፤ አንዳንዶቹም ተረድተው የሃሰት ትርከታቸውን የሚረጩት፤ በነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በሺህ የሚቆጠር ዜጋ ሥራ ተፈጥሮለት እየሰራ መሆኑን ነው። ዛሬ እነ ዮናስ ብሩ፤ በሃሰት ትርከት የሚያጣጥሉት የስማርት ሲቲ ግንባታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ገንዘብ እያተሙ” የሚገነቡት አይደለም። ይህን እውነታ ዶ/ር ዮናስ በሚገባ ያውቃሉ። ነገር ግን ቦርከና ድኅረ ገጽ ላይ “ኢትዮጽያን ና የአፍሪካን ቀንድ ለማዳን የአለማቀፍ ማህበረሰብ ጫና ወሳኝ ሚና” በሚል ርዕስ በምሁራዊ ሸፍጥ በፃፉት ጽሁፋቸው፤ “[አብይ] ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ከሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት፣ ርሃብና የጅምላ ፍጅት አልቀዋል እንዲሁም ከ 5 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በግድ ተፈናቅለዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ እሱ ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው ለታይታ መናፈሻዎችና ቤተመንግስት ግንባታዎች ነው። የሚገነባው ፈርኦናዊ ቤተ መንግስት ሶስት ሰው ሰራሽ ሃይቆች ፤ የአራዊት ፓርክ፤ ፏፏቴና በዱባይ ደረጃ ያሉ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ጨምሮ ሊሎች ቅንጡ ግንባታዎችን ያካተተ ነው ። ይህ የርሱ ፕሮጀክት በኢትዮጽያ ታሪክ እጅግ ውድ ሲሆን እስከ 15.3 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል” ይሉናል።


ይህን በሁለት ከፍሎ ማየት ይበጃል። ወደ የመፈናቀልና የጦርነት ትርከት ውስጥ ከመሄዴ በፊት፤ በኢኮኖሚው ላይ የተነሳውን ዓይን ያወጣ ሸፍጥ ትንሽ ልበልበት። 15.3 ቢልዮን ዶላር የሚያወጣው ፕሮጀክት፤ ከኢትዮጵያ ባጀት የተወሰደ፤ እንዳልሆነ፤ ዶ/ር ዮናስ በሚገባ ያውቁታል። እነዚህ ፕሮጀክቶች እሳቸው እንደሚሉት “ለታይታ” ሳይሆን የብዙ ድሃን ቤት የደጎመና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያለው ኢንቨስትመንት ነው። ይህን ፕሮጀክት ለመስራት ገንዘብ፤ ከበርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች “ገበታ ለሃገር” በሚል ፕሮጀክት የተሰበሰበና፤ እንደ አረብ ኢምሬት ካሉ ሃገራት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሰጥ ስጦታ እየተሰበሰበ ያለ ገንዘብ ነው። ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዳእባባይ ለሕዝብ ገልፀዋል። ስለዚህ ለዶ/ር ዮናስ አዲስ ነገር አይደለም። እኝህ እድሜ ጠገብ ሰው፤ ሕዝብ በግልጽ የሚያውቀውን ነገር በእንደዚህ ዓይነት ደረጃ ሲዋሹ ማየት፤ በቀላቸው ምን ያክል መርዛማ እንደሆነ እንረዳለን። ይህ ቅጥፈታቸው፤ የጥላቻቻውንና የቂማቸውን ጥግ ያሚያሳይ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች፤ ሼክ መሃመድ አላሙዲ፤ የሚሊንየምን አዳራሽ አሰርተው ለሕዝብ ጥቅም በስጦታ ከመስጠት የተለየ እሳቤ የለውም። እነዚህ ፕሮጀክቶች፤ ዶ/ር ዐብይ፤ ከባለሃብት “ለምነው” ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጡትና የሚያዘጋጁት ስጦታ ነው ማለት ይቻላል። እንኳን እንደ ዶ/ር ዮናስ ያለ ሰው ይቅርና ኢኮኖሚክስ 101 የተማረ ሰው፤ የ15.3 ቢልዮን ዶላር ኢንቨስትመንትና የእነዚህን ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ፋይዳ በሚገባ ይረዳል። ቂመኛ ስትሆን፤ ጥላቻ ሲሸፍንህ ግን እውነትን ትክዳለህ፤ እራስህንም ወደ ውርደት ትወስዳለህ። ይህ ፕሮጀክትና በርካታ “በልመና” የተሰሩትና እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሥራ የፈጠሩ ናቸው፤ ፕሮጀክቶች በሚሰሩበት ቦታ፤ መንገድ፤ ወኃ፤ ኤሌክትሪክና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ይገነባሉ። ለግንባታው የሚሆን ግብአት ይመረታል፤ ይገዛል፤ ግንባታው ባለበት አካባቢ ያሉ ነጋዴዎች ይጠቀማሉ ይህም፣ የሥራ እድል የሚፈጥር ነው። በተለይ ደግሞ የጫካው ቤተ መንግሥት ሲጠናቀቅ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሥራ የሚፈጥር ይሆናል። የአንድነት ፓርክ ሥራ ከጀመረ ከጥቅምት 2011 እስከ ሰኔ 30 2013 ድረስ (ያውም በኮቪድ ወቅት) 66.5 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል። ይህንን ግን እነ ዮናስ አይነግሩንም። እነዚህ ፕሮጀክቶች ለቱሪስት መስህብ የተሰሩ በመሆናቸው፤ ሃገራችን የሚያስፈልጋትን ዶላር የምታገኝበት አንዱ መንገድ ነው። 


በግንባታ የአንድን  አህገር ኢኮኖሚ ለማሻሻል ፖሊሲ ማውጣት አዲስ አይደለም። ብዙ ጊዜ የአሜሪካን ፖሊሲ አውጭዎች፤ ሥራ ለመፍጠር፤ በየአካባቢው አዳዲስ መሰረተ ልማት እንዲስራና ተሰርተው የቆዩ መሰረተ ልማቶች እንዲታደሱ ፖሊሲ ያወጣሉ ገንዘብ ይመድባሉ፤ በዚህም ሥራ ይፈጥራሉ። በርግጥ የዶ/ር ዮናስ እሳቤ ኢትዮጵያውያን ከልመና እንዳንወጣና ተመጽዋች ሆነን እንድንኖር የሚመክር እሳቤ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዱ ሃላፊነታቸው በሚቻለው መንገድ ሁሉ ለዜጎች ሥራ መፍጠር ነው እንጂ የእርዳታ ገንዘብ ማከፋፋልና ሕዝብን ተመጽዋች ማድረግ አይደለም። እነዚህ ፕሮጀክቶች፤ከሰማይ መጥተው የተተከሉ አይደሉም፤ ቤተስብ የሚያስተዳድሩ ሰዎች የገነቧቸውና ኑሯዋቸውን ያሻሻሉብት ሥራዎች ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ብዙዎቹ ፕሮጅርክቶች፤ የቱሪስት መስህብ በመሆን፤ ከተለያዩ ሃገራት ሰዎች፤ ለእረፈት ወደ ሌላ ሃገር ሲወጡ ኢትዮጲያን እረፍታቸውን የሚያሳልፉባት ተመራጭ ሃገር ለማድረግ ነው። ይህም በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለኢኮኖሚው ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው። የብዙ ሃገራት ችግር፤ እንዲህ በቅንነት ለሃገሩ የሚሰራ መሪ ማጣታቸው ነው። የሃገር መሪ ሲስርቅ፤ ጊዜውን ያለአግባብ ሲያሳልፍ ሊወቀስ ይገባዋል፤ የሃገር መሪ ሃገሩ ላይ 15.3 ሚልዮን ዶላር ኢንቨስት አደረገ ብሎ ለመዝለፍና ለማዋረድ መሞከር ከጤነኛ አእምሮ የሚወጣ ሃሳብ ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል። 


እነዚህ ፕሮጀክቶች በመሰራታቸው ብዙ እናቶች፤ በማህበር ተደራጅተው በሚሰሩት ሥራና በነዚህ ፕሮጀክቶች በተፈጠረላቸው የሥራ እድል፤ ወገባቸውን ከሚሰብር የእንጨት ሸክም ወጥተዋል። ይህንን በዓይኔ በማየቴ፤ ቋሚ ምስክር ነኝ። እነዚህ ፕሮጀክቶች ባይሰሩስ? ተጠቃሚው ማን ነው። ገበታ ለሃገር በሚል የተሰሩት ፕሮጀክቶች ባለሃብቶች ፈልገውና ወደው በሰጡት ገንዘብ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከከፈለው ታክስ የወጣ አንድ ሳንቲም የለም። ዛሬ የኢትዮጵያን ውብ የተፈጥሮ ገፅታ የሚያሳዩን እነ ጎርጎራና ኮይሻ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምሩ፤ ለኢትዮጵያ ያለው የኢኮኖሚ ፋይዳ ለዶ/ር ዮናስ ጠፍቷቸው ይሆን? ቸር ይግጠመን፤ (ይቀጥላል)።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here